በ1997 ዓ.ም በኢህአዴግ አመራሮች ዘንድ ያልተጠበቀ ሽንፈት መከሰቱን ተከትሎ በከተሞች በተደረገው የወጣቶች ስብሰባ ላይ ተካፋይ ነበሩ የዛሬው እንግዳችን አቶ ገብረጻዲቅ ገብረመድህን፡፡ በወቅቱ የአንደኛ አመት የባህርዳር ዩንቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ተማሪ የነበሩት አቶ ገብረጻዲቅ በእነ በረከት ስምኦን መቀሌ ላይ የተሰበኩትን አምነው አዲስ የህወሀት አባል በመሆን ድርጅቱን ተቀላቀሉ፡፡ ይሁን እንጂ የተነገራቸውን በተግባር በፓርቲው ማግኘት ሲያቅታቸው በ2006 ዓ.ም በፍላጎታቸው ከህወሓት ለቀቁ፡፡ በትግራይ ክልል ከወረዳ ጀምሮ በተለያዩ ጽ/ቤቶች አገልግለዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የዋና ስራ አስፋጻሚው የከተማ ህዝብ አደረጃጀት አማካሪ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን በተለያዩ ከተሞች እና ወረዳዎች ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰዎችን በመመልመል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ የህወሓት አባል በነበሩ ጊዜ ስላሳለፏቸው ጊዜያት እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስለተሰሩ ስራዎች እንዲሁም ስለሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎች ጠይቀናቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ገብረጻዲቅ፡- በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ችግር አለ፡፡ ችግሩ ግን ከኢትዮጵያውያን እና ከአመራሩ በላይ አይሆንም፡፡ ችግሩ ደግሞ የተከሰተው በሀገራችን ከጊዜ ወደጊዜ ብዙ ጦርነቶች ሲካሄዱ ነበር፡፡ እነዚህ ጦርነቶች የተካሄዱበትን ምክንያት ሊቃውንት በሁለት አስቀምጠውታል፡፡ አንደኛው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር እንደ ሱዳን ጣልያን ግብጽም በተደጋጋሚ አሸንፈን መልሰናቸዋል፡፡ ሌላኛው መአከላዊ መንግስትን ለመቆጣጠር በየጊዜው በሚነሱ የግዛት አስተዳዳሪዎች መሀል ጦርነቶች ነበሩ፡፡ በየጊዜው ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ተሞክሯል በነዚህ ሁሉ ጊዜያት የራሱ መልካም ጎኖችም ሆነ መጥፎ ስህተቶች ነበሩ፡፡ ከመልካሙ እየተማሩ ስህተቶቹን ባለመድገም ወደፊት መሄድ ይገባል፡፡
ባይጠቀምበትም ሀገሪቷን ወደፊት ለማሳደግ እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ ጥሩ አጋጣሚ የተፈጠረለት መንግስት የለም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛውን ኢትዮጵያ አንቀሳቅሶ የቤተሰብ ስርወ መንግስት ለመመስረት በሰራው ሴራ የኢትዮጵያ ህዝብ ተደጋጋሚ እድል ቢሰጠውም እድሉን ያልተጠቀመ ስርአት ነው፡፡ እሱ በፈጠረው መከፋፈል፤ የንግድ አሻጥር እና የሀይማኖት ግጭት የኢትዮጵያ ህዝብ አንፈልግህም፤ ብሎ ሲያባርረው ሽንፈቱን ባለመቀበልና የሚመጣውን ተጠያቂነት ለመሸሽ ለአሜሪካና ግብጽ መላላክን በመምረጡ ኢትዮጵያ ችግር ላይ ነች፡፡ ይሄ ችግር ግን የእኛ አንድነት እና ጥንካሬ ካለ በሀይማኖት እና በብሄር ካልተከፋፈልን ፍቅር መዋደድ መቻቻል ካለ ይታለፋል፡፡ ለዚህ ችግር ዋናው መፍትሄ በማንኛውም ዋጋ የአሸባሪው ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለበት፡፡ ያኔ ኢትዮጵያ ሰላም ትሆናለች፡፡ በእጅ አዙር ሀገራችንን ሊያስተዳድሩ የሚፈልጉት አሜሪካ እና ግብጽ ያበቃላቸዋል፡፡ ችግር አለ፣ ይሄንንም አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፤ ግን ችግሩን የመፍታት እና የማስወገድ ብቃት ያለው ህዝብና አመራር ስላለ ችግሩ ይፈታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በ2006 ዓ.ም በፍቃድዎ ከህወሓት ፓርቲ ለመልቀቅ ሲወስኑ ከህወሀሓት ባህሪ አንጻር እንዴት ደፍረው ሊወጡ ቻሉ?
አቶ ገብረጻዲቅ፡- ከ1ኛ-12 ክፍል በምማርበት ጊዜ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ፤ አንደኛ ካልሆነ እስከ ሶስት ካለው ደረጃ አላልፍም ነበር፡፡ ዩንቨርስቲ በነበርኩ ጊዜ ግን የፖለቲካው ስራ ስላመዘነብኝ የትምህርት ውጤቴ ላይ እራሱ ተጽእሞ አሳድሮብኛል፡፡ ህዝቤን የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ወደ ስራ አለም ከተቀላቀልኩ በኋላ ያገኘሁትና ሳስበው የነበረው ለየቅል ነው የሆነብኝ፡፡ ባህርዳር ስማርም በዘር አላምንም፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወንድሜ እህቴ ነው በሚል አስተሳሰብ የተቃኘሁ ነበርኩ፡፡ ወደስራ በተሰማራሁበት ጊዜ ግን ሁሉ ነገር ከአንድ ቤተሰብ ነው፤ ከአድዋ ከደግአሜን፣ ከአንፍሮ ወረዳ ካልሆንክ በተለይ የራያ፣ የአጋሜ፣ የእንደርታ፣ የተንቤን የሆነ ሰው ወደሀላፊነት አይመጣም፡፡ ይሄንን ትምህርት ወስጄ መታገል አለብን ብለን መታገል ስንጀምር የአንድ ወር ደሞዛችንን ሳይቀር ተቀተናል፡፡
የተቀጣንበት ምክንያት ምን መሰለሽ፤ ግምገማ ነበር የአደረጃጀት የሚባል፤ እዛ ላይ ሀላፊዎችን እንዳንገመግም ወደፊልድ ላኩን፡፡ እኛ ስንሰማ ሹፌሩን መኪናውን መልሰው የሚመጣብንን ቅጣት ሀላፊነት እንወስዳለን ብለን ግምገማውን ተካፈልን፡፡ ከዛ ግምገማው ላይ ወረዳው በትክክል ሀብቱን እየተጠቀመ አይደለም፤ በማለት ገመገምናቸው፡፡ በተለይ ከውሃ ጉድጓድ ጋር የተያያዙ ስራዎች አልተሰሩም ብለን ተናገርን፡፡
በግምገማው ማሸነፍ ሲያቅታቸው በየጽ/ቤቱ ለያዩን፡፡ አብረን የምንታገለው ፋይናስ ጽ/ቤት ስለነበርን በህዋስ እራሳችንን እንችላለን፡፡ ግን ከምክር ቤት ከፕሮፓጋንዳ፣ ከአደረጃጀት፣ ከአፈጉባኤ፣ አርገው ገመገሙን፡፡ እኔ ሰላሳ ምናምን ጥያቄ ነው የተጠየኩት፤ ጥያቄው አለ፡፡ አንድ መልስ ነው የሰጠኋቸው የማዝነው ከእናንተ ጋር አንድ ላይ መዋሌ ነው፡፡ ከዛ በመገምገማችን ማስጠንቀቂያና የአንድ ወር ደሞዛችን ተቀጣን፡፡ በኋላ ቅጣቱን የሲቪል ሰርቪስ ሀላፊ አፈረሰችው፡፡ ከዛ ወረዳችንም ተቀይሮ ወደአጋሜ ተዛወርኩ፡፡ ግልጽ መሆን ያለበት የትግራይ ወረዳዎች በእዛ አካባባቢ ተወላጆች አይመሩም፡፡ ወይ ከእዳጋ፣ ከአፍአሮም ይመጣል ወይ ከአድዋ ወይ ከአክሱም ይመጣል፡፡ ምክንያቱም የአሸባሪው ህወሓት ስብስብ እዛ አካባቢ ስለሆነ፡፡
ስናያቸው ከፋይናንስ ጋር ጭቅጭቅ ነው፣ ያልሆነ ባጀት ስጡን ይላሉ፡፡ ደሞ አንዳንዴ እስከ ስምንት ሰዓት ትቆያለሽ ግምገማ ተብሎ፡፡ ግምገማውም ስራ አይደለም፣ የምትገመግሚው አረማመድህ እንዴት ነው፤ ከማን ጋር ነው የምትሄደው፤ ምንድነው የምትናገረው፤ አይነት ነገር ነው፡፡
እኔና ጋደኞቼ ለስራ ካለን ተነሳሽነት በወረዳው የሚገኙ ወጣቶችን አደራጅተን ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ከዛ ግን አላሰራ አሉን፡፡ እኔን የማይመጥን ሰው ይመራኝ ነበር፡፡ እኔን የማያስተምረኝ በደንብ የማይመራኝ ከሆነ በሚል እና ትምህርቴንም መማር እፈልግ ስለነበር በፍላጎቴ መልቀቂያ አስገባሁ፡፡
ለመልቀቅ አንገራግረዋል፤ ክትትል ሊያረጉ ይችላሉ፡፡ አብሶ ከሰረቅሽ እና ወንጀል ከተገኘብሽ እንደማስፈራሪያ ያረጉታል፡፡ እኔ ምንም ስላልሰረኩ ወንጀልም ስላልሰራሁ በራስ መተማመን ነው የለቀቅኩት፡፡ ከፓርቲው ከለቀቅኩ ጀምሮ የምንም ፓርቲ አባል ሳልሆን ቆይቻለሁ፡፡ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንም እሰራ ስለነበር እዛም የፓርቲ አባልነት አይፈቀድም፡፡ ህወሓት ቤት በግልጽ ‹የአጋሜ ሰው ለንግድ ነው እንጂ ለፖለቲካ አይሆንም› ይሉን ነበር፡፡ ግን ደግሞ ስታይው ሀረግ አለው፤ የሼማ አጋመ ወልዱ የሚባል አብዛኛው የትግራይ አስተዳዳሪ ከዛ ነው የሚመደበው በርካታ ሰዎች ወተውበታል፡፡ የአጋሜ ህዝብ በኢትዮጵያም ሆነ በትግራይ አስተዳደር የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ያለው ነው፡፡ አሁንም ዶ/ር አብረሀም በላይ እና የአየር መንገዱ አስተዳደር ተወልደ ገብረማርያም እዛ የአለም ጤና ድርጅት ቁጭ ብሎ ለህወሓት የሚደግፈው ዶ/ር ቴዎድሮስም እዛ ናቸው፡፡ ግን በምን ተፈረጅን ለአስተዳደር አይሆኑም እያሉ ከፖለቲካው እንድንወጣ አርገውናል፡፡
እኔ ወደ ዩንቨርስቲ በምገባበት ጊዜ ወደ 20 አካባቢ ነበር የገባነው፤አሁን አንድ እንኳን አይገባም፡፡ ከስምንተኛ ክፍል ይወድቃል፣ ወይ ወደ ሳውዲ ይሄዳል፡፡ በስፔሻል ስኩል ባላምንም መቀሌ ቃላሚኖ የሚባል የተለየ ትምህርት ቤት አለ፡፡ ትምህርት ቤቱ ሲጀመር በ65 ተማሪ ነው ስራ የጀመረው፡፡ ከዛ ውስጥ ከፍተኛ ነጥብ ስላላቸው 25 ተማሪ ከአጋሜ መግባት ችለዋል፡፡ ልጆቹ ጎበዝ ሲሆኑባቸው ጊዜ በኮታ እናርገው አሉ፤ 100 ያመጣ የራያና የማይጨው ልጅ እንዳይገባ 70 ያመጣ የአድዋ ልጅ እንዲገባ ማለት ነው፡፡ ልዩ ትምህርት ቤት ብለው እንኳን የሌላ አካባቢ ልጆች የተሻለ ውጤት ሲያመጡ መግቢያው በነጥብ መሆኑ ቀርቶ በኮታ የሚያደርጉ ናቸው፡፡እኛን የበደሉን ይሄን ያህል ነው፡፡
የእነሱ ልጆች አሜሪካ ወይ አውሮፓ ሄደው የተደላደለ ሂወት ይመራሉ፡፡ የእኛ ወጣቶች ሳውዲ እና የመን በጉልበት ስራ መከራ ያያሉ፡፡ የመን ላይ በመያዣነት ተይዘው ብዙ መከራ ይደርስባቸዋል፡፡ ይሄን ስልሽ አጋሜ ብቻ አይደለም፡፡ ራያ ብትሄጂ ምን የመሰለ ለም መሬት በስመ ኢንቨስትመንት በህወሓት ተይዞ ተሰቃይተዋል፡፡ የእንደርታ ተይኝ በአጋጣሚ መሬቱ ወደ ከተማ ቀረብ ስለሚል ተወስዶባቸው ተሰቃይተዋል፡፡ ተንቤን ወልቃይት ሁመራ ብትሄጂ ተጎጂ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በብሄር መከፋፈሉ እስከወረዳ ድረስ ይወርዳል ማለት ነው?
አቶ ገብረጻዲቅ፡- አዎ፤ ህወሓት ምን ይላል መሰለሽ ትግራይ አንድ ነች፤ አትከፋፈሉ፤ ዋና ጠላታችን በመንደር ማሰብ ነው ብለው ይተርካሉ፡፡ በተግባር ግን እኩል አያይም፡፡ በአጋጣሚ ፕሬዝዳንት አስራት ነበሩ እንጂ ከዛ በኋላ ፕሬዝዳንቶቹ ሁሉም ከዛ ናቸው፡፡ አባይ ወልዱም፣ ደብረጺዮንም፣ ጸጋዬ ከውጪ ስታዪ አንድ ነን ይባላል፣ በውስጥ ግን አንድ አይደሉም፡፡ ህወሓት በከፋፍለህ ግዛ ሴራ ካልሰራ ማደር አይችልም፡፡ ካላፈነ ካልከፋፈለማ ወደአንድነት ይመጣሉ፤ አንድ ከሆኑ ደግሞ ይቃወማሉ፤ ስለዚህ መከፋፈል አንዱ አካሄዳቸው ነው፡፡ አውቀው ነው እንጂ ድሮ 1968 ዓ.ም ዘመነ እንፍሽፍሽ የሚባል ተከፋፍለዋል፡፡ አሽአ የሚባል፤ አሽአ ማለት አድዋ ሽሬ አክሱም ነው፡፡ እዛ ተገዳድለዋል፤ ህወሓት ሲባላ ነው የኖረው፡፡ ላይ ላዩን ስታይው የህዝብ ግኝኑነት ስራ በደንብ ስላቀነባበረ ነው እንጂ ውስጡ ቁስለኛ ነው፡፡ ህወሓት ለአንድነት ሰርቶ አያውቅም፤ ለአንድነት ቢሰራ ኖሮ አሁን ያጋጠማቸው ችግር አያጋጥማቸውም ነበር፡፡
ከትንሽ ተጀምሮ እያደገ እየተደመረ ሄዶ የኢትዮጵያ አንድነት ጠንካራ እየሆነ ይመጣ ነበር፡፡ ግን እነሱ ሲሰሩ የነበረው የመበተን ስራ፤ ከፋፍለህ ግዛ ነው፡፡ አሁንም በዚሁ ቀጥለው የመከፋፈል መርዝ እየረጩ ነው፡፡ አድዋ፣ ራያ፣ አጋሜ፣ አክሱም እያሉ በወረዳ ብቻ ሳይሆን ከዛም ወደ ቀበሌ ይሄዳል፡፡ አሁን ይሄንን ለመፈወስ ነው እየሰራን ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመከላከያ ሰራዊት በክልሉ እንዳይቆይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ በበቂ ሁኔታ ከህዝቡ ጋር መቀራረብ ስላልቻለና በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ስላልቻለ ነው የሚሉ አስተያየቶች ይሰማሉ፤ በዚህ ላይ የእርሶ አስተያየት ምንድነው?
አቶ ገብረጻዲቅ፡- መከላከያ ሰራዊታችን ተገቢውን ስራ ሰርቷል፡፡ በአጭር ጊዜ ነው አሸባሪው ህወሓትን ያፈራረሰው፡፡ ግን እንደዚህ አይነት ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥም ስራዎችን በሌላው ጊዜ በሚሰራበት አግባብ ብቻ መስራት በቂ አይደለም፤ የተሻለ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተቋቋመው በደንብ ታስቦበት ሳይሆን በሩጫ የተዋቀረ ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ዶ/ር ሙሉ ጎበዝ መምህር ሊሆኑ ይችላሉ፤ በሙያቸውም ሪሰርቸር ናቸው፡፡ ግን የአስተዳደር ልምድ አላቸው ወይ ተብሎ በደንብ አልታየም፡፡ ለምን መሰለሽ እንደዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲኮን ልምድ ያለው ሰው ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው በሌላ ጎበዝ ቢሆንም በሁሉም ሊሳካለት ስለማይችል፤ ስብስቡ ልምድ ያጥረዋል፡፡ ችግሮችን የማለፍ ብቃት እና ልምድ ከሌለ ይወድቃል፡፡ ገብቶትም ይሁን ሳይገባው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የአሸባሪውን ህወሓት የሚያጠናክር ስራ ሲሰራ የነበረ ሰው በመሀል አለ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ህዝብ ችግር ውስጥ ስለሆነ እርዳታ ያስፈልገዋል ብሎ ብዙ እህል እየላከ ነበር፡፡ ስለዚህ እህሉ በተገቢው ሁኔታ ለሚመለከተው ሰው እንዲደርስ ካላደረገ እና እህሉ ወደአሸባሪው ህወሓት ከሄደ ይሄ ቁጥጥር አላደረገም፤ በተዘዋዋሪም ቢሆን ሽብርተኛውን እየደገፈ ነው፡፡ ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡
ውድቀቱን በደንብ ለመገምገም ተይዞ የተገቡትን ግቦች ልንገርሽ፡፡ ጊዜአዊ አስተዳደሩ ይዞ የተነሳቸው ግቦች ነበሩት፡፡ የፈረሰውን መዋቅር መልሶ ማደራጀት፤ መንግስታዊ አገልግሎት ማስጀመር፣ የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳይ በትግራይ ማረጋገጥ/ሰው ወጥቶ እንዲገባ ነጋዴው እንዲነግድ አስተማሪው እንዲያስተምር ሀኪሙም እንዲያክም ሁሉም እንቅስቃሴ ወደነበረበት እንዲመለስ ማስቻል/ የተቋረጠውን መሰረተ ልማት ወደስራ መመለስ/ ባንክ ቴሌ መብራት፣ወዘተ/ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ነባራዊ ሁኔታውን ማስተካከል እና ምርጫውን ማካሄድ የሚሉ ግቦችን ይዞ ነበር ወደስራ የተንቀሳቀሰው፡፡
እነዚህን ግቦች ቢፈጽም ኖሮ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አይፈርስም ነበር፡፡ ግን ይሄን በብቃት አልፈጸመም፤ ዋናው የወደቅንበት ስራ ደግሞ የፖለቲካ እና የህዝብ ግንኙነት ስራ አይሰራም ነበር፡፡ ምክንያቱም የህወሓትን መጥፎ ገጽታ በደንብ በሚድያ በውይይት በድራማ እና በፊልም ለህብረተሰቡ የስርጸት ስራ ካልሰራን አደገኛ ነው፡፡ እዛ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ አሸባሪውን ህወሓት የሚደግፉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ጄነራል ተክለብርሀን ወልደአረጋይ ሲጠየቅ ማይጨው እና አይደር የእኛ አመራር ሲታከም ነበር ብሏል፡፡ እኛም እናውቅ ነበር፡፡ ጤና ጣቢያ እና ሆስፒታል ከማጠናከር የጤና ሀላፊው ተንቀሳቃሽ ክሊኒክ አዘጋጅቶ ሲያሳክማቸው ነበር፤ ስለዚህ ከታከመ መድሀኒት ካገኘ እያገገመ ነው ማለት ነው፡፡
የትራይ ጊዜአዊ አስተዳደር የወደቀው አመራሩ ድብልቅልቁ የወጣ ስለሆነ ነው፡፡ ለውጥ የሚፈልግ አመራር ነበር፤ የሚዘርፍ አመራር ነበር፤ ህወሓትን የሚደግፍ አመራር ነበር፡፡ አንዳንዶች ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ውድቀት ዋናው ተጠያቂ ብልጽግና ነው ይላሉ፡፡ ይሄ ልክ አይደለም፤ ብልጽግና ሀገራዊ መሪ ስለሆነ ድርሻውን ይወስዳል፡፡ ኢዜማ፣ ትዴፓ፣ ራያ ራዩማ፣ አረና እና ብልጽግና ነበሩ፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ከብልጽግና በአስፈጻሚነት ሁለት ሰው ብቻ ነበር የተካተተው፡፡ ዶ/ር ሙሉ እና ባረያጋብር የወጣቶች ሀላፊው ብቻ ነበሩ፡፡ ሌላው የብልጽግና ሰው ሲያይ ብልጽግና ይሆናል፤ ያ ሳይኖር ደግሞ ገለልተኛ ነኝ ይላል፡፡
በርግጠኝነት ጊዜያዊ አስተዳደሩን ብልጽግና ይዞት ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ውድቀትም አያጋጥምም ነበር፡፡ ምክንያቱም የተጠያቂነት ስራ ይሰራ ነበር፡፡ እኔ አዲግራት ላይ ዞን እያስተካከልኩ በነበረበት ጊዜ ህዝብ ሲያንገላቱ የነበሩትን አስረናል፡፡ የመንግስት ነዳጅ የዘረፉ አስረናል፡፡ እንደዚህ እርምጃ የሚወስድ አመራር ይሆን ነበር፡፡ ግን የተደባለቀ በመሆኑ ተጠያቂነትም የለም፤ እቅድም የለም፡፡ በደንብ ግልጽነት መኖር ነበረበት፡፡ ግልጽነት ማለት እቅድ ይወጣል፤ ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ይደረጋል፤ በእሱ መሰረት ተጠያቂነት ይኖራል፡፡ በአጠቃላይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተናቦ ባለመሰራቱ ወርቃማው እድል ወደ ውጤት ሳይቀየር ቀርቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጊዜያዊ አስተዳደር ላይ በነበራችሁበት ጊዜ የአሸባሪው ህወሓት ኢንጅነር እምብዛን ጨምሮ 53 የሚደርሱ የጊዜያዊ አስተዳደሩን በተለያየ መልኩ የደገፉ ግለሰቦች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ሲነጥቅ ምን ስሜት ይፈጥርባችሁ ነበር?
አቶ ገብረጻዲቅ፡- በጣም የሚያሳዝነው ይሄ የአሸባሪው ህወሓት ባህሪ ነው፡፡ እንኳን ለህዝብ ምግብ መድሀኒት እና ውሃ እያመጡ ቀርቶ ሌላ ጥፋት ቢያጠፉ እንኳን ሊገደሉ አይገባም፡፡ ንጹሀን ናቸው፤ እኛም በእድል ነው እንጂ የተረፍነው ልንገደል ነበር፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነው አዲግራት የተገደለው እኔ ያመጣሁት ከንቲባ ነው፤ በጣም ጎበዝ የሆነ ልጅ ነበር፡፡ እነዚህን አመራሮች እየለመንን ነው ያመጣናቸው፤ አሸባሪውን ፈርተው እምቢ ሲሉ ህዝብ ነው የምታስተዳድሩት፤ ፖለቲካ አትሰሩም ብለን ነው ያመጣናቸው፡፡ ህወሓት ግፈኛ አራጅ ስለሆነ ደም ጠጥቶ እና ሰው ገድሎ የማይጠግብ ስለሆነ ነው እንጂ፤ መገደል አልነበረባቸውም፡፡
በጣም ያሳዝናል፤ ለምን እንደዛ ሆነ ብትዪ ጠባቂ ስለሌላቸው ነው፡፡ ጸጥታ አስተዳድሩ ጠንካራ አልነበረም፡፡ እኔም እራሱ ፈጣሪ ነው እንጂ ያወጣኝ፤ የድርጅት አመራር ሆኜ 6 ወር ሙሉ ጠባቂ አልነበረኝም፡፡ የአዲግራት ከንቲባ የነበረው ዳዊት ከተገደለ በኋላ ነው ጠባቂዎች የተመደቡልን፡፡ እግዚአብሄር ነው እንጂ የጠበቀን እኛም ሞተናል ማለት ይቻላል፡፡ ግፈኛ ስለሆነ ነው የገደላቸው፡፡ ይሄን የሚያደርገው ዲሞክራሲ ትግራይ ውስጥ እንዳይሰፍን፤ ሰዉ እንዲፈራ፤ ኋላ የሚመጣው አስተዳደርን እንዳይጠጋ ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ የነበረውን አስተዳደር አፍርሰነዋል፡፡ ምክንያቱም የነሱ የነበረውን አደረጃጀት ፕሮፓጋንዳ ምናምን የሚሉትን አፍርሰን በከተማ አምስት ሰው ብቻ ነው እያደረግን የነበረው፡፡
የለውጥ ፈላጊ ወደ ስልጣን እየመጣ ነበር፤ ይሄ ደግሞ የጁንታውን መዋቅር ያፈርሳል፤ አስተሳሰቡም ስለሚጠፋ ለዛ ነው የገደላቸው፡፡
አዲግራት ከንቲባው ከተገደለ በኋላ ሌላ ከንቲባ ለማምጣት በጣም ተቸግረናል፡፡ የአዲግራት ከንቲባ ዳዊት ዘሩ የሚባል በጣም ጎበዝ ልጅ ነበር፡፡ የኢንጅነር እምብዛ ደግሞ በጣም አሳዛኝ የሆነ ነው፤ የአሸባሪው ድርጊት በጣም አሳዝኖኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት በተደጋጋሚ በጸብ አጫሪነት በአማራ እና በአፋር ክልል ተደጋጋሚ ጥቃት መፈጸሙን እንዴት ያዩታል? ለዘለቄታውስ በህዝብ መሀል ቁርሾ እንዳይፈጥር ምን ሊሰራ ይገባል ይላሉ?
አቶ ገብረጻዲቅ፡– ከአፋርና ከአማራ ክልል ጋር ጦርነት የከፈተው ጁንታው መጥፋቱ አይቀርም፤ ግን ደም ማቃባት ይፈልጋል፡፡ ትግራይ ከእሱ በኋላ የተረጋጋች እንድትሆን አይፈልግም፡፡ ለምን ህወሓት ታሪኩ ተበላሽቷል፤ ከጠፋ በኋላ የአሸባሪው ህወሓት ስሙም አይነሳም፡፡ ስለዚህ ደም ማቃባት ነው እንጂ የፈለገው ድሮም ቢሆን የአማራና የትግራይ ህዝብ ምንም ችግር የለባቸውም፡፡ አብረው የሀገርን ህልውና እና ሉአላዊነት ለማስከበር ሲታገሉ ኖረዋል፤ ተዋልደናል፤ ተዛምደናል፡፡ እኔ ባህርዳር ስማር ጓደኞቼ የነበሩ የባህርዳር ልጆች እስካሁን ጓደኞቼ ናቸው፡፡ ጦርነቱ ከህሓሀት ጋር ብቻ ነው ተብሎ መወሰድ የለበትም፡፡ የአሜሪካ የግብጽ የሱዳን እጅ አለበት፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ እየተቀየረ ነው፡፡ የሶማሊያ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ጥምረት አስፈርቷቸዋል፡፡ ምክንያቱም የህዳሴ ግድብን ከጨረስን በኋላ ዶላር እናገኛለን፤ ከዛ የምንፈልገውን እንገዛለን፤ ሌላ ግድብም እንገነባለን፡፡ የህብረተሰቡም ኑሮ ይሻሻላል፤ ጠንካራ ኢትዮጵያ ትፈጠራለች፡፡ ጠንካራ ኢትዮጵያ ስትኖር የነአሜሪካ ፍላጎት አይሳካም፤ ስለዚህ ህብረተሰቡ ጦርነቱ ከህወሓት ጋር ብቻ ነው ብሎ መውሰድ የለበትም፡፡
ጁንታው ወደ አማራ እና አፋር የገባው የህዝብ ጦርነት ለማድረግ፣ ህዝብ እንዲደናበር እና ለመበቀል ነው፡፡ ምን ብለው ሰብከዋል መሰለሽ ጠላትህ የአማራ ህዝብ ነው፤ /አሁን ሙሁራን ማለት ጀምረዋል/፡፡ አህዳዊ ነው ብልጽግና የኢትዮጵያን ህዝብ እየወረረ ነው ብሎ ይሰብካል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በባህሪው አፍርሶ አፈረሱ፤ ገድሎ ገደሉ ብሎ ይወነጅላል፡፡ የኤርትራን የመከላከያ የደንብ ልብስ ለብሶ ሴት ይደፍርና ሻእቢያ ደፈረ ይላል፡፡ ይሄን የሚያደርገው ደም ለማቃባት ነው፤ ይሄ ጠባሳ እንዳያሳርፍ ይታከማል፡፡ ሽብርተኛው እኮ የሚችለውን አርጓል፤ አሁን የእኛ መከላከያ እየጠረገ ነው፡፡ የሞተው ዜጋ ጉዳት የደረሰበት ሰው እና የንብረት ውድመቱ ያሳዝናል፤ መሆን ያልነበረበት ነው፡፡ ግን ደግሞ አሸባሪ እስካለ ኪሳራ ይኖራል፡፡ ህብረተሰቡ ግን በዚህ የሚፈጠር ነገር የለም፤ አብሮነቱ ተቻችሎ ይቅርም ተባብሎ ይቀጥላል፡፡ ዋናው በእነሱ በአሸባሪው ህወሓት ግብአተ መሬት የአማራ እና የትግራይ ህዝብ የአፋርና የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም ይረጋገጣል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርሶም እንዳነሱት በአንድ ወቅት የቡድኑ ቃል አቀባይ አሸባሪው ጌታቸው ረዳ ከአማራ ህዝብ ጋር ሂሳብ እናወራዳለን ብሎ ነበር፤ አሁን እየፈፀመ ያለው ጥቃት የዚህ አካል ነው ማለት ይቻላል፤ እንደው ቡድኑ ከበፊትም ጀምሮ ስናይ ከሌላው ብሄር በተለየ አማራ ላይ ጥላቻውን የሚያሳይበት ሁኔታ ነበር፤ እና ይሄ አቋም ከምን የመነጨ ነው?
አቶ ገብረጻዲቅ፡– 27 ዓመት ሙሉ አማራን ነፍጠኛ ብሎ ሲሰድብ ኖሯል፤ይሄን መካድ የለብንም፡፡ እንዲጠላ ማለት ነው፤እኔ አሁን 1997 የህወሓት አባል ሆንኩበት ባልኩሽ ስብሰባ ላይ ነበር ነፍጠኛ የሚለውን ቃል የሰማሁት፡፡ እንዲያውም እማልረሳው አንድ የህግ ተማሪ ነበር እነዚህ ነፍጠኛ አይነት ቃላት የድሮ የነሌሊን አይነት ስታይል ስለሆኑ አይጠቅሙንም እና ባይመጡ ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ ልጅ እያለሁ በትግረኛ ‹እሩጥ በለው ወያኔን እየሮጥክ አሕያ አማራን በለው› የሚል ዘፈን ነበራቸው፡፡ ለማነሳሳት በሚል ትምክህተኛው የአማራው ህዝብ ነው የበደለህ ሲሉ ነበር፡፡ ብልጽግናን መንግስት እኮ አህዳዊ ነው፤ የትምክህት የአማራ ሀይል ነው ይላሉ፡፡ ያው እነሱ ከትግራይ ህዝብ ወጥተው በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ግፍ እንደፈጸሙ ከአማራ የወጣ የተወሰነ አመራርም ችግር ፈጥሮ ሊሆን ይችላል፤ በደርግ ጊዜ ችግርም ነበረ፡፡ ከአማራ ህዝብ ጋር ሂሳብ አወራርዳለሁ የሚለውን እንደማስነሻ ነው የተጠቀመበት፡፡ አማራ ነው የበደለህ አማራ ነው መኪናህን የወሰደው፤ አማራ ነው ፋብሪካህን የሰረቀ ሚስትህን የደፈረው ብሎ ስለሰበከ እንዲነሳ ነው እንጂ የአማራ ህዝብ የትግራይ ህዝብን ያደረገው ነገር የለም፡፡ እንዲህ ካላለ ይምታታበታል፤ በስልጣን ላይ እያለም ነፍጠኛው የአማራ ህዝብ ነው የበደለህ እያለ ሲሰብክ ነበር፡፡ ያንን ለማስቀጠል ነው እንጂ ሂሳብ ማወራረድ ያለበት እራሱ አሸባሪው ህወሓት ነው፡፡
27 ዓመት ሙሉ ስንት አማራ ኦሮሞ እንደገደለ የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቃል፡፡ ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ አልፈልግህም ብሎ ያባረረው፡፡ ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ከአማራ ህዝብ የሚወራረድ ሂሳብ የለውም፤ወንድምና እህት ናቸው፡፡ ሂሳብ የሚወራረደው ከአሸባሪው ጌታቸው ረዳ እና መሰሎቹ ላይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እሱ እብድ ውሻ ነው፡፡ በራቢስ የተለከፈ ውሻ አሳዳጊውንም ይነክሳል፤ጎረቤትም እንስሳም ይናከሳል፡፡ ከዛ ሁሉም በለው ግደለው ብለው ይገድሉታል፡፡ አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት አሸባሪው ህወሓትን ከምድረገጽ ያጠፉታል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ቀደም በትግራይ ቅርንጫፍ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንደመስራቶ፤ ከዚህ ቀደም የሽብር ቡድኑ አባላት የሚያነሷቸውን ወቀሳዎች ጨምሮ ድምጹ በጉልህ ይሰማ የነበረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሸባሪው ህወሓት በንጹሀን ላይ ጥቃት እያደረሰ ድምጹ መጥፋቱን እንዴት ያዩታል?
አቶ ገብረጻዲቅ፡– ሲጀመር ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ነው ብሎ መጥራት አስቸጋሪ ነው፡፡ ችግር የነበረበት ተቋም ነው፤ ለምሳሌ ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር እያለ እኔ እዛ ነበርኩ እና ስንጨቃጨቅ ነበር፡፡ እኔ የህግ ተማሪ ስላልሆንኩ ምርመራው ውስጥ አልገባም ነበር የኢኮኖሚክሱን ነው እሰራ የነበረው፡፡ ግን ፖለቲካው ይገባኛል፤የሚሰራው ስራ ውጤታማ አልነበረም፡፡ መነሻው ጥሩ ያልሆነ ተቋም ለመሻሻል ጊዜ ይወስዳል፡፡
የአክሱም አካባቢን አጥንተናል ብለዋል፡፡ ጠንካራ ስላልሆነ ነው እንጂ አማራ እና አፋር ገብተው መመርመር ነበረባቸው፡፡ አሁን ያወጡት ምንድነው ሰላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ የሚል ነው እና ተቋሙ ጠንካራ አይደለም፡፡ እዛ ውስጥ ደግሞ የተሰገሰገ አመራርም ይኖራል፡፡ አሁን ጦርነት ካላ ሞት ውድመት መደፈር ይኖራል፤ ይሄን መውሰድ ይገባናል፡፡ ግን እንደሚባለው ነው ወይ አሁን 4 ሆነው ደፈሩ ይባላል፡፡ እራሱ አሸባሪው ህወሓት ያቀነባበረው ነው፡፡ አራት ሴት የደፈራት ሴት ማናት ብለሽ ወደቀበሌው ቢኬድ አትገኝም፡፡ ይሄም ወደፊት እናጣራለን፡፡
አዲስ ዘመን፡– የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ከሌላ ጉዳዮች የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በተደጋጋሚ ስለትግራይ ክልል አጀንዳ ማድረጉ ከምን የተነሳ ነው?
አቶ ገብረጻዲቅ፡– ፖለቲካ ማለት ከኢኮኖሚ ተለይቶ አይታሰብም፡፡አሸባሪው ህወሓት ሁለቱን ስለያዘ ነው ኢትዮጵውያንን የተጫወተብን፡፡ ኢኮኖሚውንም ፖለቲካውንም ተቆጣጥሮ የኮንትሮባንድ ነጋዴም በሁሉ ጉዳይም ፈላጭ ቆራጭም ነበር፡፡ አፍሪካ ውስጥ በተለይ እኛ አካባቢ ቻይና ተቀባይነት እያገኘች ነው፡፡ ቻይና ገባች ማለት አሜሪካ ገበያ ታጣለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ለ20 አመታት የትግራይ ህዝብ ተዘግቶበት ከወንድም እህቶቹ ተነጥሎ የነበረውን እንደ ጀርመን ግንብ አፈረሱት፡፡ ይሄ ለውጥ ያመጣው ፍርሀት አለ፡፡ ከዛም ከሶማሊያ እና ከኤርትራ ጋር የተደረገው ስምምነት ስጋት ላይ ጥሏቸዋል፡፡ ይሄ ፍርሀት እና ለአሜሪካ የምትላላከው ግብጽ ፍላጎት ታክሎበት ነው አሜሪካ ትግራይ ትግራይ የምትለው፡፡
ጠንካራ ኢትዮጵያ ማለት ጠንካራ አፍሪካ ስለሆነ ይሄ እንዳይፈጠር፤ ለሸቀጣቸው ማራገፊያ እንዳያጡ እና አሻንጉሊት መሪ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከማንም ሀገር አልነካካም፤ ሀገሬን ግን አሳድጋለሁ ብለዋል፡፡ ይሄ በመርህ ነው፡፡ እነሱ ይሄን መርህ አይከተሉም፡፡ ቀጠናውን ብታይ ሱማሊያ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገ ነው፤ አሜሪካ የምትፈልገው ብቻዋን መቆጣጠር ነው፡፡ አሁን ግን ቻይና ሩሲያ ቱርክም መኖራቸው አላስደሰታትም፡፡
እነሱ የተኩስ አቁም አርጉና ከአሸባሪ ቡድን ጋር ተደራደሩ ነው የሚሉት ይሄ ግን የእኛ የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ እኛ ነን ወሳኞቹ፡፡ ዳግም የአሻንጉሊት አመራር ወደስልጣን አይመጣም፡፡ የአሸባሪውን ህወሓት እድሜ ማሳጠር ለሁሉም መፍትሄ ነው፤ የእሱ እድሜ ሲያጥር እነግብጽም ምንም የሚያመጡት ነገር አይኖርም፡፡ ፍላጎታቸው አሻንጉሊት ሆኖ ለእነሱ የሚላላክ መንግስት መመስረት እና ዞኑን መቆጣጠር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ገብረጻዲቅ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/2013