ከተቋሙ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ የሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ልማትና እድገት የሚለካው በሰው ኃይል ላይ በሚደረገው የአቅም ግንባታ ሥራ ነው። ይህም ሀገራት ለህዝቦች እኩል መልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለሚያደርጉት ርብርብ የማስፈጸም አቅም ግንባታ ትልቅ መሣሪያ ነው። ከዚህም አኳያ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በነበረው የልማትና ዴሞክራሲ ሥርዓት የህዝቦች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ችግር የነበረ በመሆኑና ቅሬታው ጫፍ ደርሶ ህዝቡ ባደረገው የለውጥ እንቅስቃሴዎች ችግሩን ለማቃለል ጥረት አድርጓል። ለውጡ በአስተማማኝና በዘላቂነት ተግባራዊ በማድረግ ትናንት የነበረው የህዝቦች የልማትና ዴሞክራሲ እኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ በአግባቡ መመለስ የግድ ይላል። ይህ እውን እንዲሆን ከማድረግ አንጻር በአስተሳሰብና በተግባር የመምራትና የመፈጸም አቅሙ የተገነባ አመራርና ባለሙያ የግድ አስፈላጊ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በተለያዩ ጊዜያት የሰው ኃይል አቅም ለመገንባት የተደረጉ ርብርቦችና የመጡ ለውጦች ቢኖሩም እያደገ ከመጣው የህብረተሰቡ ፍላጎትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተጣጣመ ካለመሆኑም በላይ ተከታታይና ተመጋጋቢ ባለመሆኑ የተነሳ ችግሩን ሙሉ በሙሉ መቅረፍ ባለመቻሉ ህዝቡን ለተለያዩ እንግልቶች ዳርጎታል። በአገልግሎት አሰጣጡ ሂደት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች መኖር አለመኖሩ ለማረጋገጥ በተደረገው ሳይንሳዊ ጥናት ችግሩ ያለ ስለመሆኑ እና መንስኤውም የአመራሩና ባለሙያዎች የአመለካከትና ዕውቀት ክፍተት እንደሆነ ማረጋገጥ ተችሏል።
በሌላ መልኩ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና የታላላቅ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ዲፕሎማቲክ ተቋማት መቀመጫ ከመሆኗ አንጻር በከተማዋ የሚሰጡ አገልግሎቶች ውስብስብ፣ ሰፊና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠይቁ ከመሆናቸው በተጨማሪ በጥናትና ምርምር የተለዩ የአመራር እና የባለሙያዎች የአመለካከት እና የእውቀት ክፍተት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚስተዋሉ የማስፈጸም አቅም ክፍተት በስልጠና በመሙላት የማስፈጸም አቅሙን ማሳደግ ያስፈልጋል።
ከዚህም አንጻር የከተማ አስተዳደሩ ከላይ የተዘረዘሩ ችግሮቹን ለመፍታት ከሰራቸው ሥራዎች አንዱ በከተማው አስተዳደር የሚሰጡ አገልግሎቶች ለማሻሻልና ለነዋሪው ተደራሽ ለማድረግ መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ ጥናት በማድረግ ከተማ አቀፍ ተቋማዊ የአደረጃጀት ለውጥ ማድረጉ ነው። በዚህም የአደረጃጀት ለውጥ ለአዲስ አበባ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነት ዋና ዋናዎቹ በጥናትና ምርምር ግኝት ላይ ተመስርቶ የተቋማትን፣ የአመራሩና የባለሙያዎችን የመፈጸም አቅም በስልጠና መገንባት፣ ውጤታማ የማማከርና የማህበረሰብ አገልግሎትን መስጠት ሲሆን ይህንን ተልዕኮ ይዞ በከተማው የተለያዩ ተቋማት የሚስተዋሉ የማስፈጸም አቅም ውስንነት፣ የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩን መደገፍ ነው። በዛሬው እትማችን የአዲስ አበባ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት አሁናዊና ቀጣይ ስራዎችን አስመልክቶ ከኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃርጋሞ ሃማሞ ጋር የነበረን ቆይታ እነሆ።
አዲስ ዘመን፡- ስለተቋሙ አመሰራረትና አሁናዊ ገጽታ ቢገልጹልን?
አቶ ሃርጋሞ፡- ይህ ሥራ አመራር አመራር አካዳሚ ተብሎ ነበር ይጠራ ነበር። የተሰጠው ተልዕኮ የአመራርና ባለሙያ ስልጠና መስጠት ነው። በተለይም ደግሞ የመካከለኛ እና የጀማሪ አመራር እንዲሰጥ ታስቦ ነበር። በተጨማሪ ምርምር እና ጥናት ነበረው። ከዚህ ጎን ለጎን ትምህርት እንዲሰጥ የተቋቋመ ነው። በተለይም ሁለተኛ ዲግሪ እና ማማከር ሥራው በዋናነት የሚጠቀሱ ነበሩ። ጥናትና ምርምር፣ ማማከር፣ እንደ ትምህርት እና አካዳሚክ ተቋም የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጥና በዚህ አግባብ የተደራጀ ነበር። በእነዚህ ተልዕኮች መሰረት 10ሺ የሚበልጡ መካከለኛ አመራሮችን አሰልጥኗል። አመራሮችም ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና ደቡብ ብሄር፤ በሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የተሰባጠረ ሲሆን ይህም በፌዴራል አስተባባሪነት የሚካሄድ ነበር። አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ ድሬዳዋ ከተማን አቅፎ ይይዝ ነበር።
በወቅቱ ስልጠናው በሀገሪቱ ከተማ አቀፍ ፖሊሲ እና ሀገር አቀፍ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ነው። በመሆኑም አመራሩ በዚህ ላይ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ እይታ እንዲኖር ታስቦ የተሠራ ነው። ይህ ስልጠና ውጤታማ ነበር። ስልጠና ከመግባታቸውም በፊትና መውጫ ላይ ፈተና ይሰጥ ነበር። ይህም የአመራሩን ብቃት በሚገባ ለመረዳት ያግዛል። መመዘኛውም ሳይንሳዊ ነበር። በመቀጠል 2011 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጡ በኋላ በርካታ ለውጥ ስለነበር ይህ አስተሳሰብ አብሮ የመጣ ነው። ይህ ተቋም ደግሞ በአቅምና አስተሳሰብ ለውጥና ግንባታ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ይህን መሰረት ያደረጉ የመንግስት የአደረጃጀትና አስተሳሰብ ለውጦች ሲኖሩ አብሮ መቃኘት ያለበት በመሆኑ ተቋም እንደገና መፈተሽ ስለነበረበት እና በከተማ የነበረው የሥራ ድግግሞሽ ያለአስፈላጊ መዋቅር ለማስተካከል ከአካዳሚ ወደ ወደ ኢንስቲትዩት ሄዷል።
ኢንስቲትዩት ከመሆኑ በፊት ተቋሙ በቦርድ ይመራ ስለነበር እና በአዋጁ ላይ ደግሞ ትምህርት ማስተማር ይችላል ይላል። ስለዚህ ማስተማር አለበት ተብሎ ሃሳብ ሲነሳ በሀገር አቀፍ ደረጃ አሳስበን ተጀመረ። ነገር ግን ሌላ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምረውን ማስተማር የለብንም ብለን ተነሳን። ከተካሄደው ሀገር አቀፍ የፍላጎት ዳሰሳ ስናይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የከተማ ሥራ አመራር ትምህርት አይሰጥም። እኛ ደግሞ ከተማ ነው የምንመራው። ከተማ በአስተሳሰብ ካልተመራ አስቸጋሪ ነው። ከተማ አሰራርና አገልግሎት አሰጣጡ ‹‹ዳይናሚክ›› ነው። በእውቀት ካልተመራ አስቸጋሪ ነው። አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ቀጣናዊ፣ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ብሎም ብዙ ዲፕሎማቶች ያሉበት በመሆኑ ብዙ እይታና ሥራ ይጠይቃል። በመሆኑም በዚህ አግባብ መመራት ስላለበት አመራሩም አቅሙ ማደግ አለበት። በዚህ አግባብ ትምህርት መሰጠት አለበት ብለን ተነሳን።
የአመራሮቹ አመጣጥ እንዴት ነው ብለን ለማየት ሞከርን። አብዛኞቹ አመራሮች ከተለያዩ የሙያ ዘርፍ፣ አካባቢና ተቋም የሚመጡ ናቸው። ስለዚህ የተለያየ ፕሮፋይል ያለው አመራር ተናቦ ለመስራት ቢያንስ ከተማውን የሚመራበት አስተሳሰብ ያስፈልገዋል። በመሆኑም ሥርዓተ ትምህርት ታስቦ 12 ሞጁሎች ተዘጋጁ። ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት ላይ እያለን ግን ቦርዱ የፈረሰ በመሆኑ ትምህርት መስጠቱ አልቀጠለም በዚያው ተንጠልጥሎ ቀረ። ማስተማሩን ትተን ወደ የባለሙያና አመራር ስልጠና፣ ምርምር፣ ማማከር እና ሠራተኞች ጭምር የሚሳተፉበት ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ስልጠና የምትሰጡበት መስፈርት ምንድን ነው?
አቶ ሃርጋሞ፡- ስልጠና የሚሰጠው የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ተደርጎ ነው። እስከ ወረዳ ድረስ ሄደን የምናየው እንጂ ግለሰቦች ወይንም ተቋማት ስለፈለጉ ብቻ አይሰጥም። የራሳችንን ቼክ ሊስት አዘጋጅተን ተቋማት፣ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚፈልጉትን በሚገባ እንለያለን። በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ጥናት እናካሂዳለን። ካቻምና ባካሄድነው ጥናት 20ሺ ሰዎች በተቀራረቡ ኮርሶች ላይ ለመሰልጠን ፍላጎት አሳይተዋል። በ2013 በጀት ዓመት ብቻ 11 ሺ500 ባለሙያዎችና አመራሮች አሰልጥነናል። አብዛኞቹ ከወረዳ እና ክፍለ ከተማ የመጡ ናቸው። በተቋም ደረጃ ሲታይ ደግሞ 45 ተቋማትን ያካተተ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በሚያካሂዳቸው ጥናቶች እንደ ከተማ የተለዩ ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ሃርጋሞ፡– አዲስአበባ ያለው አመራር ኢንስቲትዩት ተልዕኮ እስከተጣለበት ድረስ ብዙ እንደሚጠበቅበት አስቦ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው። ከተማ ማህበራዊ፣ ከባብያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች በብዛት ይስተዋሉበታል። እነዚህ ሁሉ ቢያፈስልጉም የትኛው ከየትኛው ይቅደም የሚለውን ለማየት ሞክረናል። ከተማን የማወቅና መምራት ላይ በሚገባ መስራት ይገባል።
ከተማ የአካባቢውን ፍላጎትም ማወቅና መመራት ይፈልጋል። በዚህ እውቀት ካልተመራ የሚፈለገው ውጤት አይገኝም። የፖለቲካ ሹመኛ ፖለቲካዊ ነገሩን ሊመራ ይችላል ግን ኦፕሬሽናል ስራው በባለሙያ መመራት አለበት። ከዚህ አኳያ ስናይ አመራር በየጊዜው መለዋወጥና የሠራተኛ ፍልሰት በብዛት ይስተዋላል። በመሆኑም መመጋገብ መፈጠር አለበት። በብዛት ማስተዋል የቻልነው በርካታ አመራሮች ተቀራራቢ የመሆን ሁኔታ ይስተዋላል። ሁለተኛ የአደረጃጀት እና አሰራር ክፍተቶች ይስተዋላሉ። በመሆኑም ይህ በተቀናጀ ሁኔታ መመራት አለበት። ሌላው የከተማ አመራርነት በሚገባ አልሰረጸም። በመሆኑም ይህን በሚገባ ማጤንና መሥራት እንደሚገባ በመረዳት ይህንኑ መነሻ አድርገን ካሪኩለም አዘጋጀን። ትምህርቱን ባንቀጥልበትም አሁን ስልጠናው ላይ እየሠራን ነው።
ከጥናት ምርምርም ጋርም በተመሣሣይ መንገድ ነው። ሳይንሳዊ አሰራሮችን ነው የምንከተለው። ባለፉት ዓመታት የነበሩ ችግሮችን መድገም አንፈልግም። ጥናት ተካሂዶ መደርደሪያ ላይ ነው የሚቀመጠው። ጥናቶችን ፍላጎት ካላቸው ተቋማት ጋር ነው የምንሰራው። ብዙ ሥራዎችን የምናከናውነው በተናበበ መንገድ ነው። ጥናቶች መደርደሪያ ላይ እንዲቀመጡ አንሠራም። በመጨረሻ የሚጠናቀቀው የጥናት ውጤትም ተቋሙ ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲያስችለው ይሆናል። ወደ ውጤት መቀየሩንም እንከታተላለን። በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ችግሮች መመለስ ያለባቸውን አግባብ እንዴት ይመለሳል ለሚለው በስልጠና፣ ፕሮጀክት በመቅረጽ ወይስ በሌላ አግባብ የሚለውን እስመጨረሻው ድረስ ይሠራል። በመሆኑም የምንሠራቸው ጥናቶች የተለመደው ዓይነት ሳይሆን በተግባር የሚታይና ውጤት የሚያመጣ ነው። ናቶችን ስንሠራ እውቀትን ማስተላለፍ የሚለው ዓላማ አንግበን ነው። እኛ ተቋማት እራሳቸው ችለው እንዲሰሩና እንዲለውጡ ነው የምንፈልገው።
አዲስ ዘመን፡- ጥናትና ምርምር በጣም ጥልቅ ነው። ኢንስትቲዩቱ ይህን ሥራ የሚያከናውኑ የምሁራን ስብሰብ ይዟል?
አቶ ሃርጋሞ፡- ቆንጆ ጥያቄ ነው፤ ህመማችንም ነው። ነገር ግን ህመማችን ነው ብለን አላስቀመጥነውም። በሌላም መንገድ እየፈታን ነው። የጥናትና ምርምር ሥራ የተለያዩ የሙያ ባለቤቶችን ይፈልጋል። አንድ ጥናት ራሱ ብዙ ባለሙያዎችን ይፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የዳበረ ልምድ ያለው ሰው ይፈልጋል።ህ ሁሉ ጥምረትና ስብስብ እንዲሟሉ ደግሞ ተቋም አደረጃጀት አስፈላጊ ነው። የደመወዝ፣ የክፍያ ሥርዓቱ ወሳኝ ነው። ይህን የማይፈቅድ ከሆነ ለበጎ ተግባር ብሎ ማንም መጥቶ አይሠራም። በመሆኑም ይህ የእኛ ዋነኛ ችግር ነው። ግን ይህን ችግር ለማቃለል የምንከተለው አሰራር አለ። ከተለያዩ ተቋማት፣ እውቀትና ልምድ ካላቸው አካላት፣ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ የፌዴራል ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ ኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ ከኦሮሚያ አመራር አካዳሚ እና አዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ጋር በጋራ የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ።
አስተሳሰባችን ለክፍያ ሳይሆን ተቀናጅተን ሀገር እንገንባ በሚለው ላይ ያተኮረ ነው። በዚህ በአመራርና ባለሙያዎች ጭምር መግባባት ላይ ተደርሷል። የተወሰነ ክፍያ ይኖራል። ስልጠናውም ቢሆን በሙሉ አቅም አይደለም። ከዚህ አኳያም ፖሊሲያችን 30 በ 70 ነው። ይህ ተቋማችን 30 ከመቶ የሚሸፈን ሲሆን ቀሪውን 70 በመቶ ከተቋም ውጭ ነው የምናመጣው ብለን የተነሳነው። ይህን ስናስብ ከእጥረት አኳያ ብቻ ሳይሆን ከአስተዳደርም ጭምር ነው። ሙሉ ለሙሉ ለመቅጠር በዚያ ደረጃ ክፍያ መክፈል አይቻልም። ቢቻል እንኳ ስልጠና እና ምርምር በሌለበት ኪሣራ ነው የሚሆነው። በዚህ አግባብ አሰልጣኝና ተመራማሪዎችን እንጠራለን። ከውጭ በሚመጣው ኃይል ደግሞ ተጠቃሚ ሆነናል። ለእኛ ተመራማሪዎች የእውቀት ሽግግር ተፈጥሯል። ቀደም ሲል የሌላ ድጋፍ ይፈልጉ የነበሩ በራሳቸው ጥናት ማካሄድ ችለዋል፤ አቅም እየተገነባ ነው።
የአቅም ክፍተቱ በጣም ትልቅ ነው ቀጣይ ሊሻሻል ይችላል። ይህ የሆነው ቀደም ሲል አደረጃጀታችን በቦርድ ነበር በኋላ በመጣው አደረጃጀት ደግሞ በፐብሊክ ሰርቪስ ነው። ተጠሪነቱ፣ አደረጃጀቱ፣
የፕሮሞሽን ሥርዓቱ፣ አሰራሩ እና ክፍያው፣ በሙሉ በፐብሊክ ሰርቪስ ነው። አደረጃጀቱ የፈጠረው ጫና አለ። የሀገሪቱ ኢኮኖሚም የራሱ ችግር አለው። እኛ ይህን ችግር ለመፍታት ግን የተቻለውን ሁሉ እያደረግን ነው። ሆኖም በምንሰራው ስራ በከተማው ላይ ትልቅ አቅም ፈጥረናል።
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ የሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት ምን ላይ ያተኮረ ነው?
አቶ ሃርጋሞ፡- ይህ ጥናትና ምርምር ስናደርግ የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው አንዳንዶቹ ማማከር፣ የተወሰኑት በጥልቀት እንድንሠራ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም የተጎዳ ማህበረሰብ እንዳለ ያመላክታል። ለምሳሌ በከተማዋ ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ብዙ ጥያቄ የሚነሳበት ነው። የሚነሱት ችግሮች ከአሠራር፣ ከአደረጃጀት ወይስ ምንድን ነው ብለን ለማጥናት ሞክረናል። የተወሰኑ ሰዎች በልማት ተነሺዎች ሲኖሩ ቤት ቢያገኙም ከኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ቦንድ ይለያያሉ። ስለዚህ መልሶ ማልማቱ የተሟላ አይደለም። በመሆኑም በዚህም ቦሌ አካባቢ የተወሰነ ግሩፕ ይዘን ሥራ እየሠራን ነው። በስልጠና ጀምረን ወደ ቢዝነስ እንዲገቡ እያደረግን ነው። ይህ ለናሙና የተወሰደ ነው። ቀጣይ ሼድ እንገነባላቸዋለን። ሌላው ከተቋማት ጥያቄ በመነሳት የማህበረሰብ አገልግሎት እንሰጣለን። እንደ ተቋም ህፃናትን እናሳድጋለን፣ አቅመ ደካሞችንና የአዕምሮ ህሙማን፣ አካል ጉዳተኞችና ትምህርት ቤቶችን እናግዛለን። ይህን በቀጣይ እያሳደግን እንሄዳለን።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ ውስጥ ካሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አኳያ ኢንስቲትዩቲ ብቁ አመራር እያፈራ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ሃርጋሞ፡- ማብራራት ያስፈልጋል እንጂ መልሱ አጭር ነው፣ ብቁ አይደለም። አዲስ አበባ በጣም በፍጥነት የሚያድግ ፍላጎት ያለበት ከተማ ነው። ሁለተኛው ውስብስብ ፍላጎት ያለበት ነው። እያንዳንዱ ሲነካ ውስብስብ ነው። ውስብስብ የሆነው አገልግሎት ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ሰጪው ውስጥ ያለው አስተሳሰብ ጭምር ነው።
አዲስ አበባ የምትነፃፀረው ከዓለም ዕድገት ጋር ነው። በዚህ ልክ ያደገ አቅምና አስተሳሰብ ያለው ብሎም መልስ የሚሰጥ አመራር ያስፈልጋል። ይህ እንደሌለ ብዙ ጊዜ ያካሄድነው ጥናት ያመለክታል። ኮተቤ ሜትሮፖለቲያን እና አዲስ አበባ ባካሄዱት ጥናትም አመራር አካባቢ ችግር እንዳለ ያሳያል።
አመራሩ ቁርጠኝነት እና ውሳኔ ሰጪነት ያንሰዋል። የአሰራር ግልፅነት የጎደለው በመሆኑ ክፍተት ያሳያል ይላል። በመሆኑም በየጊዜው ችግሮች ራሳቸውን እየደገሙ ይሄዳሉ። መፍትሄም እስከመጨረሻው አይበጅላቸውም የሚል ነው። በመሆኑም በዚህ ደረጃ ያደገ አመራርና አደረጃጀት መፍጠር ይገባል። የእኛ ተቋም በዚህ ልክ አይደለም። እኛ በፐብሊክ ሰርቪስ ሥር ነው ያለነው። በመሆኑም ከውጭ የዳበረ ሰው አመቻችቶ ለመጥራት ስልጣን የለውም። ይህም በመሆኑ ከተማ ውስጥ ያለው አስተሳሰብና እኛ አካባቢ ያለው አስተሳሰብ ተመሣሣይ እየሆነ ነው። ግን የከተማዋን ችግር ለማቃለል አስተሳሰብ እያደገ መሆን አለበት፤ ለዚህ ደግሞ የሚያነብና የተሻለ የክፍያ ሥርዓት መፍጠር ይገባል። እንደዚህም ሆኖ እኛ ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው። በቅርቡ ሀገር አቀፍ ፓናል አካሂደን ነበር። በዚህ ትልቅ አድናቆትና ግብዓት፣ ልምድ ነው ያገኘነው። አሁን ባለን አደረጃጀት የሚመጣው ቀርቶ አሁናዊ የከተማዋን ችግር ለመመለስ ይከብደናል። አደረጃጀቱ ቢስተካከል ደግሞ ብዙ መሥራት እንደምንችል ተገንዝበናል። ዋነኛ ዓላማችን ግን ለሀገር እናገልግል በሚል ስለሆነ በተቻለን አቅም አሟጠን እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢንስቲትዩቱ ለችግሮቹ መፍትሄው ምንድን ነው ብሎ ያስባል?
አቶ ሃርጋሞ፡– ለከተማ አስተዳደሩም ከፍተኛ አመራር አቅርበናል። አደረጃጀቱ መሻሻል አለበት። አንደኛ በፐብሊክ ሰርቪስ አሰራር ሲመራ የተሻለ አቅም መገንባት አይችልም። ሁለተኛ የተለየ አሰራር እንዲኖር ከተፈለገ በቦርድ መመራት አለበት። የተለየ አሰራር፣ ጥቅማጥቅምና የተለያዩ ለውጦችን ተከትሎ እንዲሰራ አሰራሩን ማሻሻል ይገባል። የሁሉንም ተቋማት የሚገነባ አቅም በመሆኑ ተጠሪነቱ ደግሞ ለከንቲባ መሆን አለበት። በተለይም የሰው አስተሳሰብ ላይ የሚሰራ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል። ይህ ከፍተኛ ድጋፍና ክትትልም ይፈልጋል። በመሆኑም ባደገ አስተሳሰብ መመራት አለበት። በተለመደው አግባብም ሰራተኛ መሳብ፣ ማሳደግና መቅጠር አይቻልም። እኛ ዓመት ተቆጥሮ ነው ሰራተኛ የሚያድገው። ዓመት ተቆጥሮ ደግሞ ምርምር አይሰራም። በመሆኑም የተለየ ሥርዓት ሊኖር ይገባል።
ተቋሙ በተፈለገው መጠን ሰው እንዲያሰለጥን ከተፈለገ ግንባታዎች ያስፈልጉታል። ስልጠና እየሰጠን ያለነው ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ነው። ቢሮም ቢሆን በዓመት በ18 ሚሊዮን ብር ተከራይተን ነው። ይህ ወደ ልማት ቢገባ ብዙ ሥራ ያከናውናል። በመሆኑም ብዙ ድጋፍ ያስፈልገናል። እኛ በሳምንት 450 ሰልጣኞችን እናስገባለን ብለን እናስባለን። የተከራየነው ህንፃ ላይ ያለው ማሰልጠኛ ደግሞ 400 ሰልጣኞችን የሚይዝ ነው። ስለዚህ የሚቀረውን ለማሟላት ሌላ ቦታ መሄድ ይጠበቅብናል። ሌላው ስልጠና የሚሰጠው ቴክኒካል ጉዳይ ብቻ አይደለም።
ሰው ከተቋምና ጊቢ ውበት፣ አገልግሎትና እና አደረጃጀት ብዙ ይማራል። በሌሎች ሀገራት በጣም ምቹ የስልጠና ፋስሊቲ አላቸው። ስልጠና እውቀት መስጠት ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ነገሮችን በሙሉ ከግምት ውስጥ ያስገባል። ይህን ችግር ለማቃለል ጎሮ ላይ 10 ሄክታር ላይ የሚያርፍና በ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገነባ ህንፃ በ2008 ዓ.ም ተጀምሮ ነበር። 2014 መስከረም ይጠናቀቃል ተብሎ አሁን አፈፃፀሙ ገና 30 በመቶ ላይ ነው። ለዚህ መዘግየት በፍጥነት ውሳኔ አለመስጠትና ክፍያ ማዘግየት ናቸው። ለምን እንደዘገየ ለማወቅና ለመፍትሄው ሰባት ወራት ጥናት ተካሂዷል። አሁን ለከንቲባዋ ቀርቦ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ አቅጣጫ ተቀምጧል። በአጠቃላይ አሁን ባለው ሁኔታ ስልጠና እየሰጠን ነው የሚለው አስቸጋሪ ነው። ስልጠና ከፋሲሊቲና ከሰዎች ጋር አብሮ የሚሄድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በቀጣይ አምስት እና አስር ዓመታት ዕቅዶች ምንድን ናቸው?
አቶ ሃርጋሞ፡- ይህ ከተማው እያሰበ ካለው ጋር እና ከሀገራዊ እይታ ጋር አብሮ የሚቀናጅ ነው። ኢትዮጵያ ብቻዋን አድጋ የትም አትደርስም። ከአፍሪካውያን ጋር ወደ ተሻለ ደረጃ ማደግ ነው። እኛም የምናስበው ከዚህ አኳያ ነው። አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ ዙሪያና ወጣ ያሉ ክልሎች እና ከሌሎች ጋር ተቀናጅተን እንሠራለን። ለአብነት ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሰራን ነው። ከልሎች ተቋማት ጋር ተቀናጅተን ሀገር የመገንባት ሥራ እንሠራለን። አስተሳሰቡ ለውጡ ከከተማ ወጣ ያለና ሰፊ መሆን አለበት። እውቀትና ልምድ ከተለዋወጥን አንዳችን ለአንዳችን ካሳለፍን ትልቅ ሥራ እንሠራለን።
ሁለተኛው ይህን ተቋም በአዲስአበባ ዕድገት አግባብ ብቃት ያለው አመራር እንዲኖር ቀጣይነት ያለው አቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት ተቋማዊ አቅም ግንባታ መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህም አደረጃጀትና አሠራር በማሻሻል ዓለም አቀፍ ስም የተጎናፀፈ ተቋም ማድረግ ነው። በመሆኑም በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በአፍሪካ ቀንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አለበት ብለን ራዕይ አስቀምጠናል።
ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 22ሺ አመራሮችንና ባለሙያዎችን አፍርቷል። በ2013 በጀት ዓመት ብቻ 11 ሺ500 ባለሙያዎችንና አመራሮችን ማሰልጠን ተችሏል። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ደግሞ በአማካይ 20 በመቶ ማደግ አለበት ብለን አስቀምጠናል። ለስልጠናው ከፍተኛ ብር ወጪ እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታን ከአመራር አኳያ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ሃርጋሞ፡- በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ችግር ሆኖ የሚታየው ህወሓት እና ህወሓት የወለደው አመራር ነው። ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ሲታይ ከውስጣችን ሆኖ ከውጭ የሚመጡ የጥፋት ሥራዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ ሥራው በዚህ ደረጃ የተጋነነ አይደለም። በአሁኑ ወቅት ችግር ሆኖ የሚታየው አሸባሪው ህወሓት እና እሱ የወለደው አመራር ነው። የአሻባሪውን ህወሓት አስተሳሰብ የተቀበሉ፣ የሚያስተናግዱና የሚያሰራጩ ኃይሎች አሉ። እነዚህን ሁሉ ለመዳሰስና ለመገልበጥ በአጭር ጊዜ መሻገር አይቻልም። በመሆኑም የዚህን እኩይ አመለካከት ዋንኛ አቀንቃኝ የሆነውን ህወሓትን ማስወገድ ነው። ከውጭ የሚመጣው ጫናም በወያኔ ትከሻ ነው። ከውስጥም ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሰው ቡድን በወያኔ የሚመራና የሚደገፍ ነው። ደጋፊው፣ አሰልጣኝና የገንዘብ ምንጭ ይኸው ቡድን ነው። በመሆኑም ይህን ተልዕኮ የተሸከመውን ቡድን ማፍረስና ማሽመድመድ ይገባል።
ህወሓት አስተሳሰቡም ሕዝባዊ ሳይሆን ሀገር የማፍረስ ነው። ይህ አስተሳሰብ የሚደቆሰው ደግሞ አደረጃጀቱንና ኃይሉን በማፍረስ ነው። ይህ ካልሆነና አስተሳሰቡ ካልፈረሰ አደገኛ ሆኖ ይቀጥላል። ቡድኑ የሚኮተኩታቸው፣ የሚደጉማቸውና የሚያሰማራቸው የእኩይ ዓላማ አራማጆቹ የሰንኮፉና የአስተሳሰቡ ዋና ባለቤት የሆነው ራሱ ህወሓት ከተወገደ አብረው ይሞታሉ። ኢትዮጵውያን ከጁንታው በፊት ተዋደው፣ ተፋቅረውና አብረው ያሳለፉ በመሆናቸው በቀጣይ ሀገሪቱ ትልቅ ተስፋ ያላት ሀገር ናት። ይሁንና የሀገሪቱ ህዝብ አስተዋይና በሀገሩ ጉዳይ በጽናት የሚቆም ብሎም አርቆ አሳቢ በመሆኑ ችግሮችን በመቋቋም ኢትዮጵያን ከብተና የታደገ ህዝብ ነው።
በአመራር ዓይን ሲመዘኑም፤ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩበት ጀምሮ የተወሰነ ኃይል አደራጅቶ እንጂ ሀገራዊ እይታ አልነበረውም። እርስ በእርስም እየተበላሉና እየተገዳደሉ የመጡ ናቸው። የህወሓት አረመኔያዊ አካሄድ ለሀገር አይበጅም። ትግራይ ክልል ውስጥ ከ38 እስከ 40 ከመቶ የሚሆነው በድጋፍና በሴፍትኔት የሚታገዙ ሲሆኑ ለእነዚህ እንኳን መፍትሄ መስጠት ያልቻለ ስብስብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት አሁናዊና ቀታይ ገጽታዎች ብሎም ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብዎን ስላካፈሉን በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።
አቶ ሃርጋሞ፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12/2013