ሀገሪቱ ጦርነት ላይ መሆኗን አስታውሰን እንለፍ። የጦርነቱ የፍልሚያ ሜዳ ደግሞ አረር የሚወነጨፍበት፣ ታንክ የሚርመሰመስበት፣ ጀግኖች ከጠላት ጋር ትንቅንቅ ገጠመው እያርበደበዱ ኃያል ሕዝባዊ ክንዳቸውን የሚያሳዩበት ቀጣና ብቻ አይደለም። በዚህኛው የፍልሚያ ጎራ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንና ሕዝባዊው ሠራዊት ከዕለት ዕለት ከድል ወደ ድል መሸጋገሩን የምሥራች እያበሰረን ስለሆነ ምሥጋናችንን የምናቀርበው በታላቅ ዕልልታ አድምቀንና ከወንበራችን ከፍ ብለን በመቆም ነው።
ስለዚህኛው የጦር ሜዳ ግዳጅና ውሎ ብዙ ዝርዝር ትንታኔዎችን ለመስጠት ዕውቀትም ብቃትም ስለሚጠይቅ ወታደራዊ ጥበቡና የሙያ ሥነ ምግባሩን በሚገባ ማወቅ ግድ ይሏል። ቢሆንም ግን በጦርነት ግንባር ስለተለመደ አንድ ጉዳይ ከታሪክ፣ ከተሞክሮና ከንባብ በማጣቀስ የግል ግንዛቤን መወርወር እጅግም አያስቸግርም። ይህ ጸሐፊ ነፍሱን ለሀገሩ የሰዋ የጀግና ወታደር ልጅ ስለሆነና የአባቱን የጦር ስልት ማስተማሪያና በርካታ ሰነዶችን በአደራ ተርክቦ የመረመረ ስለሆነና የንባብ እውቀቱም ስለማያወላዳ በአንድ ጉዳይ ላይ ጥቂት ምልክታ አድርጎ ወደ ዋናው የዕለቱ ርዕሰ ጉዳይ ፈጠኖ መንደርደርን መርጧል።
በየትኛውም የጦር ሜዳና ግምባር “ፈንጂ” ይሉት አውዳሚ የጦር መሣሪያ በግዳጅ ወረዳ ላይ እየተጠመደ/እየተቀበረ በተጻራሪ ኃይል ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ማድረስ የተለመደ የውጊያ ስልት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ወጥመድ የሚዘረጋበት ቀጣና “የፈንጂ ወረዳ” በመባል ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ፈንጂ አምካኝ የሠራዊት ባለሙያዎች በግዳጅ ወረዳው ውስጥ ከሠራዊቱ ፊት ፊት እየቀደሙ የተቀበረውንና የተጠመደውን “አውዳሚ ቦንብ” በማምከን ቀጣናውን ያጸዳሉ። አሁን አሁን እንኳን አንፍናፊ ውሾችና የተራቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሥራ ላይ እየዋሉ ስለሆነ የመስዋዕትነቱን ክብደት እያቀለሉት ይመስላል። ፈንጂ የሚጠመደው በተገዳዳሪ የሰው ኃይል ላይ ብቻ ጉዳት ለማድረስ ሳይሆን ብረት ለበስ ታንኮችን ለማውደም ጭምር መሆኑን ልብ ይሏል። ከፈንጂ ጋር የተያያዙ በርካታ የሀገራችንን ጀግኖች ታሪክ ለመተረክ ቦታው ስላልሆነ እንጂ ቢሆን ኖሮ ብዙ ታሪካዊ የተጋድሎ ውሎዎችን መተረክ በተቻለ ነበር።
በጦርነት ወቅት በጠላት የተጠመደ/የተቀበረ ፈንጂ ሳይመክን ቀርቶ በድል ማግሥት ወይንም ሀገር ከተረጋጋ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በንፁሃን ዜጎች ላይ ከፍ ያለ የሕይወትና አካላዊ ጉዳት ማድረሱ ለሀገራችን እንግዳ አይደለም። የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ በሽንፈትና በውርደት ከተባረረ በኋላ በየቦታው ቀብሮና አጥምዶ የነበረው ፈንጂ መክኖ ስላላቀ በየጊዜው እየፈነዳ የብዙ ወገኖቻችንን ሕይወት ሲቀጥፍና አካላዊና ቁሳዊ ጉዳት ሲያደርስ መኖሩም የሚዘነጋ አይደለም። የዚህ ጸሐፊ አንድ አብሮ አደጉ በልጅነቱ ዕድሜ ወድቆ ያገኘው ፈንጂ መጫወቻ መስሎት ሲጎረጉር ፈንድቶ እርሱን ግራ እጁን፣ ጓደኞቹን ደግሞ ሕይወታቸውን እንደቀጠፈ አይዘነጋውም። የፈንጂ ጉዳይ እስከዚህ እያዋዛ ካጓጓዘን ዘንዳ ወደ ዋናው ጉዳይ አቅንተን በጎመዘዘብን ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ጥቂት እንተንፍስ።
ክብር ላኮሩን ጀግኖቻችን ይሁንና ሀገርን እያደማ፣ እያቆሰለና እየዘረፈ ያለው አረመኔው አሸባሪ የትህነግ ወራሪ ኃይል በቁርጥ ቀን ፈጥኖ ደራሽ የመከላከያና የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት አይቀጡ ቅጣት እየቀመሰ ስለመሆኑ ሪፖርቱ በየዕለቱ በይፋ እየተነገረን ነው። ይህንን እኩይ ወራሪ ኃይል በአጭሩ ለመግለጽ ካስፈለገ ማለት የምንችለው የናዚና የፋሽስቶች እጥፍ ድርብ ዛር የወረደበት ጨካኝ ቢባል ግብሩን በሚገባ ያመላክት ይመስለናል።
ይህ አሸባሪ ቡድን ጦርነት ከፍቶ ሀገሪቱን በማድማት፣ ንፁሃንን በመጨፍጨፍና የሕዝብና የመንግሥትን ንብረት በማውደም ብቻ የተገደበ አይደለም። በጦር ሜዳው ፍልሚያ እየተቀጠቀጠ፣ አናቱ እየፈረሰና ዕብሪቱ እየተነፈሰ ቢሆንም ያልሞተውና መርዝ የሚነዛበት ምላሱ ገና የታጠፈ አይመስልም። ላንቃው ያልተዘጋውና የሚወሸክትበት የማኅበራዊ ሚዲያውም ማቅራራቱ አልቀነሰም።
በተለይም አበክሮ ሲያሰለጥናቸው የኖሩትና በሀገር ውስጥ ፈልፍሎ ወደ ተለያዩ ሀገራት ያሰማራቸው በእባብ እንጭ የሚመሰሉት ጀሌዎቹ በነጋ በጠባ በሥልጡን ሀገራት ጎዳናዎች ላይ ሲንከባለሉ፣ በየኤምባሲ ጽሕፈት ቤቶች ደጃፍ ላይ መንግሥታትን ሲማጠኑ፣ በተራድኦ ሽፋን የተለበጡትን “አይዟችሁ” ባዮቻቸውን ሲያደነቁሩና ከሀገር ዘርፈው ባከማቹት የሕዝብ ሀብት ሲያማልሏቸውና ሲደልሏቸው እያስተዋልን ነው።
“እስከ ሲኦል ድረስ እንኳን ወርደን ሀገሪቱን ለማፈራረስ እንታክትም” እያሉ በሌጊዎኑ አለቃቸው አንደበት አማካይነት እውነቱን አሳውቀውናል። ሲኦል ውስጥ ቦታ የተዘጋጀላቸው የእነሱ ብጤ የሰይጣን ጭፍሮችና ክፉ መላእክት ስለሆኑ መዳረሻቸውን አጥብቀው ቢሹ አይፈረድባቸውም። “ዶሮ ጭራ ጭራ ታወጣለች ካራ!” እንዲሉ ውሸታቸውና የፈጠራ ትርክታቸው ለዓለም ማኅበረሰብ በግላጭ እየተስተዋለ ስለሆነ የሚንፈራገጡበት እስትንፋሳቸው በቅርቡ እንደሚያከትምለት አንጠራጠርም።
ችግሩ አፍጥጦ እየታየ ያለው ፊት ለፊት በሚደረገው ውጊያና ፍልሚያ ላይ ብቻ አይደለም። አሸባሪው ቡድን ሲሸምናቸው በከረመው ኔትወርኮችና በዘረጋቸው ስትራቴጂካል የሴራ ምድብተኞች ውስጥ ሰውሮ ባስቀመጣቸው “ሰብዓዊያን ፈንጂዎች” አማካይነት ከፍ ያለ ጥፋት እየደረሰ መሆኑን በቀን በቀን እያስተዋልን ነው።
ይህ የዲያቢሎስ መምህር የሆነው አሸባሪ ቡድን በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ በአንድ ለአምስት ስብስብ ጠርንፎ፣ ዘርቶና ኮትኩቶ ያሳደጋቸው በርካታ ጀሌዎቹ (ሰብዓዊያን ፈንጂዎች በማለት የተሰየሙት) ከተሰገሰጉበት ተለቅመው ገና ስላልመከኑ ከፍተኛ ሀገራዊ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል። በተለይም በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ እየፈጸሙት ያለው የሴራ ትብታብ እንኳንስ ተበጣጥሶ ሊያልቅ ቀርቶ ገና የውሉ ጫፍ ተመዞ ያለቀ አይመስልም።
እነዚሁ ሰብዓዊያን ፈንጂዎቹ ሕዝቡ በኑሮ ውድነት እየተማረረ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲያጣ በከፍተኛ ሁኔታ ቀን እንደ ሠራዊት ሌሊት እንደ አራዊት በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። የገበያ ሥርዓቱን ማዛባት ብቻም ሳይሆን ውስጥ ለውስጥ የሚነዙት የሽብርና የአመጽ ቅስቀሳም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የሚያሸብሩ የፈጠራ ወሬዎችን እየፈበረኩ እዚህም እዚያም የሚያፈነዱት የሴራ ቅንብራቸው ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ስለሆነ በጥብቅ ሊፈተሸ ይገባል። በዚሁ እኩይ ትጋታቸውም ቢያንስ በከፍተኛ ደረጃ በናረው የኑሮ ውድነት ዒላማቸውን በመምታት ላይ ስለመሆናቸው ለመገመት አይከብድም።
በመንግሥት የቢሮክራሲ መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ሰብዓዊ ፈንጂዎችም ሕዝብን እምባ ሳይሆን ደም እያስለቀሱት እንዳለ እያስተዋልን ነው። በተለይም በግብር ሰብሳቢ ተቋማት ውስጥ ያሉ ኔትወርኮች ተበጣጥሰው ሊያልቁ ይቅርና ጭራሹኑ የተጠናከሩ እስኪመስል ድረስ ተገልጋዩና ግብር ከፋዩ እንደምን እያለቀሰ እንዳለ በቦታው ተገኝቶ እውነታውን መረዳት አይከብድም። የነጋዴው ማሕበረሰብ የግብር ግዴታውን ተበረታትቶ በአግባቡ እንዳይከፍልና እንዳይስተናገድ በማደናገርና የጥቅም ተካፋይ በመሆን ሀገርን በማድማቱ ተግባር ላይ ተጠናክሮ እየተሠራ ይመስላል። ጉዳቱ “ጉዳት” ተብሎ የሚታለፍ ብቻም ሳይሆን ከዚህ አገላለጽም ከፍ ያለ እንደሆነ ውጤቱ በግላጭ እየታየ ነው።
ይህ ጸሐፊ “የታክስ አምባሰደር” የሚል የሀገራዊ ኃላፊነት ዕጣ የወደቀበት አንድ ዜጋ ስለሆነ ለሚጠቁማቸው ችግሮች በቂ መረጃ አለው። ቀደም ባሉት ዓመታት ኢሕጋዊ የሆኑ የታክስና የግብር ስወራ፣ ሽቀባና ስውር ሴራዎች ይፈጸሙ የነበረው እጅግ በተራቀቁ ዘዴዎችና ስምምነቶች ነበር። ዛሬ ግን በግብር ሰብሳቢው ተቋም ውስጥ በተሰገሰጉ ሰብዓዊ ፈንጂዎች አማካይነት የሙስና ድርድርና ስምምነት የሚደረገው በግልጽና “ማን ምን ያደርገኛል!” በሚል ድፍረት ጭምር ነው። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ይህ ጸሐፊ ማስረጃዎችን እየጠቀሰ ወደፊት በዝርዝር ለማቅረብ ይሞክራል። አንድም የፈንጂው ቀጥተኛ ቁስለኛ ስለሆነ፤ አንድም የታክስ አምባሳደር የአገልግሎት አደራው ግድ ስለሚለው ከማጋለጥ ወደኋላ አያፈገፍግም።
በኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት ውስጥ በአንጻሩ ቀለል የሚለው ተገቢውን ፈቃድ አውጥቶ አዲስ የንግድ ዘርፍ መጀመር ሳይሆን አይቀርም። በኪሳራና በተለያዩ ምክንያቶች የንግድ ዘርፉን ለመዝጋት የሚታለፍበት መከራና አሳር ምን እንደሚመስል የደረሰበት ያውቀዋል። የንግድ ድርጅቴን ያለ እምባና ያለ መንፈሳዊ “ስዕለት” በቀላሉ እንድዘጋ የገቢዎች ተቋም ተባብሮኛል የሚል አንድ ሰው፣ አንድ ዜጋ ማግኘት ከተቻለ ያ ሰው በእርግጥም እድለኛ ብቻ ሳይሆን “የጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ” ላይ ሊመዘገብ የሚገባው ተዓምር ያገዘው ሰው መሆን ይኖርበታል። የንግድ ድርጅቴን በኪሳራም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ልዘጋ ነው ብሎ ተቋሙ ዘንድ ብቅ ያለ ምስኪን ዜጋ በመጀመሪያ የሂሳብ ምርመራ ለማድረግ ከሚመደቡለት አንዳንድ በፈንጂ የሚመሰሉ ኦዲተሮች የሚቀርቡለት ኢ ሥነ ምግባራዊ ጥያቄዎች ምን እንደሆኑ የሚመሰክሩ እጅግ ብዙዎች ናቸው።
በሌሎቹ መንግሥታዊ የቢሮክራሲ መዋቅሮች ውስጥም የአሸባሪው ቡድን ተስፈኞችና ተደራቢ ጀሌዎች የሰብዓዊ ፈንጂነት ተግባራቸውን እየተወጡ ያሉት “የጽድቅ” ያህል ራሳቸውን እየኮፈሱ ነው። ባለጉዳይ ማንጓጠጥና ጉዳይ ማጓተት፣ ስሜቱ ተጎድቶ መንግስትን እንዲያማርር መገፋፋትና ማንገላታት ከቀድሞው በከፋ መንገድ እየተስተዋለ ነው። እኩይ ዓላማቸው ከግል ባህርይ የመነጨና ከሥራ ጠልነት የተወለደ ብቻም አይደለም። ዋናው ዓላማቸው መንግሥት የማስፈጸም አቅም እንደሌለው በማሳየት ምሬት መፍጠር ነው። በዚህ “የፈንጂ ወረዳ” ውስጥ ምድብተኛ የሆኑ የአሸባሪው ተሰላፊዎች ተልዕኳቸውን በማስፈጸም ረገድ የተሳካላቸው ይመስላል።
መገለጫው ደግሞ በየትኛውም የመንግሥት ተቋም ውስጥ ጉዳዩን ለማስፈጸም የሚሞክር ዜጋ የሚደርስበትን መንገላታትና መጉላላት በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። “የእጅ መንሻው” ጉዳይም ቢሆን ከድርጅቱ ጥበቃ እስከ መዝገብ ቤት ሠራተኛ ድረስ የተዘረጋ ስለሆነ የተወሰነን የውሳኔ ደብዳቤን ለመውሰድ “ኪስን መዳበስ” የግድ ይሏል። ጉዳይ ፈጻሚው ሹምማ ድርድር የሚያደርገው “ልክ የመብት ያህል” ዋጋ ቆርጦ እየተከራከረ ነው። “ይህንን ጉዳይ ብፈጽም ስንት ትሰጠኛለህ/ትሰጭኛለሽ? ምን ያህል ነው የምጠየቀው? ይሄንን ያህል! አቅም ስለሌለኝ ነው እኮ ሊቀነስልኝ አይችልም? የምንጠይቀው ገንዘብ እኮ በየደረጃው ስለሚከፋፈል ብዙ ከመሰለ ስህተት ነው ወዘተ.” እንደነዚህ ዓይነቶቹ ከሻገተ ስብእና የሚመነጩ ግፎች ከቀበሌ እስከ ሚኒስቴር መ/ቤቶች የሚደመጡ የሀገሪቱ ውድቀት መገለጫዎች ናቸው።
ውጊያው የተፋፋመው በጦር ሜዳ በሚደረግ ፍልሚያ ብቻ አይደለም። በዕለት ተዕለት “የኑሮ ወረዳችን ውስጥ” በተጠመዱ ሰብዓዊ ፈንጂዎች እየቆሰልን የሥነ ልቦና ሕመም ላይ ነን። እንደታደሉት ሀገራት የዕለት ማዕዳችን መትረፍረፉ ቀርቶ እንደ አቅማችን የምንጎርሰውን ዳቦ ለመግዛት ፈተና ሆኖብን ግራ ተጋብተናል። በየዕለቱ በሰብዓዊ ፈንጂዎች የሚፈጸሙ ፀረ ሀገርና ፀረ ሕዝብ ጦርነቶችን በአሸናፊነት ለመወጣት የአብዛኞቹ መንግሥታዊ የአስፈጻሚ አካላት ሹመኞች ሀሞታቸው የቀጠነ የሚመስለው በአቅም ውስንነት ብቻ ሳይሆን የበስተኋላ ምሥጢሩ ምን እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም። እርስ በእርስ መፈራራትና ወጥመድ ውስጥ ለመደፋፈቅም “አሸባሪው ትህነግ” ኔትወርኩን በደንብ ሠርቶ ስለሄደ “የእሾህ አጥሩን” ለማፈራረስ ጊዜ እንደሚጠይቅ ይገባናል።
የናፈቀን አንድ ነገር ነው። በጦር ሜዳ እንደ ተፈጠሩት ጀግኖች ሁሉ የውስጥ ባንዳዎችን (ሰብዓዊ ፈንጂዎችን) የሚያመክኑ ጀግኖች ዛሬ ከምንግዜውም የበለጠ ያስፈልጉናል። ነፍሳቸውን ለሀገር ነፍስ የሚያውሱ፣ ለሕዝባቸው የእንባ አባሽ የሚሆኑና ለህሊናቸው ክብር የቆሙ የመንግሥት የሥራ መሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ ምሁራን፣ የመደበኛና የማሕበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎችና የማሕበረሰብ አንቂዎች የእናት ሀገር ጥሪ እያስተጋባላቸው ስለሆነ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ደረስንላችሁ ሊሉን ይገባል።
“አንዳንዶች ከትቢያ እየተነሱ ለታላላቅ ኃላፊነት ከደረሱ በኋላ የማሰብና የማስተዋል ብርታታቸው እየደከመ፣ በሰው ዘር ማለቅና በሀገር መደምሰስ፣ የየዕለቱ ደስታቸው እየሆነ …ሥራቸው ወጥመድ፣ ፍጻሚያቸው አሰቃቂ ሆኖ ያለፉና ‹እያለፉ ያሉ› ብዙዎች ናቸው። (ደራሲ ማሞ ውድነህ በአንድ መጽሐፋቸው ውስጥ ያሰፈሩት ሃሳብ)- እነዚህን መሰል ሰብዓዊያን ፈንጂዎች ለማምከን እንጨክን የማጠቃለያ መልእክታችን ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013