የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች የተቋቋሙበት ዋነኛ ዓላማ ከፖለቲካ ነጻና ገለልተኛ ሆነው በችግር ላይ ላሉ ተጎጂዎች ፈጥኖ በመድረስ የዕለት ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ ነው:: አሁን ላይ ያለው ነባራዊ እውነታ ግን በተቃራኒው እየሆነ ይገኛል:: አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዓላማቸውን ከምግባራቸው የማይገጥም አራምባና ቆቦ ከመሆኑም በላይ ሽፋናቸው ሲገለጥ ውስጡ በማር የተለወሰ መርዝ እየሆነ መገኘቱ ሃቅ ነው:: እነዚህ ድርጅቶች የጥሩ ምግባርና የሰብዓዊነት ጥግ ባለቤትነትን ከላይ አንግበው ውስጥ ውስጡን ግን አደገኛ መርዝ ይረጫሉ:: በሰብዓዊ እርዳታ ሰበብ ወደ ተለያዩ ሀገራት ድንበር ዘልቀው ከገቡ በኋላ የሰወሩትን ድብቅ ዓላማ ይፈጸማሉ:: መቼም ቢሆን ተደብቆ የሚቀር ነገር የለምና በሰብዓዊነት ውስጥ የቀበሩት ተንኮል ገሃድ ሲወጣ የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ ያድርቅ አይነት ጫወታ ይጫወታሉ::
የእርዳታ ለጋሾቹ የበለጸጉት ሀገራት በሰብዓዊ እርዳታ ስም በሚፈጸሙት ሥውር ደባ በርካታ ሀገራት ተጎጂ ሆነዋል:: ለጋሽ ነን ባዮቹ የምጣኔ ሀብታቸውና ወቅታዊ አቋማቸው ወርዶል ብለው ያሰቧቸውን ሀገራት ዒላማ አድርገው በስፋት ይንቀሳቀሳሉ:: በአፍሪካ እንደ አሽን የፈሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መኖራቸው የዚሁ ማሳያ ነው:: ሰብዓዊ እርዳታን ከፖለቲካ ጋር ምንም የሚያገኘውና የሚያዛመድ ነገር ባይኖርም ለጋሾቹ ግን የፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ እና መቆጣጠሪያ ስልታቸው አድርገው ሲጠቀሙበት መቆየታቸው ይታወቃል::
የበለጸጉት ለጋሾች ለእርዳታ የዘርጉት የሴራ እጅ ባዶውን እንዳይመለስ ያውቃሉ:: አስልተው እና አስርዝመው የሚሰዱት የሚያስገኝላቸውን ትርፍ ቀድመው በማሰብ ነው:: እነዚህ የበግ ለምድ ለባሾች ትንሽ አሳይተው በብዙ ለማፈስ የሚስገበገቡ ናቸውና በሰብዓዊ እርዳታ ስም የሦስተኛው ዓለም ሀገራት ዳግም ቀና እንዳይሉ በማድረግ አሽመድመደው ወደኋላ ማስቀረታቸው ታሪክ ይመሰክራል::
በገቡበት ሀገራት ያከናወኑት ፖለቲካ ሴራ ሀገራቱን ዳግም እንዳያንሰራሩ አድርጎ አፈራርሷል:: ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ በእነዚህ ሰብዓዊ ድጋፍ አድራጊዎች ከሶሪያ እስከ ሊቢያ የተለኮሰው እሳት ዛሬም ድረስ ነበልባሉ ብዙዎችን እየገረፈ ነው:: በተለይ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ከያዙበት ወቅት ጀምሮ በተለያየ መንገድ የአህጉሪቱንና ህዝቦቿን በመጨቆን ያለው አንጡራ ሀብት፣ የተፈጥሮ ማዕድናትና የሰው ሃይል ሲበዘብዙ መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ:: ለዚህም በዋነኛ መሳሪያቸው አድርገው የሚጠቀሙት የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ነው::
በሌላ በኩል በሰብዓዊ እርዳታ ሽፋን የሀገራትን እጅ በመጠምዘዝና አልፈው ተርፈውም በዜጎች መሀል ግጭት እንዲፈጠር አበክሮ የሚሰሩ ስለመሆናቸው የድርጅቶቹ ጭምብል ሲገለጥ በደማቁ ተጽፎ የምናገኘው እኩይ ተግባራቸው ነው:: በተመሳሳይ ሀገራትንና መንግሥታትን መሰለል በሰብዓዊ እርዳታ ስም የጦር መሳሪያዎችና የሳተላይት መገናኛ ዘዴዎች ሳይቀር ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባታቸው በስውር ከሚፈጸሙት ተግባር መካከል ተጠቃሾች ናቸው:: ይህ ተግባራቸውም እውነት ስለመሆኑ በቅርቡ የአሸባሪው ህወሓት አፈ ቀላጤ ጌታቸው ረዳ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች አጋሮች እንዳላቸውና የሳተላይት መገናኛ ዘዴዎች በእጃቸው ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል::
ሰብዓዊ የእርዳታ ለጋሽ ሀገራት ምዕራባዊያንም ሆኑ አሜሪካን የሰብዓዊ እርዳታ ለፖለቲካ መጠቀሚያ በማድረግ ለሚታዘዙላቸው መንግሥታት እርዳታን የሚሰጡበት፤የማይታዘዙላቸው ከሆነ የሚከለክሉበት ሁኔታ እንዳለ ይስተዋላል:: እነዚህ የግል ፖለቲካዊ ጥቅማቸው የሚያራምዱ ሀገራት በእርዳታ ስም የጦር መሳሪያዎችን ሳይቀር ለተቃራኒው ወገን የሚያደርሱበት ሁኔታ መኖሩ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው::
አሁንም በኢትዮጵያ ላይ እየፈጸሙት ያለው ይህንኑ ተግባራቸውን ነው:: ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ከዓላማቸው ውጪ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ሦስት ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱ ይታወሳል:: ሰሞኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የዕርዳታ ተቋማት ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ መሠረት አድርገው የሀገሪቱን ህግና ስርዓት ተከትለው ሥራቸውን ማከናወን እንደሚገባቸው ማሳሰባቸው አይዘነጋም::በተመሳሳይም ጉዳዩ ያሳሰባት ቻይናም በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር በተሰየመበት ሰብሰባ ላይ ይህንኑ ሀሳብ በመድገም በሰብዓዊ እርዳታ ሰበብ ገብተው የኢትዮጵያን የውስጥ ችግር ለመባባስ የሚሰሩ አካላት መኖራቸው ጠቁማ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስባለች::
በሰብዓዊ እርዳታ ስም ለሚሰሩት ድብቅ ሴራ ምስክር ፍለጋ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን ትህነግ ከደርግ መንግሥት ጋር በሚያደርገው ጦርነት ለእርዳታ የተላከውን እህል እየሸጠ ለጦር መስሪያ ግዥ እንዲውል እገዛ ሲደርግለት እንደነበር በወቅቱ የቢቢሲ ዘጋቢ የነበረውና በአሁኑ ወቅት የትህነግ ቀንደኛ ደጋፊ የሆነው ማርቲን ፓላውት ማጋለጡን የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነበር::
ታዲያ የእጅ አመል አይለቅም እንደሚሉት ሆኖ በዚህም የካበተ ልምድ ያላቸው የእርዳታ ድርጅቶች አሁንም በኢትዮጵያ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸሙ ይገኛሉ:: አሁንም አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች የአሸባሪው የህወሓት ቡድን እየረዱ ስለመሆኑ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራዕዶ ድርጅት ዋና ሃላፊ እነ ሳማንታ ፓውር ድርጊት ይህንኑ የሚያሳይ ነው:: እነሳማንታ እንደሚሉት ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ መቸገራቸውን በመግለጽ፤ በመንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም::
ከሱዳን የጀመረው ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ጉዞ ለአሸባሪው መውጫ ቀዳዳ ፍለጋ መሆኑን ማሳያ ነው:: የዕለት ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ክልሉ ለማድረስ በሱዳን በኩል ያሉ ድንበሮች እንዲከፈቱም ሲሉም ወትወተው ነበር:: አሸባሪውን የፈጸማቸውን ድርጊት ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው እንዳልሰማ የሚያልፉት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው የተነካ ከመሰላቸው ያዙኝ ለቀቁኝ ሲሉ የሚጮሁበት ምክንያት በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል::
የአሸባሪው ሀገርን ለማፍረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲሁም የሚፈጸመውን ግፍና በደል ባላየና ባልሰማ በዝምታ ያልፉታል:: በተለይ አሜሪካ በሰብዓዊ እርዳታ ሽፋን በነሊቢያ ላይ የፈጸመችውን እኩል ተግባር በሀገራችን ላይ ለመድገም ያልጠመጠመችው ሴራ የለም፤ ጫና ለማሳደር ይረዱኛል ባለቻቸው መስመሮች ሁሉ ሞክራ አልተሳካለትም:: ያላት አማራጭ በሰብዓዊ እርዳታ ሽፋን ወደ ውስጥ መዝለቅ ነው:: አሁን ላይ አሸባሪው ህወሓት ወደ ጦርነት የሚማግዳቸውን ህጻናት የሚጠቀሙት አደንዛዥ እጽ በእርዳታ ስም የገባ አሜሪካ ሰራሽ መድሃኒት ስለመሆኑ መረጃዎች እየተጋለጡ ይገኛል::
ባለፈው ጋሳይ ግንባር የተማረከው የጁንታ ኮሎኔል ገ/ ህይወት ገ/አላፍ በእጁ በርከት ያሉ የሀሽሽ ብስኩቶች ይዞ መገኘቱም የዚሁ ማሳያ ነው:: እነ አሜሪካ ያለሙት አላማ እስኪሳካላቸው ምንም ከማድረግ ወደኋላ የማይመለሱ መሆናቸው ማሳያ ነው:: ከጥንት ጀምሮ ሲረዱት የነበረው አሸባሪ ህወሓት ዛሬም የሞቱ ጉዳይ አሳሰቧቸዋል፤ እቅዳቸው ሁሉ ውሃ እንዳይበላው ሰግተዋል፤ ስውር ተግባራቸው በይፋ እየታየ ይገኛል::
ዛሬ ላይ በካቡል ከገጠማት ቅሌት የማትማረው አሜሪካ በድጋሚ ኢትዮጵያ ላይ የጥፋት መረቧን በመዘርጋት በእጅ አዙር በሰብዓዊ እርዳታ ስም ብቅ ብላለች:: ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቀን ከሌሊት ለሚተጋው የአሸባር ህወሓት በጽኑ ከማውገዝ ጎን በመቆም በእያንዳንዱ ወታደር ኪስ የተገኘው በእርዳታ ስም የገባ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውል ብስኩቶችና እጾች ምስክር ናቸው::
ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ይህንን በጥልቀት መገንዘብ ሰሞኑን እነሳማንታን ለመቃወም በቲውተር ዘመቻ ተጠናክሮ እንደቀጠለው ሁሉ፤ አሁን በሰብዓዊ እርዳታ ስም የራሳቸውን አላማ አንግበው የሚሰሩትን ድርጅቶችን ማውገዝ ይገባል:: ኢትዮጵያ እንደሊቢያ ሊያፈረርሱ ያለመውን እና የሚሰሩት የውጭ ኃይሎች ሴራ በማክሸፈ አሸባሪውን ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎ ለመቅበር በአንድነት መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን ጠንከረን መስራት የሚጠበቅብን ጊዜ አሁን ነው::
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም