ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት። ይህ ሊለወጥ የማይችል የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ስሪት ነው። “ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን አይለውጥምና!” የብሔር ብሔረሰብ ሃገር መሆንም ችግር ሆኖብን አያውቅም፤ ብሔር ብሔረሰብ ሆነን ሦስት ሺህ ዓመታትን ኖረናልና። ሊክዱት፣ ሊሸሹት የማይችሉት ፍጹም ተፈጥሯዊ የራስ ማንነት ስለሆነ ይህንን እውነታ ማንም ሊክደው አይችልም።
ማንነቱን ክዶ፣ ከራሱ ተጣልቶ የተወለደው “የትግራይ ሕዝብ” ነጻ አውጭ ግንባር /ትሕነግ/ ብቻ ግን ይህንን እውነታ ካደ። ጉዱ ትሕነግ በማያቋርጥ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ግንኙነትና ትስስር ውስጥ፣ ፍጹማዊ በሆነ ፍቅርና መቻቻል የማያልቅ ሕብረትና አንድነት ፈጥረው ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ ዥንጉርጉር መልካቸውን ይዘው፣ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ጠብቀው፣ የተከበረና አኩሪ ታሪክ ያላት ታላቅ ሃገር መስርተው የኖሩ ኢትዮጵያውያንን አባቶቹንና እናቶቹን ማንነት ክዶ ተወለደ።
“ሃገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል” እንዲሉ በኢምፔሪያሊዝም የዘር ሾተላይ የእርግዝና ዘመኑን ሳይጨርስ የሰውነት ደረጃ ላይ ሳይደርስ ከኢትዮጵያ ምድር የተወለደው ጭንጋፉ ትሕነግ ከምን ጊዜውም በላይ የሰው ልጆች ወደ አንድነትና ትብብር እየመጡ ባሉበት በሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ሰዎችን፣ ያውም የአንድ አገር ዜጎችን ለመለያየት ሃገር ጥሎ በረሃ ገባ።
የራሱንና የሃገሩን የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ማንነት አውልቆ ጥሎ ለኢትዮጵያውያንና ለራሱ ሌላ አዲስ የሃሰት ማንነት ለመፍጠር ጫካ ገብቶ መከረ። በመጨረሻም “ኢትዮጵያ የአማራ ገዥዎች ሌላውን ብሔርና ብሔረሰብ በኃይል አስገድደው የፈጠሯት ሃገር ናት፤ ትግራይም የኢትዮጵያ አካል ሳትሆን ራሷን የቻለች ሃገር ናት፣ እናም ትግራይም ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም ማንነታቸውን ለማስከበርና ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር በጨቋኙ የአማራ ብሔር ላይ በጋራ መነሳትና መታገል አለባቸው” የሚል የጥላቻና የሃሰት ትርክት አዘጋጅቶ የጥፋት መርዙን ቋጥሮ ከጫካ ወጣ።
በዚህ መንገድ ለብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተቆረቆረ መስሎ ግን ደግሞ ማንነታቸውንና የሃገር ባለቤትነት መብታቸውን ነጥቆ ኢትዮጵያን ለአንድ ብሔር ብቻ ጠቅልሎ የሚሰጥ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ዥንጉርጉርነት ተፈጥሯዊ ማንነትን ክዶ የሚያስክድ እጅግ አደገኛ የክህደት፣ የውሸትና የጥፋት አጀንዳን ያለእረፍት እየፈጸመና እያስፈጸመ ግማሽ ክፍለ ዘመናትን በህይወት ቆይቷል። የሚያሳዝነው ግን በክህደት ተወልዶ በውሸት ያደገው ትሕነግ ዛሬም በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ከስህተቱ የማይማር፣ ከጥፋቱ የማይመለስ፣ በእርኩሰቱ የሚደሰት፣ እየተገረፈ የሚስቅ፣ ለቅሶ ተቀምጦ ከበሮ የሚደልቅ፣ መቃብር ውስጥም ሆኖ የሚፎክር ሳጥናኤልን የሚያስንቅ ከንቱ የእብሪተኛ ቡድን መሆኑ ነው።
ትዕግስት ፍርሐት የሚመስለው ወራዳው ትሕነግ ለብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር “መብት” በሚል ሽፋን የራሳቸውን ጥቅም ለማስቀደምና እነርሱ ብቻ የበላይ ሆነው ለመኖር የጥላቻና የልዩነት ፖለቲካን አምጠው ወልደው ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ በትጋት ሲተገብሩ የቆዩት ትህነግና ትህነጋውያን በተቃራኒው የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰባዊ ማንነት አጥፍተው አገርና ሕዝብ ክፉኛ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ አደረጉ።
በዚህም በትሕነግ የሴራ ፖለቲካ የተነሳ በገዥነት በቆዩባቸው ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ለጆሮ የሚከብዱ፣ ለሰሚ የሚያርዱ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የማይመጥኑ፣ በጥቅሉ እጅግ በጣም የሚዘገንኑና የሚያሳፍሩ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችንና ተዘርዝረው የማያልቁ ሌሎች ታህተ ሰብዕ ክንዋኔዎችንም በየፈርጁ ለማስተናገድና የታሪካችን አካል ለማድረግ ተገድደናል። ከዚህ ሁሉ የቁልቁለት ዘመን በኋላ ደግሞ በርካታ ዓመታትን በፈጀና አያሌ መስዋዕትነትን ባስከፈለ የሕዝብ ትግል ከሦስት ዓመታት በፊት በተደረገ ጥገናዊ ለውጥ የብዙዎችን ተስፋ ያለመለመ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ሃገራዊ ለውጥ ማምጣት ዕውን ማድረግ ተቻለ። ሆኖም የጥቅም ጀንበራቸው ያዘቀዘቀችባቸው የመሰላቸው ትሕነጎች ከለውጡ ማግስት ጀምሮ “ጨቋኝ-ተጨቋኝ” የሃሰት ፍረጃ ፖለቲካቸውን እንደ አዲስ አድሰው በለመዱት የጠላትነትና የፍረጃ ትርክታቸው ህዝብን አለያይተው፣ በጠላትነት አቧድነው ዳግም ከፋፍሎ በማዳከም ህዝብን በበላይነት ቀጥቅጦ ለመግዛት በብሔር ብሔረሰብ መብት ሽፋን ዳግም ሕዝብን ለጦርነት ቀሰቀሱ።
ለዚህ እኩይ ዓላማቸው መሳካት ያመቻቸው ዘንድም አንድ ጊዜ ለሃገራዊ አንድነት ሌላ ስም በመስጠትና ከእውነታው በተቃራኒ ለቃሉ አሉታዊ ትርጉም በመፈብረክ፣ የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የሚነፍግ፣ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን የሚንድ፣ ፌዴራላዊሥርዓቱን የሚያጠፋ፣ ወደ አህዳዊ ሥርዓት የሚመልስ፣ ብሔር ብሔረሰቦችንም የሚውጥ…ወዘተ የሚሉ የሃሰት ውንጀላዎችን በስፋት በለውጡ መሪዎች ላይ ሲያሰራጩ ከረሙ።
ሃያ ሰባት ዓመት ሕዝብን በግፍ እየገደለ አገርን በገፍ እየዘረፈ ተንደላቆ ከኖረበት የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት በሕዝብ ትግል ተባርሮ መቀሌ የመሸገው ትሕነግ ለሕዝብና ለሃገር ሰላም ሲባል በርካታ ማባበያዎች ቢደረግለትም ሰነፍ ሲያከብሩት የፈሩት ይመስለውና ጭራሽ እብሪቱ እየባሰበት ሄደ። በግለሰቦች ምርጫ ሳይሆን በተፈጥሮ አስገዳጅነት ሰዎች ላይ በተጫነ መንጋ አቧድኖ ጎራ ለይቶ ህዝብን ወደ እርስበእርስ ጦርነት ለማስገባት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በስፋት ሲሰራ የቆየው ዓለም ባወቀው ፀሃይ በሞቀው ከባድ የህልውና ችግር በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሕዝብ በህይወትና በሞት መካከል ሆኖ እየተጨነቀ ባለበት ሁኔታ በሕዝብ ላይ ጥፋትን ሊያስከትል በሚችል አኳኋን ምርጫ ካልተደረገ በሚል አገር ይያዝልኝ አለ።
ቀጥሎም ራሱ የጻፈውን ሕገ መንግሥት ሽሮ “በራሴ ክልል ላይ ምርጫ ካላካሄድኩ አገር ትፈርሳለች” በሚል ለውጡ ያመጣውን ነጻነት ተጠቅሞ ያለ ምንም ፍርሃት በነጻነት፣ ያውም ሃገርን ለማፍረስ ፎከረ። ሁኔታው ያሳሰባቸው ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እብሪተኛውን ለመሸምገል በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ መቀሌ ቢሄዱም “በፍጹም በመብታችን(በግል ጥቅማችን ማለታቸው ነው)፣ ይህ ቀይ መስመር ነው አንደራደርም” በማለት ታላቁን የትዮጵያውያን እሴት አሳንሰው ሽማግሌዎችን አዋርደው መለሱ። በዚያም እንደፎከሩት ባደረጉት ህጋዊ ያልሆነ የጨረባ ክልላዊ ምርጫቸው ከአምስት ሚሊዮን የክልሉ ሕዝብ ሁለት ሚሊዮን መራጭ ተመዝግቦላቸው እነርሱ ግን በአሥር ሚሊዮን ሕዝብ ተመርጠው በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ የተመዝገበ “ታሪካዊ” ምርጫ አካሂደው ሕዝባቸውን የሥልጣን ባለቤት አድርገው ምርጫው በድል ተጠናቀቀ¡
ባህላዊ ጨዋታውን 80 ለ 0 የተሸነፈው እብሪተኛው ትሕነግዳግም ወደ ሥልጣን ተመልሰው ኢትዮጵያን እያፈረሱ ለመግዛት ባለመቻላቸው ከማዕከላዊው ሥልጣን ተገፍቼያለሁ ብለው መቀሌ ከተሸሸጉ በኋላ ኢትዮጵያን እንዴት ማፍረስ እንዳለባቸው ለሦስት ዓመታት ሲያሴር ቆይተው በመጨረሻም ዕኩይ ዓላማቸውን እውን ለማድረግ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው አሳፋሪ ክህደት ፈጸሙ።
ሰብል እያጠፋ የነበረን የአንበጣ መንጋ ከሕዝብ ጋር ሲከላከል በዋለ የሰሜን ዕዝ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በተኛበት ከውጭና ከውስጥ ከብበው፣ በሰው ልጆች ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ክህደት በግፍ ፈጸሙበት። ከሃዲው ትሕነግ ይህን ያደረገው መካናይዝድ፣ መድፈኛ፣ ታንከኛና ሚሳኤልን ጨምሮ የሃገሪቱን ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን ዋነኛ የጦር መሳሪያና የጦር ክፍሎች የያዘውን የሰሜን ዕዝ ሙሉ በሙሉ በመደምሰስና መሳሪያውን ዘርፎ በመታጠቅ የሃገሪቱን የጦር ኃይል ለመቆጣጠርና ዳግም ኢትዮጵያን እያፈረሱ የመግዛት ዕኩይ ዓላማቸውን በኃይል ለማስፈጸም አስበው ነበር። ሆኖም በታሪኩ ሽንፈትን የማያውቀው ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እጅ አልሰጥም ብሎ፣ እጅግ በላቀ ወታደራዊ ጥበብና አስደናቂ ጀግንነት ታግሎ፣ ውድ መስዋዕትነትን ከፍሎ ከበባውን ሰብሮ የተፈጸመበትን ጥቃት በብቃት መክቶ የከሃዲውን የትሕነግ የኃይል ክንድ ሰብሮ መልሶታል።
ከጥቃቱ በፊት ከእኛ በላይ ወታደራዊ ዕውቀት ያለው የለም፣ “ጦርነት ለእኛ ባህላዊ ጨዋታችን ነው”፣ ከእኛ በላይ ጀግና የለም እያለ ጉራውን ለዓለም ሲቸረችር የነበረው ልክ አያውቄው የትሕነግ እብሪተኛ ኃይል በጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት ገና በመጀመሪያው ቀን አከርካሪውን ተመትቶ መፍረክረክ ጀመረ። ጭቆና ካማረረው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ታግሎያስወገደውን የደርግ ሥርዓት የሕዝብን ታሪክ በመስረቅና ለራሱ ብቻ በመስጠት በአስራ ሰባት ዓመት ትግል ደርግን ገረሰስን እያለ፤ “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የሚል የሃሰት ታሪክ አስጽፎ ዕድሜ ልኩን በውሸት ጀብዱ ሲታበይ የኖረው ትሕነግ አስራ ሰባት ቀን ሳይዋጋ ተፍረከረከ።
በሃሳብ ተሸንፎ ከማዕከላዊ መንግሥትነት ተባርሮ በ “ሕዝብ” ዋሻ ተከልሎ ከመሸገበት መቀሌም ተባረረ። ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የሃገሪቱን ጦር ወግቶ ያዝኩ ቢልም “ባህላዊ ጨዋታዬ ነው” በሚለው ጦርነት ሰማንያ ለዜሮ ተሸንፎ ፈርጥጦ ተንቤን የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ገባ። ከሩብ ክፍለ ዘመናት በላይ ግፍና በደልን ያሳለፈው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ አንድ ላይ ቆርጦ በመነሳቱና ጥቃቱን በመመከቱ ያሰበውን ማሳካት ያልቻለው ህወሓት እንደ ውልደት ዘመኑ ተመልሶ ወደ ቀበሮ ጉድጓድ ገብቶ በምላሱ ታንክና መድፍ እየማረከ፣ በወሬ ጀት እየጣለ፣ በፕሮፓጋንዳ መከላከያ ሠራዊትን እየደመሰሰ ስምንት ወራትን አሳልፏል። ሆኖም ጀግንነት መለያው የሆነው የአገር መከላከያ ሠራዊት ጉምቱ የትሕነግ መሪዎችን ከገቡበት እየገባ እንደ ተኩላ እየታደኑ፣ እንደ አይጥ ከየጉድጓዱ አንገታቸውን እየታነቁ ለሕግ እንዲቀርቡ አደረገ።
ብዙ ተለምነው እጃቸውን በሰላም አልሰጥ ያሉ፣ እንዲያውም በሰላም እጃችሁን ስጡ የሚለውን የመከላከያ ሠራዊት የሰላም ጥሪና በጎነት እንደለመዱት ለጥቃትና ለጥፋት መፈጸሚያ ለመጠቀም የሞከሩ አንዳንድ የክፋት ውላጅ፣ የሕዝብ ጠላት የሆኑ ከሃዲ የትሕነግ መሪዎችን ደግሞ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድባቸው በማድረግ ላይመለሱ ወደ መቃብር እንዲሸኙ አደረጋቸው። በዚህም በጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት አይበገሬ ክንድ ተደቁሶ ዳግም ሥልጣን የመያዝና አገርን እርሱን ብቻ በሚጠቅም መንገድ የመግዛት አለያም የማፍረስ የትሕነግ እኩይ ዓላማ ሙሉ በሙሉ ከሸፈ። በመጨረሻም ለጥቂት ከሃዲ ሃገር ሻጭ የትሕነግ ወንበዴዎች ተብሎ ሕዝብ በረሃብ እንዳይቸገርና ክረምቱን ያለምንም ችግር የእርሻ ስራው እንዲከናውን በማሰብ መንግሥት በሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ ከትግራይ ክልል ወጣ።
ሲይዟት ጭብጥ ሙሉ፤ ሲለቋት ሜዳ ሙሉ ይሁን እንጂ የመከላከያን ከትግራይ መውጣት ተከትሎ ከነአካቴው ከምድረ ገጽ ካልጠፋ በቀር የማይጠፋው ትሕነግ ከጉድጓዱ ወጣ፤ የተወለደበት፣ ያደገበትና ያረጀበት ክህደቱ፣ ውሸቱና እብሪቱም ከበፊቱ ብሶ መጣ። በመከላከያ ወታደራዊ ስትራቴጂም ይሁን በሌላ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት ከወንጀል መሸሸጊያ የብሔር ዋሻው በአሻገር ጥቂት የአፋርና የአማራ አዋሳኝ መሬቶችንም ያዘ። እናም እብሪቱና ውሸቱ አገር ምድር አልበቃው አለ። ያም ሆኖ በክልላዊ ኃይሎችና በአካባቢው አርሶ አደር ሚሊሻዎች ብቻ በየቀኑ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣል፣ ሕዝብ ለመቅበር እስኪቸገር ድረስ ታጣቂ ኃይሎቹን ያስጨርሳል፣ በየግንባሩ ይደመሰሳል፣ በገፍ ይማረካል። ጁንታው ግን በሽንፈቱ የሚፎክር፣ በሞቱ የሚደንስ፣ እንደ ሳጥናኤል ላይመለስ ወደ ጥልቁ እስኪወረወር ድረስ በስንፍናው የሚኮራ እብሪተኛ የማይድን ከንቱ ታህተ-ሰብዕ ቡድን በመሆኑ ዛሬም በውሸቱና በምናባዊ ጀብደኝነቱ ቀጥሏል።
ሲደመሰስ ደመሰስናቸው፣ ሲማረክ ማረክናቸው፣ የያዘውን ሲነጠቅ ያዝንባቸው በሚል የቁም ቅዠቱ ሕዝብ ማደናገሩን ቀጥሎበታል። ይህ የመጨረሻው ለመድረሱ ምልክት ይመስላል። ከአንድ ወር የጥሞና ጊዜ በኋላ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የማያዳግም ክንዱን ሊያሳርፍበት ወስኗል። በአጭር ጊዜ ውስጥም በሁሉም ግንባር አንጸባራቂ ድል እየተመዘገበ ይገኛል። የጁንታው ውሸትና እብሪት ፈጽሞ የማይሰማበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ኢትዮጵያን ለማፍረስ በቁሙ ሲኦል እስከመሄድ የቆረጠው ጁንታው ሲኦል የመግባት ሕልሙ በቅርቡ እውን ይሆናል። ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ሞት የኢትዮጵያን ሞቷን ለሚፈልጉ ሁሉ!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2013