
የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ወዲህ በብርቱ ከተደቆሱና እንደውም ከናካቴው አሉ እንዴ? የሚያስብል ደረጃ ላይ ከደረሱ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ቱሪዝም ነው፡፡ ወረርሽኙ ገና እንደተከሰተ በርከት ያሉ ሀገራት የእንቅስቃሴ ገደቦችን በመጣላቸውና ድንበሮቻቸውን በመዝጋታቸው ዘርፉ አስቀድሞ ተዳክሟል፡፡ ወረርሽኙ እየተባባሰ ሲመጣ ደግሞ አብዛኞቹ የዓለማችን ሀገራት ተጨማሪ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቦችንና የጉዞ እቀባዎችን በማድረጋቸው የቱሪዝም ዘርፉ ይበልጥ ተሸመድምዷል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቂትና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው የደቡብ ምሥራቅ እስያዊቷ ሀገር ታይላንድም ይኸው ዕጣ ፈንታ ደርሷታል፡፡ በታይላንድ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልፍ ሚና ያለውን የቱሪዝም ዘርፍ በብርቱ ፈትኗል፤ አዳክሟልም፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የታይላድ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ህልውናውን ለማስጠበቅ ሲታገል መቆየቱንና ብዛት ያለው ጎብኚ ከመቀበል ወደ ውስንና ዳጎስ ያለ አቅም ያላቸው ጎብኚዎችን ለመሳብ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑም ቢዝነስ ስታንዳርድ ከሰሞኑ በድረገፁ አስፍሯል፡፡
በዚሁ ዘገባ ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2019 አርባ ሚሊዮን የሚጠጉ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ተቀብላ ያስተናገደች ቢሆንም እ.ኤ.አ በ2020 አሃዙ ወደ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ማሽቆልቆሉን ቢዝነስ ስታንዳርድ የጠቀሰው የቻይና ዜና ኤጀንሲ ሺንዋን ሪፖርት አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2021 የታይላንድ ቱሪዝም ባለስልጣን ምቹ የቱሪዝም ወቅትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከአንድ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ሀገሪቱ እንደሚገቡ ተንብዮ እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡
ይሁንና አንዳንዶች ይህ አሃዝ አሁን በሀገሪቱ ካለው የክትባት ስርጭት መጠን አናሳ መሆንና በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣት ጋር ተያይዞ ክፉኛ በተስፋ ላይ የተንጠለጠለ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ ጎብኚዎችን ወደሀገር ውስጥ መሳብ የታይላድ የሁልጊዜ ምኞት መሆኑ የሚነገር ሲሆን፤ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት የቱሪዝም ዘርፉን ወደ ቀድሞው ሁኔታው ለመመለስ ወረርሽኙን እንደ ማነቃቂያ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ይህም የዘርፉን ህልውና ለማስቀጠልና በቀውስ ውስጥ ነጥሮ እንዲወጣ ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ባለስልጣናቱ ይናገራሉ፡፡
የቱሪዝም ዘርፉን ወደነበረበት ለመመለስ የመንግሥት ዋነኛ ስትራቴጂ በተለይ በኮቪድ 19 ወቅትም ሆነ ከዚያም በኋላ ግላዊነትንና ማህበራዊ ርቀትን የሚሹና ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያወጡ ጎብኚዎች ላይ የሚያተኩር ስለመሆኑ የታይላንድ ቱሪዝም ሚኒስትር ፊፋት ራቻኪትፕራካም ገልጸዋል፡፡ ዘርፉ እንደዚህ ቀደሙ ብዛት ያላቸውንና ሁሉንም የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ከመቀበል ይልቅ ከፍተኛ ወጪ የሚያወጡትን ጎብኚዎች ለመሳብ ጥረት ይደረጋል ብሏል፡፡
ጥራቱን የጠበቀ የጎብኚዎች ጉዞ ከወረርሽኙ በፊት በባህር ዳርቻዎችና ቤተመቅደሶች አካባቢ የሚታዩ የጎብኚዎች መጨናነቆችንና ሌሎች የአካባቢያዊ ተፅእኖ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችልም ሚኒስትሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ታይላንድ አጠቃላይ የቱሪዝም ዘዴዋን ዳግም ማስተካከል አለባት›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
ሌሎች የዘርፉ ባለሞያዎችና ተዋንያኖችም በታይላንድ በጥቅሉ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከማተኮር ይልቅ በሜዲካልና ዌልነስ፣ በስፖርትና ምግብ ብሎም በቅንጦት ጉዞዎችና መሰል የቱሪዝም ንዑስ ዘርፎች ላይ እንዲተኮር እያስተዋወቁ እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡
ሐምሌ አንድ ቀን 2021 የታይላንዷ ፉኬት ሪዞርት ደሴት ‹‹ሳንድ ቦክስ›› የተሰኘና ጎብኚዎች የሁለት ሳምንት ኳራንቲን ሳያስፈልጋቸው ከዝቅተኛና መካከለኛ የቫይረሱ ተጋላጭ ሀገራት ወደ ታይላንድ ለመግባት የሚያስችላቸውን መርሐ ግብር ይፋ ማድረጓ ለአብነት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ወር ቀደም ብሎም ሲጠበቅ የነበረው የሰባት ሲደመር ሰባት የፉኬት ሳንድ ቦክስ ማስፋፊያ እቅድ በኮቪድ 19 ሁኔታዎች አስተዳደር ማዕከል እንደፀደቀም ተገልጿል፡፡
ጎብኚዎች እንደ ኮ ሳሙኢ ፣ ኮ ፊ እና ክራቢ ወደተሰኙ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲጓዙ ፈቃድ ከማግኘታቸው በፊት መርሐግብሩ በፉኬት ሪዞርት ደሴት ውስጥ የሚኖራቸውን የቆይታ ጊዜ ከአስራ አራት ቀን ወደ ሰባት ቀናት እንደቀነሰውም ተጠቁሟል፡፡
የፉ ኬት ሳንድ ቦክስና ሌሎች በሙከራ ላይ ያሉ መርሐግብሮች የረጅም ጊዜ ፕሮጀክቶች ሆነው የተቀረፁና በታይላንድ ቱሪዝም የሚሟሟቅበትን ከህዳር አእከ መጋቢት ያሉትን ወራቶች የሚያጠቃልል እንደሆነም ታውቋል፡፡ በታይላንድ የቱሪዝም መልሶ የመክፈቻ ፕሮጀክቶች ስኬት በዓለም ዙሪያ በሌሎች የቱሪዝም ዘርፍ ያሉ አካባቢዎችም ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል፡፡
ይሁንና የታይላንድ ቱሪዝም ማገገም ፍጥነትን ሊወሰኑ የሚችሉት ሁለት ቁልፍ ምክንያቶች መሆናቸውንና እንዚህም የሀገሪቱ የክትባት ስርጭት ውጤታማንትና የቫይረሱን ስርጭት የመግታት ችሎታ በተለይ ደግሞ በይበልጥ የሚተላለፈውን የዴልታ ልውጥ ቫይረስ ስርጭትን ማቆም መሆናቸውን ተንታኞች አስቀምጠዋል፡፡
እነዚህ ዋነኛ ምክንያቶች ታይላንድ በጥቅምት ወር አጋማሽ በተሟላ ሁኔታ ዳግም ለተከተቡ ጎብኚዎች በሯን ለመከፍት ለያዘቸው ዕቅድና የቱሪዝም ዘርፉን ህልውና ለማስቀጠል ወሳኝ ስለመሆናቸውም በዘገባው ማጠቃለያ ተገልጿል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2013