ኢትዮጵያ በፀጋ የተጠበቀች፣ በፈጣሪ የተባረከችና የተመረጠች አገር ናት። ኢትዮጵያ የነካትን የምታቃጥል እሳት ናት። ኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው። ኢትጵያዊነት ነጻነትና ኩራት ነው። ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት፣ አንድነት እና ትግዕስት ነው።
ኢትዮጵያ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በአንድነት በመመከት አንፀባራቂ ታሪክ አላት። ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟትን ፈተናዎች የተሻገረችው በልጆቿ ነው። የልጆቿ በታሪኩ የሚታወቁት አገራቸው ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች ሲጠብቁና ደማቸው አፍስሰው የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍልላት ነው። ለዚህ ምስክር መቁጠር ሳያስፈልግ ታሪክ የከተባቸውን ድርሳናት ማገላበጥ በቂ ነው።
ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለማንም ጥገኛ ሆነው አያውቁም። የጥገኝነት አስተሳሰብና ስነ ልቦና የሌለው ህዝብ በታሪክ ያጋጠሙትን ፈተናዎች ያለፈውም በጠንካራ አንድነቱና ህብረቱ ነው። የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች ወይም ፍላጎቶች ቢኖሩ እና ተቃርኖ ያላቸው ወገኖች ጭምር በአገር ጉዳይ አቋማቸው ተመሳሳይ ነው።
ኢትዮጵያዊ በጠላት ፊት ያለ መንበርከክ ትልቅ የሞራል ልዕልና አለው። ለጠላት በር አይከፍትም። ለሃሳብ ልዕልና እንጂ ለጉልበት ቦታ አይሰጥም። በሃሰተኛ ወሬ ሳይደናገር እውነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል። በተጣራ ማስረጃ እንጂ በግርድፍ መረጃ አይበይንም። ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት እንጂ ለአምባገነንነት አያጎበድድም።
ኢትጵያዊያን በሀገራቸው ክብር አይደራደሩም። አይፈሩም። አይደፈሩም። አገራቸው መኩሪያቸውና መከበሪያችን ናት። ዜጎቻ እናት አገራቸውን የመከራ ቋት አያደርጉም። ባዕዳን ፍርፋሪ ሲሉ የአገራቸውን ሚስጥር አሳልፈው አይሰጡም። ስለ ፍቅር እጅ፣ ስለ ጠብ ከሆነ ነፍጥ ያነሳሉ። ከአገራቸው ህልውና በላይ ምንም የሚበልጥበት ነገር እንደሌለም ታላቁን የዓድዋ ድል ጨምሮ በርካታ ተጋድሎዎቹ ህያው ምስክር ናቸው።
በተለይ ከዓድዋ ድል በኋላ ታላላቅ ከሚባሉ ታሪካዊ ክንውኖች መካከል በሚጠቀሰው ታላቁ የህዳሴ ግድብና በቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የተለያዩ ኃይሎች ተሰልፈዋል። ስለተጠናከረች ኢትዮጵያ ሳይሆን ስለምትፈራርሰው ኢትዮጵያ ነጋ ጠባ በመደስኮር ላይ ተጠምደዋል። ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቻችን ጋር ለማጋጨትና ትርምስ ለመፍጠር የሚፈልጉ ኃይሎችም ተበራክተዋል።
ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ጣልቃ ለመግባት አሰፍስፈዋል። ከአንድ ማዕድ እየተቋደሱ የሚበሉትን፣ በደስታም ሆነ በመከራ የማይለያዩትን፣ እምነታቸውን ይዘው ለአገራቸው አንድነት በጋራ የሚቆሙትን ህዝቦች ለመከፋፈል አኮብኩበዋል። በውክልና ጦርነት ሳይቀር እጃቸውን እያስረዘሙ ሊያዳክማት ተነስተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በየፈርጁ የተለያዩ አሉታዊ ሪፖርቶች እያቀረቡባት ነው።
በተለይ አሸባሪውም ሕወሃት ቡድን የሚፈፅማቸውን በደሎች ሰምተው እንዳልሰማ፣ አይተው እንዳለየ፣ ገብቷቸው እንዳልገባቸው እያለፉት ይገኛሉ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘ ተቋም በተጠና እና በተቀነባበረ መልኩ የሽብር ቡድኑን የጭካኔ ጥግ የሚያስመሰክሩ ጭፍጨፋዎችን ከማጋለጥ ሲቆጠብ በተደጋጋሚ ታዝበናል።
ሌላው ቀርቶ በአለም አቀፍ ደረጃ ህፃናትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጦርነት መመልመል፣ ማስታጠቅም፣ ሰላይነት መጠቀም እና ተሳታፊ ማድረግ በአለም አቀፍ ወንጀል የሚያሰጠይቅ ሆኖ ሳለ አሸባሪው ቡድን ህፃናትን ለጦርነት እያሰለፈ መሆኑ በግልፅ አደባባይ እያስተዋሉ እንኳን የሚመለከታቸው አለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን ሲመርጡ እያስተዋልን እንገኛለን።
ይሕ የአድሎአዊ ምልከታም የተንሸዋረር እይታም የኢትዮጵያን ሉለአዊነት ከማሳነስ ባለፈ ምንጊዜም ለአፍሪካውያን የሚቆም ብሎም ነፃነቱን የሚያስጠብቅ መሪ እና መንግስት ሲፈጠር ማየት እንደማይፈልጉ በአደባባይ እየመሰከረ ይገኛል።
ኢትዮጵያዊያንም ይህንን የሴራ ጥልፍልፎሽ በአግባቡ መገንዘብ የግድ ይላቸዋል። ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ አብጠርጥሮ ማወቅ ይገባቸዋል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተከፈቱባትን የዲፕሎማሲና የሚዲያ ጥቃቶች በብቃት ለመመከት ካልቻለች፣ በመረባረብ ላይ ያሉ የውጭ እና የውስጥ እብሪተኛ እና ፀብ አጫሪ ኃይሎች የበላይነቱን ይዘው ከባድ ኪሳራ ሊያደርሱባት እንደሚችሉ መገንዘብ ግድ ይላል።
ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት በጎሰኝነት አስተሳሰብ፣ በመጥበብ ፖለቲካ ከሚያሳዝናት ይልቅ ለገጠሟት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች በተለይም ውጭ ኃይሎች ግፊያና ጉሽሚያ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት በሁሉም ግንባሮች ንቁና ብቁ ሆኖ የሚገኝ ትውልድ ትሻለች። የግዛት አንድነቷና ሉዓላዊነቷ ተከብሮ የውጭ ጣልቃ ገብነትን መቋቋም የምትችለው በዜጎቿ አንድነት መሆኑን ጠንቅቆ የሚረዳ ትውልድ ያስፈልጋታል።
ኢትዮጵያችን በአሁኑ ወቅት የሚክሳት እንጂ የሚከሳትን አትፈልግም። ከሚያፈርስ ይልቅ የሚያድሳትን ትውልድ ትሻለች። ቀዳዳዋን ከማስፋት ይልቅ የሚያጠብላት ትውልድን ትባጃለች። ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እፍ ብሎ የሚያቀጣጥል እና ሊያፈራርሱ የሚቋምጡ ባንዳ ጠላቶቻችን የሚመክቱ ልጆችን ትሻለች።
ኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ የሚያስፈልጋት የመላ ሕዝቧ አንድነት ነው። እያንዳንዱ አገር ወዳድ ዜጋ የአገር ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም የሚከበረው በአንድነት በመቆም ብቻ እንደሆነ ሊረዱ ይገባል። ህዝብ አንድነት ሲፈጥር ማንም አገሩን አይደፍርም። ኢትዮጵያዊያን አንድ ሲሆኑ ማንም እንደማይበግራቸው የታወቀ ነው።
ኢትዮጵያዊያን ምክንያታዊ ሆነው ሲተባበሩ ማንም አይደፍራቸውም። በዘመናት አገርን የመከላከል ተጋድሎዎቹ የሚኮራው ይህ ትውልድ በዚህ ዘመን ጀግንነቱን ከዲፕሎማሲ ጋር እያዛመደ፣ ለዘመናት ሥራ ላይ ያልዋሉ የተፈጥሮ ፀጋዎችን እያለማ፣ ከግላዊና ከቡድናዊ ፍላጎቶች በላይ አገሩን እያስቀደመና በሰላም አብሮ የመኖር ተስፋን እያለመለመ ካጋጠሙት ችግሮች መሻገር ይኖርበታል።
ኢትዮጵያዊያንን የዓድዋ የጀግንነት መንፈሳቸውን በመስበር ለማንበርከክ የሚፈልጉ ኃይሎችን ምኞት ማክሸፍ ይገባል። ኢትዮጵያን ከታሪካዊ ጠላቶች ሴራ መታደግ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት መሆን አለበት። የአገሪቱ ልሂቃን ከአሰልቺውና ከኋላቀሩ የፖለቲካ ገመድ ጉተታ በመላቀቅ አገራቸውን ማስቀደም ይኖርባቸዋል።
የኢትዮጵያ እውነተኛ የከፍታ ዘመን እንዲረጋገጥ፣ ሕዝባችን በሰላምና በነፃነት የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ፣ የሐሳብ ልዩነቶች በነፃነት እየተደመጡ አገር የዴሞክራሲ ጮራ እንድትሆን፣ ከአሳፋሪውና ከአሸማቃቂው ድህነት ለመገላገል፣ ዜጎች ከስደት ይልቅ በአገራቸው በመረጡት ስፍራ እየኖሩና እየሠሩ ሀብት እንዲያፈሩ አንድነት ማጠናከር እና ለህልውና ትግል በጋራ መቆም የግድ ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚክሳት እንጂ የሚከሳት አያስፈልጋትም። አይመጥናትም። ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ የሚፈልጉ ዜጎች እንዲህ ማሰብ አለባቸው። ልጆቿ እንዲህ ሲያስቡ ኢትዮጵያ ትደምቃለች። ታብባለች። ተፈትና ታልፋለች። ከፍ ብላ ጠላቶቿን ዝቅ ታደርጋለች። እርሷ ኮርታ ጠላቶቿን ታሳፍራለች። የጠሏት ይወድቃሉ። ያከበሯት ይከብራሉ። የደፈሯት ሁሉ ይዋረዳሉ። የናቃት ሁሉ ይወድቃሉ።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013