በተለያዩ መድረኮች እና በማህበራዊ ሚድያዎች የሚሰማቸውን ስሜት በግልጽ በመናገር ይታወቃሉ፡፡ `መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ` በሚል ርዕስ በ2011 ዓ.ም ያሳተሙት መጽሀፍ ከ80ሺ ኮፒ በላይ ተሰራጭቷል፡፡ በኢትዮጵያ ባህል እና ታሪክ ላይ የሚያጠነጥኑ ሁለት መጽሀፎችን አዘጋጅተው ለማሳተምም ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ከግል እንቅስቃሴያቸው በተጨማሪ በእምነቶች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር፤ በብሄረሰቦች መሀከል ያለውን ፍቅር ለማዳበር እና ብሄራዊ እርቅና መግባባት ለመፍጠር አልሞ በሚንቀሳቀሰው `ፍቅር ያሸንፋል` ማህበር ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ የዛሬው እንግዳችን መምህር ታዬ ቦጋለ ናቸው፡፡ ሀገራችን በታሪኳ የገጠሟትን ፈተናዎች እና ያለፈችበትን ሁኔታ በተመለከተ ከመምህር ታዬ ጋር ቆይታ አድርገን ያጠናቀርነውን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ሃገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ እንደ አንድ የታሪክ ምሁር እንዴት ያዩታል፤ እንዲህ አይነት ችግሮችስ ከዚህ በፊት ገጥመው ያውቃሉ?
መምህር ታዬ፡- ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመዋት ያውቃሉ። በተለይም የውጪ ወረራዎች በጣም በስፋት የነበሩባቸው ጊዜያት ነበሩ። በአጭሩ በ1875 በጉንዲት ላይ፣ በ1976 በጉራህ ላይ እንዲሁም ደግሞ በተለያየ ጊዜ ከጣልያን የተቃጣብን ወረራ አለ። በጊሪጎሪያውያን የዘመን ቀመር 1896 አድዋ ላይ ከዛ ደግሞ ከ1936-1941 እንዲሁ በተመሳሳይ ለሁለተኛ ጊዜ ጣልያን ኢትዮጵያን የወረረችበት ሁኔታ አለ። ከዛም አልፎ ሶማሊያ በ1968 አካባቢ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈጸመችበት አለ።
እነዚህና የመሳሰሉት ግን በአብዛኛው የሚቃጡት ከውጪ ከመሆኑ አንጻር በአንድነት ሆነን በቀላሉ መመከት የምንችልበት አይነት ሁኔታ ነበር። ከዛ አለፍ ብለን ስንመለከት ሌሎች አውዶች አሉ፤ የሀገር ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭቶች ይካሄዱ ነበር። እነዚህ ግጭቶች ምጣኔ ሀብትን የበላይ ሆኖ ለመያዝ የሚደረጉና ወደኋለኛው ዘመን ላይ በብዛት የሚስተዋሉ ናቸው። ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ ያሉትን ዋና ዋና የታሪክ ዳራዎችን ትተን አሁን ያጋጠመን ፈተና እጅግ በጣም ከባድ ፈተና ነው። ከባድ የሚያደርገው በአንድ በኩል አለምአቀፉ የምእራብ ሀይል የሞኖፖሊ ካፒታሊስት መንግስት ነው።
የአሜሪካንን መንግስት ጨምሮ የምዕራባውያን ሃገራት መንግስት የህዝብ መንግስት ሳይሆን የታክስ ከፋዮች መንግስት ነው። የታክስ ከፋዮች መንግስት እንደመሆኑ ደግሞ የሞኖፖሊስት ካፒታሊስቶችን ጥቅም የማስጠበቅ አለማቀፋዊ የሆነ ፍላጎት አለው። ኢትዮጵያ አዲስ በጀመረችው ሞዴል ከምስራቁ አለም ጋር ለምሳሌ ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከቱርክ እና ከመሳሰሉት ጋር የምታደርገው ግንኙነት ለምእራቡ አለም ከፍተኛ የሆነ ጫና ነው። ሁለተኛው እንደምናውቀው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ ጀርመኖች 300 መንግስታት ነበሩ። እነዚህ መንግስታት ወደአንድነት እንዲመጡ ያደረገው የኢኮኖሚ ውህደታቸው ነው። ያ የኢኮኖሚ ውህደት ወደ ፖለቲካ ውህደት ሄዶ ወደ 38 ከዛ ደግሞ ወደ አንድ መጥተው ዛሬ በአውሮፓ ውስጥ አንደኛ ኢኮኖሚ በአለም ላይ ደግሞ አራተኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመገንባት ችለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ መልክ ከኤርትራ ጋር ያደረገው ግንኙነት ከጅቡቲ ጋር ከሶማሌ ጋር በአፍሪካ ቀንድ የጀመረውን ግንኙነት እያሰፋ ወደ ምስራቅ አፍሪካ የሚሄድበት እና ውህደቱ እየተጠናከረ የሚሄድ ከሆነ ሸቀጥ ተቀባዮች አንሆንም። የምንደራደርበት አቅም በጣም እያደገ ይመጣል። ለምሳሌ በቀላሉ ለማስረዳት ለውጥ ብለን የምንጠራው 2010 መጋቢት ከመጀመሩ በፊት የገቢ ንግድ የሚያድገው 80 በመቶ ነበር፤ ከዚህ ውስጥ ወደውጪ የምንልከው 20 በመቶ ብቻ ነበር የሚያድገው። ይሄ ማለት ደግሞ የውጭ ሃይሎች የሚፈልጉት አይነት መንግስት ነበር ማለት ነው።
አሁን ግን ወደውጪ የምንልካቸው ምርቶች እየጨመሩ መምጣታቸው፤ እጅግ በጣም አዳዲስ የሆኑ አተያዩች መምጣታቸው እና የአፍሪካ መዲና መሆናችን ኢትዮጵያ ካደገች የአፍሪካ ሞዴል ትሆናለች በሚል አለምአቀፉ ሀይል ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥር አድሯል። ሌላው ግብፅ በአባይ ጉዳይ ሁልጊዜ የኢትዮጵያ ቋሚ ጠላት የመሆኗ ነገር ለዲፕሎማሲ ብለን ባንናገረውም ግን የማይካድራ እውነታ ነው። ስለዚህ ግብጽ በተቻላት አቅም ሁሉ ለምሳሌ የጉሙዝ ሽፍቶችን በከፍተኛ ደረጃ የምታስታጥቀው ግብፅ እንደሆነች የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ። ሱዳን የግብፅን የውክልና ጦርነት ይዛ የተነሳችበት ሁኔታ አለ። ግብፅ የአረቡ አለም ሻምፒዮን ናት፤ ልክ እኛ የአፍሪካ ህብረት መሪ እንደሆንን ሁሉ ግብፅ ደግሞ የአረቡ አለም መቀመጫ ናት። ከዚህ አንፃር የአረቡ አለም በቀላሉ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥር የሚያደርጉ ነገሮችን አድርጋ እንዳየነው ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ዜጎቻችን ከፍተኛ የሆነ ጫና ደርሶባቸዋል።
ብሪታንያ ሁልጊዜ በቀኝ ግዛት ይዛቸው የነበሩ ሀገራት ኮመን ዌልዝ የሚባሉት የበላይ ጠባቂ አድርጋ ነው እራሷን የምትገምተው። ከዚህ አኳያ የግብፅን ፍላጎት ከማስጠበቅ ጎን ትቆማለች። ለምን እንደምናውቀው 1882 ግብፅን ወርራ በቀኝ ግዛት ከያዘች በኋላ እስከ 1956 ቆይታለች፤ ምንም እንኳን 1922 የግብጾች ጊዜያዊ ነጻነት ቢኖርም። ስለዚህ የብሪታንያ ጫና ከዚህም የሚመነጭ ይሆናል።
ከዛ ባለፈ የአባይ ውሃ ጥቁር አባይ ከኛ ጋር 86 በመቶ ነው። ወደእስራኤል እና የተለያዩ ሀገሮች መስጠት ጀምራለች አሻግራ። እነዚህ ፍላጎቶች ተዳምረው ኢትዮጵያ ከምንም ነገር በላይ ፈተና ያጋጠማት ወቅት ነው። እነዚሁ ሀይሎች ይህንን ለማስፈጸም ከጠቀስኩት የቤኒሻንጉል ታጣቂዎች የበለጡ ሁለት ጠንካራ ድርጅቶች ፈጥረዋል። አንደኛው ሕወሐት የምንለው ለ27 ዓመት የኢትዮጵያን ህዝብ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና በባህላዊ የበላይነት ሰቅዞ የያዘ ሀይል አለ። ይሄ ሀይል ከስልጣን ተወግዷል። ከስልጣን ከተወገደ በኋላ የያዛቸው የበላይነት ስሜቶች እና ያጋብሳቸው የነበሩት ስሜቶች ቀርተውበታል። ስልጣንን መከታ አድርጎ የሚጠቀማቸው ሁሉ ነገሮች ቀርተውበታል። ከዚህ አኳያ በድጋሚ ወደስልጣን የመምጣት ሰፊ የሆነ ቀቢፀ ተስፋ አለው። ስለዚህ ለነሱ ቀኝ እጅ ሆኖ የማገልገል ሁኔታ ስላለው የከፈተው የውክልና ጦርነት ነው።
ሕወሓት ሁለት አይነት አላማዎች አሉት፤ አንደኛው የውክልና ጦርነት ነው፤ ስለተሸነፈ እነዚህ ሀይሎች ካላገዙት በስተቀር በፊትም ስልጣን የያዘው በእነሱ እርዳታ ነው። አሁንም እነሱ ካላገዙት ወደስልጣን ተመልሶ ደካማ መንግስት ሆኖ መቀመጥ አይችልም። ሁለተኛው የቀቢጸ ተስፋ የስልጣን ፍላጎት አለ። ስለዚህ ጦርነቱን የሚያካሂደው ውስጥ ያሉ ሰዎችን ጭምር በመጠቀም ነው። የበፊቶቹ ቀጥተኛ ውጊያ ነው የሚያደርጉት። ሶማሌ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ላይ ውጊያ ስታካሂድ የቀጥታ የፊት ለፊት ውጊያ ነው። ጣልያን የፊት ለፊት ውጊያ ነው። ይሄኛው ግን ውስጥ የራሱ የሆኑ የህቡእ አደረጃጀቶች በየከተማው እና በገጠር ውስጥ አሉት። ስለዚህ በቀላሉ በማእከል በመሆን መረጃዎችን የማቀበል ሁኔታ አለ። ቅድም እንዳልኩት አለምአቀፉ ሀይል ይረዳዋል፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ሸኔ አለ። ኦነግ ሸኔ በምእራብ በኩል በተመሳሳይ ጊዜ ከሕወሓት ጋር የተመሰረተ፤ ሁለቱም ወደ ግማሽ ክፍለ ዘመን የተጠጋ እድሜ አላቸው። ተሳስረው የመጡ ከመሆኑ አኳያ ኢትዮጵያ ከምንም ነገር በላይ የተፈተነችበት ወቅት አሁን ነው ብል ማጋነን አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የታሪክ መምህር እንደመሆንዎ በኢትዮጵያ በተወሰነ መልኩ ላለው መከፋፈል ሕወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት 27 ዓመታት አንዱን ብሄር ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ አድርጎ በህብረተሰቡ እንዲሳል ሲያደርግ የታሪክ መምህራን ምን ሰራችሁ?
መምህር ታዬ፡- የታሪክ መምህራን ማስተማር የምንችለው የተዘጋጀውን ስርአተ ትምህርት ነው። ከስርአተ ትምህርቱ አልፎ መሄድ አይቻልም። ይሁንና እኔ በአብዛኛው የታሪክ ትምህርት ያስተማርኩት በሀይስኩል እና ለ14 ዓመት ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የስነ-ምግባር እና የስነ-ዜጋ ትምህርት ነው። በዚህ ውስጥ ከሰራናቸው ነገሮች አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠናከር ማህበረሰቡ ጥሩ የሆነ የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲኖረው የትምህርቶቹ እራሱ ባህሪ ስለሚፈቅድ ደግሞ የታሪክ ትምህርት አላማ ያለፈውን በማጥናት ጥንካሬዎችን አጉልቶ ማውጣት ድክመቶች ተቀንሰው እንዲመጡ ማድረግ እና ለወደፊት ብሩህ ህይወት መመስረት ነው።
ስነ-ምግባርና ስነ-ዜጋን ስንመለከት በዋናነት የሚያተኩረው ህገመንግስት ላይ ነው። ህገመንግስቱ ደግሞ እንደሚወራው አይደለም፤ ጥቂት ቦታዎች ችግሮች አሉ መስተካከል ያለባቸው፤ ግን አብዛኛው የሚያተኩረው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ላይ ነው። ስለዚህ እነዚህ ላይ አተኩሮ ስለሰብአዊ ስለዲሞክራሲያዊ መብት ግንዛቤ እንዲኖር በጣም ተሰርቷል። ይሄም ደግሞ በአጠቃላይ በሀገሪቷ ውስጥ በመጣው ለውጥ ውስጥ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ድርሻ ነበረው።
መንግስት የታሪክ ትምህርት ክፍልን የማቀጨጭ ሚና በመጫወቱ፤ ተማሪዎች የታሪክ ትምህርትን የማይመርጡበት ሁኔታ ተፈጥሮ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አንድ አመት የሚቀበለው ተማሪ እስከማጣት የደረሰበት ሁኔታ ነበር። ነገር ግን መምህራን በአመዛኙ ባለፈው ስርአት ውስጥ በነበረው ጊዜ ኢትዮጵያዊነት በጣም በሚቀነቀንበት ስርአት የሰለጠንን በመሆናችን ህዝቡን ለማዋሀድ ተንቀሳቅሰናል።
እንደግል ከሆነ ደግሞ እንደ አንድ ማህበራዊ አንቂ ላለፉት አስር ዓመታት ይደረጉ የነበሩ ጭቆናዎች እና በደሎችን አሁን በምጠቀምበት የማህበራዊ ሚድያ ላይ በግልጽ መልእክት ሳስተላልፍ ነበር። ስለዚህ በጣም በሚቻለን አቅም በአንድ መልክ በትምህርቱ ዘርፍ በሌላ በኩል ደግሞ በራሳችን ማህበራዊ አንቂነት ጥረት ለማድረግ ሞክረናል።
አዲስ ዘመን፡– እርሶ በሰፊው የሚታወቁት በማህበራዊ ሚድያ ላይ ስለሀገሮት የተሰማዎትን መልእክት በማስተላለፍ እና ከሀገር በተቃርኖ የቆሙ አካላትን በመሞገት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእርሶን ጨምሮ የበርካታ ስለሀገር የሚሟገቱ ሰዎች የፌስቡክ አድራሻ በተደጋጋሚ እገዳ ሲጣልባችሁ ተስተውሏል። ይሄ ከምን የመጣ ነው?
መምህር ታዬ፡- አለም አቀፉ ሀይል ኢትዮጵያን የሚዋጋው በአገኛቸው መንገዶች በሙሉ ነው። እንደምናየው አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ወርልድ ባንክ የሳተላይት ስልክ ድጋፍን ጨምሮ የሚያደርጉትን ማየት እንችላለን። ቢቢሲ ሲኤንኤን አልጀዚራ የመሳሰሉ ሚድያዎች አንድም ሶስትም ሆነው የኢትዮጵያን መንግስት የሚያጠለሽ ነገር ሲኖር በጣም አጉልተው ያወጣሉ። ከዛ ሕወሓት የሚሰራቸውን በደሎች ግን ባላየ እና ባልሰማ የሚያልፉበት ሁኔታ አለ። ወደማህበራዊ ሚድያው ስንመጣ ብዙ ነገሮችን የማድረግ አቅም አለው። ለምንድነው የሚዘጉት፣ ለምሳሌ የእነ ናትናኤል መኮንን፣ ስዩም ተሾመ፣ ጌታቸው ሽፈራው፣ ደረጄ ሀብተወልድና እኔን ጨምሮ የበርካቶችን የፌስቡክ አካውንት እየዘጉ ነው። የሚያዘጉበት ምክንያት እነሱ የፕሮፓጋንዳ የበላይነቱን እንዲይዙ ነው። ፌስቡክ የአሜሪካ ድርጅት ነው። ስለዚህ እኔ አሁን ባንዳ የምትል ቃል ጻፍኩ፣ ባንዳ ናት ሌላ ነገር አይደለም። ሶስት አካውንት ከፍቼ ሶስቱንም ዘግተውታል። አንዱን ለአንድ ወር፣ አንደኛውን ለ15 ቀን እገዳውን ጨርሷል። አንደኛውን ደግሞ ለሶስት ቀን እና ተደጋጋሚ የሆነ ነገር ነው የሚያደርጉት። የጦርነቱ አካል ነው ብዬ ነው የምወስደው።
አዲስ ዘመን፡-በርካታ ሀያላን የሚባሉ ሀገራት እና ድርጅቶች ከኢትዮጵያ በተፃራሪ መቆማቸውን እያሳዩ ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ በተቸገረች ጊዜ የሚሰጡት ምላሽ ምን ይመስል ነበር?
መምህር ታዬ፡- እነሱ የሚያደርጉት ዋናው ነገር ደካማ እነሱ የሚፈልጉትን አላማ የሚያስፈጽም መንግስት በሚኖርበት ጊዜ የተለሳለሰ ነገር ይዘው ነው የሚቆዩት። ሕወሓት ለእነሱ የሚመቻቸው ድርጅት ነበር። ምክንያቱም ያለው እድገት በባለሀብቶች እና በሌላው ዜጋ መሀል ሰፊ የሀብት ልዩነት እየፈጠረ ነበር። እንዳየነው ገበሬዎችን እያፈናቀለ ስድስት ወር የማይሞላ ካሳ እየተሰጣቸው ሜዳ የሚወጡበት ሁኔታ ነበር። ከዛ ውጪ ሰፋፊ የሆኑ እርሻዎችን የያዙ ባለሀብቶች አሉ። እነሱ ገንዘባቸውን በውጪ ባንኮች የሚያከማቹበት እና ምዕራባውያን የሚፈልጉት አይነት የህንጻ ብዛት፤ እድገት የሌለበት አጠቃላይ የቻይና አይነት እድገት አይደለም የምንከተለው። ከዛ አኳያ ይሄንን በጣም ይፈልጉት ነበር። እርዳታው እንዳያማህ ስጠው እንዳይበላ ግፋው አይነት ነበር።
ሰው ሁልጊዜ በተረጂነት ስሜት ውስጥ እንዲኖር የሚያደርግ በጣም አደገኛ የሆነ ለምሳሌ ማዳበሪያ ያመጣሉ፤ ማዳበሪያው እኛ ሀገር አይደለም የሚመረተው። ለዚህም በጣም ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ያገኛሉ፤ የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና ብለን እንዘምራለን፤ ግን ጥሬ ቡና ልከን መልሰን ዱቄቱን እናስገባለን። ይሄ አይነት የእድገት ጎዳና ለነሱ አመቺ ስለነበረ መንግስት እንዳይወድቅም እንዳይነሳም አድርገው የሚይዙበት ሁኔታ ነበር። በአጠቃላይ ድጋፋቸው ኢትዮጵያ እንድታድግ የሚያደርግ አልነበረም።
አሁን ያለው ግን አስደንጋጭ ነገር ነው የሆነው። እንዳየነው የባነኑት ቆይተው ነው። ለዶ/ር አብይ የኖቬል ሽልማት መሸለም የኢትዮጵያን የእድገት አቅጣጫ የተለያዩ ሚድያዎቻቸው ያወሩ ነበር። በኋላ ላይ ግን ሲመለከቱት ፈጣን የሆኑ የኢኮኖሚ መተሳሰሮች እንደሰማነው ከዚህ ኬንያ ፈጣን አውቶቢስ ሊጀመር ነበር። ከኤርትራ ጋር ነፃ የሆነ ግንኙነት ሲመሰረት እነዚህ ነገሮች የኢኮኖሚ እድገትን ስለሚያመጡ ተከላከሉን። ግን የበፊቱ የሚፈልጉት አይነት ነው፤ የሚፈልጉት ሆኖም ተረድተንም በእግራችን እንድንቆም አይፈልጉም።
ሁልጊዜ እጃችንን ለእርዳታ እንድንዘረጋ እና ፍላጎታቸው ያለንን ጥሬ ሀብት መውሰድ ነው። መልሰው ኢንቨስተር መሆን ነው ልክ እንደኬንያ። አሁን ኬኒያ ብንሄድ ከአስር ሱቆች ያለማጋነን ሰባቱ የውጪ ዜጎች ናቸው። ስለዚህ እንደሱ አይነት ነገር እንዲፈጠር ነው የሚፈልጉት። እነሱ የራሳቸው የሆነ የኢንዱስትሪ መንደር የሚገነቡበት ሁኔታ ከአፍሪካ ርካሽ የሰው ጉልበት ሰፈራ የሚያደርጉበት ቦታ ጥሬ እቃ እና ገበያ ነው የሚፈልጉት። እነዚህን አንድ ላይ የሚያደርጉበት ሁኔታ ስለነበረ በእዛ መልክ ነው የማየው።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ህዝብና በአሸባሪው ሕወሓት መካከል የሚደረገውን ጦርነት የተወሰኑ አካላት በሁለቱም ወገን ተጎጂዎቹ እኛው ነን በማለት የወንድማማቾች ጦርነት በማለት ይገልጹታል። አንተ በቅርቡ በሚድያ ላይ በነበረህ ቆይታ የወንድማማቾች ጦርነት እንዳልሆነ ተናግረሀል፤ ምን ማለት ነው?
መምህር ታዬ፡- ወንድማማች ማለት በአንድ ቤት የሚኖሩ የአንድእናት ልጆች እየተሳሰቡ ቤታቸውን የሚያሳድጉ በአንድነት የሚራመዱ ናቸው። ሕወሓት ግን ያለፉትን 27 ዓመታት ትተን ባለፉት ዓመት ያደረገውን ስናስታውስ በራሱ ዘመን የተደራጀው ለ20 ዓመት ይጠብቀው የነበረውን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የመጨረሻ ምሽግ የሚባለውን የመከላከያ ሰራዊት ጥቅምት 24 ቀን ከጀርባው ወጋው። በሲኖትራክ ነው የሄደበት፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሴቶችን ጡታቸውን ቆርጧል።
አብዛኛውን ሰራዊት ክብሩን መለዮውን አስወልቆ ራቁቱን ነው ወደኤርትራ የሸኘው፤ ወንድም እነዚህን ነገሮች ያደርጋል ወይ? ከሚለው እንነሳ። ሁለተኛው ማይካድራን እንመልከት፤ ማይካድራ ከ1600 ያላነሰ ሰው ተጨፍጭፎበታል። ወንድም በወንድሙ ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ ይፈጽማል ወይ? ከዛ አልፎ በመላው አለም ያሉ የሕወሓት አባላት ምንድነው የሚያደርጉት ስንል ኢትዮጵያ ትውደም እያሉ በመላው አለም ላይ የሚንከባለሉ ናቸው። መሪዎቻቸው ደግሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ውስጥም ቢሆን እንገባለን ብለዋል። ወንድም አንድን ሀገር ያፈርሳል ወይ? ከዛ ውጪ የኢትዮጵያን ሰራዊት ያንን ትልቅ የፋሽስቱ የአብይ አህመድ ሰራዊት እያሉ የእነሱን ሰራዊት ግን የትግራይ መከላከያ ሰራዊት እያሉ ነው የሚገልጹት። ወንድም በዚህ መንገድ የእናቱን ጡት ይነክሳል ወይ? ብለን ስናስብ ወንድም አለማሆናቸውን በጣም በርካታ ነገሮችን ማሳየት እንችላለን።
አሁን በቅርብ ጊዜ በያዛቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች ላይ ጋሊኮማን መጥቀስ እንችላለን፤ 240 ሰዎችን ጨፍጭፈዋል። ከነዚህ ከተጨፈጨፉት 240 ሰዎች መካከል 107 እድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች ነው። በመጠለያ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በመሳሪያ ይደበድባሉ። ስለዚህ ጦርነቱ የወንድማማቾች ሳይሆን እጅግ በጣም አረመኔያዊ የሆኑ አሸባሪዎች ጅምላ ጭፍጨፋ አሪስቶክራሲ የምንለው የጥቂቶች አገዛዝ ነው። ማረሚያ ቤቶችን የማሰቃያ ቦታ ያደረገ፣ ተደራጅቶ ሲዘርፍ የኖረና አሁን ደግሞ ጥቃት የሚፈጽም ሽብርተኛን ወንድም ነው ብሎ የሚገልጽ ሰው አይኖርም። እንዲህ አይነትም ወንድም በአለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። ወንድም እኮ እኔ ካንተ ልቅደም ብሎ የሚሰዋ፤ በወንድሙ ላይ ጥቃት ሲደርስ ዘሎ የሚመጣና የሚከላከል እንጂ መልሶ ሀገር የሚያፈርስን ወንድም ብለው የሚገልጹ ሰዎች እራሱ ባንዳ የሚለው ቃል አይገልጻቸውም። ምክንያቱም ባንዳ በተወሰነ ደረጃ ነው ሀገሩን የሚጎዳው፤ አንዳንዴ በዘዴ መልክቶችን የሚያስተላልፍበትም ነበር ለወገን፤ ይሄ ግን በምንም የማይገለጽ ድርጅት ሆኖ እያለ የአረመኔ ድርጅት የአሸባሪ ቡድን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አሸባሪ ተብሎ የተወሰነን አካል ወንድም ነው ብሎ የሚያቀርብ አካል ህሊናው መመርመር አለበት።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያዊነት ስሜት ጠፍቷል፤ ሁሉም በብሄሩ ነው የሚያስበው ተብሎ በሚተችበት ወቅት ሀገር ስትነካ ሆ ብሎ ሁሉም መነሳቱ ከምን የመጣ ነው?
መምህር ታዬ፡- ኢትዮጵያዊ ስሜት ሊያጠፉት የሚችሉት አይደለም። ምክንያቱም በአንድ ጀንበር የተገነባ ስሜት አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት እርስ በእርስ በነበረ ማህበራዊ መስተጋብር የንግድ የፖለቲካ የምጣኔ ሀብት የባህል የጋብቻ የሀይማኖት የመንፈስ ትስስር ያለው ነው። ይሄ ህዝብ ደግሞ በተለያየ ጊዜ ተሰብኮ ከእኛ እንኳን የተለየችው ኤርትራ ኢፍትሀዊ ለሆነ ጦርነት ኢትዮጵያን ጎዳች በተባለበት ጊዜ ሆ ብሎ በአንድነት ነው የተነሳው። ለማፍረስ ብዙ ተሞክሯል፤ ግን ከሰባ ዓመት በኋላ 1983 ግንቦት 20 ከተሰበከ በኋላ የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ስሜት በአንድነት አሳይቷል። ሁለተኛ እግርኳስ ስንጫወት የሩጫ ውድድሮች ሲኖሩ ኢትዮጵያዊ ስሜቱን በምን መልክ እንደሚገልጽ እናውቃለን። ሊጠፋ የሚችል ስሜት አይደለም። የአሁኑ የውክልና ጦርነት ሲጀመር ህዝቡ ሕወሓትን በግልጽ የሚያውቅ በመሆኑ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ለማጥፋት የአለም ሀይል በአንድነት መሰለፉን ሲያይ ተመልከቺ። ምሁራን በእኔ እምነት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአድዋ በኋላ ከአድዋ ጦርነት በኋላ በእዛ ዘመን ምሁራን የሚባሉ የሉንም መደበኛ ትምህርት አልተከፈተም። ግን በወቅቱ የነበሩ ሊህቃን ዘምተው ነበር። አሁን ግን የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የዘመቱበት የፖለቲካ አመራሮች የዘመቱበት ጡረታ የወጡ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ካልሄድን ብለው የታገሉበት ነው።
በክልል ውስጥ ያለውን ሰላም ለማስከበር የተቋቋመ የክልል ልዩ ሀይል ከዛ ተልኮ አልፌ ካልመጣሁ ብሎ አንድ ላይ የመጣበት ነው። ህዝቡ ከምንጊዜውም በላይ ስንቅ እና ትጥቅ እየያዘ ወደግንባር የተመመበት ልክ እንደአድዋው፤ አድዋን ያነሳሁት ያኔም አንድ ላይ ሆነው ነው በቤተመንግስት ነበር ድርቆሹን በሶውን ቆሎውን ያዘጋጁ የነበረው። አሁን ደግሞ በእያንዳንዱ ባሉበት ቦታ በእያንዳንዱ ማእከል በእያንዳንዱ ሰፈር ስንቅ እየተዘጋጀ ነው። ሌላው ቀርቶ ሰራዊቱ ይደክመዋል እያለ ሰውነቱን እያሸ እግሩን እያጠበ አጋርነቱን የገለጸበትን ሁኔታ ግንባር ድረስ በአይኔ አይቻለሁ። በጎላ ላይ ወጥ እያዘጋጁ፤ እንጀራ እየያዘ ሄዶ ከፊትለፊት እየሄደ ህዝብ በአንድ ላይ ለመሞትም፤ አድዋ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳለ ሆኖ 100ሺ ነው የዘመተው። አሁን ግን ወደግንባር ሁሉም የሚገባበት እና የሚደጋገፍበት ነገር ስላለ ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ነገር ነው።
እኔ ቤተሰቤን ብዙ ጊዜ አነሳለሁ፤የኔ ባለቤት ጉራጌ ናት፤የወንድሜ ሚስት ስልጤ ናት፣ የእህቴ ባል ከንባታ ናቸው፣ የእህቴ ልጆች ከሲዳማ ተጋብተዋል፣ እኛ ቤት ውስጥ ገብተሽ ድብልቅልቅ ያለ ኢትዮጵያዊነት ታገኛለሽ። ይሄን ኢትዮጵያዊነት መለየት አይቻልም። የመላው ኢትዮጵያዊ አጠቃላይ እውነታ ነው። ኢትዮጵያዊነት እንዲህ በቀላሉ የሚደበዝዝ ስሜት አይደለም። ምክንያቱም ከቀደምቶቻችን ወርሰን ለሌሎች የምናካፍል በጣም በርካቶች አለን። ለማፍረስ የሚሞክሩ ጥቂቶች ቢኖሩም ግን አብዛኛው በዚህ መልክ ስለሚሄድ እና በተለይ ደግሞ መመስገን ያለባቸው ቀደምቶቻችን ያቆዩት ጥሩ የሆነ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ስላለ እንደዚህ በቀላሉ የሚጠፋ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ሰላማዊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች በመሀል ጉዳት እንዳይደርስባቸው እና የጥቃት ኢላማ እንዳይሆኑ ምን መደረግ አለበት?
መምህር ታዬ፡– ሁልጊዜም ማንኛውም ሰው ላይ እርምጃ መውሰድ ያለበት የህግ አካል ነው። ባጠፋው ጥፋት ላይ ተመስርቶ፤ ባደረገው ግንኙነት ላይ ተመስርቶ እርምጃ ሊወስድ ይገባል። የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ፤ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ኢትዮጵያ ስንል ትግራይን አውጥተን ወይም ለይተን አይደለም። አንዳንድ ቦታ ላይ ግን በስሜታዊነት የትግራይ ተወላጆችን የማግለል በአንዳንድ ቦታ በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሸማቀቁ የሚያደርግ ድርጊት የሚያሳዩ ሰዎች ይኖራሉ። ለነዚህ የማስተላልፈው መልእክት ኢትዮጵያን መገንባት ካለብን የምንገነባት ህዝብ ተፋቅሮ ነው።
የፖለቲካ ድርጅቶች ከህዝብ የተለዩ ናቸው። የትግራይ ህዝብና ሕወሓት አንድ ነው የሚል ትርክት አለ። ግን ይሄ በጣም ስህተት ነው። የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር ለዘመናት የኖረ በስልጣኔዋ በድሎቿ ውስጥ አብሮ ያለ የተቋደሰ ህዝብ ነው። ከዚህ ህዝብ መሀከል የወጡ ክፉዎች አሉ። በተመሳሳይ እኮ ሸኔ አለ፤ ከኦሮሚያ የወጣ ነው። የጉምዝ ታጣቂ አለ፤ እሱ ከጉሙዝ የወጣ ነው። በየቦታው ላይ አሸባሪ ሀይሎች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ አሸባሪ ሀይሎች የህዝብ ወኪል ባለመሆናቸው ልክ በሸኔ ምክንያት ኦሮሞን እንደማናገል ሁሉ በሕወሓት ምክንያት ትግሬዎችን ልናገል የሚገባበት ምንም አይነት አመክንዮ የለም። እንዲያውም የበለጠ የትግራይ ልጆችን ማቅረብ ይገባል። አስተሳሰባቸው የተገነባበት መዋቅር አለ፤ ያው እያንዳንዳችን ይሄ የ27 ዓመቱ የፈጠረው የዘውግ አመለካከት የብሄረሰብ ስሜት አለና እሱን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሚገባ ቀርቦ መወያየት፤ እውነታቸውን መረዳት፤ ከዛ የእራሳችንን እውነት ማስረዳት ይገባል።
አንድ ጓደኛዬ ሕወሓት እና የትግራይ ህዝብ እኮ አንድ ነው አለኝ። እሺ ሕወሓት ኮዳ አንጠልጥሏል በወንዶች አካላት ላይ በሴቶች ማህጸን ውስጥ ብረት ከቷል፣ ጥፍር ነቅሏል፣ የዚህ ተባባሪ ናችሁ ወይ አልኩት። አይ አይደለንም አለ፤ ያ ከሆነ የትግራይ ህዝብና ሕወሓት የተለያየ ነው፤ ካልሆነ ሕወሓት የሰራቸውን ወንጀሎች በሙሉ የትግራይ ህዝብ መቀበል አለበት አልኩት። ሂትለር እና የጀርመን ህዝብ አንድ አይደሉም። ፋሺስት ጣሊያንና የጣሊያን ህዝብ አንድ አይደሉም፤ አዲስ አበባ ውስጥ ፋሺስት ጣሊያን በሶስት ቀን ብቻ 30ሺ ሰው ጨፍጭፏል። ስለዚህ ዛሬ ጣልያናዊ ስናገኝ ምንም አንልም፤ ምክንያቱም መንግስትና ህዝብ የተለያዩ ናቸው፤ ፓርቲ እና ህዝብም በጣም የተለያዩ ናቸው። ቋሚ የሚሆነው ሀገርና ህዝብ ነው፤ ፓርቲዎች መንግስታት ተለዋዋጭ ናቸው። የኢህአዴግ መንግስት ነበር፣ የደርግ መንግስት ነበር፣ የሀይለስላሴ መንግስት ነበር። እነዚህ ያልፋሉ፣ ቋሚ መንግስት እና ህዝብ ስለሆነ በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት እያጠናከርን ብንሄድ ተመራጭ ነው።
አዲስ አመን፡- አሳዳጅ እና ተሳዳጅ የነበሩት የሕወሓት እና የሸኔ የሽብር ቡድኖች ጥምረት መመስረታቸውን እንዴት ታየዋለህ?
መምህር ታዬ፡- እንግዲህ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚባል ነገር አለ። ግን እነዚህ ሁለቱ ወዳጅ ሊሆኑ አይችሉም። ሸኔ ለኦሮሞ ህዝብ ቆምኩ ነው የሚለው፤ ሕወሓት ለትግራይ ህዝብ ቆምኩ ነው የሚለው፤ ግን ሁለቱ ምን ነበሩ ብለን እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ የኦነግን ሰራዊት ሕወሓት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ሰብስቦ አንድ ካምፕ ውስጥ እንዳለ ነው ያወደመው። ስለዚህ በማውደም ነው የጀመረው፤ የቀሩትን ደግሞ አሳዶ በነበሩበት ሁኔታ ነው የጨፈጨፋቸው።
ለኦሮሞ ህዝብ ይታገሉ የነበሩ ለኦሮሞ ነጻነት ትግል ብለው የሚታገሉ አርቲስት ኤቢሳ አዱኛ ከነ ህይወቱ ከመኪና ኋላ ተገሏል። የደምቢዶሎዋ እናት ልጇ አስክሬን ላይ ተቀምጣ እንድታለቅስ ተደርጓል። ባለፉት 27 ዓመታት አምቦ አልቅሳለች፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ሞያሌ 11 ሰዎች በጠራራ ጸሀይ ተገለዋል። እሬቻ ውስጥ 800 የኦሮሞ ተወላጆች በምስጋና ቦታቸው ላይ ተገለዋል። አርማዬ ዋቄ በጥይት ተመቶ እስር ቤት ውስጥ እዛው እስር ቤት ውስጥ ተወርውሮ እንዲቃጠል ሆኗል። ማረሚያ ቤቶች ግማሽ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ እስከሚሆኑ ድረስ በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ተሞልተዋል። ኦሮሞ ጠባብ የሚል አጠቃላይ ታፔላ በስርአቱ ተለጥፎበታል። ገበሬዎች እንዴት ከመሬታቸው ይፈናቀሉ እንደነበር የምናውቀው አጠቃላይ ሂደት ነው። ቄሮ በሚያደርገው ትግል ላይ እንዴት አድርጎ ሕወሓት ይሳለቅ እንደነበር እና የወሰዳቸው እርምጃዎች በደንብ የሚታወቁ ናቸው።
እነዚህ ሁለቱ ድርጅቶች የተቋቋሙበት አላማ አንዱ የኦሮሚያን ሪፐብሊክ አንደኛው የትግራይን ሪፐብሊክ ይበሉ እንጂ፤ ትክክለኛ ውስጣዊ ይዘታቸው ግን አለም አቀፍ ሀይል ነው ያቋቋማቸው። አሸባሪው ሕወሓት በትግራይ ልጆች የተቋቋመ አይደለም፤ አሸባሪው ሸኔም በኦሮሞ ልጆች ይሁንታና ፍላጎት በኦሮሞ ጭንቅላት የመነጨ አይደለም። አሸባሪዎቹን ሕወሓትም ሆነ ሸኔ የፈጠራቸው ምእራቡ አለም ነው።
ገራፊ እና ተገራፊ፤ አሳዳጅ እና ተሳዳጅ፤ ሰዳቢና ተሰዳቢ፤ ገዳይና ተገዳይ፤ የነበሩ እነዚህ ሁለቱ አንድ ላይ እንሆናለን ሲሉ የሚገባኝ ነገር፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልገው ሀይል ያጣመራቸው በሌሎች ሳንባዎች የሚተነፍሱ የራሳቸው የሆነ አላማና መርህ የሌላቸው መሆኑ ነው። ለሁለቱም ህዝብ ጠላት የሆኑ ስለሆኑ የነዚህ አንድነት ከግምት ውስጥ የሚገባ አይደለም። የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነውም ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ቋሚ የሆነ ጠላትነት በሁለቱ መሀከል ስላለ፤ ተደጋጋሚ ማጭበርበር የፈጸሙበት ሁኔታ ስላለ ይሄ ለኦሮሞ ልጆች አሳፋሪ ነው። ነብሱን ይማረው እና አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በኦሮሞ ደም ላይ ተደራድሮ ከሕወሓት ጋር የሚነጋገር ሰው ቢኖር አሳፋሪ መሆኑን በጥሩ ቋንቋ ተናግሮታል።
አዲስ ዘመን፡- ዘመቻ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች በአካል ተገኝቶ የመመልከቱ እድል ነበረህ እና የህብረተሰቡ፣ የመከላከያ፣ የልዩ ሀይሉ፣ እና የፋኖው ስሜት ምን ይመስላል?
መምህር ታዬ፡- በቆቦ ግንባር እና በደባርቅ ግንባር ለመገኘት ችያለሁ። ህዝቡ ከወጣቱ ጀምሮ እስከ አመራሩ አንድ ላይ በመያያዝ በከፍተኛ ስሜት የተነሳበት እና በአቅርቦት በግንባር አብሮ በመገኘት ልጆቹን መርቆ በመላክ፤ በከፍተኛ ቁጥር የአማራ ልዩ ሀይል እና መከላከያን ለመቀላቀል ያደረገው ትግል በጣም የሚደንቅ ነው።
በሌላ በኩል የተነካችው ኢትዮጵያ እንደመሆኗ ከሁሉም ክልል የተውጣጡ ልዩ ሀይሎች እዛ ቦታ ሄደው ነበር። በአጋጣሚ እኔ ስደርስ የሶማሌ ልዩ ሀይል ደርሶ ነበርና የነበራቸው ስሜት የሚገርም ነው። የትጋ ናቸው አሳዩንና እንዋጋ፣ እዛ ጋር ደግሞ አይ እናንተ መታችሁ እዚህ ጋር መሰዋት የለባችሁም፣ በቃ ለእኛ እዚህ ድረስ መምጣታችሁ በቂ ነው የሚል የአማራ ልዩ ሀይሎች ይናገሩ ነበር። የሶማሌ ልዩ ሀይሎች ደግሞ የመጣነው እኮ ኢትዮጵያ ስለተወረረች እናንተ ደግሞ ወንድሞቻችን ናችሁ እና የትኛውንም ነገር እንከፍላለን የሚል ስሜት ነበር። የሲዳማ ልዩ ሀይል ከደብረማርቆስ ጀምሮ የነበረውን አቀባበል ለማየት ችያለሁ እና የልዩ ሀይሉ የመከላከያው የፋኖው የገበሬው ስሜት እና አጠቃላይ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ስንመለከት በጣም የሚገርም ነው።
በጣም የደነቀኝ ገበየሁ የሚባል ሰው ገብቶ ነበር ሁለት ከባድ መሳሪያ የማረከ ሰው ነው። በሽፍትነት ላይ በኩርፊያ ላይ ነው ያለው፤ ነገር ግን ሀገሬ ተወራ ሀገሬ ላይ ክፉ ነገር መጥቶ ኩርፊያዬ ወደዛ ይቅር በሚል በከፍተኛ ስሜት ነው እየተፋለመ ያለው። ስለዚህ ሌላ ቀርቶ በፖለቲካ ኩርፊያ ላይ ያሉ እንደገና የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አብንን መውሰድ እንችላለን። እዛው አካባቢ የሚንቀሳቀሱ በከፍተኛ ቁጥር አመራሮቹ ጭምር ናቸው የገቡት እና በአንድ ስሜት የተነሳሱት እና ይሄ መግለጽ ከምችለው በላይ ነው። ለምሳሌ ሰራዊቱ በአንድ አካባቢ ሲያልፍ ህዝቡ የሚያሳየው ድጋፍ ፉጨት በእልልታ የአማራ ልዩሀይል ፋኖ ሲያልፍ ያሳይ የነበረው ነገር በጣም የሚደንቅ ነው። አብሮ ያለው መነሳሳት የተለየ ስሜት ነበር ያየሁት፤ በተለይ የመከላከያው ዝግጅት እና ከህዝቡ ጋር ያለው ትብብር እጅግ የሚደንቅ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት በተደጋጋሚ ከአማራ ህዝብ የምናወራርደው ሂሳብ አለ ሲሉ ይሰማል። ይህ ምን ማለት ነው?
መምህር ታዬ፡- በነገራችን ላይ ይሄ ሁልጊዜም የተለመደ የመከፋፈያ ስልታአቸው ነው። መጀመሪያ ጌታቸው ረዳ ከአማራ ልሒቃን ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለ፤ ትንሽ ቆየና ደግሞ ልሂቃኑን ለመከፋፈል ከአማራ ተስፋፊ ልሂቃን ጋር አለ። ግን እውነት ከአማራ ህዝብ ጋር ነው ወይ ብለን ብንመለከት ማይካድራ ጥሩ ምሳሌያችን ነው። መተከል ላይ እኮ የሚያስገድለው ሕወሓት ነው፤ ወለጋ ላይ ዛሬ በይፋ ከሸኔ ጋር በፊት እወቁልን ነበር፤ አሁን ተጣምረው አንድ ቤት ውስጥ እንደገቡ ነገሩን እንጂ ከተጋቡ ቆይተዋል። ከዛ ጀርባ እኮ ያለው እሱ ነው፤ ትምክህተኛ ነፍጠኛ እያለ የአማራን ህዝብ ሲያስጨፈጭፍ የነበረው እሱ ነው። ስለዚህ የሚያወራርደው ሂሳብ ከአማራ ጋር አይደለም፤ ከአማራ ጋር እንዳልሆነ ጋሊኮማ አፋር አሳይቶናል። ከዚህ በፊትም አፋር ላይ ያደረገው ሌላ ሰፊ የሆነ ጭፍጨፋ በአርብቶአደሮች ላይ አሳይቶናል።
85 በመቶ የአፋርን ማእድን ሲበላ የነበረ ድርጅት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የጋምቤላ እርሻዎች ስም ዝርዝር አውጥተን ብንመለከት አብዛኛው /98 ከመቶ/ የሕወሓት አባላት ናቸው። ለማስመሰል ሁለት ከመቶ ካላስገቡ በስተቀር፤ መርካቶ ያለውን ጉራጌ እና ስልጤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሀይማኖት ሙስሊሞች የተሻለ ነጋዴዎች ናቸው ግልጽ ያለ የተጠና ነው። በንግድ ደግሞ ጉራጌና ስልጤ ናቸው፤ እነዚህን አባሮ ራሱ በብቸኝነት የተቆጣጠረ እና ኮንሶን ጋሞን ሲጨፈጭፍ የነበረ ነው። ወላይታን ወጋጎዳ በሚል አንድ ላይ ካልተጨፈለቃችሁ ወላይታ ጋሞ ጎፋ ዳውሮ ካልተጨፈለቃችሁ ብሎ የጨፈለቀ ነው። ሲዳማ የክልል ጥያቄ ስለጠየቀ ሎቄ ላይ 38ቱን የጨፈጨፈ ነው።
ስለዚህ የሚያወራርደው ሂሳብ ከመላው ኢትዮጵያ ጋር ነው። ከአማራው ጋር አይደለም ከአማራው ልሂቃን ጋርም አይደለም። ደሞ በጣም አጥብበው ከአማራ ተስፋፊ ልሂቃን ጋር አይደለም። ያንን ብለው ነበር፤ 1983 ዓ.ም ለሰፊው ህዝብ እኩልነትን አንድነትን ፍቅርን የመሳሰሉትን እንመሰርታለን፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች 1948 የወጡትን እንደሚያስፈጽሙ ለአሜሪካም ለምእራቡም አለም ቃል ገብተው ወደዚህ ቦታ ታዝለው የገቡት በሻእቢያ ጭምር ነው። ከገቡ በኋላ ግን ያደረጉትን ስለምናውቅ የሚያወራረዱት በበለጠ ቁጥር ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው። ግጭታቸው ከአማራው ህዝብ ጋርም አይደለም፤ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው።
ደቡቡ የስብዕና መሸርሸር የሚባል ነበር፤ የትኛው ነው ያልተነካው እና ያልቆሰለው። የትኛው ህዝብ ነው ባለፉት 27 ዓመታት ያላለቀሰው፤ ልጆቹ ማረሚያ ቤት ያልገቡት። ጌዲኦ ስንት ነበር ማረሚያ ቤት የገባው፤ ሱማሌው እኮ በኮንትሮባንድ እየተዘረፈ በጀቱ እየተበላ ከዛ አልፎ ከእንስሳ ጋር ይታሰር ነበር። የአሁኑ የክልሉ ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ኡመር ወንድም ከሚሄድ መኪና ላይ ተገፍትሮ ሞቷል። ሙስጠፌ አክቲቪስት ስለሆነ እና የሙስጠፌ ወንድም በመሆኑ ብቻ። አፋር ላይ ወያኔ ዛፍ የሚባል ነበር፤ ስሙ የተሰጠው እሱ የተተከለበት አካባቢ ያሉ ዛፎች በሙሉ ይደርቃሉ፤ በዚህ የተነሳ ወያኔ ዛፍ አሉት። አፋርንም ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በሰፊ ቁጥር አጥፍቶ እዛ ቦታ ለመስፈር የሚያደርጉት ነበር። እና ይሄ ሰዎችን በዘዴ የማጥፋት ነገር ያደርጉ ነበር። የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲያቸው በጣም አደገኛ መርዘኛ መሆኑን በዚህ መመልከት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን ስትፈልግ አደራዳሪ ካልሆንኩ ትላለች፤ በይፋ ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ውዝግብ ውስጥ የነበረችበትን ቦታ በመውረር ድልድይ ሰርተው ከፍተኛ አመራሮቻቸው በተገኙበት አስመርቀዋል። በስነ-ስርአቱ ላይም ይዞታቸውን በሀይል እንዳስመለሱ ተናግረዋል፤ ይሄን እንዴት ታየዋለህ?
መምህር ታዬ፡- ሱዳን ከመነሻው ጀምሮ በውክልና ጦርነት ውስጥ እንዳለች ግልጽ ያሉ ማስረጃዎች አሉ። ከምረቃው ልነሳ የጦር ሀይል ሀላፊውም አብደላ ሀምዶክም ባለበት የተናገሩት የተወሰነ ግዛት ከኢትዮጵያ የነበረንን አስመልሰናል፤ የሚቀረን ሰፊ ቦታ አለ ብለው በያዙት ግዛት ውስጥ ድልድይ አስመርቀዋል። ይሄ አንደኛው ትልቁ የጸብ አጫሪነት ስሜት ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ሱዳን ሰራዊቷን እያስገባች አብራ የተማረኩ ታንኮች አሉ። የተመቱ የተደመሰሱ የተያዙ የተማረኩ የሱዳን ሰዎች አሉ። በጉሙዝ በኩል የሚንቀሳቀሱትን ሰዎች ከግብጽ በተጨማሪ ከፍተኛ ድጋፍ እንደምታደርግ በግልጽ የሚታወቅ ነገር ነው። ሌላው በህዳሴ ግድብ ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳያስከትልባት የያዘችው ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ይታወቃል። ከዚህ ውጪ ደግሞ ሳምሪ የሚባለውን እና ሌሎችን ሱዳን ውስጥ እያሰለጠነች ወደ ኢትዮጵያ አስርጋ እንደምታስገባ ይታወቃል። በቅርብ ጊዜ 16 ሳተላይት ስልኮች 300 የሱዳን ሲምካርዶች ይዘው ነው 1720 ሰዎች አሁን በቅርብ ጊዜ የተያዙት። ስለዚህ ሱዳን ቀጥተኛ ድጋፍ እያደረገች ኢትዮጵያን እየወጋች፤ የምትደግፈውን ቡድን እና ሌላውን ላደራድራችሁ ማለት በምንም ተአምር አይቻልም። ልክ አንድ የራስ አካል አድርገሽ የያዝሽውን ሰው ከሌላ ጋር እንዲጣላ ድጋፍ እየተሰጠ ላደራድራችሁ የሚለው ነገር ፌዝ ነው የሚሆነው። ይሄንን ኢትዮጵያ ባለመቀበሏ ደግሞ ንቃናለች የሚል ብዙ ጊዜ ማደራደር የሚችለው በሽምግልና ሂደት ሶስተኛ አካል መግባት አለበት ይሄ ድርድር ቢሆን እኛ እና ሕወሓት ነበር የምንደራደረው አስታራቂ ለመሆን የሚያስችል ብቃት የላትም።
ትልቅ የሆነ ስህተት እና ተንኮል ከበስተጀርባው የአለምአቀፉን ሀይል ስሜት ለመያዝ እና ጊዜ ለመግዛት በድርድር ውስጥም የሱዳንን ኮሪደር ለማስከፈት ነው ትግል እየተደረገ ያለው። ከምጽዋ መቀሌ በአምስት ሰዓት መድረስ ይቻላል፤ ከሱዳን ወደብ ተነስቶ ግን መቀሌ ለመድረስ የሚፈጀው ጊዜ ቀናት ነው። ስለዚህ ለምን እርዳታው በምጽዋ በኩል አይገባም፤ እንዴት በሱዳን በኩል ይግባ ተባለ ስንል፤ በግልጽ ሱዳን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራች እንዳለች እናያለን። ይሄ የመለሳለስ የዲፕሎማሲ ቋንቋ የሚለው በጦርነት ጊዜ አይሰራም። ሱዳን አምባሳደሬን ልውሰድ ኢትዮጵያ ንቃኛለች የሚሉ ነገሮችን አምጥታለች። መልሰው ደግሞ ከኢትዮጵያ አንድነት ጎን እንቆማለን የሚል የለበጣ መግለጫ አውጥተዋል። እነዚህ የተለመዱ የዲፕሎማሲ ቋንቋዎች ስለሆኑ ናቅ አድርገን ዋናውን ትኩረታችንን ላይ ማድረግ አለብን።
ሱዳን የማደራደር ብቃትም፣ ሞራሉም፣ ልምዱም የላትም። ለራሷ እኮ የፈረሰች ሀገር ነች። በሁለት መንግስት የወታደሩ መንግስት ለብቻ ሲቪሉን እንደፈለገ ቀጥቅጦ ከሌላው አለም በላይ የሚያዝበት፤ ሲቪሉ ደግሞ አቅም አጥቶ በሚሄድበት ሁኔታ በምንም ተአምር ሱዳን መንግስት ነኝ ብሎም እኮ ለማውራት የሚያስችል አይደለም። የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ እኮ ሱዳን ውስጥ አለ፤ እኛ የእሷን ሰላም ለማስከበር ገብተን እናንተን ላደራድራችሁ የሚለው ነገር ፌዝ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቀረ የሚሉት ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት ካለ እድሉን ልስጦት
መምህር ታዬ፡- እኔ ማመስገን ብቻ ነው የምፈልገው ምክንያቱም ዋና ዋና የሚባሉ ነጥቦችን በሚገርም ሁኔታ ለመናገር በሚያስችለኝ መልኩ ጠይቀሽኛል፤ ሀሳቤን በነጻነት እንድገልጽ አድርገሻል። ዋናው ለአንድነት እንቁም፤ ኢትዮጵያ ትቅደም፤ ኢትዮጵያን ለዘላለም ለማጥፋት የሚያስቡ በሙሉ ይውደሙ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ::
መምህር ታዬ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2013