እንደሚታወቀው ዓለማችን ሩብ ክፍለ ዘመን በማይሞላ ጊዜያት ውስጥ ብቻ አውሮፓ ውስጥ ጀምረው መላ ዓለምን በሁለት ጎራ ከፍለው እርስ በእርስ ያጫረሱ ሁለት እጅግ አስከፊ ጦርነቶችን አይታለች፡፡ ይህም ማህበራዊ ቀውሱንና ኢኮኖሚያዊ ውድመቱን ሳይጨምር ከሃምሳ ሚሊዮን በላይ ነፍሶችን በመቅጠፍ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሁሌም በክፉ ሲታወስ የሚኖር ጥቁር ጠባሳን ጥሎ አልፏል፡፡ እናም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ መሰል ጦርነት ዳግም እንዳይከሰት ለመከላከል ታስቦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሃምሳ ሀገራትን በአባልነት አቅፎ እ.ኤ.አ በ1945 ተመሰረተ፡፡
የእኛዋ ኢትዮጵያም ከመስራቾቹ መካከል አንዷ ናት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሥሩ በርካታ ድርጅቶችን ያቀፈ ሲሆን የጸጥታው ምክር ቤት አንዱ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እ.ኤ.አ በ1948 በቻርተር የተቋቋመ የጸጥታና የደህንነት ጉዳዮችን የሚመለከት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮችን የሚመለከተው አካሉ የፀጥታው ምክር ቤት በ193ቱ አባል ሀገራት የዘርን፣ የፆታ፣ የቋንቋ ወይም የሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ ለሁሉም አገራትና ለሁሉም የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች እና መሠታዊ ነፃነቶች እዲከበሩ በመተዳደሪያ ቻርተሩ ውስጥ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ በሥሩ ያለው የጸጥታው ምክር ቤት ሃገራትን በእኩል ዐይን ማየት ባለመቻላቸው በተለያዩ ጊዜያቶች ለአንዳንድ አባል ሀገራት በተለይም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ለተሰጣቸው ኃያላኑ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት ሲወግኑ በመታየታቸው የቆሙለትን ዓላማ ማሳካት አልቻሉም በሚል በተደጋጋሚ ሲተቹ ቆይተዋል፡፡ በመንግስታቱ ድርጅትና በጸጥታው ምክር ቤት አሰራር አድሏዊነት በማሳያነት ከሚነሱ ውሣኔዎች መካከል ከፍልስጤም እስከ እስራኤል፣ ከሶሪያ እስከ የመን፣ ከኢራቅ እስከ አፍጋኒስታን፣ ከሊቢያ እስከ ሶማሊያ በርካታ ምሳሌዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡
እናም የተባበሩት መግስታት ድርጅትም ሆነ በሥሩ ያለው የጸጥታው ምክር ቤት ሃገራትን በእኩል ዐይን ያለማየትና አድሏዊ አሠራር ለዓላማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም አሁን ላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እያራመዱ ያሉት አቋም ግን ድርጅቶቹ ከምንጊዜውም በላይ በግልጽ ከዓላማቸውና ከመተዳደሪያ ቻርተራቸው በተቃራኒው መቆማቸውን የሚያሳይ መሆኑን ዓለም ሁሉ እየመሰከረው ይገኛል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ በግልጽ አፈርስሻለሁ ብሎ ከተነሳ ጠላትና በመከላከያ ሠራዊቷ ላይ በይፋ ዘግናኝ ጥቃትን ከፈጸመ አሸባሪ ኃይል ጋር ራሷን ለመከላከልና እንደ ሃገር ሆኖ ለመቀጠል ህልውናዋን ለማረጋገጥ ተገድዳ ከገባችበት የፍትህ ጦርነት ጊዜ ጀምሮ የፀጥታው ምክር ቤት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ስምንት ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጉባኤ መቀመጡ ነው፡፡
እንደሚታወቀው የጸጥታው ምክር ቤት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት ውስጥ ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን የማድረግ ዓላማ ይዞ የተቋቋመ አካል ነው፡፡ ተቀዳሚ ተግባሩም የእያንዳንዱ አባል አገራትና በአጠቃላይ የዓለምን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ከዚህም በአሻገር ምክር ቤቱ በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት እንደማይችል በመተዳደሪያ ቻርተሩ በግልጽ አስቀምጧል፡፡
ይሁን እንጂ ኃያላኑ አባሎቹ በመተዳደሪያ ቻርተሩ የተቀመጠውን በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ያለመግባት ህግ ጥሰው ያውም አማፅያንን ደግፈው ሶሪያን ሲያወድሙ የፀጥታው ምክር ቤት አንድም ጉባኤ አልጠራም፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በኃያላኑ ህገ ወጥ የጉልበት ጣልቃ ገብነት የመን ወደ ፍርስራሽነት ስትቀየር ዜጎቿ በግፍ ሲያልቁ፣ የቀሩት በዓለም ላይ እንደ ጨው ሲበተኑ፣ ሊቢያ የእርስ እርስ ጦርነት አውድማ ስትሆን፣ ንጹሐን በጥይት በጅምላ ሲያልቁ፣ ሰብዓዊ ፍጡራን ሲሰቃዩ የፀጥታው ምክር ቤት የት ነበረ? ሴቭ ዘ-ችልድረን የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ሰብዓዊ የተራድኦ ድርጅት በሶሪያ ለሰው ልጆች የተሻለ ህይወትን የመፍጠር ዓላማ ያላቸው ሰብዓዊ ተቋማት ትምህርት ቤቶች የሰው ልጆች የማሰቃያ ማዕከላት መሆናቸውንና፤ ህጻናትና ልጆች ለጦርነት ኢላማ መለማመጃ መሆናቸውን የሚያሳይ በማስረጃ የተደገፈ ዘገባ ይዞ፤ “እባካችሁ በእነዚህ ልጆች ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው ስቃይና በአጠቃላይ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለው ዘግናኝ እውነታ እንዲያበቃ ኃላፊታችሁን ተወጡ” ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የፀጥታው ምክር ቤትን ሲማፀን የት ነበራችሁ?
የፀጥታው ምክር ቤትስ ስንት ጊዜስ ጉባኤ ጠርቶ ተቀመጠ? እንዲያውስ በአገራቱ ሰላምና ደህንነት እንዲመለስና የሕዝብ ስቃይና መከራ እንዲያበቃ በመደበኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት አባል አገራት በተደጋጋሚ የፀጥታው ምክር ቤትን ሲጠይቁ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ አልቀረምን? በተቃራኒው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የፀጥታው ምክር ቤት ሾፋሪያቸውን አሜሪካን ተከትለው በኢራን የኑክሌር መርሀ ግብር ላይ ሲጮሁ ዓለም ያላያቸውና ያልሰማቸው ይመስላቸዋልን?
ታዲያ ለኢትዮጵያ ሲሆን ፍጹም በማይመለከተው ጉዳይ ላይ ያውም የራሱን መተዳደሪያ ቻርተር በግልጽ ጥሶ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ስምንት ጊዜ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ መሰብሰብን ምን አመጣው? ምክንያቱም በግልጽ በቻርተሩ እንዳስቀመጠውም ምክር ቤቱ ጉባኤ የሚጠራው በሁለት አገራት መካከል ጦርነት ሲካሄድና አስከፊ ድንበር ዘለል ግጭት ሲከሰት ብሎም ግጭቱ ከአገራቱ ቁጥጥር ውጭ ወጥተው ለዓለም ፀጥታና ደህንነት ስጋት ሲሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ስንመለከተው ኢትዮጵያ አሁን ከአሸባሪውና ሀገር አፍራሹ ህወሓት ጋር የገባችበት ጦርነት በመጀመሪያ የህልውና ነው፤ ሲቀጥል ጦርነቱ ከሌላ የውጭ ወራሪ ወይም ሀገር ጋር ሳይሆን ከራሷ የውስጥ ባንዳ ጋር ነው፤ እናም የውስጥ ጉዳይዋ ነው፣ ሲሰልስ ደግሞ ችግሩ ከቁጥጥሯ ውጭ አልወጣም ፣ አይደለምና ለዓለም ለጎረቤት ሀገራት ጸጥታና ደህንነት ስጋትም አልሆነም፡፡
እናም የፀጥታው ምክር ቤት ምንም በማይመለከተው የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሺህ ጊዜ ጉባኤ የሚቀመጥበት ምክንያት አንድና አንድ ነው፤ እርሱም በሌሎች አገራት ላይ እንደለመደው የአዛዦቹን የአሜሪካና የምዕራባውንን ጥቅም በኢትዮጵያም ላይ ለማስፈጸም ነው፡፡ ሆኖም ይህ ፈጽሞ የማይሆንና መቸም ሊሳካ የማይችል፤ ምዕራባውያን ውድቀትን ሊያመጣ የሚችል በራስ ላይ የተጠመደ አጉል ድርጊት ነው፡፡
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013