ፕሮፌሰር ጋሬዝ ጃውት እና ፕሮፌሰር ቪክቶሪያ ኦዶኔል‹‹Propaganda and Persuasion››በሚል ርእስ እኤአ በ2011 ለንባብ ባበቁት መጽሃፋቸው፣ፕሮፖጋንዳ መረጃዎችንና ሀሳቦችን ሆን ብሎ በስፋት በማሰራጨት አንድን ግለሰብ፣ቡድን፣ተቋም፣ድርጅትና አገር ለመደገፍ ወይም ለመቃወምና ለማጥላላት በድግግሞሽ የሚሰራጭ የመረጃ ቅስቀሳ ዘዴ እንደሆነ በስፋት ያትታሉ፡፡
ሌሎች ስመጥር የኮሚኒኬሽን እና ፖለቲካ ፀሃፍት እና ምሁራንም፣ፕሮፖጋንዳን በአይነት እና በአላማው በመከፋፋል በሶስት ይመድቡታል፡፡ ከሶስቱ ፕሮፖጋንዳ አይነቶች አንዱና እጅግ አደገኛው ደግሞ‹‹ ጥቁር ፕሮፖጋንዳ ‹‹Black propaganda››የሚባለው ስለመሆኑ ይጠቁማሉ፡፡
‹‹ትልቁ ውሸት››በሚል ሌላ ቅፅላው የሚታወቀው፣ይህ አይነቱ የፕሮፖጋንዳ ዘዴ መረጃ ምንጩ የማይታወቅና በሬ ወለደ የፈጠራ ውሸት፣ ወሬ፣ ሀሜትና አሉባልታዎች እውነት አስመስሎ የማናፈስና የማሰራጨት ዘዴ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
የውሸት ፕሮፖጋንዳ በአንደኛው የአለም ጦርነት በጀርመን የተለመደ የፕሮፓጋንዳ ቴክኒክ መሆኑንም የተለያዩ መረጃዎች ይመሰክራሉ፡፡የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሲነሳም ጆሴፍ ጉብልስ‹‹The Master of Lies››አብሮ ይነሳል፡፡ሰውየው የጀርመኑ ናዚ ፓርቲ እና የመሪው አዶልፍ ሂትለር አፈ ቀላጤ ሆኖ ለአመታት አገልግሏል፡፡
ጉብልስ የውሸት ተዋናይ ነው፡፡ የውሸት አቀናባሪ፣ዲስኩር ደርዳሪ ነው፡፡ የውሸት ፈላስፋ ነው፡ ፡ የውሸትን ጥግ ያውቀዋል፡፡በውሸት ፈጠራ እና ውሸት የመዋሸት ቴክኒክ የተካነ ነው፡፡ በውሸት መሰናዶ የተዋጣለት ነው፡፡ ውሸት ለእርሱ በጣም ቀላሉ ነው፡፡ ሙያው ነው፡፡ ስራው ነው፡፡ የዕለት ጉርሱ፣እንጀራው ነው፡፡
‹‹ውሸት በተደጋጋሚ ከተነገረ በመጨረሻ ሰዎች እውነት ነው ብለው ይታለላሉ የሚል እምነት ያለው ጉብልስ፣አይን ባወጣ ቅጥፈቱ የገዛ ህዝቡን ማሞኘት ይችልበታል፡፡ ህዝቡን ግራ አጋብቶ ማወናበድ፣ምንም ቢፈጠር ምንም እንዳልተፈጠረ ፣ተሸንፎ እንደአሸነፈ በመሆን ተከታዮቹን በደስታና በድል አዳራጊነት የሚያስፈነጥዝ ሰው ነው፡፡ በዚህ ዋሾነቱም በስርዓተ መንግስቱ የፕሮፓጋንዳ ሚኒስትር እስከመሆን በቅቷል፡፡
በእርግጥ ውሸት የእውነትን አቅጣጫ ሊያዛባ ይችላል፡፡ ይሑንና ይህ አይነቱ የበሬ ወለደ ውሸት ፕሮፓጋንዳ የተገነባ ድርጅትም ሆነ ማንነት የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማነሱና ማፈሩ ብሎም መፈራረሱ አይቀሬ ነው፡፡ በአገሬ ሰው ‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል››እንደሚለው መሰል ፕሮፖጋንዳ ውሎ ሲያድር ፍፃሜው ሁሌም የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡
ውሸት ለስልጣን ዕድሜ ማራዘሚያነት ይጠቅመኛል የሚለው ጉብልም ሆነ መሪው ሂትለር በመጨረሻ የጠጣውን በውሸታቸው የተጠመቀውን መራራ እና አሳፋሪ ፅዋ ማስታወስ ግን መቼም ቢሆን እውነትን ሸፍኖ ማስቀረት እንደማይቻል ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን እብሪት እና ጥቃት ምክንያት ሳትፈልግ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ተገዳለች፡፡ የአሸባሪው ህወሓት አፈ ቀላጤዎችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው የጉብልስ ልጆችም ከትናንቱ የጉብልስ እና መሪው ውድቀት ሳይማሩ ዛሬም የውሸት ፕሮፖጋንዳን ዋነኛ ታክቲካቸው ማድረግን ተያይዘውታል፡፡
የማይካድ ሃቅ ቢኖር ጦርነት በጥይት ብቻ አይደለም። ትልቁ ጦርነት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ በተለይ በጦርነት ላይ፣ ከጥይትና ከቦምብ በላይ ሰራዊትንና ማሕበረሰብን የሚያሸብር ፣ሰራዊትን የሚፈታው ወሬ ነው፡፡ በጦርነት ውስጥ ከጦር በላይ ወሬ የሚፈታው ከባድ ነው፡፡ጦርነት ውስጥ ዜና የሚያናፍሱ ሰዎች እንደቀላል አይታዩም፡፡
አሸባሪው ህወሓት በጀግና የኢትዮጵያ ልጆች በጥይት ጦርነት እንዳታዳግም ተደርጋ ተሸንፋ በሶስት ሳምንት ዱቄት ሆና ነበር፡፡ በፕሮፓጋንዳ ጦርነት ግን አፈር ልሳ መነሳት ቻለች፡፡ ፕሮፓጋንዳና የሚድያ ዘመቻ አሸባሪው ህወሓት በህይወት ያለ አስመስሎታል፡፡
አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን ማንኛውም በተፈጥሮ ሂደት የሚያልፍ አካል መጀመሪያና መጨረሻ አለው። ይወለዳል ፣ያድጋል፣አርጅቶም ይሞታል። ህወሓት አሁን ላይ ከመኖር ወደ አለመኖር ተሸጋግሯል፡፡ጠውልጎ ከስሟል፡፡
ይሑንና አሁንም ቢሆን የቡድኑ ትርፍራፊና ጋሻ ጃግሬዎቹ ግብአተ መሬት አልተፈፀመም፡፡ የተነቃነቀ ጥርስ እንዲሉ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በመጨረሻ የሚፈራው ለውጥ እራት ሊሆኑ ተቃርቧል፡፡ ከወደቁ ወዲያ መንፈራገጥና መላላጥ ግን አላቆሙም፡፡ አጥፍተው ለመጥፋት እየባዘኑ ነው፡፡ኢትዮጵያን ለማፍረስም ሲኦል ድረስ እንደሚሄዱም ባደባባይ ሳያፍሩ ተናግረውታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ ላይ የአሸባሪው ህወሓት ጥይቷ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ በጎጥ በረት ውስጥ የተፈለፈለ ድርጅትና ባህሪ የተላበሱ፣በጸረ አንድነት፣በጸረ ዴሞክራሲ፣በጸረ ኢትዮጵያ የተሞላ የጎሳ ጡጦ ጠብተው ያደጉና ለኢትዮጵያ ህዝብ ተቆርቋሪ መስለው ቆባቸውን ለውጠው የሚጮሁ የህወሓት ጉብልሶችም በፕሮፖጋንዳ ዘመቻው እየተውተረተሩ ናቸው፡፡
በስሙ ስልጣኑን ለመያዝ ወይም ይዘው ለመቆየት ወይም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በሚሹ የውጭ ሃይሎች የተገዙ ባንዳዎች፣የስልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ከእኛ በላይ ላሳር በሚል ትእቢት ተወጥረው ፣ ጤንነታቸውን በሚያጠያይቅ መልኩ የበሬ ወለደ የውሸት ፕሮፖጋንዳ መንዛታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ዮሴፍ ጉብልስ መቃብር ፈንቅሎ ቢነሳ ሊቀናባቸው የሚችሉ ውሸቶችን እያስተጋቡ ናቸው፡፡
ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው አይደል የሚባለው፣ በአሁኑ ወቅት አሸባሪዋ ህወሓት እዚህ ገባሁ፣ እዚያ ታየሁ፣እገሌ ክፍለ ጦርን ደመሰስኩ፣እገሌን ማረኩ››የሚለውን ወሬ እያስወራች ፍራቻ ለመፍጠር እየተጋች ትገኛለች፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ጠላትን ለማሸነፍ በአስተሳሰብ በልጦ መገኘት ወሳኝ መሆኑን በመጀመሪያ ጠንቅቀህ ተረዳ፡፡ የጉብልስ ልጆች አላማ ሕዝብ እና ሰራዊቱን በስነ ልቦና ዘመቻ ለመፍታት መሆኑን ጠንቅቀህ እወቅ፡፡ ውሸታቸውን ሰምተህ ከራድክ እንዳስደሰትካቸውና እንደተሸነፍክ እወቅ፡፡ በውሸቱ ከመዳር ተቆጠብ፡፡ የውሸት ፕሮፖጋናዳው ሰለባ አትሁን። ውሸቱን እያስተጋባህ የሽብር ቡድኑ ዓላማ አስፈጻሚ እንዳትሆን ተጠንቀቅ፡፡
አሸባሪውን ቡድን ግብአተ መሬት በማፋጠን ሂደት ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጎንና ከሰንደቅ ዓላማ አጠገብ ቁም። ለጀግናው ሰራዊት ሞራል ሁነው እንጂ፣ከጠላትህ ጋር ሳታውቅ አብረህ የስነ ልቦና ጦርነቱ አካል አትሁን፡፡ ለከፋፋይ ጆሮ አትስጥ፡፡ ለጠላትህ ሞራል፣መሣሪያ እና አገልጋይ አትሁን፡፡ይልቁስ ለዜግነትህ ለአገርህ ክብር በኢትዮጵያዊነት አንድ ላይ ታገል።
ከወገኖች ምክር ተነጋገር፡፡ተመልሳ እንደማትወጣ የቤት ስራህን ከደጀኖች ጋር ቀምር፡፡ ስለ ሀገር ስላለው ሁኔታ ከትክክለኛው ከመንግስት አካላት ስማ፡፡ ከአንድ ግለሠብ እና ከፌስ ቡክ አርበኛ መቶ እጅ የበለጠ ስለ ኢትዮጵያ ጀግኖች ወታደሮች እና መሪዎቻችን እንደሚያስቡ ለአፍታም አትጠራጠር፡፡
ሰራዊታችን ደግሞ ‹‹በማንኛውም ግዳጅ ወይም ተግባር የላቀ ውጤት››በሚል እሴት የተገነባ ስለሆነ በየትኛውም ሁኔታ በማንኛውም የአየር ፀባይ ማንኛውም ግዳጅ በውጤት የሚያጠናቅቅ እና አንፀባራቂ ድል የሚያስመዘግብ መሆኑን ሁሌም ቢሆን እርግጠኛ ሁን፡፡
የሀገርህ ፍቅር የሚገለፀው ባዲራዋን ይዘህ ጠላቷን ተከላክለህ አለኝታ ስትሆን ነው። ሰንደቋን ከፍ አርገህ ከፊት ስትገኝ ነው፡፡ በእርግጥ ዳር እስከ ዳር አንድ በመሆን በኢትዮጵያዊነት ስሜት ከመከላከያና ከመንግስት ጎን መሆንህን እያሳየህ ትገኛለህ፡፡ይህን ማጠናከር እንዳለብህ መናገርም ለቀባሪው እንደማርዳት ድፍረት ይሆንብኛል።ብቻ በጉብልስ ልጆች የበሬ ወለደ አንቶ ፈንቶ አትፈታ፡፡ ጆሮ አትስጥ፡፡ያኔ ውሸትና ጉብልሶች ተሸንፈው በውርደት ይወድቃሉ፣ እውነትና ኢትዮጵያውያን አሸንፈው በክብር ይቆማሉ!
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም