ትምህርት የሁሉም ነገር መሰረት ነው የመባሉ ዋናው ጉዳይ፣ የሰው ልጅ አዕምሮን በእውቀት ሞልቶ ለአገርና ህዝብ የተሻለ ነገር ለመስራት የሚችል ዜጋን የመፍጠሪያ ቀዳሚ መሳሪያ በመሆኑ ነው፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን በሶማሌ ክልል ያለውን የትምህርት እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲላሂ መሐመድ ጋር ያደረግነውን አጭር ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሶማሌ ክልል ታዳጊዎችና ትምህርት እንዴት ተገናኝተዋል?
አቶ አብዲላሂ፡- ወጣቶች መማር ካልቻሉ ለራሳቸውም ሆነ ለአገራቸው ጠቃሚ ነገርን ማድረግ አይችሉም፡፡ በመሆኑም ወጣቶች እንደ ዜጋ ብቻ ሳይሆን እንደነገ የአገር ተረካቢነታቸው ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘት አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ ክልሉ እንደ አርብቶ አደር አካባቢነቱ በተለይ ባለፉት ዓመታት ያን ያህል በዘርፉ ተሰርቷል ማለት አይቻልም፡፡ ደካማ የትምህርት መሰረተ ልማት ስለነበረም የትምህርት ጥራቱም የወረደ ሆኖ ቆይቷል፡፡
እናም ትምህርት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎችና ለሁሉም ህጻናት መድረስ ስላለበት፤ አሁን ላይ በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችሉ እርምጃዎች እየወሰድን እንገኛለን፡፡ ስር ከሰደደው ችግር አኳያ ስራው ቀላል ሊሆን ባይችልም ሁሉም ህጻናት ትምህርት ማግኘት ስላለባቸው፤ ቢያንስ ችግሩን በግማሽ ያክል ለማቃለል የሚቻለንን ሁሉ እያደረግን እንገኛለን፡፡
ለዚህም የክልሉ ህብረተሰብ የወደፊት ህይወታቸው ተምሮ በሚገኝ እውቀት ላይ የተመሰረተ መሆኑን መረዳቱና በክልሉ ያለው የትምህርት ፍላጎት ለስራችን መቃናት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ መረዳቱ ተገቢ ነው፡፡ ወላጆችም የወደፊት ተስፋቸውን በማሰብ ልጆቻቸውን ወደትምህርት ቤት እየላኩ ነው፡፡ አሁን እየሰራን ያለነውም መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት እነዚህ ታዳጊዎች በጥራት ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ትምህርት ቤቶች እንዳይስፋፉና ጥራቱም እንዳይመጣ ያደረገው ምንድን ነው ብላችሁ ለያችሁ?
አቶ አብዲላሂ፡- ቀደም ሲል በተለይም ላለፉት አስር ዓመታት በክልሉ ሃብትን በአግባቡ ማስተዳደር ባለመቻሉ ክልሉ በልማት ተጠቃሚ አልነበረም፤ ያለው ሃብትም ቢሆን ለትምህርት ዘርፉ እምብዛም ትኩረት የሰጠ ስላልነበረ እንደ ክልል ትንሹ በጀት የሚያዘው ለትምህርት ዘርፉ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በሁሉም መለኪያ ሲታይ በክልሉ ያለውን ትምህርት ዝቅተኛው አድርጎታል፡፡
ለምሳሌ፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት በአገር ደረጃ በአማካይ 45 በመቶ ነው፤ በሶማሌ ክልል ግን ሰባት በመቶ ብቻ ነው፡፡ በተመሳሳይ፣ በክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል (5-8) ሽፋን 26 በመቶ፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ክልሉ 15 በመቶ ብቻ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ከአገራዊ አማካይ አንፃር እንኳን እጅጉን ያነሰ ነው፡፡ በመሰናዶ ትምህርት ሽፋንም ክልሉ ሰባት በመቶ ብቻ ሲሆን፤ አገራዊ አማካዩ 45 በመቶ፣ ትግራይ ክልል ደግሞ ከ90 በመቶ በላይ ነው፡፡ ይህ በክልሉ ያለውን ሰፊ ክፍተት አመላካች ነው፡፡
ይህ የሆነው ክልሉ ከሌሎች ክልሎች ያነሰ በጀት ስለሚመደብለት አይደለም፡፡ ችግሩ የመጣው ለዘርፉ ትኩረት ከመንፈግ፣ እንዲሁም የሚመደበውን በጀት በአግባቡ ካለማስተዳደርና ካለመጠቀም ነው፡፡ በዚህም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንኳን እንደ አገር የተቀመጠው ግብ እና በክልሉ የተገኘው ውጤት እጅጉን የተራራቀ ነው፡፡ በአንጻሩ በክልሉ የሚወጡ የዘርፉ ሪፖርቶች የተጋነኑ ናቸው፡፡ ምናልባትም 500 ተማሪዎች በትምህርት ቤት ካሉ፤ የክልሉ መንግስት 5000 ተማሪዎች አሉ ብሎ ነው የሚያስተላልፈው፡፡
የክፍል ተማሪ ጥምርታን በተመለከተም ሌላው ቀርቶ በጅግጅጋ እንኳን ከ150 እስከ 180 ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ለመማር ይገደዳሉ፡፡ የትምህርት ጥራትም አንገብጋቢ ችግር ነበረ፡፡ ለምሳሌ፣ በተማሪዎች መካከል መኮራረጅ ያለ ቢሆንም፤ በጉዳዩ ባዝንም ልናገረውና በሶማሌ ክልል በመንግስት የሚደገፍ የስርቆት መርሃ ግብር (ገቨርንመንት ስፖንሰርድ ቺቲንግ ፕሮግራም) ተዘርግቶ በተለይ የአስረኛና አስራ ሁለተኛ ተማሪዎች አገራቀፍ ፈተናዎችን እንዲሰሩ ይደረግ ነበር፡፡
ለዚህም ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጀምሮ ተማሪዎች ፈተናን እንዲሰሩ ይመቻችላቸዋል፤ የትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራንም አንድም ተማሪ እንዳይወድቅ የሚል መመሪያ ስለሚተላለፍላቸው ፈተናዎች እየወጡ እንዲሰሩና መልሶቹም ለተማሪዎች እንዲሰራጩ ይደረግ ነበር፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ የሶማሌ ክልል 85 በመቶ ተማሪዎች ሃይስኩልን ጨርሰው ዩኒቨርሲቲን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ቢችልም፤ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ግን እንዲቆዩ ማድረግ ስላላስቻላቸው በመጀመሪያው ዓመት ይባረራሉ፡፡
ካልሆነም በአብዛኛው ከኢንጂነሪንግ ወይም ከጤና ዘርፎች ወደ ሶሻል ሳይንስ ትምህርት ዘርፎች ሲገቡ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ተምረው የወጡ የክልሉ ተወላጆች ኢንጂነሮች፣ የጤና ባለሙያዎችና መምህራን ጭምር በገበያው ላይ እንዳይገኙ አድርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ የነበረው ሂደት ትውልድን በእውቀት ማነጽና ለነገ አገር የሚረከቡ ዜጎችን መፍጠር ሳይሆን ትውልድን የመግደል ተግባር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ችግሩን ለማቃለል ምን እርምጃ ወሰዳችሁ?
አቶ አብዲላሂ፡- እነዚህን ችግሮች ከለየን በኋላ ምንም እንኳን በአንድ ዓመት መፍታት ባንችልም፤ በሂደት ችግሮችን ማቃለል የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ በዚህ ዓመትም አብዛኞቹን ለመፍታት ጥረት ጀምረናል፡፡ ለምሳሌ፣ በዚህ ዓመት አምና ለትምህርት ቢሮው ተመድቦ የነበረውን አራት እጥፍ እንዲበጀት ተደርጓል፡፡ ይህ የሆነው ለክልሉ አዲስ በጀት ስለተመደበ ሳይሆን በጀቱ ሳይባክን ለተፈለገለት ዓላማ እንዲውል በማድረግ ነው፡፡ እርምጃውም የክልሉ መንግስት ዘርፉን ትኩረት ሰጥቶ በመደገፍ የሰው ሃብት ልማቱን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡
በተመሳሳይ በበጀት ዓመቱ የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደ ክልል በሃይስኩል ደረጃ 21 አዳዲስ ለመገንባትና 25 ለማስፋፋት፤ በመጀመሪያ ደረጃም 187 አዳዲስ፣ 200 የሚሆኑ ደግሞ በማስፋፊያ የሚሰሩ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ዓምና በአዳዲስ ግንባታም ሆነ ማስፋፊያና ጥገና ከ50 ትምህርት ቤቶች የዘለለ ማከናወን አልቻልንም ነበር፡፡
የጥራት ችግርን ለመፍታትም ትኩረት የተሰጠ ሲሆን፤ ከፈተና ስርቆትና ኩረጃ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ሙሉ በሙሉ መቅረፍ እንዳለብን በማመን ለተማሪዎች፣ ለመምህራንና ወላጆች ጭምር የማሳወቅና በኩረጃ ሳይሆን በማወቅ ማሸነፍ እንደሚገባ የማስገንዘብ ስራ እያከናወንን ይገኛል፡፡ ይህ ምናልባት በአንድ ጊዜ ሲቀር በርከት ያሉ ተማሪዎች ፈተናን እንዳያልፉ ሊያደርግ፤ በተማሪዎች ላይ መደናገጥና ፈተናን አለማለፍን እንደ ውድቀት የመቁጠር አዝማሚያን ሊፈጥር ይችላል፡፡
ሆኖም መውደቁ ዩኒቨርሲቲ ደርሶ ከመባረር አይብስምና ፈተናን ሰርቆ በማሰራት ሳይሆን በአግባቡ እውቀት አስጨብጦ ለማሳለፍ እየሰራን ነው፡፡ ተማሪዎች እንዳይወድቁ ለማስቻልም በሜካፕ፣ በተጨማሪ ሰዓት ትምህርት፣ በትምህርት ክለሳና ሌሎችም መርሃ ግብሮች ተማሪዎቹን ለማገዝ ከቢሮው እስከ መምህራን በቁርጠኝነት እየሰራን ነው፡፡
ባለፈው ሐምሌ 28 በክልላችን በተከሰተው ችግር የተነሳ በርካታ መምህራን በመውጣታቸው በክልሉ የመምህራን እጥረት ከመኖሩ ጋር ተዳምሮ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የቅጥር ስራ እየተከናወነ ሲሆን፤ ችግሩ ሲረጋጋ ለተመለሱ መምህራንም ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገላቸው እያስተማሩ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ ካሉ 190 ሃይስኩሎች ውስጥ፣ 100ዎቹ (ከ55 በመቶ በላዩ) ፕላዝማ የላቸውም፤ 85 በመቶዎቹም ቤተ መጻህፍትና ቤተ ሙከራ የላቸውም፡፡ በዚህ ዓመት ቢያንስ ለ50 ሃይስኩሎች ፕላዝማ ለመግዛት፤ ለ20 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ቤተ መጻህፍትና ቤተ ሙከራ እንዲኖራቸው ለማድረግ አቅደናል፡፡ እናም ዘንድሮ በጀመርነው መልኩ ቀጣይ ዓመት መድገም ከቻልን በክልሉ ያለውን የትምህርት ተደራሽነትም ሆነ ጥራት ችግር ለማቃለል የተሻለ መጓዝ ያስችለናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ጥራትን ለማምጣት መሰረቱ ላይ በምን መልኩ እየሰራችሁ ነው?
አቶ አብዲላሂ፡- ባለፉት አምስት ወራት ከ300ሺ በላይ ከሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመወያየትና ግንዛቤ በመፍጠር ታዳጊዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ለማስቻል ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ ተካሂዷል፡፡ የህዝባዊ ንቅናቄ ስራው ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርት እንዲጀምሩ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ጥራት ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም በጋራ ለመስራት ያስቻለ ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ በገጠር ያሉ መምህራን ደሞዛቸው አነስተኛ እንደመሆኑ ለመምህራኑ ህብረተሰቡ ነጻ ቤትና ምግብ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል፡፡
የመምህራንን አቅም የማጎልበትና የቴክኒክ ድጋፍ ስራ እየተከናወነ ሲሆን፤ ከጅግጅጋና ቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ለመምህራኑ አጫጭር ስልጠናዎችን ጭምር እየሰጠን እንገኛለን፡፡ ስኩል ኢምፕሩቭመንት ፕሮግራምም በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ሆኖም ከ90 በመቶ በላይ የክልሉ ትምህርት ቤቶች ለማስተማሪያነት ምቹ አይደሉም፤ ስታንዳርዱንም አያሟሉም፡፡ ይሄን ችግር ለመፍታትም ህብረተሰቡንና ትምህርት ቤቶችን የማስተሳሰር ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩም ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው እንዲቆዩ፣ ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩና የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ እንዲጎለብት ጉልህ ሚና አበርክቷል፡፡ የተማሪዎቹን ተነሻሽነት ለመጨመርም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የክልሉ ተወላጆች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ታዳጊዎች አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች በትምህርት ቤቶች እየተገኙ ለተማሪዎች አነቃቂ ንግግርና መልዕክቶች እንዲያስተላልፉና ተማሪዎች እነርሱን ለመሆን እንዲያልሙ እየተደረገ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሶማሌ ክልል የተማሩና ነገ አገር ሊረከቡ የሚችሉ ወጣቶች መፍለቂያ እንድትሆን ምን አስባችኋል?
አቶ አብዲላሂ፡- ለዚህ ውጤት መገኘት ከወላጆችና ከራሳቸው ከተማሪዎች ጋር በመቀራረብ በቀድሞው አካሄድ ውጤት እንደማይመጣና በርትቶ በመማርና በማጥናት ለስኬት እንደሚደረስ የማስገንዘብ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ የወላጆች፣ የመምህራንና የተማሪዎች ህብረትንም ለማጠናከር እየሰራን ነው፡፡ ሁሉም ለስራው ድርሻ እንዲኖረው ለማስቻልም ከወላጅ ህብረት ጋርም በየወሩ እየተገናኘን እየመከርን ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በየአካባቢው የተቀመጡ ወጣቶችም በቅዳሜና እሁድ ቀናት እንዲያስተምሯቸው እያደረግንም ነው፡፡ ዘንድሮ 12ኛ ተፈትነው ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡትም በክረምቱ ለዩኒቨርሲቲ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በፍሬሽ ማን ኮርስ አይነት ስልጠናዎች እንዲወስዱ በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ቀና እንዲሆን ለማስቻል ይሰራል፡፡
እንደ አጠቃላይ ከአሁኑ ጀምረን ፈተናን ማለፍ በአቅምና እውቀት እንጂ በኩረጃና ፈተና በመስረቅ ሊሆን እንደማይገባው፤ እንደማይሆንም ለተማሪዎች እያስረዳን እንገኛለን፡፡ እናም በእኛ በኩል ለነገሮች ትኩረት በመስጠት፣ ወላጆችም በቁርጠኝነት፣ መምህራንም በተገቢው ድጋፍና ተማሪዎችም ከልብ በሆነ ቁርጠኝነት በአንድ ላይ ከሰራን በእርግጥም ተማሪዎች በራሳቸው አቅም የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ አብዲላሂ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
ወንድወሰን ሽመልስ