የትኛውም ነገር የሚለካበት የራሱ ሚዛን አለው። ዘመናችን መሬት ላይ ተገጥመው ግዙፍ ነገሮችን ከሚመዝኑት አንስቶ ጥቃቅን ነገሮችን እስከሚለኩት ሚዛኖች አሳይቶናል (ያውም ከጣሳና ቁና እስከ ዲጅታል)። ቢሆንም ግን የተፈጥሮን ያህል ሚዛን ማግኘት የማይታሰብ ነው፤ ምክንያቱም የተፈጥሮ ስራ ሁሉን ያመጣጠነ ነዋ።
ይህ ያልገባው አንድ ተላላ ሰው ታዲያ፤ ከጠዋት እስከ ማታ ካልተኛ በቀር ያለ እረፍት ወዲህ ወዲያ እያለ የሚቦርቅን ህጻን «እስተካከላለሁ» ብሎ ከባልንጀሮቹ ጋር ይወራረዳል። በውርርዱ መሰረትም ህጻኑ ጠዋት ሲነሳ ተከትሎት፤ የሚያደርገውን፣ የሚሰራውን፣ የሚሄድበትን፣ … ሁሉ እንደ እርሱ ሲከውን ዋለ። የማታ ማታ ግን መቋቋም ተስኖት እጅ ሰጠ።
እህሳ፤ ተፈጥሮ የራሷ ሚዛን አላት ብያችሁ አልነበር? ህጻኑ ለትንሿ አካሉ ፍጥነት ሲሰጠው ለትልቁ ሰው ደግሞ ትልቅ አካል ከኃይል ጋር እንጂ ከዚያን ያህል ፍጥነት ጋር አልነበረም። የተሰመረልንን ምህዋር የመከተል ያህል ትክክለኝነት ላይኖር አጉል መንፈራገጥ ዋጋ ቢስ መሆኑንም ያሳያል ገጠመኙ።
አበው ሲተርቱ «…ነገርን በምሳሌ» ስለሚሉ ነው ምሳሌውን አስቀድሜ ነገሬን ማስከተሌ። ጉዳዬ ግን ከመታዘብ ነው፤ እኛኑ ከመታዘብ። አስተውላችሁ ከሆነ እኛ የአሁኖቹ፤ የምንነጋገርበትና የምንግባበት አጀንዳ ጠፍቶብናል። ውሏችን ከማህበራዊ ድረገጾች ጋር ነውና አንዱ «….» ብሎ ከመለጠፉ፤ ሌላው ተከትሎት«.. .. ..» በሚል ይለጥፋል (ያው መልስ መሆኑ ነው)።
ከዚያማ እኔ፣ አንተ፣ አንቺ፣ ሁላችን፤ ነገሩን ነገራችን አድርገነው ቁጭ ነው። አንድና ሁለት ሳምንት ሙሉ አንዲቷን ጉዳይ ላይ ሰፍረን፤ ስንተማማ፣ ስንካሰስ፣ ስንሰዳደብና ስንጣላ እንቆያለን። በዚያኛው ሳምንት ደግሞ አንዲት ነገር ኮሽ ትልልናለች፤ እርሷንም ጉዳያችን አድርገን ወደ ጭቅጭቃችን እንገባለን።
ማሳያ አንሺ የሚለኝ ካለ ልቀጥል። አቶ እከሌ የተባሉ ባለስልጣን፣ ምሁር፣ ከበርቴ፣ የጥበብ ሰው፣… (ያሻችሁን በሉት) የሸሚዛቸውን ቁልፍ አዛንፈው በመገናኛ ብዙሃን ቀረቡ እንበል። የእኛ ምላሽ ታዲያ የሸሚዝ ቁልፍን ከማዛነፍ ታሪካዊ አመጣጥ አቶ እከሌ ሊያዛነፉ እስከ ቻሉበት ሁኔታ መዘርዘርን ያካትታል (አሁን ይሄን ምን ይሉታል?)።
ብዙ ተከታዮች ያሉት ሌላ ሰው ደግሞ «እከሌ የተባሉት የ… ባለስልጣን መንገድ ሲሄዱ ተደናቅፈው ወደቁ» ብሎ የጭቅጭቅ መነሻ ይጠናል። እኛም የጫማውን ዓይነት፣ የመንገዱ ምቾት፣ የጫማቸው መስፋት፣ የጫማ ክራቸው መፈታት፣ የአካሄዳቸው መንሻፈፍ፣ … የማያልቅ ትንታኔያችንን ስላላየነው ጉዳይ እንሰጣለን።
አሁን አሁንማ የ«እንሞካከር» የትግል አውድማችን ፌስ ቡክ ሆኗል። ያም የመሰለውን ያነሳል ሌላውም የጣመውን ያንጸባርቃል (ለሚቃረኑትም ስድብ ይደርሰዋል)። ሃሳብን በግልጽ ማንጸባረቅ ስህተት ባይሆንም ቅሉ ስራ ፈትቶ በተራ ሃሳብና ንፋስ አመጣሽ ወሬ ላይ መራኮት ግን ከእኛ አይጠበቅም።
የሚገርመው ደግሞ እኛ በምንራኮትበት ሃሳብ ላይ፤ ባለስልጣናቱ፣ ምሁራኑ፣ የምናከብራቸው ታላላቅ ሰዎችም ምላሽ መስጠታቸው ነው (አሁንማ ተቋማቱም ለግለሰቦች ምላሽ መስጠት ጀምረዋል)። እነርሱን ተከትለን ደግሞ እኛ ሌሎች ገባሮቻችንን ፈጥረን ለሁለት ሳምንት እንከራከርበታለን።
ሃቀኛ ስራ የሚሰራ ሰው «ሌሎች እንዲህ አሉኝ» ብሎ ለምን መልስ ሊሰጥ ይፈጥናል? አንዳንዶች ይህንን ዓይነት አጀንዳ የሚፈጥሩት አንድም ከሩጫ ገታ ሊያደርጓቸው አንድም የመተቸት አባዜ ተጠናውቷቸው ነው። የተለመደም ቢሆን አንድ አባባል አለ፤ «ውሾቹ ይጮሃሉ፤ ግመሎቹም ይጓዛሉ» የሚለውን መከተል ተገቢ ይመስለኛል።
ከላይ እንዳነሳሁት ታሪክ ከዚህ ጋር ይሄዳል፤ በደረጃችንና መሆን ባለብን ልክ መሆን ሳንችል መልሶ ራሳችንን መጉዳቱ አይቀሬ ነው (ትልቅ ሰው እንዴት ከህጻን ጋር ይፎካከራል?)። ሁሉም የሚለካበት የራሱ ሚዛን አለው ብለንም አልነበር?
ሆኖልን ስለ ሚጠቅመን ነገር ብናወራ እሰየው፤ አብዛኛው ግን ጉንጭ አልፊና መቋጫ የሌላቸው አሉባልታዎች ናቸው። ሚዛን የማይደፋ አንድ ጉዳይ ላይ ጊዜያችንን መግደላችንም ዘመናችንን አይመጥንም።
ምክንያቱም ህይወቱን ከድህነት ያላላቀቀ ህዝብ አጀንዳ አጥቶ በትርፍ ጉዳዮች መራኮቱ ግራ አጋቢ ነዋ። ኑሯችንና ኢኮኖሚው፣ የጤና እና የትምህርት ጉዳይ፣ የወጣቱና ታዳጊዎች ስነ-ምግባር፣ በእጅጉ እየተስፋፋ የሚገኘው የመጤ ባህል፣ … ማለቂያ የሌላቸው በርካታ ጉዳዮች አጀንዳችን ሊሆኑ አይችሉም ነበር?
«ስራ ከምፈታ ልጄን ላፋታ» እንደሚለው ተረቱ ስራ ሲፈቱ «ምን ብለን ህዝቡን እናወዛግብ?» በሚል የቤት ስራ የሚሰጡን እኮ በርካቶች ናቸው። በዚሁ ከቀጠልን እነሱ ሲነዱን እኛ ስንነዳ ተያይዘን ገደል መግባታችን ነው።
ከሁሉ ይልቅ እኔን የሚገርመኝ ግን፤ መቼ እንዲህ እንደሆንን ነው። ከማህበራዊ ገጾች ጋርስ ውል ያሰርነው መቼ ነው? የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን ቢያዘጋጁ በፌስቡክ የሚሰራጩትን የወሬ ጫፎች ይዘው፣ ባለስልጣናቱ መግለጫ ቢያዘጋጁ «በፌስቡክ ምን ተባልኩ?» ብለው፣ እኛ ብንወያይ አሊያም ብንከራከር ፌስ ቡክ ላይ ከተባለው ተነስተን፣…። መነሻና መድረሻችን ከዚህ አቅጣጫ መሆን ከጀመርን ስንት ጊዜ ሆነን?
አልታወቀንም እንጂ የአጀንዳ ያለህ እያልን እኮ ነው። ወገን ጉዳያችን በምን ሚዛን ይለካል፤ ተግባራችንስ? አድራጎታችን ከሚዛን ሲቀመጥ ከሁሉ የቀለለ እንዳይሆን ማሰብና መጠንቀቅ እኮ አለብን። አጀንዳችንን በእጃችን ከምናሽከረክራት ትንሿ ስልካችን ላይ ከማድረግ ወደ ሚጠቅመን ነገር ብናዞረው አይሻልም?
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
ብርሃን ፈይሳ