የአንድ አገር ኢኮኖሚ ብቻውን የሚቆም እንዳልሆነና ከማህበራዊ ና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ እምነትም፣ ኢኮኖሚ በተለይ ከፖለቲካ ስክነት ጋር ጠንካራ ቁርኝት አለው፡፡ ፖለቲካው ካልተረጋጋ ኢኮኖሚው ይረበሻል፡፡
በተለይ በግጭትና በጦርነት ወቅት የአገር ኢኮኖሚ ጤና በህገወጦች ይታወካል፡፡‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› እንደሚባለው፣ ሰላም ጠፍቶ አገር በጦርነት ላይ ስትሆን በተለይ የኢኮኖሚ አሻጥር በመጠንም ሆነ በአይነት በእጅጉ ይበራከታል፡፡በተለይ የቁጥጥር ስርአት ላልቶ በሚስተዋልበት ወቅት እድሉን በመጠቀም በአቋራጭ ለመክበር የሚደረግ ሩጫ ይበልጥ ይንሰራፋል፡፡
ለግል ጥቅም ባሻገር ከኢኮኖሚ አሻጥር ከፖለቲካ ወገንተኝነት ጋር ይዛመዳል፡፡ በዚህ ተግባር ለሚሰማሩ አካላት በተለይ ጦርነት ማለት ቃታ መሳብና ቦንብ መወርወር ብቻ አይደለም፡፡ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በመረጃ ዘርፍ ከፍተኛ አሻጥር ብሎም ተጽእኖ መፍጠር ነው፡፡
በአሁን ኢትዮጵያ እንዳለችበት ሁኔታ ማለት ነው ፤ ብዙ የኢኮኖሚ አሻጥሮች እየተመለከትን እንገኛለን፡፡በአሁን ወቅትም መሰል ተፅእኖ በማድረግ ዋናው የመንግስት ተልእኮ እንዳይሳካ የሚያደርጉ እና ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች አሉ፡፡ በኢኮኖሚ አሻጥሩ ተዋናዮች ስር የነበሩና በርካታ የተደበቁ እቃዎች፣ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ የተከማቹ የውጭ አገራት ገንዘቦችና ለተለያዩ አላማዎች ሊውሉ የሚችሉ ቁሳቁሶች እየተያዙና እየተጋለጡ መሆኑን ለዚህ ማስረጃ ሆነው መቅረብ የሚችሉ ናቸው፡፡
ከቀናት በፊት ነሐሴ24 በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ ወረዳ 7 ለግንባታ አገልግሎት ሊውሉ የሚገባቸው ለረጅም ጊዜ ህገ-ወጥ በሆነ መልኩ የተከማቹና የተለያየ አይነትና መጠን ያላቸው በወቅቱ በገበያ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ሚና ይኖራቸው የነበረ የብረታ ብረቶች ክምችት የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተዋቀረው ግብረ ኃይል ከተደበቁበት መገኘታቸውም አንዱ ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡
ከምርት ስወራና ማጭበርበር ባሻገር የተጋነነ ዋጋ ጭማሪም የኢኮኖሚ አሻጥሩ ሌላኛው ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል ፡፡ በአሁን ወቅት ለሚስተዋለው የዋጋ ግሽበቱ የተለያዩ ምክንያት የሚዘረዘሩ ቢኖርም የኢኮኖሚ አሻጥር ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ አገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ላይ ሳይቀር ከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ እየታየ መሆኑም ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገለጻም፣አገር በጦርነት ውስጥ በምትሆንበት ወቅት ክፍተቱን የሚጠቀሙ ሃይሎችም በአቋራጭ ለመክበር ምርቶችን ይደብቃሉ፡፡ ዋጋ ይጨምራሉ፡፡ አቅርቦቱ እያለ መንገድ ተስተጋጉላል ፣ተዘግቷል፣የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ የሚሉና ሌሎች ምክንያቶችን በመደርደር አሻጥር ይሰራሉ ።
በሚቀጥለው ወር ምርት ላይመጣ ይችላል። ለአብነትም ጤፍ ላይገባ ይችላል፡፡ ባቄላ የለም፡፡ ምስር አይኖርም እያሉ ሰዎች ላይ ስጋት በመፍጠር በነቂስ ወጥቶ ያገኘውን በተጠየቀው ዋጋ እና በብዛት እንዲገዛ ያደረጋሉ፡፡ የዚህ አይነቱ ተግባር ዋነኛ አላማም ሰው ሰራሽ ግሽበት መፍጠር ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ደኑም ‹‹በተለይ በግጭትና በጦርነት ወቅት የኢኮኖሚ አሻጥር በመጠንም ሆነ በአይነት ይበራከታል›› በሚለው እሳቤ ከሚስማሙ ምሁራን አንዱ ናቸው፡፡ የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ‹‹ ምክንያቱ ደግሞ ጠንከር ያለ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ሊቀንስና የመንግስትም ሆነ የህዝቡ ትኩረት ወደ ግጭቱ ስለሚሆን ብሎም ሊያመዝን ስለሚችል ነው›› ይላሉ፡፡
በተለይ በዚህ ወቅትም የአገርን የኢኮኖሚ ደህንነት እንቅስቃሴ በልዩ ትኩረት መከታተል እና መጠበቅ፣ተፅእኖው ለመቋቋም ፤ ግጭት ቢኖር እንኳን የአገርን የኢኮኖሚ ደህንነት እንቅስቃሴ ለአንድ አፍታም ሳይዘናጉ መከታተል እና መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አፅእኖት ይሰጡታል፡፡
‹‹በአሁን ወቅት መንግስት የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመከላከል ረገድ የተለያዩ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ ነው ብዬ አምናለሁ››የሚሉት ዶክተር ብርሃኑ ፤ በዚህም በርካታ የተደበቁ እቃዎች፣ ገንዘቦችና ለተለያዩ አላማዎች ሊውሉ የሚችሉ ቁሳቁሶች እየተያዙና እየተጋለጡ መሆኑን ማስታወስ በቂ ምስክር እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡ነገር ግን ይህከብዙ በጥቂቱ የተደረሰበት ሊሆን ስለሚችል ይበልጥ መስራት የግድ እንደሚልም ያስገነዝባሉ፡፡
ሰዎች ገንዘባቸውን በሚያንቀሳቅሱበት ጊዜ በባንክ እንዲሆን መደረጉም ህገወጥነትን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አቅም እንደፈጠረ የሚገልፁት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ፣ በዚህ ወሳኝ ወቅትም በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ በተለይም በፋይናንስ ተቋማት ላይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባም ነው ያሰመሩበት፡፡ በተለይ ተመሳሳይ የገንዘብ ኖት እንዳይሰራጭ በፋይናንስ ደህንነት በኩል ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የግድ ይላል ነው ያሉት፡፡
ወንጀሉን በመከላከል እና በመቆጣጠር ሂደት በጉምሩክ፣ በፀጥታ አካላት እና በኢኮኖሚ ደህንነት በኩል ጥብቅ ክትትል ሊደረግበት ይገባል፡፡ በግምገማ እና በክትትል በመለየት ለመቋቋም የሚያስችሉ ስልቶችን ማዘጋጀት የግድ ይላል፡፡ ይህን ማድረግም ችግሮች የከፋ ጉዳት ሳይስከትሉ ለማስቀረት አቅም አንደሚፈጥር ይገልፃሉ ፡፡
እንደ ዶክተር ብርሀኑ ገለፃም፤ መንግስት የኢኮኖሚ አሻጥሩን ለመቆጠጠር እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው ህዝብም በግልፅነት የራሱን ጥቅም አገር ለመጠበቅ መትጋት አለበት፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የተከማቹ ለምሳሌ ዘይት፣ እህል፣ ብረት እና ሌሎችንም ምርቶች ተከማችቶ ሲመለከት ለምን ብሎ በመጠየቅ ማጋለጥና መጠቆም ይኖርበታል፡፡የግድ ፖሊስ በአሰሳ እስኪደርስበት ጊዜ መጠበቅ አይገባም ፡፡
ህገወጥ የሆኑ ነገሮችን ሲመለከቱ ምንድ ነው ብሎ የሚጠይቅና የሚጠቁም ህዝብ መኖር አለበት። የፀጥታ አካላት ብቻቸውን ሁሉን ሊቆጣጠሩ አይችሉም፡፡ ህዝብ የመከላከልና የጥቆማው ተሳታፊ ከሆነ እና ጥፋት ሲገኝ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ተባባሪ መሆን ከቻለ ለፀጥታ አካላት ስራ በእጅጉ እንደሚያቀል መረዳት ይኖርበታል፡፡
የዋጋ ግሽበቱን በማስተካከልና በመከላከል ረገድም በጠንካራ አመራር ስር ያሉ ሸማቾች ማደራጀትና መሰረታዊ የሆኑ እቃዎችን ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ የግድ እንደሚል የሚያስገነዝቡት ዶክተር ብርሃኑ፣አሁን አገሪቱ ባለችበት የኢኮኖሚ ችግር ብዙ ምርቶችን ከውጭ ማስገባት አዋጪ ላይሆን ይችላል፡፡
ሙሉ በሙሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መዝጋት አይቻልም፡፡ይሁንና ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው፣ እጅግ በጣም አስፈላጊ እና መሰረታዊ የሆኑትን መለየት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚገቡበትን ሁኔታ መፈጠር ያስፈልጋል፡፡
የዋጋ ግሽበትን ለማስተካካል በተለይ ሸማቹ ህብረተሰብ እንዳይጎዳ መንግስት ጠንካራ የቁጥጥር ሁኔታ መኖር እና መከታታል አለበት፡፡ ለምን ክትትል ይደረጋል የምንከተለው ነፃ ገበያ ነው የሚል ቅሬታ ሊነሳ ይችላል፡፡መሰል ቅሬታ በተለይ ጦርነት እና የግጭት ጊዜ ጤናማ ያልሆነ ነው፡፡
ኢኮኖሚ አሻጥር በተለይ በጦርነት ወቅት ይበልጥ እንደሚንሰራፋ ከማይጠራጠሩ ምሁራን መካከልም የህግ ባለሙያው ኪያ ፀጋዬም አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ኪያ፣የኢኮኖሚ አሻጥሩ በተለይ መሰረታዊ ሸቀጦችና ምርቶች ላይ ሰው ሰራሽ ዋጋ ንረት በመፍጠር በአገር ላይ ኢኮኖሚ ቀውስ እንዲፈጠርና ይሕን ተከትሎም የፖለቲካ ምስቅልቅል እንዲከሰት ማድረግን አላማው ያደረገ መሆኑን ይስማሙበታል፡፡
‹‹በተለይ ኢትዮጵያ አሁን እንዳለችበት ወቅታዊ የጦርነት ሁኔታ ኢኮኖሚ አሻጥር ዋነኛ አላማ ና ግብ በፖለቲካ ውግንና ግንባር ሳይሄድ ከተማ ላይ ቁጭ ብሎ ኢኮሚያዊ ጫና ብሎም ቀውስ በመፍጠር ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ማድረግ ነው››ይላሉ።
በአሁን ወቅትም የአሸባሪው ቡድን ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸውና ደጋፊ የሆኑ እንዲሁም በስግብግብ ነጋዴዎች በከፍተኛ መጠን ተከማችተው ብሎም ተደብቀው የሚገኙ ምርቶች መገኘት፣ የጥቁር ገበያ መበራከት፣ ህገ ወጥ የገንዘብ በተለይ የወጭ አገራት ገንዘቦች ዝውውር ተሳታፊች የአኮኖሚ አሻጥሩ ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስ እንደሚችልም ይጠቁማሉ፡፡
ይህን ጦርነት እንደ አጋጣሚ ተጠቅሞ የፖለቲካ ድጋፉን ለማሳየትና ትርፍ ለማግበስበስ የሚራወጥ ስለመኖሩ የሚጠቁሙት አቶ ኪያ፣ በተለይም‹‹ኢትዮጵያ የምትከተለው ነፃ ገበያ ነው በሚል የምርት ዋጋን ለመጨመር መራወጥ ፈፅሞ ተቀባይነት እንደሌለው ያስገነዝባሉ፡፡
‹‹ማንም እየተነሳ የሸቀጣ ሸቀጥ እና ምርቶችን ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመር የነፃ ገበያ መገለጫ ሊሆን አይችልም››የሚሉት አቶ ኪያ፣በበለፀጉት ጨምሮ በተለያዩ አገራትን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመንግስት ቁጥጥርና ገደብ የሚደረግበት መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡
ሆን ብሎ ምርቶችን ሰብስቦና አከማችቶ ነገ ከነገ ወዲያ ዋጋ ሊጨምርልኝ ይችላል በሚል በመጋዘን ማከማቸው በህግ የተከለከለ እንደሆነ እና በአስተዳደራዊም ሆነ በወንጀል እንደሚያስቀጣ መሆኑን የሚያስገነዝቡት የህግ ባለሙያው፣በዚህ ወቅት መሰል ኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀም በኢትዮጵያ ላይ ከባድ ጦርነት እንደመክፈት ሊታይ የሚችል ስለመሆኑም አፅእኖት ሰጥተው ይናገራሉ ፡፡
‹‹መንግስት የኢኮኖሚ አሻጥሩን በመከላከል ረገድ በሰራ ላይ የሚያገኛቸው ተግባራት ጥሩ የሚባሉና የሚያስመሰግኑ ናቸው››የሚሉት አቶ ኪያ፣እርምጃውን ተከትሎም ህገ ወጥ ተግባር እና ወንጀሉ ለመፈፀም የሚያስቡ ካሉ ቆም ብለው መንገዳቸውን እንዲያስተካክሉ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ነው የገለፁት፡፡ ገበያውን ከማረጋጋት አንፃርም ትልቅ ሚና እንዳለውም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
ይህ ሁኔታም ልዩ የሆነ ትብብር ይጠይቃል። ነጋዴውም ትርፍ የሚኖረው ሰላም እና አገር ሲኖር መሆኑን ጠንቅቀው ሊረዱት ይገባል፡፡መንግስት ውስጥ የተሰገሰጉና የችግሩ ተባባሪ የሆኑ አንዳንድ አካላትን በመከታተል ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
አላግባብ የሆነ ዋጋ ጭማሬ፣በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ መጋዘኖች አጠራጣሪ እና ህገ ወጥ የሆኑ የምርት ክምችቶችን ሲያስተውል ጥቆማ መስጠትና መንግስት ፈጣን ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ በተዋናዮቹ ላይ በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎች ህብረተሰቡ በግልፅ እንዲያውቃቸው በመገናኛ ብዙሀን ሊታዩ ይገባል፡፡
ይህም በኢኮኖሚ አሻጥሩ ለመሳተፍ ሃሳቡ ላላቸው ተገቢን የማስጠንቀቂያ መልእክት እንደሚያስተላላፍ ያመላከቱት አቶ ኪያ፣ የኢኮኖሚ አሻጥር ወንጀሉን መቆጣጠርና በመከላከል ረገድ በሚከናወኑ ተግባራት ህጋዊ የሆኑ ነጋዴዎችና ኢንቨስተሮች በዚህ መሃል ተጎጂ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግና በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበትም ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013