በውጭ አገር ያለው የአሸባሪው ጁንታ ተላላኪ ጀሌ፤ አንዴ በሆዱ በመንከባለል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጀርባው በመንጋለል ያስጥሉልኛል ብሎ እምነት በጣለባቸው ኃያላኑ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት ደጅ ከመጥናት ሰሞኑን ጋብ ያለ ይመስላል፡፡ አሁን ደግሞ ቀድሞም ቢሆን የተካነበት የቆርጦ ቀጥልነቱን ስራ አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ በመቀላመዱ በኩል የሚያዛምተው የውሸት ወሬ በብዙ እጥፍ የጨመረ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ወደ አማራ እና አፋር ክልል በእውር ድንብሩ የገባው አሸባሪው ትህነግ፣ ያልያዛቸውን ቦታዎች ያዘ በሚል የሚያባዛው መረጃ ከእውነት የራቀ ስለመሆኑ በእውነተኛው መረጃ በመረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡
በአገር ቤት ያለውም ባንዳው ጁንታ፣ በቆርጦ ቀጥልነቱ ውጭ አገር ካለው ባንዳው ተላላኪ ጋር ፍጹም አንድ ነው፡፡ ያው የእባብ ልጅ እባብ እንዲሉ ማለት ነው፤ እዚህ ያለው አሸባሪ፣ አንዴ ለማኝ፤ ሌላ ጊዜ ሴት በመምሰል በግፍ ለመውረር ወደቋመጠው የአማራ ወይም የአፋር አንድ ከተማ ተጠግቶ አንድ ወይም ሁለት በመሆን ፎቶ ይነሳል፤ በቃ ከዚያ በኋላ ያን ቦታ በታላቅ ተጋድሎ እንዳገኘና አካባቢውን እንደተቆጣጠረ ያስመስላል፡፡ ውሸቱን ኳኩሎ በማቅረብ ያልሞከረውን ተግባር አከናወንኩ ማለቱንም ውጭ አገር ያለው ባንዳ ያደርስለታል፡፡ መቼ ተያዘና ቢባል፤ መቼ ሞከሩና ነው መልሱ፡፡
አሸባሪው ጁንታ፣ ቀደም ሲል እንዳሻው ያደርግ የነበረው የህግ ጥሰትን መፈጸም ባለመቻሉ፤ እንደፈለገው ከውጭ አገር ያለምንም ቀረጥ ልቡ የወደደውን እቃ ማስገባት ባለመቻሉ፤ ውስጡ እንደሚመራው ሌላውን ህዝብ እያስለቀሰ የለመደውን ድልቅቅ ያለ ኑሮ ማጣጣም ባለመቻሉ የእግር እሳት ሆኖበታል፡፡ በዚህ ቆሽቱ ቢያርም ከምንም በላይ ደግሞ በህዝብ ተጽዕኖ እና በለውጡ አመራር ብልህነት እንደ ቀልድ ቁጭ አድርጎት የሄደው ስልጣኑ ድንገት ውል ሲልበት በለውጡ አመራር የተነገረውን ‹‹የያዝከውን ይዘህ ተቀመጥ፤ ከዚህ በኋላ አትረብሽ›› የሚለውን ተግሳጽ ሁሉ ረስቶት ድንገት ብትት ብሎ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ለመፈረካከሱ የመጀመሪያ ቀን ሆኖታል፡፡
የፌዴራል ሰራዊት፣ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም መቀሌን መቆጣጠሩን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጦርነቱ መጠናቀቁን እና ቀጣይ የመንግሥታቸው ተግባር በሕግ የሚፈለጉ የህወሓት አመራሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋል እና ትግራይን መልሶ መገንባት መሆኑን በወቅቱ ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህንንም በአግባቡ ስለመፈጸሙ ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች በመከላከያ ቁጥጥር ስር ሲውሉ የተወሰኑት ደግሞ መገደላቸው ይታወሳል፡፡
እያደር በቁጥርም በሐሳብም እየመነመነ የመጣው የሽብርተኛው ቡድን ህወሓት፣ እምጥ ይግባ ስምጥ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ግራ ግብት ብሎታል፡ ፡ ኃይል ይሆኑት ዘንድ ከዚህ ቀደም በጠላትነት ሲፈርጀው የነበረውን ሸኔን፣ አጋር ይሆነው ዘንድ በመሻቱ ከሰሞኑን ያልተቀደሰ ጋብቻውን እንደ እርሱ በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ከዚሁ አካል ጋር መስርቷል፡፡
እነዚህ ህወሓት እና ሸኔ የተባሉ አሸባሪዎች በግብራቸው ታናሽ ታላቅ የሚያስብላቸውን ተግባር በመፈጸም እዚህ የደረሱ ቢሆንም አሁን ያላቸው ነገር ቢቆጠር ያልተገራ ምላስ ብቻ ነው፡፡ ሁለቱም በቆርጦ ቀጥልነታቸው ይታወቃሉ፡፡ እርግጥ ነው በዚህ ተግባራቸው ሲያሞኟቸው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍል አሁን ግልጽ አድርገውላቸዋል፡፡
ጀግናው የኢትዮጵያ ሰራዊት ‹‹ይህን ከተማ ያዝን›› እያሉ የፎከሩባቸውን አካባቢዎች በወሬ እንጂ በተግባር አለመያዛቸውን እግር በእግር እየተከታተለ ለኢትዮጵያውኑ በተግባር በማሳየት ላይ ይገኛል፡ ፡ ጁንታው የለመደውን ውሸት እያስወራ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሰራዊት እረፍት በማጣቱ ከተራራው ማዶ በመሆን እያላዘነ ይገኛል፡፡
በጣት የሚቆጠር ጁንታ እንደምንም በቅጥረኞች እየታገዘ ወደመሃል ቢዘልቅም በጀግናው የኢትዮጵያ ሰራዊት ተቆርጦ እየቀረ በመሆኑ እጣ ፈንታው ከሞት ጋር መላተም ብቻ ሆኗል፡፡ ዓላማ የሌለውን ጦርነት አንግቦ እየተደናበረ ያለው አሸባሪው ትህነግ በጀግናው የኢትዮጵያ ልጅ አይቀጡ ቅጣት በመቀጣት ላይ ነው፡፡ በቅጥረኞች ታግዞ በሰፊው መንገድ የገባ የመሰለው ጁንታ፣ አሁን ዙሪያ ገባው ገደል ብቻ አልሆነበትም፤ መቀበሪያው አጠገቡ ተገኝቷል፡፡
እንዲህም እየሆነ ባለበት ጊዜ እንኳ እስትንፋሱ እንዳልተቋረጠ የሚሞግቱለት የተለያዩ የውጭ አገር መገናኛ ብዙኃን በርታ፤ ግፋ እያሉ መገኘታቸው ፍርደ ገምድልነታቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ለሽብርተኛው ጁንታ ለቆርጦ ቀጥል መረጃው ዋና አቀንቃኞች ሆነው እያገለገሉት በመሆናቸው ለተራ ፕሮፓጋንዳው ብርታት እየሆኑት ይገኛሉ፡፡
ምንም እንኳ እነዚህ መገናኛ ብዙሃን፣ የቱሪናፋውን ጁንታ የሐሰት ፕሮፓጋዳ ተቀብለው ቢያስተጋቡም፤ ጁንታው ውሸታም ስለመሆኑ ኢትዮጵያውያን በአግባቡ እየተገነዘቡት ነው፡፡ ለዚህ ትልቁ ማሳያ የሚሆነው ከየትኛውም የኢትዮጵያ ጥግ የአሸባሪውን የሚቃትት እስትንፋስ ጸጥ ለማድረግ ያለማንም ጎትጓች ‹‹ሆ!›› ብለው መነሳታቸው ነው፡፡
አሁንም አሸባሪው ህወሓት ሰርጎ ገቦችን ወደ መሃል በመላክ ‹‹እዚህ ቦታ ገባን፤ ይህን አካባቢ ተቆጣጠርን›› እያለ የህዝብን ስነ ልቦና ለመስለብ የሚያደርጋቸው የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ከወዲህ መረዳት አግባብ ነው፤ ነገር ግን ሁሉም መረጃዎች ባዶ እና የውሸት ጋጋታ መሆናቸውን ማወቅ ደግሞ ብልህነት ነው፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም መንገድ በውሸትና በመቀላመድ የሚወረስ ከተማም ሆነ መሬት አይኖርም፡፡ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የአማራ ልዩ ኃይል እንዲሁም ከተለያዩ ክልሎች የተሰባሰቡ ልዩ ኃይሎች፣ አሸባሪውን ትህነግ ከተደበቀበት ጉድጓድ ፈንቅለው እያወጡ በመምታት ድል እያስመዘገቡ ነው፡፡
ወትሮም ቢሆን አገር ለመበተን የተነሳን የአገር ጠላት በጋራ መመከት የተለመደ ነው፡፡ አሁንም እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሉዓላዊነቷን የሚዳፈር የትኛውንም ጠላት መቼም ቢሆን ታግሳ አታውቅም፡፡ አሻፈረኝ ብሎ ቆርጦ የገባውን ቆርጣ ያስቀረችው ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ዋሾው እና ዘራፊው ጁንታም በሀሺሽ ተገፋፍቶ መገኘት ወደሌለበት አካባቢ ሳያስበው ዘሎ እየገባ ጉድ እየሆነ ነው፡፡ ዘሎ እንደገባ ሁሉ ዘሎ መውጣት ግን የህልም እንጀራ ሆኖበታል፡፡ ለማፍረስ የቋመጠው ስፍራ ሁሉ እርሱ ራሱ ፈርሶ እየተቀበረበት ነው፡ ፡ የተረፈ ቢኖር እንኳ ሆዱን ለመሙላት ሲል ዘርፎ ለማምለጥ በሚያደርገው ሙከራ እየተዋረደና እየተሸማቀቀ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ አሸባሪው ጁንታ በሚያፈልቃቸው የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች ማንም አይታለልም፤ የሐሰት ፕሮፓጋንዳውን እውነት እየገለጠው በመሆኑ ጊዜ ያለፈበትና ያረጀ አካሄድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በእውነት የቆመች አገር እንደመሆኗ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ አትፈርስም፡፡ ሰላም!
ቅድስት ሰለሞን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2013 ዓ.ም