ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተደጋግሞ ሲባል የኖረን እውነታ ቢያሰለችም ዛሬም ደግመን እናስታውሰው፡፡ “አዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ አህጉርም ዋና ከተማ ጭምር ነች፡፡” ይህንን አባባል የምናስታውሰው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ ግልጽ መሆን ስላለበት ነው፡፡ የአፍሪካ ዋና ከተማነቷ በርግጡ “ለፖለቲካ መዲናነት ነው ወይንስ ባህልን ያካትታል?” መልሱ እጅግም ሩቅ ማማተርን አይጠይቅም፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለአህጉራችን የዋና ከተማነቱን “ታሪካዊ ቁልፍ” ያስረከቡት ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር “የባህሉንም ጉዳይ” ታሳቢ አድርገው ነበር ብንል ትርፉ ምጸት ይሆናል፡፡ ለምን ቢሉ ትናንትም ሆነ ዛሬ ታስቦበት ስለመሆኑ አልተገለጸልንም ወይንም አልታሰበበትም፡፡
የባህልና የፖለቲካ ማዕከልነትን አጣምሮ መያዝ ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ተወካዮች በዋና ከተማችን በሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት ጽ/ቤታቸውና የመሰብሰቢያ አዳራሾቻቸው ውስጥ በዋነኛነት የሚገናኙት በራሳቸውና ከሌሎች ሀገራት ጋር ባላቸውና ሊኖራቸው በሚገቡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የፀጥታና መሰል የመደጋገፊያ ስልቶችና ስትራቴጂዎች ላይ ለመመካከር እንጂ ስለ አፍሪካ አህጉር የጋራ የባህል እሴቶችና ትሩፋቶች ልብ ለልብ ተወያይተው ወደ አንድ ሀሳብ ለመድረስ እንዳልሆነ ቀርፀው የተወያዩባቸውን አጀንዳዎች በሙሉ ለመፈተሽ ቢፈቀድልን እውነቱን ማረጋገጥ አይከብድም፡፡ ቢሆንልንማ ኖሮ በባህል አዝመራዎቿ ላሸተችው አፍሪካችን አንድ ታላቅ የባህል ማዕከል በዚሁ በአዲስ አበባችን ተመስርቶ በቀለመ ደማቅ ፀጋዎቿ “ዓለምን ጉድ የሚያሰኝ” ውጤት ባስመዘገብን ነበር፡፡ “ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ!” አለ ብሂለኛው፡፡
ይህንን ግዙፍ ርዕሰ ጉዳይ ጊዜ በፈቀደ መጠን ደግመን ደጋግመን እየመዘዝን ስለምንወያይበት ለዛሬው ጥቁምታው በቂ ስለመሰለን ወደ ዋናው የመነሻ ሃሳባችን እናዘግማለን፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአዲስ አበባ ክብርት ም/ከንቲባ እየተጉ ካሉባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል አንዱ “ለ…ክልለ/ዞን የባህል ማዕከል መገንቢያ የቦታ ካርታ አስረከቡ” የሚለው ዜና ከዋና ዋና የፖለቲካ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ክልሎች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ዞኖችም ዕድሉ እንደደረሳቸው ልብ ይሏል፡፡
የፌዴራል መንግሥቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ክልሎችና ዞኖች በምልዓትና “በይገባኛል ባይነት” የባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታ የመጠየቅ መብትና ሥልጣናቸው እስከ ምን ድረስ በፀና ውሳኔ እንደተደነገገላቸው ለጊዜው እጃችን የገባ መንግሥታዊ ሰነድ ለማግኘት አልቻልንም፡፡ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 91 “ባህል ነክ ዓላማዎች” በሚል ርዕስ ሥር የተጠቀሱት ሦስቱ መሠረታዊ ጉዳዮችም የተብራራ መልስ አልሰጡንም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ በምትመራበት ሕግ ላይ “የባህል ማዕከላት መገንቢያ ቦታ ክፍፍልን” በተመለከተ የተደነገገ ጉዳይ ስለመኖሩ አላጣራንም፡፡ ይኖር ከሆነም የአስተዳደሩ ካቢኔ መፍቀዱ ብቻም ሳይሆን የሚዲያ ዜናውም “በሕጉ መሠረት ስለመፈጸሙ” ቢጠቀስ ኖሮ ከብዥታ ይገላግለን ነበር፡፡
ለማንኛውም ግን እየተገነዘብን ያለነው ፖለቲካዊው ውሳኔ ፈጣንና የቸርነቱም እጅ ሰፊ መሆኑን ነው፡፡ እንደ አንድ ሀገር ዜጎች ውሳኔው አያስከፋንም፡፡ ሁሌም የምንከፋው በአንድ መሠረታዊ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ እንደ ከፋን ኖረን እንደ ከፋን መሞቱን ስናስብም ይበልጥ ሆድ ይብሰናል፡፡ ለሚያብከነክነን ጉዳይ ምክንያቱ ይህ ነው “አይዟችሁ አትከፉ!” የሚለን አጽናኝ መሪ ማጣታችን ይበልጥ ግርታ ፈጥሮብናል፡፡ ስለዚህም መከፋታችን ዕለት ተዕለት ቢጨምር አይፈረድብንም፡፡
የመከፋታችን ምክንያቱ ምንድን ነው? የፖለቲካ መሪዎቻችን ይህን መሰሉ ጥያቄ ባይጥማቸውም በጥቂቱ ያመቅነውን ስሜት እንደ ዘርፉ ባለሙያ መተንፈሱ አይከፋም፡፡ የፖለቲካው ምድብተኞች “ሥልጣነ መንግሥት የጨበጥነው ውጣ ውረድ የበዛበት ፈተና አልፈን ነው” ብለው እንደሚያምኑት ሁሉ ዜጎችም “በሰለጠንኩበት ሙያዬ የብቃት ማረጋገጫ ያገኘሁት ላብና መስዋዕትነት ከፍዬ ነው” ብለው “ስሙኝ” እያሉ ቢሟገቱ አግባብ ይመስለናል፡፡ ስለዚህም የምክንያቱ ሥረ መሠረት ለሕዝብ በአግባቡ ሳይገለጽ እንዲፈርስ የተደረገው የቀድሞው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል” በማን ውሳኔ፣ ድፍረት፣ ለምንና በምን ተጠየቅ እንዲንኮታኮት እንደተፈረደበት ብናውቅ ኖሮ እስከዚህም ባላማረርን ነበር፡፡
ይህ “ብሔራዊ የባህል ማእከል” መሠረቱ በተጣለበት ወቅት ተጠርቶ ለነበረው ታላቅ ሀገር አቀፍ ጉባኤ ሚያዝያ 25 ቀን 2004 ዓ.ም “ብሔራዊ የባህል ማዕከል ለሀገርና ለሕዝቦች የጋራ ጥቅምና ትስስር” በሚል ርዕስ ዘርዘር ያለና ጥልቅ የሆነ ጥናት ያቀረበው ይህ ጸሐፊ ነበር፡፡ ይመለከተኛል ባይ ክፍል በዚህ ወቅት መድረክ ቢያዘጋጅ ዐውድና ወቅቱን በዋጀ ሁኔታ ድጋሚ ጥናቱን ለማቅረብ ጸሐፊው ዝግጁ ነው፡፡ ጥረቱና ድካሙ “በነበር አያኮራም” ቢሂል ተድበስብሶ ፉርሽ የሚደረግ ከሆነም ችግር የለውም፤ እንደተከፋን እናልፈዋለን፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል የተቋቋመበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ 258/2004 ታህሳስ 19 ቀን 2004 ዓ.ም በሥራ ላይ አለ ወይንስ ተሽሯል? ለእኛ ተራ ዜጎች ይሄኛው ጥያቄ ተብራርቶ ቢገለጽልን አንጠላም፡፡ “ሰነድና ማስረጃ አታጣቅሱ፤ ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው!” ከተባለም ከተራራ ጋር ስለማንጋፋ “አፉ!” ይበሉን፡፡ ለማንኛውም ግን አስር ጊዜ ጠይቀን አስር ጊዜ ባይመለስልንም አስር ጊዜ ጠይቀን ለታሪክ ጭብጣችንን ማስመዝገባችን ግን አይቀርም፤ ግድም ነው እንጂ ጎበዝ፡፡
ወደ መነሻ ጉዳያችን እንዝለቅ፡፡ ክልሎችም ሆኑ ዞኖች በአዲስ አበባ ከተማ የራሳቸው የሆነ የባህል ማዕከል ቢኖራቸው መብታቸው ብቻም ሳይሆን በፌዴራል መንግሥቱ የቤተሰብ አባልነታቸው ማንም ተቃውሞ ሊያቀርብባቸው አይገባም፡፡ በተለይም የፖለቲካው ትኩሳት ከዕለት ዕለት በራስ ህመም የሚያሰቃያት አዲስ አበባችን በውሳኔ እየፈጠነች ለተዥጎረጎረው የገመናዋ ችግሮች የመሰላትን በመወሰን ቀን መግፋቷም መብቷ ነው፡፡ ችግሩ ዛሬ ጎንበስ ብለን የምንተክለው የውሳኔ ችግኝ ነገ ተነገወዲያ ረዝሞና ፈርጥሞ የተንዠረገገ ፍሬ በማፍራት ሲጎመዝዘን እንዳይኖር ነው፡፡ ብዙ መፍጠኑ ለብዙ ችግር እንዳያጋልጠን ማሳሰቡ እንደ ባለሙያና ተቆርቋሪ ዜጋ ግድም ውድም ነው፡፡ “ብዙ መፍጠን ብዙ መዘግየት ነው” የሚለውን ብሂል ማስታወሱም አይከፋም፡፡ አስተዳዳሪዎቻችንም እንዲህ ዓይነት ሙያዊ አስተያየት ሲቀርብላቸው በሆደ ባሻነት ፊታቸውን አኮሳትረው እንዴት እንደፈራለን ባይሉ እንወዳለን፡፡ ለነገሩ በጣት አሻራችን ፈርመን ከሥልጣን መንበር ላይ ከፍ ያደረግናቸው እኛው ተራ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ማቲዎች አይደለን፡፡
ለክልሎችና ለዞኖች የባህል ማዕከል መገንቢያ መሬት እየሸነሸኑ መለገሱ ባልከፋ፡፡ ነገር ግን ለአፍሪካና ለዓለም ምሳሌ መሆን የሚችል አንድ ጠንካራ ሀገራዊ የባህል ማዕከል በመገንባት “ግዙፍ የኅብረ ብሔር ሙዚዬምነታችንን” ማረጋገጡ አይሻልም ነበር ወይንስ እያንዳንዱ ክልልና ዞን የግሉን ሩጫ ቢሮጥ ይመረጣል? ይህ ጸሐፊ የሰለጠነው በባህል ላይ ትኩረት በሚያደርግ ዋነኛ የጥናት ዘርፍ ላይ ስለሆነ ሁሌም የሀገሩ የባህል አመራርና አተገባበር እንዳሳሰበው አለ፡፡
የኢትዮጵያ ባህሎችን ውበትና ምጥቀት በጋሞ የሽመና ጠቢባን የሀገር ባህል ጥበብ ውጤት መመሰሉ ጉዳዩን አያሳንሰውም፡፡ የሀገር ባህል አልባሳቱ ጥበባት የኅብረ ቀለማት ውበትና ድምቀት ውቅር አጃኢብ የሚያሰኝ ስለመሆኑ ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል፡፡ ያምራል አይገልጸውም፡፡ ድንቅና ውብ ነው፡፡ የሐረር እናቶችና እህቶች ደማቅና የተዋቡ አልባሳትም ለዓይን ውበትን ለስሜት እርካታን የመስጠት ብርታታቸው ከ እስከ ከ የሚባል አይደለም፡፡ ባህሎቻችን አንድ ላይ ተዋህደው ሲቀርቡ የሚፈጠረው ስሜት ከማሳያዎቻችን ከፍ ያለ ገለጻ ቢያስፈልገው እንጂ አይበዛበትም፡፡
ክልሎችና ዞኖች በአንድ ጣሪያ ሥር ተዋህደው ባህሎቻቸውን ቢያስተዋውቁና ቢያሳድጉ ይሻላል ወይንስ በተናጥል እዚያና እዚህ ተበታትነው “እኔ ለራሴ ብቁ ነኝ” እያሉ ጎጆ ቢያዋቅሩ ይበጃል? የመሬቱ ችሮታስ ለማን ተሰጥቶ ለማን ይቀራል? ለጠየቀው ሁሉ የሚታደል ከሆነስ የአዲስ አበባን ውሱን የመሬት ሀብት ከሰማኒያ በላይ ብሔረሰቦች አሉኝ ለምትል ሀገር አከፋፍሎ ማስደሰት ይቻላል? ደግሞስ መሬቱ ተሰጥቶ ሁሉም ብሔረሰቦች የባህል ማዕከላቸውን ገንብተው ካጠናቀቁ የከተማዋ መታወቂያ እንዲጎላ የሚፈለገው በባህል ማዕከላት መናኸሪያነት ነው? ወይንስ…?
ነገ ተነገወዲያ የአፍሪካ ሀገራት በዚህ ውሳኔ ተበረታትተው “መዲናችን” ከሚሏት አዲስ አበባ ልክ መንገድ በስማቸው እንደተሰየመው ሁሉ የባህል ማዕከላቶቻችንንም እንድንከፍት መሬት ይሰጠን ቢሉ ያስኬዳል? ይህንን የመሰለ ጥያቄ ለመጠየቅ እንኳን ባይደፍሩ በጋራ ለምንገነባው ግዙፍ የባህል ማዕከል ዐይነ ግቡ የሆነ ቦታ ተመርጦ ይሰጠን ቢሉ ይቻላል?
ይኼ ሁሉ ግምታዊ ፍርሃት ለጊዜው አያሰጋንም ብለን ሃሳቡን ውድቅ ብናደርግ እንኳን ለመሆኑ ክልሎችና ዞኖች በሚገነቡት ማዕከላት ውስጥ ምን ምን ተግባራት ይከውኑባቸውል? ከሌሎች ጋርስ እንደምን ጥረታቸውን ያስተባብራሉ? ጠንከር አድርገን ስጋታችንን እናጉላው ከተባለም የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ዜጋ በአንድ ጣሪያ ሥር ያበቡ የባህል ትሩፋቶችን መጎብኘት ይቀለዋል ወይንስ “እዚያም የእከሌ ክልል የባህል ማዕከል አለ፣ እዚህም እነ እከሌ አሉ ወዘተ…” እየተባለ ጎብኚዎች ቢንከራተቱ ይመረጣል? አንድነትና ወዳጅነት ፓርኮችስ ትምህርት አልሰጡን ይሆን?
ቋንቋን መሠረት አድርጎ የተዋቀረው የሀገሪቱ ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ትቶብን ያለፈው ቁስል ገና ጠግጎ ሳይፈወስ ይብስ እንዲሉ “ክልሎችና ዞኖች በአንድ ከተማ ውስጥ ራሳቸውን እንዲከልሉ” ከማበረታት ለምን ብሔረሰቦች በአንድ ጣራ ሥር ተሰባስበው እንዲደምቁና እንዲያሸበርቁ አልታሰበበትም? የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፍልስፍና በባህል ማዕከላት ግንባታው ላይ አይሰራም ይሆን ወይንስ…? በባህሏ የከበረችው፣ በብሔረሰቦቿ ትውፊት የበለፀገችውና በልጆቿ አንድነት ተከብራ የኖረችው ባለዝናዋ ኢትዮጵያ የምትጠቀመው ተሰባስቦ ታላቅ በመሆን ወይንስ ለየብቻ እየሮጡ ታላቅ ለመባል ራስን ማሳየት?
አንድ መለስተኛ ጥያቄ እናክልበት፡፡ የተትረፈረፉ የሀገሪቱ ባህሎች ከተከማቹባቸው የሕዝባዊ ክዋኔ “ጎተራዎች” ባልተናነሰ ሁኔታ የኪነ/ሥነ ጥበባት ማኅበራትም ድርሻቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ማኅበራቱ የሚጠበቀውን ያህል ባለመስራታቸው ያንክሱም ያጉብጡ ብቻ ራሳቸውን በብሔራዊ ማኅበራት አደራጅተው እስትንፋሳቸው ጭል ጭል ማለቱ አልቀረም፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን፣ ሠዓሊያንና ቀራጺያን፣ ሙዚቀኞች፣ ተዋንያን፣ ሠርከስ፣ ውዝዋዜና ፋሽን በሚል አደረጃጀት ተዋቅረው “የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ሠርቲፊኬት” መውሰዳቸው ይታወቃል፡፡ ለእነዚህ የባህል “አምባሳደር” ማኅበራት በግል እንኳን ባይሞከር በጋራ የባህል እንቅስቃሴ መከወኛ ማዕከል እንዲገነቡ ቢበረታቱ አይመጥናቸውም ይሆን? ዘመን-ዘለቅ ጩኸታቸውስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተደምጦላቸዋል? ወይንስ ፖለቲካዊው ውሳኔ እነርሱን አይመለከታቸውም፡፡
በዚህ አጋጣሚ የደጋፊዎች እጅ አጥሮት እስከ ዛሬ ድረስ ዳዋ ለብሶ ተከልሎ ቢቆይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአፍሪካ ደራስያን ዋና ጽ/ቤት መገንቢያ እንዲሆን ለኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ስለሰጠው ቦታ ከወንበራችን ከፍ ብለን ባናመሰግን የብዕራችን አምላክ ቅር የሚለው ስለመሰለን ባለውለታችን ሆይ “ገለቶማ!” እንላለን፡፡
ብዕርና ሀብት ጀርባና ሆድ ለሆኑበት ማኅበርም ማዕከሉን ለመገንባት የተባረኩ እጆች እንዲዘረጉለት ማስታወሻ ማኖሩ አይከፋም፡፡ የባህልን ጉዳይ በተመለከተ “ባለፀጋ ነኝ!” ባይዋ ሀገሬ ትሩፋቶቿን ምን ያህል ለዓለም እንዳስተዋወቀች ሁላችንም የምንረዳውን ያህል እንረዳለን፡፡ ለአብነት ያህል ጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ባህሏን አጎልብታ በኢኮኖሚውና በሕዝቦቿ የሥራ ባህርይ ላይ ያመጣቸው ለውጥ ፍንትው ብሎ የሚታይ ነው፡፡ የቻይና የደቡብ ኮሪያና የእስራኤል ታሪክም ከዚህ እውነታ ያፈነገጠ አይደለም፡፡ የእነዚህን ሀገራት ተሞክሮ ልባችንን ከፍተን ብንማር ብዙ እውቀት መገብየት ይቻላል፡፡ ቀጥሎ የምጠቅሰው ዘለግ ያለ ጽሑፍ ከማከብረው መምህሬ ከዶ/ር ፈቃደ አዘዘ አንድ የጥናት ጽሑፍ ላይ የተወሰደ ስለሆነ ሃሳቤን በአግባቡ ይጠቀልል ስለመሰለኝ ለማሳረጊያነት ተጠቅሜበታለሁ፡፡
“ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህልን መሰብሰብ፣ ማጥናትና መተንተን ለልማት አስተዋፅኦ አለው? የእኔ አጭር መልስ – አዎ አለው! የሚል ነው… አንድ የልማት ሥራ ሲታሰብ ሥራውን ይሠራል ተብሎ የሚታሰበው ሰው ፍላጎት፣ እምነት፣ የሕይወት ፍልስፍና የመኖሪያ አበይት እሴቶች፣ ክሂሎቶች ወዘተ… መታወቅ አለባቸው፡፡ እነዚህን ለማወቅ ደግሞ የተለያዩ ባህሎቹን…(ማለትም ተረቶቹን እንቆቅልሾቹን የሕይወት ፍልስፍናዎቹን የሸክላና የአንጥረኛ ስራዎቹን የልዩ ልዩ እምነቶቹን እሴቶች እና አምልኮዎቹን ወዘተ…) ማጥናት ይገባል፡፡ በዚህ መልክ ባህሉን አውቆ ሊሰራ የታቀደውን ስራ በዚያ ‹የባህል ማዕከል› ውስጥ አቀልጥፎ እንዴት ማከናወን እንደሚቻል አስቦ ልማቱን መከወን ይገባዋል፡፡ የውጥኑና የስራው ንቁ ተሳታፊና ፈቃደኛ አካል ዋና ተዋናይ እና ጠንካራ ኃይል አድርጎ መራመድ ካልተቻለ ግን የልማቱ ስራ ችግር ይገጥመዋል፡፡ በጥቅሉ ሲነገር ባህል ለልማት አስተዋፅኦ ያደርጋል ማለት ይኸው ነው፡፡” የእኛው የባህል ማዕከላት ግንባታ የግል ሩጫ የት ደርሶና የት ደርሰን እናይ ይሆን! “ቦ ጊዜ ለሁሉ!”፡፡ ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/2013