የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ተጽእኖዎች በቅርሶች ጥበቃ ላይ አደጋ ማሳደሩ አይቀሬ ነው። ጦርነቶች እና አለመግባባቶች በሚፈጠሩባቸው ወቅቶች የቅርሶች ደህንነት በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅትም ሆነ አሁን ላይ በሚፈጥራቸው ግጭቶች ምክንያት በርካታ የውጭ ጎብኚዎችን መሳብ የሚችሉ ሃይማኖታዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ለጉዳት ተጋልጠዋል። ቅርሶች ላይ አደጋ ሲያንዣብብ ለታሪኩና ማንነቱ የሚቆረቆረው ዜጋ ድምጹን ከማሰማት ባለፈ ሀገሩን ለመከላከልም በቦታው ተገኝቶ የግሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ቅርስና ታሪክን መሰረት አድርገው የተደራጁ ተቋማት በያሉበት ሆነው ድምጻቸውን ሲያሰሙ ይደመጣል። በዚህ ረገድ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት ቅርሶች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ካወገዙ ማህበራት አንዱ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበር አንዱ ነው። እኛም አሸባሪው ህወሓት በታሪክና ማንነት ላይ ያደረሳቸው በደሎች፣ ትውልዱ ላይ የደረሰው በደል፣ ሃይማኖታዊ ተቋማትን ለጦርነት ዓላማ የማዋል ተልዕኮ፣ የውጭ ሀገራት ዝምታ እና የቅርሶች ስርቆት አደጋን በተመለከተ አንስተን ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መቆያ ማሞ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበር የተቋቋመበት ዋና ዓላማ ምንንን መሰረት ያደረገ ነው፤ ምን አይነት ስራዎችንስ እያከናወናችሁ ነው?
አቶ መቆያ፡- የቅርስ ባለአደራ ማህበር በ1984 ዓ.ም ነው የተቋቋመው። የመጀመሪያ ዓላማውም ተፈጥሯዊ ባህላዊ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን እንዳይጎዱ መጠበቅ ነው። በዚህ አግባብ ላለፉት ጊዜያት አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ላይ ጽህፈት ቤቶችን አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል።
በድሬዳዋ 35 የቅርስ ቤቶች እንዲመዘገቡ አድርገናል፤ የልጅ ኢያሱን ቤት ጨምሮ ሌሎች እድሜ ጠገብ ቅርሶችን በማስመዝገብ እና ጥበቃ በማድረግ እየሰራን ይገኛል። ማህበሩ የቅርስ ባለሙያዎችን በመቅጠርም ከቱሪዝምና ቅርስ ቢሮዎች ጋር በቅንጅት ቱሪዝም የሚያድግበት መንገድ ላይ ይሰራል።
ማህበሩ 72 የቅርስ ቤቶች እንዲመዘገቡ እና አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው አድርጓል። በሀገር ውስጥ ጉዳይ የደረሰባቸውን ቅርሶች በመለየትና አስፈላጊው እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ጥናት ያስጠናል። መረጃቸው በምስልና ድምጽ እንዲደራጅም እናደርጋለን። ከዚህ በተጨማሪ የቅርስ ቤቶች ወደግለሰቦች ሲተላለፉ አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው ሙያዊ ድጋፍ እናደርጋለን።
የቅርስ ባለአደራ ማህበር ከሀገር ውስጥ ስራዎች በተጨማሪ እንግሊዝ ሀገር ጭምር ባለው ቅርንጫፍ ቢሮ አማካኝነት በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ የተለያዩ ጥረቶች ያደርጋል። ሀገር ወዳድ ዜጎችን በማስተባበር በተለያዩ ዓለማት በግለሰብ እና በየሙዚየሙ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዲመለሱ እየሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ሀገር በቀል ዛፎች እንዲጠበቁ እና እንዲለሙ ፕሮጀክት ነድፋችሁ የምታከናውኑት ስራ አለ፤ በዘርፉስ ምን ያክል ሰርታችኋል?
አቶ መቆያ፡- ቅርስ ስንል ህይወት ያለውንም ሆነ የሌለውን ይጨምራል። በዚህ አግባብ ለሀገር በቀል ጥንታዊ ተክሎች የምናደርገው ጥበቃ አለ። በተለይ በእንጦጦ ተራራ የሚገኙ ሀገር በቀል ችግኞች ላይ ባለሙያ ቀጥረን ጭምር ጥበቃ እናደርጋለን።
በሀገር ውስጥ ብቻ የሚገኙ የእጽዋት ዝርያዎች እንዳይጠፉ እንሰራለን፤ እንደ ኮሶ፣ ዋንዛ፣ ወይራ፣ ብሳና እና ሌሎች ከ12 በላይ ሀገር በቀል ዝርያዎች ላይ የጥናትና ጥበቃ ስራዎች እናካሂዳለን። በእንጦጦ አንድ ሺህ ሶስት መቶ ሄክታር በሚሆን ቦታ ላይ የሀገር በቀል ዛፎችን እናለማለን።
ከዚህ ውስጥ 600 ሄክታሩ ላይ የነበረውን ባህር ዛፍ በማስወገድ በሀገር በቀል ችግኞች የመተካት ስራ ሰርተናል። የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በተለይም ተክሎችን በመንከባከብ ረገድ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ላይ እየሰራን ነው።
እስካሁን በተሰራው ስራ 25 ሺህ ሀገር በቀል ችግኞች ተተክለዋል። ከዚህ ባለፈ ትውልዱ የሀገር ታሪክ እና ቅርስ ጥበቃ ላይ ያለውን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎች ላይ በሰፊው እየተንቀሳቀስን ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ባለው ጊዜ ለቅርሶች የሚደረግ ጥበቃ እና እንብክብካቤ ምን መልክ ነበረው?
አቶ መቆያ፡- በ27 ዓመቱ የህወሓት ስልጣን ዘመን ቅርሶችን የማፍረስ ትልቅ ችግር ነበር። በርካታ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ የቅርስ ቤቶች በልማት ሰበብ እንዲፈርሱ ተደርጓል። በወቅቱ ይህንን አቤት የምትልበት አሰራር እና የምትጋፈጥበት ሁኔታ አልነበረም።
ለምን ይፈርሳሉ? ብትል እንኳን የልማት አደናቃፊ የሚል ቃል ነው የሚሰጥህ። በማን አለብኝነት ቅርሶች እንዲፈርሱ ይደረጋል። ሌላ ተለዋጭ መሬት እያለ እንኳን እድሜ ጠገብ የቅርስ ቤቶችን ለማውደም ፍላጎት ያላቸው ባለስልጣናት በርካታ ነበሩ። ህዝብ እንኳን አቤት እንዳይል በበዓል ቀናት እና በእረፍት ቀናት ጭምር ቅርሶች እንዲወድሙ ተደርጓል። ከዚህ አንጻር የ27 ዓመቱ የህወሓት ዘመን ቅርሶች የወደሙበት ነው ማለት ይቻላል።
በተለይ በኪራይ ቤቶች ስር የነበሩ ቅርሶች ያለማንም ይሁንታ እና ፈቃድ በወቅቱ ለነበሩ ባለስልጣናት ጥቅም እንዲፈርሱ ተደርጓል። ሲጠየቅ እንኳን ምንአገባህ? አንተ ማን ነህ? የሚሉ ማስፈራሪያዎች ነበር የሚደርሱት። ቅርሶች በፎቶ ማስቀመጥ እንችላለን የሚል መጥፎ ልምድ አሳይተዋል።
ካለው ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ጋር ተያይዞ ቅርሶች አሁንም አሳሳቢ የጉዳት ደረጃ ላይ ቢገኙም ይሁንና ካለፈው ሥርዓት ጋር ሲነጻጸር ግን የተሻለ ግንዛቤ አለ። አሁን ላይ ቅርሶች ጉዳት ቢደርስባቸው እንኳን ለምን ብሎ የመጠየቅ እና ተጋፍጦ ለመሄድ የሚያስችል አሰራር አለ። አመራሮችንም ሆነ መገናኛ ብዙሃንን በግልጽ አግኝቶ ለማነጋገር ይቻላል። ያለምንም ችግር ቅርስ ላይ የሚደርሰውን ችግር ለመግለጽ ችለናል፤ ይህ ለውጥ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት ትውልዱ ከቅርስና ታሪክ ጋር ያለው ግንኙነት መሰረት እንዳይኖረው አድርጓል የሚል ክስ ቡድኑ ላይ ሲቀርብ ይደመጣል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ መቆያ፡- ህወሓት በስልጣን ዘመኑ ትውልዱን ስለቅርስና ታሪኩ እንዳያውቅ ብቻ ሳይሆን እንዲጠላው አድርጎ ነው ለመቅረጽ የሞከረው። በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ስለቅርስ የሚያስረዱ ክፍሎች ውስን ናቸው። ያ የፈጠረው ከፍተት ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች በቅርስነት የተመዘገቡ ሃውልቶችን ጭምር እንዲያፈርሱ አድርጓል።
ቅርሱን ሲያፈርሱ የነበሩ ወጣቶች የተነገራቸውና፣ ይማሩ የነበረው ማንነታቸውንና ታሪካቸውን እንዳያውቁ ተደርገው እንደነበር ነው። ያንን ቅርስ ተጠቅሜ ለገቢ ማግኛነት መቀየር አለብኝ የሚል እሳቤ ሳይሆን በዘረኝነት መንፈስ ማውደም አለብኝ የሚል ትርክት ነው ህወሓት ሲፈጥር የኖረው።
አሸባሪው ህወሓት በ27 ዓመቱ የስልጣን ቆይታው ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውን እንዲያጡ ነው አበክሮ የሰራው። ከብሔር ጋር ተያይዞ አንዱ ሌላውን እንዲጠላ ስለሰራ አንተ ከሌላ ብሔር ሆነህ አንኮበር ላይ አንድ በዓል ስታከብር ብትታይ ሌላ ስም እንዲሰጥህ ይደረጋል። ስለዚህ ትውልዱ በእራሱ አካባቢ ማንነት ብቻ ታጥሮ የሌላውን እየነቀፈ እንዲኖር አድርጎት ነበር።
ታሪክን በመነጣጠል አንድነታችንን እንድናጣ ሲሰራ የቆየ ቡድን ነው። አንድ ወጣት ከእራሱ ብሔር ውጪ የሌላው ብሔር ቅርስ የሀገሪቷ ሀብት እንዳይመስለው የሚያደርግ ሥርዓተ ትምህርት እና የፖለቲካ አካሄድ ነው ሲተገበር የቆየው። ይህ አካሄዱ በቅርስ ላይ ተጽእኖው ከፍተኛ ነው።
ለአብነት በቀደመ ጊዜ የነበሩ ነገስታትን ሃውልቶች ሐረር ላይ ያፈረሱ ወጣቶች ከተዘራባቸው ዘረኝነት ውጪ ቢጠየቁ ሌላ ምክንያት የላቸውም። ጊዜው ሲያልፍ ንብረቱን ያወደሙ ሰዎችም ይጸጸታሉ፤ ይሁንና ቅርሱ ግን አይመለስም። እራሳቸው ተቀጥረው የሚሰሩበትን ቦታ ያፈረሱ ወጣቶች አሁን ላይ ሊያገኙ የሚችሉትን ገቢ አሊያም ስለቅርሱ ደህንነት እንዳያስቡ ሆነው ነበር። ይህም የ27 ዓመቱ አገዛዝ ያስከተለው መጥፎ ተጽእኖ ውጤት ነው።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበር አሁን ቢሮው የሚገኘው በ1880ዎቹ በተገነባው የራስ ከበደ መንገሻ ቅርስ ቤት ውስጥ ነው፤ ቤቱ አሰራሩ እና ጥንካሬው ለትውልዱ ማስተማሪያ የሆነ የሀገር ሀብት ነው። ዛሬ እኔ ተነስቼ ቅርሱን ለማፍረስ መዶሻ ይዤ የምነሳ ከሆነ ትልቅ በሽታ ነው።
ይሄ የእከሌ ቁስ ነው፣ ይሄ የእዛኛው ነው በሚል እንድንጠላው ተደረገ እንጂ የኢትዮጵያ ንብረት ነው፤ የኢትዮጵያውያን ቅርስ ነው፤ የሚል አስተሳሰብ እንዲሰርጽ አልነበረም አሸባሪው ቡድን ሲሰራ የቆየው። በዚህ ረገድ ትልቅ በሽታ ነው ውስጣችን ለማሳደር ሲጥር የቆየው።
ታላላቅ ሰዎች በጊዜአቸው ለሀገራቸው ሰርተው አልፈዋል፤ አሁን ባይኖሩም ቅርሱን አስቀምጠውልን አልፈዋል። ቅርሱን እየተንከባከብን የእራሳችንን አሻራ ለሀገራችን እያሳረፍን እንቀጥላለን የሚል አስተሳሰብ እንዳይስፋፋ በወጣቱ ላይ ተሰርቷል። ይሄ ደግሞ የህወሓት ሴራ አካል ነው።
ይህ ደባ የተሞላበት አካሄዱ ነው ህወሓትን እንዲጠላ ያደረገው። አሁን ላይ ኢትዮጵያዊነት፤ ማንነታችን የማክበርና የመጠበቅ እንዲሁም አንድነታችንን የማጎልበት ስራዎች አሉ፤ የሚበረታቱ ናቸው፤ ይህ እሳቤ እንዲያድግ ግን ይበልጥ መስራት ያስፋልጋል። ስለማንነት እና ታሪክ ይበልጥ ስናውቅ ደግሞ ቅርሶቻችችንን መጠበቅ እና በቅርሶቻችንን ይበልጥ መጠቀም እንጀምራለን።
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎቹ በዓለም ቅርስነት በተመዘገበው ላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት አካባቢ ታይተዋል፤ ይህ ቅርሱ ላይ የሚያሳድረው ጫና እስከምን ድረስ ነው?
አቶ መቆያ፡- የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች ወደ ላሊበላ ገቡ መባሉን እኛም ሰምተናል። የውጊያ መሳሪያዎችን ይዘው ወደ ታሪካዊቷ ከተማ መግባታቸው ደግሞ ቅርሱ ላይ የሚያሳድረው ጫና አለ። ወደ ላሊበላ ገብቶ ጦርነት መክፈት ለቅርሱ አለማሰብና ለማንነታችንም አለመጨነቅ ነው።
ወደ ላሊበላ አካባቢ የአሸባሪው ሰዎች ምን አይነት ጉዳት እንዳደረሱ እንኳን በበቂ ሁኔታ መረጃ መሰብሰብ አልተቻለም። የአሸባሪው ህወሓት ሰዎች ወደላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት መግባታቸው ሲሰማ ብዙ ነገር ሊጠፋ እንደሚችል ተገማች ነው።
በግጭቱ ምክንያት በርካታ የኢትዮጵያን ቅርሶች አደጋ ውስጥ ናቸው። ቅርስ ሲባል ቋሚ ቅርስ ብቻ አይደለም፤ በአብያተ ክርስቲያናቱ ውስጥ የሚገኙ ዘመናትን ያስቆጠሩ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችም አሉ። እነዚያን ቅርሶች አንዳቸው በኪሳቸው ይዘው ሊወጡበት የሚችል እድል አለ። ከዚህ አንጻር ብዙ ጥፋት ይከሰታል።
የላሊበላ ውቅር ህንጻ አለመፍረሱ ብቻ ሳይሆን በውስጡ ያሉ በየትኛውም ቦታ ሊገኙም ሆነ ሊተኩ የማይችሉ ቅርሶች የህወሓት ታጣቂዎች ምን አይነት ጉዳት አድርሰውባቸው እንዳለፉ በቀጣይ የምናየው ይሆናል።
አሸባሪው ህወሓት በፈጠረው ግጭት የሀገሪቷ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆኑ በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከባድ ነው። ቡድኑ በፈጠረው ግጭት ሰላም አለመኖሩ በራሱ በቅርሶቻችን ደህንነት ላይ ትልቅ ዋጋ ያስከፍለናል።
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በአብያተክርስቲያናትና በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መሳሪያ ያከማቹበት እንዲሁም ጥቃት እንዲደርስባቸው ያደረጉበት መንገድ ምን ያመላክታል?
አቶ መቆያ፡- ሃይማኖታዊ ተቋማትን ከዓላማቸው ውጪ የመሳሪያ ማከማቻ እና የግጭት መናኸሪያ እንዲሆኑ ማድረግ ከባድ ዓለም አቀፋዊ ወንጀል ነው። ሌላው ይቅርና ቤተክርስቲያናት እና መስጂዶች ውስጥ ከባድ መሳሪያዎች መታየታቸው በእራሱ አሳፋሪ ነው።
በሽብር የተሰማራው ቡድን በሃይማኖታዊ ተቋማቱ ውስጥ መሳሪያዎችን ካከማቸ በየተቋማቱ የነበሩ ቅርሶችስ አሁን በቦታቸው አሉ ወይ የሚለው በእራሱ አጠያያቂ ነው። ትልቅ የሀገር ሀብት እንዲወድሙ እና እንደጠፋ አያጠያይቅም። አሸባሪው ህወሓት በሚያካሂዳቸው ጦርነቶች የሀገርን ሀብት እያወደመ እና ቅርሶችን ባለቤት አልባ እያደረገ መሆኑ ግልጽ ነው።
አልነጃሺ መስጂድ እና በርካታ የኦርቶዶክስ ሃይማኖታዊ ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሷል። ይህንን እያዩ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን መምረጣቸው በእራሱ አስገራሚ ጉዳይ ነው። አሁንም ቡድኑ በሚፈጽማቸው ጥቃቶች በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አማራ ክልልም ሆነ አፋር ክልልን ጨምሮ ላይተኩ የሚችሉ ቅርሶች ላይ ጉዳት ማድረሱ አይቀርም።
ቅርሶቻችን አብዛኛዎቹ ጥገና ያስፈልጋቸዋል፤ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል እያልን በነበረበት ወቅት ህወሓት ግጭት መፍጠሩ ጉዳዩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው አድርጎታል። ይህ ነገር መቼም በዚሁ አይቀጥልም፤ ነገሮች ሲረጋጉና ሰላም ሲወርድ አጠቃላይ ቅርሶቻችን ላይ ጥናትና ቆጠራ እንደሚደረግ እንጠብቃለን።
አዲስ ዘመን፡- በግጭቱ ምክንያት በቅርሶች ላይ ለሚደርስ ጉዳይ ተጠያቂው ማነው?
አቶ መቆያ፡- ተጠያቂው መሳሪያውን በቤተክርስቲያኖች ያስቀመጠው፤ ግጭት የፈጠረው አሸባሪ ቡድን ነው። እራሳቸው በለኮሱት እሳትና ችግር ምክንያት የታሪክ ማህደሮች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂ መሆን አለባቸው።
ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመው ውድ ቅርሶችን ለሌላ አጀንዳ ማዋላቸው የሚያስወግዛቸው ነው። እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ስናይ የአሸባሪው ህወሓት ሰዎች ለቅርስና ታሪክ ዴንታ የማይሰጡ መሆኑን ይበልጥ እንረዳለን።
ቡድኑ በሚያደርሰው ጉዳት ዓላማው ማንነታችንን እያጣን እንድንሄድ ማድረግ ነው። ትላልቅ ህንጻዎችን ልንገነባ እንችላለን፤ ባህላችንን የቀደመ አኗኗርና ታሪካችንን እንዲሁም ትውፊቶቻችንን በአግባቡ የሚገልጹ ማንነቶቻችንን ግን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እንዳንችል ነው አሸባሪው ህወሓት እየሰራ ያለው።
በሃይማኖት ተቋማት ላይ፤ በሙዚየሞቻችን እና በተለያዩ ተፈጥሯዊ ቅርሶቻችን አቅራቢያ በሚፈፀም ጥቃት ንብረቶቻችን ይወድማሉ፤ የህወሓት ታጣቂዎች ይህንን ነገር ፈጽመውት ወደሌላ ቦታ ሊሸጋገሩ ይችላሉ። ትውልዱ ግን ንብረቶቻችንን አልጠበቃችሁም ብሎ የሚወቅስበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል።
ህወሓት እራሱን ችሎ በአሸባሪነት ተፈርጇል፤ ለሚያደርሰው ጉዳትም የሚጠየቅበት የእራሱ መንገድ አለው። የአሸባሪ ቡድን አባላት ተገቢው እርምጃ ሊወሰድባቸው እና የእርምት እርምጃ ሊሰጣቸው ይገባል። የሚያወድማቸው ቅርሶች ግን አንዳንዶቹ ሊመልሳቸው የማይችሉ ናቸውና ከዚህ በኋላ ላለው እና ሊደርስ ለሚችለው ጉዳት ሁሉ መጠንቀቅ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት የሚያደርሰው ጥቃት በዚሁ ከቀጠለ በቅርሶች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምን አይነት መዘዝ ይዞ ሊመጣ ይችላል?
አቶ መቆያ፡- በጣም ከባድ ነው። ቡድኑ ቅርሶች ላይ ጉዳት ማድረስን እንደቀላል ነገር እያየነው ነው። ነገር ግን ቡድኑ ለደረሰበት ጉዳት በአካባቢው የሚያገኛቸውን ቅርሶች ማውደምን የመበቀያ መንገድ አድርጎ ሊወስድ ይችላል።
ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ቅርሶቻችን የትም ይኑሩ የትም የኢትዮጵያ ንብረቶች ናቸው። የውጭ ዜጎችም ሊጎበኟውቸው ሲመጡ የዚህ ብሔር የዚያኛው አካባቢ ብለው በመከፋፈል ሳይሆን የኢትዮጵያን ቅርሶች እንጎብኝ ብለው ነው የሚመጡት። እነዚህን ቅርሶችን ማጣት ማንነትን የማጣት ያክል ነው የሚጎዳን።
ግጭቱ በዚሁ ከቀጠለ ህልውናችን አደጋ ላይ ነው፤ ድሮ ይህን የመሰለ ታሪክ ነበረን ብለን የምናስተዋውቅባቸው ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ቅርሶች አይኖሩንም። ይህ ደግሞ በሰብእና ግንባታ ውድቀት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አለው።
አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ውድ ቅርሶችን ማጥፋት እራስን የመግደል ያክል ነው። በተለይ እንደ ላሊበላ አክሱም እና ሌሎች በርካታ ጎብኚ የሚናፍቃቸውን ቅርሶቻችን በግጭቱ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ሃዘናችንም የከፋ ይሆናል። ለቀጣዩ ትውልድም የምናስተላልፈው ነገር ከማጣት ባለፈ የታሪክም ተወቃሽ እንሆናለን።
ስለዚህ ውስብስብ የሆነውን ችግር ለማቃለል ግጭት ፈጣሪውን ቡድን በጋራ ማስቆም ይገባል። የአሸባሪው ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች የሚያደርሰውን ጥቃት በመቀልበስ ሀገርን የማዳን እና ቅርሶችን የማትረፍ ተግባር ላይ መንግስትና ህዝብ ይበልጥ ተባብረው መሳተፍ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት በሚፈጥረው ጥቃት ምክንያት ቱሪዝም ዘርፉ ላይ የሚደርሰው ጫና እስከምን ድረስ ነው?
አቶ መቆያ፡- ግጭት ካለ ጎብኚ ለመምጣት አይደፍርም፤ የሚመጣም ካለ በእርዳታ እና በተለያየ ሰበብ ቅርሶችን ለመዝረፍ የሚፈልገው ሊሆን ይችላል። ቱሪዝም የለም ማለት የአየር መንገድ እንቅስቃሴውም በዚያው ልክ ይቀንሳል፤ የአየር መንገድ ገቢውም ላይ ተጽእኖ ያሳድራል ማለት ነው።
የሆቴሎች ገቢ፤ የአስጎብኚው የታክሲ አገልገሎት ሰጪው እና በየዘርፉ ያለው የስራ እድልና ገቢ በዚያው ልክ እያሽቆለቆለ ይሄዳል። በተቃራኒው ደግሞ የስራ አጥ ቁጥር ይጨምራል። ስለዚህ ግጭት ፈጣሪው ቡድን እያደረሰ ያለው ኪሳራ ተነግሮ የማያልቅ ነው።
ቡድኑ የሚፈጽመው ጥቃት ቢቀንስ እና መንግስት ሙሉ በሙሉ ሀገር የማረጋጋት ስራውን ቢያጠናቅቅ እንኳን ወዲያው ቱሪስት የማግኘት እድሉ ዝቅተኛ ነው። በኮቪድ የተጎዳው የቱሪዝም ዘርፍ አሁን ደግሞ አሸባሪው ህወሓት በሚፈጥረው ጥቃት ይበልጥ እየተጎዳ ነው። በአስጎብኚነት በሆቴል እና ትራንስፖርት ዘርፍ ተሰማርተው ገቢ መሰብሰብ የነበረባቸው የትግራይ ወጣቶችም በብዛት ወደጦርነት እንዲማገዱ እያደረገ ነው።
ስለዚህ የተያያዘ ጫና ነው እየደረሰ ያለው። መንግስትም አሸባሪ ቡድኑን ለማስወገድ የሰጠው ትኩረት እና የህዝብ ድጋፍ ተዳምሮ ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ሲወገድ የቱሪዝሙም ጉዳይ እልባት ያገኛል። እስከዚያው ድረስ ግን ከፍተኛ ቅርስ ያለባቸው ቦታዎች ተለይተው በልዩ ሁኔታ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት በተለያዩ ቅርሶችና ከተሞች ላይ ጥቃት ሲፈጽም ዓለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን የመምረጣቸው ጉዳት ምክንያቱ ምንድንው ይላሉ?
አቶ መቆያ፡- አሁን ባለው ሁኔታ አሸባሪ ቡድኑ ንጹሃን ላይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ እና ቅርሶች ላይ አደጋ ሲጥል ዓለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን የመምረጣቸው ጉዳይ እኛንም እየገረመን ነው። ምክንያቱም ብዙዎቹ ስለሰብአዊነት እና ስለቅርሶች ደህንነት የሚሟገቱ ተቋማት ነበሩ፤ አሁን ላይ ግን እንዳላዩና እንዳልሰሙ የመሆናቸው ሚስጥር አሳፋሪ ነው።
ኃያላን የሚባሉ ሀገራት ጭምር ጥቃቶቹን እየሰሙ የብዙዎቻችንን ጥሪ ወደጎን መተው መምረጣቸው ጉዳዩን ከባድ ያደርገዋል። የጥቃቱ አካል የሆኑም የውጭ ኃይሎች አሉ። ይህ አካሄድ ግን በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ነው።
ለኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ በየመገናኛ ብዙሃኖቻቸው ችግሮችን የሚያባብሱ ጉዳዮች ላይ አተኩረዋል። አንዳንድ ኃያላን ሀገራት ዓላማቸው አሸባሪ ቡድኑን መደገፍ ነው ወይስ ሌላ ዓላማ አላቸው የሚለውን ለፖለቲከኞቹ ትተነው እንደቅርስ ተቆርቋሪ ግን አካሄዳቸው ተቀባይነት የሌለው ነው።
የውጭ ዜጎች ከዚህ ቀደም በረሃብ ነው የሚታወቁት እያሉን ይህን አስተሳሰባቸውን ለመቀየር ብዙ ጥረናል። አሁን ደግሞ መልሰው ቅርሶቻቸውን አውድመው ጨረሱ ለማለት የሚሯሯጡም አይጠፉምና ጥንቃቄ ማድረጉ በእያንዳንዳችን እጅ ነው።
የውጭዎቹ ረዱንም አልረዱንም እኛ ቅርሶቻችችንን መጠበቅ አለብን። ስለዚህ መንግስት ባለው መረጃ መሰረት አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል የሚባሉ ቦታዎችን በመለየት ቅርሶች ላይ ጥበቃ ያደርጋል ብለን እንገምታለን። ህዝብም በዚህ ጉዳይ ከመንግስት ጎን በመቆም ሊተባበር ይገባል። የዓለም አቀፍ ተቋማት ግን ዝምታ መምረጣቸው ከቆሙለት ዓላማ ጋር የሚጋጭ ተግባር ላይ መሆናቸው ያሳያል።
አዲስ ዘመን፡- በተለያየየ መንገድ ወደሀገር ውስጥ የገቡ የውጭ ዜጎችና ተቋማት ግጭቱን ተንተርስው ቅርሶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱበት መንገድ አይኖርም?
አቶ መቆያ፡- በሀገራችን የሰሜኑ ክፍል ግጭት ባለባቸው ቦታዎች ላይ የውጭ ዜጎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰራተኞች በእርዳታ ሰጪነት ስም ገብተው ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ከዓላማቸውም ውጪ የሚንቀሳቀሱ ናቸው።
በሰብአዊ ድጋፍ ስም የገቡ የውጭ ዜጎች ግጭቱን ተጠቅመው የማንተካቸውን ቅርሶች ለማሸሽ ሁኔታዎችን ሊያመቻቹ የሚችሉበት እድል አለ። በተግባርም እንደታየው ከሱቅ ነው የገዛሁት ከዚህ ቦታ ተረክቤ ነው በማለት ይዘው ሊወጡ ሲሉ በአየር መንገድ የተያዙ በርካታ ሰዎችም አሉ።
በተለየ ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶች በሌላው ዓለም የማይገኙ ናቸው። ስለዚህ ግጭት ሲፈጠር ስራዬ ብሎ እነዚህን ቅርሶች ፍለጋ የሚመጣም ዘራፊ ሊኖር ይችላል። ግጭት ሲኖር ደግሞ የኢትዮጵያ ቅርሶች በተለያየ መንገድ ለማውጣት የሚጥሩ ሰዎች ይበልጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋልና ቅርሶቻችችን የት እንደደረሱ እንኳን ሳናውቅ ደብዛቸውን ሊያጠፏቸው እንደሚችሉ ይገመታል።
የውጭ ሰዎች ደግሞ ባገኙት አጋጣሚ ወደሀገራቸው ይዘው ቢሄዱ ቅርሶቹ በውጭ ገንዘብ ይሸጧቸዋል። አሊያም የእኛ ንብረት ናቸው ብለው ለሌላ ዓላማ ያውሏቸዋል። ስለዚህ በጥቃቶቹ ምክንያት የሚፈጠረው ችግር ሀገርን የሚጎዳ ማንነትን የሚያሳጣ ነው።
በተለያዩ ሀገራት የተበተኑትም ቅርሶቻችንን እንዴት ማስመለስ አለብን ብለን እያሰብን ህወሓት በሚፈጽመው ጥቃት ምክንያት ደግሞ ሀገር ውስጥ ያለውም ለዘረፋ ተጋልጧል። ይህ ችግር የሀገርን አንጡራ ሀብት እስከማሳጣት የሚያደርስ ስጋትን የፈጠረ ነው።
ስለዚህ በእርዳታ ስም እየመጡ የሃይማኖት ተቋማትንም ሆነ በየሙዚየሞቻችን የሚገኙ ቅርሶቻችችንን እንዳያሸሹ መውጫ መግቢያዎች ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥር ማጠናከር ይገባል። በተለይ አየር መንገድ ፍተሻዎች ላይ ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በበቂ ሁኔታ መለየት የሚችሉ መሳሪያዎች እና ባለሙያዎችን በመመደብ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ ነን።
ለዚህ አይነቱ የጥንቃቄ ስራ ያደጉ ሀገራት የሰለጠኑ ውሾችን እና ዘመናዊ መሳሪያዎችን ይጠቀማሉ። እኛም ደግሞ ባለን አቅም ልምዳቸውን ልንተገብር ይገባል። በሌላ በኩል በሃይማኖት አገልግሎት ያሳለፉ ወጣቶች እና በዘርፉ ልምድ ያላቸውን ምሁራንን በበቂ ሁኔታ መጠቀም ይችላል። አንዳንድ ወጣቶች የትኛው የብራና መጽሐፍ በቅርብ ጊዜ የተጻፈ ነው የትኛው ጥንታዊ ነው የሚለውን ከልምድ የመለየት ችሎታ አላቸውና ከእነሱም ጋር ተቀራርቦ መስራት ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ ግን ከጦርነቱ በላይ ቅርሶቻችን ላይ አፍጥጠው የሚጠብቁ የውጭ ዜጎች በርካታ ናቸው። የውጭ ዜጎች የኢትዮጵያን ቅርሶች ካገኙ አያልፏቸውም፤ ያጓጓቸዋል። የኢትዮጵያን ቅርሶች የተረዱ የውጭ ዜጎች ቅርሶቻችንን በተገኘው አቅጣጫ አሾልከው ሊያስወጡ እንደሚችሉ ይገመታል። በዚህ ጦርነት ወቅት ቅርስን ማሸሽ ብቻ ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስም አካል ይኖራል።
ይሄን አጋጣሚ ተጠቅመው ንብረቶቻችንን ለመቀባበል ከፍተኛ ዝግጅት እንዳደረጉ ይገመታል። ከዚህ አደጋ ለመዳን ሁሉም ዜጋ የየትኛውም አካባቢ ቅርስ የእራሱ ንብረት እንደሆነ በመረዳት አጠራጣሪ ነገሮችን ሲያይ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ መቆያ፡- እኔም ለቃለመጠይቁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2013