አንዲት በጭስ የታፈነች ቤት ውስጥ ዘልቄያለሁ። እዚህ ሰነፈጠኝ፣ አቃጠለኝ ብሎ መነጫነጭ የለም። ቤቷን ለተላመዷት ሰዎች የምድር ዓለም ናት። ሠላምታ ሰጥቼ ለማዕድ ቤት ቀረብ ብዬ ከመደቡ ላይ ተቀመጥኩ። ግራ ቀኝ የተደረደሩ ሰዎች ቁልጭ ቁልጭ እያሉ የሚጠብቁት እንዳለ ሁኔታቸው ያሳብቅባቸዋል። የልባቸውን ያሳኩት ደግሞ እንደየአቅማቸው፣ ሻይ፣ አረቄ፣ ቢራና ውሃ እየተጎነጩ ይጨዋወታሉ። በዚያች ጭስ ባፈናት እልፍኝ በጥዋቱ ጨዋታው ደርቷል። ሁኔታውን ላልተላመደ እንግዳ ሰው ግን ጭሱ ስለሚያፍነው፤ በደቂቃዎች ውስጥ ሊወጣ ይችላል። ወደ ቤቱ የመጣሁበትን ጉዳይ አስረድቼ፤ በጭስ በታፈነችው ማብሰያ ክፍል ውስጥ እየተጨናበስኩ ዘለቅሁ። በሐዋሳ ሙቀት ላይ ተጨማሪ በዚች ጠባብ ክፍል ውስጥ በሚንቀለቀለው እሳትና ጭስ ታፍኜ ቆይታ አደረግሁ። ከብረት ምጣዱ ላይ የተጣደው ነገር በኃለኛው ይንቸከቸካል።ሽታው ሆድ ያላውሳል፤ ጭሱ ያፍናል፣ ሙቀቱ ጉልበት ያዝላል። በዚህች ቤት የተገኘሁት በሐዋሳ ‹‹ኦልካ›› እየተባለ የሚጠራውን ምግብ ከጅምሩ እስከ አሠራሩ ላስተዋውቃችሁ ነው።
የዚህን ምግብ ስያሜ ማን፣ መቼ እና ለምን እንደሰጠው በትክክል ለመለየት አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ተጠቃሚዎቹ ‹‹ኦልካ›› በሚለው ስያሜው ይግባባሉ። ወይዘሮ ብርቱካን ብርሃኑ ‹‹ኦልካ›› ለደንበኞቿ ማቅረብ ከጀመረች አምስት ዓመታትን አስቆጥራለች። እርሷ ለኦልካ፤ ኦልካም ለእርሷ ባለውለታ ሆነዋል። ‹‹ኦልካ›› ማለት በዋናነት የከብቶች አንጀት ከተለያዩ ቅመማቅመሞች ጋር ተከሽኖ የሚዘጋጅ ምግብ ነው። አሰራሩም አድካሚና ፍዳ የሚያበላ ነው። ወይዘሮ ብርቱካን የኦልካን አሰራር አንዲህ ትተርከዋለች። በመጀመሪያ የከብት አንጀት በሚገባ ይታለባል፤ ከዚያም ይከተፋል። በዚህ ሁሉ ሂደት ግን አንዳችም የውሃ ጠብታ አይነካውም። ‹‹ኦልካ›› በተፈጥሮ ቅባት ስላለው ተጨማሪ ቅባትና ፈሳሽ አያስፈልገውም። ከዚያ በመጥበሻ ላይ በእሳት ብስል ተደርጎ፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ አዝሙድ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ኮረሪማ እና መከለሻ ቅመም በአንድነት ተፈጭቶ በስሱ ብን ይደረግበታል። ሊወጣ ሲልም የስጋ መጥበሻ (ሮዝመሪ) ጣል ይደረግበታል። በመጨረሻም ለተጠቃሚው ሲቀርብ ነጭ ሽንኩርት ከዝንጅብል ጋር ስልቅ ተደርጎ ይፈጭና ለማባያ እና ማጣፈጫ ከላይ ይጨመራል። ‹‹ኦልካ›› በበቆሎ ቂጣ ዛቅ ተደርጎ፤ አሊያም ደግሞ በእንጀራ ጠቅለል አድርገው ሲመገቡት አንጀት ያርሳል። ኦልካ ሰውነትን ሰፋ፣ ደረትን ገፋ የሚያደርግ ሲሆን፤ ከጠቀሜታው የተነሳ ስፖርተኞችም በሚገባ እንደሚያጣጥሙት ነው ወይዘሮ የምትናገረው። ሽሮ እና ኦልካን የሚበለ ሰው ልዩነቱ የትዬሌሌ ነው የምትለው ብርቱካን የምትናገረው።
ኦልካ አንዴ ልክክ አድርጎ የበላ ሰው ሙሉ ቀን የርሃብ ስሜት አይሰማውም። በጨዋታችን መሃል የኦልካው መረቅ እንጀራው ላይ እንዳያርፍም ወንፊት በመሰለ መካከለኛ ጭልፋ ዛቅ እያደረገች ታወጣለች። ‹‹ኦልካ›› በአብዛኛው በጥዋት የሚመገቡት ምግብ ነው የምትለው ወይዘሮ ብርቱካን፤ ከፍተኛ ስብ ስላለውና ከፀሐይ ሙቀት ጋር ስለማይስማማ ተመራጩ ጊዝ ማለዳ ላይ ነው። ረፈድ ሲል ብዙ ተጠቃሚ የለውም። ወይዘሮ ብርቱካን የአንድ ከብት አንጀት ከ150 እስከ 200 ብር ከቄራ ተቀብላ፤ የትራንስፖርት፣ ከታፊ እና ሌሎች ሂሳብ አውጥታ አንድ ኦልካ በአንድ ጭልፋ ሙሉ እና ግማሽ በ25 ብር ትሸጣለች። ‹‹አንጀት ዱሮ መሬት ተቆፍሮ የሚቀበር እንጂ ለምግብነት አይውልም ነበር›› የምትለው ወይዘሮ ብርቱካን፤ እንደምግብ የሚጠቀሙት ቢኖሩ እንኳን በገጠሪቱ አካባቢ ያሉ ሰዎች እንጂ ከተሜው አያውቀውም ነበር። አሁን ግን ሐዋሳ ውስጥ ኦልካ፤ አንጀት የሚያረካ፣ ዝናው እየናኘ ያለ ምግብ መሆኑን ትናገራለች። በእርግጥ ከሩቅ የሚመጡት ብቻ ሳይሆኑ ሐዋሳ ውስጥ ሆነውም ‹‹ኦልካ››ን የማያውቁ አያሌ ሰዎች አሉ። በተለይም በሐዋሳ ውስጥ ፒያሳ፣ አቶቴ፣ ሎጊታ በሚባሉ አካባቢዎች ኦልካ ብዙም አይታወቅም።
ሐዋሳ ኦልካን በሰፊው እየተጠቀመችበት ቢሆንም፤ ስሙ ይለያይ እንጂ በሌሎች አካባቢዎች ጥቅም ላይ እንደሚውል ይነገራል። በአንዳንድ ስፍራዎች ‹‹ቲሽ፣ ሞርቶ›› እና የመሳሰሉ ስሞች አሉት። ከአምስት ዓመት በፊት ቄራ ከሚሠራው አጎቷ የምግቡን አሰራር የቀሰመችው ወይዘሮ ብርቱካን ዛሬም ድረስ ከኦልካ ጋር ወዳጅነታቸው እንደቀጠለ ነው። ሐዋሳ ሠላም ሆና ሳለ እስከ 100 ኦልካ በቀን ትሸጣለች። በአሁኑ ወቅት ግን የሐዋሳ የሠላም አየር አልፎአልፎም ቢሆን ስለተረበሸ ከ40 ኦልካ በላይ አትሸጥም። ወይዘሮ ብርቱካን ከኦልካ ጋር ፍቅሯን ማዝለቅ ትፈልጋለች። ‹‹ኦልካ›› ከጨረጨሰችው ማዕድ ቤት ወጥቶ ባለኮኮብ ሆቴሎች ዝናን ያተረፈ ምግብ እንዲሆ ትፈልጋለች። አልፎ አልፎ አዲስ አበቤዎችም ወደ ብርቱካን ቤት ሲያቀኑ ‹‹ኦልካ ምንድን ነው?›› ብለው ሲጠይቋት በአጭሩ ‹‹የተከሸነ ስጋ ጥብስ ነው›› በማለት ታላምዳቸዋለች። አንዴ የቀመሱት ሳያመነቱ ደምበኞቿ ይሆናሉ። አቶ በኃይሉ ማቲዮስ ከባለቤቱ ብርቱካን ጋር ነው ለደንበኞቹ ኦልካ እየከሸነ የሚያቀርበው። ኦልካ ሲሰራ ቢላዋውም በጣም መሳል እንዳለበት ይናገራል። ሽንፍላ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ በሚገባ መለያየት አለበት። የበሬውን አንጀት የሚከትፈው ሰውም ፈርጠም ያለ ጡንቻ ሊኖረው ይገባል። ከውሃ ንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ በሚገባ መፅዳት አለበት። ሞራውንም ገለል፤ ገለል አድሮ መለየት ያስፈልጋል።
ኦልካ ሲዘጋጅ ከባዱ ሥራ አንጀት መክተፉና ንጹህ አድርጎ ከውስጡ ያለውን ፈሳሽ ማለብ እንደሆነ ይነገራል። ‹‹በሐዋሳ የበሬ አንጀቱ ብቻ ሳይሆን ከንፈሩም ጥቅም ላይ ይውላል›› የሚለው በኃይሉ፤ በተለምዶ በአካባቢው አጠራር ‹‹ቡርቡርቻ›› ተብሎ የሚጠራው የከብቶች ከንፈርም ለጥርስ ጥንካሬ ሲባል ለምግብነት ይውላል። «ከበሬው አካል እጢዎች፣ ከዓይንና ጆሮው በስተቀር አንዳችም የሚጣል የለም። ሁሉም ተፈላጊ፤ ሁሉም አስፈላጊ በመሆኑ እንክት ተደርጎ ይበላል። በሬ ሲታረድ ከድምፁ በስተቀር አንዳችም ነገሩ መሬት አይወድቅም» የሚለው አቶ በኃይሉ እርሱም ኦልካ እያጣጣመ ደንበኞቹንም እያስደመመ ኑሮውን ይገፋል። አቶ በኃይሉ ኦልካ በማን እና መቼ እንደተጀመረ በትክክል ማወቅ አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራል።
በአሁኑ ወቅት እርሱ በሚሠራበት አካባቢ ቄራ በመኖሩ ‹‹ኦልካ›› በዚያው ሰፈር ስለመጀመሩ ግን በወሬ ወሬ ሰምቷል። የኦልካን ውለታ በሚገባ ጠንቅቀው ከሚመሰክሩት ወጣቶች መካከል የገበያ ሰፈር ነዋሪው ምስጋናው ጳውሎስ አንዱ ነው። ምስጋናው ሰውነቱ በእጅጉ ደንዳና ነው። የእጁ ውፍረት፣ የደረቱ ስፋት እና ሁለመናው የኦልካን ውለታ በቅጡ ካስመሰከሩ ሰዎች አንዱ ይመስላል። ኦልካ የሚበላ ሰው ሰውነቱ ደንዳና፤ ተክለ ቁመናው ማራኪ እንደሆነና ለችግሮች የማይገበር ሰውነት እንዳለው የሚገልፀው ምስጋናው፤ የእርሱ ሰውነት በኦልካ የተገነባ መሆኑን ይናገራል። ኦልካ አንዴ በልተውት ሙሉ ቀን ሌላ ምግብ የሚያስረሳ፤ የድሆች አለኝታ ነው። አሁን ግዙፍ ሆኖ ለሚታየው ተክለ ሰውነቱ የኦልካ ውለታ የበዛ እንደሆነ አጫውቶኛል። ቢያንስ በሳምንት ሦስት ቀን ኦልካን ይመገባል። አሁንም ከኦልካ ጋር ወደጅነታቸው እንደቀጠለ ነው። ኦልካ ለምስጋናው የምግብ ልክ፤ ምስጋናው ለኦልካ የአስመስጋኝ ልክ ናቸው። እንዲያው በደፈናው ላይለያዩ ተዋደዋል! ጉዶ ደላላው ሐዋሳ ውስጥ አረብ ሰፈር ነዋሪ ሲሆን፤ ጌታቸው ከሚባል ወዳጁ ጋር ኦልካን ሲያጣጥም ነው ያገኘሁት። ከኦልካ ጋር ነው ያደገው። ‹‹ምግባችን ኦልካ፣ ዘፈናችን ዋካ! ዋካ!›› ነው ይላል።
20 ለሚጠጉ ዓመታት ኦልካን በፍቅር ቅርጥፍ አድርጎ አጣጥሟል። ምንም እንኳን ጉዶ ደላላው የኦልካ አፍቃሪ ቢሆንም ሰውነቱ እንደ ሌሎች ተመጋቢዎች ደንዳና አይደለም። ያም ሆኖ አብሮ አደጉ በመሆኑ ‹‹ኦልካ›› ባለውለታው ነው። «በሬ ሁሉ ነገሩ ጥቅም ላይ ውሎ እያመለጠ ያለው ድምፁ ብቻ ነው» የሚለው ጉዶ ደላላው፤ ‹‹ኦልካ›› ከበላ በኋላ ቅባቱ ከፍተኛ ስለሆነ በፍጥነት እንዲለቅ እጁን በአጃክስ ሳሙና እጥብ፤ ጉሮሮውን ደግሞ ሻይ ተጎንጭቶ ፅድት ያደርገዋል። በዋጋ ደረጃም ቢሆን፤ ኦልካ ከምግብ ሁሉ ርካሽ ነው። ‹‹ዛሬ ኦልካን ልክክ አድርጎ ያጣጣመ ሰው፤ ከምግብ ጋር የሚገናኘው በሁለተኛው ቀን ነው፤ እንዲሁም ኦልካን የበላ ሰው አሲድ ቢጠጣም አይጎዳውም›› ሲል ኦልካን ያንቆለጳጵሰዋል። ጉዶ ደላላው፤ በፆም ወቅት ‹‹ኦልካ›› አቅራቢዎች በእጅጉ ስለሚቀንሱ፤ ወደ ሐዋሳ ፍቅር ኃይቅ ጎራ ብሎ ዓሳ ያጣጥማል። ፆም እስኪፈታ ድረስ ከኦልካ ጋር ይነፋፈቃሉ። «አፍህ ወተት እንደጠጣ ህፃን፤ እጅህ ደግሞ ሊጥ እንዳቦካች ሴት ነጭ ከሆነ አንተ ኦልካን ስለመመገብህ ማንም ያውቃል» የሚለው ጉዶ ደላላው፤ ኦልካ መብላት ብቻ ሳይሆን ከአሠራሩ እስከ አበላሉ መላ አለው ይላል። «ኦልካ አጣጥመህ በሰከንዶች ልዩነት እጅህን በሳሙና እና አመድ እሽት አድርገህ ካልታጠብከው ቀኑን ሙሉ የበላኸው ምግብ አጠገብህ ያለውን ሰው አፍንጫ ቢረብሸው፤ ሊያስደንቅ አይገባም። አፍህ ወዝ በወዝ ሆኖ ደጋግመህ ብትጠርገው አንዳችም አያስገርምም» የሚለው ጉዶ ደላላው፤ ከፍተኛ የቅባት መጠን ስላለው፤ ሲበላ ከሆድ እስከ እጅ ልክክ ይላል። የስጋ ተዋፅኦዎችን በ25 ብር መጠቀም ቀርቶ ማሰቡ ነውር በሆነበት ጊዜ፤ ኦልካን በ25 ብር ስለምናጣጥም የስጋ አምሮታቸውን እንደሚቆርጡ ይናገራል። ‹‹ኦልካ›› በሐዋሳ ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው በርካታ ሰዎች የሕይወት ወዳጅነቷ የጠነከረ በመሆኑ እያመሰገኑ የሚቋደሱት ብዙናቸው። በአንጻሩ ደግሞ ስለምግቡ ስምና አሠራር ሲሰሙ ‹‹ዓጃኢብ›› የሚሉ ከተሜዎች በሐዋሳ ይገኛሉ።
ኦልካ ለሰሚው ግራ፤ ለተጠቃሚው ምቾት ነው። ኦልካ የሚያዘወትር ሰው ከሌላ ምግብ ለመላመድ ብዙ አያስቸግረውም፤ ወዲያውኑ ሊወዳጅ ይችላል። አሁን በሬው ሁሉ ነገሩ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ቆዳው ጫማ፣ ቀንዱ ዋንጫ፣ ስጋው በውድ የሚሸጥ ነው። አንጀቱም ቢሆን ዕድሜ ‹‹ኦልካ››ን ለሚከሽኑ ሁሉም ነገር ሥፍራ ሥፍራውን ይዟል። በሐዋሳ የኦልካ አፍቃሪዎች ‹‹ምግባችን ኦልካ፤ ዘፈናችን ዋካ ዋካ!›› እያሉ በፍቅር ይሰለቅጡታል። ግን የሚያሳስባቸው ነገር ቢኖር የበሬን ድምፅ እንዴት ወደ ጥቅም እንቀይረው? የሚለው ሆኗል!
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር