አሜሪካ ከመስከረም አስራ አንዱ የአልቃኢዳ የሽብር ጥቃት በኋላ ወደ አፍጋኒስታን የገባችው “የዜጎቸን ጠላት ለመበቀልና በዚያ ያለውን የአልቃኢዳ ክንፍ ታሊባንን ከስልጣን ለማንሳትና ከምድረ ገጽ ለማጥፋት” ነበር። እናም ከመስከረም 2001 ጀምሮ አሜሪካ ከትንሿ ሊትዊኒያ እስከ ታላቋ ብሪታንያ፣ ከምስራቅ አውሮፓዋ አልባኒያ እስከ ምዕራብ አውሮፓ ኃያላኑ ጀርመንና ፈረንሳይ ከሰላሳ በላይ ሃገራትን የያዘውን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) አባል አገራትን በማስተባበር በአፍጋኒስታን ላይ ዘመተ። በዚህም ከኔቶ በተጨማሪ ከአፍጋኒስታን መንግስትም ወታደሮችንና ሚሊሻወችን በመመልመልና በማሰልጠን በጥቅሉ ከሁለት መቶ እስከ 6 መቶ ሺሕ የሚገመት ጦር በማሳለፍ በታሊባንና ተባባሪዎቹ በሚላቸው ኃይሎች ላይ ዘመተ። ሚያዚያ 2002 ላይም እንዳቀዱት የአሜሪካና የተባባሪዎቿ ጦር ታሊባንን ለመደምሰስ መቃረቡን የወቅቱ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ አበሰሩ። ቀሪ የአልቃኢዳና የታሊባንን አባላት እስከመጨረሻው እያደኑ ለመደምሰስ ወሳኝ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑንም አሳወቁ።
በዚህ መካከልም አሜሪካ የቀድሞ ገዥዋና ቁጥር አንድ ወዳጅዋ ከሆነችው ብሪታኒያ ጋር በመተባበር በ2003 ኢራቅ ላይ ሌላ ጦርነት ከፈተች። ፕሬዚዳንት ቡሽና አጋሮቻቸው ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ “ታሊባንን ደምስሰን አፍጋኒስታንን ነጻ አውጥተናል” በማለት በእብሪት የደነፉበት የአሜሪካና የምዕራባውያን አጋሮቿ የአፍጋኒስታን ዘመቻም ከጉራቸው በተቃራኒ ሃያ ዓመታትን ቀጥሎ በአሳፋሪ ሽንፈት ተጠናቋል።
በውጤቱም አሜሪካ ከሦስት ሺሕ በላይ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ዳን ድርጅት አባል ሐገራት ወታደሮች፣ ከአራት ሺሕ በላይ የኮንትራት ሠራተኞች፣ ከ66 ሺሕ የሚበልጡ የአፍጋኒስታን መንግስት ወታደሮች ተገድሎዋል። በተጨማሪም አሜሪካ ሁለት ቢሊዮን ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብም በታሪኳ አሳፋሪ የሆነውን መራር የሽንፈት ጽዋ ለተጎነጨችበትና በዓለም መድረክ ላይ ክፉኛ ተዋርዳ አንገቷን ደፍታ ለወጣችበት ለዚሁ ጦርነት ገብራለች።
በታሊባን በኩልም 50 ሺሕ የታሊባን፣ ሁለት ሺሕ የአልቃኢዳ፣ ሦስት ሺሕ የእስላማዊ መንግስት ተዋጊዎች ተገድለዋል። 60 ሺሕ የሚሆኑ፣ አብዛኞቹ ሮጠው ማምለጥ የማይችሉ ህጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና አቅመ ደካማ ንጹሐን አፍጋናውያን የአሜሪካና የተባባሪወቿ ሚሳኤሎች በአፍጋኒስታን ምድር ላይ ባዘነቡት ጥይት አረር በግፍ አልቀዋል። እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚገመት ሠላማዊ ሕዝብ ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት ከገዛ አገሩ ቀየ፣ ከሞቀ ጎጆው ተፈናቅሏል፤ ለአስከፊ ስደት ተዳርጓል።
በመጨረሻ ግን ጠላቶቸ ናቸው ያለቻቸው የታሊባን መሪዎች ጦርነቱን ስትጀምር እንደዛተችው “አንገታቸውን ታንቀው” ለህግ ሳይቀርቡ፣ ገና በመጀመሪያው ዓመት “ደምስሰነዋል” የተባለው ታሊባንም ሳይደመሰስ፣ ባለፉት ሃያ ዓመታት በቁጥጥራቸው ሥር የቆየው የአፍጋኒስታን ምድርም “ሰላምና ዲሞክራሲ” ሳይሆን ሞት፣ ስደትና ስቃይ አስፍነውበት ከአፍጋኒስታን ወጡ። በመስከረም 11ዱ ጥቃት በሽብር ጥቃት የተገደሉ ሦስት ሽሕ ዜጎቻቸውን ደም ለመመለስ በከፈቱት ጦርነት ከሦስት ሺሕ በላይ አሜሪውያንን አስገድለው፣ የዜጎቻችን ገዳዮች ናቸው ያሏቸውን ጠላቶቻቸውን ሳይሆን ስድሳ ሺሕ ንጹሐን አፍጋናውያንን ተበቅለው፣ ሚሊዮኖችን ከሃገራቸው ነቅለው፣ አፍጋኒስታንን አፍርሰው፣ እናፈርሰዋለን ያሉትን ታሊባንን ደግሞ አንግሰው በእብሪት የያዙትን ምድር በውርደት ለቀቁ። ፎክረው ገብተው ኮስሰው ወጡ፣ እጅጉን ታላቅ ነን ሲሉ እጅጉን አንሰው፣ አሳፋሪ ሽንፈትን ቀምሰው ጦርነቱን አጠናቀቁ።
ከሽንፈቷም በላይ ያለምንም ዓላማ ሃያ ዓመታት ሙሉ በአፍጋኒስታን ላይ ላካሄደችው ግብ አልባ ጦርነትና ላስከተለችው ውድመት ዓለም በተጠያቂነት በትችትና በወቀሳ እያብጠለጠላት ይገኛል። የአሁኑ የአሜሪካ የአፍጋኒስታን ሽንፈት ከአሜሪካ አልፎ ለመላው ምዕራባውያንም የሚተርፍ እጅግ አሳፋሪና ከእንግዲህ ወዲህ የአሜሪካ የታላቅነት ጀንበር እያዘቀዘቀች እንደሆነ ማሳያ መሆኑንም ሁሉም በአንድ ድምጽ ምስክርነቱን እየሰጠ ይገኛል።
ለመሆኑ ግን ታላቋ አሜሪካን ለዚህ አሳፋሪ ሽንፈት የዳረጋት ምንድነው? ለዚህ ጥያቄ መልሱ በአጭሩ፤ “ጣልቃ ገብታ ጦርነት የምትገጥመውን ሃገርና ሕዝብ ማንነትና ታሪክ አለማወቅ” የሚል ነው። ዓለም ላይ አሉ የተባሉ አሜሪካንን ያጠኑ ምሁራንም የሚያስረግጡት ይህንኑ ነው። የአሜሪካንን የውጭ ግንኙነትና የጦርነት ታሪክ በጥልቀት ያጠኑት ታዋቂው የፖለቲካል ሳይንቲስት ዶሚኒክ ትሪየኒ፤ የአፍጋኒስታኑ ሽንፈት በአሜሪካ የጦርነት ታሪክ ውስጥ ትልቁ እንጅ ብቸኛው አለመሆኑን ይገልጻሉ። በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ሃያ ዓመታትን የፈጀው ረጅሙ የአፍጋኒስታን ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሚጀምረው የአሜሪካ የጦር ታሪክ አንድ አካል ነው መሆኑንም በማሳያ ያነሳሉ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካ ባካሄደቻቸው ጦርነቶች አንዱንም በአሳማኝ ሁኔታ አላሸነፈችም፣ ሁሉንም ተሸንፋለች ማለት ይቻላል። በ1991 ያካሄደችው የባህረ ሰላጤው ጦርነት በጥቂቱም ቢሆን በአሸናፊነት የወጣችበት ቢሆንም ድሉ ግን በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት የለውም፣ የኮሪያውም እንደዚሁ ነው። ይባስ ብሎ ቬትናም ላይ በይፋ ከባድ ሽንፈትን አስተናገደች። ኢራቅ ላይም አልተሳካም፣ እዚያም የአሜሪካ ሽንፈት ነው አመዝኖ የተስተዋለው። በሊቢያ፣ በሶማሊያ በአጠቃላይ ጣልቃ ገብታ ጦርነት ባካሄደችባቸው ሃገራት በሁሉም ተሸንፋለች። “ምክንያቱ ምንድነው? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄም፤ “አለማወቅ፤ አሜሪካ ጣልቃ ገብታ ጦርነት የምትገጥማቸውን አገሮች ማንነት አለማወቋ ነው የሽንፈቷና የውርደቷ ዋነኛ መንስኤው። የአሁኑን ጦርነት ብንወስድ እንኳን አሜሪካ ስለ አፍጋኒስታን ታሪክ፣ ሕዝብ፣ ማንነት ምንም የምታውቀው ነገር አልነበረም”። “ፕሬዚዳንት ቡሽና ጦር አዛዣቸው ዶናልድ ራምስፊልድ በ2001 አፍጋኒስታን ሲገቡ ትክክለኛው የአገሪቱ ካርታ እንኳን አልነበራቸውም፣ በብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ዘመን የነበረውንና ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የተለወጠውን የድሮውን የአፍጋኒስታን ካርታ ይዘው ነበር እርግጠኛ ሆነው በዚያ እየተመሩ ወደ አፍጋኒስታን የገቡት” በማለት መልሰዋል።
እኛም እንላችኋለን፤ አፍጋኒስታንን አለማወቃችሁ አሁን ሽንፈትና ውርደትን አምጥቶባችኋል ኢትዮጵያን አለማወቅ ደግሞ ከሽንፈትም በላይ የመጨረሻ ውድቀትን ያመጣልና እባካችሁ ቢያንስ አሁን እንኳን እወቁ። በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እየገባችሁ የማይመለከታችሁን እየፈተፈታችሁ ባለማወቅ ውድቀታችሁን ከምትጠሩ፣ ቆም ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ዕወቁ። የምታደርጉትን እያደረጋችሁት ያላችሁት እኛ መሳሪያ አለን፣ እኛ ቴክኖሎጅ አለን፣ እኛ የበላይ ነን በሚል ከሆነም ያኔ ከመቶ ሃያ አምስት ዓመት በፊት ልክ አሁን እናንተን እንደሚያደርጋችሁ ሲያደርገው የነበረው እብሪት መጨረሻውን ያገኘው በማን እንደሆነና ውድቀቱም የት እንደነበረ አያቶቻችሁን ጠይቁ!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2013