አሸባሪው ሕወሓት ጫካ በገባ ማግስት የትግል አጋሮቼ እና የአለም ህዝብ ይወቅልኝ ባለው ማንፌስቶው በክፍል (ሀ) “የአብዮታዊው ትግል አላማ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ማቋቋም ይሆናል” በማለት እንቅጩን ይናገራል።
ከዚህ ጋር አያይዞ የትግራይ ህዝብ የደኸየውና ያልሰለጠነው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመኖሩ ነው ሲል አሻባሪው ሕወሓት በፅኑ እንደሚያምን በማንፌስቶው በማያወላዳ እና በማያጠራጠር መልኩ ነግሮናል። ይህን አቋሙን በአደባባይ ማስተማሩን ተከትሎም የሽበርተኛው የማንፌስቶ ፍሬ አፍርቶ አሁን ላይ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የትግራይ ተወላጅ ስለ ኢትዮጵያ ያለውን አመለካከት በአደባባይ እየተመለከትን ነው።
አሸባሪው ቡድን የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የማቋቋም ህልሙን እውን ለማድረግ እና ለህልሙ መሳካት እንደ ዘላቂ መፍትሄ በማሰብ መሬት ላይ የተገበረው ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ በማይታረቅ የብሄር ቅራኔ ውስጥ በመክተት እርስ በርሱ ማባላት እና በማጫረስ ሃገርን ማተራመስ ነው።
በዚህም ኪሳራ የ“ታላቋን ትግራይ” ግንባታ ያለማንም ጠያቂ ማከናወን እንደዋነኛ የትግል አቅጣጫ አድርጎ መነሳቱን በግልፅ በማኒፌስቶው ነግሮናል። እንደ ወያኔ እሳቤና እቅድ ከሆነ ማንኛውም መስዋዕትነት ተከፍሎ የኢትዮጵያን ህዝብ እርስ በርሱ ማባላት ያስፈልጋል። ባለቤት አልባ በምትሆነው ኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይም በህልም ዓለም ያለችውን ታላቋን ትግራይ ለመገንባትና ለሃገርነት ዝግጁ ማድረግ ዕቅዱ ሆኖ ኖሯል። ይህ አይነቱ እውነታም ከጫካ ጀምሮ የፈጸማት እያንዳንዷ ኢንች እንቅስቃሴ እጁ በደም እንዲጨማለቅ አድርጎታል።
ይህን ህልሙን እውን ለማድረግ ያፈሰሰውን የእልፍ አላፍ ኢትዮጵያኖችን ደምና የግፍ ድርጊት በወፍ በረር ማየቱ አይከፋም። ይህን የደም የማፍሰስ ሱስ አንድ ብሎ የጀመረው ‹‹ነጻ አወጣዋለሁ›› ሲል የለበጣ በሚምልበት እና በሚገዘትበት የትግራይ ህዝብ ላይ ነው።
ይህ ሲባል ትህነግ የሰው ልጆችን መብላት እና በደም መጨማለቅ የጀመረው “ የኢትዮጵያዊነት ስሜት አላቸው” ብሎ በሚያስባቸው የትግራይ ሰዎች እና በትግራይ የመሳፍንት ዝርያ ባላቸው ግለሰቦች ላይ ነው። ይሄም በትግራይ ህዝብ ላይ የተካሄደው የግፍ ጭፍጨፋ ከ1969 ዓ.ም እስከ 1974 ዓ.ም መቀጠሉን የሕወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በተደጋጋሚ በሚዲያዎች እና በጻፉአቸው መፅሃፍቶች ሲናገሩ መመልከት ችለናል።
ትህነግ ከደም ሱሰኝነቱ በተጨማሪ ፍቅረ ነዋይ ያደረበትም ነበር። ኢትዮጵያዊ ስሜት አላቸው የሚላቸውን ለመግደል በእስር ካንገላታቸው በኋላ ገንዘብ መክፍል የቻሉትን ብቻ ይፈታ እንደነበር እነ ገብረመድህን አርአያን የመሰሉ የትህነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምስክርነት ሰጥተዋል።
ሌላው የሕወሓት የደም እጆች የተጨማለቁት ደግሞ በአማራው ብሄረሰብ ላይ ነው። ይህን እውነት ለማገናዘብም የሕወሓት ማንፌስቶ ስለአማራው ብሄረሰብ የሚለውን ሀቅ ማየቱ ተገቢ ነው። ምንም እንኳ የአሸባሪው ጁንታ ማንፌስቶ በተዘጋጀበት ወቅትና ስልጣን ላይ እስኪወጣ ድረስ በሀገራችን እራሱን በ“አማራ” ስም አደራጅቶ ኢትዮጵያን ያስተዳደረና ለመምራት የሚታገል አንድም የፖለቲካና የሲቪል ድርጅት አለመኖሩ ቢታወቅም፤ ሕወሓት ግን በቅዠት በጻፈው ማንፌስቶው “አማራ” የሚባል ጨቋኝን በመፍጠር ለትግራይ ህዝብ በጠላትነት አስፈረጀው።
አሸባሪው ወያኔ በማኒፌስቶው ‹‹ አማራ ጨቋኝና የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው›› በማለት በግልፅ አስቀምጧል። የትግራይ ህዝቦች ለደረሰባቸው ህብረተሰባዊ ደረጃዎች ሁሉ ተጠያቂው “ጨቋኟ አማራ ናት” ይላል። በተለይም በማኒፌስቶው ከገጽ 14 እስከ 16 “ሕብረተሰባዊ ሁኔታዎች” በሚለው ርዕስ ስር ስለትግራይ ህዝብ “እራስን መጣል (dehumanization)” በሚለው ክፍል “ይህም በደል ጨቋኟ የአማራ ብሄር ሆን ብላ እንደ መንግስት መመሪያዋ አድርጋ ስትሰራበት የቆየች….” በማለት አማራን ጨቋኝና ተጠያቂ ያደርጋል።
“ወደ ኋላ መቅረትና እረፍት ማጣት” በሚለው ክፍል ደግሞ “ሰፊው የትግራይ ህዝብ ስራ አጥቶ በስደት ወዘተ ብቻ ሳይሆን በረሃብ፣ በድንቁርናና፣ በበሽታ እየተሰቃየ ይገኛል። ለችግሩ መሰረታዊ ምክንያት …ጨቋኟ የአማራ ብሔር የምታደርገው የኢኮኖሚ ብዝበዛና ጭቆና ታክሎበት ነው።” በማለት ለትግራይ ህዝብ ሕብረተሰባዊ ውድቀት ዋነኛ ምክንያትና ተጠያቂዋ “አማራ” የምትባል “ጨቋኝ” መሆኗን በመፈረጅ ይደመድማል።
አማራን ለማጥፋት ሕወሓት አንድ ብሎ የጀመረው ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ይህንንም አስቀድሞ ተግባራዊ ያደረገው በወልቃይት ህዝብ ላይ ነው። ወልቃይትን ለትህነግ ያጋለጠው ምንድን ነው? ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል።
ትህነግ በማንፌስቶው የወልቃይት መሬት በታላቋ ትግራይ ማካተት እንዳለበት አስቀምጧል። ይህን ለመተግበር ያደረገው ሙከራም በወልቃይት ህዝብ ትግል ሊቀመስ አልቻለም። ትህነግን በመጣበት እግሩ አቅምሶ ይመልሰዋል። አንድ ቀን ግን የወልቃይትን ህዝብ እና መሬት ለትህነግ አሳልፎ የሚሰጥ አጋጣሚ ተፈጠረ።
በ1960ዎቹ መጨረሻ በወልቃይት አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎች ኢህአፓና እና ኢዲዩ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ኢህአፓም ሆነ ኢዲዩ በተደጋጋሚ ከደርግ፣ ከሕወሓትና፣ አንዳንዴም እርስ በእርሳቸው አውዳሚ ጦርነቶችን በጎንደር አካባቢ አካሂደዋል።
ከነዚህ ጦርነቶች አንዱ በ1969 ዓ.ም በደርጉ ገስጥ ጦርና በኢዲዩ መካከል የተደረገው ውጊያ ይጠቀሳል። በዚህ ወቅት ከኢዲዩ ጋር ተሰልፈው የተዋጉ የወልቃይት ህዝብ ዋነኛ መሪዎችና ጀግኖች የተሰው ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ ህዝብ በቁጣና በዕልህ ለተደጋጋሚ ጦርነቶች ተዳርጓል። ቀሪው ህዝብም ወደ ሱዳን እንዲሰደድ ሆኗል። ይህ የወልቃይትን ህዝብ መሪዎችና ጀግኖች የበላው ጦርነት የወልቃይትን ሃይልና ከጠላት ጋር የመዋጋት አቅም በእጅጉ ያዳከመና ያደቀቀ ነበር። ይህም ወልቃይትን ለመያዝ በማኒፌስቶው ላረቀቀው ትህነግ ሰርግ እና ምላሽ አደረገለት።
በወልቃይት ህዝብ ላይም በሰው ልጅ ሊሰራ የማይችል ድርጊት ተፈጸመ። ከአይረሴ ግፎች መካከልም፡- በባዶ ስድስት የሰውን ልጅ ከእነ ህይወቱ እግሩን ከአንድ እንጨት፣ እጁን ከአንድ እንጨት በአየር ላይ በመወጠር፤ ከታች እሳት በማንደድ በርካቶች እንደ ጥይት እየፈነዱ መሞታቸውን በትህነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የነበሩ ለተለያዩ ሚዲያዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ሌላው የትህነግ ኢትዮጵያን አፍርሰን በፍርስራሿ ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ብሄር ብሄረሰቦችን ማባላት አለብን ብሎ በማንፌስቶው ባስቀመጠው መሰረት በኢትዮጵያ ብዙ ቁጥር ያላቸውን የአማራ እና የኦሮሞ ብሄሮችን ለማጋጨት ሲያሴር ቆይቷል። ለዚህ ማሳያ በክንፈ ገበረ-መድህን ጭንቅላት የተከተበውን በተስፋየ ገብረ እባብ (ገብረአብ) እጅ የተጻፈው ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› በሚል ርዕስ የተጻፈው መፅሃፍ አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ነው።
በዚህ መፅሃፍ የተከተበው ፅሁፍ ሁለቱን ብሄሮች እስከ መጨረሻው ሊያቆራርጥ የሚችል እኩይ ተግባር ነበር። ነገር ግን ሁለቱም ህዝቦች ኢትዮጰያዊነትን አጥብቀው በመውደዳቸው ምክንያት የትህነግ ህልም ሳይሳካ ቀርቷል።
የቡርቃ ዝምታ በሚባለው መፅሃፍ ከተጻፉ ጉዳዮች እና ለማመንም ከሚቸግሩ እውነቶች አንዱን መመልከቱ አይከፋም።
ፅሁፉ ባጭሩ እንዲህ ይላል “በአርሲ የነበረው የቡርቃ ወንዝ ምኒሊክ ወደ አርሲ ዘምቶ ኦሮሞን እስከሚገድል ድረስ ወንዙ ከመሬት በላይ ይፈስ ነበር። የምኒሊክ ጦር ኦሮሞን ካጠቃ በኋላ ግን ወንዙ አኩርፎ እና አዝኖ በመሬት ውስጥ ለውስጥ መፍሰስ ጀመረ። ይህ ወንዝ እንደ መጀመሪያው ወይም እንደ ቀድሞው ከመሬት በላይ የሚፈሰው ‹‹ዋቆ ጉቱ›› የሚባሉ በአካባቢው ያሉ አንድ ትልቅ ሰው ሊሞቱ ሲሉ እንደሆነ ትንቢት አለ። ትንቢቱ ደርሶ ዋቆ ጉቱ ሲሞቱ ኦሮሞ አማራን ይበቀላል። ቡርቃም እንደመጀመሪያው ከመሬት በላይ ይፈሳል።”
ልክ ወያኔ አዲስ አበባን በተቆጣጣረ ማግስት ወያኔ እና ጀሌዎቹ ‹‹በአርሲ አካባቢ ዋቆ ጉቱ ሊሞቱ ነው፤ ኦሮሞም አማራን የሚበቀልበት ቀን ደርሷል፤ ቡርቃም ከመሬት በላይ መፍሰስ ይጀምራል›› ብለው ማስወራት ያዙ። ወያኔም በአካባቢው ሰርጎ በመግባት እና አንዳንድ የአካባቢውን ሰዎች በማታለል በአማራ ብሄረሰብ ነዋሪዎች ላይ ጭፍጨፋ አካሄደ። ቡርቃ ግን ወያኔ እንዳስወራው ሆኖ ከመሬት በላይ ሊፈስ አልቻለም። በወቅቱ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው ቢጎዳም ሁለቱን ብሄረሰቦች እስከመጨረሻው አጋጭቶ ኢትዮጵን የማፍረስ የወያኔ ህልም ግን ምኞት ብቻ ሆኖ ቀረ።
ሌላው በትህነግ የደም እጆች የተጎዳው የኦሮሞ ህዘብ ነው ። እንደሚታወቀው ደርግን ታግለው ከጣሉት ነፍጥ አንስተው ሲዋጉ ከነበሩ ድርጅቶች መከካል አንዱ ኦነግ ነው። ይህን ተከትሎ ወያኔ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ማግስት የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረውን ኦነግ ለሽግግር መንግስት ምስረታ ጋበዘ። በኋላ ግን በኦነግ ላይ አሳፋሪ ክህደት ፈጸም። ከከህደቱ ጋር ተያይዞ አንቅልፍ የነሳው ትህነግ ኦሮሞ የሆነ ሁሉ ኦነግ አንደሆነ በማሰብ ኦሮሞ የሆነን ህዝብ በሙሉ ሲገድል፣ ሲያስር፣ ሲያሳድድ እና ሲያሰቃይ የኖረ የእርኩስ መንፈስ የሰፈረበት ደርጅት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሳይቀሩ ‹‹ሁሉም ኦሮሞ ቢገለበጥ ጀርባው ኦነግ ነው ብለው›› ተሳለቁ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጀምሮ አያሌ የኦሮሞ ተወላጆችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል። አካል ጉዳተኛ አድርጓል።
በወያኔ ግፍ የደረሰባቸውን የኦሮሞ ተወላጆች ለመቁጠር ሊያደክም ይችላል። ከግፍ አገዳደሎች በጉልህ የሚታወቁ አንድ ሁለት ሰዎችን እና የተፈጸመባቸውን ግፍ ግን ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል።
በወጣት ከፍያለው ተፈራ እና በአርቲስት ኢብሳ አዱኛ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ብቻ መመልከቱ የወያኔን አውሬነት ያሳያል። ኢብሳ አዱኛ በኢትዮጵያ በኦሮምኛ ቋንቋ ዘፈኑ ያላዝናናው አልነበረም ማለት ይቻላል። ኢብሳ እጅግ ተወዳጅ ድምጻዊ ነበር። ነገር ግን ወያኔ ገና ስልጣን በያዘ ማግስት በዘፈኑ ለአድናቂዎቹ ሃሴት የሚፈጥረው ኢብሳ አዱኛ ምንም በማያውቀው ነገር በመኪና ተጎትቶ ገደለ።
የአምቦ አካባቢ ተወላጅ የሆነው ከፍያለው ተፈራም ምንም በማያውቀው ነገር ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ ሁለት እግሩን ይቆርጡታል። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ እግሩን ከቆረጡት በኋላ የሰጡት ምላሽ ነው። ‹‹ይቅርታ ነጻ ነበርክ፣ ተሳሳትን አሉት። ምን አይነት አረመኔነት እንደሆነ ልብ ይሏል።
ወያኔ በኦሮሞ ላይ ራሱ ከሚፈጽመው ሰቅጣጭ እና ዘግናኝ ተግባሩ ባለፈ ኦሮሞን ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በማባላት የኦሮሞን ደም ለማፍሰስ የሚፈጽመው ተግባር ነው። ጉዲፈቻን ለሃገራችን በማስተማር ሰውን በሰውነቱ መውደድ እንደሚገባ በብሄሰረቦች የተጠላ እንዲሆን በማድረግ ከተለያዩ ብሄረሰቦች ጋር ደም አቃብቶታል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ወያኔ ኦሮሞን ከሶማሊያ፣ ከቡርጅ (ደቡብ ክልል) ከጉጂ ኦሮሞ፣ ወዘተ በማጋጨት የኢትዮጵያ ልጆችን ደም አፍስሷል። ነገር ግን ኢትዮጵያኖችን እርስ በርስ በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የቋመጠው ትህነግ ሙከራው ከህልምነት ሊያልፍ አልቻለም።
በ2008 ዓ.ም እና 2011 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ በተለይም ደግሞ በኦሮሞ፣ በአማራ፣ በሶማሊያ፣ በአፋር፣ በደቡብ በነበረው አመፅ ሕወሓት ከ5000 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን መግደሉን በወቅቱ ይፋ ያደረገው የሒውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ይጠቁማል። ከተገደሉት መካከልም የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥራቸው እንደሚበዛም በድርጅቱ ተገልፆ እንደነበር አይዘነጋም።
ይህንን እውነታ የተመለከተ ማንም ኦሮሞን እወክላለሁ የሚል ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ከትህነግ ጋር ቆሞ ለመስራት መፈራረም አይደለም ማሰብ ጭምር ጤነኛ አያስብልም።
ከሰሞኑ ኦነግ ሸኔ ለ27 ዓመታት ወያኔን በመደምሰስ ለኦሮሞ ነጻነት እታገላለሁ ብሎ ሲምል ሲገዘት እንዳልነበር እንዴት አሁን ላይ የኦሮም ህዝብ በገፍ ሲጨፈጭፍ ከነበረው ከሕወሓት ጋር ለመስራት አሰበ ? እዚህ ላይ ሁሉም ሰው ሊገነዘበው የሚገባው ከትህነግ በላይ ለኦሮሞ ህዝብ ጠላቱ ኦነግ ሸኔ እንደሆነ ነው።
ለዚህ እውነትም ሌላ ማሳያ ማቅረብ ያስፈልጋል። ኦነግ ሸኔ ስንት አመት ጫካ ገብቶ ለኦሮሞ ህዝብ እየታገልኩ ነው ብሎ በማስመሰል አንድም ስራ ሳይሰራ በቆመበት የደረቀ ድርጅት ነው። በነዚህ ታገልኩበት በሚላቸው ዓመታት ሸኔ ለወያኔ ቅጥረኛ በመሆን በርካታ ቁጥር ያላቸውን የኦሮሞ ልጆች አስበልቷል። ይህንን በግብዝነት እንዳላልኩት ለማሳየትም በቂ ምክንያት ማቅረብ ያስፈልጋል።
የኦሮሞ ህዝብ ከ2008 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ባደረጋቸው ትግሎች በአጭር ጊዜ ትህነግን መሬት መቅበር የቻለ ጀግና ህዝብ ነው። በዚህም የኦሮሞ ልጅ ሲታገል ጀግንነቱ ምን ይመስላል የሚለውን በግልፅ ያሳየ ነው። በዚህም ኦነግ ሸኔ ስንት ዓመት በጫካ በነበረበት ጊዜ ለወያኔ ተላላኪ በመሆን ዕልፍ የትግል ፅናት እና አላማ የነበራቸውን የኦሮሞ ልጆችን ለወያኔ አሳልፎ እየሰጠ፤ የኦሮሞን የመታገል መንፈስ መቀመቅ ውስጥ በመጨመር የኦሮሞን የትግል መንፈስ ያላሸቀ ድርጅት ስለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ነው።
የደም ሱስ ዛር የሰፈረበት ትህነግ ኢትዮጰያን ለማፍረስ ሁሉንም ብሄረሰቦች ማባላቱ አልበቃ ብሎት በመከላከያ ሰራዊት ላይ በአለም ታሪክ ተፈፅሞ የማያውቅ ግፍ ፈጸመ። ይህን ተከትሎ የደም የማፍሰስ ጥሙ ያልወጣለት ትህነግ፣ በማይካድራ እና በአፋር ህዘቦች ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋን አከለበት።
ህይወት የመቅጠፍ ሱስ የተጠናወተው ትህነግ በመጨረሻም ከስልጣን ተባሮ የልምዱን የሚያስታግስበት ደም ቢያጣ ከህግ ማስከበሩ በኋላ መከላከያ የተናጠል ተኩስ አዋጅ አድርጎ ከትግራይ ክልል ሲወጣ ሀሰት ትርክት ቀጠለ።
ለትግራይ ህዝብ ጦርነቱን እንዳሸነፈ አድርጎ በመሳል እና አዲስ አበባ ሊመለስ መሆኑን በመዋሸት፣ ለትግራይ ህዝብ ህጻን፣ ሴት፣ አዛውንት፣ ባልቴት፣ ነፍሰጡር ሳይቀር አሰለፈ። አሁንም ድረስ ይህ ግፈኛ ቡድን የትግራይ ሰዎችን የእሳት እራት እያደረገ ይገኛል። በዚህም ድርጊቱ አገርን ለማፍረስ ካደረገው ሙከራ በተጨማሪ በትግራይ ምድር አንድም ሰው እንዳይቀር አቅዶ በ‹‹ህዝብ ማዕበል››ስያሜ በርካታ ንጹሀንን እያስፈጀ፤ እያስጨረሰ ይገኛል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2013