የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማዕድ፤
የተሸፋፈነው ስውሩ የትህነግ ጭካኔና አረመኔያዊ ገመና በሚገባ መገላለጥ የጀመረው ቀደምት አባላቱና ቡድኑን በከፍተኛ ኃላፊነት ሲመሩ የነበሩት ሁለት ግለሰቦች በ1982 ዓ.ም እጃቸውን ለደርግ መንግሥት በመስጠት በይቅርታ ተጸጽተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት ከተቀላቀሉ በኋላ ነበር። እነዚህ ሁለት ግለሰቦች አቶ አብርሃም ያየህና አቶ ገብረ መድህን አርአያ ይባላሉ።
ዛሬም ድረስ የቡድኑን እኩይ ተልእኮ ከማጋለጥ ያልቦዘኑት እነዚህ ሁለት የቀድሞ የትህነግ አመራሮች እጃቸውን ለመንግሥት መስጠት ብቻም ሳይሆን አዲስ ዘመን ጋዜጣን ጨምሮ በወቅቱ በነበሩት ሚዲያዎች በሙሉ የቡድኑን ግፍ በመዘርዘር ጉዱንና ክፋቱን ይዘከዝኩ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ይሄው ምስክርነታቸው ከወቅታዊ የሚዲያ ፍጆታ በዘለለ “ታላቁ የወያኔ ሴራ” በሚል ርዕስ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲታላለፍ ታስቦ በመጽሐፍ ታትሞ ለህዝብ መሰራጨቱ ይታወሳል።
በተለይም የቡድኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፋይናንስ ክፍሉ ኃላፊ የነበሩት አቶ ገብረ መድህን አርአያ ቀደም ባሉት ዓመታትም ሆነ በቅርቡ በኢሳት ቴሌቪዥን ቀርበው የሰጡት ምስክርነት በእጅጉ የዚህን እኩይ ቡድን ጭካኔና አረመኔያዊ ድርጊት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ስለሆነ ቃል በቃል ያሉት እንዲህ ነበር።
“በ1977 ዓ.ም በነበረው ድርቅ የህወሓት አመራር የትግራይ ህዝብ እየሞተ ዓለም በሙሉ የረዳውን እህል አመራሩ ሸጠው።በዚያ ወቅት ህወሓት ለማሌሊት (ማርክስሲት ሌኒንስት ሊግ ኦፍ ትግራይ) ምስረታ ሸብ ረብ የሚልበት ወቅት ነበር። ይኸው ማሌ በመባል የሚታወቀው ሊግ የተመሠረተው ለድርቅ የመጣው እህል ተሸጦ በተገኘው ስልሳ ስድስት ሚሊዮን ብር ነበር።
የእርዳታ እህሉ እንዴት ይገኝ እንደነበረ የገለጹበት ዘዴም በራሱ የቡድኑ አመራሮች በርግጥም ሰብዓዊ ፍጡራን ናቸው ወይ? አሰኝቶ የሚያስጠይቅ ነው።በርካታ ዝርዝር መረጃዎችን የሰጡበት ዋናው ፍሬ ሃሳብ ሲጨመቅ የሚከተለውን የመሰለ ይዘት ነበረው።“በድርጅቱ የፋይናንስ ኃላፊነቴ አንድ በስውር የተቀናበረ ተልዕኮ ተሰጥቶኝ ነበር።የተልዕኮው ዋና ዓላማ የሰብል እህሎች ነጋዴ በማድረግ ራሴን ለርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ማቅረብ ነበር።(ምናልባትም አቶ ገብረ መድህን ባይገልጹትም የመራር ተውኔቱን ትርዒት የከወኑት ሱዳናዊ ዜጋ መስለው ሳይሆን እንደማይቀር የገመታል‹?›)።ስሜም ተለውጦ ሐጂ መሐመድ ተብሏል።በዚሁ መሠረትም በርሃብ ለተጠቃው የትግራይ ህዝብ የነፍስ አድን እህሉን እንዲሸምቱ የውጭ ተራድኦ ድርጅቶችን ከእኔ ጋር አስተዋውቋቸው።
እኔም የፈለጉትን የእህል መጠን ያህል በሽያጭ ለማቅረብ መቻሌን አረጋገጥኩላቸው።በውሉ መሠረትም ግዢው አምስት ሺህ ኩንታል ከሆነ ሦስት ወይንም አራት ሺህ ውን ኩንታል አሸዋ እንዲሞላበትና አንድ ወይንም ሁለት ሺው ማሽላ የያዘ ጆንያ ከፊት ለፊት እንዲደረደር አደረግን።አሥር ሺህ ኩንታል የሚገዙ ከሆነ ትክክለኛው እህል ከሁለት ሺህ ኩንታል አይበልጥም ነበር።በተቀሩት ጆንያዎች በሙሉ የሚጠቀጠቀው አሸዋ ነበር።በዚሁ መሠረትም ተልዕኮው እየተሳካ የቡድኑ ልብ ማበጥ ስለጀመረ ወደ መንግሥት ስልጣን መጨበጫ ዳርቻ እየተቃረበ መምጣት ጀመረ።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም በቅርቡ በነበረው የፓርላማ ውሏቸው የቡድኑ የጥፋት ጡንቻ ፈርጥሞ አንዳንድ አካባቢዎችን በጦርነት አሸንፎ መቆጣጠር የቻለው ከ1977 ዓ.ም ድርቅ በኋላ እንደነበር ፍንጭ አከል ሃሳብ መሰንዘራቸው ይታወሳል።
እጅግ ህሊናን የሚያቆስለው ይህን መሰሉ ኢሰብዓዊ ተግባር ይፈጸም የነበረው በሺህዎች የሚቆጠረው የትግራይ ህዝብ በርሃብ እየተሰቃየ በነበረበት ወቅት መሆኑን ቡድኑ ራሱ ባቀረበው ሪፖርት ውስጥ እንዲህ በማለት ሰፍሯል፤ “በ1977 ዓ.ም አሰቃቂ የድርቅ አደጋ ምክንያት አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ ከሞት አፋፍ ላይ ደርሶ ነበር። ከ36 ሺህ በላይ ህዝብ ሞቷል።ሃምሳ ሺህ ህዝብ ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከ170 ሺህ ህዝብ በላይ ደግሞ ወደ ሱዳን ተሰዷል። …በሪጂን 2 እና 3 ብቻ 318 ሺህ የቤት እንስሳት አልቀዋል።” (የህወሓት ህዝባዊ ትግል፤ ከ1967-1992 ዓ.ም ገጽ 139)።
ሌብነትና ዘረፋ የትህነግ ዋና መገለጫና የህልውናው እስትንፋስ ጭምር ስለመሆኑ ከዚህ ሌላ ምን ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። በበረሃ የውንብድና ዘመኑ ሲተገብረው የኖረው ስርቆትና ማጭበርበር ወደ ከፍታ ተሸጋግሮ የሀገረ መንግሥትን በትረ ሥልጣን ከጨበጠም በኋላ በህዝብና በሀገር ላይ ሲፈጽማቸው የኖሩት የግፍ ተግባራቱ ምን እንደነበሩ ያልመሸበት ታሪካችን ምስክር ነው።
ይህ አሸባሪ ቡድን በ27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ የሰረቀውና የዘረፈው ቁሳዊ ሀብት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ራሷን እየጋጠ ገድሏታል። በመዋቅር ባደራጃቸው የንግድ ተቋማቱ “የብረት ሰንሰለት” ጠፍንጎ ህዝቡንና ሀገሪቱን ጠፍሮ በማሰር “ህጋዊ ሲለው በከረመው ዘዴና በኮንትሮባንድ ንግድ ከኩሽና ቁሳቁስ እስከ ከፍተኛ ፕሮጀክቶች ድረስ የአንጡራ ሀብታችንን መቅኒ ሙጥጥ በማድረግ ውስጣዊ ሰብእናችንና ሀብታችንን እንዳሻው ሲጨማለቅበት ኖሯል።ለጋሷን ተፈጥሮ ጭምር እንድትራቆት ሆን ብሎ በእኩይ ተግባሩ ቀጥቷታል።“የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማዕድ” የሚለው ብሂል ለዚህ እኩይ ቡድን መገለጫነት የዋለውም በዚሁ ምክንያት ነው። በአጭር አገላለጽ ትህነግ በጭካኔ ሲያላምጥ የኖረው ህዝብንም ሀገርንም አንድ ላይ በማኘክ ነው።
መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል፤
ይኸው የወንበዴ ቡድን “ከእሾህ ወጥቶ ጋሬጣ” እንዲሉ ከሰሞኑ በወረራቸው የአማራና የአፋር ክልሎቻችን ውስጥ ምን እየፈጸመ እንዳለ እለት በእለት እየተከታተልን ነው። ዋነኛው ዓላማው አንድም “ሲኦል ድረስ ወርዶም ቢሆን” ከሳጥናኤል ጋር በመስማማት “ኢትዮጵያን ለማፈራረስ” መትጋት ሲሆን ይህ ተግባሩ እየተደገፈ ያለው በውስጥና በውጭ በፈለፈላቸው ጀሌዎቹ አማካይነት ነው። ለተልዕኮው ዋነኛ መጋለቢያዎቹ ያደረጋቸው ደግሞ አንዳንድ ከሙያ ሥነ ምግባራቸው ጋር የተፋቱ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ የተራድኦ ድርጅቶችና “ሰብዓዊ መብቶችን እናስከብራለን” የሚል ታርጋ ለራሳቸው የለጠፉና አጋሰሳዊ ባህርይ የተላበሱ ተቋማት መሆናቸው በእጅጉ ያሳፍራል። ይህን መሰል የሴራ ተግባሩን እየከወነ ያለው ንፁሐንን ከጨፈጨፈ በኋላ የተጋተውን ደም እያቀረሸ በሚሰጠው መግለጫ ጭምር ነው። የሥነ ልቦናው ውቅር ከሌብነትና ከዘረፋም ከፍ ያለ እንደሆነ ለማረጋገጥ ይህ ክፋቱ በአስረጂ አብነት ሊጠቀስ ይችላል።
የሁለተኛው ተልዕኮው ዓላማ የወረራቸውን ክልሎች ዘርፎና ቀምቶ ምስኪኑን ዜጋ “እርቃኑን በማስቀረት” ማዋረድ ነው። ስለሆነም የቡሆ ዕቃ ውስጥ ካለው ሊጥ እስከ ከፍተኛ የሀገር ሀብት አጋብሶ በመውሰድና ሊወስዳቸው ያልቻላቸውን ደግሞ ማውደሙን እያስተዋልን ነው። አልሆነለትም እንጂ ቢሆንለት ኖሮ የወረራቸውን ክልሎች ኦና አድርጎ እንደሚፎክረው በበቀል በትሩ “ሂሳብ እያለ በነጋ በጠባ የሚፎክርበትን የጭካኔ ቁማሩን ለማወራረድ” ነበር።
እንደዚያም ቢሆን ግን ለቀናትና ለሳምንታት በቆየባቸው አካባቢዎች ያደረሰው ጥፋትና ጉዳት ከ እስከ ከ ተብሎ ግምት የሚወጣለት አይደለም። ከማሳ እስከ ጎተራ፣ ከግለሰቦች ቤት እስከ ተቋማት እንደ አንበጣ ወሮ ንፁሐንን ገፏል፤ ቆርጥሟል። ወደፊት ታሪክ ምስክርነቱን እስኪሰጥ ድረስ ለጊዜው መመስከር የሚቻለው ያልዘረፈውና ያላወደመው የንብረት ዓይነት እንደሌለ ብቻ ነው። ዳሩ ቤተ አምልኮዎችን የተዳፈረ ጨካኝ እንደምን ለንብረትና ለእንስሳት ሊሳሳ ይችላል?
“ሌባ ውሻ በአፉ ሊጥ፤ ለወገቡ ፍልጥ” እንዲሉ በጀግናው ሠራዊታችንና በአካባቢ ሚሊሽያዎችና ልዩ ኃይሎች እየተቀጠቀጠ እንኳን ከነፍሱ ይልቅ የሙጥኝ ብሎ እየረገፈ ያለው የዘረፋው ምርኮ እያሳሳው መሆኑን እያስተዋልን ነው። የጥፋት ድርጊቱ ነግ ተነገወዲያ በመላው ዓለም ዘንድ ትክክለኛ የአሸባሪነት ባህርይ መገለጫ ሆኖ ለትምህርትና ለማሳያነት መዋሉ እንደማይቀር ግብሩ ምስክር ነው።
“መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል” እንዲሉ፤ ህዝብንና ሀገርን መዝረፉ የእኩይ ተግባሩን አራራ ሊያረካለት ስላልቻለ ለተራድኦ ሥራ በትግራይ ክልል የተሰማሩ የዓለም አቀፍ ተቋማትን የእርዳታ እህልና ቁሳቁስ የተከማቸባቸውን መጋዘኖች እየሰበረ መዝረፍና ማቃጠሉን እንደ አዲስ ፋሽን ወስዶ ሰይጣናዊ ተግባሩን እየተወጣ መሆኑንም ሰሞኑን የሚወጡ መረጃዎች እያረጋገጡ ይገኛሉ። በዚሁ ዓመት በመጋቢት ወር የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን (ኤም.ኤስ.ኤፍ) ንብረት የሆኑትን የሕክምና ተቋማት መድኃኒቶችና መገልገያዎች መዝረፉ ይታወሳል። አንዳንድ የዓለም አቀፉ የተራድኦ ድርጅቶችና የወያኔው አፈ ቀላጤ የሆኑ ሚዲያዎች ይህንን መሰሉን ዘረፋ አውሸልሽለው ማቅረባቸው አይዘነጋም።
እውነትና እርግዝና ቀን ሲገፋ አፍጥጦ መገለጹ አይቀሬ ነውና ከጥቂት ቀናት በፊት ይኸው አሸባሪ ቡድን የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅትን (USAID) የእርዳታ እህልና ቁሳቁሶች የተከማቹበት መጋዘን መውረሩና መዝረፉ ይፋ ተገልጦ በመላው ዓለም ዋና የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ መሰንበቱ ይታወሳል።ይህንኑ ድርጊቱን የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ዳይሬክተር ሚ/ር ሾን ጆንስ ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ በዝርዝር አስረድተዋል።የዳይሬክተሩን መግለጫና ምስክርነት መነሻ በማድረግም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከእንቅልፋቸው ባንነው በመቀስቀስ ዜናውን እየተቀባበሉ ቡድኑን በማብጠልጠል ላይ ይገኛሉ።
ያፈጠጠውና ያገጠጠው የአሸባሪው ቡድን ድርጊት ግልጽ ሆኖ በተቋሙ ተወካይ ምስክርነት እየተረጋገጠ እያለ ይሄንን አሳዛኝ ዜና ፊት ለፊት ከማውገዝና አቋሙን በይፋ ከመግለጥ ይልቅ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ያወጣው አሸማቃቂ መግለጫ “አራንባና ቆቦ” ተብሎ የሚታለፍ ብቻ ሳይሆን አንገት የሚያስደፋ ክህደት ጭምር ነው። የተራድኦ ድርጅቱ መሪ በይፋ የገለጹትን እውነታ ገሸሽ በማድረግና በመቃወም በሚመስል ድምጸት ኤምባሲው ያወጣው መግለጫ በታሪካችን ጥቁር መዝገብ ውስጥ በጠቆረ ቀለም ተጽፎ ሊቀመጥ እንደሚችል ያለማስተዋላቸውም ያስገርማል።አንዳንድ የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት የቡድኑን እኩይ ማንነት በይፋ መግለጥ እየጀመሩ ስለሆነ በቅርቡ አለንልህ እያሉ ሲያንደረድሩት የከረሙት ሁሉ አንቅረው እንደሚተፉት ይጠበቃል።
ትህነግ አድጎ የጎለመሰበት የሌብነት፣ የዘረፋ፣ የውሸትና የክህደት ባህርያቱ እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ከእርሱ ጋር ፀንተው የሚኖሩ እንጂ ይሻሻላል ተብሎ አይገመትም። “ተፈጥሮን ተመክሮ ስለማይፈውሰው”ም የመጨረሻ ዕድሉ ግብዓተ መሬቱ እስከፈጸም ድረስ “ክፉን እስከ ክንፉ” እንዲሉ እስከ ወዲያኛው ድረስ ቀብሮ መገላገል ብቻ ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013