የጸረ ሽብር ትግል በአውደ ወጊያ በሚቀዳጁት ድል ብቻ አይረጋገጥም ። የአሸባሪው ፓለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት የሆነውን ሕዝብ ልቦና እና አመለካከት ከወዲሁ መማረክ ግድ ይላል ። አሸባሪውን ከሕዝብ የመነጠል የተቀናጀ ርብርብ ይጠይቃል ። አሜሪካ ለ20 አመታት ከ2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገፍግፋ በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ሰውታና አካል ጉዳተኛ አድርጋ በባዶ እጇ አጨብጭባ ተሸንፋና ተዋርዳ የወጣችው የአፍጋኒስታውያንን ልቦና ማሸነፍ ባለመቻሏ ነው ። የግንባሩን አውደ ውጊያማ ከ20 አመት በፊት ታሊባንን አይቀጡ ቅጣት ቀጥታ አሸንፋ ነበር ። በኢራቅ በሶሪያ በሶማሊያ በየመን በሊቢያ በናይጀሪያ በማሊ በሞዛምቢክ ወዘተረፈ….. አሸባሪዎችን በቀላሉ ማሸነፍ ያልተቻለው ለዚህ ነው። አሸባሪዎችን በጦርነት ለማንበርከክ ከሚደረገው ፍልሚያ ባልተናነሰ ርዕዮተ አለማቸውን እንደ ሰብዓዊ ጋሻ ከሚጠቀሙበትና በአካልም በስነ ልቦናም ካገቱት ሕዝብ ማውጣትና ማጽዳት ይጠይቃል ። በአሸባሪው ህወሓት ላይ ከሶስት ሳምንታት ባነሰ ጊዜ የተቀዳጀነውን አንጸባራቂና በጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የተዋጀውን ድል ማጽናት ያልቻልነው የትግራዋይን ልቦና በቅጡ ባለመማረካችን ነው። አሁንም የማይቀረውን ወታደራዊ ድል ለማጽናትና ለማዝለቅ ከወዲሁ የትግራዋይን ልብ በማሸነፍ ልናጅበው ይገባል ። ይበል የሚያሰኙ ሕዝባዊ ውይይቶችና ሌሎች ጅምሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ። ከሸኔ ከጉምዝና ከሌሎች አሸባሪዎችና ሽፍቶች ጋር የምናደርገውን ትግልም እንደዚሁ ። በይፋ ባንገነዘበውም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ሰዓት አንስቶ የኢትዮጵያውያንን በተለይ ደግሞ የትግራዋይን ልብና አመለካከት ለማሸነፍ ብዙ ጥረዋል ። ዋጋም ከፍለዋል ።
ለሰላም ካላቸው ቁርጠኝነትና ጦርነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በውትድርና ህይወታቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁት፤ ጓደኞቻቸውንና ወንድማቸውን ስለ ነጠቃቸው ፤ ጦርነት የሀገርን ኢኮኖሚ ምን ያህል እምሽክ ድቅቅ እንደሚያደርግና እንደሚያወድም አበክረው ስለተገነዘቡና ፤ የትግራይ ሕዝብም ጦርነት ይበቃዋል በሚል ጽኑ እምነትና የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ ኃይሎች የድሀን ልጅ የእሳት ራት ያደርጋሉ እንጂ እነሱ አይዋጉም በማለት ለትግራይም ሆነ ለሌሎች ሕዝቦች ደህንነት ሲሉ እስከ መጨረሻው ሰዓት ሆደ ሰፊነትንና ትዕግስትን መርጠዋል ። አበው ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች እንዲሉ በከሀዲውና የእናት ጡት ነካሹ በሆነው ትህነግ መከላከያችን፣ ሉዓላዊነታችን ፣ ሀገራችንና ሕዝባችን ለሰላም በታመኑ ከጀርባ ተወጉ ። ባጎረሱ ጣታቸውን ተነከሱ ። አሸባሪው ህወሓት በእብሪት በጫረው እሳት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት ጠፋ ፤ አካል ጎደለ ፤ የሀገር ኢኮኖሚ ክፉኛ ደማ ፤ የሽብር ኃይሉ ያወደማቸውን የመሠረተ ልማቶች መልሶ ለመጠገን ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ሆነ ። ልብ አርጉ ይህ ወታደራዊውን ወጭ አይጨምርም ። ጥገና ሲያካሒዱ የነበሩ የኢትዮ ቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎች በግፍ ተገደሉ ። ይህ የትግራዋይን ልብ የማሸነፍ ጥረት አካል ነበር ። መንግስት ከስምንት ወር ቆይታ በኋላ ለሰብዓዊነት ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም ያወጀውም ለዚሁ ሰናይ አላማ ነበር ። አሸባሪው ህወሓት ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአማራና የትግራይ ክልሎችን በመውረር በአፋር ፈንቲ ረሱ ዞን በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ ፤ በራያ ቆቦ አጋምሳና በሌሎች አካባቢዎች ንጹሐን በመግደል አስገድዶ በመድፈር በመዝረፍ ግፍ መፈጸሙ ሳያንስ የቤት እንስሳትን በጥይት በመደብደብ ጥረቱን ዋጋ አሳጥቶታል ።
ጠቅላይ ሚንስትር ሀገሪቱን ከጠብ መንጃ አዙሪት ለማውጣትና ከዚህ ቀደም የነበሩ ገዥዎች ያልሄዱበትን የሆደ ሰፊነትና ቁጭ ብሎ የመነጋገር አዲስ መንገድ በመምረጣቸው በልኩ እውቅና ሊሰጣቸውና አብዛኛው ዜጋ ከጎናቸው ሊቆም ሲገባ መንግስታቸው በልፍስፍስነት ከመወቀሱ ባሻገር ፓርቲያቸውም ሆነ እሳቸው ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ደጋፊያቸውና ተከታያቸው ብዥታና ድንጋሬ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል ። እነዚህ ሁሉ ጥረቶች የትግራዋይን ልብ ለመማረክ የተደረጉ ዕንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ግንዛቤ አልተያዘም። ይሁንና የእፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24ቱን ታላቅ ክህደት ተከትሎ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና የሀገር ህልውናን ለማስቀጠል ያሳዩት ቁርጠኝነት እና ሰራዊቱ ከተፈጸመበት ታሪክና ትውልድ ይቅር ከማይለው ክህደት በኋላ ሞራሉና ወኔው አንሰራርቶ በእልህና በቁጭት ተነሳስቶ እጅን በአፍ የሚያስጭን አንጸባራቂ ድል በማስመዝገቡ ሀገራዊ ሞራሉ እንዲያንሰራራ አድርጓል ። እፉኝቱ ትህነግ ይታበይበትና ይመካበት የነበረውን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ በሶስት ሳምንታት ውስጥ ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓም መቐለ ሊገባ ችሏል ። ለዛውም እጅ የመስጫ የመጨረሻ ቀነ ገደቡን ጨምሮ ስድስቱ ቀናት ሳይታከሉ ።
በነገራችን ላይ ይህ ሕግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ሶስት ግንባሮች አሉት ። የመጀመሪያው ከእፉኝቱና ከሀዲው የአሸባሪው ህወሓት ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ ሀሰተኛ ፣ የተዛባና በሴራ ኀልዮት የተለወሰና የተበረዘ መረጃ ከሚነዛው የትህነግ መደበኛና ማህበራዊ ( ዲጂታል ወያኔ ) ሚዲያ ጋር ነው ። ስለ ሁለት ግንባሮች በቀጣይ መጣጥፎች በዚሁ ጋዜጣ በቅርቡ እመለሳለሁ ። ሶስተኛው ግንባር ደግሞ ትህነግ ላለፉት 50 አመታት በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ጠርንፎ በስሙ ሲነግድበት ፣ ሲምል ሲገዘትበትና በፈጠራ ትርክት ፣ በአስገድዶ ማጥመቅ (ኢንዶክትሬሽን) እና በፕሮፓጋንዳ ያለ ፈቃዱ ሲወቀር የኖረውን የትግራዋይ ልብ የመመለስና የመማረክ ግንባር ነው ። ይህ ከሁለቱ ግንባሮች ባልተናነሰ ጽናትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን ማጤን ያሻል።
ከአሁኑ ትግራዋይን ከአሸባሪው ህወሀት የመነጠል፤ አመለካከቱንና ልቡን የማሸነፍ ስራዎች ጎን ለጎን መሠራት አለባቸው ። አሁንም ጦርነቱን ብቻ ማሸነፍ ድሉን ሙሉ ስለማያደርገው የትግራዋይን ልብ ማሸነፍና ማሳመን የጦርነቱ ስትራቴጂ አካል መሆን አለበት ። ፈጣሪ ከብልቶቻችን ሁሉ ያስቀደመው ልባችንን ነው ። እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሁሉ አንድ የሕግ አዋቂ ፈጣሪን ሊፈትነው ፤ ” መምህር ሆይ ፥ ከሕግ ማንኛይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ” ፈጣሪም በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ማቴዎስ 22 ÷ 37 _ 38 ላይ እንዲህ ሲል ይመልስለታል ፤ ” ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት ። ” በዚህ ታላቅና ቀዳሚ ትዕዛዝ እየሱስ ክርስቶስ ከነፍስም ሆነ ከአሳብ በፊት ልብን እንዳስቀደመ እንረዳለን። የ32ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የፍራንክሊን ዴሎን ሮዝቬልት ባለቤትና ቀዳማይ እመቤት ኤሌንኖር ሮዝቬልት ፤ ሮዝቬልትን ጨምሮ የበርካታ ፕሬዝዳንቶች አማካሪና ሊቅ የነበረውን በርናንድ በሩክ፤
“አእምሮየና ልቤ በሀሳብ ቢለያዩ ማንኛውን ልከተል!? ” ስትል ትጠይቀዋለች ፣ እሱም ያለምንም ማወላወል ፣” ልብሽን ተከተይ ” ሲል ይመልስላታል ። እነዚህ መንፈሳዊና አለማዊ ዋቢዎች ልብ በሰው ልጅ ዘንድ ያለውን ከፍ ያለ ስፍራ ያሳያል።
በዲፕሎማሲው መልክዓ ከ30 አመታት ወዲህ ብቅ እንዳለ የሚነገርለት የመማረክ ወይም የማግባባት ጥረት ( የሶፍት ፓወር ) መንግስታት እንዴት በሌሎች ሀገራት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ ለመረዳት የማይተካ ሚና እንዳለው ” ፎሪን ፓሊሲ ” መጽሔት ያትታል ። አሜሪካዊው የፓለቲካ ሳይንቲስት ጆሴፍ ኔይ ፤ ሶፍት ፓወር አንድ ሀገር በምትከተለው የፓለቲካ ስርዓት ፤ ፓሊሲ ፣ እሴቶች እንዲሁም በሲቪል ማህበረሰቧና በባህሏ አማካኝነት ሀገራትን የመማረክና የመሳብ ዲፕሎማሲያዊ ሀተታ ነው ። የሕዝቦችን አእምሮና ልብ በመማረክ ( አትራክሽን) ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ አይነት ነው ። ሀርድ ዲፕሎማሲ ከዚህ በተቃራኒው ወታደራዊ ኃይልንና ጉልበትን የሚጠቀም ነው ። አሜሪካ የሳዳምን በማስከተል የታሊባንን አገዛዞች በጦር ሜዳ ማንበርከክ ብትችልም ፤ የኢራቃውያንንና የአፍጋኒስታውያንን ልብና አእምሮ መማረክ ላይ ባለመስራቱ ተልኮውን ሙሉ በሙሉ ሊያሳካና ግቡን ሊመታ አልቻለም ። በአፍጋኒስታን ሰሞኑን ያስተዋልነው ወታደራዊ ድል ለብቻቸው የትም እንደማያደርስና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፓሊሲም መባረቁን ነው ። ሶፍት ፓወር ምን ያህል ወሳኝ ሚና እንዳለው ከዚህ መረዳት ይቻላል። የአሜሪካ ዴሞክራሲ ፣ እሴቶች ፣ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ፣ የሰላም ጓድ ፣ ዩኤስኤይድ ፣ ሆሊውድ ፣ የትምህርት ተቋማት ሙዚቃው ፣ ወዘተረፈ የሀገራትን ልብና አእምሮ መማረኪያ የሶፍት ፓወር አካል ናቸው።
እንደ መውጫ
አሸባሪው ህወሓት እንደ ሰብዓዊ ጋሻና እንደ መደበቂያ የሚጠቀምበትን የትግራዋይ ልብና አመለካከት ማሸነፍ ሳይቻል ወታደራዊ ድሉ ምሉእ አይሆንም ። በጦር ሜዳ የሚገኘው ወታደራዊ ድል የትግራዋይን ልብና አመለካከት በማሸነፍ ካልታጀበ የአሸባሪው ህወሓት መደምሰስ ብቻ ድሉን ዘላቂና አስተማማኝ አያደርገውም ። የኢፌዲሪ መንግስት ከጦርነቱ ባልተናነሰ የትግራዋይን ልብና አመለካከት ለማሸነፍ የተግባቦት ስልት ነድፎ ሌት ተቀን መስራት አለበት ። ደጀኑን ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ለማነቃነቅ እና የአሸባሪው ህወሓትን ጭካኔና ሀገር የማፍረስ ደባ ለማጋለጥ እየሰራው ባለ ልክ የትግራይ ሕዝብን ለመማረክም በአግባቡ መንቀሳቀስ አለበት ። ለ50 አመታት ያህል እንደ መዥገር ደሙን ከሚመጠው ፤ የወላድ መካን ካደረገው ፤ በአንድ ለአምስት ጠርንፎ በአፈናና ጭቆና ባሪያ ካደረገው ፤ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ደም እያቃባው ካለ ፤ በስሙ እየማለና እየተገዘተ የቡድናዊ ጥቅም ማሳደጃ ካደረገው ፤ ወዘተረፈ……. ይልቅ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በእኩልነት በፍቅር በሰላም በነጻነትና በአንድነት የመበልጸግ አቅምና ተስፋ እንዳለው ፤ ለአሸባሪው ህወሓት ግለኛ ጥቅም ሲባል ልጆቹ ከጉያው እየተነጠቁ ለጦርነት እንደማይማገዱ ፤ የትግራዋይ እጣ ፈንታ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር በመስዋዕትነት የተሳሰረና የተገመደ መሆኑን ደጋግሞና በጥበብ አዋዝቶ በመግለጽ ልቡንና አመለካከቱን ማሸነፍ አለበት ። በስሙ እየማለና እየተገዘተ ለ27 አመታት ሀገርንና ሕዝብን በጠራራ በአደባባይ እየዘረፈ ራሱን ሲያበለጽግ እሱን ከድህነት አረንቋ ከሴፍቲኔትና ከተረጅነት ነጻ እንዳላወጣው ፤ አንድ ጊዜ ዐቢይ ሊያንበረክክህ ነው ሌላ ጊዜ አማራ ሊያጠፋህ ነው እያለ ፤ በተሳሳተ ትርክትና ቁጭት ሲያታግለውና ሲማግደው የኖረው ፤ ከተደቀነብህ አደጋ የምታደግህ እኔ ብቻ ነኝ የሚለው ለግል ጥቅሙና ከተጠያቂነት ለማምለጥ መሆኑን ደጋግሞ ማጋለጥ ያስፈልጋል ።
የትግራይ ሕዝብ መጻኢ እድል ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር በመስዋዕትነት የተሳሰረ ነው !!!
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com