
ኢትዮጵያን ታላቅና ባለ ታሪክ አገር ካደረጓት ሕዝቦች መካከል የኦሮሞ ሕዝብ አንዱና ሰፊ ድርሻ ያለው ነው። ኢትዮጵያ ከውጭ ወራሪዎችም ሆነ ከውስጥ ባንዳዎች ፈተና በገጠማትና ጥቃት በተሰነዘረባት ወቅት ሁሉ ከኦሮሞ አብራክ የወጡ ጀግኖች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ግንባራቸውን ለጥይት አንገታቸውን ለሰይፍ እየሰጡ ነጻነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን አቆይተውናል።
ፋሺዝም በኢትዮጵያ ላይ የሰነዘረውን ወረራ በመዋጋት ብቻ ሳይሆን በፋሽስቶች ምድር አውሮፓ ላይ ነጮችን በማንቃትና በማደራጀት ፋሽስቶችን ተዋግተው እንዲያሸንፉ የታገለውና ያታገለው ብዙ ያልተዘመረለት አብዲሳ አጋ ከኦሮሞ አብራክ የተገኘ የምንጊዜም የዓለም ጀግና ነበረ። በፋሽስት ዳግም ወረራ ወቅት የኢትዮጵያን ጦር በመምራት፣ በመዋጋትና በማዋጋት ለአፍሪካ የነጻነት ትግል ነጸብራቅ ከሆኑት መካከል እነ ባልቻ አባነፍሶ፣ እነ ገበየሁ ጉርሙና እነ ሀብተ-ጊዮርጊስ ዲነግዴ ከኦሮሞ ማሕጸን የተገኙ ለኢትዮጵያም ልዕልናን ያላበሱ ታሪክ ሲዘክራቸው የሚኖር ባለውለታዎቻችን ናቸው።
በዘመናዊት ኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ በመያዝ፣ ዓለምአቀፋዊ ፖለቲካዊ ለውጦችን በመረዳት፤ ወቅታዊና ዘመናዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ወደ አገራችን እንዲገባ በተለይም ወጣቱንና ምሁራኑን በማንቃትና ለለውጥ በማነሳሳት ረገድ እነ ኃይሌ ፊዳ የዘመናቸው አይረሴ ከዋክብት ነበሩ። በአገራችን የፊውዳሉን ሥርዓትም ሆነ ወታደራዊ አገዛዙን ለማስወገድ በተደረገው ትግል፣ ለብሔሮች እኩልነት፣ ለዜጎችና ለቡድን መብት መከበር በተለይም ለኦሮሞ ሕዝብ መብት መከበር ከተዋደቁ ቀደምት ታጋዮችና ሰማዕታት መካከል እነ ጀነራል ታደሰ ብሩ፣ ኤሌሞ ቂልጡ፣ ባሮ ቱምሳና ሌሎች በርካታዎችን ማንሳት ይቻላል።
እነዚህ የኦሮሞ ልጆች በአንድ በኩል ለኦሮሞ ሕዝብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ባሕል፣ ቋንቋና ታሪክ መዳበር በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነትና በአንድነት ጠንካራ አገርን ለመገንባት እንዲችሉ እጅግ ውድ የሆነውን የሕይወት መስዋዕትት የከፈሉ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው።
የኦሮሞ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ያገኙ ዘንድ የዛሬ 50 ዓመታት ገደማ የተመሰረተው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ለዚህ ሕዝብ ጥያቄዎች አንዳች መፍትሔ ያስገኛል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። በርካቶችም ለሕይወታቸው ፍጹም ሳይሳሱ መራር መስዋዕትነት ከፍለውለታል።
ኦነግ ከተመሰረተ የአንድ አዛውንት ዕድሜ ቢያስቆጥርም አለመታደል ሆኖ አሁንም ድረስ በመስራቾቹ እየተመራ ይገኛል። ታላቁን የኦሮሞ ሕዝብ የዓመታት ደጀንነት ቢታደልም በመሰነጣጠቅና በሽንፈት ባሕሉ፣ በበታችነትና በጠባብ ትርክቱ ተተብትቦ ሕዝቡንና ዘመኑን የሚመጥን የትግል ስልት መከተል ባለመቻሉ የኦሮሞን ሕዝብ ትግል መድረስ ከነበረበት እጅግ ወደኋላ እንዲቀር አድርጎታል። ይልቁንም ድርጅቱ ለመሪዎቹና ለቤተሰቦቻቸው የአውሮፓና አሜሪካ ኑሮ ማደላደያና ጥገኝነት መጠየቂያ ሆኖ ኖሯል።
ኦነግ በየወቅቱ ላጋጠመው የመሰነጣጠቅና የመከፋፈል አደጋ በውስጡ የነበሩ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚነግዱና የኦሮሞ ሕዝብ ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲራመድ የማይፈልገው የህወሓት ቅጥረኞች ሚና ከፍተኛ ነበር። ህወሓት በኦነግ ውስጥ ቅጥረኞቹን አስርጎ በማስገባት አመራሮቹ መረጋጋትና አንድነት እንዳይኖራቸው በማድረግ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በትጋት ሰርቷል። በተለይም ኦነግ እንደ ድርጅት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተዛባ አቋም እንዲይዝ በማድረግ በኩል ህወሓትና የህወሓት ቅጥረኞች ለዓመታት አሲረዋል። ለከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲያቸው በሚያመች መንገድ የኢትዮጵያ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲደበዝዝ አድርገዋል።
ኦነግ ከአስርት ዓመታት ውጤት አልባ ጉዞ በኋላ በጊዜው በነበሩ ኃይሎችና በኢትዮጵያ ሕዝቦች ድጋፍ የደርግን መንግሥት ካስወገዱ በኋላ በትግሉ አስተዋጽኦ ሳይሆን በኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር ተሰልቶለት የሽግግር መንግሥቱ ሁለተኛ ባለ ብዙ መቀመጫ ድርጅት ሆነ። ወያኔ ሲጀመር ኦነግ በሽግግር መንግሥት በስፋት እንዲሳተፍ ያደረገው የኦሮሞን ሕዝብ ይሁንታ ለማግኘት እንጂ ለኦነግ ክብርም ቦታም ኖሮት እንዳልነበር ሁሉም ያውቀዋል። ይህ እውነታ የተገለጠው በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ወያኔ ኦነግን እንደ አሻንጉሊት ሲጠቀምበት ከቆየ በኋላ አሁን ሸኔ ሆኖ የወጣውንና በኦነግ ውስጥ አንጃ ሆኖ የቆየውን ጸረ-ኦሮሞና ጸረ-ኢትዮጵያ ቡድን በመጠቀም የድርጅቱን መሪዎች፣ አባላትና ሰራዊቱን በማሰር፣ ከአገር በማባረርና በመግደል ከጨዋታ ውጪ ሲያደርገው ነው። ኦነግም ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በህወሓትና በውስጡ ባሉ ቅጥረኞች ደባ በውስጡ የዓላማ አንድነትና ጽናት እንዳይኖረው ተደርጎ ከአዲስ አበባ ብሎም ከምድረ ኢትዮጵያ ተጠራርጎ እንዲወጣ ተደረገ። ዘወትር ስህተት መስራት እንጂ ከስህተቱ ተምሮ የማያውቀው ቅጥረኛ አንጃም ከህወሓት የተሰጠውንና ኦነግ እንዳያንሰራራ ሆኖ እንዲንኮታኮት የማድረግ ግዳጁን ፈጸመ። በዚህ ድርጊቱም የኦሮሞን ሕዝብ አሳፈረ አንገትም አስደፋ።
የወያኔን አፈና ከጅምሩ የተረዳው የኦሮሞ ሕዝብ በተለይም ወጣቶችና ምሁራን በጻዕረ-ሞት ላይ ለነበረው ኦነግ ነፍስ ሊዘሩበት ብዙ ደከሙ፣ ከባድ መስዋዕትነት ከፈሉ። የኦሮሞን ሕዝብ ቀልብ መግዛት ያልቻለው ወያኔም የኦሮሞን ሕዝብ ይበልጥ አንገት ለማስደፋትና ለማፈን በአንድ በኩል በኦነግ ውስጥ ቅጥረኞቹን አሰማርቶ ድርጅቱን እያፈረሰ በሌላ በኩል ደግሞ ኦነግን እንደ ድርጅት በሽብርተኝነት ከፈረጀ በኋላ ጥያቄ ያነሳን ኦሮሞ ሁሉ በሽብርተኝነት መፈረጅና ማሳደድ ጀመረ። በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ምሁራን በጅምላ በእስር ቤት እንዲታጎሩ አደረገ።
በማሰቃያ እስር ቤቶች ፍዳቸውን እንዲያዩ ሆነ። በርካቶች በቀያቸው ተረሸኑ፤ እነ ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳና ሌሎች በርካቶች በእስር ቤቶች ውስጥ ተገደሉ። እነ ከፍያለው ተፈራ ሁለት እግራቸው ተቆርጦ ተጣለ፤ በርካቶች ተኮላሹ። አሸባሪው ህወሓት የእነ ነዲ ገመዳን ደብዛም አጥፍቷል። በርካታ ባለሀብቶች ንብረታቸው ተዘርፎ ወደ ድህነት እንዲመለሱ አድርጓል። በሺዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ ኦነግ በሚል ታፔላ ሽብርተኛ እየተባሉ ከትምህርት ገበታቸው ተባርረዋል። ሌላም…ሌላም…ብዙ ገፍ ተፈጽሟል። በኦሮሞ ልጆች ላይ በኦነግ ስም ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስ ኦነግ ውስጥ ሆነው ለህወሓት ያደሩና መረጃ የሚሰጡ ቅጥረኞች ሚና ከፍተኛ ነበር።
ከብዙ መፈረካከስ የተረፉት ጥቂት መሪዎቹ ከነቤተሰቦቻቸው ባህር ማዶ እየኖሩ በኦሮሞ ወጣቶች ድጋፍ ዳግም ለመንቀሳቀስ የሞከረው ኦነግ አብዛኛው አባላቱና ሰራዊቱ በኤርትራ በረሃ ሲንከራተት 50 ዓመት ሊሞላ ጥቂት ጊዜ ቀራቸው። በዚህ ወሳኝ ወቅትም በስም ብቻ የቀረው ኦነግ ምንም ሊፈይድ እንደማይችል የተገነዘበው የኦሮሞ ቄሮና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የነበረው የለውጥ ኃይል አዲስ የትግል ስልት ቀይሰው ተነሱ። የኦሮሞ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ አተኮሩ። የትግል አጋሮቻቸውንና ዋና ጠላታቸውን ለይተው ተረባረቡ። ኦነግ ያደበዘዘውን የኦሮሞን ኢትዮጵያዊነት አፈኩት።
ኦሮ-ማራ ብለው የኦሮሞን ሕዝብ በህወሓት ክፉኛ ከተገፋውና ከተጎዳው የአማራ ሕዝብ ጋር በነፃነት ትግል አስተሳሰሩት። ለድልም በቁ። ይህ ድል ግን በቀላሉ የተገኘ አልነበረም። ከ5000 በላይ የኦሮሞ ቄሮዎች የተሰውበት፤ የዚህ እጥፍ የሚሆኑት ደግሞ ለአካል ጉዳት የተዳረጉበት ነበር እንጂ።
ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም. ተቀጣጥሎ በነበረው ፋታ የማይሰጥ የቄሮ ትግልና ከአማራ ወጣቶች ጋር የተፈጠረው የተቀናጀ ተጋድሎ ያበሳጨው የትናንቱ የመንግሥት ቃል አቀባይ፤ የዛሬው የሽብርተኛው ጁንታ አፈ-ቀላጤ ጌታቸው ረዳም በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል ለኦነግ የነበረውን ንቀት ገልጾ ነበር «50 ዓመት ሙሉ በኢትዮጵያ ትልቅ የሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ አርሶአደር ማታገል ሳይችልና የረባ ነገር ሳይሰራ ዘር በመቁጠር ብቻ የኖረን ድርጅት ባንዲራ ጥቂት ሰውም ቢሆን ይዞት መመልከት የሥርዓታችንን ድክመት ያሳያል» ከማለትም አልፎ ከአራት ኪሎ ፈንቅለው ያባረሩትን ቄሮዎች «ጂኒ»የትግሉን መሪዎች ደግሞ «ጠንቋዮች» በማለት ለትግሉና ለኦሮሞ ሕዝብ የነበረውን ንቀት በእብሪት ገልጾ ነበር።
በዛው ሰሞን ጌታቸው ረዳ እሳትና ጭድ የነበረው የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ እንዴት ሆኖ በሥርዓታችን ላይ አንድ ሆኖ ሊነሳ ቻለ? በማለት ሁለቱን ሕዝቦች እሳትና ጭድ ለማድረግ በብዙ እንደደከሙ ነግሮን ነበር። የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ለማኮላሸት የቆረጠው የወያኔ መንግሥት በመስከረም 2009 ዓ.ም የኢሬቻን የምስጋና በዓል ለማክበር በወጡ ከ700 በላይ የኦሮሞ ልጆች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ስለመፈጸሙ ኦነግ ብቻ ሳይሆን ዓለም በሙሉ የተመለከተው ነበር።
አፋኙ ወያኔ ከአራት ኪሎ ከተወገደ በኋላ የመግባቢያ ቋንቋቸው ኦሮምኛ ሆነው የነበሩ እስር ቤቶች ባዶ ሆኑ። በኦነግ ስም ለዓመታት በከባድ እስር ቤቶች ሲማቅቁ የነበሩ የኦሮሞ ልጆች ነጻነታቸውን አገኙ። ኦነግም የሽብርተኝነት ፋይሉ ተዘግቶለት ወደ አገር ቤት ገብቶ ሰላማዊ ትግል እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበለት። ከስህተት መማር ያልፈጠረበት የጥፋት አንጃው ግን ጥሪውን ተቀብሎ ወደ አዲስ አበባ ከገባ ጀምሮ ሁከትና አመጽ ተለይቶት አያውቅም ነበር።
ይህ አንጃ በጫረው እሳት የኦሮሞ ወጣቶች ከሌሎች የአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር እንዲጋጩ፣ ደም እንዲፈስ፣ ሕይወት እንዲጠፋ አድርጓል። አንድ ጥይት ያልተኮሰበት ጠብመንጃውን ይዞ በሰላም ከገባ በኋላ አንድ እግሩን ፊንፊኔ አስቀምጦ ሁለተኛ እግሩን ደግሞ ሸኔ አድርጎ ወደ ጫካ በመግባት ንጹሃንን ማረድና ማፈናቀሉን ተያያዘው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የህወሓትና የቅጥረኛው ሸኔ አንድነትና የቆየ ጥምረት ይፋ እየሆነ መጣ። ሁለቱ ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች እየተናበቡ አገራችንን ለማፍረስና በሺዎች መስዋዕትነት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰውን የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ለመቀልበስ መረባረባቸውን ቀጠሉ። ሸኔ ህወሓት መቀሌ ከትሞ በነደፈው አገር የማፍረስ ፕሮጀክት ተባባሪና ዋና ፈጻሚ ሆኖ ተገኘ። የወያኔ የይስሙላ ምርጫ ሚዜና አጃቢ ሆኖ የኖረው የነመረራ ጉዲናው፣ የነ በቀለ ገርባው ኦፌኮን ጨምረው የመቀሌው አገር በታኝ ፕሮጀክት ማሕበርተኛነታቸውን ግልጽ አደረጉ።
እንቁው የኦሮምኛ ቋንቋ አቀንቃኝ፣ አገር ወዳዱና ታጋዩ ሀጫሉ ሁንዴሳ ይህን የአፍራሾች ማሕበር በመታዘብ እንዲህ ብሎ ነበረ «ምንም ያህል ፖለቲካ ልታውቅ ትችላለህ፤ እናም ምሁር ልትሆን ትችላለህ። ነገር ግን ኦሮሞ ሆነህ መቀሌ ሄደህ ከወያኔ ጋር ለመስራት ማሰብ ቅሌት ነው» ብሎ ነበር። ለምን? ተብሎ ሲጠየቅ «የወያኔ እጅ በኦሮሞ ልጆች ደም የተጨማለቀ ነው፡ ጉማ (ደም) በመካከላችን አለ። እንደ ባሕላችን ይቅርታ ጠይቀው እርቅ ባልተፈጸመበት ከእነርሱ ጋር ተባባሪ መሆን እነሱ የፈጸሙትን በደል መድገም ነው። » ሲል እንደ ዜማው በሚጣፍጥ አንደበቱ አስረድቷል።
ይህ ታሪካዊና እውነተኛ ንግግሩም ሁለቱን ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኦሮሞ ኃይሎች ክፉኛ አስቆጣ። በመሆኑም አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ የህወሓትን ትዕዛዝ በተቀበለውና በግፈኛው ሸኔ እንዲገደል ምክንያት ከመሆኑም በላይ ራሱ ከገደለ በኋላ የሀጫሉ ተቆርቋሪ በመምሰል በኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ በተለይም አማራዎችን በግፍ በመግደልና ንብረታቸውን በማውደም በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ቅራኔ በመፍጠር አገር የማፍረስ ፕሮጀክቱን ሊተገብር ሞክሮ ነበር።
በእርግጥ በኦነግ ውስጥ የታገሉት ሁሉ አፍራሾች ነበሩ ማለት ተገቢ አይሆንም። በበቂ ዓላማና ምክንያት ሲታገሉ የነበሩ አንጋፋዎቹ የኦነግ መስራቾችና መሪዎች እነ ሌንጮ ለታ፣ እነ ሌንጮ ባቲ፣ እነ ገላሳ ዲልቦ፣ እነ ዲማ ነገዎና ሌሎችም በተደጋጋሚ እንዲህ ሲሉ ተደምጠዋል፡- «አሁን የኦሮሞን ሕዝብ መብት ለማረጋገጥ የሚያስችልና ለዘመናት ጥያቄዎቹም ምላሽ የሚሰጥ ሥርዓት ተፈጥሯል። ስንታገል የኖርነውም ለዚህ ነው። ጥያቄው ከተመለሰ ያለ ዓላማና ያለ ምክንያት በተቃርኖ መቆም ሕዝባዊነት አይደለም። የኦሮሞን ሕዝብም ኢትዮጵያንም ይጎዳል። » ሲሉ ኦነግ ሸኔ ከጥፋት መንገዱ እንዲመለስ ደጋግመው መክረዋል። ሸኔ ግን ይህ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ድል ለማጨናገፍና ሰላማዊ መንገዱን እምቢ ብሎ ጫካ በመግባት አሁንም ንጹሃንን እየጨፈጨፈ ይገኛል፣፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ገድሏል።
ሸኔ ለአገራችን ህልውና የተዋደቁትን የነ አብዲሳ አጋን፤ የነ ታደሰ ብሩን፣ የነ ደጃዝማች ባልቻን አሻራ ለመፋቅ ዛሬ በተቃራኒው ቆሟል። ስህተትም ባህሉ ሆነና ዛሬ ከገደል አፋፍ ላይ ካለው ጁንታ ጋር ቀደም ብሎ ያሰረውን ቃልኪዳን በጋብቻ ደምድሟል።
ይህም የሸኔ የጥንት የጠዋት ባህሪው ነው። ኢትዮጵያ ፈተና ላይ በወደቀችበት ጊዜ ሁሉ ጀርባዋን ከመውጋት ተመልሶ አያውቅም። ከህወሓት ጋር የፈጸሙት ጋብቻም የሚገርም አይደለም። ባሕሪያቸው፣ አፈጣጠራቸውና የቆየ የኦሮሞን ሕዝብ ትግል የማምከንና ኢትዮጵያን የማፍረስ ግባቸው ነው አንድ ያደረጋቸው።
እንደሚታወቀው የወያኔ ዓላማ እኔ ያልገዛኋትና ያልዘረፍኳት ኢትዮጵያ ትፍረስ የሚል ሲሆን የቃልኪዳን አጋሩ ሸኔ ደግሞ እኔ ያልተጨማለቅኩባት ኦሮሚያ ኢትዮጵያን ይዛ ትፍረስ ነው። መጠነኛ ልዩነታቸው ወያኔ ኢትዮጵያን አፍርሼ በፍራሿ ላይ ታላቋ ትግራይን ልመስርት እያለ ሲሆን ሸኔ ደግሞ ኦሮሚያ ኢትዮጵያን ይዛ ትፍረስ የሚል ነው። ዞሮ ዞሮ ዋናውና የጋራ ግባቸው ግን ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው።
ሸኔና ክፉ እጢ/እባጭ አንድ ናቸው። እባጭ በወፈረ ስጋ ውስጥ ከተደበቀ አይታይም። ውስጥ ውስጡን ግን እያደገና ሰውነትን እያዳከመ ካንሰር ሆኖ ለሞት ሊዳርግ ይችላል። በሆነ አጋጣሚ ስጋ ተጎሳቁሎ ሰውነት ሲከሳ እጢው/እባጩ ተለይቶና ፍንትው ብሎ ይታያል። በዚህ ጊዜ የእጢው ዓይነትና ህክምናውም በቀላሉ ሊታወቅ ይችላል። እንደ ሁኔታው በቀዶ ጥገና ተቆርጦ ሊጣል ይችላል። ወይም ደግሞ በጨረር ተቃጥሎ እንዲሞት ይደረጋል። ለሰውነትም ዘላቂ ፈውስ ይሆናል።
ሸኔም እንደዚሁ በትልቁ የኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ተደብቆ ኖሯል። ዓላማውም አገር ማፍረስና የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ከጁንታው ጋር ሆኖ ወደ ኋላ መመለስ ሆኖ ሳለ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነኝ በማለት ብዙዎችን አደናግሯል። አሁን የኢትዮጵያና የኦሮሞ ሕዝብ ፈተና ላይ ሲወድቁና የሕልውና አደጋ ሲገጥማቸው አጋጣሚ ያገኘው እባጩ ሸኔ በሚገባ ከኦሮሞ ሕዝብ ተነጥሎ ታየ። ማንነቱም ፍንትው ብሎም ወጣ። እንግዲህ መድኃኒቱም ታውቋል። እንደ እባጩ ቆርጦ መጣል ወይም ማቃጠል ነው። ይህ ፈተና መሰል መልካም አጋጣሚም በእባጩ ሸኔ ለሚሰቃየው የኦሮ ሕዝብ ፈውስ ለኢትዮጵያም ድህነት ይሆናል!
አቡሌ ከጉለሌ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም