እንበልና እርስዎ በአውሮፓ አሊያም በአሜሪካ ነዋሪ ነዎት። ወቅቱ ዝናባማ እንደመሆኑ የቀን ውሎዎን አጠናቀው ምሽት ወደ አልጋዎ ሲያቀኑ ዝናብ መጣል ጀምሮ ነበር። በመስኮት በኩልም አካባቢው በነጭ በረዶ መሸፈኑን ተመልክተው ይተኛሉ።
ሲነጋም ወደ መዋያዎ ሊሄዱ በር ሲከፍቱ ግን መንቃት አለመንቃትዎን የሚያጠራጥር ነገር ይመለከታሉ። በድንጋይ ከሰል ማውጫ አካባቢ ያሉ ይመስል አካባቢው በሙሉ ጥቁር ሆኗል። እርስዎ የሚያውቁት ነጩን በረዶ፤ የሚያዩት ግን ጥቁር በረዶ። ምን ይሉ ይሆን?
በሩሲያ የሁለት ከተሞች ነዋሪዎች ግን ተኝተው ሲነሱ ያጋጠማቸው ይህ ነው (ይህስ ለምድሪቷም አዲስ ሳይሆን አይቀርም)። እንደ ኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ከሆነ ኪስሌቪስክ እና ፕሮኮፒቪስክ በተባሉት ሁለት ከተሞች ነገሩ የተከሰተ ሲሆን፤ በወቅቱ ነዋሪዎች ተደናግጠው እንደነበረም ተመልክቷል።
በፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማህበራዊ ሚዲያው ተሰራጭቶ ሲያነጋግር የነበረው ጥቁሩ በረዶ በአብዛኛው ከሰል በመሰለ ብናኝ የተሸፈነም ነበር። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ከከተማ ወጣ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች የቆሸሸ የሚመስል በረዶ የታየ ሲሆን፤ ከቆይታ በኋላ በከተማ የታየው ግን በፍርሃት የሚያርድ ጥቁር ሽፋን ነበር።
ይህንን ተከትሎም ነዋሪዎች ፎቶውን በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ በመለጠፍ የአየር ብክለት የት እንደደረሰ ሲያመላክቱ ነበር። ነገሩ አሳሳቢ እንደመሆኑ ባለስልጣናት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ለማመላከትም ሞክረዋል። ይህንን ተከትሎም አንድሬ ፓኖቭ የተሰኙ በአካባቢው በትራንስፖርት፣ ኢንዱስትሪ እና በስነምህዳር ላይ የሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣን፤ በአካባቢው ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል ፍጆታ መኖሩን ጠቅሰዋል። ትልልቅ ህንጻዎች ሳይቀሩ ለሙቀት የድንጋይ ከሰል የሚጠቀሙ ሲሆን፤ የንግድ ማዕከላትና ግለሰቦችም የተሽከርካሪዎቻቸውን ጭስ ጨምሮ ለአየር ብክለት የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኙ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
አናቶሊ ቮልኮቭ ከከተሞቹ አቅራቢያ የሚገኝ የድንጋይ ከሰል ማውጫ ኃላፊ ሲሆኑ፤ ድርጅታቸው የትኛውንም ዓይነት ብናኝ ወደ ውጪ እንዳይወጣ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም መሆኑን ለሃገሪቷ ቴሌቪዥን ጣቢያ ገልጸዋል። ሆኖም ድርጅታቸው እጁ የለበትም ለማለት አዳጋች መሆኑን በመጠቆም ጥፋታቸውን ያመኑ የሚያስመስል አስተያየት ሰጥተዋል።
የሃገሪቷን የአካባቢ ጉዳይ በበላይነት የሚቆጣጠረው ኤጀንሲ አጣሪ ቡድኖችን ወደ ቦታው የላከ ሲሆን፤ በጉዳዩ ላይ እንዲነጋገሩበትም በአካባቢው የሚገኙትን ሁለት የድንጋይ ከሰል ማውጫ ኃላፊዎችን ጠርተዋልም ተብሏል። ፎቶው በማህበራዊ ድረ ገጾች ከተሰራጨ በኋላ በተሰጡት አስተያየቶች ላይ በርካቶች መንግስትን የወቀሱ ሲሆን፤ ሌሎች በበኩላቸው ክስተቱን «ውብ» በማለት እያሞካሹት ይገኛል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
ብርሃን ፈይሳ