እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር ሴፕቴምበር 17 ቀን፣ 1787 ዓ.ም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ አለው ይለናል ትንታጉ ጉምቱውና ደማሙ ጋዜጠኛ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ ነፍሱን ይማርና ። መቼም በዚች ምድር እንደሱ ልቅም ጥንቅቅ ያለ አርበኛ ጋዜጠኛ ገጥሞኝ አያውቅም ። ወደተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ በጦቢያ ፣ ቅጽ 7 ፣ ቁ.2 ፣ 1992 ዓ.ም ፣”እኛም አንናገር እነሱም አይሰሙ፣የገዥዎቻችን እዳ የለብንም” በሚል ርዕስ ባስነበበን መጣጥፉ ። 39 ልዑካን ከ12 ግዛቶች ተወክለው የሕገ መንግሥት ጉባዔ መስርተው የውይይታቸውና የእጃቸው ፍሬ የሆነውን ሰነድ ለሕዝቡ ያቀረቡበት ዕለት ነበር ። እኔ ደግሞ ወሳኝ መታጠፊያ/critical juncture /እለዋለሁ ። ታሪኩ እንደሚለው በዚህ ዕለት አንዲት ሴት ቤንጃሚን ፍራክሊን ዘንድ ቀርባ፤”እህሳ ዶክተር ምን ተገኘ? ሪፐብሊክ ወይስ ግዛተ ዘውድ!”ብላ ትጠይቃለች። እሱም ወዲያው”ሪፐብሊክ ነው_ልትጠብቂው ከቻልሽ”(A Republic if you can keep it) ሲል መለሰላት ። ፍራንክሊን ይህን ያለው ሀገሩን ይዞ የስርዓተ መንግሥቱን ቅርጽ ነው ልትጠብቂው ከቻልሽ ሪፐብሊክ ያላት ። ባልጠብቀውስ !? ብትለው መቼም መልሱ የእንግሊዝ ግዛተ ዘውድ ፈላጭ ቆራጭ ወይም አምባገነን ቅኝ ገዥ ነበር የሚላት ብዬ አምናለሁ ። ወገኖቼ የአሸባሪው ህወሓት አፈር ልሶ እንደ ዙምቢ መምጣት ዝም ብሎ የስርዓት ለውጥ ከመሰላችሁ በህይወት ዘመናችሁ ትልቅ ስህተት ፈጽማችኋል። በመላው ዓለም ከሚገኙ አመራሮቹና ደጋፊዎቹ ጋር ባደረገው የዙም ውይይትም ሆነ ፤ ጂኦፖለቲክስ ፕሬስ ይፋ ባደረገው “ከባዝማ እስከ ኢትዮጵያ”ሰነድም ሆነ በአሸባሪው ቃል አቀባይ በእብሪት”ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን፤” ከማለቱ በአሜሪካ የሚገኙ ጭፍራዎቹ”በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ታላቋ ትግራይ እውን”እንደምትሆን ሲፎክሩ በአማራና በአፋር ክልሎች ሰርጎ የገባው አሸባሪ አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩን ባንዲራ አውርደው የራሳቸውን አርማ ሲሰቅሉ ፤ ሟቹ መለስ ባንዲራውን ጨርቅ ነው ይል ስለነበር ብጤዎቹ የዱቄት መቋጠሪያ አድርገውት እንደነበር ስታስታውስ ህወሓት መንግሥት በመለወጥ ብቻ የሚቆም አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል ። አዎ አሸባሪው ህወሓት የሚመጣው ሀገር የማፍረስ ጅምሩን ለማጠናቀቅ ነው ። ኢትዮጵያን ወደ ስድስት ሀገራት በመበታተን ታላቋን ትግራይ መመስረት ። ይህ እኩይ አላማ በኤርትራም የመንግሥት ለውጥ በማድረግ በትግራዋይ የሚመራ አሻንጉሊት መንግሥት የማቆም እና ኤርትራን የታላቋ ትግራይ አካል የማድረግ አላማንም ያካትታል ።
እኔም ከውስጥና ከውጭ የተናበበና የተቀናጀ ከበባና ጫና የበዛበትን ብዙ ዋጋ ከፍለን ያመጣነውን ለውጥ እንደ አይናችን ብሌን “ልንጠብቀው ይገባል እላለሁ፡፡ ያለበለዚያ አሸባሪው ህወሓት የጀመረውን ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ እንዲፈጽም፤ ዳግም እንደ ብረት ቀጥቅጦ እንዲገዛን፤ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለምዕራባውያን አሳልፎ የሚገብር ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት የሚል ተላላኪና ጉዳይ አስፈጻሚ፤ እንዳለፉት 27 ዓመታት በገዛ ሀገራችን ሁለተኛ ዜጋ የምንሆንበት ነጻነት እኩልነት ፍትሐዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የሌለበት፤ ዘራፊ አምባገነን ፈላጭ ቆራጭና አፋኝ ኢትዮጵያን አምርሮ የሚጠላ ፤ የገዛ ዜጋውን የሚያሰቃይ በግፍ የሚገል የሚገርፍ የሚያግዝ የሚያስር ሕዝብን የሚከፋፍልና ሀገርን የሚያፈርስ አፈር ልሶ የሚነሳው አሸባሪው ህወሓት እጅ ሀገር ሕዝብ ዳግም ፍዳቸውን ሊያዩ ይወድቃሉ ማለት ነው ። በግሌ ወደዛ የግፍ የመከራና የጨለማ ዘመን ከምመለስ አንድ ጊዜ አይደለም አስር ጊዜ ደጋግሜ መሞትን እመርጣለሁ ። የመንግሥቴን ጥሪ ያለምንም ማቅማማት የተቀበልሁት ለዚህ ነው ። አሜሪካዊው ፓትሪክ ሔነሪ “ነጻነትን ስጡኝ ወይም ሞትን አትንፈጉኝ!”/Give liberty or give me death/ እንዳለው ። ሔነሪ ነጻነቴን ያለው ሀገሩ ላይ ቆሞ ስለሆነ እኔ ግን ቆሜ ነጻነቴን የምጠይቅባት ምትክ የሌላት ሀገሬ ላይ የህልውና አደጋ ስለተደቀነባት ፤ ሀገሬ ወይ ሞት ! ለማለት ተገድጃለሁ።
ከአሸባሪው ህወሓት ጭፍራዎች በስተቀር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምርጫ ይኸው ነው ። ኢትዮጵያውያን የህወሓት ቂመኛ ከሀዲና ዘራፊ ቡድን ዳግም የጭቆና ቀንበር እንዲጭንባቸው አይፈቅዱም ። አንቅረው ወደተፉት ግፈኛ አገዛዝ አይመለሱም። ወደትፋቱ የሚመለስ እሪያ ነውና ። ይህ እንዳይሆን ግን መላ ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ ይህን ለውጥ መጠበቅና መከላከል ይጠበቅባቸዋል። ጠላቶቻቸውን ሳይቀር ያስገረመ ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ፤ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ደጀን በመሆን፤ የሕዳሴውን ግድብ እስከ 16 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ በመደገፍ አለኝታነታቸውን አረጋግጠዋል። ለሰብዓዊነት ሲል መንግሥት ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም አሸባሪው ህወሓት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ትንኮሳ ከማድረግ አልፎ ወረራ ፈጽሟል ። በአራት ግንባር በሕዝባዊ ማእበል የታገዘ ጦርነት ከፍቷል። “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ።” በሚል መሀላ ተማምሎ ሀገርን ለማፍረስ ከየጎሬው ሲወጣ፤ ኢትዮጵያውያን እንደ ጀግኖች አባቶቻቸው በአንድነት ቀፎው እንደተነካ ንብ ወደ ሰሜን ተመዋል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን ወደ ኃላፊነት ያመ ጣው ለውጥ ከቀደመው አብዮትም ለውጥም ፍጹም ይለያል። ደርግ ንጉሳዊውን አገዛዝ በመፈንቅለ መንግሥት ገርስሶ በምትኩ የባሰ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ተከለ። ትህነግ/ኢህአዴግ ሶሻሊስታዊ አምባገነን ገዥ የነበረውን ደርግ ለ17 ዓመት ነፍጥን ከሴራና ደባ አጃምሎ ለስልጣን ቢበቃም ታገል ሁለት ያለው እኩልነትና ነጻነት ክዶ የአንድን አውራጃ የበላይነት ብቻ ሳይሆን ለ30 ዓመታት አንድም ቀን የመንግሥትነት ባህሪ ሳያሳይ በአሳፋሪ ሁኔታ ራሱን በራሱ አጥፍቷል ። ለነገሩ መንግሥት የመሆን ቅን ፍላጎትም አልነበረውም ። ሕገ መንግሥት ያለው ብቸኛ ማፊያ ቡድን እንጂ ። በመጨረሻዎቹ የክህደትና የአረመኔነት ቀናት ያረጋገጠልን ይህን ማፊያነቱን ነበር። ሆኖም በፖለቲካው መልክዓ የነዛው የጥላቻ፣ የልዩነትና የመጠራጠር መርዝ በቀላሉ አይረክስም። እንኳን ለ47 ዓመታት የተለፈፈ የጥላቻና የፈጠራ ትርክት፤ በጣሊያን የአምስት ዓመታት ቆይታ ለዛውም በጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ ለአንድ ቀን እንኳ ያለስጋት ውሎ ባላደረበት ለከፋፍሎ መግዛት እንዲያመቸው የዘራው የማንነትና ጨቋኝ ተጨቋኝ የፈጠራ ትርክት በቀላሉ ሰኮናው ሳይነቀል ኖሮ በ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከሶሻሊዝም ጋር ተላቁጦ የሀገራችንን ፖለቲካ እስከመበየን ደርሷልና ከዚህ አባዜ ሰብሮ ለመውጣት ብርቱ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል ። ለደቂቃም ቢሆን አይንን ከትልቁ ስዕል ሳያነሱ።
የአፄ ሀይለስላሴ ፣ የደርግና የትህነግ አገዛዞች ያባከኗቸውን ወሳኝ መታጠፊያዎች ሀገራችንን ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳስከፈሏት በውል ተገንዝቦ ከሶስት ዓመት ወዲህ በእጁ የገባውን ወሳኝ መታጠፊያ በብልህነትና በአስተዋይነት መጠቀምን የሞት ሽረት ጉዳይ ማድረግን ይጠይቃል ። እዚህ ላይ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሚመራው የለውጥ ኃይል ከእነውስንነቶቹ ያለንፍገት እውቅና ሊቸረው ይገባል ። ይሁንና ይቺ ሀገር እንደ ቀደሙት ሶስት የቅርብ ዓመታት መታጠፊያዎች የምታባክነው እድልም ሆነ አጋጣሚ እንደማይኖርና እንደ ከዚህ በፊቱ ብታባክነው አምባገነናዊ አገዛዝ በመተካት ብቻ የሚቆም ሳይሆን በሀገር ቀጣይ ህልውና ላይ አደጋ የሚደቅን መሆኑን በውል ተገንዝበው የአምባገነንነት ቀለበቱን ሰብሮ ለመውጣት የሚያግዝ ስልት ተልመዋል። አሳታፊ ፖለቲካዊ ስርዓትና አካታች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለማስፈን ቆርጠዋል ። እንገጭ እገው እንዳለ ሆኖ። ቁርጠኝነታቸውንም የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባትና ኢኮኖሚውም ፍትሐዊ እንዲሆን ማሻሻያ ቀርጸው ወደ ትግበራ ገብተዋል ። ሆኖም ለውጡ ከቀደሙ አብዮቶቹም ሆነ ለውጦች በፍጹም ሊባል በሚችል ሁኔታ የተለየ በመሆኑ ፤ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተዘራው ልዩነትና ጥላቻ ፤ ትህነግ ጥርሱን በነቀለበት ሴራና ደባ መቐሌ ላይ መሽጎ እንዲቀጥል ጊዜ ማግኘቱ ፤ ለውጡ ቢያንስ ሆን ተብሎ የባረቁ ሶስት ለውጦችና አብዮት ዘርፈ ብዙ ቀውስን እንደ ትኩስ ድንች ተቀባብለው የጣሉበት ባለዕዳ በመሆኑ የቀውሶች ቋጥኝ በአንድ ላይ ስለ ወደቁበት እና በለውጡ ተዋንያን ወጥ ቁርጠኝነት ባለመያዙ ምልዑ – በኩሌ ሳይሆን ቀርቷል ። ምንም እንኳ የእውነተኛ ለውጥ መንገድ አሚካላና ኩርንችት የበዛበት ቢሆንም የተገኘው አበረታች ውጤት በዚህ ሁሉ እሾህ ታንቆ ያለፈ እንዳይመስል አድርጎታል።
እንደ መውጫ
የዐቢይ መንግስት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግን ባታ አዕማድ የሆኑ ተቋማትን ቅድሚያ በመስጠት ማሻሻ ያዎችን አድርጓል ። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ፣ የፍትህና የዳኝነት ስርዓቱ ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ኮሚሽን ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ የብሔራዊ ደህንነትና የመረጃ ተቋም ፣ ፌዴራል ፖሊስ ፣ መገናኛ ብዙኃን ፣ ወዘተረፈ ላይ የተፈጠሩ የአደረጃጀትና የአመራር ለውጦችን በአብነት ማንሳት ይቻላል ። የለውጥ ኃይሉ በምርጫ ዋዜማ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፤ ክብርት መዓዛ አሸናፊን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፤ አቶ ዳንኤል በቀለን (ፒኤችዲ) በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነርነት መሾሙ የለውጥ ኃይሉ የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ በዴሞክራሲ ፣ በፍትሕ፣ በእኩል ነትና በነጻነት ለመዋጀት የቆረጠ መሆኑን ያረጋግጣል። የዴሞክራሲያዊ ተቋማት አዕማድ የሆኑ እነዚህን ተቋማት በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙ ሰዎች ገለል ተኝነትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት መከበር ያላቸው ቁርጠኝነት የለውጥ ኃይሉ ሀገሪቱን ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመገላገልና አርነት ለማውጣት መወሰኑን በተግባር አረጋግጧል ።
የለውጥ ኃይሉ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በአደረ ጃጀትና ገለልተኛ አመራሮችን ከመመደብ ባሻገር የትህነግ አገዛዝ ለአፈና መዋቅሩ እንደ መሳሪያ ይጠቀምባቸው የነበሩ ሕጎች በገለልተኛ ምክር ቤት እንዲሻሻሉ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል ። የሲቪል ማህበራት ፣ የመገናኛ ብዙኃን ፣ የጸረ ሽብር ፣ የአስተዳደር ፣ የምርጫና የፖለቲካ ድርጅቶች አዋጆች የተሻሻሉ ሲሆን ቀሪዎችን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው ። እነዚህ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ያሉት ለዚህ ተግባር በገለልተኝነት በተቋቋመ ምክር ቤት መሆኑ፤ የምክር ቤቱ አባላትም በገለልተኝነታቸው የታወቁ ምሁራን ፣ ጠበቃዎችና የሙያ ማህበራት መሆናቸው፤ በሕግ ማሻሻያ ሂደቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሙያ ማህበራትና የሕዝብ ወኪሎች በሒደቱ በንቃት መሳተፋቸው ሌላው የለውጥ ኃይሉ አካታች የፖለቲካ እና አሳታፊ የኢኮኖሚ ስርዓት ለመትከል ምን ያህል እንደ ተነሳሳ እማኞች ናቸው ። የለውጥ ኃይሉ ሀገራችን ድሀ ፣ ኋላቀርና አምባገነናዊ አገዛዝ ሲፈራረቅባት የነበረው ተረግማ ወይም ሕዝቧ ጥቁር ስለሆነ ሳይሆን አሳታፊና አካታች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ባለመከተሏ መሆኑን በመገንዘብ በእጁ የገባውን ወሳኝ መታጠፊያ እንደ ቀደሙት ላለማባከን ቃል ኪዳን ገብቶ እየሰራ ይገኛል ። ሀገራችንን ለዘመናት ቀስፎ የያዛትን ችግር ለይቶ ለማያዳግም መፍትሔ እየሰራ ነው ። በዚህም ስሙ በፋና ወጊነት ሲወሳ ይኖራል ። ምርጫው ነጻ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ማለቱም አበክሮ የፈጠረውን መደላድል ታሳቢ በማድረግ ነው ። ምርጫው ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት ነው ያለውም ወሳኝ መታጠፊያውን በአግባቡ ትጠቀማለች ብሎ ስለሚያምን ነው ። በተግባርም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከእነ ውስንነቶቹ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ።ይሁንና አሸባሪውና ከሀዲው ህወሓት በሀገራችን ህልውና የደቀነውን አደጋ በአንድነት የመመከት ጉዳይ ከሁሉም በላይ የወሳኞች ሁሉ ወሳኝ መታጠፊያ መሆኑን ተገንዝበን ሀገርንና ተስፋ የተሰነቀበትን ለውጥ ለማዳን ጥሪው ፈጣን ምላሽ እንሰጥ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጇቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2013