ሰላም ወዳጆቼ! በጥንት ጊዜ ከአበቦች ሁሉ የተለየች አንዲት ጽጌረዳ አበባ ነበረች አሉ፡፡ ይቺ ውብ ጽረጌዳ አበባ መልካም ምድራዊ አቀማመጡ ባማረ፣ በተራራማ ለእይታ እጅግ ማራኪ በሆነ ስፍራ ላይ መበቀሏ ይነገራል፡፡ አበባዋ የበቀለችበት ስፍራ ተመልካችን የሚስብ ውበትና ማራኪ ገጽታ ያለው ከመሆኑም በላይ፤ የሰው ልብ የሚያሸፍት በቃላት ሊገለፅ የማይችል ሽታንም ፅጌረዳዋ ታድላለች፡፡
ታዲያ መዓዛዋ ከሩቁ የሚጣራውን ጽጌረዳ አበባ ለማየት የማይጓጓ አልነበረም፡፡ እዩኝ እዩኝ ፤ አሽትቱኝ አሽትቱኝ ፣ መዓዛዬን አጣጥሙት ብላ የምትጣራዋን ጽጌረዳ አበባ በቀላሉ መጠጋት እና የራስ ማድረግ አይቻልም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ስለውበቷ እና መዓዛዋ ሰምተው፤ እሷን ለማየት የሚጎርፉ ሰዎች ስፍር ቁጥር አልነበራቸውም፡፡ ብዙዎቹ ስለ አበባዋ ከሰሙት በላይ በቦታው ተገኝተው አይተው ከሩቅ አድንቀዋል። ይቺን ውብ ጽጌሬዳ አበባ የራሱ ለማድረግ ያልደከመ ያለም። ብዙዎች እረፍት የለሽ ምልልስ በማድረግ በከንቱ ሲደክሙ ኖረዋል፡፡ ምንም እንኳን አንድም ሰው ፅጌሬዳዋን ቀርቦ ቀጥፎ ውበቷን በኮቱ ኪስ ላይ ሰክቶ ሊደምቅባት ባይችልም ነጋ ጠባ አይናቸውን ከእርሷ ላይ ሳይነቅሉ ቀርበው ለመቅጠፍ የሚችሉበትን መንገድ ፈለጋ መድከማቸው አልቀረም፡፡
ወዳጆቼ! ይህች ተዓምረኛ ጽጌረዳ አበባ ለፈላጋዎቿ ፈተና የሆነችው እንዴት ነው የሚል ጥያቄ ማንሳታችሁ አይቀርም፡፡ እንግዲህ ፈላጊዎቿ እንደፈለጉት እንዳያገኟት ጽጌረዳ አበባዋ የበቀለችበት ስፍራ ለየት ያለ ዙሪያዋ በእሾህ የታጠረ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገርም እጅግ የሚያስገርመው ስፍራው በተፈጥሮ የተቸረው፣ ለምለም መስክ ፣ ያልተነካ ድንግል መሬት ፣ የስልጣኔ መገለጫ ፣ የታሪክ እምብርት፣ የሰውልጅ ዘር መገኛ ምድር እና ብርቅዬ መሰዕቦች ባለቤት ሆኖ መገኘቷ ነው ፡፡
እናንተዬ ! እንግዲህ የፈላጊዎቿ መብዛት ሚስጥር ያለው እዚህ ጋር ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ በዙሪያዋ ያሉ ፈላጊዎቿ አይናቸውን ከላይዋ ላይ ባይነቅሉ ምን ይገርማል? ይልቅስ በእጅጉ የሚያስገርመው ይቺን የመሰለች እንቁ እንዴት ሊያገኟት እና ሊቀጥፏት አልቻሉም የሚለው ነው። ጽጌረዳዋ መቼ የዋዛ ሆነችና በዙሪያዋ ያለው የእሾህ አጥር በቀላሉ የሚፍረከረክና የሚከፋፈት ስላልሆነ ማንም ደፍሮ ሊነቀንቀው ባለመቻሉ ነው፡፡ እሾሁ በአንድነት ስንሰለት የተሳሰረ በመሆኑ አንዱን ከአንዱ ለመለየት በፍጽም የማይቻል ነበር፡፡ ፈላጊዎቹ ግን እሾሁን በመለያየት መግቢያ ቀዳዳ ለማብጀት በጣም ለፍተዋል ፤ ደክመዋል ፡፡ ሆኖም ግን ለአንድ ጊዜ እንኳን እድሉን አግኝተው ከውበቷ ፀዳል ሊቋደሱ እና ሊደምቁባት አልታደሉም፡፡ በፍጽም ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡
አንዱን ከአንዱ ለይተው መግቢያ ቀደዳ አግኝተው እጃቸውን ወደ ውስጥ ለመስደድ ሲሞክሩ እሾሁ እጃቸውን እየወጋ፤ ቆራርጦ ያስቀረዋል። እጃቸው ሰደው በሰላም የተመለሱ በታሪክ አለመኖራቸው ይነገራል፡፡ ሽንፈታቸውን ተቀብለው መቀምጥ ያቃታቸው ደግሞ ያለ የሌላ ኃይላቸውን በመጠቀም የተለያየ ዘዴ ተጠቅመው በገዛ ቅርንጫፏ አበባዋን ለመቁረጥ እጃቸውን ቢሰዱም እሾሁ ጋሬጣ ሆኖ እጃቸው እያደማ ዳግም እጃቸውን እንዳይሰዱ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣቸዋል:: ሆኖም ግን ፈላጊዎቿ ጽጌረዳዋን ለመቁረጥ አጥሯን ከመነቅነቅ አላረፉም። ለአንዲትም ቀን አጥሩን ሳይነቀንቁ ውለው አያውቁም። የጽጌረዳዋን እጣ ፈንታ ለመወሰን በእጅጉ ቢቸኩሉም አጥሯን ከመነቅነቅ በዘለለ ውስጥ ገብተው የሚፈልጉትን አንዲት ነገር እንኳን ማድረግ ባለመቻላቸው በቁጭት እየተብሰለሰሉ ኑሯቸሯ ቀጥለዋል ይባላል፡፡
ወዳጆቼ! ይህንን ታሪክ ያለምክንያት አላወጋ ኋችሁም። ዛሬ ላይ በሰለጠነው ዓለም የስልጣኔ ማማ ላይ ነን የሚሉ ኃያላን አገራት ልክ እንደ ጽጌረዳዋ አይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ተክለዋል። ከሩቅ ሆነው አጥሯ እየነቀነቁ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ልዕል ኃያላን ሀገር ከአፍሪካ ቀንድ ከሚገኙት ሀገራት በቀዳሚነት የሚትጠቀሰው ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት ሰጥተው አይናቸውን አፍጥጠው፤ ጥርሳቸውን አግጥጠው የተነሱበት ጊዜ ነው፡፡
ምዕራባዊያኑ አፍሪካ እንደ ቅርጫ ስጋ በመከፋፈል በቅኝ ግዛት ይዘው ያገኙት ትርፍ ዛሬም ከውስጣቸው የወጣ አይመስልም፡፡ እነሱ የሚጸየፉትን ጥንታዊውን ባርነት ወደ ዘመናዊ ባርነት በመቀየር በእጅ አዙር የሚያደርጉት የእጅ አዙር አገዛዝ ለማስፈን የማይወጡት ዳገት፤ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። በተለይ ኢትዮጵያ የጥንቱ የጥቁር ህዝቦች የባርነት ሰንሰለት በጣጥሳ የጣለች ሀገር መሆኗ ቁጭት ውስጥ የከተታቸውንና ራስ ምታት ሆኖባቸው የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያን የሚያንበረክኩበት መንገድ ሲፈልጉ የኖሩት፡፡
ወዳጆቼ! እጅግ የሚያስደንቀው ጉዳይ እኮ ነው! እራሳቸውን የዲሞክራሲና ስልጣኔ ባለቤት አድርገው ኋላቀርና ደካማ የሚሏቸውን ቀና እንዲሉ ስለማይፈልጉ በሀገራቱ መጠቀም የሚፈልጉ እነሱ ብቻ ብልጦች ሆነው መገኘት የሚፈልጉ የእውር ደንበሮች ናቸው እኮ!፡፡ ብልጣ ብልጥ ጫወታን በመጫወት ለራሳቸውና ለራሳቸው ብቻ ቅድሚያ የሚሰጡ በመሆናቸው የእጅ አዙር አገዛዝን ለመዘርጋት መረባቸውን ያሰፋሉ፡፡ ኧረ ምን ይሄ ብቻ በሌላው በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ጣልቃ ገብተው የሚፈተፈቱ እና መዳኘት የሚፈልጉ ደፋሮች መሆናቸው ቁልጭ ያለው ተግባራቸው ምስክር ነው።አሁን ላይ ደግሞ በእጅጉ ሀገራችንን እየተገዳደሯት ይገኛሉ፡፡ እንደፈለጉትና እንደሚመኙት አይነት አድርጎ ለመግዛት ያስቸገረቻቸውን በእጅ አዙር ለማስገባት የሚያስችላቸውን ስትራቴጂ ቀርጸው እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጥንት ጀምሮ ታሪክ እንደምንረዳ የማይተኙልን መሆኑን መረጃዎችን ማመሳከር ሳይስፈልግ የቅርብ ጊዜ ተግባራቸው በይፋ ያሳብቃል፡፡
አይኗን በጨው አጥባ ከፊታችን የምትቆመው አሜሪካም ብትሆን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገቸው ስውር ሴራ በታሪክ የተመዘገበ መቼም የማይረሳ ነው፡፡ በ1969 ዓ.ም በነበረው የሶማሊያ ወረራ ወቅት የዚያድ ባሬን መንግሥት በመርዳትና በመደገፍ ኢትዮጵያ የማፍረስ ድብቅ ሤራ ስትፈጽም እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ ሆኖም ግን ለጠላት እጅ ሰጥቶ የማያቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ስትረዳው የነበረችውን የሶማሊያን ጦር ድባቅ መትቶ፤ ድል ተጎኖጽፏል። ልክ በዕሾህ እንደተከበበችው ፅጌሬዳ ወታደሩ መከላከያው አገሩን ከቦ በማጠር ለጠላት እሾህ ሆኖ ኢትዮጵያን ከጥቃት እና ከመቀጠፍ ታድጓታል፡፡
የተንኮል ወጥመድ ውስጥ አልገባም ብላ ያስቸገረቻቸውን ሀገር ለማጥመድ በእጅጉ ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹እሾህ በእሾህ ›› እንዲሉ ከዘመነ ጥንሰሱ ጀምሮ ከጎኑ ሆና ስትደግፈው የነበረውን የህውሐት አሸባሪ ቡድን ጠበቃ ሆና ከተፍ ብላለች፤ አሜሪካ፡፡ አሜሪካ ሰውን መርዳት እንደምትፈልግ ለማስመሰል ብትሞክረም አልተሳካለትም፡፡ ‹‹ዶሮ ብታልም ጥሬዋን›› እንዲሉት ሆኖ የአሜሪካ ህልምና ምኞት የጠነከረውንና የማይናጋውን የኢትዮጵያውያን አንድነት አናግታ መንግስትን ሽባ በማድረግ ኢትዮጵያን ማፈራረስ ነው፡፡
በክፉ ልማዷ የምትታወቀው አሜሪካ እነአፍጋኒስታን፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ሶማሊያን የመሳሰሉ አገራት እንደፈራረሱት የኢትዮጵያን እጣፈንታ በእነርሱ መልኩ ለመደምደም መሞከር አይቻልም፤ ምክንያቱም በሾህ እንደታጠረችዋ ፅጌሬዳ ኢትዮጵያ ላትቀጠፍ ልጆቿ ተማምለዋል፡፡
እሾህን በሾህ ብላ እየተጠቀመችባቸው ያሉ የህውሃት የሽብር ቡድኖች የአሜሪካ ድጋፍ ‹‹ የአህያ ባል ከጅብ አያስጥል›› አይነት መሆኑን ከአፍጋኒስታን መማር አለባቸው።ከ20 ዓመታት በላይ የሸብርተኛ አውድማ እንድትሆን በአሜሪካ ሲሰራባት የቆየችዋ አፍጋኒስታን በመጨረሻ ዛሬ ስትጠቀምባቸው የነበሩ አፍጋኒስታናውያንን ጥላ ዜጎቿን ጠቅልላ ወጥታለች፡ ፡ አማጺያኑ መንበር ስልጣኑን ሲቆጣጠሩ እኔ አይገባኝም ብላለች፡፡ አሸባሪውን ህውሐት እንዲሁም ለማድረግ ያለመች ይመስላል፡፡
እናንተዬ! እንደዚች አገር ወራዳ የለም እኮ! የአገራትን ልኡዋላዊነት እስከመዳፈር ድረስ ሰተት ብላ የሰው ሀገር ከመግባት የማትቆጠብ ናት፡ ፡ ከአገራቱ በስተጀርባ በምታሴረው ስውር ሴራ የምትታወቀው ይቺ አገር ሰሞኑን ወደ ሀገራችን መልክተኞቿን ማመላለሳ ይዛለች፡፡ እንደውሃ ቀጂ በየጊዜው እየቀያየረች የምትልካቸው መልዕክተኞቿ የምትልከው ለምን ይሆን ብለን እንድንጠይቅ ግድ ይለናል። ወዳጆቼ! እስኪ ልብ በሉልኝ ሃያ ሰባት ዓመታት በሙሉ ኢትዮጵያ ዳግም እንዳታንሰራራ ቀብረው፤ በመለያየትና በመከፋፈል ሴራ ህዝቦቿን ለማያባራ ስቃይና መከራ ዳርገው፤ ህዝቡ በቃን ብሎ ከስልጣን ካወረዳቸው በኋላ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ለማድረግ የአሸባሪው የህውሐት ቡድንን አለሁልህ የምትል አገር ምን ትባላለች፡፡ አሁን ላይ ደግሞ መልዕክተኛን ማንጋጋት የምን አትርሱኝ ነው፡፡
ወዳጆቼ! ‹‹የጉድ ሀገር ገንፎ እየደር ይፈጀል›› ማለት አሁን አይደለም! የሳማንታ ፓውር ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አላማ ምን እንደሆነ በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል። ሳማንታ በቅድሚያ ወደ ሱዳን አቅንታ ከትግራይ የወጡ ስደተኞች አግኝታለች፡፡ በመቀጠል ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣቷ ሚስጥር በርካታ የተንኮል ሴራ የተሸረበ ቢሆንም አሜሪካ ላይ ሆና በፎከረችው ልክ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ግን በተመለከተች የኢትዮጵያኑ ቁርጠኝነት ደንግጣ ኮምሽሽ ብላ ወደ ሀገሯ ተመልሳለች፡፡ ተረኛው ደግሞ ለመምጣት በር በሩን እያየ መሆኑ እየተገለፀ፡፡
ኡኡቴ አሉ እማማ! ማማሰያ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥ እንዲሉ ፤ የሰዎቹ መቀያየር ምን እንደሚፈይድ ማየት ነው እንግዲህ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሁለተኛው መልዕክተኛ የኢትዮጵያን ምድር ለሦስተኛ ጊዜ ለመርገጥ መታደላቸው ነው፡፡ እኚህ ሰው የሀገራችንን ናፍቆትና የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት ከአይናቸው ላይ ድቅን እያለ ትዝታ ቢሆንባቸው እንጂ፤ ደጋግመው ለመምጣት መሞከራቸው ለሌላ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ እመጣለሁ ጠብቁኝ አይሉም ነበር።ወደው አይሰቁ አሉ! ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ እንዲሉት አይነት ሆኖ ተገኝቷል፡፡
እናም ሰውዬው! የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን መሆናቸውን ተነግሯል፡፡ ሰውዬው የሚመጡበት ምክንያት ምንጮች ሹክ እንዳሉት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ዳግሞ ላይመለስ እየተደመሰሰ ያለውን አሸባሪ ቡድን ህይወት ሊዘራበት ያሰበ ይመስላል፡ ፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የልዩ መልዕክተኛውን ጉዞ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ “ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም ለማስፈንና መረጋጋትን እንዲሁም ብልጽግናን ለመደገፍ ያሉ ዕድሎችን” በተመለከተ ውይይት የሚያደርጉ መሆኑን ጠቁሟል። አሜሪካ የኢትዮጵያን እጅ በመጠምዘዝ ለአሸባሪው ዋስ ለመሆን እየሞከረች ነው፡፡ እንደማይሳካለት እንኳን እያወቀች ከመጣር ወደኋለ ብላ አታወቅም፡፡
እኔ የሚገርመኝ ግን መቼ ይሆን እጇ ከሀገራችን ላይ የምትሰበሰበው የሚለው ነው፡፡ በዚህ ስትባል በዚያ እያለች ዙሪያችን እየተሸከረከረች ጊዜዋን ታባክናለችና እረፊ ማለት ካለብን ጊዜ አሁን ነው። ይቺ ዘለለ ዘለለ ለጣሊያን አላዋጣችም፡፡ ምነው ከጣሊያን መማር አቃታቸው። ‹‹የጣሊያንን ጠባሳ ያየ በእሳት አልጫወተም›› የሚለው የሀገሬ ሰው አባባል አሜሪካ አታወቀውም እንዴ ብትረሳ ብትረሳ የአፍሪካ ቀንዷን በማይነጥፍ መዝገብ የተጻፈውን የአድዋ ድል በፍጽም አትረሳም ባይ ነኝ፡፡
የአሜሪካ አሁናዊ ድርጊት ‹‹ይቺ ጎንበስ ጎንበስ እቃ ለማንሳት ነው ያሉትን›› የሀገሬ ሰዎች አባባል አስታወሰኝ፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ የተከፋፋለች መስሏቸው መግቢያ ቀዳዳ ፍለጋ ሲያፈላልጉ መቼም ቢሆን ያለሙት ምኞት እንደማይሰምርላቸው ሊያውቁት ይገባል፡፡ እንኳን ድንበሯ የደፈረ ይቅርና በሩን ያንኳኳውን እንኳን አይሆኑት ሆኖ በመጣበት መንገድ መመለስ አቅቶት ተቀብሮ መቅረቱን ታሪክ ያወሳል ፡፡
የምን አስታውሱኝ ማለት ነው! ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል ያበራች የአፍሪካዊያን ተምሳሌት የሆነችውን ሀገር ኢትዮጵያ በእጅ አዙር መጠምዘዝ አንበርክኮ ለዘመናዊ ባርነት ለመዳረግ የሚደረግ ሴራ በፍጽም ኢትዮጵያውያኑ እንደማይቀበሉት መረዳት አለባቸው፡፡
ምዕራባውያኑ የኢትዮጵያን ህዝቦች ገድል ረስተውታል የሚል እምነት ባይኖረኝም ሀገራቸው ጠልቆ ለገባ ቀርቶ ዳር ድንበሯን ለደፈረ የመለሱትን ምላሽ የታሪክ መዛግብት በማገላበጥ እንዲረዱት ልንመክራቸው ይገባል፡፡
እናንተዬ ! እስኪ እውነቱ የሚታየው ገለልተኛ የሆነ ወገን ይፍረደን፡፡ እኛ ያልነው የእኛ ለእኛ ተውልን በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እየገባችሁ አታቡኩ ነው። በማያገባችሁ አትግቡ የውስጥ ጉዳያችን የኛ ነው ብንል ሰሚ አጥተናል። እናም ! ምዕራባዊያን ሆይ እጃችሁን ከሀገራችን ጫንቃ ላይ አንሱ ልንላናቸው ግድ ይለናል። አትንኩን በመንገዳችን ጋሬጣ ከመሆን ገለል በሉልኝ እንበላቸው፡፡
ዛሬ ሚሊዮኖች ሆ! ብለው በአንድነት የተነሱት ሀገርን ለማዳን ነው፡፡ ከውስጥ ባውጪ ድጋፍ የተፈጠረውን ሀገር የማፈራረስ ሴራን በማክሸፍ ባንዳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ የኢትዮጵያ ልጆች በአንድነት ቆመዋል። አሁን ላይ ሀገር ለማደን እየተመመ ያለ ሀይል የሀገር ኩራት ሆኗል። እኛ ኢትዮጵያን የተጋረጠብን አደጋ በድል በመወጣት የኢትዮጵያን ትንሳኤ የሚረጋገጥበት ቀን ሩቅ አይሆንም። የምታጓጓዋ ፅጌሬዳ አበባ መቼም አትቀጠፍም ደግሞም አትረግፍም ምክንያቱም የኢትዮጵያ ልጆች እናታቸውን ለመጠበቅ ሁል ጊዜም ዝግጁ ናቸው፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም