አሸባሪው ህወሓት አሁን አሁን ጭንቅ ጥብብ ብሎታል:: ነፍሱን ለማዳን ሲልም በተንፈራገጠ ቁጥር እያበላሻቸው ያሉ ነገሮች በርክተዋል:: ከእነዚህም መካከል ልትወጣ የደረሰች ነፍሱን እስትንፋስ ሆነው እንዲታደጉለት ወደጦርነቱ የሚማግዳቸው ህጻናት ግንባር ቀደም ተጠቃሾቹ ናቸው:: ከቀናት በፊት ደግሞ ብቻዬን አልሞትም በሚል ያፈሳሰው የንጹሃን ደም ሌላው ማሳያ ነው:: አገር ለማፍረስ የያዘውን አጀንዳ ለመተግበር ከበስተጀርባው ያሻውን ያህል የውጭ ኃይል ያሰለፈ ቢመስለው የንጹሃንን ደም እያፈሳሰ እንዳይቀጥል ግን የኢትዮጵያዊያኑ ትብብርና ህብረት የሚጠበቅ ነው:: በዚህ ሂደትም የየክልሎቹ ልዩ ኃይሎች አገርን የማዳን ጥሪ ተቀብለው በጋራ ተሰልፈዋል::
አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ልዩ ኃይሎቻቸውን ከላኩ ክልሎች መካከል ደግሞ የጋምቤላ ክልል አንዱ ነው:: እኛ በዛሬው የአዲስ ዘመን ወቅታዊ ጉዳያችን አሁን ላይ በጋምቤላ ክልል እና በድንበር አካባቢ ስላለው ሰላም ሁኔታ፤ እንዲሁም ከክልሉ ወደአገር የማዳኑ ጥሪ ስለተጓዙት ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ አዲስ ዘመን የጋምቤላ ክልል የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶማስ ቱት ፑክ ጋር አጭር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አሰናድቶታል:: መልካም ንባብ ይሁንልዎ::
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ክልል ያለው የሰላሙ ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ቶማስ፡– በእስካሁኑ ሂደት የጋምቤላ ክልል የሰላም ሁኔታ ደህና የሚባል አይነት ነው:: አንዳንድ የተለመደ አይነት የከተማ ውስጥ ሌብነትና ጥቃቅን የሆነ ንጥቂያ ካልሆነ በስተቀር ክልሉ ሰላም የሚባል ነው:: በድንበሮች አካባቢም ችግር የለም:: በክልላችን የዚያን ያህል የከፋ ችግር የለም::
አንዳንዶች ብዙ ሊያስቡ ይችላሉ:: በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል ችግር ያለ ሊመስላቸውም ይችላል:: ነገር ግን በእኛ ክልል የሰላሙ ሂደት በተረጋጋ መንፈስ የቀጠለ ሲሆን፣ እንደሁልጊዜውም የጸጥታው ኃይል የሚጠበቅበትን ፀረሰላም ኃይሎችን የመከላከል ተግባሩን በንቃት እየተወጣ ይገኛል:: እስካሁን የተፈጠረ አንዳችም ችግር የለም::
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የሽብርተኛው ህወሓት ሰርጎ ገብ እንዳይኖርና የተለመደ እኩይ ተግባሩን እንዳይፈጽም በምን አግባብ ነው እየተሰራ ያለው?
አቶ ቶማስ፡– ክልላችን ከሌሎች ክልሎችም ሆነ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋስን ድንበር ላይ ያለ ነው:: በመሆኑም የህወሓት ሰርጎ ገብ አለ ብለን በእርግጠኝነት ባንናገርም፤ ቀድመው ያልነበሩ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች ከሰሞኑን መታየታቸውን ደርሰንበታል::
በእኛ በኩል እነዚህ አካላት ከሌላ አካባቢ በመሸሽ ወደጋምቤላ የመጡ ናቸው የሚል ጥርጣሬ ነው ያለን:: እነዚህን ሰዎች ዋንታዋ በምትባል አካባቢ ያገኘናቸው ሲሆኑ፣ ሰዎቹ የመከላከያ ልብስ የለበሱ ወታደሮች ናቸው:: እነሱም ትግርኛ ተናጋሪዎች በመሆናቸው ወደጋምቤላ ፈርተውና ራሳቸውን ደብቀው መምጣታቸውን ነው የተናገሩት:: ሆኖም ሰዎቹን የያዝናቸው ሲሆን፣ የተናገሩት ነገር እውነት ስለመሆኑም ማጣራት እያደረግን ነው::
እነዚህን ሰዎች ከያዝናቸው ሳምንት ያህል እድሜ አስቆጥሯል:: በቁጥርም ወደ ስድስት ናቸው:: ከእነዚህ ሌላ ስለመኖር አለመኖራቸውንም የማጣራት ስራ በመስራት ላይ ነንና ቁጥራቸው ከዚህም ከፍ ሊል ይችላል የሚል እምነት አለን::
አዲስ ዘመን፡- ሰዎቹ በእርግጥ መካላከያ ውስጥ የነበሩና ከድተው የመጡ ናቸው ወይስ ሌላ ተልዕኮ ያላቸው ናቸው ይሆን?
አቶ ቶማስ፡- መከላከያ ውስጥ የነበሩ ናቸው:: ራሳቸው ሸሽተው ነው ወደጋምቤላ የመጡት:: መንግስት የህግ እርምጃ ሲወስድ ነው የመጡት:: ከእነሱ መሀል አንደኛው ደቡብ ሱዳን ለመሄድ በመሞከር ላይ እያለ ነው የተመለሰው:: ወደ ደቡብ ሱዳንም ለመሄድ ወስነው የነበረው ከአንድ ባለሀብት ጋር ሲሆን፣ ሁሉም ግን ጉዟቸውን ወደ ደቡብ ሱዳን አድርገው በዛው የማምለጥ ፍላጎት ነው ያላቸው::
አዲስ ዘመን፡- ምናልባት ወደጋምቤላ የመምጣታቸው ምስጢር ወደ ደቡብ ሱዳን ለማለፍ ስለሚቀላቸውና በዛው ወደፈለጉት አገር ለመሻገር ብለው ወይስ ሌላ ተልዕኮ ይኖራቸው ይሆን?
አቶ ቶማስ፡– እሱ ገና በውል ያልታወቀ ጉዳይ ነው:: የእኛ ጥርጣሬ ግን በዚሁ ወደ ደቡብ ሱዳን ለመሻገር ነው ወደ ጋምቤላ የመጡት የሚል ነው::
አዲስ ዘመን፡- ድንበር አካባቢ ሰርጎ ገብ ችግር እንዳይፈጠር ያለውን ሰላም በማስጠበቁ በኩል ከሚሰራው ስራ በተጓዳኝ፤ አሸባሪው ቡድን የሚያሰማራቸው ሌሎች ተላላኪዎችን ተግባርና እንቅስቃሴ ተከታትሎ ከማረም አኳያ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ቶማስ፡– ድንበር አካባቢ በአሁኑ ወቅት የተለየ ችግር የለም፤ በእስካሁኑ ሂደት ሰላም ነው:: በአሁኑ ወቅት ክረምት እንደመሆኑ ያሉት የባሮ፣ ጊሎ፣ አኮቦና አልዌሮ ወንዞች ሞልተዋል:: ስለዚህም የሙርሌ እንቅስቃሴ በወንዙም መሙላት የተነሳ የተገታ ነው ማለት ይቻላል:: ከእነዚህ ውጭ ያሉት በጣም ውስን መንገዶች በመሆናቸው የሰዎች እንቅስቃሴ እንደ በጋው ቀላል አይሆንም:: በመሆኑም በደቡብ ሱዳን በኩል ያለው የድንበር ሁኔታ በአሁን ሰዓት ብዙም የሚያሰጋ ነገር የለውም:: ነገር ግን ይነስም ይብዛ በአሁን ወቅት ያለው ስጋት በኦሮሚያ ቄለም ወለጋ አንፊሎ ወረዳ በኩል የሚያዋስነው ቦታ ነው:: በዛ አካባቢ ከሽብርተኛው ሸኔ ጋር ተያይዞ የሽፍቶች እንቅሳቃሴ አለ::
በቅርቡ ግን እንደ አንድ ችግር ሊወሰድ የሚችለው የጋምቤላ ክልል ተወላጅ የሆነ፤ የጋምቤላ ህዝቦች ፍትህ ለሰላምና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ ፓርቲ (ጋህሰልዴን) አመራር የነበረ ግለሰብ በማህበራዊ ትስስር ገጹ የጦርነት አይነት ጥሪ ማድረጉ ሲሆን፣ በእርግጥም ይህም ቢሆን ብዙም ችግር የሚፈጥር ነው የሚል እምነቱ የለንም:: ግለሰቡ፣ ሰኔ 14 በተካሄደው ስድሰተኛ አገራዊ ምርጫ ላይ ለውድድር የቀረበ ነው:: ይሁንና በተወዳደረበት ቦታ ሌሎቹን ፓርቲዎች በማሸነፍ ማለፍ ባለመቻሉ ፓርቲው እንደማያወጣው በማመን ከድርጅቱ ወጥቷል:: ይህድርጅት ደግሞ ቀደም ሲልም የህወሓት ክንፍ እንደሆነ የሚታወቅ ነው:: በወቅቱ አሳዳጊ አባቱ ወደሆነው ወደ ጁንታው ቡድን እስከመቀሌ ድረስ በመዝለቅ ድጋፍ ለማግኘት ይጥር ነበር:: በጊዜው የገንዘብ ድጋፍም ከጁንታው ይደረግለት ነበር::
ይህ ከጁንታው ጋር የነበረው አካሄድ በመቋረጡ እንደማንኛውም ድርጅት ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲወዳደር ተደረገ:: ከጁንታው ጋር የፌዴራሊስት ኃይሎች በሚል ግንኙነት ፈጥሮ ወደመቀሌ መለስ ቀለስ ሲልም ነበር:: በወቅቱ ጁንታው የመከላከያ ኃይሉ ላይ ባደረሰው እኩይ ተግባር ተከትሎ የፌዴራል መንግስት በጥቅምት ወር ህግ የማስከበር እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል:: ይህን ተከትሎ ይህ ድርጅት ሁሉን ትቶ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ:: ወደ ሰላማዊ መስመር በመግባቱም እንደ የትኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ አስፈላጊውን መስፈርት ሁሉ በማሟላቱ ያለምንም ችግር በሰላማዊ መንገድ ለውድድር የበቃ ቢሆንም፤ ለማሸነፍ ባለመታደሉ ወድቋል:: በወቅቱም የፓርቲው አባላት ውጤታቸውን የተቀበሉት በአወንታዊ መልኩ ነው::
የምርጫውን ውጤት ካወቁ በኋላ የፓርቲው ጸሐፊ የእኔ የሚለውን ሐሳብ አመነጨ:: አሁን ተወዳድሮ በወደቀው ፓርቲ ስም ወደ ጁንታው ቢሄድ እንደማይቀበለውም አወቀ፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያ በተካሄደው ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ ላይ ተሳትፏል:: ስለዚህም በመጀመሪያ ካለበት ፓርቲ ወጥቻለሁ በሚል ይፋ አደረገ:: ቀጥሎም ህጋዊ ሰውነት ያላገኘ ሌላ ድርጅት መሰረተ:: የመሰረተው ድርጅት ስምም የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) የሚል ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ የእኔ ስያሜ ይህ ነው ሲል አወጀ::
በዚህ ብቻም አላበቃም፤ ለጋምቤላ ህዝብ ነፃነትና ፍትህ ለማስገኘት የትግል ስልታችንን ወደ ትጥቅ ትግል ማሸጋገር የግድ ሆኗል ሲል በአደባባይ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ለጠፈ:: የትጥቅ ትግል መስመር ለመከተል ተገድጃለሁ ብሎ ሌላ ስም አውጥቶ ቢንቀሳቀስም፤ ህጋዊ ያልሆነ ስምና ይሁንታን ያላገኘ መሆኑ ግልጽ ነው:: ይህ አዲስ ድርጅት ከተቋቋመ ገና አንድ ወሩ ነው::
ይህን አዲስ ማንነቱን ተከትሉ የክልሉን ወጣቶች ለማሰባሰብ የተለያዩ ጥረቶችን እና ጥሪዎችን እያካሄደ ነው:: ለራሳችሁ መብትና እኩልነት ከሌሎች በትጥቅ ትግል ላይ ካሉ ብሔር ብሄረሰቦች ጋር በመሆን የጋራ ጠላታችን የሆነውን የብልጽግና መንግሥት ለማስወገድ ወደ ትጥቅ ትግል እንድትቀላቀሉ በሚል ነው በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ወጣቱን ወደ ትግል በመጋበዝ ላይ የሚገኘው። ይሁንና ምንም እንኳ ይህን እያለ አንድ ወር ያህል ቢያስቆጥርም በቂ ኃይል ማግኘት አልቻለም::
በክልላችን ያሉ ወጣቶች በፊት የጋምቤላ ህዝቦች ፍትህ ለሰላምና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ በሚል ስም የሚጠራው ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል በመሆኑ እና በብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ህጋዊ እውቅና ያለው እንደመሆኑ ሲወዳደር ያላቸውን ድጋፍ አልነፈጉትም ነበር:: ይህንንም ሲያደርጉ ነበር:: በአሁን ሰዓት ግን በዚህ መስመር ውስጥ በመግባቱ ሌላ ተጨማሪ የወጣቱን ኃይል ሊያገኝ ይቅርና የራሱ የሆኑት እንኳን ሸሽተውታል:: ለዚህም ምክንያታቸው በሰላማዊ መንገድ መታገል እንጂ በአደባባይ ጦርነት ካወጀ አካል ጋር ግንኙነት እንደማይፈጥሩም ነው የተናገሩት::
ይህ በአደባባይ ጦርነት ያወጀው ግለሰብ፣ ቀደም ሲል በእስር ላይ የነበረና በዋስ ወጥቶ ለውድድር እንዲበቃ የተደረገ የነበረ ነው:: ዛሬም ከጁንታው ጋር አብሬ የኢትዮጵያን መንግስት እዋጋለሁ ብሏል:: በአሁኑ ሰዓት ይህ ግለሰብ ወደኬንያ ወጥቷል:: የዚሁ ግለሰብ ምክትል ደግሞ ያለው በአገረ አሜሪካ ነው:: እኛ በተቻለን ሁሉ ክትትል እያደረግን ከመሆናችን በተጨማሪ እነዚህ አካላት ወጣቱን ኃይል ወዳልተፈለ ድርጊት ውስጥ እንዳያስገቧቸው ግንዛቤ እንዲጨብጡ በማድረግ ላይ ነን::
አዲስ ዘመን፡- በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰላም በማረጋገጥ በኩል በአካባቢው ያለ የታጣቂ ኃይሉ እንቅስቃሴ እንዴት ነው የሚገለጸው?
አቶ ቶማስ፡– እኛ በአሁኑ ሰዓት በቂ ኃይል አለን:: ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ በሚለው መርሃግብር የተወሰኑት እንዲሳተፉ ወደስፍራው የላክናቸው:: ለጊዜው ድንበራችንን የሚጠብቁ ኃይሎች አሉን:: ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ ችግር ቢያጋጥም እንኳ ምንም የሚያሳስበን ነገር የለም:: ምክንያቱም የአገር መከላከያ ሰራዊት በቅርብ ርቀት ላይ ነው ያለው:: ስለዚህም እንደ ክልል የሚያሰጋን አንዳች ነገር የለም ብሎ መናገር ይቻላል::
ከመከላከያ ጋርም ያለን ስምምነት የትኛው በድንበር በኩል ሊያጋጥም የሚችል ችግር ቢኖር በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የመከላያ ኃይል ወዲያውኑ በቦታው እንደሚደርስ ነው፤ ይሁንና እስካሁንም ቢሆን በቀጣይ የከፋ ችግር ያጋጥመናል የሚል ስጋት ስለሌለን አሁንም በክልላችን ኃይል እየታገዝን የክልሉን ሰላም በማስከበር ላይ እንገኛለን::
ጥቃቅን የሆኑ ጉዳዮችን ባለን ኃይልና ሚሊሻዎችን በመጠቀም የሚስተካከል በመሆኑ ምንም ችግር አይኖርም:: በከተሞች አካባቢ ደግሞ የእኛ ክልል እንደሌሎች ክልሎች አይደለም:: እስካሁን ድረስም በቂ የፌዴራል ፖሊሶችም በክልላችን አሉ:: ለአብነት ያህል መጥቀስ ካስፈለገ ከክልሉ ፖሊስ ውጭ ተጨማሪ አድማ በታኝ ፖሊስ አለ:: በጥቅሉ ሊያሰጋ ይችላል ተብሎ በሚታሰብ ቦታ ሁሉ ከእኛ ውጭ የፌዴራል ፖሊስ በበቂ ሁኔታ አለ::
አዲስ ዘመን፡- የህልውና ዘመቻውን በተመለከተ የክልሉ ተነሳሽነት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ቶማስ፡- በክልላችን ያለው ህዝብ ከአገር መከላከያ ጎን ለመቆም ያለው ዝግጁነት በጣም የገዘፈ ነው:: ክልላችን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይም ይገኛል:: ገሚሱ ግንባር ድረስ በመሄድ፣ ሌላው ደግሞ ለመከላከያ ሰራዊት ያለውን ድጋፍ በተለያየ መልክ በመግለጽ አጋርነታቸውን በአግባቡ በማሳየት ላይ ናቸው:: በተለይ ህዝብ ቀለቤ ነው ብሎ ያለውን ሳይሰስት ልክ ለልጁ የሚሰጠውን ያህል ድጋፉን አጠናክሮ ቀጥሏል::
አዲስ ዘመን፡- የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል የሽብርተኛውን የህወሓት እኩይ ተልዕኮ ለማፍረስ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር መሰለፉ ይታወቃል፤ በእስካሁኑ ሂደት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እና ተጨማሪስ ኃይል የሚፈለግ ከሆነ የክልሉ ዝግጁነት ምን ይመስላል?
አቶ ቶማስ፡- እኛ የተሰጠን አቅጣጫ ወደቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አካባቢ እንዲሁም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለበት አካባቢ ጭምር ነው:: ይህንን የምናደርገው በቅርብ ርቀት ካሉት ከደቡብ እና ከሲዳማ ክልል ልዩ ኃይሎች ጋር ሆነን ነው:: በእዛ አካባቢ የተመደቡ ልዩ ኃይሎቻችንም እጅግ በጣም በተቀላጠፈ ሁኔታ ተልዕኳቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ:: በዚህም ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል ባይ ነኝ:: ይህን የምለው በአካባቢው የነበሩ የሽፍቶች እንቅስቃሴ መቀነስ በመቻሉም ጭምር ነው:: ሲካሄድ የነበረው የከብቶች ዝርፊያም እንዲቆም ተደርጓል:: ሌላው ቀርቶ እዛው ቤኒሻንጉል አካባቢ ቀደም ሲል የተወሰዱ ከብቶችን የማስመለስ ስራ መስራት ተችሏል:: በዚህ ስራቸው የክልሉ መንግስትም በእጅጉ ደስተኛ ሆኗል::
የጸጥታ ኃይላችን ይህን የሚያደርገው የጋምቤላ ችግር የኢትዮጵያ ችግር ነው በሚል ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው:: በኢትዮጵያ ውስጥ ችግር የሚኖር ከሆነ እሱ ችግር የጋምቤላም ችግር ነው:: አንድ አካል በመሆናችንም ነው የየበኩላችንን በመወጣት ላይ የምንገኘው:: ስለዚህም ነው በቤኒሻጉል ጉምዝ ያሉ ወታደሮች አካባቢውን ልክ እንደጋምቤላ ክልል በመጠበቅ ላይ ያሉት::
እኛ አሁንም ቢሆን ሌላ ተጨማሪ ኃይል ጨምሩ ከተባልን ለመጨመር ዝግጁዎች ነን:: የኢትዮጵያ ጥሪ ሁላችንም በባለቤትነት የምንሳተፍበት አገራዊ ጥሪ ነው:: ለተወሰኑ ክልሎች ወይም ለተወሰኑ ኃይሎች ብቻ የሚተው ጥሪ አይደለም:: ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሙሉ ሰላማቸውን እስከሚያገኙ ድረስ ተሳትፏችን ቀጣይነቱ የተረጋገጠ ነው:: እኛ በክልላችን ሊያሰጋን የሚችለውን ለመመከት የሚያስችል ኃይል አለ:: በስጋትነት ሊጠቀስ የሚችለው ሙርሌ ሲሆን፣ እሱም ቢሆን ምንም አይነት ችግር እንዳያመጣ የበኩላችንን በመወጣት ላይ እንገኛለን:: ስለዚህ አስቀድመንም በቂ ኃይል ልከናል፤ ተጨማሪ የሚያፈልግ ከሆነ ደግሞ ለመላክ ዝግጁዎች ነን:: ኢትዮጵያ ስትኖር ነው ጋምቤላም ኦሮሞም ሆነ ደቡብና ሌላው መኖር የሚችለው የሚል እምነት አለን:: በመሆኑም ኢትዮጵያ የማዳንና የመታደጉ ጉዳይ የጋራችን ጉዳይ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ሽብርተኛው ህወሓት አገር የማፍረሱን ተልዕኮ አሜሪካንና ምዕራባውያኑን ጨምሮ አንዳንድ ጎረቤት አገሮችንም አካቶ በመታገዝ ነው የሞት ሽረት ትግሉን በመፈጸም ላይ ያለው፤ ይህን ጉዳይ እርስዎ እንዴት ያዩታል?
አቶ ቶማስ፡- አሸባሪው ህወሓት አገር የማፍረሱን ተልዕኮ አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ያለው ብቻውን እንዳልሆነ ይታወቃል:: ይሁንና ኢትዮጵያ አትፈርስም:: ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሙከራ የማድረጉ ሂደት ዛሬ ብቻ አይደለም:: ድሮም ቢሆን ኢትዮጵያን ለማዳከም ያልተደረገ ጥረት የለም:: ይሁንና የትኛውም ኃይል ኢትዮጵያ ሊያንበረክክ አልተቻለውም::
ለአብነት ያህል መጥቀስ የሚያስችሉን ብዙ ድሎች አሉን:: ኢትዮጵያ ከጣሊያ ጋር፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር እያልን መዘርዘር እንችላለን:: እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በሁሉም ግንባር ያስመዘገብነው ሽንፈትን ሳይሆን ድልን ነው:: እነዚህን ድሎች ኢትዮጵያ ማጣጣም የቻለቻቸው የከፈለቻቸው ከባድ መስዋዕትነቶች በመኖራቸው ነው::
ስለዚህ እኔ እንደ አንድ ግለሰብ ሆኜ ሳየው ኢትዮጵያ በአህጉራችን አፍሪካ ውስጥ ካሉ አገሮች ያልተደፈረች አገር መሆኗን ነው:: ትናንት በማንም ያልተደፈረች አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም በማንም ልትደፈር አትችልም:: ከዚህ በኋላ የትኛውም ኃይል አንገቷን ሊያስደፋት አይቻለውም:: ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ትናንት አገራችንን ያላስደፈሩ አባቶቻችን ዘንድ ጀግንነት ዛሬም በእኛ ውስጥ ስላለ ነው::ይህን ጀግንነት ይዘን ደግሞ የሚመጣብን ችግር አይኖርም ባይ ነኝ::
ሱዳንም በግብጽም በይው በሌላ ኃይል ተደግፋ ከኢትዮጵያ በተጻራሪ ጎን ብትቆምም፤ ግብጽም ራሷ ብትመጣ፤ ሽብርተኛው ህወሓትም የአገሩን ክብር ወደጎን ትቶ ከጠላት ጋር ቢያብርም ምንም የሚያመጡት ተጽዕኖ አይኖርም:: በአሜሪካ በኩል እየተደረገብን ያለ ጫና ቢኖርም የሚመጣ ችግር ብዙም አይደለም:: አሜሪካ አንዳንድ ጊዜ የአገራቱ ሁሉ ፊት መሪ እኔ ነኝ፤ ከእግዚአብሄርም ይልቅ የምቀርባችሁ እኔ ነኝ የማለት ነገር ቢኖርባትም የእግዚአብሄርን ያህል አቅም ስለሌላት ምንም አታመጣም:: ስለዚህም ታሪካችንም የሚያሳየን ድል አድራጊነትን በመሆኑ ትግላችንን መቀጠል ነው የሚኖርብን::
የእኛ ክልል ለምሳሌ የሚዋሰነው ከደቡብ ሱዳን ነው:: እኛ አሁን እንደምናስተውለው ከሆነ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ የሚያሰጋ ነገር አለመሆኑን ነው:: እኛ ደቡብ ሱዳንን መዋሰን ብቻ ሳይሆን እነርሱ የሚናገሩትንም ቋንቋ አሳምረን ስለምናውቅ በእነርሱ በኩል የሚያጋጥም ችግር አይኖርም::
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት በአሁን ሰዓት አፈር ልሶ ለመነሳት ትግል እያካሄደ እንደሆነ እሙን ነው፤ ይህን ትግሉን ግን ልክ ከአማራ ክልል ጋር ብቻ እየተዋጋ እንደሆነ አድርጎ የመናገርና ይሄው እንዲታወቅለት ነው የሚፈልገው፤ ይህን እርስዎ እንዴት ያዩታል?
አቶ ቶማስ፡– አሸባሪው ጁንታ ባህሪው ብዙ ነው፤ አስቀድሞም ቢሆን በስልጣን ላይ ቆይታው ሲያደርግ የነበረው ዝርፊያ ነው:: ይህ ዝርፊያው ደግሞ በአንድ ክልል ብቻ የተወሰነ አልነበረም:: ስለዚህ የአሸባሪው ህወሓት ኩርፊያ ከአንድ ክልል ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም:: በአሸባሪው ህወሓት ላይ የተናደደው ህዝብም የአንድ ክልል ብቻ አይደለም::
ለምሳሌ ያህል የጋምቤላን ጉዳይ ብጠቅስልሽ፤ በክልሉ ያለው መሬት ሁሉ ማለት በሚያስችል መልኩ በዚህ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ተዘርፎ ነበር:: በመሬቱ ላይ የነበረው የተፈጥሮ ደን በማን አለብኝነት ያለምንም ማንገራገርና ርህራሄ ተጨፍጭፎ የተባለውም ልማት ሳይሰራበት መራቆቱ በእጅጉ የሚያሳዝን ጉዳይ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው::
ይህ የጁንታው ዝርፊያ እንደተጠበቀ ሆኖ የእኛን መሰል ክልል ደግሞ ሲያስተዳድር የነበረው በሞግዚት መሆኑም ሌላው እኩይ ተግባሩ ነው ማለት ያስችላል:: በስም ብቻ ሽፋን በማድረግ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት የሚያስከብረው እኔ ነኝ ሲል ይናገራል:: በተግባር ሲታይ ግን ለተወሰኑ አካላት ብቻ የቆመ ስለመሆኑ ምግባሩ ይመስክራል:: እኛ እና እኛን መሰል ክልሎች ለኢትዮጵያ ተብሎ ከቀረበ ገበታ በስተጀርባ ነበር ስቀመጥ የነበረው::
አሁንም ያንን የድሮውን አይነት ጨዋታ ለመጫወት መፈለጉን ነው እያስተዋልኩ ያለሁት:: በአሁን ወቅት እየፈጸመ ባለው እኩይ ተግባሩ እያጠቃ ያለው የአማራን ወይም የአፋርን ክልል ብቻ አይደለም:: ኢትዮጵያን ነው:: አገርን ነው ለማፍረስ የተነሳው:: ደግሞም ይህን ክፉ ተግባሩን እያደረገ ያለው ራሱ ሽብርተኛው ህወሓት እንጂ የትግራይ ህዝብ ጭምር አለመሆኑ እርግጥ ነው::
የትግራይና የአማራ ህዝብ እርስ በእርስ በጠላትነት የሚፈራረጁ አይደለም:: ይህ ከጥንትም ጀምሮ ያለ ነው:: ዛሬ የሚመጣ አዲስ ነገር አይኖርም:: የትግራይ ህዝብ ወይም የአማራ ህዝብ በትግሬ ላይ ወይም በአማራ ላይ ህዝብ እንደ ህዝብ ሊነሳ አይችልም:: የጁንታው ቡድን አገር የማፍረስ ዓላማ ስለያዘ ነው እንዲህ አይነት ችግር እየፈጠረ ያለው::
አሸባሪው ጁንታ አንዱን ከአንዱ ጋር የማወሳሰብ ስራ የተካነበት ነው:: ጉዳዩን ክልል ከክልል ጋር ለማስባል በብዙ ቢጥርም ይህ ሳይሆን ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው:: ክልል ከከልል ጋር ሆኖ ቢሆን ኖሮማ ለምንድን ነው ከየክልሉ ልዩ ኃይሉ እኩይ ተግባሩን ድባቅ ለመምታት ወደስፍራው የተመመው ልትይ ትችያለሽ:: ለምንድን ነው በየክልሉ ያለው ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊት ያልተቋረጠ ድጋፉን በሆታ እየገለጸ ያለው ብሎ መጠየቅ ይቻላል::
ይህ የጁንታው ቡድን ከዚህ ቀደምም በየቦታው ቀውስን በማስነሳት አንዱን የአንዱ ጠላት በማስመሰል ሲያጣላ እና ሲያባላ የነበረ ነው:: እንዲህ አይነት ተግባሩ ሁሉም የሚያውቀው ሆኗል:: ዛሬም ይህን ውሸት በመፈብረክ ጉዳዩ የአማራና የትግሬ ለማስመሰል አየጣረ ነው:: ነገር ግን በጎን ሄዶ ደግሞ የአፋርን ህዝብ እየወጋ ነው:: ስለዚህ ጁንታው በአንድ ክልል ላይ ብቻ ጉዳዩን ለማስቀመጥ የሚሞክረው ሙከራ የከሸፈ ነው:: ጉዳዩ የአገር ጉዳይ ነው:: የጁንታው ቡድን አንግቦ የተነሳው አገር የማፍረስ አጀንዳ ሲሆን፣ እሱንም በሌሎች እየታገዘ ነው እያደረገ ያለው:: መላው ኢትዮጵያውያንን ይህን እኩይ ዓላማውን ለማጨናገፍ ሲሉ ነው በአሁን ወቅት ሰልፋቸውን በአንድ ያደረጉት::
አገር የማፍረሱን አጀንዳ የቀረጸው ብቻውን ሳይሆን ከጀርባው ብዙዎችን አዝሎ ነው፤ ከእነዚህም መካከል አሜሪካና ግብጽ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሾች ናቸው:: በተለይም ትልቁ ትኩረታቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው:: ይሁንና በህዳሴ ግድብ ላይ ምንም አይነት መብትን አሳልፎ የሚሰጥ ድርድር የለም::
በጥቅሉ የጁንታው ቡድን ከሌላው ጋር በመተባበር አገር የማፍረስ አጀንዳ በመንደፉ ከዚህ በኋላ ሊያንሰራራ እንዲያስችል የሁላችንም ህብረት ወሳኝ ነው:: ዛሬም ቢሆን ነገ ከመከላከያችን ጎን በመሆን ጁንታው የያዘውን ዓላማ ማምከን ከሁላችንም የሚጠበቅ ጉዳይ ነው:: በዚህም የኢትዮጵያንም የትግራይንም ህዝብ ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ በማድረግ ሂደት የአማራ ወይም የአንድ ክልል ስራ ብቻ ባለመሆኑ በጀመርነው አካሄድ ተጠናከረን ልንሄድ የግድ ይለናል እላለሁ:: የተጀመረው አገርን የማዳን ትግል በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁላችንም ከአገር መከላከያ ጎን እንድንቆም እና እንድንረባረብ ነው ትልቁ ምኞቴ::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::
አቶ ቶማስ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 14/2013