* የዴሞክራሲ ተቋማት የዜጎችን መብት ለማስከበር ደካማ መሆናቸው ተጠቆመ
አዲስ አበባ፡-የማንነትና የዜግነት ፖለቲካ ፅንፍ ከወጣ አገር ሊያፈርስና ወደ እርስ በእርስ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል አንድ ምሁር ገለጹ፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት የዜጎችን መብት ለማስከበር ደካማ መሆናቸው ተጠቆመ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ‹‹የዜጎችን መብት ለማስከበር ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት›› በሚል ርእስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር አሰፋ ፍስሃ በአቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ እንደገለጹት፣ የማንነት ፖለቲካ ፅንፍ ከወጣ የዜግነት መብቶችን አያከብረም፡፡ የሰዎችን ተዘዋውሮ የመስራት መብት ይገድባል፡፡መፈናቀልን ያስከትላል፡፡ በአንጻሩ የዜግነት ፖለቲካ በርካታ ማንነቶች ባሉበት አገር ጸንፋ ሲወጣ ማንነቶችን ይደፈጥጣል፣የባህል ዕድገቶችን ይገታል፡፡ ስለሆነም ሁለቱም ጽንፍ ከወጡ የአገርን ሰላም በማናጋት ወደ እርስ በእርስ ግጭት በማምራት አገርን ሊያፈርሱ ይችላሉ ፡፡
የማንነት ፖለቲካ ጫፍ በመውጣቱ በአሁኑ ጊዜ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀላቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አሰፋ፣ በክልሎች የሚኖሩ ውህዳን ህዝቦች በአገራቸው የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ባይታወር እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡በአንጻሩ የዜግነት ፖለቲካ በምትኩ ጽንፍ ከወጣ ብዙ ማንነቶች ያሉባት አገር በመሆኗ ማንነቶች የመጨፍለቅና ባህላቸውን የማቀጨጭ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
ጽንፍ የወጡ የማንነትና የዜግነት ፖለቲካ አገርን ሊያፈርሱ ስለሚችሉ፣ አገራዊ ማንነት የብሄር ማንነቶችን በማይደፈጥጥና ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ በመንግሥት ፖሊሲዎች ተቀርጾ የሚፈጸምበት የክትትል ስርዓት ሊዘረጋለት ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ የጋራ ውይይት በማድረግ ሁለቱን የፖለቲካ ስርዓቶች ባጣጣመ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ በመስማማት መፍትሄ ሊያበጁለት እንደሚገባ በመፍትሄነት አስቀምጠዋል፡፡
የኢፌዴሪ ፌዴሪሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው፣ በአገሪቱ የዜጎች መፈናቀልና የህይወት መጥፋት፣የመንግስትና የህዝብ ንብረት መውድም ችግሮች ይታያሉ፡፡እነዚህን ችግሮች ፈጥነን ማስቆም አልተቻለም፡፡የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በህገ መንግሥቱ ቢቀመጡም አልተተገበሩም፡፡ ምክንያቱ የዴሞክራሲ ተቋማት የዜጎችን መብት ለማስከበር ደካማ በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ ከተፈለገ የዴሞክራሲ ተቋማት ራሳቸውን ችለው በነጻነት መንቀሳቀስ አለባቸው ያሉት አፈ ጉባኤዋ፡ በዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገን ከሰራን ችግሮቻችን ይፈታሉ ብለዋል፡፡
የዴሞክራሲ ተቋማት ዋና ዓላማ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት ማስከበር መሆኑን ያስታወሱት ወይዘሮ ኬሪያ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ውስጣዊና ውጫዊ ችግራቸውን ፈትተው በአሰራር፣በአደረጃጀት በዕውቀት፣የዜጎችን መብት ማስከበር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከኦሮሚያ ክልሎች የመጡት አቶ ፍቃዱ ታደሰና አቶ ዋቅወያ ቶሌራ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻ፣ገለልተኛና ጠንካራ ማድረግ የዜጎችን ሁለንተናዊ መብት ለማስከበር ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አስምረውበታል፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅነት ‹‹የዜጎችን መብት ለማስከበር ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት›› በሚል በአምባሳደር ሆቴል በተዘጋጀው የምክክር መድረክ የክልልና የፌዴራል የዴሞክራሲ ተቋማት፣የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣የምርጫ ቦርድ፣እንባ ጠባቂ፣ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ሲቪክ ማህበራት ተሳትፈውበታል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2011
በጌትነት ምህረቴ