
ዓለም በርካታ ጨካኝና አረመኔ ቡድኖች አይታለች። ከሰው ልጅ ሞራልና ስብዕና ባፈነገጠ መልኩ የንጹሃን ደም የሚጠጡና በሰው ልጅ መከራና ስቃይ የሚረኩ በላኤሰቦች ዓለማችን በጉያዋ ታቅፋ ኖራለች፤ አሁንም የሀገራትና የህዝቦች መከራ ሆነው የንጹሃንን ደም ቀለብ አድርገው የሚኖሩ አልጠፉም፡፡
ቀደም ባሉት ዘመናት ከነበሩና አሁን ህልውናቸው ካከተመ አረመኔ ቡድኖች መካከል የካምቦዲያውን ኬሜሩዥ የሚስተካከል ያለ አይመስልም፡፡ እ.ኤ.አ. በ 1951 በድብቅ በካምቦዲያ የተፈጠሩት እና የተፈለፈሉት የኩመር ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ነን የሚሉት የኬሜሩዥ ዓማፅያን ዘግናኝና አረመኔያዊ ተግባራቸው የሰው ልጅ ይፈጽመዋል ተብሎ የማይታሰብ ነው። ይህን አረመኔ ቡድን እንድናስታውሰው ካደረጉን አበይት ጉዳዮች አንዱ በአረመኔና በአጸያፊ ድርጊቱ ከአሸባሪው ህወሓት የሚመሳሰሉበት ጉዳይ በርክቶ መገኘነቱ ነው፡፡
በመሰሪው ፖል ፖት የሚመራው የኬሜሩዥ ቡድን ጫካ ገብቶ በጉሬላ ውጊያ የአገሩን የካምቦዲያን መንግስት ለመጣል ጥረት አድርጓል፡፡ በአገሩ የኖርዶም ሲሃኖክ ንጉስን ለመጣል ጥረት ሲያደርግ ቡድኑ ብቻውን አልነበረም፤ ከውጪ ሃይሎች ጋር በመመሳጠር የመሳሪያ ስጦታ እየተበረከተለት ሲዋጋ የካምቦዲያን ተወላጆች በብዛት ፈጅቷል፡፡ ቬትናም አማፂውን ኬሜሩዥን እንደደገፈች በይፋ ባትገልፅም መጠለያ እና የጦር መሣሪያ መስጠቷን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አሜሪካም የዚሁ ቡድን ቀንደኛ ተባባሪ ነበረች፡፡
የኬሜሩዥ ጨፍጫፊ እና የዘር አጥፊ ቡድን በውጭ የጥፋት ፈላጊ ሃይሎች ድጋፍ የካምቦዲያን ንጉስ ጦር ማዳከም ችሏል፡፡ ከምዕራብያውንና ከጎረቤት ሀገራት በሚደረግለት ድጋፍም የኬሚሩዥ አማጺ ቡድን ሃይል እየተጠናከረ ሄደ፡፡ ገና ስልጣን ሳይዝም የካምቦዲያ ኮሚኒስት ፓርቲ መሆኑን በይፋ አወጀ፡፡
እ.አ.አ 1970 በተካሔደው ጦርነት በውጭ ጠላቶች ድጋፍ የአገሪቱ መከላከያ ጦርን አዳከመ፡፡ በካምቦዲያም ሁከትና ብጥብጥ ነገሰ፡፡ ሁከቱና አለመረጋጋቱ ሲብስም በመፈንቅለ መንግስት የካምቦዲያው የወቅቱ ንጉስ ሲሃኖክ ከስልጣናቸው ለቀቁ፡፡ የአገሩ መንግስት ቢወርድም አማፂው እና አሸባሪው ኬሜሩዥ በወታደራዊ የጫካ ጦርነቱን ቀጠለ።
በመጨረሻም የአሜሪካ ድጋፍ ታክሎበት አክራሪው የኬሜሩዥ ኮሚኒስት ፓርቲ የካምቦዲያ ከተሞችን ብቻ ሳይሆን ገጠሩንም መቆጣጠር ቻለ፡፡ በመጨረሻም 1975 የኬሜሩዥ ኃይሎች በዋና ከተማዋ በፍኖም ፔን ድል አድራጊ ሆነው ካምቦዲያን ለመግዛት ብሔራዊ መንግሥት አቋቋሙ።
የአማጺው ቡድን መሪ አረመኔው ፖል ፖትም የካምቦዲያ መሪ መሆኑን አወጀ፡፡ ከ1975 እስከ 1979 አረመኔው ፖልፖት ካምቦዲያን በጨካኝ መዳፉ ጨምድዶ ያዘ፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ተፈፅሞ የማያውቅ ግፍ በካምቦዲያውያን ላይ ፈፀመ፡፡ እጅግ የተማሩ እና አገራቸውን በእጅጉ መጥቀም የሚችሉ ካምቦዳውያን ምሁራን እና ባለሙያዎች እየተለቀሙ በዚህ አማፂ ሃይል በግፍ ተገደሉ፡፡ ህጻናትን ያለርህራሄ ፈጀ፤ ሴቶችን በገፍ ደፈረ፤ ገደለ፡፡ ቀድሞ ለነበረው አስተዳደር ድጋፍ ይሠጣሉ በሚል የጠረጠራቸውን እያደነ በአሰቃቂ ሁኔታ ረሸነ፡፡
በወቅቱ ከኬሜሩዥ ጋር በነበረው የሲቪል ጦርነት አንዳንድ መረጃዎች ‹‹ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ አልቋል፤ ›› የሟቾቹን ቁጥር ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚያደርሱትም አሉ፡፡ የኬሜሩዥ አማፂያን ተግባር ስልጣን ከመያዙ በፊትም ሆነ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የብዙዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ ገና ለገና አድገው ይበቀሉኛል በሚል ዕምነት ብዙ ወንድ ህፃናት በአዋጅ ጨፈጨፈ፡፡ ደስ ሲለውም ወደ አንድ አካባቢ ሄዶ በጅምላ በማሰር ካሰቃየ በኋላ በጅምላ ይረሽናቸዋል። የቡድኑ አባላት ደስ ሲላቸው ሰዎችን እራቁታቸውን በማቆም ከተዝናኑባቸው በኋላ በአደባባይ ይገድሏቸዋል።
ኬሜሩዥ አሰቃቂ ድርጊቱ ሰዎች እርቃናቸውን አስቁሞ መግደል ብቻ ሳይሆን ቤተሰብ ያለበትን እና የተሸሸገበትን ቤት በታንክ እየደፈጠጠና እያቃጠለ ንብረትን ብቻ ሳይሆን የሰው አካልንም አመድ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ካምቦዳውያንን በማስተኛት በላያቸው ላይ ታንክ ነድቶባቸዋል፡፡ በየቤቱም እያደነ ይቃወሙኛል የሚላቸውን ንጹሃን ዜጎች በእሳት ለኩሶ አቃጥሏል፡፡
በትምህርት ቤቶች የሚማሩ ህጻናትን ሳይቀር እንደጠላት በመቁጠር በጥይት አረር ፈጅቷቸዋል። በሆስፒታሎች የተኙ ህሙማን ሳይቀሩ የአረመኔው ቡድን ሰለባ ሆነዋል፡፡ አረጋውያን የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ ከጨካኙ ፖልፖት አሰቃቂ ግድያ ሊያመልጡ አልቻሉም።
ይህ ግፍ ያንቀጠቀጠው የካምቦዲያ ዜጋ ሞትን ሳይፈራ በአረመኔው ቡድን ላይ አመጸ፡፡ የኬሜሩዥን ግብዓተ መሬት ለመፈጸም በአንድ ላይ ሆ ብሎ ተነሳ። የህዝቡን ቁጣ መቋቋም ያልቻለው አረመኔው የኬሜሩዥ ቡድን መልሶ ወደ ጫካ ፈረጠጠ። ህፃናትን ሳይቀር መሳሪያ እያስታጠቀ ህዝቡን በማሰቃየት ግፍ ሲሰራ የኖረው የኬሜሩዥ ቡድን ግፍ ገፍቶ ጣለው። የምንጊዜም ባለድል የሆነው ህዝብ እንደተራበ ዝሆን ተነስቶ የኬሜሩዥን ቡድን እያሳደደ ቀጣው ፡፡ ኬሜሩዥም በቀቢጸ ተስፋ በድንበር አካባቢ የሽምቅ ውጊያ ጀመረ፡፡
እ.አ.አ በ1982 ከሌሎች ከካምቦዲያ መንግስት ጠላቶች ጋር ጥምረት ፈጠረ፡፡ እስከ እ.አ.አ 1991 ከሌሎች ጋር እየተጣመረ አገሩን ሲወጋ ቆየ፡፡ በተባበሩት መንግስታት የሰላም ስምምነት ጥሪ የቀረበለት ኬሜሩዥ ከስልጣን ከወረደም በኋላ ለጥሪው ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በካምቦዲያ የተካሄደውን የመድብለ ፓርቲ ምርጫ በመቃወም ጦርነቱን እስከ 1993 ቀጠለ። በአገሪቱ አንድ አውራጃ ለይቶ የእኔ ናት ብሎ አወጀ። ግዛቴ ነው ብሎ ባወጀው አካባቢም የኮንትሮ ባንድ ንግዱን አጧጧፈ። ሆኖም ቡድኑ በሚያደርጋቸው አጽያፊ እና አረመኔያዊ ድርጊቶች መስማማት ያቃታቸው አንዳንድ አባላቱ የቡድኑን አካሄድ መቃወም ጀመሩ፡፡ ኬሜሩዥም መሰነጣጠቅ ጀመረ።
በመጨረሻም የኬሜሩዥ መሪ ፖል ፖት በውስጥ በነበረ አለመግባባት በሌሎች መሪዎች ተይዞ ታሰረ። ለመንግስት ተላልፎ በ1997 ተሰጠ፡፡ ፖልፖትም የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት፡፡ ሆኖም የጭካኔና የአረመኔነት አባት የሆነው የኬሜሩዡ መሪ ፖልፖት በ1998 ህይወቱ አለፈ፡፡ ቀሪዎቹን የኬሜሩዥ መሪዎችን ለፍርድ ለማቅረብ በተደረገው ጥረትም በ2006 ዓ.ም ክስ ተጀምሮ በጦር ወንጀል እና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠይቀው ብዙዎቹ በዕድሜ ልክ እስራት ተቀጥተዋል። ግማሾቹ እዛው በእስር ላይ እንዳሉ ሞተዋል፡፡
የኬሜሩዥ አረመኔ በቡድን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ የሆነው አሸባሪው ህወሓት በብዙ መልኩ ከኬሜሩዥ ቡድን ጋር የሚያመሳስለው ባህሪ አለው። ህውሓትን ከኬሜሩዥ ጋር የሚያመሳስሉት ነገሮች ብዙ ናቸው ስንል መነሻችን፤ እርሱም እንደኬሜሩዥ በጫካ ከ47 ዓመት በፊት በ1966 ዓ.ም ተመስርቶ የኢትዮጵያ ጠላት በሆኑ የውጭ ሃይሎች ታግዞ ብዙዎች ላይ ግፍ እየፈፀመ ብዙዎችን መፍጀቱን በማስታወስ ነው፡፡ አንደኛው የሚያመሳስላቸው ተግባር ህወሓት በመሣሪያ ትግል በጫካ በነበረበት 17 ዓመታት ቆሜለታለው በሚለው በትግራይ ህዝብ ላይ ብዙ ግፍ መፈጸሙ ነው፡፡
ከፈጸማቸው ወንጀሎች እና ግፎች መካከል በ1977 በድርቅ ወቅት ዓለም አቀፍ ለጋሾች በህውሓት ቁጥጥር ሥር ለነበሩ የትግራይ ወረዳዎች እንዲከፋፈል የሰጡትን የነፍስ አድን እርዳታ ከአሜሪካና ከምዕራባውያን ጋር በመተባበበር እህል እነ መለስ ዜናዊ፤ እነ ስዩም መስፍን፤ ስብሃት ነጋ እና ብርሃነ ገብረኪርስቶስ የመሳሰሉ የህወሓት መሪዎች በማጭበርበር ከረሃብተኛው ጉሮሮ ቀምተው በአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘበብ በሱዳን በኩል ወደ ውጭ ልከው ሸጠዋል፡፡ በዚህም በገንዘቡ ድርጅታቸውን በመሳሪያና በሎጀስቲክ እንዲጠናከር አድርገዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በተላከላቸው የምግብ ዕርዳታ ህይወታቸው ይድን የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች በረሃብ እንደቅጠል ረግፈዋል።
ህውሓት የትግራይን ህዝብ ለማነሳሳት እና ከጎኑ ለማሰለፍ በጫካ ሆኖ ለደርግ የተሳሳተ መረጃን በማቀበል በውሸት ቆሜለታለሁ የሚለውን የትግራይን ህዝብ ገበያ ላይ በአገሪቱ አየር ሃይል በግፍ እንዲጨፈጨፍ አድርጓል። ጭፍጨፋውን ደርግ እንደፈፀመው ነግሮ ህዝቡን በማነሳሳት ብዙ ወጣቶች እና የትግራይ ልጆች ከጎኑ እንዲቆም በማድረግ በሰፊው ከአገሪቱ ጦር ጋር ውጊያ ለመፈፀም ችሏል፡፡ በዚህ መልኩ እየፈፀመ ባለው ሤራ ከውስጥ ድጋፍ ከማግኘት በተጨማሪ በውጭ የኢትዮጵያ ጠላት እርዳታ ሰጪዎችም ያበረከቱት አስተዋፅኦ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የኬሜሩዥ አማፂ ድርጅት ከካምቦዲያውያን ድጋፍ በላይ የውጭ ሃይሎችና የጎረቤት ሀገር ድጋፍ በሰፊው ረድቶት ነበር፡፡
ልክ ሱዳንና ግብጽ ለአሸባሪው ህወሓት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ሁሉ ቬትናም ለኬሜሩዥ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ኬሜሩዥ የአሜሪካና የአውሮፓውያን ድጋፍ እንዳልተለየው ሁሉ ህወሓትም በተመሳሳይ መልኩ የአሜሪካና የአወሮፓውያን የጡት ልጅ ነው፡፡ ኬሜሩዥ ከትጥቅ ትግሉ በኋላ መንግስት መስርቶ የሀገሪቱን ሃብት ብዝብዟል፤ ይቃወሙኛል ያላቸውን አሳዶ ገድሏል፡፡ የአሸባሪው ህወሓት ተግባር ከዚሁ የራቀ አይደለም፡፡
ህወሓት በስልጣን ዘመኑ የኢትዮጵያን ሃብት ቅርጥፍ አድርጎ ከመብላቱም ባሻገር ለስልጣኑ እንዲያመቸው የጥላቻ ፖለቲካን በማራመድ ኢትዮጵያውያንን እርስ በእርስ ለማባላት ሞክሯል። ብሄር ተኮር ጭፍጨፋም አካሂዷል፡፡ ግፎችን ፈጽሟል። የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የአፋርም ሆነ የሶማሌ እና የመላው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እና የተማሩ ሰዎች በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በየእስር ቤቱ ለማሰብ እና ለመስማት የሚዘገንኑ እጅግ የከፉ ድርጊቶችን ከመፈፀም አልፎ የራሳቸውን መቀበሪያ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ በማድረግ ጭምር እየገደለ የፈጸመባቸው ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች ህውሓትን ከካምቦዲያው ኬሜሩዥ ጋር ያመሳስለዋል።
በእርግጥም እነዚህ ቡድኖች ሌላም የሚያመሳስላቸው ነገር አለ፡፡ ስልጣንን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይሆን በጦርነት ማግኘታቸው እና በመንግስትነት በቆዩባቸው ዘመናት ሁለቱም የሚያስተዳድሩትን ህዝብ በመበደል ሰብአዊ መብት በመግፈፍ እና በማሰቃየት ወደር የሌላቸው መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ስልጣን ከለቀቁም በኋላ መልሰው ወደ ጦርነት መግባታቸው እና አገር ማተራመሳቸው አንድ አይነት ናቸው ለማለት ያስገድዳሉ።
ህውሓት በስልጣን ዘመኑ የቀበረው የሴራ ፈንጂ ከስልጣን ከወረደም በኋላ በየቦታው እየፈነዳ ብዙዎች በእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ዘር በሚል አጥር ውስጥ ተወሽቀው አንዱ ሌላውን የሚያጠቃበትን መሰረት በማመቻቸት ሲያስተዳድረው የነበረውን ህዝብ እርስ በራሱ እንዲጨፋጨፍ በማሴር በተደጋጋሚ ወደ ስልጣን ለመመለስ ሞክሯል፡፡ የሸፈነውን የረመጥ እሳት እያቀጣጠለ በማራገቡ ብዙዎች በየክልሉ የሚያልቁበትን ሤራ እየወጠነ ቢተገብርም ያሰበውን ያህል ሊሆንለት አልቻለም፡፡
ከኬሜሩዥ አማጺ ቡድን በላቀ መልኩ አሸባሪው ህወሓት የለየለት አረመኔና ከሃዲ የሆነባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም እራሱን ጨምሮ ሀገርን ሲጠብቅ በኖረ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ከጀርባ የፈጸመው ክህደት ግን በታሪክ የሽብር ቡድኑን ከሃዲነት ወደር የሌለው ያደርገዋል፡፡ የህውሓት አሸባሪ ቡድንም በሤራ ያሰበው አልሳካ ቢለው በአደባባይ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ላይ ለዘላለም ሊረሳ የማይችል ግፍ ፈፀመ፡፡ ቡድኑ ምን ያህል የአስከፊዎች እና የአውሬዎች ስብስብ መሆኑ ታየ፡፡ በገዛ አገሩ ላይ ጦርነት አወጀ፡፡
የኬሜሩዥ አረመኔ ቡድን በስፋት በጅምላ ሰዎችን ገድሎ ቀብሯል፡፡ በቁም ሰዎችን አቃጥሏል። ብዙሃንን አስተኝቶ በታንክ ደፍጥጧል፡፡ አሸባሪው ህወሓትም በጋምቤላ፤በመተከል፤በማይካድራና በአፋር ሰዎችን በጅምላ ፈጅቷል፡፡ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በተኙበት በጅምላ አርዷል፡፡ በላያቸው ላይም ሲኖትራክ ነድቷል። በተለይም በማይካድራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ዘግናኝ ነበር። የቡድኑንም የአረመኔነት ጥግ የሚያሳይ ነው። አሸባሪው ህወሓት አሰልጥኖ ባሰማራው ሳምሪ በተሰኘው ወጣት ገዳይ ቡድን አማካኝነት ከ1 ሺህ 600 በላይ ሰዎችም በማይካድራ ተጨፍጭፈዋል፡፡
የኬሜሩዥ አማጺ ቡድን በተደጋጋሚ ሲቀርብለት የነበረውን የሰላም ሃሳብ በመግፋት ጦርነትን ዋነኛ አማራጭ አድርጎ ቆይቷል፡፡ አሸባሪው ህወሓትም አስራ አንድ ጊዜ የሰላም ጥሪ ቢተላለፍለትም አሻፈረኝ ብሎ በጦርነቱ ቀጥሏል፡፡ ቡድኑ ብዙ የትግራይ ልጆችን አሰልፎ እንዲያልቁ እያደረገ ነው፡፡ መንግስት ለትግራይ ህዝብ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጠብ አጫሪነቱን ገፍቶበታል፡፡ የህውሓት አሸባሪ ቡድን ግን ስለህዝብ ደንታ የሌለው በመሆኑ ከክልሉ አልፎ አፋር እና አማራ ክልል ድረስ ዘልቆ ንጹሃንን እያጠቃ ይገኛል፡፡ በአፋርም ከ200 በላይ ወገኖች ህፃናት እና ሴቶችን በመጨፍጨፍ ተጨማሪ ሌላ የዘር ማጥፋት ድርጊት ፈጽሟል፡፡ ቡድኑ ሃሳቡ መነሻው እና መድረሻው ሰላም ሳይሆን ጥፋት ብቻ ነው፡፡ ይህ ከኬሜሩዥ ጋር ተመሳሳይ ያደርገዋል፡፡
ኬሜሩዥ በመጨረሻ ዘመኑ አንድ አካባቢን የሙጥኝ ብሎ ሌላውን የሀገሪቱን ክፍል ሲወጋ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን የቡድኑ አካሄድ የትም እንደማያደርስ የገባቸው አንዳንድ የቡድኑ አመራሮች በማፈንገጣቸው ቡድኑ ሊሰነጣጠቅ ችሏል፡፡ ከወደ ህወሓት መንደር የሚሰማው ተመሳሳይ ነው፡፡ የአሸባሪው ቡድን አካሄድ እንደማያዋጣ እና በቅሌት እንደሚደመደም የገባቸው አንዳንድ የቡድኑ አመራሮች የተለየ ሃሳብ በማንሳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ቡድኑም በተለያዩ አስተሳሰበቦች እየተከፈለም እንደሆነ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በመጨረሻም የኬሜሩዥ አመራሮች ተይዘው ለህግ እንደቀረቡ ሁሉ የአሸባሪው ህወሓት አመራሮችም የማይቀርላቸውን ጽዋ ለመጎንጨት የቀናት ጊዜ ብቻ የቀራቸው ይመስላል፡፡
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013