የልብ ጉዳይ ልብ ይባል!!

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና አገልግሎት በተወሰኑ የመንግሥት ጤና ተቋማት ውስጥ ይሰጥ የነበረ ቢሆንም ከፍተኛ የአገልግሎት ውስንነት እንደነበረበት ይታወቃል። በዘርፉ የሰለጠኑ የሕክምና ባለሞያዎችም ቁጥር እጅግ አናሳ በመሆኑ የሚሰጡት የሕክምና አይነቶችም በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ።

በሌላ በኩል ደግሞ ሕክምናውን ለመስጠት የሚያስችሉ መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ አልነበሩም። በዚህም ምክንያት በልብ ሕመም የሚሰቃዩ ዜጎች እጣ ፋንታ ከሕመማቸው ጋር እየታገሉ መኖር ወይም ሞት ነበር ማለት ይቻላል። በተለይ ደግሞ ሕፃናት የልብ ታማሚዎች ሕክምና አጥተው ለስቃይና ለሞት ሲዳረጉ ማየት በወቅቱ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነበር።

በመንግሥት ብቻ ከሚሰጠው የልብ ሕክምና አገልግሎት ውጪ ከዛሬ ሶስት አስርት ዓመታት በፊት በዶክተር በላይ አበጋዝ ሀሳብ አመንጪነት አንድ ብሎ የጀመረው የልብ ሕክምና አገልግሎት ግን ለዚህ ሕክምና ዘርፍ ማደግ ትልቅ ተስፋ ፈንጥቋል። በተለይ ሕክምናው ሕፃናት ተኮር የነበረ በመሆኑ በግዜው በርካታ ሕፃናት የልብ ሕክምና አገልግሎት አግኝተው ወደጤናቸው መመለስ ችለዋል። በተመሳሳይ በወቅቱ እድሉ ቀንቷቸው የታከሙ አዋቂዎችም ዳግም የመኖር ተስፋቸው ለምልሟል።

ለጋሽ ድርጅቶችን፣ ግለሰቦችን፣ በጎ ፍቃደኞችን፣ ደጋግ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች ተባባሪ አካላትን በማስተባበርና ድጋፋቸውን እንዲቸሩ በማድረግ በዶክተር በላይ አበጋዝ ፊት አውራሪነት የተጀመረው የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና አገልግሎት በብዙ ውጣውረዶች ውስጥ አልፎ ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

በወቅቱ በነበሩ የሕከምና መሳሪያዎችና የሕክምና ባለሞያዎች ተደራጅቶ ብዙ ኢትዮጵያዊያን የልብ ታማሚዎች ሕክምና እንዲያገኙ አስተዋፅኦ ያደረገው ይህ ድንቅ ሀሳብ ኋላ ላይ ጎልብቶ የኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል እንዲቋቋም በር ከፍቷል።

ከዛሬ ሰላሳ ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል ከተለያዩ ልበቀና ግለሰቦችና ሀገር በቀል እንዲሁም ከሀገር ውጪ ካሉ ድርጅቶች በሚያገኘው እርዳታ አማካኝነት እስካሁን ድረስ ከ3 ሺ በላይ ሕፃናት ያለምንም ክፍያ እንዲታከሙ አድርጓል። ለበርካታ ሕፃናትም ትልቅ የሕይወት መድህን ሆኗል።

ዛሬም ይህንኑ ድንቅ ተግባር በመከወን የብዙ ኢትዮጵያዊያንን በሕይወት የመኖር ተስፋ እያለመለመ ይገኛል። ዛሬም ድረስ ብዙ የልብ ታማሚ ሕፃናት ይህንኑ ማዕከል ተስፋ አድርገው ለመታከም ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

እንዲያም ሆኖ ግን ማዕከሉ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚላኩ ታካሚዎችን የሚያስተናግድ በመሆኑና አሁን ባለው የልብ ታማሚዎች ቁጥር ልክ ተደራጅተው የልብ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ሌሎች ማዕከላት በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው አሁን ላይ ከ7 ሺ በላይ ሕፃናት የልብ ቀዶ ሕክምና ለማግኘት በወረፋ ላይ ናቸው።

በማዕከሉ በተመላላሽ ሕክምና ክፍል በዓመት ከ13 አስከ 14 ሺ የሚሆኑ ሕፃናት ክትትል ያደርጋሉ። በአንድ ዓመት ከ400 አስከ 450 የሚሆኑ ሕፃናት ደግሞ ቀዶ ሕክምና ይደረግላቸዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከ780 እስከ 1000 የሚሆኑ አዳዲስ ታካሚዎችን መርጃ ማዕከሉ ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል። ይህ በንፅፅር ሲታይ የአዳዲስ ታካሚዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል።

ማዕከሉ ያሉበትን ችግሮች ተቋቁሞ የልብ ሕክምና አገልግሎቱን ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ቢሆንም አንድ ነገር ግን ተዘንግቷል። ሁሉም እንደሚያውቀው ይህ ማዕከል በኢትዮጵያ አንድና ብቸኛ የልብ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ነው። አብዛኛው በተለይ ደግሞ አቅም የሌለው ታካሚ የሚጎርፈውም ወደዚህ ማዕከል ነው። ይህ ደግሞ ማዕከሉ ላይ ምን አይነት ጫና ሊያሳድር እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

ማዕከሉ አሁን ባለው አቅም ደግሞ ከመላው ኢትዮጵያ የልብ ሕክምና አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ዜጎችን ማስተናገድም አይችልም። አንደኛ ይህን ሁሉ ታካሚ ሊያስተናግድ የሚችል በቂና የተሟላ የሕክምና መሳሪያዎች እንዲሁም መሰረተ ልማት የለውም። ሁለተኛ ታካሚዎችን ያለወረፋ ተቀብለው የሚያስተናግዱ በቂ ባለሞያዎች የሉትም።

እስካሁንም ያለበትን ጫና ተቋቁሞ ለበርካታ ሕፃናት የልብ ሕክምና ተደራሽ መሆን የቻለው የተለያዩ ልበቀና ግለሰቦችና ሀገር በቀል እንዲሁም ከሀገር ውጪ ያሉ ድርጅቶች ባደረጉለት ድጋፍ ነው። ይህም ማዕከሉ በራሱ አቅም ብቻ የተሟላ የልብ ሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚያዳግተው ያሳያል።

ማዕከሉ በተቻለው አቅም ሁሉ ለሕፃናቱ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም አገልግሎቱን ከሚፈልጉ ሕፃናት ቁጥር ጋር በሚመጣጠን መልኩ ባለመስፋቱ፣ አስፈላጊ የሕክምና ግብአቶችን በየግዜው በቶሎ ባለማግኘቱና በበቂ ሁኔታ ድጋፍ እያገኘ ባለመሆኑ የልብ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቱን በሚፈለገው ልክ ለታካሚዎች ተደራሽ ማድረግ ተስኖታል። እንዲያም ሆኖ ግን በብዙ ደጋግ ኢትዮጵያውያን በየግዜው በሚደረግለት ድጋፍ እስካሁን ድረስ አገልግሎቱን ማስቀጠል ችሏል።

ለአብነት እንኳን የእዮብ ተስፋ ለልጆችና ለወጣቶች ተራድኦ ድርጅት ከ25 ሺ ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የልብ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የሕክምና ግብአቶችን ለልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ በቅርቡ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል። በዚህ ድጋፍ የተካተቱ የሕክምና ግብአቶች ለልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እጅግ አስፈላጊ የሆኑና በዋናነት የልብ ክፍተት ችግር ያለባቸው 40 ወረፋ በመጠበቅ ላይ ያሉ ሕፃናት በድጋፍ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸው ተነግሯል።

ከዚህ በፊትም ድርጅቱ 20 ሺ ዶላር ዋጋ ያላቸው ተመሳሳይ የሕክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጎ 32 ሕፃናት የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ከልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ በተጨማሪ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተመሳሳይ የሕክምና ግብአት ድጋፎችን ማድረጉ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ኑሯዋን በሰሜን አሜሪካ ያደረገችውና ከአራት ዓመታት ወዲህ ‹‹ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ›› በሚል መሪ ቃል የምትታወቀው ጋዜጠኛ ሕይወት ታደሰ የልደት ቀኗን ምክንያት በማድረግ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን የሕፃናት መርጃ ገቢ በማሰባሰብ በተለያዩ ግዚያት ሕፃናቱን ስታሳክም መቆየቷንና ከሰሞኑ ደግሞ ይህንኑ የልደት ቀኗን ምክንያት በማድረግ በዚሁ መርህ ለኢትዮጵያም ለማዕከሉም ብቸኛ የሆነውንና 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት፤ በማዕከሉ የሚሰጠውን ሕክምና በእጅጉ የሚያዘመን የሕክምና ቁሳቁስ ለማዕከሉ ማስረከቧ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል ተነግሯል።

ጋዜጠኛዋ ከዚህ ቀደምም ለማዕከሉ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ለልብ ቀዶ ሕክምና፣ በደም ስር ውስጥ ለሚደረግ ሕክምና እንዲሁም በፅኑ ሕሙማን ክፍል ለሚደረግ ሕክምና የሚሆኑና ከታካሚ አልጋ ጀምሮ ሕክምናው የሚሰጥባቸው አላቂ እቃዎችንና መድሃኒቶችን እንዲሁም በርካታ ጠቃሚ ድጋፎችን ለማዕከሉ ማድረጓም ተገልጿል።

ይህም ማዕከሉ አሁንም ድረስ ምን ያህል በግለሰቦችና ረጂ ድርጅቶች ድጋፍ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን ያሳያል። በተመሳሳይ ከእንዲህ አይነት ድጋፍ ተላቆ በራሱ መቆም እንደሚጠበቅበትም ያመላክታል። ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ላላት ሀገር ይህ መርጃ ማዕከል በቂ እንዳልሆነና በእርዳታ ድርጅቶች ብቻ ማዕከሉ ሊቀጥል እንደማይችል ይጠቁማል።

ማዕከሉ አሁን ባለው አቅም አንድ ሶሰተኛ ያህሉን የልብ ሕክምና ብቻ የማከናወን አቅም እንዳለውም ነው እየተነገረ ያለው። አሁን በኢትዮጵያ ካለው የልብ ሕሙማን ቁጥር አንፃር ደግሞ ቢያንስ የዚህን ማዕከል አይነት በበቂ የሕክምና መሳሪያዎችና ባለሞያዎች የተሟሉ 12 ተጨማሪ ማዕከላት እንደሚያስፈልጉ ተገልጿል። ስለዚህ አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሚታየውን የልብ ሕክምና አገልግሎት እጥረት ለመቅረፍ ተጨማሪ ማዕከላትን መገንባት ወሳኝ መሆኑ የማይታበል ሀቅ ነው። የልብ ሕክምና ማዕከላቱን የመገንባት ድርሻ ደግሞ የሁሉም ነው።

ማዕከላቱን በመገንባት ሂደት ከመንግሥት ጀምሮ ባለሃብቶች፣ ግለሰቦች፣ በጎ ፍቃደኞች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎችም አካላት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ማዕከላቱን ለመገንባት እርዳታዎቹ ከተለያዩ ቦታዎች ከመጡና ትብብርና ድጋፍ ካለ አሁን ላይ በማዕከሉ እየተሠራ ያለውንና በቀጣይ በሚከፈቱ ማዕከላት የሚሠሩ የልብ ሕክምና ሥራዎችን በእጥፍ እንደሚያሳድገው ይገመታል። የልብ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነቱም ይበልጥ እየሰፋ እንዲሄድ ያደርጋል።

የልብ ሕክምና ማዕከላትን ከመገንባት ባለፈ ባለሞያዎችን በበቂ ቁጥር ማፍራትም ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም። አሁን ካለው የልብ ሕመም አይነትና ብዛት አኳያ በኢትዮጵያ ያለው የልብ ሀኪም ቁጥር ተመጣጣኝ አይደለም። ስለዚህ በልብ ሕክምና የሰለጠኑ ባለሞያዎችን በሀገር ውስጥ ከማፍራት በዘለለ በሰብ ስፔሻሊቲ የሕክምና ዘርፎች ባለሞያዎች ከሀገር ውጪ ስልጠና አግኝተው ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል።

የልብ ሕክምና በባህሪው ውድና ለሕክምና መሳሪያዎቹ ግዢ የሚወጣው ወጪም ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን በተለይ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከልም ሆነ በቀጣይ ሊከፈቱ የሚችሉ የልብ ሕክምና ማዕከላት በበቂ የሕክምና መሳሪያዎች የተሟሉ እንዲሆኑና ያልተቆራረጠ አገልግሎት እንዲሰጡ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶች፣ ግለሰቦች፣ በጎ ፍቃደኞች ያልተቋረጠ የገንዘብና የመሳሪያዎች ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የልብ ሕክምና አገልግሎት ችግር የገዘፈና አሁንም ያልተቀረፈ ነው። ችግሩን ለመቅረፍም ገና ብዙ መሥራትን ይጠይቃል። መጠነ ሰፊ ድጋፍም ያስፈልገዋል። ለዛም ነው ‹‹የልብ ጉዳይ ልብ ሊባል ይገባል!! የምንለው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You