እንደ መነሻ ከሃያ ዓመታት በፊት ስለነበረው የአገራችን እግር ኳስ የሚያወጉ ሰዎች አሁን ላይ ኳሱ እንደወደቀና ላዩ ላይ የሚፈሰውን ገንዘብ እንደበዛ ይናገራሉ። ከሃያ ዓመታት በፊት የአንድ ተጫዋች ትልቁ ደመወዝ ቀይ ወጥ መብላትና ሻወር መውሰድ እንደነበር ታሪክ ሰንዶታል። ዘመነኛው እግር ኳስ ከየትኛውም መስክ በበለጠ በወር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ የሚታፈስበት ሆኖ እንዳረፈው በቁጭት የሚናገሩ ተቆርቋሪዎች ጥቂት አይደሉም። ይህ ቁጭታቸው ግን በተጫዋቾች ዘንድ ከቅናት የመነጨ ተደርጎ ሲቆጠር ይታያል። የቁጭታቸው እውነታ ግን እግር ኳሱ ላይ አንድ ነገር ጠብ ሳይል እንዲሁ በከንቱ ወጪው ጣሪያ በመንካቱ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያጠናክሩትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች በተለይም የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊዎች የሚያወጡት ገንዘብ ቅጥ ያጣ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የተጫዋቾች ደመወዝ ዓመታዊ ወጪ መጠን በሚያስደነግጥ መልኩ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱ ለማንም የተደበቀ አይደለም።
ማሳያ
የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የ2010 የሂሳብ ሪፖርት አንድ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። ኢትዮጵያ ቡና ለተጫዋቾች የሚያወጣው የገንዘብ መጠን በአራት ዓመት ልዩነት ውስጥ ከብር 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ወደ 30 ነጥብ 244 ሚሊዮን ብር ንሯል። ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና ዓመታዊ በጀቱን መሙላት ዳገት እየሆነበት መምጣቱን በይፋ ማሳወቅ ከጀመረም ሰንብቷል። የገንዘብ ጉዳይ አሳስቦት የማያውቀው ቅዱስ ጊዮርጊስም ቢሆን ገቢና ወጪው እኩል መራመድ እየተሳነው ኪሱ እየሳሳ ስለመምጣቱ የአደባባይ ወሬ ከሆነ ቆይቷል።
ከፍተኛ የደጋፊ መሰረት ያላቸው ሁለቱ የአገራችን ታላላቅ ክለቦች ለአብነት ያህል ተነሱ እንጂ ጣሪያ የነካ የደመወዝ ክፍያ በመፈፀም የሚታወቁት በርካታ ናቸው። በውድድር ዓመቱ ከአንድ እስከ አስር ባለው ደረጃ ውስጥ የተቀመጡ የከተማ ክለቦች የፋይናንስ ከፍታው ሰለባ እንደሚሆኑም ጥርጥር የለውም።
የወጪ ዕድገቱ በዚሁ ከቀጠለ በርከት ያሉት ክለቦች በውድድሩ ላይ የመቆየት ዕድላቸው አደጋ ውስጥ እንደሚገባ ከወዲሁ ምልክቶች እየታዩ ነው። በየዓመቱ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ የተጫዋቾች ክፍያና አጠቃላይ የበጀት ጫና ምክንያት አደጋ ውስጥ የገቡ ክለቦች ቁጥር አንድና ሁለት እንደማይሆን ግልፅ ነው። መንግሥት ለእግር ኳሱ የሚመድበው በጀትና የተጫዋቾች ክፍያ ነባራዊውን የአገር ኢኮኖሚ ያላገናዘበ፣ የክለቦች የፋይናንስ ስርዓት የሌለበት፤ ዘመናዊ የእግር ኳስ አመራርና አደረጃጀት የሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ግን ሊጉ ቀጥሏል። ብዙዎቹ ክለቦች ቋሚ ገቢ የሌላቸው ሲሆኑ ከከተማ አስተዳደሮችና በመንግሥት ተቋማት በቀጥታ በጀት የሚመደብላቸው ናቸው። የተጫዋቾች ዝውውርና ሌሎች ክፍያዎቻቸውም ከዚሁ በጀት ላይ የሚታሰብ ሲሆን የሊጉ ተወዳዳሪዎች በየዓመቱ ከ30 እስከ 80 ሚሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
የተጫዋቾች የዝውውር ገንዘብ በየዓመቱ እየናረና እያደገ መምጣቱን ተከትሎም በአማካኝ ከ50 እስከ 100 ሺ ብር ወርሃዊ ደመወዝ ከአንዱ ክለብ ወደ ሌላኛው እየተዘዋወሩ ይገኛሉ። ዘንድሮ እንኳን በተጫዋቾች የዝውውር መስኮቱ አማካኝ ገንዘብ 100 ሺ ብር ሲሆን አነስተኛው 25 ሺ ብር ነው። አንድ ክለብ በዓመቱ በሚያስፈርማቸውና ውላቸውን የሚያድስላቸው የውጭና የአገር ውስጥ ተጫዋቾች ከአስር እስከ አስራ ሁለት ቢገመቱ፤ ሃያ ሚሊዮን ብር በተጫዋቾች ዝውውር ብቻ እንደሚያወጣ መገንዘብ ይቻላል። ይህም ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ፈተና የአብዛኛዎቹን ክለቦች እንዲሁም የፕሪሚየር ሊጉን ግብዓተ መሬት እያፋጠነው ይገኛል።
የተደቀነው አደጋ
ትናንት እንደ ቀላል በመቶ ሺዎች ለተጫዋቾች ደመወዝ ከፋይ የነበሩና ለገበያው ጣሪያ መንካት ዋና ተዋናይ የሆኑት ክለቦች ዛሬ ላይ ካዝናቸው ተራቁቷል። ለወሳኝ ተጫዋቾቻቸው በጊዜው የሚከፍሉት አጥተው ከዋክብቶቻቸው የተሻለ አቅም ወዳለው ክለብ ሲኮበልሉ እጃቸውን አጣጥፈው መመልከት ዕጣ ፋንታቸው ሆኗል። ለዚህ ደግሞ ከዓመትና ሁለት ዓመት በፊት ከፍተኛውን የተጫዋቾች ደመወዝ ከፋይ ከነበረው ከደደቢት የበለጠ ማሳያ የለም።
ደደቢት በዚህ ማዕበል ክፉኛ ከተመታ ወዲህ መቀመጫውን ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ ቀይሯል። ከፍተኛውን የተጫዋቾች የደመወዝ ጣሪያም ሃያ አምስት ሺ ብር ለማድረግ ተገዷል። በዚህም ሳይበቃ የተሻለ ውጤታማ የሆነው የሴቶች ቡድኑን ለማፍረስ ሲወስን ሁለት ጊዜ አላሰበበትም። ትንሽ የተባለውን የደመወዝ ጣሪያም በወቅቱ መክፈል ተስኖት እየተንገዳገደ የወንዶቹም ቡድን እንደ ሴቶቹ ተመሳሳይ ዕጣ ፋንታ ሊገጥመው አንድ ሐሙስ ቀርቶታል። ለዚህም ማሳያው በሊጉ አጋማሽ ላይ የሰበሰበው የአንድ ዕጅ ጣቶችን ቁጥር የማይሞላ ነጥብ ነው። ደደቢት በቀጣዩ ዓመት በሊጉ ለመቆየት ተዓምር መፈጠር ይኖርበታል። በሊጉ መቆየት ካልቻለ ደግሞ የሚመጣውን መዘዝ መገመት ቀላል ነው። ምክንያቱም በአገራችን እግር ኳስ እንኳን በፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የገባ ክለብ ቀርቶ ጠንካራ የፋይናንስ አቅምና ታሪክ ያላቸው ክለቦች ከሊጉ ወርደው ለመውጣት ከመታተር ይልቅ ለመፍረስ ቅርብ ሆነዋል። ለዚህም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሙገር ሁነኛ ማሳያ መሆናቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
የክለቦች ቅጥ ያጣ የገንዘብ አወጣጥ የኋላ ኋላ ራሳቸውን ጠልፎ እንደሚጥላቸው ማሳያ ደደቢት ብቻ አይደለም። የአምናው ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር የዚሁ ችግር ተመሳሳይ ሰለባ ሆኗል። ዋንጫውን ባነሳ ማግስት አሁን እየገጠመው የሚገኘውን የፋይናንስ ቀውስ መመልከት ይቻላል። ጅማ አባ ጅፋር አምና በጉብዝናው ወራት የውጭ ተጫዋቾችን ጭምር ረብጣ ገንዘብ አውጥቶ በመግዛት በሊጉ ማማ ላይ ተቀምጦ እንደነበር አይዘነጋም። ይህም የአንድ ተጫዋች የወር ደመወዝ እንኳን መሸፈን የማይችል የመቶ ሃምሳ ሺ ብር ሽልማት አስገኘለት።
ዘንድሮ ግን በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሙሉ ቡድኑን እንኳን ይዞ ባህር መሻገር ተሳነው። ለአሰልጣኝና ተጫዋቾች ከሁለት ወር በላይ ደመወዝ መክፈል አቅቶትም ውዝግብ ውስጥ እንደሰነበተ ይታወሳል። ቀጣይ ጉዞውም እንደ አምናው ዋንጫ ለመሳም ሳይሆን ላለመውረድ እንደሚሆን አሁን ካለበት ቁመና ተነስቶ መናገር ይቻላል። ሌሎቹም ክለቦች ከዚህ የተለዩ አይደሉም። የወጪ ዕድገት ጣሪያው እንዳደጉት አገራት ሊጎች ክለቦቻችን በነዳጅ ገንዘብ ኪሳቸው ባበጠ የአረብ ባለሀብቶች ካልተደገፈ በስተቀር ቀና ብለው የሚያዩትና ውሉን የሚጨብጡት ዓይነት አይደለም።
የፋይናንስ ከፍታው የፕሪሚየር ሊጉን ክለቦች አንደርድሮ ከገደል አፋፍ ላይ አድርሷቸዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። የገቢ መንገዶች እየቀነሱ ወጪያቸውም ከዚህ በኋላ ይበልጥ እየተመነደገ እንደሚሄድ ከሁኔታዎች ተነስቶ ቢተነበይ ደግሞ ችግሩ ይበልጥ ጥርስ ያወጣ ይመስላል። የፕሪምየር ሊጉ ከከተማ ከተማ ተዟዙሮ የመጫወት መርሐግብር የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች መልክዓምድራዊ አቀማመጥ የተራራቁ ያደርጋቸዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት አንድ የአዲስ አበባ ክለብ ለሊጉ ውድድር አንድም ጊዜ ወደ ትግራይ ክልል አይጓዝም ነበር። ዘንድሮ ግን አራት ጊዜ መጓዝ ግድ ይለዋል። ባለፉት ሦስት የውድድር ዘመናት በየዓመቱ አንዳንድ የአዲስ አበባ ክለቦች ከሊጉ መውጣታቸውን ተከትሎ (አዲስ አበባ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክና ደደቢት) ከአምና እና ከካቻምና ይልቅ የአዲስ አበባ ክለቦች ለበለጠ ጊዜያት ወደ ክልሎች እየተጓዙ ለመጫወት ተገድደዋል።
ክለቦቹ ብዙ በተጓዙ ቁጥር ወጪያቸው እየጨመረ መሄዱን ማስተዋል ይቻላል። በቀጣይ ዓመታትም ፕሪሚየር ሊጉን የሚቀላቀሉ ሦስት አዳዲስ ክለቦች ከየትኛውም ክልልና ከተማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ለብዙሃኑ የክልል ክለቦች ችግሩ ይበልጥ ብርቱ እንዲሆን ያደርገዋል።
እነዚህ ክለቦች የህዝብ ሀብት የሚፈስባቸው እንደመሆናቸው «ሚሊየኖችን ዘርተው ምን አጨዱ?» ብለን ብንጠይቅ መልሱ በቀላሉ ምንም ይሆናል። አሳዛኙ ነገር በእግር ኳሱ ይህን ያህል ገንዘብ እየተረጨ ከፋይናንስ ዕድገቱ ጋር ኳሱ አብሮ መራመድ ይቅርና በግማሽ መንገድ እንኳን ሊከተለው አቅሙ አለመፍቀዱ ነው።
ከአስር ጨዋታ ዘጠኙ አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት በሚጠናቀቅበት አሰልቺ ሊግ ሆኗል። የስፖርት ቤተሰቡ ለመዝናናት ካምቦሎጆ ገብቶ ፀያፍ ስድብ ሰምቶ ከመመለስ የዘለለ ያገኘው ነገር የለም። ይህ ሁሉ የገንዘብ ክምር ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ አገራት ከአስራ ስድስት ወደ ሃያ አራት አድጎ እንኳን ተወዳጁ መድረክ ጋር ሊያደርሰው የሚችል አቅም አልፈጠረለትም። የዘወትር ጩኸት ለሆነው የታዳጊ ወጣቶችና ተተኪዎች ላይ ገንዘቡ ባክኖም ቢሆን እሰየው ነበር። ከእነዚህ ሁሉ አንዱ እንኳን ተሳክቶ ቢሆን የስፖርት ቤተሰቡ አሜን ብሎ በተቀበለም ነበር።
ምክረ ሃሳብ
ገቢያቸው ከወጪያቸው በእጅጉ የላቀ በሆነበት የአውሮፓ አገራት ሊጎች ውስጥ አንድ ክለብ ገንዘብ ስላለው ብቻ የፈለገውን መዥረጥ አድርጎ አውጥቶ ያሻውን ተጫዋች ሊገዛ አይችልም። እነርሱ የፈረጠመ የገንዘብ አቅም ያላቸውን ለመቆጣጠርና ጤናማ የገበያ ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል (financial fair play)የሚሉት ጠንካራ ህግ አላቸው። ይህ አሠራር ከእኛ ሀገር ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ ተግባራዊ ቢደረግ ችግሩን ለመቆጣጠር ያስችላል። ከድሃ አገርና ህዝብ የሚገኝ ገንዘብ የጀርባ አጥንቱ ለሆነው የአገራችን እግር ኳስ ግን የፋይናንስ ስርዓትን ለመቆጣጠር የሚያስችል በልካችን የተሰፋ ጠንካራ የህግ አንቀፅ ማስቀመጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። መንግሥት ፊፋን በማያስቆጣ መልኩ ለዚህ ችግር መፍትሔ ካላበጀ እንዲህ በቀላሉ እግር ኳሱን መታደግ የሚቻል ባለመሆኑ መፍትሔው ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል። ከዚህ ጎን ለጎን እግር ኳሱን አንቆ የያዘው የወሮበላ ቡድኖች ሰንሰለት እስካልተበጠሰ ድረስ የቱንም ያህል የእግር ኳስ አመራር ቢቀያየር ለውጥ እንደማይመጣ ማረጋገጥ ይቻላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ቦጋለ አበበ