ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በዛሬው ዕለት በኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር መስመር አጠቃቀምን እና ክፍያ ዙሪያ የማዕቀፍ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የተፈራረሙትም ኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ናቸው።
የኦፕቲካል ግራውንድ አገልግሎቱ ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት ስራ ላይ የዋለ ቢሆንም፤ እሰካሁን በሁለቱ ተቋማት መካከል አግልግሎቱን ከማስፋት አኳያ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳች ላይ የሃሳብ ልውውጥ ሲደረግ መቆየቱ ነው የተገለፀው።
በዚህም መሰረት ተቋማቱ አገልግሎቱን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችለውን ስምምነት የተቋሙ ስራ አስፈፃሚዎች እና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የረጅም ጊዜ የማዕቀፍ ውል ስምምነት ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ መሰረትም ኢትዮ ቴሌኮም ኦፕቲካል ግራውንድ ዋየር መስመርን ለዘረጋው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአመት 20 ሚሊየን ብር ይከፍላል ተብሏል፡፡
ይህም ኢትዮ ቴሌኮም በምድር በዘረጋው የፋይበር መስመር ላይ ይደርሱ የነበሩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በመከላከል፥ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ መቆራረጥና የጥራት መጓደል ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ነው የተባለው ።
በተጨማሪም በአገልግሎቱ በቴሌኮም መስመሮች ላይ ብልሽት ሲያጋጥም ዋና ዋና መስመሮች ላይ የአገልግሎት መቆራረጥ ሳያጋጥም ብልሽቶች የሚጠገኑበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል ሲል የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው።