
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለማችን ተላላፊ በሽታዎች አስጊ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የብዙዎችን ሕይወትም እየቀጠፉ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት የኮቪድ 19 ወረርሽኝና ኢቦላ እንዲሁም ኮሌራ በዋናነት የሚጠቀሱ የበሽታ ዓይነቶች ናቸው። አሁን ደግሞ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በአፍሪካ አንዳንድ ክፍሎች በማንሰራራት ለሕብረተሰብ ጤና ስጋት ሆኗል። በተለይም ላለፉት ጥቂት ዓመታት በመካከለኛውና በምዕራብ አፍሪካ ተንሰራፍቶ የቆየ ነው። ይህ በሽታ አደጋው የከፋ ባይሆንም ችግሩ ቶሎ እልባት ካልተሰጠው ግን ማኅበረሰቡን መጉዳቱ አይቀሬ ነው፡፡ በሽታው በቅርቡ በጤና ሚኒስቴርና በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይፋ በተደረገው መረጃ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በቫይረሱ የተጠቁ ጥቂት ሰዎች መኖራቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመግለጫው ላይ እንዳመለከተው፤ በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ እስተዳደር ከታማሚዎች በተወሰደ ናሙና ቫይረሱ የተገኘበት የ21 ቀን እድሜ ያለው ሕፃን ልጅ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ለእናቱም በተደረገው ቀጣይ ምርመራ ለቫይረሱ እንደተጋለጠች ማወቅ ተችሏል፡፡ የሕፃኑ አባት ወደ ጎረቤት ሀገር ሄዶ የነበረ መሆኑ መታወቁና የሄደባቸውን አካባቢዎች እንዲሁም በሽታው ካለባቸው ግለሰቡ ጋር የቅርብ ንክኪ እንደነበራቸው ለማወቅ ተችሏል። አሁን ግለሰቦችን የመለየትና ክትትል የማድረግ ሥራ ተጀምሯል። ታማሚው ሕፃን እና እናቱ፣ አስቀድሞ በተዘጋጀው የለይቶ ማከሚያ፣ ተገቢው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ የከፋ የጤና እክል አልገጠማቸውም ተብሏል።
የአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥር እና መከላከል (ሲዲሲ) ማብራሪያም የዝንጀሮ ፈንጣጣ (mpox) በሽታ የአፍሪካ አስቸኳይ የጤና ስጋት ሆኗል ሲል ያወጀው በሽታው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአፍሪካ ውጪ እየተከሰተ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ችግሩን ዓለም አቀፋዊ ስጋት እየሆነ መምጣቱን ያመላክታል።
ለመሆኑ ይህ በሽታ ምንድነው? መነሻ ምክንያቱና ሕክምናውስ፤ የት ሀገር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ታየ እንዲሁም አሁን ያለበት ሁኔታስ የሚሉትን ጉዳዮች በዛሬው የማኅደረ ጤና›› ዓምዳችን የምንዳስሰው ይሆናል፡፡ ሀሳቦችን ደግሞ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ወስደናል፡፡
የዝንጀሮ ፈንጣጣ (mpox) በሽታ ምንድን ነው?
አዲሱ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (mpox) በሽታ ቫረሰዮላ በተባለ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው። ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1950ዎቹ በዝንጀሮዎች ላይ ነበር የተገኘው። ይህ በሽታ ዘር፣ ሃይማኖት፣ እድሜና ጾታ ሳይለይ ማንኛውንም ሰው ሊይዝ የሚችል ሲሆን፤ በበሽታው በያዙም ብዙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ የሚድኑበት ነው፡፡ በዚያው ልክ አንዳንዶቹ በጸና ሊታመሙበት ይችላሉ፡፡ በሽታው በተለይ ሕጻናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶችና የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች ላይ ይበረታል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ እንዴት ይተላለፋል?
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተላላፊ ከሚባሉ በሽታዎች መካከል ይመደባል፡፡ ሕመሙ በተለያየ መንገድ የሚተላለፍ ሲሆን፤ ከሰው ወደ ሰው፤ ከእንስሳት ወደ ሰው፤ ከእናት ወደ ልጅ እንዲሁም የተበከሉ ነገሮችን በመንካት ይተላለፋል፡፡ በበሽታው ከተያዘ ሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በመተንፈሻ አካላት ብናኞች፣ የቆዳ ቁስል ወይም የሰውነት ፈሳሾች አማካኝነት በቅርብ ንክኪ፣ መሳሳም፣ መተቃቀፍ፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት እና በቆዳ ለቆዳ ንክኪ ነው። በተጨማረም የተያዘ ሰው ተጠቅሞባቸው ከተበከሉ ልብስ፣ የቤት እቃዎችንና ሌሎች ግኡዝ ነገሮችን በመንካት ሊተላለፍ ይችላል።
ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍበት መንገድ ደግሞ ከታመሙ የዱር እንስሳት (አይጦች እና ፕሪምቶች) ጋር መገናኘት፤ የታመመ የእንስሳት ስጋን መመገብ አለያም በታመሙ እንስሳት መቧጨር ወይም መያዝ ሊሆን ይችላል። ሌላው ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ሲሆን፤ ነፍሰጡሮቹ ቫይረሱ ካለባቸው ወደ ማሕፀን የመሸጋገር እድሉ ይኖረዋል፡፡ በዚህም ልጁን የበሽታው ተጠቂ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህም ከታመሙ ሰዎች፣ እንስሳት እና የተበከሉ ነገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት መቀነስ ኢንፌክሽኑን ለመከላከል ይረዳልና ይህንን ማድረግ የግድ ያስፈልጋል።
የበሽታው ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የበሽታው ምልክት መታየት የሚጀምረው አንድ ሰው ለቫይረሱ ከተጋለጠ ከሳምንት በኋላ ሲሆን፤ አንዳንዴ በቶሎ ወይም ሌላ ጊዜ ዘግየት ብሎ ሊጀምር ይችላል። የተለመዱ ምልክቶቹ ደግሞ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የመገጣጠሚያ ሕመምና ድካም ጨምሮ የጉንፋን ዓይነት ምልክቶች ነው። ቆዳ ላይ የሚወጣ ቁስል (ሽፍታ) ዋነኛው መገለጫው ነው። ይህ የቆዳ ምልክት መጀመሪያ ላይ ጠፍጣፋ ቀላ ያለ ሽፍታ ሆኖ ይጀምርና ከዚያ አብጦ ፈሳሽ ይቋጥራል። በመቀጠልም ይፈርጥና ይቆስላል። ይህ ቁስል በፊት ላይ፣ በአፍ ውስጥ እና እንደ እጅ፣ እግር፣ ደረት፣ የመራቢያ አካላት ወይም ፊንጢጣ ያሉ ሌሎች የአካል ክፍሎች ላይ ሊወጣ ይችላል። ቁስሉ ሲቆይ ይደርቅና ተቀርፎ ይወድቃል። ከዚያም በአዲስ ቆዳ ይተካል። በተጨማሪም የተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚወጡ ንፍፊቶች ማበጥ ያሳያል። ምልክቶቹ ብዙውን ጊዜ ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት ይቆያሉ። ከቁስሉ ላይ ናሙና በመውሰድ በላብራቶሪ ምርመራ ማድረግ ደግሞ ችግሩን በቀላሉ ለማወቅ የሚቻልበት መንገድ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
የዝንጀሮ ፈንጣጣን ውስብስብ የሚያሰኘው ምኑ ነው?
የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚድን ቢሆንም፣ ለከባድ ሕመም እና ለመተላለፍ ባለው አቅም ምክንያት ከፍተኛ የጤና ችግሮችን የሚፈጥር ነው። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ በሽታው በተለይም የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅማቸው በተዳከመ ግለሰቦች ላይ ወደ ብዙ ችግሮች ሊያመራ ይችላል። አንዳንድ ሊሆኑ የሚችሉ ውስብስቦች የሚከተሉትን ያካትታል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ኢንፌክሽኖች መፍጠር፤ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች በቆዳ ቁስሎች ውስጥ እንደዳብሩ ማድረግ፤ ለሳንባ ምች ማጋለጥ፤ የሳንባ ምች ከፍ ሲል የአተነፋፈስ ችግርን ማምጣት፤ አልፎ አልፎ ደግሞ ቫይረሱ የአንጎል እብጠትን እስከማስከተልም የመድረስ ጉዳትን ያመጣል፡፡
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የረጅም ጊዜ ተጽእኖዎችን እስከማምጣት የሚደርሱ ናቸው፡፡ በሽታው ሽፍታው ወይም ቁስሎቹ ዓይን አካባቢ የሚከሰቱ ከሆነ ደግሞ የማየት ችግርን አልፎ ተርፎም ዘላቂ የዓይን ጉዳትን ሊያስከትል እንደሚችል ይነገራል፡፡ የቆዳ ቁስሎች ዘላቂ ጠባሳ ሊተው መቻሉም እንዲሁ ሁለተኛ ደረጃ ኢንፌክሽኖችን ሊከስቱ እንደሚችሉም ተመላክቷል። አንዳንድ ግለሰቦች እንደ ድካም፣ ሕመም ወይም በመገጣጠሚያዎች ላይ (የአርትራይተስ) እብጠት ያሉ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ምልክቶችን ሊያሳዩ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዳለ ይገለጻል፡፡
በሽታው ነፍሰጡሮች ላይም ከባድ የሚባሉ ችግሮችን ይከስታል፡፡ ይህም በእርግዝና ወቅት በሽታው ያለባት ሴት ፅንስ ማስወረድ፣ ያለጊዜው መወለድ ሊያስከትል ይችላል።
ሕክምናው ምንድን ነው?
ሕክምናው በዋናነት የተያዘውን ሰው ለይቶ ማስቀመጥ (ኳራንቲን) ማድረግ ነው። ከዚያ ለታማሚው ሁኔታው እየታየ ማስታገሻዎች ይሰጣሉ። ችግሩ በጣም ካልገዘፈ የትኩሳት ማብረጃ መድሃኒት መውሰድ ወይም የሕመም ማስታገሻ መዋጥ በቂ ሊሆን ይችላል። ቁስሎች እስኪድኑ እና አዲስ ቆዳ እስኪወጣ ድረስ ኳራንቲን መቀጠል አለበት፣ ይህም ከሦስት እስከ አራት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል። ከዚያ ባሻገር ክትባቱ በተለይም በሽታው ካለበት ሰው ጋር በተገናኘ በአራት ቀናት ውስጥ መሰጠት ይኖርበታልም፡፡
ሌላው የሕክምና ባለሙያዎችን የሚመለከተው ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥንቃቄ ማድረግ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ በሽታው ያለባቸው ታካሚዎችን ሲንከባከቡ ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ታካሚዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። እነርሱ እንዳይበከሉ የግል መከላከያ መሳሪያዎችን መጠቀም (PPE) ይኖርባቸዋል፡፡ በጤና እንክብካቤ መስጫ ቦታዎች ውስጥ ሊበከሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችን በሚይዙበት ወቅት እንደ ጓንት፣ ጭንብል እና ጋወን መጠቀም የግድ ይሆናል።
የክትትል እና የቁጥጥር ርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ፤ ለጤና ባለሙያዎችና ለሕዝቡ መሰረታዊ የሆኑ መረጃዎችን መስጠትም የግድ ያስፈልጋልም፡፡ በተለይም ጤና ሚኒስቴርና መሰል ባለድርሻ አካላት ጉዳዩንና ወረርሽኙ የደረሰበትን ደረጃ ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ በተለያየ መልኩ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ሕክምና በጤና ተቋማት ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም በሚከናወኑ ተግባራትም ይፈጸማል። ምክንያቱም በሽታው በግል ደረጃ ከሚደረግ ጥንቃቄም አንጻር ብዙ መፍትሄ የሚሰጠው ነው። እናም በሽታው የተገኘበት ሰው ሊያደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል በቤት ውስጥ ተለይቶ መቀመጥና የተለያዩ ሕክምናዎችን ማድረግ፤ እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና እና በውሃ እንዲሁም ሌሎች ማጽጃዎች በመጠቀም ማጽዳት፤ ማስክ ማድረግ፤ ከሌሎች ጋር የምንጋራቸው እቃዎችን መለየት፤ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባት መውሰድ ኢንፌክሽንን ለመከላከል የሚረዱ ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ ደግሞ የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ስለመሆኑም አንስቷል፡፡
እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ ከሆነ፤ በሽታው በአኅጉራችን ከተከሰተበት ወቅት ጀምሮ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባና ከገባም ጉዳቱን ሳይከፋ በቁጥጥር ውስጥ ለማድረግ እንዲቻል በርካታ ሥራዎችን ተከናውነዋል፡፡ ለዚሁ በሽታ መካላከል ሲባል በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ የድንገተኛ አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል ተቋቁሞ እየሠራ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር በቫይረሱ ለመያዛቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ማቆያ የሚሆኑ የተለዩ የጤና ተቋማት የተዘጋጁ ሲሆን በዚህ በሽታ የታመሙ ሰዎችን ለማከምና ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ የጤና ተቋማት አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቅቀዋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ስርጭቱ አስጊ ደረጃ ቢደርስም መደናገጥ አያስፈልግም። በበሽታው የተያዙ አብዛኛዎቹ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ይድናሉ። አብዛኛውን ጊዜ ለሞት የሚዳርግ አይደለም። በተገቢው የግንዛቤ እና የመከላከያ እርምጃዎች እራሳችንን እና ማኅበረሰባችንን መጠበቅ እንችላለን።
እንዴት እንደሚተላለፍ በመረዳት፣ ምልክቶቹን በማወቅ እና የመከላከያ ርምጃዎችን በመውሰድ ቫይረሱን ለመከላከል፣ ስርጭቱን ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚረዱን ዘዴዎች በእጃችን ናቸው። ስለሆነም አሁን ሀገር ውስጥ በመከሰቱ የተነሳ ከመደናገጥ ይልቅ ለመፍትሄው መሥራት አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ይገባል እያልን ለዛሬ የያዝነውን አበቃን፡፡
በጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም