እንደ አገር በመጣው ሁለንተናዊ ለውጥ ሳቢያ ከፍተኛ የሪፎርም ስራ ከተከናወነባቸው ክልሎች አንዱና ዋነኛው የሶማሌ ክልል ነው፡፡ በሪፎርሙ የክልሉን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን በክልሉ በተለይም በከተሞች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ባሉ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዱልፈታህ ሼክ ቢሂ ጋር ያቀረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሶማሌ ክልል እና ከተሞች እንዴት ይገለጻሉ?
ዶክተር አብዱልፈታህ፡- የሶማሌ ክልል በአገሪቱ ካሉ ክልሎች መካከል በስፋቱም ሆነ በህዝብ ቁጥሩ ትልልቅ ክልሎች ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡ አንጋፋና ታሪካዊ ከተሞችም አሉት፡፡ ሆኖም በታሪካቸውና እድሜያቸው ልክ የተጓዙና ያደጉ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ፣ እኔ መቀሌ ተምሬያለሁ፤ እዛ ስማር የመቀሌ ከተማን ታሪክ ሳነብና እኔ የተወለድኩባት ዋርዴር የምትባል ከተማን ታሪክ ሳነብ ታሪካቸው በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እድገታቸው ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የሶማሌ ክልል መልኩን እየቀያየረ የሚከሰት የግጭት ቀጠና ሆኖ የመቆየቱ ውጤት ነው፡፡
ለምሳሌ፣ ጎዴ የንጉስ ኃይለሥላሴ ትልቅ ቤተመንግስት እስካሁንም ድረስ በታሪክነት አለ፡፡ ይሄም ልክ አዲስ አበባ እንዳለው ቤተ መንግስት የከተማዋን ታሪክ የሚገልጽ መሆን ቢችልም ከተማዋ መጠቀም አልቻለችም፡፡ በተመሳሳይ ዋርዴር ከተማ በፍጥነት እያደገች የነበረች ቢሆንም ከኦብነግ መውጣት ጋር በተያያዘ በተፈጠረባት ተጽዕኖ ከ25 ዓመት በፊት የነበረውን እድገትና አሁን ያለው እድገት ሲታይ በአንጻራዊነት የበፊቱ የሚሻል ይመስላል፡፡ ሌላዋ የክልሉ የታሪክ ከተማ የሆነችው ደግሞ ዋልዋል ናት፡፡ አድዋ ሲባል ጣሊያን የተሸነፈበት ቦታ መሆኑን ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡ ይሁን እንጂ የመጀመሪያው የጣሊያን ሽንፈት ዋልዋል ላይ ነው፡፡ ከትላልቅ ሰዎች በስተቀር ይሄንን ታሪክ የሚያውቁት የታሪክ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ዕድሜ ጠገብና ታሪክ ያላቸው ከተሞች በተጓዳኝ አዳዲስ ከተሞች እየተፈጠሩና በቁጥር እየተበራከቱ ነባሮቹም እየሰፉ ይገኛል፡፡ በተለያየ ምክንያትም የህዝብ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ ሆኖም የእድገትና ልማት ሂደታቸው በዚህ ልክ የሚገለጽላቸው አይደሉም፡፡ ጅግጅጋ ግን የክልሉ ዋና ከተማና ትልቋ ከተማም እንደመሆኗ በማደግ ላይ ትገኛለች፡፡
አዲስ ዘመን፡- እነዚህን ከተሞች በቀጣይ የቱሪስት መዳረሻ፤ የቴክኖሎጂ መፍለቂያና የስራ እድል መፍጠሪያ ማዕከል እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ በምን መልኩ ለመስራት አስባችኋል?
ዶክተር አብዱልፈታህ፡- ይሄን የማድረግ ኃላፊነቱ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የበርካታ አካላት ድርሻ ነው፡፡ ለምሳሌ ታሪክን ከማልማት፣ ከማስተዋወቅና የቱሪዝም መስህብ ከማድረግ አኳያ ከኮሚዩኒኬሽንና ከባህልና ቱሪዝም ተቋማት ጀምሮ የበርካታ አካላትን ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ብዙ ባለድርሻ ስላለ ተባብረንና ተጋግዘን እንድንሰራ እየተደረገ ነው፡፡
ከተሞች የቴክኖሎጂ መፍለቂያ እንዲሆኑም ክልሉ ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ባለድርሻዎችም ጋር እየሰራ ሲሆን፤ ክልሉ እያበረታታው፣ ዩኒቨርሲቲውም የቴክኖሎጂ ፈጠራን እንደ አንድ ዓላማ ይዞ ኃላፊነቱን በመውሰድ እየተሰራ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ከሚሰራ አንድ የግል ድርጅት ጋርም ወጣቶችን በማደራጀት አዳዲስ ተክኖሎጂዎችን እያስተማርን ሲሆን፤ ይህም ለወጣቶቹ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያፈልቁ ከማስቻሉ በተጓዳኝ ለስራ እድል ፈጠራ ይረዳቸዋል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ አሁን ያለው አመራር ሲመጣ፤ በካቢኔ ቁጭ ብለን ለድርድር ከማይቀርበው የሰላም ስራ በተጓዳኝ እንደ ቁጥር አንድ ቢ የወሰድነው የሥራ እድል ፈጠራን ነው፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ስራ አልባ ከሆነ ያስባል፤ ይጨነቃል፡፡ በአንጻሩ እንደ አገርም ሆነ እንደ ክልላችን ያለውን ለውጥ ማደናቀፍ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ የቸገረውንና በልቶ ማደር ያቃተውን ለመጠቀሚያነት ስለሚፈልጉ ስራ የሌለው ህዝብ በተለይም ወጣቱ ለእነዚህ ሰዎች ተግባር ተጋላጭ ይሆናል፡፡ ይህ እንዳይሆንም ነው ሁሉም የድርሻውን ወስዶ እየሰራ ያለው፡፡
ለዚህም በምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራና 12 ቢሮዎች አባል የሆኑበት የሶማሌ ክልል የስራ እድል ፈጠራ ካውንስል ተመስርቶ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተተገበሩ ሲሆን፤ ሥራውም በክልሉ በጀት፣ በወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ፣ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተደረገ ድጎማ ፋይናንስ ተደግፎ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የነበሩ ክፍተቶችንና ያሉ እድሎችን በመለየት ወደተግባር የተገባ ነው፡፡
በዚህም ከጅግጅጋ ባለፈ በእያንዳንዱ ከተማ በተለይም በክልሉ ባሉ 11ዱም ዋና ዋና የዞን ከተሞች፤ እንዲሁም በክልሉ ባሉ 93 ወረዳዎች ምን አይነት እድል አለ የሚለው ተለይቷል፡፡ ለምሳሌ፣ በአፍዴር ዞን በምትገኝ ቦታ የሚመረተው ጨው ጥራት ያለውና ገበያ ላይ ቢቀርብ ከውጪው ጋር የሚወዳደርና ሊያሸንፍም የሚችል ነው፡፡ ሆኖም በተደራጀ መልኩ ስላልተሰራ ከ30 እስከ 40 በመቶ ነው እያመረተ ያለው፡፡
በዚህ መልኩ በተለዩ ሀብቶች ላይ ወጣቱን አደራጅቶ ለማሰማራትም የአቅም ክፍተታቸውን በመለየትም መሰማራት እንደሚፈልጉበት የስራ መስክ ከክልሉ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ጋር በመሆን የሙያ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፡፡ ከስልጠናው ጎን ለጎንም ወደስራ ሲገቡ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመለየት የሚያስችላቸውን የቢዝነስ እቅድ እንዲያዘጋጁ ይደረጋል፡፡ የቁጠባ ባህላቸው እንዲያድግና የስራ መነቃቃት እንዲፈጥሩም እየሰራን ነው፡፡
የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና እናቶችን በማሳተፍ ጭምር እየተሰደዱ ለችግር መዳረግ እንዲበቃ የማስገንዘብ ስራ እየሰራን፤ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ተግባራዊ እያደረግን ነው፡፡ ለዚህም በጅግጅጋ ብቻ 20 የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እንዲኖሩ እየተሰራ ሲሆን፤ እስካሁን አምስቱ ወደተግባር ገብተዋል፤ አምስቱ ደግሞ በሳምንት ውስጥ ስራ ይጀምራሉ፤ በሁለት ወር ውስጥ ደግሞ 20ውም ወደተግባር እንዲገቡ ይደረጋል፡፡
በተመሳሳይ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ወደስራ ያልገቡ ወጣቶችን (በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠኑና ከአስር እስከ አስራ ሁለት ሆነው ከተደራጁ) በመስኖ ስራዎች ተሰማርተው እንዲሰሩ የሚያስችል ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በመጣ ድጋፍ በክልላችን አራት ዞኖች (ፋፈን፣ ጎዴ፣ ሽንሌና ኮራሂ ዞኖች) ላይ እየተሰራ ይገኛል፡፡
የስራ ቅጥር ፍትሃዊ ተወዳዳሪነትን ከማስፈን አኳያም በዘመድ ወይም ደግሞ በሌላ ምክንያት ብቻ ወደስራ ይገቡበት የነበረበትን የተበላሸ አሰራር እንዲታረምና ግልጽ የቅጥር መስፈርት ኖሮ በግልጽ ማስታወቂያ ተወዳድረው እንዲገቡ እየተደረገ ነው፡፡ ቅሬታ ሲኖራቸውም በየደረጃው እያቀረቡና ኮሚሽን ድረስ በመሄድ ጉዳያቸው እንዲጣራለት የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቷል፡፡ ይህም ወጣቶች ተወዳድረው ስራ መቀጠር እንደሚችሉ በማመን መማራቸው ትርጉም እንዳለው እንዲያስቡ፤ ባለስልጣኖችም ስራቸውን በጥንቃቄ እንዲሰሩ እያደረጋቸው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ከተሞች የመኖሪያ ቤት ችግር እንዴት ይገለጻል? ችግሩን ለመፍታትና ጅግጅጋንም ለሌሎቹ የክልሉ ከተሞች ሞዴል ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?
ዶክተር አብዱልፈታህ፡- የቤት ጉዳይ እንደ ክልል ሰፊ ችግር ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታትም አሁን ላይ በክልሉ ከተሞች 1000 ቤት እየገነባን ነው፡፡ በቅርቡም ሌላ አንድ ሺህ ቤት ይጨመራሉ፡፡ በጥቅሉ በሁለት ዓመት ውስጥ እስከ አራት ሺህ ቤት ለመስራት እየጣርን ነው፡፡ የሚገነቡ ቤቶችም የነዋሪውን አቅም ያገናዘቡ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
መንግስት በራሱ ከሚገነባቸው ባለፈም መሬት በማቅረብ በማህበራትና በሪል ስቴት አልሚዎች አማካኝነት የቤት ፍላጎቱ እንዲሟላ ለማድረግ እቅድ ተይዟል፡፡ የቤት ግንባታ ስራዎችም ከጅግጅጋ ጎን ለጎን አማራጭ ከተሞችን ለመፍጠር በእያንዳንዱ የዞን ከተማ ላይ የሚተገበር ነው፡፡ ጅግጅጋም የክልሉ ዋና ከተማ እንደመሆኗ ሌሎች የክልሉ ከተሞች የእርሷን ፈለግ ሊከተሉ የሚያስችል ስራ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የክልሉ ከተሞች ዘመናዊና ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ምን አቅጣጫ አስቀምጣችኋል? ከባለድርሻዎች ምን ይጠበቃል?
ዶክተር አብዱልፈታህ፡- እኛ ጤናማ ያልሆነ የከተሞች መስፋፋት አንፈልግም፡፡ ስትራቴጂውም ትልልቅ የሆኑ ከተሞች፤ ነገር ግን ከህጻናት እስከ አዛውንት ላሉ ለሁሉም ነዋሪዎቻቸው ምቹ የሆኑ ከተሞች መፍጠር ነው፡፡ አንዲት ከተማም ለህይወት ምቹ እንድትሆን በጣም ትልቅ መሆን የለባትም፡፡ ትንሽም ከተማ ብትሆን ከስነ ህንጻዋ በተጓዳኝ ጽዳቷን ከጠበቀች፤ እንደ ውሃ፣ መብራት፣ ጤና ተቋም፣ ትምህርት ቤትና መሰል መሰረታዊ አገልግሎቶች ከተሟሉላት፤ አረንጓዴ ቦታዎች ካሏት ዘመናዊና ለህዝቦቿም ምቹ ትሆናለች፡፡
የምናስበውም፣ በክልሉ ጥሩ ፕላን ያላቸውና በፕላን የሚመሩ ከተሞችን የመፍጠር፤ ጽዳታቸውን የጠበቁ ከተሞችን ዕውን የማድረግ፤ ለአይንና ስሜት ገዢ የሆኑ፣ ለአካባቢ ጥበቃም የሚያግዙና የከተሞች ሳንባ በመሆን ለሰው ልጅ ጤናማነት ምክንያት የሚሆኑ አረንጓዴ ቦታዎችን የተጎናጸፉ፤ መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች የተሟሉላቸው ከተሞችን ለመገንባት ሁሉም በየሴክተሩ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ለማድረግ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ከመብራትና ቴሌ ጋር በተያያዘ እኛጋ በአብዛኛው ችግር ይታያል፡፡ ለምሳሌ፣ አሁን ላይ ከጅግጅጋ ቀጥላ ትልቅ የሆነችውና ከምኒልክ ጊዜ ጀምራ የነበረችው የደገሃቡር ከተማ እስካሁን የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት አላገኘችም፡፡ ባደረግነው ግምገማ መሰረትም የሶማሌ ክልል 0ነጥብ04 በመቶ ብቻ ነው የኤሌክትሪክ ድርሻ ያለው፡፡ ይህ ደግሞ እጅጉን የሚያሳዝን፣ ፍትሃዊነትም የጎደለው ተግባር ነው፡፡ አንዳንዴም እኛ ዜጋ አይደለንም ወይ በሚያስብል ደረጃ የሚገለጽ ነው፡፡
ምናልባት ቀደም ሲል ይህ ከጸጥታ ጋር ሊያያዝ ይችላል፤ አሁን ግን ለውጡን ተከትሎ ችግሮቹ ስለተቃለሉ የተደራሽነት ተግባሩን ማከናወን ይቻላል፡፡ እናም ህዝቡ ኢትዮጵያዊነቱ እንዲሰማው እንጂ በኢፍትሃዊ አሰራሮች ዜግነት እንዳይሰማው ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ እናም እኛ በራሳችን ለመስራት ስንጥር ከእኛ በላይ ላለው ጉዳይ ደግሞ የፌዴራል መንግስት ሊያስብበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልስ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ!
ዶክተር አብዱልፈታህ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
ወንድወሰን ሽመልስ