አቶ ዳኛቸው ወርቁ ሳልለው ይባላል:: ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከባድ ክህደት ፈፅሞ ያልተጠበቀ ጥቃት ከተፈፀመ ጀምሮ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ከባድ ሃዘን ተናግሮ የማይወጣለት ቁጭትና በቃላት የማይገለፅ እልህ በውስጡ ይዟል:: ታዲያ መቆጨት ብቻ ሳይሆን በሙያው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል:: በአሽከርካሪነት ሙያ 17 ዓመታት ያገለገለ ሲሆን በዚህ ሙያ ሀገሩን ለማገዝ ወደ ግንባር ከዘመቱ ጀግና አሽከርካሪዎች ቀዳሚው ሰው ነው::
በመጀመሪያ ዙር ሦስት ወር ቆይቶ ወደ ቤተሰቡ ተመልሶ ነበር:: በሁለተኛው ዙርም ግንባር ዘምቶ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ተወጥቷል:: ለኃላፊነቱም የምዕራብ ዕዝ የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ለፈፀመው ጀብድ ሁለት የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል:: ዳኛቸው አሁንም ለእናት ሀገሩ በየትኛው ቦታ ለማገልገልና ኢትዮጵያን ለመታደግ ዝግጁ ነው:: ሀገር ከሌለች እኔም፣ ልጆቼም የልጆቼም እናት መኖራችን የማይታሰብ ነው የሚለው ዳኛቸው ስለ እናት ሀገሩ ሠላም፣ ነጻነትና አንድነት መከበር እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመስጠት ዝግጁ ነው:: በዛሬው ዕትማችን አሽከርካሪዎች በህግ ማስከበር ዘመቻው በጦር ግንባር ስለነበራቸው ሚና፣ የሰራዊቱ ወኔ እና ስለነበሩት ገጠመኞች ይነግረን ዘንድ እንግዳችን አድርገነዋል::
አዲስ ዘመን፡- ወደ ዘመቻ የሄድከው መቼ ነው?
አቶ ዳኛቸው፡- ወደ ግንባር የሄድኩት የአሸባሪው ህወሓት ጁንታ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በወሰደው ዘግናኝ ጭፍጨፋ በሙያዬ ኃላፊነቴን ለመወጣት ነው:: የሀገር አቋራጭ አውቶብስ ሹፌር ስሆን ስራዬ ሰራዊቱን ማጓጓዝ ነበር:: ግን ነገሩ ተቀይሮ ወታደር ሆኜ ነበር::
በወቅቱ ባለቤቴ ወልዳ አራስ ነበረች:: እቤት ትቼያት ነው የሄድኩት:: ይህ ለእኔና ለቤተሰቤ ከባድ ነበር:: ግን በቦታው ላይ ደርሰህ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈፀመውን ስትመለከት እዚህ ያለውን ሙሉ ለሙሉ ትረሳለህ:: በቃ እዚህ ሰላም ነው:: ነገር ግን ከፈጣሪ ቀጥሎ ሀገር የሚጠብቅ የሀገር ሰራዊት ላይ ያንን የመሰለ ግፍ ተፈፅሞ ስትመለከት ሁሉም ነገር ትዝ አይልህም:: በሃሳብህ፣ ውሎህ እና አስተሳሳብህ በሙሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ይሆናል:: ሁኔታው እጅግ ክፉና አሰቃቂ ስለነበር ሳስበው ማመን ይከብደኛል:: በመጀመሪያው ዘመቻ ከቤት ስወጣ መደበኛ ሥራ ነው ብዬ ነው ከቤት የወጣሁት:: ቦታው ከደረስኩ በኋላ ስልክ የማይሠራ ቦታ ልገባ እንደምችል ማሳወቅ ነበረብኝ:: ሁኔታውን ለባለቤቴ ሳስረዳት ለሀገርህ እስከሆነ ድረስ በርታ ብላ ተለያየን:: እኔም ቀጥታ ወደ ጦር ግንባር ነበር የገባሁት::
አዲስ ዘመን፡- ሁለት ህፃናት እና አራስ ባለቤትህን ተከራይተህ በነበረበት ቤት ነው ጥለሃቸው የወጣኸው:: ይህስ ነገር አላሳሰበህም?
አቶ ዳኛቸው፡- ሌላ ጊዜ ለሥራ ስወጣ ገዛዝቼ የምመጣው ነገር አለ:: አሁን ይህ ቀርቶ ነብስ መትረፍ አለመትረፏም እርግጠኛ መሆን አይቻልም:: ግን ለሀገር ስለሆነ አትፈራም:: እንደ ዕድል ሆኖ መልካም አከራይ ነው የገጠመኝ:: አብረውኝ የነበሩ ሌሎች አሽከርካሪዎች ግን ሁኔታው ያሳስባቸው ነበር:: አጠገቤ በአጋጣሚ በፈንጅ የተሰዋ ሰው ነበር:: እኔ እና የተሰዋው ሰው አንድ ትምህርት ቤት ነው ልጆቻችንን የምናስተምረው:: ስለቤተሰቡ በጣም ያስብ ነበር:: በእርግጥ እኔ ምንም ዓይነት ችግር ቢገጥመኝ አከራዮቼ ልክ እንደእኔ ለልጆቼ እንደሚያስቡና እንደሚንከባከቡ ስለሚገባኝ ብዙም አልጨነቅም ነበር:: ባለቤቴም በጣም ጠንካራና በሀገር ጉዳይ ከማንም ጋር የማትደራደር ሀሞተ ኮስታራ ናት:: ግን የጓደኛዬን ነገር ሳስበው አሁንም ከባድ ነው:: ባለቤቱ ችግር ላይ ናት::
አዲስ ዘመን፡- መጀመሪያ የት ግንባር ነው የሄድከው?
አቶ ዳኛቸው፡- ከሁርሶ ወደ ቆቦ ነው የሄድኩት:: ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ቆቦ ደረስኩኝ:: ከባድ ጦርነት ነበር:: በዚያው ሌሊት ወደ ጎንደር ነው ያመራሁት:: ከጎንደር ሰራዊቱን ጭነን ወደ ሑመራ ገባን:: ከዚያ ወደ ሽሬ ካምፕ ገባን:: ከዚያ በምሽት ወደ ደደቢት በረሃና አስፈላጊ ቦታዎች ስንቀሳቀስ ነበር:: በዚህ ጉዞ ውስጥ ድካም የሚባል ነገር አልነበረም:: ሀገር የማዳን ጥሪ እስከሆነ ድረስ ሌት ተቀን መሥራት ግዴታ ነው:: ሰራዊቱ ህይወቱን እየገበረ ምንም ወደ ኋላ ማለት የለም:: ሁሉም ነገር በሀገር ፍቅር ወኔ የሚከናወን ስለሆነ የአዲስ አበባ ጣጣ ይረሳል:: ሁሉ ነገርህን የምትሰጠው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ነው:: የመከላከያ ጥረትና ወኔውን ስታይ ጀግንነት ይሰማሃል::
አዲስ ዘመን፡- ሰራዊቱን ከቦታ ቦታ ስታጓጉዝ የነበረው ስሜት ምን ይመስላል?
አቶ ዳኛቸው፡- በተዓምር ሰራዊቱ ላይ የፍርሃት ስሜት አይታይባቸውም:: ስለቤተሰብ ማሰብና ወደ ኋላ መንቀራፈፍ የለም:: የሚያስቀድሙት ሃሳብ ጠላትን እያጠቁ ድል ማድረግ ነው :: ይልቅስ እነርሱ የሚያስቡት ለሲቭል ማህበረሰብ ነው:: ጭራሽ እኛ አሽከርካሪዎች እንጀራ ባለመብላታችን ይጨነቁልናል:: ከተማ ብትሆኑ የተለያየ ምግብ ትበሉ ነበር ይሉናል:: የራሳቸውን ሬሽን እያካፈሉን እየተሳሳቅን ነበር የምንጓዘው:: በእርግጥ አርሶ አደሩ በየቦታው ምግብና ውሃ ያቀርባል:: እነርሱ ግን ዋና ዓላማቸው ሀገር ማዳን ስለሆነ ጊዜ አልነበራቸውም፤ እረፍትና እንቅልፍ አይናፍቃቸውም:: ምግብ ለመከላከያ ምኑም አይደለም:: የሚያስቡት ጠላትን ማንከት ብቻ ነው:: ዲኮር የሆነ ምግብ ምናቸውም አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- በጦር ግንባር የተጎዱ ቁስለኞች በማጓጓዙ ረገድ ተጎጂዎች ዘንድ የነበረው ሁኔታ እንዴት ነበር?
አቶ ዳኛቸው፡- ቁስለኞችን ከአንዱ ቦታ ወደሚታከሙበትና ትዕዛዝ ወደሚሰጠኝ ቦታ አጓጉዝ ነበር:: ራሳቸውን ችለው የማይንቀሳቀሱ ካሉ ተሸክሜ አስገባለሁ:: በሙያዬ እና በጉልበቴ የምችለውን ነገር ሁሉ ሳግዝ ነበር:: ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ይህን አደረኩኝ ብሎ አይወራም:: እኔ ለእነርሱ ልፋትና ትጋት ብሎም ታማኝነት ነፍሴን ብሰጥ አይቆጨኝም:: በቃ ለእነርሱ ውለታ መክፈል ከባድ ነው:: እኔ ይህን አደረኩኝ ብዬ ራሱ ማውራት ይከብደኛል:: እነርሱ እኮ አንዲት ነብሳቸውን ነው ለእኔ እና ለሀገሬ እየሰጡ ያሉት:: ከምንም በላይ የሚገርመው ደግሞ ቁስለኞች በፍጥነት አገግመው ወደ ጦርነት ተመልሰው ጠላትን ለመደቆስ ሲቻኮሉ ስታይ ይደንቃል:: የተመታ ሠራዊቱ ደሙ እየፈሰሰ ተውኝ ወደ ህክምና አትውሰዱኝ አቅም አለኝ፤ ከጓዶቼ ጋር መዋጋት እችላለሁ ብለው የሚከራከሩ ነበሩ:: ወደ ከተማ መሄድ አይናፍቃቸውም::
ብዙ ተዓምር ታያለህ:: አንድ አማራ ሰራዊት ሲሰዋ የኦሮሞ ሰራዊት እንዴት እንደሚጸጸትና ደረቱን እንደሚደቃ ስታይ ይገርምሃል:: አንድ ሲዳማ ሲሠዋ ወላይታው እንዴት እንደሚቆጨው ብታይ ማመን ይከብዳል:: አንድ የጋምቤላ ተወላጅ ሰራዊት አባል ሲሰዋ ወይንም ሲጎዳ ሀረሪው፣ ጉሙዙ፣ አማራው፣ ኦሮሞው፣ ሲቆጭና በእልህ ሲነሳሳ በእጅጉ ትገረማለህ:: አንድ ጓዳቸው ሲሰዋ ሌላው በእልክ ነው የሚነሳሳው:: አንድ የሰራዊት አባል ሲሰዋባቸው 10 ጠላት አርግፎ መበቀል ነው የሚፈልጉት:: መከላከያ ውስጥ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች መዋደዳቸው፣ መከባበራቸውና መተሳሰባቸውን ስታይ ትቀናለህ:: እዚያ ያለው ፍቅር መሃል ከተማ ቢኖር የት እንደምንደርስ አላውቅም:: በውስጣቸው ያለው የአንድነት መንፈሱ ይደንቃል:: ተጎድቶ ህክምና የማይፈልግ ሰራዊት አለ:: ደሙ እየፈሰሰ ሀገሬ ደሜ ይፍሰስልሽ እኔ ልሙትልሽ ብሎ ወደ ጦርነት እየፎከረ ይሄዳል::
የተወሰነ ቢሆንም አሽከርካሪ የመንግስትን እይታ የማየት አቅም አለው ብዬ አስባለሁ:: በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች እሄዳለሁ:: የብሄር ፖለቲካን ተምረናል የሚሉት የሚያራግቡት እንጂ ህዝቡ በፍቅር እየተንከባከበ ነው የሚቀበለን:: ኢትዮጵያዊ ከመሆናችን የዘለለ ብሄራችን አይገደውም::
አዲስ ዘመን፡- ሰራዊቱ ከድል በኋላ የሚያሳየው ስሜትስ ምን ይመስላል?
አቶ ዳኛቸው፡- ከድል በኋላ በጣም ደስ ይላል:: የሚናፈቀው ደስታ ነው:: በጋራ ደስታቸውን ይካፈላሉ:: የኢትዮጵያ ባንዲራ በእጃቸው ይዘው ሲያለቅሱ፣ ሲተቃቀፉ እና ያለውን ተካፍለው ሲበሉ አግራሞት ይፈጥራል:: አንዱ ለአንዱ አስቀድሞ የሚሰጥ ነው:: ሁሉ ነገር ቤተሰባዊ ነው:: የአንድን አካባቢ ከጠላት ሲያስለቅቁ የሀገራቸውን አደራ በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን በሚገባ ይገነዘቡታል:: ልክ እንደ አንድ ቤተሰብ ነው የሚተዛዘኑት:: የሀገር መከላከያ ዘንድ ያለው መተባበር እና ፍቅር እንደ ሀገር ቢተገበር ትልቅ የመሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል:: እኛም ከእነርሱ ጋር ሆነን ድሉን እናከብራለን፤ ማዕዱን እንቋደሳለን:: ደስታውን እንጋራለን:: እነርሱ ተታኩሰው ድል አድርገው ሲመለሱ እኛም ደስታችን ወደር የለውም::
አዲስ ዘመን፡- ትግራይ ክልል የነበረው አቀባበል ምን ይመስል ነበር?
አቶ ዳናቸው፡- በቀላሉ ለመግለፅ አስቸጋሪ ነው:: አሁንም ህወሓት ተመልሶ ሀገር ያስተዳድራል ብለው የሚያስቡ አሉ:: አፈር ልሶ ይመጣል ማንም አይችለውም ብለው ያስባሉ:: ሌላው ብሄር እንደ ትግራይ የአንድነት ስሜት የለውም ብለው ይናገራሉ:: ይህ ነገር በህዝብ ውስጥ የረጩት መርዝ ነው:: ተሸንፈውም መሸነፋቸውን ማመን አይፈልጉም፤ ደግሞም አያምኑም:: ሲሚንቶ የሚጭኑ እና ከሀገር ውጭ የንግድ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የመስቦ ተሽከርካሪዎች መድፍ ተጭኖባቸው ተይዘዋል:: የአመራሮቹ ተሽከርካሪዎች ከመሬት ውስጥ ተቆፍረው ወጥተው እኛ እያሽከረከርናቸው እየተመለከቱ እነ አቶ ስብሃት፣ አቦይ ፀሃዬ፣ አቶ ደመላሽ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ እና ሌሎችም ተመልሰው ይመጣሉ ብለው የሚያምኑ ሰዎች አጋጥመውኛል:: መሞታቸውን እንኳ ስንነግራቸው እንኳ መቀበል አይፈልጉም:: በውሸት ብዙ ሰው አሳምነዋል::
ህወሓትና ተከታዮቻቸው ውሸት አንዱና ትልቁ መሳሪያቸው ነው:: የሆነ ቦታ ሳይደርሱ ደረስን ብለው ያስወራሉ:: ብዙ ቦታዎችን ቀድመው ወረናል፣ ይዘናል ብለው በፌስ ቡክ ያስወራሉ:: የሚገርመኝ ይህን መረጃ አይቶና ሰምቶ የሚሸበረው ነው:: እኛ መሸበር የለብንም:: እነርሱ ውሸታቸው ከባድ ነው:: ሌላው ቀርቶ እኛ ሽሬ ገብተን የሀገር መከላከያ ከተማውን ተቆጣጥሮ እያለ ህዝቡን በውሸት ከመሙላታቸው የተነሳ ጀነራል ባጫ ደበሌ ተይዟል ብለው መቐለ ላይ ህዝቡን ሲያስጨፍሩ አድረዋል:: ጥዋት ግን ህዝቡ ከእንቅልፉ ነቅቶ ሲመለከት ከተማው በሙሉ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ሥር ነበር::
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት ለትግራይም ለኢትዮጵያም ዕድገት አምጥቻለሁ ብሎ ሲፎክር የኖረ ነው:: አንተ እንደ አንድ ሀገር አቋራጭ አሽከርካሪ ወደ አካባቢው ስትመላለስ ምን ታዝበሃል?
አቶ ዳኛቸው፡- በትግራይ አካባቢ የከተማው ሰው አልፎለት ሊሆን ይችላል:: የከተማው ሰው ነጭ በነጭ ለብሶ ነው የምናየው:: አርሶ አደሩ ግን ሁለት ሰዓት በእግሩ እየሄደ የጉድጓድ ውሃ የሚፈልግ ማህበረሰብ ነው:: 17 ዓመት በአሽከርካሪነት ሙያ ላይ ቆይቻለሁ:: እዚህ አካባቢ የተጎዳው እንጂ የተጠቀመውን ማየት አልቻልኩም:: ሌላው ቀርቶ ለትራንስፖርት መሣፈሪያ ሳንቲም እያጡ እየለመኑን ነበር በነፃ የምንጭናቸው:: አሁን ያለው ጦርነት ግን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ነው የሆነባቸው:: ሰው ያልበላን ለማብላት ይሠራል እንጂ፤ እንዴት ያልበላን እንደገና ላለማብላት ይጣጣራል፤ ይህ ነገር በጣም ያሳዝናል::
አዲስ ዘመን፡- ከሠው በተጨማሪ የተማረኩ ተሽከርካሪዎች ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱት እንዴት ነበር?
አቶ ዳናቸው፡- እኛ የራሳችንን ተሽከርካሪ አቁመን የተማረኩትን ተሽከርካሪዎች እንሰበስብ ነበር:: የእነርሱ አሽከርካሪዎችም አብረዋቸው ነበር የሚሠወሩት:: በአንድ ቦታ ላይ ከ60 እስከ 70 ተሽከርካሪዎችን ጥለው ይፈረጥጡ ነበር:: ብዙዎችን ደግሞ ቆልፈው ነበር የሚጠፉት:: መኪናው እንዳይንቀሳቀስ ቁልፉንም ይዘው ነው የጠፉት:: ግን የሀገር መከላከያ ያፈራቸው መካኒኮች፣ ባለሙያዎች እና አሽከርካሪዎች በጣም ጥበበኞችና እውቀታቸው የላቀ በመሆኑ በርካታ ተሽከርካሪዎች የተበጣጠሰ ኤሌክትሪካቸውን እያገናኘኝ ነው ስናስነሳ የነበረው:: አንስተንም በህጋዊ መንገድ ወደ ካምፕ ነበር ያስገባነው:: የሀገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥም የተቀናጀ ሥራ ነው የሚሠራው:: ጁንታው ሲሠራው የነበረው የክፋት ጥግ በሙሉ ይገርማል:: ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ተሽከርካሪዎቹ ናፍጣ ወይንም ቤንዚን ያላቸው እንደሆነ አፍስሰው ነው የጠፉት:: የሀገር መከላከያ ሰራዊት ግን በጣም ስርዓት በተሞላው መንገድ ሁሉንም ነገር ሲከውን ነበር:: እኛም በሚሰጠን ትዕዛዝ የሚጠበቅብንን ሁሉ ስናከናውን ነበር::
አዲስ ዘመን፡- ተሽከርካሪዎቹ ምን ዓይነት ነበሩ?
አቶ ዳኛቸው፡- በዓለም ውድ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን በሙሉ ይዘው ነበር:: በዓለም ውድ የሆኑ ክሩዝ ቮልቮ የሚባሉትን ለጦርነት ይጠቀሙ ነበር:: የመቐለ ዩኒቨርሲቲ እና የሌሎች ድርጅቶችን ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት ይጠቀሙ ነበር:: እንደዚያም ሆኖ እየተሸነፉ ሲፈረጥጡ መንገድ እየቆረጡ ነው የሄዱት:: ይህ ግን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ካለው ብቃትና ቆራጥነት አኳያ በጣም ቀላል ነበር:: የተቆረጠውን መንገድ በደቂቃዎች እየተጠገነ እናልፈው ነበር:: በመጨረሻም እየፈረጠጡ ወደ ዋሻቸው ነበር የገቡት:: ፉከራቸውና ቀረርቷቸውን ስትመለከት አንድም እርምጃ የሚሸሹ አይመስልም:: ነገር ግን የሀገር መከላከያ፣ የክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻዎች የሚሰነዝሩትን ከባድ ምት ለደቂቃዎችም ስለማይቋቋሙ እግሬ እውጪኝ ብለው በየገደሉ ነብሴ አውጪኝ እያሉ ይኳትኑ ነበር::
አዲስ ዘመን፡- መቐለ ስትቃረቡ እንጠቃለን በሚል የፍርሃት ስሜት አልነበረም?
አቶ ዳኛቸው፡- እኔ ሞትን አልፈራሁም:: ሠራዊቱ ወኔው ሲታይ በጭራሽ ፍርሃት የሚባል ነገር የለም:: አጠገባችን ያለው ኃይል ጥላ ከለላችን ነው:: በእርግጥ የሞተ ጓደኛችን አለ:: ግን ቢሞትም እኔ ብዙም አልገረመኝም:: ለሀገራችን እስከሆነ ድረስ አማራጭ የለም:: ዓላማችን ሀገር ማዳን ነው:: ጦርነቱ ከሚካሄድበት ስፍራ ከሁለት እስከ ሦስት ኪሎ ሜትር በሆነ ርቀት ነው ስንከተል የነበረው:: አንዳንዴ ከተፈቀደልን ግንባር ላይ እንገጥማለን:: መኪና አቁሞ ወደ ብሬን ተኩስ የገባ ጓደኛችንም ነበር:: እጅግ እልከኛ እና አደገኛ ተኳሽ ነበር:: አቶ ስብሃት ነጋ የተያዘበት አዴት በምትባል አካባቢ ትንሽ ፈተና በዝቶብን ነበር:: ከባድ መሣሪያ ብዙ ተኩሰውብናል:: ግን እንዳሰቡት አልሆነላቸውም፤ ዒላማ የጠበቀ ሳይሆን በደመ ነፍስ የሚተኩሱት ነው:: የተወሰነ ጉዳት ቢደርስም በድል አጠናቀናል::
አዲስ ዘመን፡- እየሸሹ ከሆነ ከባድ መሣሪያዎቹን የሚተኩሱት የት ሆነው ነበር?
አቶ ዳኛቸው፡- ይህን ብነግርህ ይገርምሃል:: ሽሬ ላይ ብቻ የሆነው ላስታውስህ:: ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤተክርስቲያን የሚመስል ቤት ተሠርቶ ነበር:: ትግራይ አካባቢ ቤተክርስቲያን ቢበዛም እኔ ሳውቀው ከሽሬ ወደ ዓዲ ዳሮ መውጫ ላይ ቤተክርስቲያን የሚባል አልነበረም:: በጦርነቱ ወቅት አብዛኛውን መሳሪያ ጥለው ነው የፈረጠጡት:: ታዲያ እዚህ አካባቢ እየተጠጋን ስንሄድ ከባድ መሣሪያ በተደጋጋሚ ወደ እኛ ይተኮሳል::
ከየት እንደሚተኮስ በቀላሉ ለማወቅ ከባድ ነበር:: ግን ሲተኮስ የነበረው ከቤተክርስቲያን ውስጥ ነበር:: በመጨረሻ ወደዚያ አካባቢ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የመልስ ምት ለመስጠት ሲሞክር ሙሉ ለሙሉ ነው የተበተኑት:: ተደብቀው የነበረው ቤተክርስቲያን ብለው ቆርቆሮ በቆርቆሮ ባሰሩት ቤት ውስጥ ነው:: በመጨረሻ ወደ ውስጥ ስንገባ ከአንድ ‹‹ስዕለ አድህኖ›› ውጭ ምንም ነገር የለም:: ይህ ሆን ተብሎ ቤተክርስቲያን አስመስለው የሰሩትና ለጦርነት እንዲመቻቸው የተደረገ መሆኑ መገንዘብ ችያለሁ:: ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች ውስጥ መደበቅ ቋሚ ሥራቸው ነው:: አመራሮችም ሆኑ ሰራዊቶቹ ካህን መስለው ቤተክርስቲያን ውስጥ ይደበቃሉ::
አዲስ ዘመን፡- በግንባር ከተማረኩ የህወሓት አመራሮች እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሲገናኙስ ምን ይሉ ነበር?
አቶ ዳኛቸው፡- በሀገር መከላከያ ውስጥ ሎጂስቲክስ ላይ ይሰራ የነበረ ገሬ የሚባል አመራር ነበር:: ሽሬ ላይ ማረኩት:: ቀድሞ አብረውት የነበሩት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ሲመለከቱት እጅግ በጣም አዝነውም በጣምም ተናደው ነበር:: ‹‹ምን አደረግንህ፣ ምን በደልንህ፣ አብረን በልተን ጠጥተን እንዴት ክህደት ትፈጽምብናለህ፣ ከምንበላው ቀንሰን ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ በገነባን፣ አዝመራ በሰበሰብን በደላችን ምን ነበር?›› ብለው ሲጠይቁት አስተውያለሁ:: የሚገርመው ይህን ሁሉ በደል የፈጸመባቸውን ሰው እንበቀልህ አላሉትም:: በህግ ፊት ፍርዱን ያገኛል ብለው ነበር በሥርዓት ወደሚመለከተው አካል አሳልፈው የሚሰጡት:: ይህን ስመለከት የሰራዊቱ የሞራል ልዕልና እና የታነፁበትን ሥርዓት ስመለከት ማመን ከብዶኛል::
ታዲያ እነዚህ ምርኮኞች የሀፍረታቸው ብዛት አንገታቸውን ደፍተው እግራቸው ሲንቀጠቀጥ ተመልክቻለሁ:: ልብሳቸውም ሲቪል መስለው እንጂ እንደ ወታደራዊ አመራር በዩኒፎርም አይደለም የነበሩት:: ሌላው ቀርቶ የሴት ‹‹ታይት›› ለብሰው ይሄዱ ነበር:: ለጁንታው መረጃ የሚያቀብሉ አካላትም አለባበሳቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ነበር::
አዲስ ዘመን፡- ሁለተኛ ዙር የዘመትከው በየትኛው ግንባር ነው?
አቶ ዳኛቸው፡- በመጀመሪያ ዙር ሦስት ወር ቆይቼ ነው የመጣሁት:: ሁለተኛ ዙር የዘመትኩት ደግሞ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ሥምምነት አድርጎ የትግራይ ክልልን ለቆ ሲወጣ 24ኛ ከፍለ ጦር ሠራዊትን ለማምጣት ከሄዱት አንዱ ነኝ:: በዚህም በሰቆጣ ግንባር አበርገሌ አካባቢ ነበርኩ:: በዚህ ወቅት ግን የሆነው እውነታ የኢትዮጵያ ህዝብ ማወቅ አለበት:: ሠራዊቱ በሠላማዊ መንገድ ክልሉን ለቆ እየወጣ ሳለ ህወሓት ተመልሶ ይመጣል ብለው ተስፋ የሚያደርጉና የጁንታው ደጋፊዎች እንደ ማዕበል በብዛት ወጥተው የመከላከያን ጉዞ ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል:: ውስጣችን የጁንታው ደጋፊ የሆኑ አሽከርካሪዎችም ነበሩ:: በዚህም ሠራዊታችን ከፍተኛ መስዋዕት ለመከፈል ተገዷል:: ለህዝብ ብሎ የሚሰዋን ሰራዊት በዚህ ደረጃ እንቅፋት መሆን አደገኛ ነው፤ ሰራዊቱ የያዘው እሳት ነው:: ህዝብ ላይ አልተኩስም እያለ ሌላው ቢቀር ራሱን ማዳን ሲችል ሙያዊ ግዴታውን ለማክበር ብሎ እራሱ መሥዋዕት ሲሆን በጣም ያሳዝናል::
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎች አሽከርካሪዎችን በገንዘብ ለመደለል አይሞክሩም?
አቶ ዳኛቸው፡- የማይሞክሩት ነገር የለም:: አንዱ ወደ እኔ መጥቶ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እየተሸነፈ ነው፤ ወደ ኋላ እያፈገፈገ በመሆኑ ወደቤተሰቤ በሕይወት ልመለስ እባክህ ተባበረኝ አለኝ:: ቱታ አልብሰህ እንደ ሲቪል አሳልፈኝ ብሎ ለመነኝ:: በዚህ ሁኔታ አሳልፈን ብለው ብዙ የሚመጡ አሉ:: እኔ ነገሩን ቀለል አድርጌ ያዝኩትና አቀረብኩት:: ቀስ ብየም ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ መረጥኩኝ:: በኋላ ነገሩ ሲመረመር እና ስራው ሲታይ የጁንታው ሰላይ ነበር:: ይህን ሰው ለሚመለከተው አካል አሳልፌ ሰጥቻለሁ:: አብዛኛው መረጃ የሚያቀብላቸው፣ ሰላያቸው እና አመራራቸው አለባበሱ ሲቪል ሲሆን ሥራው ግን ወታደራዊ ነው:: አማራ ክልል ገብተው መረጃ ሰብስበው ሲቪል መስልው ወደ ትግራይ ክልል ሲመለሱም የተያዙ ብዙ አሉ::
አዲስ ዘመን፡- ለጥንቃቄም ይሁን በቀጣይም መሆን ስለሚገባው መልዕክት አለህ?
አቶ ዳኛቸው፡- ሰዎች ያለመረጃ በየቦታው ባያወሩ ጥሩ ነው:: የጁንታው ተላላኪዎች የሆነ ቦታ ተያዘ ብለው ሲያስወሩ መሸበር አይገባም:: ወያኔ ተመልሶ አይመጣም:: ይህ ህልም ነው:: ኢትዮጵያ ህዝብ በሄድንበት ቦታ ሁሉ አቀባበሉ ይገርማል:: አንዳንድ ቦታ መንገድ ዘግተው ሳትበሉ አትሄዱም ብለው ያስቆሙናል:: ሸንኮራ አገዳ የሚሸጠው እንኳን በመስኮት ወርውሮልን ሂሳብ መቀበል አይፈልግም:: ህዝቡ ፍላጎቱ ሀገሩ ሠላም እንድትሆን ነው:: ሰራዊቱ ድል አድርጎ መመለሱን ነው የሚመኙት::
እኔም አሁን በግሌ ይህ ነገር ይደረግልኝ ብዬ ምንም መጠየቅ አልፈልግም:: መጀመሪያ ሀገር እና መንግስት ይረጋጋ:: ከዚያ እንደ ዜጋ የቆጠብኩት የጋራ መኖሪያ ቤት ቢደርሰኝ ደስ ይለኛል:: የምኖረው ተከራይቼ ሲሆን ሦስት ልጆች አሉኝ:: ቢቻል ቀበሌ ቤት እንኳን የማግኘት ዕድል ቢኖረኝ ብዬ አስባለሁ:: ከምንም በላይ ግን በግንባር ለተሳተፉ አሽከርካሪዎች በተቻለ መጠን የምስጋና መርሐ ግብር ቢዘጋጅ እመኛለሁ:: ከዚህ በዘለለ ሀገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች ረጅም እርቀት አቆራርጠን የምንመጣና ብዙ ውጣ ውረድ ያለብን ሰዎች ነን:: አልፎ አልፎ አንዳንድ የትራፊክ ፖሊሶች ያልተገባ ባህሪ ቢስተካከል ብለን እንጠይቃለን:: በሌላ ጎኑ በህግ ማስከበሩ ወቅት የሚሰዋ አሽከርካሪ ሊኖር ስለሚችል ቤተሰቡን መንግስትና ማህበረሰቡ የሚንከባከብበትና የሚያስተምርበት መንገድ ቢኖር መልካም ነው:: ከዚህ በዘለለ በማንኛውም ግዳጅ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ነኝ:: ኢትዮጵያ ሁሌም ሠላም ትሁን::
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጠኸኝ ቃለምልልስ አመሰግናለሁ::
አቶ ዳኛቸው፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም