‹‹ስምን መላዕክ›› ያወጣዋል ያሉት እውነት ትክክል ስለመሆኑ ጊዜና አጋጣሚዎች ያሳዩን ጀምረዋል። መጠሪያውን ከዓለማችን ጨካኞች በአንዱ ያደረገው የዘመናችን ፈላስፋ ነኝ ባይ ለዚህ አባባል እማኛችን ይሆናል። ትክክለኛ የመጠሪያ ስሙ ይህ እንዳልሆነ በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ። ከጊዜያት በኋላ ግን ራሱ ባወጣው የዳቦ ስም ‹‹ስታሊን›› ተብሎ መጠራት ጀመረ። ‹‹ስታሊን ገብረስላሴ››
ከታዋቂው ጆሴፍ ስታሊን ቅንጫቢ ታሪኮች አንዷን ሀረግ ስንመዝ ሰውየው ለስልጣን ሲል የትግል አጋሩን ያስገደለ ራስ ወዳድ ስለመሆኑ እንደርስበታለን። ከሩሲያ አብዮት ማግስት የሀገሪቱ የጦር ሚኒስትር የነበረው ‹‹ሊዮ ትሮትስኪ››የጆሴፍ ስታሊን የቅርብ ወዳጅና የትግል አጋር ነበር።
ሁለቱ ወንድማማች ታጋዮች ቀድሞ በሩሲያ የነበረውን ንጉሳዊ ስርዓት ለመገርሰስ ነፍጥ አንስተው ሲታገሉ፣ለዓላማቸው በጽናት ሲዋደቁ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። ከጊዜያት በኋላ በርካታ መስዋዕትነት የተከፈለበት የሩሲያው አብዮት ትግል በነስታሊን አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ከድሉ ማግስትም ቪላድሚር ኤሊች ሌኒን የሀገሪቱ መሪ እንዲሆን ይሁንታን አገኘ። ከሌኒን ሞት በኋላም ስታሊን ወደስልጣን ወጣ። የሀገሪቱ መሪም ሆነ። በሌላ መልኩ ሊዮ ትሮትስኪ የሩሲያ የጦር መሪ መሆኑ ተረጋገጠ።
ይህ ይሆን ዘንድ ውስጡ ያልተቀበለው ስታሊን ግን የትግል አጋሩ ጥንካሬ ስጋት ሆነበት። በዚህ ቂም አርግዞም በምቀኝነት እንዲነድ አስገደደው። የትሮይስኪ አቋምና ማንነት ያስፈራው ዕንቅልፍ ይነሳው ያዘ። ቅናትና ምቀኝነቱ ራሱ ላይ ወጣ። በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱም ከልብ አተከነው።
ስታሊን የትግል አጋሩን የሚያስወግድበትን ዘዴ ጧት ማታ ማብሰልሰል ልምዱ ሆነ። ጥርሱን እያሳየ ከጎኑ እንደቆመ ማስመሰሉ ከጥርጣሬ አልጣለውም። ያሰበው እስኪደርስ፣ ያቀደው እስኪሳካ በይሁንታ ቆየ። አንድ ቀን ስታሊን የስልጣን ሀይሉን ተጠቅሞ ትሮይስኪ ወደ ሜክሲኮ እንዲሄድ ትዕዛዝ ሰጠው።
የመሪውንና የትግል አጋሩን ሀሳብ ያልተቃወመው የጦር መሪ የተባለውን ሊፈጽም ወደ ሜክስኮ አቀና። በስፍራው ሲደርስ ግን የጠበቀው እውነት የሞት ድግስ ሆነ። ትሮይስኪ በስታሊን ቅጥረኞች የታለመ ጥይት ውድ ህይወቱን ተነጠቀ። የሁለቱ ትግል አጋሮች መጨረሻም በስልጣን ናፋቂው ጆሴፍ ስታሊን የተንኮል ወጥመድ በሞት ተደመደመ።
ወደ ዘመናችን ስታሊን ተብዬው ወገኛ እንመለስ። ስሙን በሩሲያዊው አብዮተኛ ጆሴፍ ስታሊን መቀየር የፈለገበትን እውነተኛ ምክንያት ከእሱ ወዲያ የሚያውቀው የለም።
እንገምት ከተባለ ግን የስም አወጣጡና የልቡ ክፋት ወንድሙን ለስልጣን ሲል ከሰዋው ጆሴፍ ስታሊን ጋር በልክ ያመሳስለዋል። እናም ሰውየው በስያሜው አልተሳሳተም። ሰው መሰል እባብ ነውና ስምና ግብሩ በትክክል ሰምሯል። አጀብ! ስም አወጣጥ አወይ ልክ ማወቅ።
ስታሊን ተብዬው ዋሽቶ አደርና ጥቅመኛ ባንዳ ነው። ሁሌም በበላበት የሚጮህ ሶሎግ ውሻ ሆኖም በምላሱ ሲገለጥ ይውላል። ላውራና ልዋሽ ካለ ህሊና ይባልን ጉዳይ አያውቀውም። ሁሌም ያለማስረጃ በሚመዛቸው አሳፋሪ ወሬዎቹ ለአንዲትም ቀን አፍሮና ተሸማቆ አያውቅም።
ለነገሩ ውሸትና አስመሳይነት የአያት ቅድመ አያቶቹ ውርስ ነው። መቼም እናንተዬ ከኋላ ማንነት አሳፋሪ ታሪክን እንደመውረስ የሚያሳቅቅ አይኖርም። ቀድሞ እሱን መሰሎች በባንዳነት አገር ሲሸጡ ፣ወገኖቻቸውን ሲያስፈጁ ኖረዋል።
ስታሊን ተብዬው ልበ ገዳዳም ይህን ማንነቱን ለማስመስከር የማይገባበት ጉድጓድ የለም። ስለቆመበት አገር የማጥፋት ዓላማም የሚሮጥበት አቅጣጫ ጫፍና ጫፍ የለውም። እስከዛሬ ልብወለድ የሚመስሉ የፈጠራ ታሪኮችን በሚዘራበት ማህበራዊ ሚዲያ ብዙዎችን ሲያሳስት ቆይቷል።
ዛሬም ቢሆን በየቀኑ ለሚነዛቸው ሀሰተኛ ትርክቶች ጆሮ ለሰጡ የወሬ ቆሎውን ለማቃም ምላሱ የሰላ ነው። አንዳንዴ ‹‹ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው ይሉትን አባባል የሚያውቀው አይመስልም። ‹‹አልሰሜን ግባ በለው›› አሉ። በየቀኑ ብቅ እያለ በሚደሰኩረው ፍሬ አልባ ጨዋታው ማንም እንደሚዝናናበት ማን በነገረው? መሳቂያ መሳለቂያነቱ ቀጥሏል። ውሸቱ የሳቅ ምንጭ ሆኖም ብዘዎችን ያዝናናል።
ድከም ያለው ሆኖ ዕለት በዕለት መረጃ አልባ መረጃውን ሲነዛ እረፍት ያለው አይመሰልም። ስታሊን ገብረስላሴ የአፉ ማሟሻ የሚያደርጋትን ኢትዮጵያ ውሎ አዳሩን ቢያነሳሳት አይጠግብም። ተወልዶ ባደገባት፣ ተምሮ እንጀራ በቆረሰባት ድንቅ አገር ላይ ያለው ምቀኝነትም በግልጽ ይስተዋላል። ለነገሩ ምን ያድርግ? ኢትዮጵያ በእሱና በመሰሎቹ መጋዝ ጥርስ ተገዝግዛ አላለቀችም። ጅቦቹ ጨርሰን በላናት ሲሉ እንደ አዲስ እየተወለደች ብሽቀት ሆነችባቸው። ታላቅ ብሽቀት።
ይህን እውነት ለማወላገድ ቀጣፊው የሚፈጽማቸው አሳፋሪ ስራዎች ከእሱ ይልቅ ብዙዎችን የሚያሸማቅቅ ሆኗል። እስከዛሬ ከልምዱ እንደታየው ከመናገሩ በፊት ማሰብ ፣ ማሰላሰል ይሉትን ማስተዋል ደርሶበት አያውቅም።
በቅርቡ ‹‹ስሙኝ›› ባለው ገዳዳ ትርክቱ የቀድሞዋን ኢትዮጵያ ከአሁኑዋ እያነጻጸረ ልዩነታቸውን ሊያስቀምጥ ሞክሯል። በእሱ እንጭጭ አዕምሮ የቀድሞዋ ኢትዮጵያ ከአሁኒቷ በእጥፍ ደረጃ የምትሻል ሆናለች።
ለዚህ ትርክቱ የሚያስቀምጠው አንዳች ምክንያት ባይኖርም የአሁናዊውን ዕድገትና ብልጽግና ላለማንሳት ከራሱ ሲጣላ መታየቱ ሁሉንም ያስቃል። እኛም ወገባችንን ይዘን፣ ልባችንን ደግፈን ትን… እስኪለን ስቀንበታል።
ከስታሊን አይቀሬ ልማድ አስገራሚው ደግሞ ሁሌም በማፈሪያ ትርክቱ መሀል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን ሰላም ሳይል አለማለፉ ነው። ንገሩኝ ! ባይ። የትኛው ማንነቱ ይሆን? ከአንድ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ጫማ የሚያለካካው? ‹‹ወጊቲ›› አለች ሴትዬዋ። እውነትም‹‹ ወጊቲ››
ለስታሊን ሁሌም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓለም ዓቀፍ እውቅናና የህዝብ ፍቅር እንዳስቀናው እንዳንገበገበው ነው። ባለችው የምላስ አቅም መልካምነታቸውን ለማጉደፍ የማያጣቅሰው መረጃ የለም። ይህን ሲያስብ ‹‹ሰማዕት›› የሚላቸውን የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍንን ንግግር ያሰማናል።
ከዚሁ አያይዞም ‹‹ዶክተር ዐብይ የስዩምን ምክር ቢሰሙ ኖሮ … ›› እያለ ይተቻል፣ ይወርፋል። ‹‹ጠንቋይ ለራሱ አያውቅ›› እንዲሉ ስለ ኢትዮጵያ መጻኢ ዕድልም አስረግጦ ሊናገርና ሊገምት ይዳዳዋል።
በጣም የሚገርመው ጉዳይ የኢትዮጵያን አቅምና ዕድገት የሚለካበት ሚዛኑ ነው። በእሱ ኋላ ቀር እሳቤ የኢትዮጵያን ቁልፍ ሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይዘውት ሄደዋል። እሱ ባልተገራ አንደበቱ እንዳስቀመጠውም፤ ከመለስ ማለፍ በኋላ ኢትዮጵያ ይሏት አገር ፈጽሞ አልቀናትም። ጉድ! እኮ ነው። ‹‹የት ሄጄ ልፈንዳ›› አለች እንቁራሪት።
ከሰሞኑ ደግሞ በሌላ አስገራሚና አስቂኝ ትርክቱ ተከስቷል። ዋሾው ስታሊን ስለ መንግስት ምርኮኞች አያያዝና አመጋገባቸው ሲደሰኩር ኩራት ቢጤ እየተሰማው ነው። ቀላጤው የምርኮኞቹን የምግብ ሜኑ ሲዘረዝርልን አንዱ ማሳያው የዶሮ አሩስቶ ሆኗል። እሱ ምርኮኞቹ ‹‹ዶሮ ቀረበልን›› ሲሉ መናገራቸውን ከአንደበታቸው እንደሰማ ይናገራል።
‹‹የዶሮን ነገር ዶሮ ያነሳዋል›› አሉ። ምን ማንሳት ብቻ እመት ኩኩም ጉዱን ስትሰማ ክንፏን እያራገፈች ‹‹ ኣከከከከ…..ኣከከከ…›› ሳትል አልቀረችም። እኛም የጥብሱ፣ የግብዣው ሽታ ከአፍንጫችን ሳይርቅ የእሱ ዶሮ መጋቢ ሼፎች ከየሰው ማጀት ሽሮና በርበሬ፣ አሻሮና እንኩሮ፣ ሊጥና ፣ድፍድፍ መዝረፋቸውን ሰማን። ከሌማቱም እንጀራውን፣ እንጎቻውን መናጠቃቸውን አስመሰከሩ። አይ! ውርደት።
እነ ወይዘሮ ጸጋ ዋለ የተራቆተ ጓዳቸውን እያሳዩ ጥሪት እርሾአቸው በርሀብተኞቹ ጁንታዎች መሟጠጡን አጋለጡ።ይህ ብቻ አይደለም፡ ከተማረኩ የጦር መኮንኖች ኪስ ሳይቀር በእርዳታ ልመና የተገኘ ሀይል ሰጪ ምግብ ቢጤ ሲልሱ ሲያሸቱ ተመለከትን።
ይባስ ብለውም ለተፈናቃይ ህጻናት የገባውን አልሚ ምግብ እየነጠቁ መሰልቀጣቸውን ሰማን። አይ ሆዳምነት፤ አሁን ለሚሞት ሰው ሆድ ማብዛት ምን ያደርግለታል? ምንም።
ይህን ያዩ ታዲያ በነስታሊን ስብከት ለምርኮኞች ተርፏል የተባለውን የዶሮ ጥብስ እያሰቡ በግርምታ ታዘቡ። የዋሾው ጋዜጠኛ ተብዬ ስታሊን ወልጋዳ ትርክቶች ግን አላባሩም። የጁንታ ተዋጊዎችን ጨዋነት የመመስከር ተረቱን ‹‹ስሙልኝ›› ሲል ቀጥሏል።
የነስታሊን ዶሮ መጋቢ ሼፎች እኮ ! ሆስፒታል ከተኙ ህሙማን ክንድ ጉሉኮስ እየነቀሉ ነው። የአካል ጉዳተኞችን ሰው ሰራሽ እግሮችን ፈተው እየወሰዱ ነው። መቼም ወዳጆቼ ! ከዚህ የባሰ ሞትና ውርደት ይኖራል? በፍጹም። ውሸት የማይደክመው ቀላጤያቸው ግን ዛሬም ዓይኑን በጨው አጥቦ የዘመዶቹን ጨዋነት ላስረዳችሁ እያለን ነው። ‹‹ድንቄም›› ጨዋነት።
ውሸት በመናገር ሱስ አይድኔ በሽታ የያዘው ስታሊን ዘወትር በሚያቅራራበት ያልታረመ አንደበቱ የማይደርስበት፣ የማይረግጥበት ጥግ የለም። አንድ ሰሞን የአዲስ አበባን ህዝብ እማኝ አድርጎ ነዋሪው የወያኔን መመለስ እንደሚናፍቀው ሊነግረን ሞክሯል።
በዚህ ትርክቱም ህዝቡ እስካሁን በሆነው ሁሉ ተጸጽቶ አሸባሪውን ይቅርታ ሊጠይቅ መዘጋጀቱን ያለ አንዳች ሀፍረት ሲዘረዝር ቆይቷል። አይ የአዲስ አበባ ምኞት። ቀላጤው ሆይ ! ‹‹ሲያምርህ ይቅር›› ተብለሀል።
ስታሊን ህዝብን በማናናቅ በሚያሳየው ድፍረቱ ብዙዎች ከመገረም አልፈው ተዝናንተውበታል። ደጋግመውም ‹‹ልብ ዕንቅርት ይመኛል›› ይሉትን ተረት ‹‹ላንተ ይድረሰ›› ሲሉ ሸልመውታል። ዋሽቶ አደሩ ቀላጤ ራሱን እንደ ቅዱስ አድርጎ ሌሎች ሚዲያዎችን ለመውቀስም ምላሱ እንደሰላ ነው።
በከፋ ግብሩ የተሸነፈ በመሰለው ጊዜ ደግሞ እንደሱ ላይ ታች የማይረግጡ ጋዜጠኞችን እያነሳ ይኮንናል፣ ስማቸውን እያጎደፈም ትንታኔ ሀሳባቸውን ያጣጥላል። አንዳንዴም መለስ ብሎ የምዕራባውያኑን ውለታ ለማስታወስ ይሞክራል። ይህኔ ቁራሽ የማይነፍጓቸው እነሳማንታ ፓወር ትዝ ይሉታል።
ስታሊን ሴትዮዋን ደጋግሞ እያነሳ ያወድሳል። ለጁንታው ከተጣለለት ብስኩት መሰል ማታለያ በዘለለ ተዘርፎ ለሚሸቀጠው የእርዳታ እህላቸው መገኛ ሰበብ ሆናለችና ደጋግሞ ያመሰግናታል።
የስታሊን ተብየው ወልጋዳ ቀስቶች የማይሰኩበት የለም። በአሽባሪው ህወሓት የተፈጸሙ የአፋርና የአማራ ህዝቦችን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ሸምጥጦ ይክዳል። በጦርነቱ በየቀኑ ድል የሚቀናውም የህወሓት ጁንታ ብቻ መሆኑን ምላሱን እየያዘው ይመሰክራል።
ስታሊን በየደቂቃው ጁንታውን የሚገርፉ ጀግኖችን ገድል ለማጣጣል፣ የወታደሩን ብቃት ለማውረድ ፣ የልዩ ሀይልና ፋኖዎችን ህብር ለመናቅ እንደዘመዶቹ ሹል ጥፍር የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም። ደጋግሞ እንደሚለውም እሱና መሰል ብላሽ ትውልዶች ኢትዮጵያ ስትፈራርስ ቆመው ማየት ያስደስታቸዋል።
‹‹የሚሞት ልጅ አንገቱ ረጅም ነው›› እንዲሉ እነስታሊን የውርደት ሞታቸውን አውቀውት ቀድመው ቢናዘዙ አይገርምም። ተስፋ ከቆረጠ ምላስ የሚጠበቅ እውነት ይህ ነውና በቀደመው ኑዛዜያቸው ‹‹ነፍስ ይማር›› ብለናል። አወይ! እነወሬ ስንቁ ስታሳዝኑ ! ለካስ ከአንዲት ድንቅና ታላቅ አገር ጋር የሚያፎካክር የሙት መንፈስ ውስጥ ናችሁ። ምስኪን ቅዠታም ህልመኞች።
ስታሊን ሞራል የለሽ ሆድ አደር ስለመሆኑ በራሱ አንደበት መመስከር ከያዘ ሰንብቷል። በየቀኑ በግንባር ለሚሞግቱት አስተያየት ሰጪዎቹ ምላሽ ለመስጠት ወኔ ሲያንሰው ይስተዋላል።
አንዳንዴ ንፋስ እንዳየው አሮጌ ጨርቅ የሚውለበለው ምላሱ፣ ድርቅ ይልና ውሸታም አንደበቱ ይታሰራል። ጎማ ሲፈነዳ ክው የሚለው ማንነቱም በየጊዜው ልኩን ሲያሳዩት ይይዘው ይጨብጠው ያጣል። አይ ስታሊን ! ወጊቲው የጨካኝ ስም ሌባ።
ስታሊንን አሳምረው የሚያውቁ ብዙዎች ‹‹ፊሽካው›› ሲሉ ይጠሩታል። እውነትም ፊሽካ። የእሱ ወዛም ምላስ እኮ አንበጣን ከማባረር የዘለለ ሀይል ኖሮት አያውቅም። ፊሽካው ስታሊን አሸባሪው ጁንታ ቁምስቁሉን ሲበላ ብቅ ይልና የተስፋ መቁረጡን ያህል ዘበራርቆ ይመለሳል። ‹‹ነውር ጌጡ›› የሚል ስያሜ የተቸረው ነውረኛ ዛሬም በሰው አገር ባላ ቆሞ ላይወድቅ ይወዛወዛል።
ዋሽቶ አዳሪው ቅጥረኛ የኢትዮጵያ ህዝቦችን አይበገሬ አንድነት አሳምሮ ያውቀዋል። የህወሓት የመቃብር ጉድጓድ መከፈቱንም ጠንቅቆ ይረዳል። ‹‹አለሁ›› ባይ ማንነቱ ግን የአባቶቹን አይቀሬ ሞትና ኑዛዜ አምኖ መቀበል እንደተሳነው ቀጥሏል።
አሁንም ስታሊን ተብዬው ዕብድ ውሻ ጭራውን ቆልፎ እያላዘነ ነው። ዕብድ ውሾች ደግሞ ታክመው አይድኑም፡ ፡ለጌታቸው አይጠቅሙም። በየደረሱበት ሰው ይሸሻቸዋል። የሞት መርፌ ይጠብቃቸዋል። ልክ እንደስታሊን።
እነሆ! ዛሬ ድሉ ተቀጣጥሏል። አሸናፊነት ሰምሯል። ቀጥፎ አዳሪው ምላስ ግን እንዳልተዘጋ ሬዲዮ መጮህ፣ መለፍለፉን ይዟል። በወልጋዳና ገዳዳ ትርክቱ።
ከአትጠገብ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27/2013