
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከጀመረች ወደ 120 ዓመታት እየተጠጋት ነው። በአሜሪካም ሆነ በኢትዮጵያ መንግሥታት ቢቀያየሩ አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ አልፎ አልፎም ለብ እያለ ቀጥሏል። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አሜሪካ ከሌሎች ሀገራት ጋር ታራምደው ከነበረ ግንኙነት የተለየ አልነበረም። ከብሔራዊ ጥቅሟ በተጻራሪ የሚቆም መንግሥት በመጣ ጊዜ ለመቀየር የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን(መክዘ) እኩሌታ ማብቂያ አካባቢ በላቲን አሜሪካ በደቡብ ምዕራብ ፓሲፊክ እንዲሁም በ20ኛው መክዘ መግቢያ ደግሞ በፓናማ ሆንዱራንስ ኒካሯጓ ሜክሲኮ ሄይቲ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ መንግሥታትን ለውጣለች።
በተለይ በቀዝቃዛው ጦርነት (1945_1991 እኤአ)ዓለም በሶሻሊስትና በካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለም ጎራ በተከፈለ ጊዜ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ሻክሮ ነበር። ደርግ ሶሻሊስት ስለነበርና አሰላለፉም በሶቭየት ሕብረት ረድፍ ስለነበር አሜሪካና አጋሮቿ ለሸዓብያና ለወያኔን በግልጽ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ በማድረግ ደርግን በተራዘመ ትጥቅ ትግል ገርስሰው አሥመራና አዲስ አበባ እንዲገቡና የስልጣን መንበሩን እንዲቆጣጠሩ በማድረግ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
በተለይ አሜሪካ በኢትዮጵያ እንዳደረገችው በመላው ዓለም የ70 ሀገራትን መንግሥት ለመለወጥ በህቡዕና በይፋ ተንቀሳቅሳለች። የቀዝቃዛው ጦርነት በበርሊን ግንብ መፍረስ በሶቪየት ሕብረት መበታተን ከተቋጨ ከ30 ዓመታት በኋላ ዛሬም የማትፈልገውን መሪ ለማስወገድ በምርጫ ጣልቃ ትገባለች በውክልና ወይም በቀጥታ መንግሥት ትገለብጣለች። ሀገሬን ያለ ብሔርተኛ/nationalist/ ተላላኪና አሻንጉሊት አልሆንም ያለና ለዜጋው ጥቅም የቆመ መንግሥት ከአሜሪካና ከምዕራባውያን ጥቅም በተጻራሪ እንደቆመ እንደጠላት ተቆጥሮ እንዲወገድ ይደረጋል። ባላንጣየ ከምትላት ቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለውም በጠላትነት ተፈርጆ ጥርስ ይነከስበታል። የቡርኪናፋሶው ቶማስ ሳንካራ የጋናው ኩዋሚ ንኩሩማህ የኢራቁ ሳዳም ሁሴንና የሊቢያው ሞአመር ጋዳፊ ከሰለባዎቿ መካከል ይጠቀሳሉ።
በምርጫ ጣልቃ መግባትም ሆነ የመንግሥት ለውጥ ማምጣት የአሜሪካንን ጥቅም ለማስከበር አዋጭ ነው ቢባልም መጨረሻው ግን ሀገራትን ወደለየለት የእርስ በርስ ጦርነት እና ቀውስ ስለሚዘፍቅ ውጤታማ ባይሆንም ዛሬም በጀ ብላ ቀጥላበታለች። የቅርቦቹን እነ አፍጋኒስታን ኢራቅ ሶሪያ የመን ቬኒዞላ ሄይቲ ልብ ይሏል። ዛሬም ጥቅሜን ያስከብርለኛል የምትለውን መንግሥት ለማንገስ በኢራን በሶሪያ በኢትዮጵያና በሌሎች በርካታ ሀገራት አሻንጉሊትና ተላላኪ መንግሥት ለመተካት ከከሀዲዎችና ከባንዳዎች ጋር በመቀናጀትና በመናበብ ሌት ተቀን እያሴረች ነው። አሜሪካ እ.ኤ.አ 1946-2000 በ81 ሉዓላዊ ሀገራት ምርጫ በይፋ ወይም በስውር ጣልቃ ገብታለች። በጣሊያን በፊሊፒንስ በሊባኖስ በጃፓን ምርጫዎች ጣልቃ በመግባት እንዳሻት የምታሽከረክረው መንግሥት እንዲመረጥ አድርጋለች።
የመንግሥታቱ ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 2 ቁጥር 4 ላይ በግልጽ የአንድን ሉዓላዊ ሀገር መንግሥት በኃይልም ሆነ በሴራ ለመለወጥ የሚደረግ እንቅስቃሴን የሚያወግዝ ድንጋጌ ከጸደቀ በኋላ እንኳ አሜሪካ ይህን ዓለምአቀፍ ሕግ በመተላለፍ የ70 ሀገራትን መንግሥታት ለውጣለች። ለዓለም ሰላም ለሕግ ልዕልና ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ቆሜያለሁ የምትለው አሜሪካ እንዲህ ናት። ቆሜለታለሁ የምትለው እሴትና መርህ የውሸት ነው። ዛሬ በሀገራችን እየሆነ ያለው ይሄን የሚያረጋግጥ ነው። በሦስት ዓመታት በሀገሪቱ ታሪክ ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማስፈን ሰብዓዊ መብትን ለማክበር አሠራሩንና አደረጃጀቱን ለመለወጥ አፋኝ ሕጎችን በማስወገድና በማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም አዳዲስ ሕጎችን በማውጣት ምቹ መደላድል እየፈጠረ ለውጡ ዘላቂ እንዲሆንም ገለልተኛና ነፃ ተቋማትን እየገነባ ነው።
እንደ ምርጫ ቦርድ ፍርድ ቤት የደህንነትና የጸጥታ መዋቅር የዕንባ ጠባቂና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኖችን መስርቷል። በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ወደ ሀገር እንዲገቡና ታግደው የነበሩ ከ200 በላይ ጋዜጦች መጽሔቶች ድረ ገጾች ጦማሮችና ዩቲውቦች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ከመደረጉ ባሻገር በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃ ተአማኒና ዴሞክራሲያው ምርጫ በሰላም ተጠናቆ እያለ አሜሪካና ምዕራባውያን በልኩ እውቅና መስጠት አልፈለጉም። ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የመረጠውን መንግሥት ከመቀበል ይልቅ በግልጽም ሆነ በስውር የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ ሴራ እየሸረቡና በተግባርም እየተንቀሳቀሱ መሆኑን “ከባዝማ እስከ ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በዚሁ ጋዜጣ ያስነበብሁት መጣጥፍ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የሚያሳዝነው አሜሪካ በኮንግረሷ ሳይቀር በአንድ ወቅት በአሸባሪ ብሎ ከፈረጀው አሸባሪው ህወሓት ጋር በማበር እውነተኛ ማንነቷን አሳይታናለች። ለዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት መከበር እና ለቀጣናው ሰላም ቆሜያለሁ የምትለው ልግጫ መሆኑን ተገንዝበናል።
ህወሓት ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያውያንን በገፍ ሲገድል ሲያሰቃይ ሲያጉር ሲያግዝ ሲዘርፍ ፤ የሰሜን ዕዝን ሲያጠቃ በማይካድራ 1600 አማራዎችን ሲጨፈጭፍ፤ መንግሥት ለሰብዓዊነት የተናጠል የተኩስ አቁም ሲያውጅ የአማራንና የአፋር ክልሎች ወሮ ሰላማዊ ሰዎችን ሲያጎሳቁል ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ሲያፈናቅልና ሲዘርፍ ፤ ሰሞኑን ደግሞ በከባድ መሳሪያ ከ240 በላይ በአፋር ንፁሐን ላይ እልቂት ሲፈጽም አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ሲያልፉ የነበሩት አሜሪካና አውሮፓ የዐቢይን መንግሥት ግን በሐሰተኛ መረጃ እየከሰሱትና ጫና እየፈጠሩበት ይገኛል።
የትግራይን ሕዝብ በማስራብ በዘር ማፅዳት በአስገድዶ መድፈርና በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ጥቃት በመፈጸም የሐሰተኛ ክስ እየደረቱበት መሆኑን ስንታዘብ ሳዳም ሁሴንን ከስልጣን ለማውረድ ጅምላ ጨራሽ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ አለው በሚል በኢራቅ ላይ ያካሄዱትን ጦርነት ያስታውሰናል። አሜሪካ የመንግሥት ለውጥ ባደረገችባቸው በእነ ኢራቅ አፍጋኒስታን ሊቢያ የመን ሶማሊያና ሌሎች ሀገራት የተባባሰ ቀውስና ትርምስ መፈጠሩን የታዘቡት የተፍተስ ዩኒቨርሲቲው ቤንጃሚን ዴኒሰን በጣልቃ ገብነት ላይ የተመሠረተው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሽፏል ይላሉ።
በዚሁ ጋዜጣ በዚያ ሰሞን እንዳስነበብሁት ፤ አንዳንድ ጉምቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቃውንት ቢቸግራቸው የ98 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ወደ ሆነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደራሲ እስከ መባል ወደ ሚሞካሸው ሄነሪ ኪሲንጀር ዘመን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የታነጸ ዲፕሎማሲ ማማተር ጀምረዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከመሠረቱ ተናግቷል በማለት ማሳያዎቻቸውን ያነሳሳሉ። በቀዝቃዛው ጦርነት ርዕዮት ዓለምን ተከትሎ ያራምደው የነበረው የእመቃ ዲፕሎማሲ በዊልሰናዊያን የተስፋፊነት የተሳሳተ አባዜ ከቬትናም ጋር የተካሄደው ጦርነት የ50 ሺህ አሜሪካዊ ወታደሮች ያስገደለ ፤ ከ70 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ አክስሯል።
ከሁሉም በላይ የሽንፈት ከል አከናንቦታል። የአሜሪካን ገጽታ ክፉኛ ጎድቶታል። እንዲሁም በድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት በአዲሱ የሬጋን “ሰይጣን” አገዛዞችን በኃይል የማስወገድ ዕርምጃ ከፍ ብሎ እንደተመለከተው ተሞክሮ ከሽፏል። 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ደግሞ የ1950ዎቹንና 60ዎቹን “አሜሪካ ትቅደም!” ፖሊሲ አቧራውን አራግፎ ወደፊት ቢያመጣውም አሜሪካን ነጥሎ ብቻዋን በማስቀረት ከስሯል። ባሪ ጌዌን”The Inevitability of Tragedy” በተሰኘው የሄነሪ ኪሲንጀርና የዛን ዘመን የዲፕሎማሲ አካሄድ በሰነደበትና በተነተነበት ማለፊያ መጽሐፉ” በእርግጥ ሔነሪ ኪሲንጀርን ልትጠላውና ከይሲ ነው ብለህ ልታስብ ትችላለህ። ልትረሳው አልያም ልተትተው ግን አትችልም። ለዚያውም በዚህ ጊዜ።
እውነት ለመናገር የኪሲንጀር እሳቤም ሆነ ተፈጥሮው ወይም ደመነፍሱ በዚህ ሰዓት ክፉኛ ያስፈልገናል።” በማለት የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚታደገው ኪሲንጀርና መንፈሱ ብቻ እንደሆነ ይነግረናል። ቀራጮች የሚከተሉትም አዲሱ ወግ አጥባቂነት Neoconservative አልያም ዴሞክራቶች የሚያራምዱት ሊበራል ዓለምአቀፋዊነት Liberal internationalism የአሜሪካን ዲፕሎማሲ ከገባበት ቅርቃር አያወጣውም። ለዚህ ነው ጌዌን በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ወደተቀረጸው የሔነሪ ኪሲንጀር የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንመለስ ሲል የሚወተውተው።
ማይክል ሒርሽ”WELCOME To Kissinger’s World” በሚል ርዕስ በፎሪን ፖሊሲ መጽሔት ባለፈው ዓመት ባስነበበን ወግ፤ የኮሮና ወረርሽኝ የትራምፕን” አሜሪካ ትቅደም!” የሚለውን የተነጣይነት አጀንዳ ለማጉላት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። የንግድ ወኪሉ ሮበርት ሊቲዘር ቻይና በምትከተለው አደገኛ የንግድና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ አሜሪካ በውጭ የሚገኙ ፋብሪካዎቿንና ኩባንያዎቿን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ያስፈልጋታል ሲል የትራምፕን የተነጣይነት ፖሊሲ ያቀነቅናል። ትራምፕ በዚህ አያበቃም። ሳይሳካለት ቀረ እንጂ የቻይናን የኢኮኖሚ እድገት ግስጋሴን ለመገዳደር የሚችል የተለያዩ ሀገራትን ግንባር ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ዴሞክራቶች ይህን የትራምፕ ገዳዳ አቋም በገደምዳሜ ከመደገፍ አልፈው በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት የነበረውን ዓይነት ትንቅንቅ እስከመቆስቆስ ደርሰዋል።
የዚያን ጊዜው ዕጩ የዛሬው ዴሞክራት ፕሬዚዳንት ባይደን በተደጋጋሚ የቻይናውን ፕሬዚዳንት ዢ ዥንፒግ ከማድነቅ አልፈህ ፊት ትሰጥ ነበር በማለት በምርጫው ክርክር ወቀት ይከስ ነበር። ዴሞክራቶች ከዚህ አልፈውም በእነሱ ሊበራል ዓለምአቀፋዊነት መርህ መሠረት የተቋቋሙ እንደ የዓለም ንግድ ድርጅት ያሉ ተቋማትን የቻይና መጠቀሚያ እየሆኑ ነው በማለት ማብጠልጠል መጀመራቸው ፤ ሳያንስ ቻይና የአሜሪካውያንን የሥራ ዕድል እየተሻማች ነው በሚል መክሰሳቸውን ሒርሽ ያትታል። ይሁንና ይህ የቀራጮች ተነጣይነትም ሆነ የዴሞክራቶች ዓለምአቀፍ ተቋማትንና ቻይናን የማጠልሸት አባዜ ነባራዊውን ዓለምአቀፍ ሁኔታ ለየፓርቲዎቻቸው ማህበራዊ መሠረት መስዋዕት የማድረግ የሕዝበኝነት populism አጓጉል አመል።
የደጋፊዎቻቸውን ብሶት በመጋለብና ቁስል በማከክ ጊዜያዊ ፖለቲካዊ ነጥብ የማስመዝገብ ዘመን አመጣሽ ፖለቲካዊ ስብራት። የሚገርመው ቻይና ላይ ይህን ሁሉ ውርጅብኝ እያጎረፈች ፤ ከቻይና ጋር የሚናገዱ ሀገራትን ዓይናችሁ ለአፈር እያለች እሷ ግን በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ሸቀጥ ትሸጣለች ትገዛለች። ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ከቻይና ተበድራለች። “እስከ መቼ !? ዓለም የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ሰለባ መሆኗ ይቀጥላል !?” የሚለው የብዙዎች ጥያቄ በቅርብ መልስ የሚያገኝ ይመስላል። የቻይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ እድገት እና አሜሪካውያን የመንግሥታቸውን የዓለም ፖሊስነትና ጣልቃገብነት አምርረው እየተቃወሙ መሆኑ አሜሪካ ዓለምን እንዳሻት በብቸኝነት የምታተራምስበት ዘመን ማብቂያው እየተቃረበ መሆኑን ያረጋግጣል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሐቀኛና ጀግኖች ልጇቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013