እንደ “አድዋ ድል” ሁሉ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን በአንድ ጥላ ስር ማሰባሰብ የቻለ፣ የመላ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ የገዛና የሁሉም ዜጎች አሻራ ያረፈበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኃይል ማመንጫነቱ ባሻገር ለኢትዮጵያዊያን የአንድነታቸውና የትብብራቸው ማሳያ ነው።
የዛሬ 10 ዓመት ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ይፋ ሲደረግ በርካታ ወዳጅ አገራት ጭምር ሳይቀር ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር እንዲህ ያለ የባለ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪንና የካበተ ልምድን የሚጠይቅ ፕሮጀክት እንደ ኢትዮጵያ ያለች ድሃና ታዳጊ አገር ልትሰራው አትችልም የሚል ግንዛቤ አድሮባቸው ነበር። እርግጥ እነዚህ አገራት እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ቢፈጠርባቸው የሚገርም አልነበረም። ምክንያቱም ለበርካታ ዓመታት በዓለም ህዝቦች ዘንድ ኢትዮጵያ ትታወቅ የነበረው በጦርነት፣ በኋላ ቀርነት፣ በረሃብና በድርቅ እንጂ በመልካም ጎኗ አልነበረም።
ነገር ግን መንግስትና ህዝብ የይቻላልን መንፈስ ሰንቀው ትኩረታቸውን ድህነትን መዋጋት ላይ በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእውቀታቸው፣ በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በቁሳቁስ አቅርቦት ከመንግስት ጎን በመቆም አይደፈርም የተባለውን የአባይን ወንዝ ደፍረው ግድቡን መገንባት ተያያዙት።
ይህ ግድብ ለእኛ ኢትዮጵያዊያኖች የ“አይቻልም” መንፈስን የሰበረ፣ የህዝቦችን የትብብርና የአንድነት መንፈስ ያጎለበተ ተምሳሌታዊ ፕሮጀክት ቢሆንም ቅሉ፤ በተለይ ከለውጡ በፊት የነበረው አመራር ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ህብረተሰቡን የቱርፋቱ ተካፋይ ከማድረግ ይልቅ፤ በህዳሴ ግድቡ ስም ከድሃ መቀነት የተሰበሰበውን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው በማዋል፤ ህዳሴ ግድቡ “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” የሆነበት የኢትዮጵያ ህዝብ የፕሮጀክቱ እውን መሆን ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አድሮበት ከፍተኛ ኩርፊያ ውስጥ መግባቱ የአደባባይ ሚስጥር ነበር።
ሕወሓት መራሹ መንግስት ፕሮጀክቱን በ2003 ዓ.ም ጀምሮ በ2007 ዓ.ም ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምርና አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ደግሞ በ2009 ዓ.ም ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፤ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ቀነ ገደብ ከማጠናቀቅ ይልቅ እንደሃብት ማካበቻና መዝረፊያ መንገድ በመጠቀም ለግድቡ ግንባታ ድሃው ህብረተሰብ ጾሙን እያደረ የሚዋጣውን ገንዘብ መመዝበሩን ተያያዘው።
መጀመሪያ ፕሮጀክቱን ሙሉ ለሙሉ ለማከናወን ጨረታውን ያሸነፈው ሳሊኒ የተሰኘው የጣሊያኑ ተቋራጭ ነበር። ነገር ግን ከለውጡ በፊት የነበረው አመራር ለፕሮጀክቱ የሚዋጣውን ገንዘብ ለመዝረፍ ያመቸው ዘንድ ፕሮጀክቱ በተጀመረ በሰባት ወር ገደማ የግድቡን እምብርት ስራ የሆነውን የኤሌክትሮ መካኒካል ስራውን ለብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አሳልፎ በመስጠት ግድቡን ቅርቃር ውስጥ ከተተው።
ሕወሓት መራሹ መንግስት ትልቅ ዕውቀትና ልምድ የሚጠይቀውን የኤሌክትሮ መካኒካል ስራውን ከዚህ በፊት መሰል ፕሮጀክቶችን ሰርቶ ለማያውቅ ልምድና እውቀቱ ለሌለው ለሜቴክ አሳልፎ በመስጠቱ የግድቡ ስራ ከመጓተቱ ባሻገር የኤሌክትሮ መካኒካልና የብረታ ብረት ስራው ፕሮጀክቱን የማይመጥን፣ አበያየዱ የግድቡን እድሜ የሚያሳጥርና የሁሉንም ልማት መና የሚያስቀር ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እንዳሉትም እንኳን ገድብ መስራት ይቅርና ትልቅ ግድብ አይቶ ለማያቅ ሜቴክን ለመሰለ ድርጅት የህዳሴ ግድብን የመሰለ ትልቅ ፕሮጀክት እንዲሰራ መፍቀድ በሀገር ሃብት ላይ መቀለድ ነው፡፡
መሬት ላይ የነበረው እውነታ ይሄ ሆኖ እያለ ውሸት እስትንፋሱ የሆነው የጁንታው ቡድን ይባስ ብሎ ግድቡ ያሉበትን ችግሮች በመደበቅና እውነታን መሰረት ያላደረገ ተስፋን ለህዝብ በመስጠት መሬት ላይ የሌለ በሬ ወለደ ወሬውን መንዛቱን ተያያዘው።
በዚህም ሕወሓት መራሹ መንግስት እዚህ ግባ የሚባል ስራ ሳይሰራ ህዝቡን “ነገ ኤሌክትሪክ ኃይል ልታገኝ ነው። በአሳ ምርት ልትንበሸበሽ ነው። ውሃ ጥምህን ልትቆርጥ ነው። በመስኖ አልምተህ ጎተራህን ልትሞላ ነው” የሚሉ የመደለያ ቃላቶችን በማዠጎድጎድ፤ ህዝቡ ነገ ያልፍልኛል በሚል ጾሙን እያደረ ለግድቡ ግንባታ የሚያዋጣውን ገንዘብ ግልጽነት በጎደለውና የተጠያቂነት በሌለበት መንገድ ስራ ላይ እንደዋለ በማስመሰል ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ ከድሃው ኪስ የተዋጣውን ገንዘብ አሸባሪው ቡድን ወደ ኪሱ አስገብቶታል።
በጥቅሉ ሕወሓት መራሹ መንግስት ፕሮጀክቱ በአምስት አመታት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይውላል በሚል ቃል ቢገባም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በከፈለው መራራ መስዋዕትነት በ2010 ዓ.ም በአገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጥ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የግድቡ ግንባታ እውን መሆኑ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቶ ተሰነካክሎ ነበር ማለት ይቻላል። አብዛኛው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራው ተኮላሽቶ ግድቡ በዘመናት ሂደትም ቢሆን የማያልቅ ግድብ ወደ መሆን ተቃርቦ ነበር፡፡
በ2003 ተጀምሮ በ2009 ዓ.ም ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል የተባለው ይህ ፕሮጀክት ጁንታው በ2010 ዓ.ም ከስልጣን ገሸሽ ባለበት ወቅት ሲፈተሽ፤ ግድቡ 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የዋናው ግድብ ከፍታ 145 ሜትርና ርዝመቱን 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ማድረስ ይጠበቅ ነበር።
ከዚህ አኳያ ህዳሴ ግድቡ የሚገነባበት ቦታ በራሱ 500 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ከፍታ ያለው ቦታ ነው። ለውጡ እስከመጣበት ጊዜ ግድቡ ከባህር ወለል በላይ 525 ሜትር ከፍታ ላይ ብቻ ነበር ማድረስ የተቻለው። ማለትም ከ2003 አስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ሰባት ዓመታት የዋና ግድቡ ግንባታ 25 ሜትር ከፍታ ብቻ ነበር የተሰራው።
የሲቪል ስራውን የሚሰራው ሳሊኒ የኮርቻ ግድቡን (ሳድል ዳሙን) እና የግራ ቀኙን የግድቡን ግንባታ ከፍ ቢያደርግም ሜቴክ ሲያከናውነው የነበረው የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው በመጓተቱ ሳሊኒ ስራውን ሊሰራ አልቻለም። ይህም ሳሊኒ ዋናው ውሃ የሚያዝበትና ኤሌክትሪክ ማመንጫ ተርባይን የሚተከልበትን የግድቡን የሲቪል ስራ በወቅቱ ለመስራት አልቻለም። በሜቴክ ኋላ ቀር የግንባታ አፈጻጸም ምክንያትም ዓለም አቀፉ የግንባታ ድርጅት ሳሊኒ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጉንም ይህንንም ኪሳራ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲከፍልለት ሲማጸን ተሰምቷል፡፡
በዚህም ፕሮጀክቱ ስድስት ዓመት በመዘግየቱ በየአንዳንዱ አመት ኢትዮጵያ አንድ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንድታጣ ሆናለች። ግድቡ በመዘግየቱ ምክንያት በየጊዜው አገሪቱ ወጪ የምታደርገውን ዶላር ሳይጨምር ስድስት ዓመት በመዘግየቱ ስድስት ቢሊዮን ዶላር አጥታለች። ሜቴክ ስራውን በተገቢው ፍጥነትና ጥራት ባለመከናወኑ ፕሮጀክቱ በመዘግየቱ፤ የሲቪል ተቋራጩ ኪሳራ ውስጥ በመግባቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ካሳ ሊጠይቅም ችሏል።
እንዲሁም ሜቴክ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራውን ከማጓተቱ በላይ ስራው ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ አልነበረም። ይህም አገሪቱ ከፍተኛ ወጪ አውጥታ ልታገኝ ያሰበችውን ጥቅም የሚያሳጣና ግድቡ ለይስሙላ እንጂ የታሰበውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አያስችልም ነበር። ከዚህ ባሻገር በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ላይ የደህንነት ስጋት የደቀነ ነበር።
በተጨማሪም ከለጡ በፊት የነበረው አመራር በነበረው የፕሮጀክት አስተዳደር ችግር ምክንያት ሃገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ የዳረጋት ሲሆን፤ የግድቡን ኃይል ለማስተላለፍ ተብሎ ከህዳሴ ግድቡ እስከ ሆለታ ድረስ የተዘረጋው አገር ውስጥ ካሉት ከፍተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ የትኛው ፕሮጀክት መቅደም እንዳለበት ሳይተሳሰብበት በዕውቀት ማነስ ቀድሞ በመሰራቱ ከአራት ዓመት በላይ ያለምንም አገልግሎት ቆሞ ይገኛል። ይህም አገሪቱ በሌላት የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ወጪ አውጥታ ሰርታ ያለምንም አገልግሎት አስካሁን ድረስ በመቀመጡ አገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጋት ይገኛል።
በጥቅሉ የግድቡ እውን መሆን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቶ እያለ ወደ ስልጣን የመጣው የለውጡ አመራር ግድቡ ያሉበትን ውስብስብ ችግሮች በማጤን የመፍትሄ እርምጃዎችን በመውሰድ ግድቡን ከሞት መታደግ የቻለ ሲሆን፤ በመጀመሪያ የለውጡ አመራር የወሰደው እርምጃ አስተዳደር ቦርድ ማቋቋም ነበር። አመራሩን ማስተካከል ብቻ በቂ ስላልነበር፤ ስራውን በብቃትና በጥራት የሚሰሩ ልምድ ያላቸው ተቋራጮችን ማምጣት ነበረበት።
በዚህም ሙሉ ለሙሉ በሳሊኒና በሜቴክ ተይዞ የነበረውን የፕሮጀክቱን ስራ፤ ሜቴክ ከፕሮጀክቱ እንዲወጣ ሲደረግ በሱ ፋንታ ስድስት መሰል ግዙፍ ፕሮጀክት የሰሩ፣ ብቃታቸው የተመሰከረላቸው የአውሮፓ ተቋራጮችን ወደ ፕሮጀክቱ እንዲገቡ ተደርጓል። ከሳሊኒ ጋር ደግሞ የሲቪሉን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል መግባባት ላይ ተደርሶ ስራውን እያቀላጠፈ ይገኛል።
ይህ ከተደረገ በኋላ ከለውጡ በፊትና ለውጡ ከመጣ በአጭር ጊዜ ወስጥ የተሰራውን ስራ ብናይ ግድቡ እንደሰው አፍ አውጥቶ አይናገር እንጂ ለውጡ የመጣው ለህዳሴ ግድቡ ጭምር ነው ማለት ይቻላል። ምከንያቱም ለውጡ በመጣ በአንድ ዓመት ተኩል ወስጥ የዋና ግድቡን ግንባታ 25 ሜትር ከፍታ ብቻ የነበረውን ተጨማሪ 35 ሜትር በመስራት ግድቡን ከባህር ወለል በላይ ወደ 560 ሜትር ከፍ ለማድረግ ተችሏል።
እንዲሁም ሜቴክ ይዞት የነበረው የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው ደግሞ ከፍተኛ የጥራት ችግርና የደህንነት ጥያቄ የሚነሳበት ስለነበር፤ ስራው ከለውጡ በኋላ ከዜሮ እንዲጀመር ተደርጓል። በዚህም የኤሌክትሮ መካኒካል ስራውን ጥራቱን በጠበቀ መንገድ በማሳለጥ በአንድ ዓመት ከመንፈቅ ውስጥ 27 በመቶ ማጠናቀቅ ተችሏል።
ከለውጡ በፊት አጠቃላይ የግድቡ ስራ ከ60 በመቶ የማይበልጥ የነበረ ሲሆን፤ ለውጡ በመጣ በአንድ አመት ከመንፈቅ ውስጥ የሲቪል ስራውን 87 በመቶ፣ የተርባይን ተከላና የብረታብረት ስራውን ከዜሮ በመጀመር በቅደም ተከተል 44 በመቶና 27 በመቶ በማጠናቀቅ አጠቃላይ የግድቡን የሲቪልና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራውን ከ73 በመቶ በላይ ለማጠናቀቅ ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም አጠቃላይ የግድቡ ስራ 80 በመቶ አካባቢ ደርሷል፡፡
ይህም አገሪቱ በ2012 ዓ.ም መጨረሻ የግድቡን የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት በስኬት እንድታከናውን ያስቻላት ሲሆን፤ ከለውጡ በፊት በነበረው የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌት በ2015 ዓ.ም ማከናወኗ እራሱ አጠያያቂ ነው።
በ2012 ዓ.ም ክረምት ግድቡ የያዘው 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ማለት የግቤ አንድ የኤሌክትሪክ ውሃ ማመንጫ ሶስት እጥፍ ማለት ሲሆን፤ በ2013 ዓ.ም ደግሞ የዋና ግድቡን ግንባታ ተጨማሪ 35 ሜትር በመስራት ግድቡን ከባህር ወለል በላይ ወደ 595 ሜትር ከፍ በማድረግና ጎን ለጎን ደግሞ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራውን በማሳለጥ አጠቃላይ የግድቡን ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ በማጠናቀቅ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ማከናወን ተችሏል።
በዚህም ወደ 18.4 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ በመያዝ ግቤ አንድ፣ ሁለትና ሶስት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች ማመንጨት የሚችሉትን ያክል ተጨማሪ አቅም የተፈጠረ ሲሆን፤ ከነሃሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ በሁለቱ ተርባይኖች 700 ሜጋ ዋት ሀይል ማመንጨት ይጀመራል ማለት ነው።
የለውጡ አመራር የዋና ግድቡን ግንባታ ተጨማሪ 50 ሜትር በመስራት ግድቡን ከባህር ወለል በላይ ወደ 645 ሜትር ከፍ በማድረግና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራውን በዛው ልክ በማሳለጥ በ2015 ዓ.ም የግድቡን አጠቃላይ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ግድቡ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በመያዝ ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ለማመንጨት ከወዲሁ በትጋት እየሰራ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪ የለውጡ አመራር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፈርና የአካባቢ አጠባበቅ ፖሊሲ ክፍተት ባለባቸው አገራት የኃይል ማመንጫ ግድቦች በደለል ተሞልተው እድሜያቸው የማጠር እድላቸው ሰፊ መሆኑን በመረዳት፤ በአራት አመታት ውስጥ ከ20 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ደለልን የመከላከል ስራ ከወዲሁ ታስቦበት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ይህም ነገ ላይ ችግኞቹ አድገው የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ግድቡ በደለል እንዳይሞላና የግድቡን እድሜ ከማራዘም ባሻገር አመቱን ሙሉ በአገሪቱ ዝናብ እንዲኖር ስለሚያደርግ የታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት በቂ ውሃ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
እንዲሁም ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ፕሮጀክቱ በመዘግየቱ የሲቪል ስራውን የሚሰራው ሳሊኒ የተሰኘው ተቋራጭ ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ካሳ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፤ መንግስት ተቋራጩ ያቀረበውን የካሳ ይገባኛል ጥያቄ በድርድር መፍታት ባይቻል ኖሮ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ዛሬ ላይ ያሳካናቸውን ወሳኝ ምዕራፎች ማሳካት አንችልም ነበር፡፡ በተጨማሪም ከለውጡ በፊት ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተገመተ ዕዳ ያጋጠመ ሲሆን፤ ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ በኋላ ግን በግድቡ ላይ የአንድ ብር ዕዳ እንኳ እንዳልተመዘገበ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሁሌም አይናቸው ከህዳሴ ግድቡ የማይነቀለው የታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ለውጡ ከመምጣቱ በፊት የነበረው ዓመራር ግድቡን ሽባ አድርጎ የፕሮፓጋንዳ መንፊያ ማድረጉን በመረዳታቸው ያን ያህል የዲፕሎማሲ ጫና ሲያሳድሩ አይስተዋልም ነበር። ግድቡም እንደመከነ ስለተረዱም ትኩረታቸውን ከግድቡ ላይ አንስተው ቆይተዋል፡፡
ነገር ግን በለውጡ የግድቡ ስራ ከልብ መሰራት ሲጀምርና ግድቡ እውን መሆኑ የሚያጠያይቅ አለመሆኑን የተረዳችው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሆነችው ግብጽ፤ በመንግስትና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የዲፕሎማሲ ጫና ከማሳደር ባለፈ የህዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌት ጉዳይ እስከ ተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ ብትወስደውም በመንግስት የሰላ የዲፕሎማሲ አካሄድ ድል ተደርጋለች።
የኢትዮጵያን እድገት ሁሌም የማይዋጥላቸው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጥላቶች ግን በዲፕሎማሲ ጫናው አልሳካለቸው ሲል የዕጅ አዙር ጦርነት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፍተዋል። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ይሄንን የተከፈተባቸውን የዕጅ አዙር ጦርነት በአንድነት ድባቅ መትተው ወደ ብልጽግና ማማው መውጣታቸው ግን አይቀሬ ነው።
በአጠቃላይ ለውጡ የኢትዮጵያን ህዝብ ከጭቆና ቀንበር እንዳላቀቀው ሁሉ ህዳሴ ግድቡንም ከሞት ነው የታደገው። ከህዝቡ ባሻገር ለውጡ ለህዳሴው ግድቡ የመጣ መሆኑን የአለም ህዝብ በአንድ ድምጽ መስክሯል። ለዓብነት የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ሁለተኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተጠናቀቀ ማግስት እንዲህ ስትል ለአለም ህዝብ እንደሚከተለው አስተጋብታለች።
“ተፈጥሮ ተገዳ ሳይሆን አገሪቱ አስገድዳ እድለኛ አድርጋዋለች። ወታደርም መሳሪያም ዘበኛም አያስፈልገውም። ማንም የምድራችን ሀይለኛ ነኝ የሚል መሳሪያ አይነካውም። ምናልባት አንድ አቶሚክ ቦንብ ሊዳፈረው ይችላል። ለሱ የተላከው ቦንብ ግን አንድ ግድብ ብቻ ነው የሚነካው። ጥቃት የተሰነዘረበት ግድብ ግን ለጥቃቱ የሚሰጠው መልስ ከ40 ሚሊዮን በላይ ዜጎችንና የሁለት አገር ትልልቅ ከተሞችን ማለትም የሱዳንን ዋና ከተማ ካርቱምን፣ የግብፅን ዋና ከተማ ካይሮን ያለምንም ከልካይ፣ አፍርሶና ወደ አፈር ቀይሮ ከውሀ ጋር ቀላቅሎ ነጭ ባህር ይጨምራል።
ማንኛውም የአለማችን መሳሪያ ነው ከኢትዮጵያ እስከ ነጭ ባህር ድረስ ከተሞችንና የመሰረተ ልማቶችን፣ ህዝቦችን እየጠራረገ ነጭ ባህር የሚዶለው ? እስካሁን ድረስ ይህ መሳሪያ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ጉባ ተራራ ሸለቆ ላይ የተጠመደ፣ አንድ አፍሪካዊ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ፣ መሳሪያም ወታደርም ዘበኛም የማያስፈልግ እድለኛው የአባይ ግድብ ብቻ ነው። አዎ አንተ እድለኛ ነህ! በአለማችን ላይ ከህፃናት እስከ አዋቂዎች ስምህን የሚያውቁት ! ራስን በራስህ ያስከበርክ !” ስትል ጋዜጠኛዋ ልታሞካሸው የወደደችው በለውጡ በተደረገ መራራ የዲፕሎማሲ ትግልና ስራ እንዲሁም ህዝቡ ጦሙን እያደረ ለግድቡ ባደረገው ድጋፍ ነው።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2013