እንደ ሳኡዲ አረቢያ ኢራን ባሉ ሀገራት ክፉ አመል የለመደ እጅ የሚደርስበት ፍርቅ ከበድ ያለ ነው፤ በህዝብ ፊትም ጣት አስቆርጦ እስከወዲያኛው እንዲጣል የሚደረግበት ሐይማኖታዊ ህግጋር ተግባራዊ ሲደረግ ታይቷል። በአንዳንድ የአፍሪካ ገራት ውስጥ ደግሞ በቀደመ ጊዜ በስርቆት የተጠመደ ሰው ያለምግብና ውሃ ለቀናት ይታሰር እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል።
በቡድን ተደራጅቶ ስርቆትን ዋነኛ ስራው ያደረገ አሸባሪ አካል ቢፈለግ ግን እንደህወሓት የሚሆን እንደሌላ በገሃድ ታይቷል። አሸባሪው ቡድን ህወሓት በአማራ እና አፋር ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ዘረፋ እና ውድመት ሲፈጠር የተጠናወተው የስርቆት አባዜ ስለመሆኑ ማወቅ ይገባል።
አሸባሪው ህወሓት ትላንት በመንግስት ካዘና ዘረፋ የለመደውን ዛሬ ደግሞ በገሃድ የህዝብን ንብረት ዘረፋውን አሸጋግሮታል። ይህ ክፉ ልምድ ግን እንዲሁ ያልመጣ እና ከአመሰራረቱም ጀምሮ የነበረ የተለመደ እና አመራሩም ጭምር የሚሳተፍበት ነው።
የአሸባሪው ህወሓት የስርቆት አመል ሲወለድ ያጠለቀ ሲሞት አወለቀ ይሉት ብሂል ያስታወሰ ክስተት ሰሞኑን በስፋት ታይቷል። ቡድኑ እስካልተወገደ ድረስ ይህንን የስርቆት አመሉን እንደማይተው አረጋግጧል። ካለፈውም የሚማር ባለመሆኑ ስርቆቱን ዛሬም ሊያቆም አልቻለም።
የንጹሃንን ዜጎች የዕለት ምግብ እና መገልገያ ከመዝረፍ አልፎ በህጻናት ላይ ጭምር ጭፍጨፋ ሲፈጽም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮች ምዕራባውያን ዝምታን መምረጣቸው ደግሞ የሚገርመውና የሚደንቀው ጉዳይ ሆኗል። ይባሱንም ዘራፊውን ወደጎን ተወት አድርገው አይናቸውን መንግስት ላይ ማድረጋቸውና መጮሃቸው ትዝብት ውስጥ ከቷቸዋል።
የነጮቹ ዝምታ አለማው ለየት ያለ ነውና እሱን ለሌላ ጊዜ አቆይተን ስለህወሓት የስርቆት ልምድ ግን ጥቂት ማለቱን መረጥኩ። ልምዱ ሁሉ ከዘረፋ እና ማጋበስ ጋር የተያያዘው ትህነግ የቀድሞውን ታሪኩን ብንመለከት ከዚህ ውጪ የተለየ አላማ እንደሌለው እንረዳለን።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1980ዎቹ አጋማሽ በኢትዮጵያ ሰሜን ክፍል ተከስቶ በነበረው ረሃብ ከምዕራባውያን የተሰበሰበውን ገንዘብ ህወሓት ከእርዳታ ድርጅቶች ጋር ተመሳጥሮ ለመሳሪያ ግዥ እንዳዋለው የአሜሪካው የስለላ ተቋመ ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጎታል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በተደጋጋሚ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ማረት የተሰኘ በእርዳታ ድርጅት ስም የሚንቀሳቀስ ተቋም ነበረው። ይህ በእርዳታ ድርጅት ስም የሚንቀሳቀስ ተቋምን ተጠቅሞ በ1977 ዓ.ም ድርቅ ወቅት ከአለም አቀፍ እርዳታ አቅራቢዎች የተለያዩ የእርዳታ ምግቦችን ይቀበል ነበር።
ለንጹሃን ዜጎች መድረስ የነበረበትንም ስንዴ እና አልሚ ምግብ በድርጅቱ ስም በመስረቅ ለታጣቂዎቹ ያውለው እንደነበር አስረድተዋል። የጁንታው አካሄድ ምን ያክል በስርቆት ላይ ህይወቱን መሰረት እንዳደረገ በርካታ ማስረጃዎች አሉ የሚሉት ዶክተር አረጋዊ፤ በየጊዜው ግን ይህ እክይ ምግባሩ ይወጣ እንደሁ እንጂ የፈጸመው በደል በአንድ ጊዜ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም ይላሉ።
ቀድሞ ህወሓት ውስጥ የነበሩት ዶክተሩ ቡድኑ ቢመቸው ሀገር ሸጦ ለግሉ ጥቅም ለማዋል የማይዳዳ ስብስብ ነው ሲሉ በግልጽ አማርኛ አሸባሪውን ቡድን መግለጻቸው ያለምክንያት አልነበረም። ህዝብ በተራበበት ወቅት እንኳን የእርዳታ እህል እና ገንዝብ ወደኪሱ የሚያስገባ የአሸባሪው ቡድን አመራር ቀላል እንዳልነበረ በወቅቱ የነበሩ የአይን እማኖች ጭምር የሚገልጹት ሃቅ ነው።
ሌላኛው የቀድሞው የህወሓት አባል አቶ የቀድሞ የህወሓት ፋይናንስ ክፍል ሃላፊ ገብረመድህን አርአያ በአንድ ወቅት ህወሓት በእርዳታ ስም የሚመጣዉን ምግብ ለመስረቅ አባላቲን የሙስሊም ልብስ አልብሶ የእርዳታ ሰራተኞችን ይቀበል እንደነበር አጋልጠዋል። ለምን የሙስሊም ልብስ አለበሰ የሚለውንም ሲመልሱ ታጣቂዎቹ እንዳይታወቁበት እና በሐይማኖታቸው ምክንያት በአገዛዙ የተገፉ ዜጎች ናቸው በማለት ከእርዳታ አቅራቢዎች ስንዴ ይቀበል እንደነበር በተለያየየ ጊዜ ገልጸዋል። ይህ ለህዝብ የመጣን የመዝረፍ እና ዴንታ ቢስነት ሲፈጠርም የነበረ በመሆኑ ሲሞት ያበቃለት እነደሆን እንጂ ሊለቀው ያልቸለ ጠባዩ ሆኗል።
በሌላ በኩል የአሁኑ የአሸባሪው ህወሓት ወዳጅ የቀድሞው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውት ከ11 ዓመታት በፊት በሰራው የምርመራ ዘገባ ህወሓት ለእርዳታ የመጣን ዶላር ለመሳሪያ መግዣ ማዋሉን አረጋግጧል።
በእነቦብ ጊልዶፍ የሙዚቃ መሰናዶ አማካኝነት የተሰበሰበውን የእርዳታ ገንዘብ 95 በመቶው ህወሓት ለጦር መሳሪያ ግዝ አውሎት ነበር ሲልም በማስረጃ አረጋግጦ ነበር። በ1977 ከተከሰተው ረሃብ በኋላ የተገኘውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለግል ጥቅሙ ሲያውል የነበረ የህወሓት አባልንም ጭምር እነደነበር ደግሞ ግልጽ ነው።
ቢቢሲ በወቅቱ በሰራው ዘገባ ህወሓት በርሃብ የተጎዱ የትግራይ ዜጎቻችን ህይወት ለመታደግ ከበርካታ ሃገራት የተለገሰውን ገንዘብ ለታሰበለት አላማ እንዳልዋለ የቀድሞ የህወሓት አመራር አባላት የነበሩትን አቶ ገብረ መድህን አራያንና ዶክተርር አረጋዊ በርሄን በመጥቀስ ጭምር ይፋ አድርጓል። በጊዜው የሚላስ የሚቀመስ ያጡ ዜጎች ከድጋፉ እንዲደርሳቸው የተደረገው አምስት በመቶው ብቻ መሆኑ ደግሞ ቡድኑ ምን ያክል በስርቆትና ዘረፋ ናላው እንደዞረ ያሳየ ሆኗል።
የቀድሞ የህወሓት አባሎች ይፋ ባደረጉት መረጃ መሰረት ከየአካባቢው እህል ገዝተው ለረሃብተኛው እንዲከፋፈል ለሚፈልጉ ለጋሽ ድርጅቶች የህወሓት ታጣቂዊች እራሳቸው የእህል ነጋዴ መስለው እንዲቀርቡ ይደረግ ነበር። በኋላ በአሸዋ የተሞሉ ብዙ ሺ ጆንያዎች ይደረድሩና ለማስመሰል ያክል ግን ከፊት ጥቂት ማዳበሪያ ስንዴ አስቀምጠው ማጭበርበርም ይፈጽሙ ነበር።
በዚህ የክህደት ስራ ያጋበሱትን ገንዘብ ወዲያውኑ ለመለስ ዜናዊ እና ሌሎች ታማኝ የህወሓት ባለሟሎቻቸው ያስረክቡ እንደነበረ ቢቢሲ በወቅት ዘግቦታል። ይህን ሁሉ ስርቆትና ዘረፋ አመል ታዲያ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልምዳቸው በመሆኑ አሁንም በአፋርና አማራ ክልልች ላይ ያገኙትን የቤት እቃ ጭምር እየያዙ ቢፈረጥጡ አይገርምም።
የአሸባሪው ቡድን አመራሮች ከኮሮጆ ስርቆት አንስት የኮንዶሚኒየም ህንጻ ጠፋ እድስከማለት የደረሰ የስርቆት አይነቶችን አሳልፈዋል። ይህን የስርቆት አይነትና አመልም እየሰማን እዚህ ደርሰናል። እነሆ አሁን ደግሞ ሊጥና በርበሬ መስረቅም ተጀምሯል። በለመደ እጃቸው በአማራ እና አፋር ክልል በሚገኙ ንጹሃን ቤት ወረራም አካሔደዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ የዩኤስ አይ ዲ ቅርንጫፍ የሆነው ኤፍ-ኤች ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ቡድን ንብረቶቹ ተዘርፈዋል መውደማቸው በግልጽ ታይቷል። በአካባቢው ያገኘውን ሁሉ እያጋበሰ የሄደው ዘራፊ ቡድን ከሊጥ እና ዱቄት አንስቶ እስከባንክ ቤት ዘረፋ ላይ ተጠምዶ ሰንብቷል።
የዘረፋውን ብዛትና አይነት በተመለከተ የማህበራዊ ትስስር መረጃ ማጋሪያዎች ላይ ቀልድ አዘል መልዕክት ያላቸው ፎቶዎችን እያየን ነው። ነገሩ እንዲያው ዝም ብሎ ለመዝናኛ ብቻ የቀረበ ሳይሆን በእውነተኛው የህወሓት ጀሌዎች ታሪክ ላይ ተመርኩዞ የሚሰራ እና ፖለቲካዊ ሳታየር ባህሪ ያለው አቀራረብ ነው። ይህ እንግዲህ ዘመኑን በዋጀ የቴክኖሎጂ መንገድ ስርቆቱን ለማሳየትም የሚደረግ ጥረት አንድ አካል መሆኑን መታዘብ ይገባል።
የሽብርተኛው ቡድን በገባባቸው ከተሞች በተለይ የፈጸማቸው ዘረፋዎች ከቤት ቁሳቁስ ጀምሮ እስከ ትላልቅ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ነቅሎ እስከመውሰድ የደረሰ መሆኑን ለተመለከተ ሌላ ሀገር አለን እንዴ የሚያስብል ጥያቄ ያጫረ ሆኗል። ታሪካዊው ጨጨሆ መድሐኒአለም ቤተክርስቲያን ጁንታው አውድሟል፤ የበርካቶችን ቤት ቆርቆሮ ነቅሎ ወስዷል።
ከታሪካዊ ስፍራ እስከ አቅመደካሞች ቤት ሲያወድምና በሂሳብ ማወራረድ ስሌት ሲዘርፍ የቆየው ጁንታው ባስ ሲልም እራሱ እንደተበደለ አድርጎ ወሬ ማስወራቱንም አላስታጎለም። ከዚህ ውጪ የምናየው የዘራፊው ቡድን አካሄድ መጠነኛ ስልጠና የታከለበት መሆኑን ማጤን ይገባል።
በአማራና አፋር ሕዝብ ላይ ዘረፋ እና ግድያ እንዲፈፅሙ ተከታታይ ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ምርኮኞች ሲናገሩ ተደምጠዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የገበሬዎችን ንብረት ከመዝረፍ ባለፈ፤ ነድቶ መውሰድ ያልቻለ ከብቶች በጥይት እየረፈረፉ ለቀው መውጣታቸው ሲታይ ውስጣቸው ያለው የጥላቻ መንፈስ ምን ያክል እንደሰረጸባቸው ያሳያል።
አሸባሪ ቡድኑ በደረሰባቸው ከተሞች ሁሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተዘርፈዋል። እንደ ወልደያ ሆስፒታል ያሉ የጤና ተቋማት በእነዚሁ ዘራፊዎች የተዘረፉ ሲሆን፤ ማጓጓዝ ያልቻሉትን ደግሞ አውድመዋል።
የቆቦ፣ የወልድያ፣ የኮን ፣ የላሊበላ፣ የሰቆጣ፣ ንፋስ መውጫ፣ አደርቃይት፣ መርሣ እና ሌሎችም ከተሞች ሆስፒታሎችን ጣራና ግድግዳቸው ሳይቀር ሁሉንም ቋሚና አላቂ ዕቃዎችን በሙሉ ዘርፈው አጓጉዘዋል። የወልዲያ ዩኒቨርሲቲና የተለያዩ የትምህርት ተቋማት ንብረቶች በተመሳሳይ በዘራፊ ቡድኑ ስለመወሰዳቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የበርካታ ባለሀብቶች የተለያዩ ንብረቶች የተዘረፉ እና የወደሙ ስለመሆኑም እንደዝሁ ሰሞናዊ መረጃዎች አመላክተዋል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚንስትር የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሽብር ቡድኑ በገቡባቸው አካባቢዎችአባላት ሰሞኑን የሚፈጽሙት የዘረፋ ዘመቻ የሴቶች ቀለበት፣ የጆሮ ወርቅ ሀብልና የመሳሰሉትን ሳይቀር የጨመረ መሆኑን ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።
ቡድኑ በአፋር ክልልም ተመሳሳይ ጥቃትና ዘረፋ በማከናወን የአርብቶአደሩንም ግመል እና ፍየሎች ነድቶ ወስዷል ያልቻለውንም አጥፍቷል። ይህ የስርቆት ልማድ የበርካታ ንጹሀንን ህይወት ችግር ውስጥ መጣሉ አይቀሬ ነው። ይህ በስርቆትና ዘረፋ ልምድ ያለው ሲፈጠርም ጀምሮ ክህደት የተዋሃደው ቡድን ታዲያ ከዚህ አመሉ በቀላሉ ይላቃል ተብሎ አይጠበቅም።
ቡድኑ በቢሊዮን ዶላሮችም አግበስብሶ በካዝናው ቢያስቀምጥ እንኳን ምሱን ለማድረስ ለስርቆት ኩሽና ውስጥ ገብቷል። ልባሽ ጨርቆችን ሳይቀር ለመውሰድ እና በየመዝናኛ ቦታው የተቀመጡ መጠጦችን ገልብጠው ለመጠጣት ያልሳሱ ዘራፊዎችአሳዛኝ ክስተት ነው።
የዚህ የሽብር ቡድን ሲፈጠርም የተላበሰውን የስርቆት አመል ተፈጥሯዊ ሞት ሲወስደው ይለቀው እንደሁ እንጂ ከስህተቱ አልማር ካለ ሰነባብቷል። በአጠቃላይ የቡድኑ አባላት የስርቆት አመላቸው የሚተዋቸው ተገቢውን ቅጣት ሲያገኙ እንደሁ እንጂ ሌላ ምን መላ ይገኝላቸዋል።
ለዚህ መፍትሄ ደግሞ ለሀገራቸው ህልውና ዘብ የቆሙ ኢትዮጵያውያን ጥሩ መድሃኒት ናቸው። መከላከያ ሰራዊት፤ ልዩ ሃይሎች እና አጠቃላይ ህብረተሰቡም ይህን ዘራፊ ቡድን ለመታገል በሚደረገው ጥረት ከፊት ተሰልፈዋል። ውድ ኢትዮጵያውያን ልጆች ይህን አውዳሚ ቡድን ለማጥፋት ቆርጠው በመነሳታቸው የዘረፈውንም ቡኮ እና መሳሪያ እያንጠባጠበ ሲፈረጥጥ የተስተዋለበትም ጊዜ ጥቂት አይደለም።
ሰሞኑን ደግሞ የአሜሪካው የተራድኦ ደርጅት (ዩኤስ ኤድ) አሸባሪው ህወሓት የምግብ እርዳታ እና ቁሳቁሶችን እንደዘረፈው ተናግሯል።የዩኤስ ኤድ ሚሽን ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ሾን ጆንስ እንደተናገሩት ህወሓት የዩኤስ ኤድን የእርዳታ ንብረቶች እና ቁሳቁሶችም መዝረፉን አምነዋል። ዳይሬክተሩ ጨምረውም ድርጅታቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የተፈናቃዮች እና የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች በቅን ልቦና እያገዙ መሆኑን ይናገራሉ።
ዳይሬክተሩ ጨምረውም ‹‹ህወሓት ሁኔታውን ያለአግባብ እየተጠቀመበት እንደሆነ እናምናለን። ከተረጂዎች ላይ በሃይል እርዳታዎችን እየነጠቀ እንደሆነ ይሰማናል። እርግጠኛ ሆነን መናገር የምንችለው ግን ሰርገው በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ ያሉትን የእርዳታ ካዝኖቻችንን ዘርፈዋል። ይህ የምናውቀው ሃቅ ነው ። የህወሓት ወታደሮች ሰርገው በገቡባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ጥፋት በማድረሳቸው የእርዳታ ሂደቱን በከፍተኛ ሁኔታ እያወኩ ይገኛሉ።
አሁን በግልፅ የምናውቀው ነገር ቢኖር የህወሓት ወታደሮች በገቡባቸው የአማራ ክልሎች በሙሉ የእርዳታ መጋዘኖችን ዘርፈዋል። መኪኖችን ሰርቀዋል። በየመንደሮቹ ብዙ ውድመቶችን አድርሰዋል። ይህ ለተጎጂዎችም ሆነ ለእኛ ለረጂ ድርጅቶች እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ››ሲሉ የዩኤስ ኤድ ሚሽን ዳይሬክተሩ ሾን ጆንስ የአሸባሪውን ህወሓት አሳፋሪ ድርጊት ለአለም ህዝብ ይፋ አድርገዋል።
ዳይሬክተሩ ዛሬ ይህንን ሃቅ ይፋ ቢያደርጉትም ኢትዮጵያውያ ግን ቀድመው በመረዳት የህወሓትን አሸባሪነት ለአለም አሳውቃል።ይህ እኩይ ቡድን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሰነበተ ጉዳቱ የከፋ በመሆኑም አንድነታቸውን አስተባብረው የአሸባሪ ቡድኑን ግብዓተ መሬት ለመፈጸም ቆርጠው ተነስተዋል። ሀገርም በልጆቿ ትግል ድል የምታደርግበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ምንም ያክል የውጭ ተጽእኖ እና አለሁ ባይነት ቢያገኝም አሸባሪው ቡድን ከነስርቆት አመሉ እንደሚወገድ ጥርጥር አይኖርም። ለዚህም የተጀመረውን የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል። ቸር ያቆየን።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27/2013