እንደ መነሻ
ህንዳዊቷ ወይዘሪት ሚኒክሲ ጄቴላን ኢትዮጵያን እንደ ሀገሯ ተቀብላ መኖር ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ እውነት ደግሞ የእሷ ብቻ አይደለም። አብረዋት የሚኖሩ ቤተሰቦችዋ ጭምር እንጂ። እነርሱ ኢትዮጵያን «ውድ ሀገራችን» ሲሉ ይጠሯታል።ኢትዮጵያና ሀገራቸው ህንድ በርካታ ዓመታትን የተሻገረ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ያውቃሉ። ይህ በጎነት የወለደው ትስስርም ዛሬ ለእነርሱ ተርፎ በሀገረ ኢትዮጵያ እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል። ከቴዎድሮስ አደባባይ ከፍና ዝቅ ያሉ ስፍራዎች ለህንዳውያኑ ሩቅ አይደሉም። መሀል ፒያሳን ይዞ ዙሪያ ገባ ያለው አካባቢም የእነዚህ ዜጎች መገኛ ነው። በቀደምቶቹ የፒያሳ ቤቶችና ዕድሜ ጠገብ ህንጻዎች ህንዶች ቤተሰብ መስርተው፣ ልጆች አፍርተው ኖረዋል። ሁለቱን ሀገራት ለዓመታት ያስተሳሰራቸው የዕውቀት ዕትብት ህንዳዊ ምሁራን በበርካታ ትምህርት ቤቶች ተገኝተው ለኢትዮጵያውያን ዕውቀትን እንዲዘሩ ምክንያት ሆኗል።
ዛሬም እነዚህ ዜጎች ከአዲስ አበባ መሀል እምብርት አልራቁም። ልክ እንደ ቀድሞው ሁሉ በነበረው ልምድና ህይወታቸው ከከተማዋ ነዋሪ ጋር ተቀላቅለው ሰላማዊ ኑሯቸውን ቀጥለዋል። የጄቴላን ቤተሰቦችም ቢሆኑ ከዚህ የዘለለ ታሪክ የላቸውም። እንደ አብዛኞቹ ወገኖቻቸው ኢትዮጵያን «ሀገራችን» ሲሉ ይኖሩባታል። እስካሁን የዚህች ሀገር ቆይታቸው መልካም የሚባል ነው። የራሳቸውን ንብረት አፍርተው በሰላም ኖረዋል። ልጆች ወልደው አሳድገዋል፣ አስተምረዋል። መተዳደሪያ የሆናቸው የንግድ መደብርም በርካታ ጎብኚዎች አሉት። እስከዛሬ በንግድ ውሏቸው የገጠማቸው ችግር የለም። እነርሱ ኢትዮጵያውያን ሰው አክባሪና እንግዳ ተቀባዮች መሆናቸውን ያውቃሉ። የአንዳንዶቹ ልጆችም በትምህርት ቤቶቻቸው ባልንጀሮች ሆነው አብረው ይውላሉ። እነርሱም ከአዋቂዎቹ ጋር በጉርብትና ይገናኛሉ። የሁለቱ ሀገራት ባህልና ልምድ እምብዛም ያለመራራቅ ደግሞ ባዕድነቱን አሳስቶታል። ይህ መሆኑም በመደብራቸውና በመኖሪያቤታቸው ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ዓመታትን ከነሱ ጋር እንዲዘልቁ አስችሏል።
ቴዎድሮስ አደባባይ የሚገኘው መኖሪያቤታቸው ከንግድ መደብራቸው ብዙ አይርቅም። ይህ መሆኑም ስራውን በአግባቡ እንዲወጡ አግዟቸዋል። ሁሌም ከስራ መልስ ቤተሰቡ ወጣ ብሎ ይዝናናል። በዚህ ሰአት የሚጠየቁ ዘመዶች፣ የሚጎበኙ ህሙማንና ሌሎችም ካሉ በቂ ጊዜ ይሰጣቸዋል። እንዲህ በሚሆን ጊዜም የቤቱን አባወራና እማወራ ጨምሮ ሁለቱ ልጆቻቸው አይለያዩም። ወንዱ ልጃቸው መኪናውን እያሽከረከረ፣ ሴቷ ልጃቸው ጄቴላንም ከጎናቸው እያወጋች ያሻቸው ደርሰው ይመለሳሉ። እስከዛሬ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከነሰላማቸው ጠብቀዋቸዋል። ካሰቡት ቦታ በቸር ደርሰው የሚመለሱት ያለስጋት ነው። በሰፈርም ቢሆን ከሌሎች ነዋሪዎች አይለዩም። በሰፊው የመኖሪያ ግቢያቸው ዓመታትን ቢያሳልፉም ባዕድነትና ባይተዋርነት ተሰምቷቸው አያውቅም። አዎ! ኢትዮጵያ ማለት ለእነርሱ ሁለተኛዋ ሀገራቸው ናት። ልክ እንደ እናት ምድራቸው ህንድ ሰርተው የሚያድሩባት፣ ውለው የሚሰባሰቡባት እልፍኛቸው ሆናለች። የመኖሪያ ግቢያቸው ሁሌም በዘበኞች ይጠበቃል። የጥበቃ ሰራተኞቹ በፈረቃ እየተለዋወጡ ያድራሉ። የስራ ባህርይው ወጣቶችን ከዕድሜ ጠገቦች የሚለዋውጥ ስለመሆኑ የቤተሰቡ አባላት አይጠፋቸውም። ይህ ደግሞ ይበልጥ ደህንነት እንዲሰማቸው አድርጓል። በሰፊው ግቢያቸው ጥሩ እንቅልፍን ጠግበው የሚያድሩት የእነሱን ጥበቃ አምነው ነው።
የስልሳ ስድስት ዓመቱ አዛውንት አቶ ደምሴ ገዳ ተረኛ በሚሆኑበት ጊዜ ዙሪያ ገባውን ይቃኛሉ። ይህ ዓይነቱ ጥንቃቄ በስራ ቆይታቸው ያዳበሩት ልምድ ነው። ለተቀጠሩበት ሙያና እንጀራን ለሚያገኙበት ውሎ አይቀልዱም። ከሌሎች ወጣቶች ይልቅ በእርሳቸው ላይ የሚኖረውን እመኔታ ያውቁታልና ሁሌም በስራቸው እንደተጠነቀቁ ነው።
ሂደት
ብርዳማው የጥቅምት ወር ተጠናቆ የህዳር ወር ገብቷል። ይህ ወቅት ከውርጭና ቅዝቃዜ አይርቅም። በማለዳ ወጥተው በምሽት ለሚመለሱ ሁሉ ቅጣቱ የከፋ ነው። እያንቀጠቀጠ፣ እያንዘፈዘፈ ጉልበቱን ያሳያል። የረፋዷ ጸሀይ ደርሳ ሙቀቷን በስሱ እስክትለግስም ከሰው አንጀት ፈጥኖ አይወጣም። ይህ አይነቱ ጊዜ በጥበቃ ስራ ለሚሰማሩትን በእጅጉ ይፈትናል። አዳራቸውን በደጅ፣ ትኩረታቸውን በበራፍ ለሚያደርጉ ብርቱዎችም ውርጩ የየዕለት ጓደኛቸው ይሆናል። ህዳር 12ን አብዛኞች በተለየ ቀን ያስቡታል። ዕለቱን አስታውሰውና የሚሆውን አድርገው አካባቢውን በጭስ የሚያጥኑ ጥቂቶች አይደሉም።
በዚህ ቀን ከተማው ሁሉ በጥቁር ጭስ ዳመና ይታፈናል። የመንደሩ ቆሻሻ ሁሉ ተጠራርጎ በእሳት እየጋየም ዶጋ አመድ ይሆናል። ህዳር 12 ቀን 2002 ዓ.ም የሆነውም እንዲሁ ነው። በዕለተ ህዳር ሚካኤል ፒያሳና አካባቢውን ይዞ መላው አዲስ አበባ ቆሻሻውን ሲያቃጥልና ጭሱን ሲያቀረና ውሏል። በአንድ ጥግ ተቀምጠው በትኩረት የሚያወጉ ቡድኖች ግን ይህ ሁሉ አላሳሰባቸውም፤ አላስጨነቃቸውም። ለእነሱ እንዲህ አይነቱ ወግና ልማድ ምናቸውም ሆኖ አያውቅም። አሁን በዋዛ የማይተውት ታላቅ ጉዳይ ላይ ይገኛሉ። ይህን ለማሳካት ደግሞ ዛሬን ጨምሮ በርካታ ጉባኤዎችን ተቀምጠዋል። ላሰቡት ዓላማ የሚውሉትን ዕቃዎች ለማዘጋጀት ጊዜ ወስዶባቸዋል። በሀሳብ ለመዛመድና ስምምነት ለመድረስም እንዲሁ።
አሁን ባሉት ቁሶች ላይ አዲስ ለማከል፣ በጎደሉትም የተሻሉትን ለመተካት ምክክር ይዘዋል። አምስቱ የቡድን አባላት ለምሽቱ ተግባራቸው የሚያስፈልጉትን ሁሉ በአይነት ለይተው ስራ ተከፋፍለዋል። ሀላፊነቱን ሲረከቡም ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ምክር ተለዋውጠዋል። ለዚህ ደግሞ ከእስከዛሬው ተሞክሯቸው ልምድን በትዝታ እየጨለፉ እቅዳቸውን በጥንቃቄ ነድፈዋል። በያዙት አጀንዳ ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች፣ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሮችና ስለሚወሰዱ ፈጣን ርምጃዎች ሁሉ አስቀድሞ ታስቦባቸዋል። ለዕቅዳቸው ስኬት ደግሞ ተባባሪ ባለውለታዎቻቸውን አልረሱም። እነርሱን በቅርበት መያዙ መውጫ መግቢያውን ለማወቅ ያግዛል። ለእንዲህ አይነቱ ታላቅ ጉዳይም ሁነኛ የመረጃ ስንቆች ይሆናሉ።ያለነርሱ ዓላማቸው የሳሳ፣ ውጥናቸው የኮሰሰ እንደሚሆን ተረድተዋል። እስከዛሬ በመረጃ አቀባዮቻቸው እየታገዙ ብዙ እቅዶቻቸውን አሳክተዋል። ከጥቅማቸው እያጋሩ፣ ከቀመሱት እያላሱ በርካቶቹን ድልድይ አድርገው ተሻግረዋል። አሁንም ስራቸውን ያለኮሽታ ለማጠናቀቅ ያሰቡትን ውስጥ አዋቂ በእጃቸው ይዘዋል። በእርሱ እየተመሩ መንገዱን ያለስጋት ይጀምሩታል። በሚያልፍበት እያለፉም ካሰቡበት ይደርሳሉ።
ይህን ታላቅ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ልበ ደንዳና መሆን ያስፈልጋል። ይህ ስሜት ደግሞ ሁሌም ከእነሱ ጋር የኖረ ነው። የሁልግዜው ጭካኔና ድፍረታቸው ደብዝዞ አያውቅም። ጄቴላንና ቤተሰቦቿ ስራቸውን አጠናቀው በጊዜ በቤታቸው ታድመዋል። ከትንሽ የዕረፍት ቆይታ በኋላ ደግሞ ከቤት የሚወጡበት ጉዳይ አላቸው። ጊዜው ከምሽቱ አንድ ሰአት ከሰላሳ መሆኑን ያመለክታል። በዚህ ሰዓት ከቤት ርቆ ጉዳይን ለመከወን ይከብዳል። ቤተሰቡ ግን ይህ አላስጨነቀውም። ያሻው ስፍራ ደርሶ ለመመለስ የቤት መኪናውን ይጠቀማል። አዛውንቱ የጥበቃ ሰራተኛ አባ ደምሴ ቤተሰቡ ከወጣ በኋላ እንደወትሯቸው ዙሪያ ገባውን ጎብኝተው ተመልሰዋል። የዋና በሩንም ከዕለቱ ወጣት ተረኛ ዘብ ደነቀ ጋር ተባብረው ዘግተዋል። ትንሹ የእግረኞች በር ቁልፍ ስለሌውና ጠባብ ስለሆነ እንደነገሩ መለስ አድርገውታል። ከመግቢያው ትይዩ ተቀምጠው ደጁን እየተቆጣጠሩ ነው። ብርዱ አንጀታቸው ሲገባ ይታወቃቸዋል። አባ ደምሴ በድንገት ከበስተኋላቸው አንድ ድምጽ የሰሙ መሰላቸው። እሱን ተከትለው ዞር ከማለታቸው ግን ከአስደንጋጩ እውነታ ጋር ተጋፈጡ። አምስት ሰዎች ወደ እርሳቸው እየመጡ ነው።
ሁሉም በአለባበሳቸው ይለያሉ። ሳንጃና ጩቤ ታጥቀው ፊታቸውን በጭንብል ሸፍነዋል። አባ ደምሴ ልክ እዳይዋቸው ለመጮህ ሞከሩ። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን በፈርጣማ እጆች ታንቀው የኋሊት ወደቁ። ባለጭንብሎቹ ሽማግሌውን መሬት ለመሬት እየጎተቱና ተቀባብለው እያንገላቱ ወደ ጓሮ ወሰዷቸው። በጀርባቸው አስተኝተውም በወፍራም ፕላስተር አፋቸውን አሸጉት። ሁለቱን እጆቻቸውን ወደ ኋላ የፊጥኝ አስረው ወደ ዕቃ ማስቀመጫው ኮንቴነር አስገቧቸው። ይህ ሁሉ ሲሆን ለአፍታ እንኳን እረፍት እልሰጧቸውም። በእርግጫ እያሽቀነጠሩ፣ በጥፊ እያቃጣሉ አሰቃይ ዋቸው። ጥበቃው የእነርሱን ድርጊት መቃወማቸው አናዷቸዋል። ለመጮህ ማሰባቸውንም ከድፍረት ቆጥረውታል። እናም «ይገባቸዋል» ያሉትን ማስፈራራትና ከባድ ምት እያሳረፉባቸው ነው። ከመንገላታቱና ከድብደ ባው በኋላ አዛውንቱ ጥበቃ ስቃያቸውን ውጠው በዓይናቸው መታዘብ ይዘዋል። ከሰዎቹ መካከል አንደኛውን በድምጽ የሚያውቁት መስሏቸው ደነገጡ። በእርግጥም አልተሳሳቱም። ፊቱን ሸፍኖ ድርጊቱን የሚያስተባብረው ወጣት አብሯቸው ያመሸው ተረኛ ዘብ ነበር። አዎ! ጥበቃው ደነቀ ለምሽቱ እንግዶች ውስጥ አዋቂያቸው ነው።
እስካሁንም በእርሱ ምሪት ታግዘው ያሰቡትን አድርገዋል። ጊዜው እየገፋ ጨለማው እየበረታ ነው። ከሶስት ሰዓት በኋላ የፒያሳ ጎዳናና አካባቢው ከእግረኞች ግርግር ይታቀባል። ከወዲያ ወዲህ የሚሮጡ የጎዳና ልጆችና ከየመዝናኛ ቤቱ ጎልቶ የሚወጣ ሙዚቃም ስፍራውን ተቆጣጥሮት ያመሻል። ከፒያሳ አፋፍ ቆልቆል ብለው ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ ሲሻገሩ ደግሞ ይበልጥ መቀዛቀዙ ይታያል። አብዛኞቹ ህንጻዎች የቀን ንግድ ቤቶችና የመኖሪያቤቶች በመሆናቸው ተዘግተው ያመሻሉ። ከምሽቱ አራት ሰዓት እያለፈ ነው። የስፍራው ጭርታ ጨምሯል፤ የተለመደው ቅዝቃዜ ጀምሯል። በድንገት ግን የጨለማውን ግዝፈት ያሸነፈ ረጅም ብርሀን ታየ። እሱን ተከትሎም ጭርታውን የሚሰብር የመኪና ጡሩንባ ተሰማ። ይሄኔ ፊቱን በፎጣ የጠመጠመ አንድ ሰው እየተጣደፈ በሩን ወለል አድርጎ ከፈተው። ወዲያው ከደጅ የቆመው መኪና ወደግቢው ዘለቀ። ቦታ ለመያዝም አቅጣጫውን ቀይሮ ወደማደሪያው ተጠመዘዘ። አሁን አምስቱ ሰዎች ከተደበቁበት ጥግ ወጥተዋል። ሁሉም ፊታቸውን በጭምብል ሸፍነው በመከላከያ ሰራዊት ልብስ ይታያሉ።
በእጃቸው የያዙት የፖሊስ ዱላ እህል ውሃ አያሰኝም። ያገኘውን ሁሉ ለመጨርገድ የተዘጋጀ ይመስላል። ከነርሱ መሀል ሁለቱ ድንገት መዘው ያወጡትን ቢላዋ እያብለጨለጩ ነው። ከመካከላቸው አንዱ ማጭድ መሳይ ባለጥርስ ቢላዋውን እያወዛወዘ ወደፊት ቀርቧል። በድንገቴው ከበባ ብርክ የያዛቸው አራት ቤተሰቦች ባሉበት ሆነው እየተንቀጠቀጡ ነው። ጄቴላን የመኪናውን በር የከፈተላትን ወጣት ጥበቃ ለይታዋለች። ሁሌም ፊቱን የሚሸፍነው ወጣት ደነቀ ነው። ሌሎቹም ቢሆኑ ከእሷ የተለየ ግምት የላቸውም። ፊት ለፊት የተጋፈጧቸው ቡድኖች ወደእነሱ ቀርበዋል። አመጣጣቸው በፍጥነት፣ ንግግራቸውም በታላቅ ቁጣ ሆኗል። የመኪናውን የፊት በር በርግዶ የከፈተው
አንደኛው ባለጭንብል ሾፌሩን ከጋቢናው እየጎተተ አወረደው። ይህኔ እናት አባቱ በድንጋጤ እየጮሁ ሊያስቆሙት ሞከሩ። ነገሬ አላላቸውም። የልጁን አንገት እንቆ እንደያዘ ከመሬት ላይ አንጋለለው። ወዲያው ፕላስተር ይዘው የቆሙት ባልንጀሮቹ በአፉ ላይ ለጥፈውበት ወደቀሪዎቹ ቤተሰቦች አመሩ። ጄቴላንንና አዛውንት እናትና አባቷን በተመሳሳይ ዝም ለማሰኘት ጊዜ አልወሰደባቸውም። የምሽቱ እንግዶች መላውን ቤተሰብ በገዛ ቤታቸው ተቆጣጥረው ያሻቸውን ማድረግ ይዘዋል። ሁሉንም በሲባጎ ገመድ ከወንበር ጋር ጠፍረውም በስል ጩቤዎቻቸውና በያዙት ሽጉጥ እያስፈራሯቸው ነው። ከዚህ በኋላ ቀጣዩን ስራ ለመከወን መንገዱ ቀና ነው። የሚጠበቁት ተይዘው ግቢው ጭር ብሏል። ትልቁ ቤት ዘልቀው ወደ መኝታ ቤት ሲያመሩ ከዘመናዊ ቁምሳጥኖች ጋር ተፋጠጡ።ጊዜ አልፈጁም። የወርቅና የአልማዝ፣ ጌጣጌጦች የሚገኝበትን ፈልቅቀው ባዘጋጁት ሻንጣ መክተት ጀመሩ። በርካታ የወርቅ ካቴናዎች፣ ጉትቻዎች፣ ውድ ዋጋ ያላቸው አርቴፊሻል ጌጦች፣ የእጅ ሰዓቶችና ሌሎችም ከእጆቻቸው ገቡ። ወርቅ ቅብ ዕቃዎችና የጸሎት መጽህፍቶቹንም አልማሯቸውም። ሰላሳ አምስት ሺህ የኢትዮጵያ ብርና ሌሎች የውጭ ሀገራት ገንዘቦችንም ሰበሰቡ። ሌሎች ቁምሳጥኖችን ከፍተው የሚፈልጉትን በአይነት እየለዩ አከማቹ። ሁሉን ጨርሰው የልባቸው ሲሞላም በውስጥ አዋቂያቸው ዘብ እየተመሩ በገቡበት ወጥተው ከአካባቢው ተሰወሩ።
የፖሊስ ምርመራ
ሲነጋ ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ ከስፍራው ደረሰ። የሆነውን ተመልክተውና የተደረገውን አረጋግጠው መረጃዎችን ሰበሰቡ። የአሻራ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ሁሉ በጥንቃቄ እየመዘገቡ ከመዝገባቸው ከተቱ። ተበዳዮችን ጨምሮ በአካባቢው ለምስክርነት የሚበጁ ማስረጃዎች ሁሉ አንድ በአንድ ተፈልገው ሰፈሩ። መዝገቡን የያዘው የምርመራ ቡድን በቴዎድሮስ አደባባይና አካባቢው የሚጠረጠሩ ደጋጋሚ ወንጀለኞችን ጠንቅቆ ያውቃቸዋል። እነርሱን መነሻ አድርጎም በርካታ እውነታዎችን መለየት እንደሚቻል ያምናል። ይህ ሁሉ ከምርመራው ክፍል አንዱ ነው። ይህ ብቻ ግን በቂ አይሆንም። በቡድን የተደራጀ የፖሊስ ሀይል ጉዳዩን በጥንቃቄ ይዞታል። ድርጊቱ ሁሌም ሰላማዊነቷን ለሚመሰክሩላት ኢትዮጵያና አምነዋት ለሚኖሩባት የውጭ ዜጎች ሁሉ በጎ ገጽታን የሚያበላሽ ነው። እናም ስለ ሀገሪቱ መልካም ስም ሲባል ተጠርጣሪዎቹ በፍጥነት ሊያዙ ግድ ይላል። የምርመራ ቡድኑ ሳይሰለች መረጃ ማሰባሰቡን ተያይዞታል። አሁን የቀን ከሌቱ ድካም ፍሬ ይዟል። በጥርጣሬ የተያዙት፣ ከተያዙትም እውነቱን ያመኑት፣ድርጊቱን ሁሉ ለፖሊስ ተናዘዋል። በምርመራው ሂደት ወጣቱ ጥበቃ ደነቀ ሀብቱ አስራ አምስት ሺህ ብርና የተለያዩ ጌጣጌጦችን ከቀበረበት ጉድጓድ አውጥቶ አስረክቧል። ፖሊስ ሌሎችንም መረጃዎች አጠናክሮ መዝገቡን ለክስ አቅርቧል። ተከሳሾች በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጧል።
ውሳኔ
መስከረም 29 ቀን 2006 ዓ.ም ማለዳ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ተሰይመዋል። ክስ ከቀረበባቸው አምስት ተከሳሾች መሀልም የሶስቱን ለማየት ተዘጋጅተዋል። ደበበ ዘሩ፣ ጌታነህ ብርሀኑና ደጉ በላቸው እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንድ እስከሶስተኛ ተከሳሾች ሆነው ቀርበዋል። የመሀል ዳኛው ዛሬ ከመጨረሻ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የክሱን ዝርዝር እያነበቡ ነው። ሶስቱ ግለሰቦች በውጭ ሀገር ዜጎቹ ላይ በፈጸሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል አንደኛ ተከሳሽ በአስራ ሁለት ዓመት ጽኑ እስራት፤ ሁለተኛና ሶስተኛ ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በአስራ አንድ ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
መልካምስራ አፈወርቅ