የአሜሪካ ዳያስፖራ የሰላም ጓድ 13 ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ያዋቀሩት ድርጅት ነው። በዚህ ውስጥ ደግሞ አቶ ዳዊት ገለሶ አላምቦ የወከሉት ድርጅት ‹‹ኦሞ ኢትዮጵያ አንድነትና ፍትህ ማዕከልን ሲሆን፣ እርሳቸው የድርጅቱ መስራችና ፕሬዚዳንት ናቸው። በአገር ቤት እያሉ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ያስተማሩ ሲሆን፣ በተወሰኑ መስሪያ ቤቶች ደግሞ በኃላፊነት ደረጃ ሠርተዋል። እንዲሁም በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ኃላፊ ሆነው እየሠሩ ሳለ የስኮላርሺፕ ዕድል አግኘተው ወደውጭ አገር አቀኑ። በውጭ አገር በተለያየ ቦታ የቆዩ ሲሆን፣ በቆይታቸውም በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል። እርሳቸው ከሰላም ጓዱ በተጨማሪ 20 ያህል ድርጅቶች ያቋቋሙት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ፀሐፊ ናቸው። የሰላም ጓዱ ከተመሰረተ ስምንት ወር ያህል አስቆጥሯል። ምንም እንኳ ወደኢትዮጵያ የመጡት ዘጠኝ ያህሉ ብቻ ቢሆኑም ብዙዎቹ በተለያየ ምክንያት ሳይመጡ ቀርተዋል። ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ምን ዓይነት አበርክቶ እንዳለውና ኢትዮጵያ አጣብቂኝ ውስጥ በገባች ጊዜ በምን አግባብ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳሉ እንዲሁም ሊወጡ ስላሰቡት ጉዳይ የሰላም ጓዱ ፕሬስና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ከሆኑት አቶ ዳዊት ጋር አዲስ ዘመን ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- በአገረ አሜሪካ ያለው ዲያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ያለው ዋና ዓላማ ምንድን ነው?
አቶ ዳዊት፡-ቀደም ሲል በአገራችን ጉዳይ ብዙ ጊዜ ተወያይተናል። ለበርካታ ጊዜያትም በአገር ጉዳይ ሰልፍ ወጥተናል። በእነዛ ሰልፎች ላይም በርካታ አገርን ሊታደጉ የሚችሉ መልዕክቶችን አስተላልፈናል። በተለያዩ ጊዜያትም መግለጫዎችን በየድርጅቶቻችንና ሲቪል ማህበራት አማካይነት አውጥተናል። ከዚህም ጎን ለጎን መንግሥት እንዲህና እንዲያ ያድርግ ስንልም ተናግረናል።
በአሁን ወቅት ደግሞ ያሉት ወቅታዊ ጉዳዮችና በተከታታይ የሚወጡ ዜናዎችን ብቻ ከማየትና ከመናገር በላይ ህዝብ መሃል ገብተን እውነታውን የምናረጋግጥበት ጊዜ ላይ በመድረሳችን እነሆ ወደትውልድ አገራችን መጥተን መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በመከታተል ላይ እንገኛለን። በአሁን ወቅት ወደኢትዮጵያ የመጣው የዳያስፖራው የሰላም ጓዱ ዋና ዓላማ ምንድን ነው ብትይኝ በውጭ ሆነን በስማ በለው መረጃ ከምንሰማ በአገሪቱ ውስጥ ተገኝተን የችግሩም ሆነ የመፍትሔው አካል መሆን አለብን የሚል አቅጣጫ የያዘ ነው።
በውጭ አገር ኢትዮጵያን የመወንጀልና ስሟን የማጠልሸት ሥራ ይሠራልና በአገር ውስጥ ተገኝተን በዚህ ልክ የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸት ምን ተገኝቶ ነው በሚል ያለውን እውነታ ለመረዳት ነው ወደአገር ቤት የመጣነው። ይህን ስናደርግ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተወስነን ሳይሆን ተፈናቃዮች ወዳሉበትም በተለያየ አቅጣጫ ተከፋፈለን በመጎብኘት ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በዚህ አጣብቂኝ ጊዜ ውስጥ ባለችበት ወቅት ዲያስፖራው ለአገሩ የመቆሙና የመወገን እንቅስቃሴው ምን ይመስላል? በቀጣይስ ያለው ዓላማ ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ዳዊት፡- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለአገሩ አሳቢና ተጨናቂ ነው። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ዜና ከመሰማቱ በፊት ውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ ነው ቀድሞ የሚሰማው። ሌት ተቀን የሚዲያ አውታሮችን በመፈተሽ የኢትዮጵያን ጉዳይ በንቃት ሲከታተል ነው የሚውለው። አገሩ ባጋጠማት ችግር ሁሉ ለመርዳት የሚሹ በርካታ ናቸው። ይህ ድጋፍ ማለት ደግሞ ለውጡም ከመምጣቱ በፊት ለዴሞክራሲና ለሰላማዊ ትግል ሰልፍ መውጣትን ሁሉ የሚያካትት ነው።
ኢትዮጵያን በሚጎዱ ጉዳዮች ላይ የውጭ ኃይሎች በሚወስዷቸው ርምጃዎች ሁሉ በየአቅጣጫው ድምፃችንን ስናሰማ ነው የቆየነው። እኔ ለምሳሌ የምኖረው በዋሽግተን ዲሲ ሲሆን፣ ከሰዋሽግተን ዲሲ ኒውዮርክ በመሄድ ሰላማዊ ሰልፎችን በማድረግ ለአገሬ ይበጃታል ያልኩትን ሳደርግ ቆይቻለሁ።
እኔ ለምሳሌ ከዛሬ ሦስት ወር ገደማ በፊት ዲያስፖራው በራሱ ተነሳሽነት ወደ 375 ሺህ ያህል ዶላር ካዋጣው ድጋፍ ውስጥ ለአገር መከላከያ የሚሆነውን ይዘን ወደ አገር ውስጥ በመምጣት ለአገር መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ አስረከረበናል። እኔ ለውጥ ከመጣ በኋላ በኢትዮጵያ ጉዳይ ወደኢትዮጵያ ስመጣ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነው።
በመጀመሪያው ዙር ስመጣ ያደረኩት ነገር ቢኖር በቀጥታ ያቀናሁት ተወልጄ ወዳደኩት ወላይታ ነው። የመሄዴም ዋናው ነገር የአካባቢው ማህበረሰብ ለለውጡ የነበረውን አመለካከት በመረዳትና ባለመረዳት ውስጥ ስለነበር ነው። ይህ የሆነበትም ዋና ነገር የተለያዩ አካላት ማህበረሰቡን ወዳልተገባ ነገር ሲገፉት ነበር። ለውጡ ለወላይታ ህዝብ እንዳልመጣ እና እንዲያውም አገር የሚጎዳ እንደሆነ አድርገው ነበር ያልተገባ መረጃ ለወላይታ ሲያቀብሉት የነበረው።
እኛ ግን ለውጡን በተግባር ስናይ ኢትዮጵያውያኑን የሚያጠናክር እንጂ አንዱን በሌላው ላይ የበላይ የሚያደርግ ለውጥ እንዳልሆነ ነው መረዳት የቻልነው። እኛ በወቅቱ ልማትና ዴሞክራሲን ሊያመጣ የሚችል የመንግሥት ኃይል አንዳለ መረዳት ችለናል። ስለዚህ ይህን መረዳት ይዤ ህዝቤን በቋንቋዬ ማስተማር አለብኝ በሚል ነበር ወደስፍራው ላቀና የቻልኩት። በዚያም ለሦስት ወራት ያህል በወላይታ ገጠራማው ክፍል መብራት በሌለበት አካባቢ ሁሉ እዚያው በማደርና እውነታውን በማስተማር ቆይታ አድርጌያለሁ። በወቅቱ የእኔን ማስተማር ያልፈለጉ ኃይሎች በግልጽ ጉዳት ሊያድርሱብኝ ብዙ ጥረዋል።
በኋላ ወደአሜሪካ በመመለስ ነው ሲቪክ ማህበሩን ለማቋቋም የወሰንኩት። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በግል በብዙ ዋጋ ብከፍልም እውቅና የሚሰጥና ጉዳዩን ከልብ ተቀብሎ የሚተገብረው አካል የታሰበውን ያህል መሆን ባለመቻሉ ነው። ለዚህም ነው የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች የሲቪክ ማህበሩን ለመመስረት የተነሳሳሁት። ይህ ሲቪክ ማህበር ሲቋቋም ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ድርጅቶች ጋር ህብረት ፈጥርን፤ ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበርን መሰረትን፤ በቅርቡ ደግሞ የሰላም ጓድ መመስረት ቻልን።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በፊት የነበረው በርካታው ዳያስፖራ ብዙ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣው መንግሥትን ለመቃወም ነው ይባላል፤ ከለውጡ በፊትና ከለውጡ በኋላ ያለው ዳያስፖራ የሚገለጸው እንዴት ነው?
አቶ ዳዊት፡- እኔ ይህን በሦስት ደረጃ ከፍዬ ነው የማስቀምጠው። ከለውጥ በፊት የነበረው ዳያስፖራ 75 በመቶ መንግሥትን ተቃዋሚ ነው ማለት ያስደፍራል። በጠቅላላ መንግሥትንና መንግሥት የሚፈጥረውን ጭቆናን በመቃወም ሰልፍ የሚወጣ ነበር፤ ለዚህ ዋና ምክንያቱ ዜጎች ያለአግባብ አይታሰሩ፤ ዴሞክራሲ በአገሪቱ ይኑር የሚሉና መሰል አስተሳሰቦችን በመያዝ እና እሱን ለማንጸባረቅ ነበር ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደግሞ መንግሥት ይውረድና በምርጫ ሰላማዊ የሆነ ሽግግር ይመስረት የሚልም ጭምር ነበር። እነዚህ ነገሮች የተለያየ ንቅናቄንም በመፍጠርና ወደአገር ቤትም በመዝለቅ መንግሥት ሊለወጥ በቃ።
በወቅቱ በመጣው ለውጥ ሁላችንም በሚያስብል መልኩ ፍጹም ደስተኞች ነን ማለት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ወደዋሽንገተን ዲሲ በመጡበት ጊዜ የአቀባበል ኮሚቴው አንዱ አስተባባሪ ነበርኩና በወቅቱ የተደረገው እጅግ በጣም ትልቅ የአቀባበል ሰልፍ ነበር። ሰልፉም ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ እዚያው የሚጠበቅበት ቦታ ፍራሽ በማንጠፍ ነበር ድጋፍ ለመስጠት ዋጋ ሲከፍል የነበረው። በዚህ ልክ ነበር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲደረግ የነበረው ድጋፍ የሚታወሰው።
ከዚህ ሌላ ደግሞ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማኪያቶ ቀንሳችሁ አንድ ዶላር በማለታቸው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የሚል በመቋቋሙ ገንዘብ ማዋጣት ጀመርን፤ ይህም ሥራ ውጤታማ ይሆን ዘንድ በየጊዜው ቅስቀሳ ማድረግ ጀመርን፤ በዚህም ውጤታማ መሆን ቻልን።
በመሃል ግን በአገር ቤት ከወደ ቡራዩ አካባቢ ችግር ተከሰተ፤ ይህ በዚህ ሳያበቃ አዲስ አበባን ለአዲስ አበቤ የሚል ሌላ ድርጅት ደግሞ ተቋቋመ። አገሪቱ በማዕበል መናወጥ ጀመረች። በጉጂና በጌዲዮ መካከል ችግር ተፈጠረ፤ ተፋናቃዮች በየቦታው በረከቱ። አንዱ ሌላውን ሲገፋ መታየት ተለመደ። ይህን ሁሉ የራሱን እቅድ ነድፎ በየቦታው ሲያስተገብር የነበረው የጁንታው እጅና እሱ ያዘጋጀው ፓኬጅ ነው። በዚህ ሳያበቃ የጁንታው ፓኬጅ አሜሪካ ድረስ ዘለቀ። በዚህ ጊዜ በውጭ አገር ያለው ዳያስፖራው ለሁለት ተከፈለ።
አንደኛው ቡድን አዲስ አበባን የመቆጣጠር ስሜት የነበረው ሲሆን፣ አዲስ አበባ ክልል መሆን አለባት የሚል ጽኑ አቋም የያዘ ሆኖ ቁጭ አለ። ይህ ደግሞ ህገ መንግሥታዊ ስርዓትን ባልተከተለ ሁኔታ አዲስ አበባ ክልል መሆን አለበት በሚልም ደመደመ። ይህ አይሆንም የሚል ደግሞ በሌላ ጽንፍ የቆመ ሌላ ኃይል ደግሞ ነበረ። ይህን ተከትሎ እንደ 360 ያሉ ሚዲያዎች (መረጃ አቀባዮች) ወጡ።
የተለያዩ ውዝግቦች በመከሰታቸው የለውጡን መንግሥት ለመደገፍ እንዳያስችለን ፈተና ሆኑብን። አንደኛ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በሚል ተቋቁሙ የገንዘብ ድጋፍ ሲደረግ የነበረበትም ቀጣይነቱን ማረጋገጥ አልተቻለም።
ከዚህ ጎን ለጎን የዘር ፖለቲካ የሚያራምደው የጁንታው ኃይል አለ። በወቅቱ ችግሮቹን ለማራገብ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ነበር ሲያካሄድ የነበረው። እነርሱ የተደራጁት አስቀድመው ነው። ይህን ሲያደርጉ የነበረው በእጃቸው በነበረው የመንግሥት ስልጣን በመጠቀም ነው። ከአገር ሲወጡ የነበራቸውን ስልጣን በመጠቀም በተለያየ ስልት ሲሆን፣ በወቅቱም ይዘው የሄዱት በርካታ ገንዘብ ነው። በውጭ አገር ደግሞ አርፈው የሚቀመጡ ሳይሆን ይዘው በወጡት ገንዘብ ሎቢስት ገዝተው ሌላውንም እንደየፈርጁ አደራጅተው ነው የተለመደ ሥራቸውን ሲሠሩ የቆዩት። በዚህ ሥራቸው ደግሞ ከፍተኛ ጥረት ለማድረግ ያሰቡት ኢትዮጵያን ለማንበርከክና ወያኔን ወደስልጣን ለመመለስ ነው።
በተለያየ መንገድ ወደውጭ አገር የሚወጣ የእነርሱ ሰውም ሆነ የእነርሱን ዓላማ የሚደግፍ ሁሉ ከአገር ሲወጣ ገንዘብ እየያዘ ነው። በቅርቡ የማውቀውን ለመግለጽ ያህል በአሁን ወቅት በማረሚያ የሚገኘው የቀድሞው የሱማሌ ርዕሰ መስተዳደር አብዲ ኢሌ፣ ከመታሰሩ በፊት ጁንታዎቹ አመቻችተውለት ብዙ ገንዘብ ይዞ ወደ አሜሪካ በማቅናት ድርጅት ከፍቶ እንደነበር አውቃለሁ። አጋጣሚ ሆኖ መንግሥት ቀደመው እንጂ ባይያዝ ኖሮ በአገረ አሜሪካ የተደላደለ ኑሮ እንዲኖር ነው ታቅዶ የነበረው።
በነገራችን ላይ ጁንታዎቹ ሱማሌ ወይ አማራ ወይ ትግሬ ወይም ሌላ ብሄር ብቻ አይደሉም። በእነዛ ስብስብ ውስጥ የወላይታውም ጭምር አለበት። እነዚህ አካላት በሚፈልጉት ልክ የተደራጁ ነበርና እነርሱ በሚፈጥሩት ወከባ ዳያስፖራው እየተከፋፈለና ጥንካሬው እየላላ መጣ።
በዚህ መሃል የአርቲስት ሃጫሉ ግድያ ተከሰተ። በዚህም መነሻነት ሌሎች ኃይላት ራሳቸውን በማጠናከር ሰላም እንዲጠፋ በብዙ መሥራታቸውን ተከትሎ በዳያስፖራውም ውስጥ እንዲሁ የተለያዩ ክፍፍሎች ሊፈጠሩ ቻሉ። ኢትዮጵያ ትውደም፤ ትፍረስ የሚልና መሰል መግለጫዎችን ያወጣሉ።
ይህ እየሆነ ባለበት ነው የኢትዮጵያ መንግሥት ወደህግ ማስከበሩ ተግባር የተሰማራው። ይህ ማለት መንግሥት አንዱን ችግር ሳይሻገር ሌላ ችግር ተደቀነበት ማለት ነው። ይህን ጉዳይ ደግሞ በገንዘብ ተገዝተው የሚያራቡ በርካታ ሰዎች አሉ። እነዚህ ጉዳዮች ዳያስፖራውን ከፋፈሉት ማለት ነው። ደጋፊ እንዳለ ሁሉ፤ ከፍተኛ ተቃዋሚ አለ። አሁን እንኳ ወደአገር ቤት የገባነው የሰላም ጓዱ አባላትን መንግሥት በገንዘብ ገዝቶ እንዳስመጣን አድርጎ እያስወራ ያለ አካል አለ። ገሚሱ ደግሞ ለሲ.አይ.ኤ ለመሥራት ነው ሲል ያልተገራ ሐሳቡን ሲገልጽ ይደመጣል። በጥቅሉ የተለያየ ትርጉም በመስጠት በጋዜጣውም በማህበራዊ ትስስር ገጹም ላይ ይጽፋሉ። ይህን ከሚያደርጉት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፎቶ በፊት ለፊት በማድረግ ለአገር ሰላም መሆን የሚሠራ በመምስል መንግሥትን ሲኮንን የሚውልና ስም ሲያጠፋ የሚያመሽ ኃይል ነው።
እኛ ያለውን ኃይል የምንፈረጀው የአገር ተቃዋሚና የአገር ደጋፊ ኃይል በሚል ነው። አገር ካለ ነው መንግሥት የሚኖረውና ማስተዳደር የሚችለው የሚለውን መርህ ነው የምንከተለው። እኛ የአገር ሉዓላዊነት ከሁሉም ይበልጣል የሚለውን ነው የምናስቀድመው። ከዚህ በተቃራኒው የቆሙና ለፓርቲያቸው ጥቅምና ስኬት ብቻ የሚሠሩ ኃይሎች ደግሞ መኖራቸው እሙን ነው። ከዚህ ሌላ ሁሉም በየብሄሩ እንዲደራጅ እና ኢትዮጵያውያን አንድ እንዳይሆኑ የሚሠሩ ኃይሎች አሉ።
በእርግጥ ሁሉም አንድ ነው ማለት እንዳልሆነ አስቀድሜ የጠቅስኩት ጉዳይ። ለአገር አንድነትና ለአገር ጥቅም አጥብቀው የሚሠሩ አሉ። ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ግብረኃይል የሚባል ዲሲ አካባቢ አለ። ይህ ግብረኃይል ከድሮ ጀምሮ ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚጮህ ኃይል ነው። እስከዛሬም ድረስ በመሥራት ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያን የተመለከተ ነገር ሲመጣ ትክክለኛውን በመግለጽ ረገድ ሰልፍ ከመውጣት በዘለለ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተቻለውን ሁሉ በማዋጣት የበኩል የሚያደርግ ግብረኃይል ነው። ከህዳሴ ግድብ በተጨማሪ ገበታ ለአገር በሚል በተነደፈውና ወደሥራ ለገባው ለኮይሻ፣ ለጎርጎራና ለወንጪ ፕሮጀክቶችም ጭምር ነው የሚያዋጣው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በአገር ቤት ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የቻለውን ያህል ይለግሳል። እኛም ወደኢትዮጵያ ስንመጣ ለተፈናቃዮች ይውል ዘንድ የበኩላቸውን ድጋፍ አድርገዋል። በመሆኑም ነው እጅግ በጣም አገር ወዳድ የሆነ ኃይል በርካታ ነው ብዬ ለመናገር የምደፍረው።
ነገር ግን በተቃራኒው የቆሙ ጥቂቶች፣ ጫጫታቸው በርካታ ነውና የሌሎች መልካም አሳቢዎችን አመለካከት በማዛባት የተሳሳተ መረጃ እንዲይዙ በማድረግ ነው ጠንከረው የሚሠሩት። እንዲያም ሆኖ ግን አብላጫው ዳያስፖራ የቆመው ከኢትዮጵያና ከህዝቦቿ ጎን ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥት ጦሩን ወደኢትዮጵያ ያስገባ የሚል ጥያቄ ከዳያስፖራው ቀርቦልናል በሚል ከወደአሜሪካ መረጃ ተሰምቶ ነበር፤ እውን ይህን ጥያቄ ያቀረበው ዳያስፖራው ነው?
አቶ ዳዊት፡-ይህን ያሉት የአሜሪካ ሴናተር ናቸው። በእርግጥ ዳያስፖራ ነው ላንል እንችላለን፤ የአሸባሪ ህወሓት ኃይሎች ናቸው። በእነሱ የተገዙ ሲኤንኤን እና ቢቢሲ ሙሉ በሙሉ ለእነርሱ የሚሠሩ የሚዲያ ተቋማት ናቸው ማለት ይቻላል። በመሆኑም ነው በእነርሱ ተደግፈው የተለያየ መረጃ በማግኘት ነው እኚህ ሴትዮ ጉዳዩን ያቀረቡት። ይሁንና እሱም ገና ውሳኔ ላይ ያልደረሰ ነው። መንግሥትም አልተቀበለውም፤ እኛ ግን ሉዓላዊነታችንን የሚዳፈር ነገር ተቀባይነት እንደሌለው ዳያስፖራው ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጎ ለመንግሥት ስቴት ዲፓርትመንትም ሆነ ለኋይት ሃውስም ይህንን ሐሳብ አቅርበናል።
ዋናው ነገር የአሜሪካ መምጣት ወይም ጦር የመላክና ያለመላክ ጉዳይ አይደለም። የኢትዮጵያውያን መጠናከር ነው። አባቶቻችን ወደዓደዋ ጦርነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሆ! ብለው እንደሄዱ ሁሉ ኢትዮጵያውያን አምርረው ለህዝባዊ ንቅናቄ መነሳት አለባቸው። ለውጭው ኃይል ይህን አብሮነታቸውን መግለጽ ያሻል። ኢትዮጵያውያን በሌላው የሚደርስባቸውን ጫና እና ተጽዕኖ በቃኝ ካሉና አንድ ከሆኑ ምንም የሚያዳግታቸው ነገር አይኖርም።
እነሱ ያሻቸውን ማለት ይችላሉ፤ አሜሪካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሩ ጦሯን ይዛ የገባችባቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ የሆኑ በርካታ አገሮችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ሲሪያ፣ አፍጋኒስታን እና ሌሎችም ሲሆኑ፣ ገሚሱ እንዳልነበር ሆኗል፤ ገሚሱም ሲንገታገት ይታያል። አሜሪካኖቹ ይህን ሲያደርጉ ጥቅማቸውን አስጠብቀው ለማስቀጠል ነው።
ኢትዮጵያ ገናና እና ኃይል አገር ሆናለች። የህዳሴ ግድቡ ተጠናቆና ህዝቡ ተጠናክሮ ሠርቶ ከድህነት አረንቋ ከወጣ አሜሪካ ከሚባለው ዜጋ ቢበልጥ እንጂ በአንዳች አያንስም። እኔ በፈረንጅ አገር አሜሪካም ሆነ አውስትሪያሊያና ሌሎችም ቦታዎች ከሃያ ዓመት በላይ ኖሬያለሁ። እነዚህ ፈረንጆች ከኢትዮጵያውያን ጋር ሳስተያያቸው ኢትዮጵያውያን የሚያስገርም ማንነት ያላቸው ናቸው። ይህንን አስገራሚ ማንነቱን ለሰላማዊ ነገር ሁሉ ማዋል ቢችል አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ኃያል የማትሆንበት ምክንያት አይኖርም። ይህን ማንነት በመያዝ ለአገር ክብርና ለአገር ህልውና ብንሠራ እጅግ በጣም ተፈሪ እና ተከባሪ አገር መሆን እንችላለን።
አሜሪካ አንድ ነገር ስትል ወይም ስትሠራ ‹‹አሜሪካ ምን አለች›› ለማለት የሚቀድመን የለም። በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ምን አገባን። አሜሪካ እኮ መሥራት የምትፈልገውን ነገር ስትሠራ ሜክሲኮ ምን አለች፤ ጀርመን ምን አለች አትልም። ዝም ብላ መሥራት የምትፈልገውን ነገር ነው የምትሠራው። እኛም እዚህ ደረጃ ላይ ነው መድረስ የሚጠበቅብን። ስለዚህም እኛ አምርረን በመሥራት በውጭም በአገር ውስጥም ያለን ሰዎች ለአገራችን የሚበጀውን ለማድረግና ለመሥራት ዝግጁዎች መሆን አለብን።
ኃያላን ነን የሚሉት እኛን የሚንቁን ከፋፍለናቸዋል በሚል ነው። ምክንያቱም አንዱ አካባቢ የእንትን ብሄር ነፃ አውጪ፣ ሌላኛው አካባቢ ደግሞ የእነእንትና ብሄር ነፃ አውጪ በሚል ሰው እርስ በእርሱ ጎራ ለያይቶ ከፋፍሏል። በውጭ አገር ያሉ ውስን የሆኑ አካላት ኢትዮጵያ ያለውን አካል በዚህ በዚህ ስለተደራጃችሁ በሚል የተለያዩ ፈንዶችን በመልቀቅ ኢትዮጵያን ወዳልተገባ ሁከት ውስጥ ለመክተት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላሉ። በቅርቡ እንኳ ኢትዮጵያ ህግ ወደማስከበሩ ዘመቻ ስትገባ ነው ጎረቤት አገር ሱዳን ወደኢትዮጵያ መጥታ የኢትዮጵያን ድንበር ለመድፈር የተነሳሳችው።
ኢትዮጵያ፣ በአንድ ቀን ውስጥ ሱዳንን ማስወጣት አቅቷት አይደለም። ነገር ግን በወቅቱ የነበረው ወከባ ሆን ተብሎ የተደረገ በመሆኑ ተጨማሪ ጦርነት መክፈቱ ለአገር ሰላምም ሆነ ኢኮኖሚ አግባብነት የሌለው መሆኑ ተመዝኖ ነው። መንግሥታችንም ጉዳዩን የያዘው በጥበብ በመሆኑ ነው። ይህን የመንግሥትን አካሄድ ደግሞ ህዝቡ በአግባቡ መረዳት መቻል አለበት። ህዝቡ ‹ዋይ› እና ‹ኤክስ› የተባሉ አካላት በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ እጁን መስጠት የለበትም።
ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ይበጁኛል፤ ያገለግሉኛል ብሎ መሪዎቹን እንደመረጠ ሁሉ፤ውሸታሞቹን ደግሞ እንዲሁ ማሳፈርና ማጋለጥ እንዲሁም የእነርሱን ቅራቅንቦ ወሬ መዝጋት አለበት። ይህ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ እንደምንፈልጋት ዓይነት ኃያል አገር መሆን ትችላለች። አሁን በተለያየ መስክ የተለያዩ ሥራዎችን ጀምረናል። የወደቡም ጉዳይ በመልካም ሁኔታ ላይ እየሄደ የሚገኝ ነው። ግድቡም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። አልፎ ተርፎ ደግሞ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚያደርጉት ትብብር እንዲሁ ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ ታላቅ አገር መሆን ብዙም የሚከብድ ነገር አይደለም። እኛም እንደ ዳያስፖራ የሰላም ጓድነታችን ሆኖ ማየት የምፈልገውና እንዲሆን የምንሠራው ይህንኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ የማሳደሯ ምስጢር ንቀት ወይስ ፍራቻ ነው ይላሉ?
አቶ ዳዊት፡-ንቀት አይደለም። ንቀት አለመሆኑን አንድ ማሳያ ልንገርሽ፤ አሜሪካ የኢትዮጵያን ህዝብ አገር ወዳድነት ጠንቅቃ ታውቃለች ማለት እችላለሁ። አርበኝነቷን ጭምር እንዲሁ። በአሜሪካ አገር ራሱ አንድ የሥራ ማስታወቂያ ሲወጣ ከተመዘገቡ ሌሎች አገር ዜጎች ይልቅ ቅድሚውያን የሚያገኙት ኢትዮጵያውያኑ ናቸው። ይህ የሚሆነው ኢትዮጵያን በመናቃቸው አይደለም። በመሥራታቸው ነው።
የአሜሪካውያኑ ተጽዕኖ ተያያዥነቱ በአብዛኛው ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ታላቅ ግድብ የተነሳ ታላቅነቷ እየጎላ ከመጣ እና አንገቷንም ማቃናት ከጀመረች አስቸጋሪ ነው በሚል ምክንያት ይመስለኛል ይህ ሁሉ ጫና መፈጠሩት። ከድህነት መላቀቅ ለጥላቻም ሆነ ለንቀት አይዳርገንም። ለማንም ታዛዥ ልንሆንም አንችልም።
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ያህል በአገራችን የነበረው መንግሥት የአሜሪካ ታዛዥና የሚሉትን ለማድረግ የሚፈጥን ነበር። ህወሓት የፈለገውን ወንጀል ሲፈጽምና እኛም እንደለመድነው ይህ ወንጀል በአገር ውስጥ አይከናወን እያልን ሰላማዊ ሰልፍ በወጣንባቸው ጊዜያት እነሱን በሚኮንን መልኩ አንድም አርቲክል አይጻፍም ነበር። ምክንያት ቢባል ለእነርሱ የሚታዘዝ መንግሥት ስለሆነ ነበር። አሁን ግን ኢትዮጵያ የሚል መንግሥት መጣ። ይህን ለመቀበል የተመቻቸው አይመስልም። ይህ አርበኝነት እየተጠናከረ ከሄደ ወደ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ዘልቆ ይገባል። ከዚህም በኋላ ኢትዮጵያን ሊጎዳ የሚችል አጀንዳ ቢመጣ አለመቀበልና አይሆንም ልንል ነው የሚገባን፤ እኛ ይህን ማድረግ ነው የሚገባን።
አዲስ ዘመን፡- የዳያስፖራው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ያለውን ትክክለኛ ነገር እና ስለኢትዮጵያ ትክክለኛ መረጃ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እንዲኖረው በቀጣይ ምን ለማድረግ ተሳቧል?
አቶ ዳዊት፡- በጣም ትልቅ ሥራ ይጠበቅብናል። አንደኛ እነሱ ማለትም የኢትዮጵያን በጎ ነገር የማይፈልጉ አካላት በፕሮፓጋንዳውም ሆነ በመረጃው ገስግሰዋል። መንግሥትንም ሆነ ዳያስፖራውን የቀደሙ ናቸው። እኛ ደግሞ የራሳችንን ኔትዎርክ መዘርጋት አለብን። ይህንንም ጀምረናል። የተለያዩ ቡድኖችንም አዋቅረናል። እነዚህ የተዋቀሩ ቡድኖች በተቀናበረ መልኩ መረጃ እየተለዋወጡ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችንም ወደሚመለከተው እያደረሱ ያለውን እውነታ ለመግለጽ ዝግጁዎች ነን።
ከዚህ ጎን ለጎን በዲፕሎማሲው ጉዳይ ከፍ ያለ ሥራ መሠራት አለበት። በዘርፉ ያሉ አካላትም በብቃት ሊንቀሳቀሱ ይገባል። የአገር ውስጡንም ሆነ የውጭውን ሁኔታ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሊሆኑ ይገባል ባይ ነኝ። የመንግሥት ሠራተኛ ብቻ ሆኖ በተለያየ የመንግሥት መስሪያ ቤት የሥራ ሁሉ ዲፕሎማት ሊሆን አይችልም። የራሱ የሆነ መስፈርትና መለያ መንገድ ሊኖረው ይገባል። የእነርሱ በብቃት መሥራት ዳያስፖራውንም በሚፈልገው ልክ ሥራውን መሥራት እንዲችል ያደርጉታል። ደግሞም መዋቅራችንን እየዘረጋን ነው። በጥቅሉ ግን በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉትን በመከታተል የተቀናጀ ፕሮጀክት በመዘርጋት የአገራችንን ገጽታ ከፍ ሊያደርግ የሚችል ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅተናል ነው ማለት የምሻው።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ መረጃ ከልብ አመሰግናለሁ?
አቶ ዳዊት፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2013