– በሦስት ተቋማት ብቻ ከ672 ሚሊዮን ብር በላይ ጉድለት ተገኝቶባቸዋል
-ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ከደንብና መመሪያ ውጭ ግዢ ተፈጽሟል
አዲስ አበባ፡- ጥሬ ገንዘብ በማጉደል፣ የተሰበሰበ ገንዘብ በወቅቱ ፈሰስ ባለማድረግ፣ ባለማወራረድ፣ በአግባቡ ወጪ ባለማድረግና በብክነት ለከፍተኛ ኪሳራ የዳረጉ 25 ተቋማት በህግ ሊጠየቁ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር አስታወቁ። የከተማ አስተዳደሩ ዋና ኦዲተር ወይዘሮ ፅጌወይን ካሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ መስሪያ ቤታቸው በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በ27 ተቋማት ላይ የፋይናንስ ህጋዊነት ኦዲት ለማድረግ አቅዶ በ25 ተቋማት ላይ ባከናወነው የኦዲት ስራ ተቋማቱ አስተዳደሩን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጉ መሆናቸው አረጋግጧል። በመሆኑም ተቋማቱ እስከ የካቲት 2011ዓ.ም መጨረሻ ሂሳባቸውን ማስተካከል ካልቻሉ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተሰጥቷቸዋል።
እንደ ዋና ኦዲተሯ ማብራሪያ፤ ኦዲት ከተደረጉ ተቋማት መካከል ከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ 672 ሚሊዮን 689ሺ ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት የታየባቸው ሲሆን፣ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ኦዲት ከተደረገ በኋላ ጉድለቱን ተመላሽ በማድረግ ማስተካከል ችሏል። ሁለቱ ተቋማት ግን እስካሁን የጎደለውን ሂሳብ አላስተካከሉም። በተለይም የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 534ሺ ብር ከተማሪዎች የሰበሰበውን የወጪ መጋራት ሂሳብ ለፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ፈስስ ባለማድረግ ክፍተት ታይቶበታል።
በተመሳሳይ የጉለሌ እጽዋት ማዕከል ከመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው በተቋሙ ከተቀጠሩት ሰራተኞች ከወርሃዊ ደመወዛቸው ላይ የወጪ መጋራት 10 በመቶ ተቀናሽ ሳያደርግ 17ሺ347 ብር ከፍሎ ተገኝቷል። በተጨማሪም ዘጠኝ ተቋማት 32ሚሊዮን 562 ሺ328 ብር በወቅቱ ሳይሰበስቡ መቅረታቸውን በምርመራው መረጋገጡን ወይዘሮ ፅጌወይን ጠቁመው፤ ከእነዚህም መካከል የትራንስፖርት ፕሮግራም ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት፣ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልና ትምህርት ቢሮ በዋነኝነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አመልክተዋል። ውበትና መናፈሻ ዘላቂ ማረፊያ ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ጉለሌ እፅዋት ማዕከል፣ እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልና ትምህርት ቢሮ 26 ሚሊዮን 558ሺ 141ብር በውሉ መሰረት ቅድሚያ ክፍያ ከተፈፀመ በኋላ ተመላሽ ሳያደርጉ መቅረታቸውን አስገንዝበዋል። «በጉለሌ እፅዋት ማዕከል ግንባታውን ከሚያከናውን ህንፃ ተቋራጭ ቅድመ ክፍያ 2ሚሊዮን 232ሺ 906 ብር መሰብሰብ ሲገባው መሰብሰብ የቻለው 1ሚሊዮን 944ሺ 266 ብር ብቻ መሆኑን አረጋግጠናል» ብለዋል። ይህም የቅድሚያ ክፍያ ተመላሽ ሲደረግ ሂሳቡ በትክክል ባለመሰላቱ መሆኑን አስረድተዋል።
በተመሳሳይ ትምህርት ቢሮ 3 ሚሊዮን 104 ሺ 125 ብር ከማን እንደሚሰበሰብ የማይታወቅ ሂሳብ መገኘቱን አመልከተዋል። ይህም የሆነው ሂሳብ በዝርዝር መመዝገብ ባለመቻሉና ማስረጃዎች በተገቢው ሁኔታ ተደራጅተው በወቅቱ እንዲሰበሰብ ባለመደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ዋና ኦዲተሯ ማብራሪያ፤ ኦዲት በተደረጉ ተቋማት የግዢ አዋጅ ደንብና መመሪያ ተጠብቆ መከናወኑንና ክፍያውንም ህጋዊነቱን ተከትሎ መፈፀሙን ለማረጋገጥ ሲጣራ 18 ተቋማት 26 ሚሊዮን 586ሺ 626 ብር ከደንብና መመሪያ ውጭ ግዢ ፈፅመው ተገኝተዋል። ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል 6 ሚሊዮን ብር፣ የአስተዳደሩ አደረጃጀትና መዋቅር ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት 3 ሚሊዮን 943 ሺ ብር እንዲሁም ውበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ 3ሚሊዮን 883ሺ477 ብር ያለአግባብ ግዢ በመፈፀም ተጠቃሽ ናቸው።
ከደንብና መመሪያ ውጪ አበልና ደመወዝ በመክፈል ረገድም 11 ተቋማት ከመመሪያ ውጭ 3ሚሊዮን 397ሺ 668 ብር አበል መክፈላቸውን እንዲሁም ስድስት ተቋማት 2ሚሊዮን 300ሺ833 ብር ደመወዝ ያለአግባብ ከፍለው መገኘታቸውን በምርመራ መረጋገጡን አስረድተዋል። በተመሳሳይ ከንቲባ ጽህፈት ቤትና እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በድምሩ 57ሺ 316ብር ከመመሪያ ውጪ የትርፍ ሰዓት ክፍያ መፈፀማቸውን አመልክተዋል። ዋና ኦዲተሯ «ባደረግነው ማጣራት የአስተዳደሩ አደረጃጀትና መዋቅር ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት በሌላ የመንግስት ተቋም የሚሰራና ደመወዝ በየወሩ የሚቀበል ሰራተኛን በ2008 እና በ2009በጀት ዓመት ያለአግባብ 279ሺ106 ብር ከፍሎ ተገኝቷል» ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ተቋሙ አንድ ሰራተኛ ሲቀጠር ከዚህ ቀደም ይሰራ ከነበረበት ተቋም መልቀቂያ ማምጣቱን የሚያረጋግጥበት አሰራር ባለመፍጠሩ መሆኑን ተናግረዋል። በእነዚህና በሌሎች ተቋማቱ ላይ ያሉ ብልሹ አሰራሮች የከተማ አስተዳደሩን ብሎም የአገርን ኢኮኖሚ ለኪሳራ እየዳረገ በመሆኑ መስሪያ ቤታቸው ከከተማዋ ምክትል ከንቲባ ከኢንጅነር ታከለ ኡማ ጋር በመነጋገር ተቋማቱ እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ ያጎደሉትን ሂሳብ እንዲያስተካክሉ አለበለዚያ በህግ ተጠያቂ መሆን እንደሚገባቸው ውሳኔ ላይ መደረሱን ገልጸዋል። በዚህም መሰረት ለሁሉም ተቋማት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ማህሌት አብዱል