በቅርቡ ሁለቱ የሽብር ድርጅቶች በጋራ ለመስራት ተስማምተናል ሲሉ ተሰምተዋል። የህወሓት እና የሸኔ የሽብር ቡድኖች በጋራ የሽብርና የጥፋት ስራቸውን ለመፈጸም መስማማታቸው ስሰማ ወደ አዕምሮዬ የመጣው ነገር ይህ ጉዳይ ጥምረት ሳይሆን ጭንቀት መሆኑ ነው። የቸገረው እርጉዝ ያገባል ስትወልድበት ገደል ይገባል አይነት ነገር….. የኢትዮጵያውን በተጠናከረ ክንድ የሽብር ቡድኖችን ለማጥፋት ያሳዩት ቁርጠኝነትና የፈጠሩትን አንድነት በመፍራት ይመስላል ጥምረት መስርተናል ያ ሉት።
ሁለቱ የሽብር ቡድኖች በሰላም የማያምኑና በንፁሃን ደም ስልጣንን የሚመኙ እንደሆኑ የከዚህ በፊት ምግባራቸው ህያው ምስክር ነው። መንትያዎቹ እነዚህ የሽብር ቡድኖች በንጹሃን ንፍስ የሚቆምሩ ኣላማቸው መክፈል የሆነ አንድነት የሚባል ቃል መስማት የማይፈልጉ ትዕቢተኛ እብሪተኛ ናቸው። እነዚህ የሽብር ቡድኖች የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገር ሲኖር ሁሌም ቢሆን ለሰላም ቅድሚያ አለመስጠት፣ በስቃይ መርካት፣ ንብረት ማውደምና ንጹሃንን በመጨፍጨፍ ስልጣንን መቆናጠጥ ዋነኞቹ ናቸው።
ለ17 ዓመታት በበረሃ ለ27 ደግሞ በስልጣን ላይ የነበረው አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዲሞክራሲን እንደ ጭምብልና መጠቀሚያ ሲገለገልበት ነበር። ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን የይስሙላ ምርጫ እያካሄደና ተቃዋሚዎችን እየገፋ ሰልጣን የሚገኘው በዲሞክራሲያዊ መንገድ ከምርጫ ኮሮጆ ነው በሎ ሲሰብክም ነበር። አሁን ከስልጣን ከወረደ በኋላ ደግሞ ወደ ተቀማው ስልጣን ለመመለስ ህዝባዊ ትግል በሚል የዳቦ ሥም ንጹሃንን በመግደልና ህጻናትንም ጭምር ወደ ጦርነት በማሰለፍ የአለም አቀፍ ህግንም በመጣስ ጭምር ሃገሪቷን የብጥብጥና የትርምስ ቀጠና እንድትሆን ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
ለውጭ ጠላት የአገር ሉኣላዊነት ለማስደፈርና አገር ለማፍረስ አልሞ እየሰራ ያለውን የዚህን አሸባሪና ሴረኛ ቡድን ባህሪ ለዓመታት ጠንቅቀው የሚያውቁት ኢትዮጵያውያን በፈጠሩት ኅብረት ይህ ህልሙ የተሳካለት አይመስልም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊባል በሚችል ደረጃ ኢትዮጵያውያን የሽብር ቡድኑን በማውገዝና በመፋለምም ጭምር ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራውን ቅዥት እያደረጉበት ይገኛሉ።
በጥፋት ቡድኑ አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ የአፍ ወለምታ እንደተገለጸው የሽብር ቡድኑ ዋነኛ ዓላማ ኢትጵያውያንን በመከፋፈል አገር ማፍረስና በህዝብ ላይ የጥላቻ ሂሳብ ማወራረድ ነው። ይሄን ሀሳቡን በተግባር ላይ እያዋለው እንደሚገኝም በቅርቡ በአፋርና አማራ ክልል በህዝብ ላይ በፈጸመው ግፍ ተረጋግጧል። ለትግራይ ህጻናት የተላከን አልሚ ምግብ ለሆዳም አባላቱ ያለምንም እፍረት ያደለው ይህ የጥፋት ኃይል በአማራ ክልል ከአንድቤት እስከ አምስት የሚደርሱ ንጹሃን ዜጎችን ከባድ መሳሪያ ተኩሶ በመግደል የአረመኔያዊነቱን ልክ አሳይቷል። በአፋር ክልልም ንጹሃንን በመጨፍጨፍ የህዘብ ጠላትነቱን በይፋ አሳይቷል።
የሽብር ቡድኑ የጭካኔና የአገር ማፍረስ ዓላማን ለማክሸፍ ኅብረታቸው እንደብረት በጠነከረው ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ እየተደቆሰ ይገኛል። ለትግራይ አርሶ አደር ተብሎ የተወሰነውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ከፍርሃት በመቁጠር ወደአማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ይህ ቡድን ከኢፌዴሪ መከላከያ፣ ከክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ከፍተኛ ምት እየተሰጠው ይገኛል። አቅም ያገኘ ሲመስለው እንበር ተጋላይ ሲመታ እምበር ተንከባላይ የሚሆነው ይህ ኃይል እየተወሰደበት ባለው እርምጃ ጭፍራዎቹ አውሮፓ ላይ እንዲንከባለሉ ከመወትወት ውጪ ሌላ አማራጭ አጥቷል።
በዚህ ተስፋ የቆረጠው ቡድን ከሌላኛው የሽብር ቡድንና መንትያው ከሆነው ሸኔ ጋር በቅርቡ አንድ ላይ ለመስራት ወስነናል ሲል ኅብረት መፍጠሩን መናገሩ ሁለቱም እርባና ቢስ ድርጅቶች በዚህ ወቅት እያጋጠማቸው ያለውን ኪሳራ ያሳያል። ማንም እንደሚመሰክረው ሸኔ የተሰኘው አሸባሪ ቡድን በየአካባቢው በፈጸማቸው አሰቃቂ የሽብር ስራውና በሃይልና በጭካኔው የሚታወቅ ከንቱ ቡድን ነው። ተምረው ሃገርን እና ህዝብን የሚጠቅሙ ህጻናትን ሳይቀር የሚጨፈጭፍ ለኦሮሞ ህዘብ ጠላት የሆነና በተለያዩ ኢ-ሞራላዊ በሆኑ ድርጊቶቹ የሚታወቅ ቀንደኛ አሸባሪ ነው። ታዲያ እነዚህ ታሪካቸው ጥቀርሻ የሆነ የሽብር ቡድኖች አሁን ጥምረት መስርተናል ሲሉ መስማቱ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው አንድ እንደመሆኑና ይህንን ድርጊታቸውን እንዳይቀጥሉ የተወሰዳባቸው ከባድ ምት ተደናግረው ተጣመርን ማለታቸው የቀቢጸ ተስፋ ውሳኔ እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም።
ጥምረት የሚባለው የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸውና በሰላም የሚታገሉ ሃይሎች አንድ ላይ በሰላማዊ መንገድ ህዝብን ለሚጠቅም ስራና በጋራ ሃገርንና ህዝብን በኢኮኖሚ የተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚራመዱበት እርምጃ እንጂ እርኩስ ጋብቻ አይደለም። ለህዝብና ለሃገር ቀና አመለካከት ያላቸው ሃይሎች ለሃገር ሰላም ሲሉ የተለያየ አመለካከትና አቋም ቢኖራቸውም ልዩነታቻውን አቻችለው በጋራ በአንድ ላይ ለመስራት ሲስማሙና ሲሰሩ ጥምረት ሊባል ይችላል። እነዚህ የሽብር ቡድኖች ግን አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይዘው ለዘመናት በሴራና በክፋት ቢዘልቁም ለውጥ አላመጡም። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ሽብርተኝነትን አለመደገፉና ሰላምን ማስቀደሙ ነው።
በግል ሆነው ሲዋጉ ስላልተሳካላቸው አሁን በጋራ እንሰራለን ቢሉም ካጋጠማቸው የህዝብ አንድ መሆንና ሁሉም ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ካለው ቆራጥነት የተነሳ ከጭንቀት የመነጨ ነው ያልኩትም ለዚህ ነው። ህዝብን በመበታተን እና በመከፋፈል ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራቸው ሳይሰራ ቀርቷል። ለዚህም ይመስላል እነዚህ የሽብር ቡድኖች ጭንቀት ውስጥ የገቡት። ለበጎ ምግባር አዕምሮ ያልታደሉት እነዚህ የሽብር ኃይሎች ዘመናቸውን ሙሉ ኢትዮጵያን በማዳከም ተግባር ላይ ቢጠመዱና፣ ዘረኝነትን ለማስፋፋትና የሃይማኖት ግጭትን ለመፍጠር ብዙ ርቀትን ቢጓዙም ያሰቡት ሊሳካ ፈጽሞ አልቻለም። ይሁንና በእኩይ ድርጊታቸው በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የብዙ ሰው ህይወት እንዲጠፋ ከፍተኛ ግምት ያላቸው ንብረቶች እንዲወድሙና ብዙዎች ለዘመናት ካፈሩት ሀብት ንብረትና መኖሪያ እንዲፈናቀሉ አድርገዋል።
እነዚህ የሽብር ቡድኖች በተለያየ አቅጣጫ ሆነው ለአንድ ዓይነት የሽብር አላማ ቢሰሩም የሞከሩት የሽብር ሴራ በተለያየ መንገድ ሲከሽፍባቸው እንጂ ያሰቡትን አገር የማፍረስ ዓላማ ውጤት ሊያመጣ አልቻለም።
ዓላማቸው ርኩስ የሆነው እነዚህ አሸባሪዎች አሁን ላይ በይፋ ጥምረት መመስረታቸው ምንም ዓይነት የተለየ ስጋት አያመጣም። እንዲያውም ጠንካራ አለመሆናቸውን በይፋ ያሳዩበት መግለጫ ነው። ለየብቻ ሆነው እንደተመኙት ኢትዮጵያን የመበታተን ሴራቸው ሊሳካላቸው ስላልቻለ በጋራ እንሰራለን የሚለው ጩኸት ምንም ዓይነት አዲስ ነገር የሌለውና የተሸናፊነት ማሳያና ከጥምረት ይልቅ ጭንቀት የወለደው የቀቢጸ ተስፋ ሙከራ መሆኑን ያሳየ ነው።
በኤም
አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 ቀን 2013 ዓ.ም