አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ሲያሻው በሰብዓዊ ጋሻነት ፤ ለመደራደሪያነት በማገት ፤ ሌላ ጊዜ ነፍስ የማያውቁ ህጻናትን ከጉያው እየነጠለ በሕዝባዊ ማዕበል በጦርነት በመማገድ ፤ በስሙ የሚላክለትን እርዳታ በመሸጥና ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲል እንዳይደርሰው መንገድ በመዝጋትና ድልድይ በማፍረስ በርሀብ እንደ ቅጠል እንዲረግፍ በማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመበት ይገኛል ። የዚህ የሽብር ቡድን የኋላ ታሪኩ ሲፈተሽም ርሃብን እንደጦር መሳሪያ የሚጠቀምና በሺዎች ህልፈት ላይ ማንነቱን ማቆም የሚሻ እኩይ ቡድን ነው፡፡
ገና ከምስረታው እንደሱ የደርግን ወታደራዊ አገዛዝ ለመታገል ጫካ የገቡትን ኢህአፓ ፣ ኢዲዩና የትግራይ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንደራደር ፣ በሚል ሰበብ በጅምላ ወጣቶችን የጨረሰ አረመኔና የዘር አጥፊ ስብስብ ነው። እነ ስሁልን ፣ ሙሴን ፣ ዩሐንስ ገ/መድህን/ዋልታ/ ሀይሎምንና ሌሎቹ በሀሳብ የተለዩትን እልፍ አእላፍ ታጋዮችንና ልጆቹን እንደ ድመት የበላ ፤ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም በሰሜን እዝ ፣ በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የፈጸመ ፤ በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ እንደፈጸመው ክህደት ከጀርባ ወግቶ ወይም በጥይት ደብድቦ በርካቶችን የገደለ ማህበረሰብንና ዘርን የጨረሰ ነቀርሳ ነው። ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም ሲል የሀውዜንን ሕዝብ በገበያ ቀን በአውሮፕላን አስፈጅቶ ሙሾ የሚያወርድና የአዞ እንባ የሚያነባ የሀፍረተቢሶች ስብስብ ነው ። በ1977 ድርቅ ለትግራይ ሕዝብ የተላከ እርዳታን ሽጦ የጦር መሳሪያ የገዛ ትግራዋይን በርሀብ የጨረሰ ለፖለቲካዊ ቁማር ምንም ከማድረግ የማይመለስ ቡድን ነው።
አሸባሪው ህወሓት በ1977 የነበረውን ድርቅ ለፖለቲካ ፍላጎቱ ማስፈጸሚያ አድርጎት እንደነበር በወቅቱ የህሓት የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ ገብረ መድህን አርአያ ያስረዳሉ “በ1977 በትግራይ የደረሰውን አስከፊ ድርቅ ተከትሎ በለጋሽ አገራት እና ህዝቦች ዘንድ ለነብስ አድንት ተብሎ የተላከውን እርጥባን የህወሓት አመራር በጥሬ ገንዘብ የመጣውን በቀጥታ ወደግል ካዝናቸው በአይነት የተለገሰውን ደግሞ በሱዳን ገበያ በመቸብቸብ ለትጥቅ መግዣ እና ለግል ሃብት አዋሉት:: እርዳታ ተላከለት የተባለው ምስኪን ህዝብም በየበረሃው ወድቆ ረገፈ:: ለመለመኛ ለታሰበ ድራማ ወደሱዳን እንዲሰደድ በህወሓት የታዘዘው ረሃብተኛም በየመንዱ ቀረ:: የትግራይ ህዝብም ታሪክ ሊረሳው የማይገባው ታላቅ ክህደት ከአብራኩ ወጣሁ በሚሉ ከሃዲዎች ተፈጸመበት::”ሲሉ አሳዛኙን ታሪክ እማኝ ሆነው ያስረዳሉ፡፡
ህውሓት ከ1977ዓ.ም ድርቅ በፊት መኖሩ የማይታወቅና የሽፍታነት ባህሪ የነበረው ቡድን ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሰሞኑን ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅም እንዳስታወሱት፤ ህውሓት ከድርቁ በፊት መኖሩ በአግባቡ የማይታወቅና አንዲትም መሬት ተዋግቶ ያልያዘ ቡድን ነበር፡፡ ሆኖም በግብረሰናይ ድርጅት ስም ከሚንቀሳቀሱና በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለመጫን ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር በመመሳጠር ስንዴ ሸጦ መሳሪያ በመግዛት ኃይሉን ማጠናከር ችሏል፡፡ በምዕራባውያንና በረድኤት ድርጅቶቻቸው በመታገዝም የደርግ መንግስትን ገዝግዘው ለመጣል በቅተዋል፡፡
አቶ ገብረ መድህን አርአያ እንደሚናገሩትም፤ ምዕራባውያንና በረድኤት ስም የገቡ የስለላ ድርጅቶቻቸው ባደረጉለት ድጋፍም በ1981ዓ.ም ደርግ ትግራይን ለቆ እንደወጣ ህወሓት ካለምንም ችግር በሩ የተከፈተ ቤት በማግኘቱ ሰተት ብሎ መሃል ትግራይ ገባ:: ገብቶም አላረፈም:: በየከተማው ይኖሩ የነበሩ መምህራንን እንዲሁም የመንግስት ተቀጣሪ ዜጎችን ጠላት ብሎ በደርግ ደጋፊነት በመወንጀል ለቅሞ እንደፈጃቸው እማኝ ሆነው ያስረዳሉ፡፡
ብዙዎች እንደሚያምኑት ምዕራብያውንና በረድኤት ስም ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የረድኤት ድርጅቶቻቸው ባይኖሩ ህወሓት እንኳን ደርግን አሸንፎ ሀገር ሊመራ ይቅርና በአንድ አውደ ውጊያም ቢሆን የማሸነፍ ብቃት አልነበረውም፡፡ ሆኖም ግን በምዕራባውያንና በእርዳታ ድርጅቶቻቸው አራት ኪሎ ቤተ መንግስት በመግባት ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት በጨካኝ መዳፉ ሲያስተዳድራት ቆይቷል፡፡
ይህ ቡድን ከፌዴራል መንግስቱ በህዝብና በለውጥ ሀይሉ ተገፍቶ ወደ መቀሌ ሲሸሽ ከስህተቱ የሚማርበትና ሰክኖ የሚያስብበት ዕድል ተሰጥቶት ነበር። ሆኖም የተሰጠውን ዕድል ሊጠቀምበት አልቻለም። ‹‹የበላይነት የለመደ እኩል ሁን ስትለው ያኮርፋል›› እንዲሉ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ወደ ባሰ ጥፋት ሊሸጋገር ችሏል፡፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ ሁሉ ይህ ቡድንም እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ ትበታተን በሚል ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዘርና ሀይማኖት ተኮር ግጭቶችን ሲጠምቅና ሲያቀጣጥል ቆይቷል፡፡ ቡድኑ ከዚህ እኩይ ተግባሩ እንዲታቀብና ችግሮችም ካሉ በውይይት ለመፍታት በፌዴራል መንግስት በኩል በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። በሀይማኖት አባቶች፣በዲፕሎማቶች፣በታዋቂ ሰዎችና በአገር ሽማግሌዎች በኩል ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረጉት ጥረቶች በአሸባሪው ህወሓት ለስሜቱ በመገዛቱና ለራሱ የተሳሳተ ግምት በመስጠቱ ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡
ቡድኑ ያሰባው ግብ ሳይሳካለትና ግጨቶቹም እየመከኑ ሲሄዱበት ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ጥቅምት 24 ቀን 2013ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከፍቷል፡፡ይህ ውለታ የማይገባውና ከስህተቱ የማይማረው ቡድን ጥቃት የከፈተባቸው የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የትግራይ ህዝብ ለ20 ዓመታት በምሽግ ውስጥ ሆነው ሲጠበቁ የነበሩ ናቸው፡፡ በዚህ ጨካኝ ተግባሩም ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ጡታቸውን በመቁረጥ በታንክ ጨፍልቋል፡፡የአርሶ አደሩን ሰብል ሲሰበስብ የዋሉትን የሰራዊት አባላት ተኩስ ከፍቶ ብዙዎቹን ረሽኗል፡፡ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ድግሞ ሊነገር የማይችል ስቃይና ግፍ ፈጸሞባቸዋል፡፡
በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የከፈተው ሽብተኛ ቡድን በዚህ ብቻ ሳይወሰን ከአማራ ህዝብ ጋር ሂሳብ አወራርዳለሁ በሚል ንጹሃንን በግፍ ፈጅቷል።በአፋር ጋሊኮማ ከ250 በላይ ንጹሃንን ፈጅቷል። የእርዳታ መጋዘኖችንም በማቃጠል በነፍስ የተረፈው ዜጋ በርሃብ አለንጋ እንዲቀጣ አድርጓል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፤ የአውሮፓ ህብረት ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ቢሮዎች እና ሌሎች ኤጀንሲዎች በትግራይ ተከሰተ ስላሉት ረሀብ ፤ የንጹሀን ሞት ፤ አስገድዶ መድፈር ፤ የእርዳታ መንገድ መስተጓጎል ወዘተ…ቀን በቀን ሪፖርት እና መግለጫ ሲያወጡ ከርመዋል፡፡ አብዛኞቹ መግለጫ የሚያወጡባቸው ጉዳዮች መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሀቅን ያላገናዘቡ እና የአንድ ወገን ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ መግለጫዎች አለቅጥ በተጋነኑ ጥቃቅን እውነቶች እና ሀሰተኛ ድምዳሜዎች የተሞሉ ሲሆን የሆነ አይነት አላማን ለማሳካት ያቀዱ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም በተደጋጋሚ እነዚህ ተቋማት የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ፖለቲካዊ አላማ ያላቸው እንደሆነ ሲያሳስብ ከርሟል፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ጉዳይን እንደ ግል ጉዳያቸው አስመስለው የያዙ ተቋማት ታዲያ አሸባሪው ህውሓት የሚፈጽማቸውን ነውረኛ ተግባራት በማንቆለጳጰስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለአቅመ ጦርነት ቀርቶ ለአቅመ አዳም እና አቅም ሄዋን ያልደረሱ ህጻናት በጦር ሜዳ መሳሪያ ታጥቀው ሲታዩ እስካሁን መግለጫ ሲጽፉበት የከረሙበት ብእር ቀለሙ ያለቀ ይመስል ዝምታን መርጠዋል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ፤ የአውሮፓ ህብረት ፤ ብሪታንያ ፤ አምነስቲ ኢንተርናሽና ፤ ተመድ እና ሌሎችም እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ አንድም ያሉት ነገር የለም፡፡ ምናልባትም ከህጻናቱ ጦርሜዳ ላይ መገኘት ይልቅ የዚህ ፎቶ ሾልኮ መውጣት ሳያናድዳቸው አልቀረም፡፡ወይም ይህን ያህል ጊዜ የወሰዱት እንዲህ አይነቱን ነውር በምን አይነት መልኩ ምክንያታዊ ማድረግ እንደሚችሉ እየተመካከሩ ሊሆን ይችላል፡፡ሁኔታው ግን ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ሌሎች አካላት እነዚህ ተቋማት ገለልተኝነት እና የሞራል ከፍታ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ የሚያሰፋ ነው፡፡
ሆኖም ሰሞኑን በዩኤስ ኤድ ላይ ህወሓት የፈጸመው ዘረፋ ወንጀልን ግን መደበቅ አልተቻለም፡፡ የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት ዩኤስ ኤድ አሸባሪው ህወሓት የምግብ እርዳታ እና ቁሳቁሶችን እየዘረፈ መሆኑን በኃላፊው አማካኝነት ግልጽ አድርጓል፡፡ ‹‹ሰርገው በገቡባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች የእርዳታ መጋዘኖችን ዘርፈዋል፣ ንብረትም አውድመዋል›› ሲልም ከሷል፡፡
የዩኤስ ኤድ ሚሽን ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ሾን ጆንስ እንዳብራሩት፤ ህወሓት የዩኤስ ኤድን የእርዳታ ንብረቶች እና ቁሳቁሶችም መዝረፉን ማመናቸውን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት ድርጅታቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የተፈናቃዮች እና የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች በቅን ልቦና እያገዘ ይገኛል። ‹‹ ህወሓት ሁኔታውን ያለአግባብ እየተጠቀመበት እንደሆነ እናምናለን ፡፡ ከተረጂዎች ላይ በሃይል እርዳታዎችን እየነጠቀ እንደሆነ ይሰማናል፡፡ እርግጠኛ ሁነን መናገር የምንችለው ግን ሰርገው በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ ያሉትን የእርዳታ መጋዘኖቻችንን ዘርፈዋል፡፡ ይህ የምናውቀው ሃቅ ነው፡፡ የህወሓት ወታደሮች ሰርገው በገቡባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ጥፋት በማድረሳቸው የእርዳታ ሂደቱን በከፍተኛ ሁኔታ እያወኩ ይገኛሉ፡፡አሁን በግልፅ የምናውቀው ነገር ቢኖር የህወሓት ወታደሮች በገቡባቸው የአማራ ክልሎች በሙሉ የእርዳታ መካዘኖችን ዘርፈዋል፡፡ መኪኖችን ሰርቀዋል። በየመንደሮቹ ብዙ ውድመቶችን አድርሰዋል፡፡ ይህ ለተጎጂዎችም ሆነ ለእኛ ለረጂ ድርጅቶች እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ››ሲሉ የአሸባሪውን ህወሓት ዘራፊነት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ አድርገዋል፡፡
ለዩኤስ ኤድ ሚሽን ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ሾን ጆንስ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ መንግስት በተደጋገሚ ህወሓት የእርዳታ ድርጅት መካዘኖች እየዘረፉ ነው የሚል ክስ ሲያሰማ ለምን ዝም አላችሁ? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ ‹‹ዝም ያልነው ከመንግስት ሃሳብ ጋር ስለምንቃረን አልነበረም። አሜሪካ በሁሉም ጉዳይ ላይ ሃሳብ የመስጠት ወይንም መግለጫ የማውጣት ልምድ የላትም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በጥርጣሬዎች እና ባልተጨበጡ ወሬዎች ላይ አስተያየት አንሰጥም፡፡ ስጋታችንን የምንገልጸው ተጨባጭ መረጃ ሲኖረን ነው፡፡ አሁን ይህን የምናደርገው የህወሓት ወታደሮች መጋዘኖቻችንን እንደዘረፉ በግልፅ ስለምናውቅ ነው፡፡››የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በአጠቃላይ ዩኤስ ኤድ ሚሽን ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ሾን ጆንስ የህወሓትን ዘራፊነት በዚህ መልኩ ማብራራታቸው አሸባሪው ህወሓት በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በአሳፋሪ ድርጊቱ የበለጠ እንዲታወቅ የሚያደርገው ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን ከቡድኑ ምስረታ ጀምሮ ይህንን ሃቅ በአግባቡ የሚያውቁት ነው፡፡አሸባሪው ህወሓት ርሃብን እንደጦር መሳርያ በመጠቀምና ዝርፊያን እንደህልውና ማቆያ በመገልገል ዛሬ ላይ ደርሷል።ሰርጎ በገባባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ሊጥና ወጥ ሳይቀር በመስረቅ ነውረኛነቱን አሳይቷል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 አመታት የሀገሪቱን ሃብት በመዝረፍ ለራሱ ጥቅም አውሏል፡፡ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከሀገሪቱ በማሸሽ ኢትዮጵያ በእዳ እንድትዘፈቅ አድርጓል፡፡ ተማሪዎችና ጉልት ነጋዴዎች ሳይቀሩ ከዕለት ጉርሳቸው ቆጥበው ለህዳሴ ግድብ ያዋጡትን ገንዘብ ሰርቆ ኪሱ ያስገባ ነውረኛ ቡድን ነው፡፡ ሜቴክ የተሰኘ የዘረፋ ተቋም በመመስረት ተቋማዊ የሆነ የዘረፋ ስንሰለት ዘርግቶ የኢትዮጵያን ሃብት ሲመዘበር ኖሯል፡፡
ቡድኑ ሀገር ሲያስተዳድር ቆየባቸው አመታት መንግስታዊ ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረግ ሙስናና ሌብነት እንዲንሰራፋ አድርጎ ቆይቷል፡፡ በተለይም ሃብት ያላቸው ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ የእኔ ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን አባላቱን በህቡዕ እንዲዘርፉና ሃብት እንዲያከማቹ ሲያደርግ ኖሯል፡፡ አርሶ አደሮችን ከመሬታቸው በማፈናቀልም መሬትን እንደቆሎ በመቸርቸር የዘረፋ ጥሙን ሲያረካ ቆይቷል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚመረቱና በውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በግለሰቦች ቁጥጥር ስር በማድረግ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በግለሰቦች ኪስ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ አሸባሪው ህወሓት የዘረፋ ተግባር ከቡድኑ መስረታ ጀምሮ አብሮ የተወለደና ያለዘረፋም ህይወት የሌለው አካል ነው፡፡ ቡድኑ ለእርዳታ የሚመጣ እህልን በመሸጥና የጦር መሳሪያ በመሸመት የደርግን መንግስት ለመገዳደር ከመብቃቱም ባሻገር በርሃብተኞች ውስጥ በመደበቅም ከጥቃት እራሱን በማሸሽ ተረጂ ወገኖችን በጥይት ሲያስበላ የኖረ ጨካኝ ቡድን ነው፡፡ ይህንኑ ተግባሩን በመቀጠልም ዛሬም የትግራይ ህዝብን በሰብአዊ ጋሻነት በመያዝ ህዝቡን በርሃብ አለንጋ በመቅጣት ላይ ይገኛል፡፡ሆኖም የዚህ አረመኔ ቡድን ጸያፍ ድርጊቶች በአለም መድረክ ጸሃይ የሞቃቸው ከመሆናቸውም ባሻገር የኢትዮጵያ ህዝብ ቡድኑን ለመቅበር ከዳር እስከ ዳር የተነሳ በመሆኑ ከነአረመኔ ተግባሩ የሚቀበርበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡
በአሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013