ጅግጅጋ፡- በክልሉ በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የመምህራን እጥረትን ለማቃለል እንዲቻል ለመምህራን የማበረታቻ ፓኬጅ ለመተግበር የሚያስችል ጥናት እየተደረገ መሆኑን የሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ። የቢሮው ሃላፊ አቶ አብዲላሂ መሐመድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ባለው የመምህራን ፍላጎትና አቅርቦቱ መካከል ሰፊ ክፍተት አለ። በተለይ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ችግሩ ሰፊ ነው። ይህ ደግሞ በመማር ማስተማሩና በትምህርት ጥራት ላይ የራሱ ተጽዕኖ ስላለው፤ ክልሉ የሚያስፈልጉትን መምህራን ለማግኘት እንዲችል በጥናት ላይ የተመሰረተ የመምህራን ማበረታች ፓኬጅ ለመተግበር እየሰራ ይገኛል። በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ተግባራዊ እንደሚሆንም ይጠበቃል።
እንደ አቶ አብዲላሂ ገለጻ፤ በክልሉ አሁንም ድረስ 90 በመቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ፍላጎቱን የሚሸፍነው ከሌሎች ክልሎች በመጡ መምህራን ነው። ሆኖም በቋንቋ ምክንያት ይህ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አለመኖሩ ፈተና ሆኗል። የክልሉ ተወላጆች ደግሞ በቂ ደመወዝና ማበረታቻ ስለማያገኙ እምብዛም አስተማሪ መሆን አይፈልጉም። በክልሉ ያሉ የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችም ጥቂት በመሆናቸው፤ በክልሉ ወደ አራት ሺ ለሚሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአንድ ዓመት ለአንድ ትምህርት ቤት አንድ ሰው እንኳን እመድባለሁ ቢባል 4000 ሰው ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው፣ ሦስት የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች ደግሞ በጥቅሉ በዓመት 700 መምህራን ነው ለገበያው የሚያቀርቡት ብለዋል። ይህ ደግሞ በፍላጎቱና አቅርቦቱ መካከል ሰፊ ክፍተት መኖሩን ያሳያል። በዚህም አስር አስተማሪ ሊኖረው የሚገባ ትምህርት ቤት በሁለትና አምስት አስተማሪ እንዲሰራ መገደዱን አስታውቀዋል።
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ መምህራንን ለመቅጠር ክልሉ ተወዳዳሪ ሆኖ ሰው እንደሚያገኝ የጠቆሙት አቶ አብዲላሂ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ግን ከፍተኛ ችግር ላይ ስላለ ይሄን ለማሻሻል እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም መምህርነትን የተሻለ ሙያ መሆኑን ለማሳየት እንደሚፈልጉና ጥሩ አቅም፣ ሙያና ስነምግባር ያላቸውን ሰዎች ወደ ማስተማር በማምጣት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የደመወዝ ችግሩን የመፍታት ጉዳይ በፌዴራል መንግስት የሚወሰን መሆን ለዚህ እርምጃቸው ምክንያት እንደሆናቸው በመጥቀስም፤ ጥናቱን መሰረት በማድረግ የሚከናወነው የመምህራን ማበረታቻ ፓኬጅ ለመምህራን በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ ላሉት የተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋል ሲሉ አብራርተዋል። ለዚህም የተለያዩ የማበረታቻ አማራጮችን እያዩ መሆኑንና ምናልባትም በዚህ ዓመት ከሐምሌ ወር አንስቶ ማበረታቸውን ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ወንድወሰን ሽመልስ