መቼም የአንዳንዱ ሰው ግምትና አስተያየት በእጅጉ ያስገርማል፡፡በውስጡ ያለውን ሀሳብ ለሌላው ሲያጋባ ያለአንዳች መነሻና መሰረት ነው።በእርግጥ አስተያየት መስጠትና፣ እንዳሻ መገመት የማንም መብት ሊሆን ይችላል።እንደፈለጉ መናገርና ያለልክ መስመር መሳትንም በዘመናችን እያየነው ያለ እውነት ነው፡፡
ዛሬ ላይ ይህ ዓይነቱን ልማድ ማንም ተነስቶ ቢፈጽመው ‹‹አጀብ›› የሚያሰኝ ፣አፍ አስይዞም ራስ የሚያስነቀንቅ አይሆንም።አዎ! ጊዜው ለዚህ ዕድል ሜዳና ፈረስ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያዎች መፈንጫ ነውና ጆሯችን ብዙ ሲሰማ ዓይናችን ዕልፍ ሲታዘብ ኖሯል።
አንዳንዴ ለእኔ ከትዝብት በላይ የሚሆኑቡኝ ወሬዎች አይጠፉም። እንዲህ አይነቱ ቅጥ ያጣ ንፋስ በጆሮዬ ሽው ባለ ጊዜም ጉዳዩ ከማስገረም አልፎ ብሽቅ ትክን ያደርገኛል።ለነገሩ ዘንድሮ ምን የማያተክን፤ ምንስ የማያናደድ ነገር ይኖራል።ሁሉንም እንየው እንታዘበው ያልን እንደሁ ውስጡ በብሸቀት የተሞላ፣ ስሩ በንዴት የተያዘ ምርጊት ይሆናል ። ይህ ብቻም አይደለም።ጫፍ የሌለውና ፣ውሀ የማያነሳ ግምት መያዝም ትርፉ ዞሮ ያው የወሬ ድምር ነው።
ወዳጆቼ! የአንዳንድ ሰዎች ሁኔታ ደግሞ በእጅጉ ያስገርማል፡፡ አንድን ጉዳይ መነሻ አድርገው ሲያወሩ፣ አልያም ሲገምቱ እንበለው መነሻና መድረሻ ያላቸው አይመስልም፡፡ እንዲህ አይነቶቹ ውል አልባዎች ፣ ጫፍ ሳይዙ መተርተር ፣ ልምዳቸው ነው። ይህን ለማለት ያስገደደኝን አንድ እውነት ልምዘዝ ፡፡
አሁን ከሰሞኑ ይህ ሽብርተኛ ቡድን እንደዝንብ በወረራቸው አንዳንድ ከተሞች የለመደውን ድርጊት ሲፈጽም ከርሟል።ነውርነት ልብሱ፣ክፋት ጭካኔ ጉርሱ የሆነው ይህ ቡድን አሁንም በርካቶችን እየገደለ፣ ብዙሀንን እያፈናቀለ፣ ነው ።መቼም ተስፋ የቆረጠ አይገባበት ጉድጓድ፣ አይወጣበት ዛፍ የለ ሆኖ፤ ስልጣን የማለሚያውን፣ከአፈር የመነሻውን ጥግ አሁንም ድረስ እየታዘብነው ነው ፡፡
አስገራሚው ጉዳይ እንዲህ መሆኑ ብቻ አይደለም ። የህልመኛው ቡድን ደጋፊ ነን ባዮች ያሳዩን አሳፋሪ ድርጊት እንጂ።እንዲህ አድራጊዎቹ የሽብርተኛውን ማንነት ከማወቅ አልፈው በቢሆን ዓለም የሚቃዡ ፣ጉም እንጨብጥ ባይ ወገኖች ናቸው።‹‹ወጊቲ ›› አለ ሰውዬው፣ ‹‹ወጊቲ… ››
እነወጊቲ ቡድኑ ‹‹ዛሬ እዚህ ደረስኩ፣ ይህን ከተማ ተቆጣጠርኩ፤ ነገ አዲስ አበባ ነኝ›› ባለ ቁጥር አጉል ምኞቱን ተቀብለው ቅዠቱን እናቀብል ባዮች ናቸው። ‹‹አ.ከ.ከ.ከ.ከ.ከ›› አለች ዶሮ። ‹‹ድንቄም›› አዲስ አበባ። እነ ወሬ ግብሩ ይህን ሲሉና ሲለፍፉ አስተማማኝ መረጃና እውነትን ይዘው አይመስላችሁ። ምኞታቸውን ሲቀምሩ በተለምዷዊው የውሸት ምሪት ተጉዘው ፣አይሰለቼውን የወሬ መስመር ተከትለው ነው፡፡
በጣም ገራሚው ጉዳይ ይህ የተበጣጠሰ ቡድን ህልሙ ዕውን ቢሆን ሲሉ በቁሙ የሚቃዡ አንዳንዶች የሚያሳዩን ምልክት ነው።ለነገሩ ! ድርጊታቸው ሁሉ ከምልክት አልያም ከነጥብ አቅም አያልፍም ።አንዳች ኮሽታን በሰሙ ቁጥር ዳናውን እንከተል፣ ጭብጨባውን እናዳምቅ ባዮች በየስርቻው ተዘርተው ይገኛሉ።
እነ እመት ህልመኛ እነ አብዬ ሩጫ እስቲ ካሳፋሪው ድርጊታችሁ አንዱን እናንሳ ። በዛሰሞን መንግሥት በይሁንታው ‹‹መቀሌን ለቅቂያለሁ›› ባለ ማግስት ከበሯችሁን አዝላችሁ ጨፈራችሁ፣ ዘፈናችሁ አሉ።አይ የእናንተ ነገር ለማይበጅ ህልም እኮ ዜማና ግጥም፣ እልልታና ጭፈራ አያሻም ነበር ። ክንፍን ለማርገፍ እንደፌንጣ መዝለልና ፣ እንደ አንበሳ ማግሳትም ራስን ማሞኘትና ሌላውን ማታለል ነው ።
እንደው ልፉ፣ ተዋረዱ ብሏችሁ እንጂ እውነታው ሁሉ ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› መሆኑን አሳምራችሁ ታውቁታላችሁ ።አዎ! ለእናንተ አይነቱ ኮሽታ ናፋቂ ደግሞ በየጊዜው ‹‹እያነቡ እስክስታ›› ን ማስታወሱ ግድ አይሆንም።የእናንተ አዕምሮ ዘሎ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት ጥቂት ቢያስብ መልካም ይሆን ነበር።
መንግሥት መቀሌን ከተማ በፈቃዱ ለቆ ተኩስ አቁምን ቢተገብር በመሸነፉ፣ እንዳልሆነ ዓለም ሁሉ ያውቃል ።ይህን ተከትሎ ሽብርተኛው ቡድን በአማራና አፋር ክልል ወረራ መፈጸሙን እናንተም አትክዱም።ዛሬ ህጻናትን አሰልፎ የፈሪ ዱላ የሰነዘረው የእናንተው ወዳጅ የነገ መጨረሻው የት እንደሚሆን ፈጽሞ አያጣውም ።
ይህ ቡድን ከተቀበረበት ጉድጓድ ለጊዜው አፈር ልሶ ቢነሳም ህልሙ መቼውም ዕውን እንደማይሆን የተባበሩት የኢትዮጵያውያን ክንዶች በዓይኑ እያሳዩት ነው ። ‹‹ዶሮ ርቃ ላትሄድ ማልዳ ትነሳለች›› ሆኖበት መንደፋደፍ ቢጀምርም በሩቅ የተለመው ምኞቱ ከዛሬው እንደመከነ በተግባር ተረድቷል።
እናንተ ደግሞ ዘራፊው ቡድን አንድ ከተማ አድሮ በተባረረ ቁጥር አዲስ አበባ ይገባል፣ ከቤተመንግሥቱም ይመለሳል ይሉት ቅዠት አላስተኛችሁ ብሏል ።ወዳጆቼ! ይህ አይነቱ ስሜት ደግሞ እጅግ የከፋ ነው።ፈጽሞ ሰላም አይሰጥም።የቁም ቅዠት እኮ አያደርገው፣አያደርሰው የለም። በመንቃትና መተኛት መሀል የሰውን አዕምሮ እንደ ጥጥ አቅልሎ እንደ ኳስ እያጎነ መቀለጃ ያደርጋል፡፡
ይህ አይነቱ ጭንቀት አንድን ሰው በወጉ እንዳይቆምና እንዳይተኛ በሁለት ጫፍ የሚወጥር ወፍራም ገመድ ነው።የእናንተው ጉም እንጨብጥ ህልምም ልክ እንደ ቅዠቱ ይመሰላል።ከማይታሰብ የገነት ዓለም ዘፍቆ፣ ከማይወጡበት ጥልቅ ባህር እንደሚዘፍቅ ከንቱ ህልም ፡፡
ንገሩን፣ አስታውሱን ካላችሁ ደግሞ እሺ እናስታውሳችሁ ።እናንት ሀፍረተ ቢሶች መንግሥት መቀሌን ቢለቅ እኮ ለአራሹ ገበሬ በማሰብ ፣ለሰፊው የትግራይ ህዝብ በመጨነቅ ነበር ።
እናንተና ጀሌዎቻችሁ ግን ሆቴል አዘግታችሁ ድቤ መታችሁ፣ ባንዲራ ረግጣችሁ ኢትዮጵያዊነትን ካዳችሁ፣ ደስ የሚለው እውነት ግን ሳቅ ፈገግታችሁ ውሎ አላመሸም።የእናንተው ድል አድራጊ ህጻናትና ሴቶችን አሰልፎ ፣እናቶችን ማስለቀስ ፣ ጎጆን ማዘጋት ቤተሰብ መበተን መያዙን ዓለም ሁሉ አወቀው ።
ዛሬ እንዳሻችሁ የምትዘባነኑባት፣ እንጀራ ቆርሳችሁ የምትጎርሱባት ፣ልጆች ወልዳችሁ የምታሳድጉባት ምድር ታላቂቱ አገር ኢትዮጵያ ስለመሆኗም አትዘንጉ፡ ፡ይህች ድንቅ አገር እናንተን መሰል እሾህና አሜክላ አብቅላ ቀኝ ግራዋን ብትወጋ ደሟን የሚመልሱ፣ ቁጭቷን የሚወጡ ጀግኖችን በየቀኑ ትወልዳለች፡፡ ንጹሁን የትራይ ህዝብም ቢሆን መቼም ከእናት ሀገሩ ልትለዩት አትችሉም፡፡
ወዳጆቼ እውነት እላችኋለሁ አሁንም በምትሰሩት ድርጊት ህሊና ያለው ሁሉ ያፍርባችኋል ፡፡እናንተ እንደምትሉት ኢትዮጵያዊነቱን ባትፈልጉትም ዜግነቱን ከወርቅና ዕንቁ ዋጋ የሚያስበልጠው መላው ኢትዮጵያዊ ዛሬ ለህልውናው ዘመቻ እንደማይደራደር በገሀድ አሳይቶ ምላሽ ሰጥቷችኋል።
ደግሞም ምኞትና ፍላጎት በወጉ ሲሆን መልካም ነው ።ከማያገኙት ድልና ስልጣን መንጠልጠሉም ትርፉ ያው ከመሰበር አያልፍም።እንደው እኮ! እናንተዬ ዝም ብዬ ሳስባችሁ ‹‹ድሀ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ …›› አይነት ትሆኑብኛላችሁ ፡፡
በአባባል የምናውቀው ይህ ድሀ ‹‹ሁሌ በህልሜ ቅቤ ባልጠጣ ኖሮ ንጣት ይገለኝ ነበር›› እያለ ራሱን ያሞኛል አሉ።ምስኪን… የእናንተ ቢጤ። እናንተም ብትሆኑ ዘራፊው ቡድን ድል ነስቶ አዲስ አበባ ቢገባ በሚል እያሰባችሁ አንጀታችሁ ቅቤ ይጠጣ ይዟል።‹‹ወግ ነው አሉ ሲዳሩ ማልቀስ››
እንዲያው ለመሆኑ ይህ ዘራፊ አዲስ አበባ እስኪዘልቅ፣ ስልጣነ መንበሩን እስኪጨብጥ ማን የማንን ጎፈሬ ያበጥር ይመስላችኋል።እንግዲያውሰ ቁርጣችሁን እወቁ እዚህ ላይ ቀልድ ይሉት ጨዋታ፣ ምኞት ይባል ዕቅድ አይሰራም።
ትናንት በህወሓት ጨንገር የተገረፉ፣ በአስከፊው መንገዱ የተጓዙ፣ የውዶቻቸውን ህይወት በግፍ የገበሩ ዕልፎች ለዓመታት አስሮ ክፉ መንፈስ የሆነባቸውን ሀይል በመቅበር ላይ ናቸው።
በእርግጥ እናንተና መሰሎቻችሁ ዛሬ ላይ ቆማችሁ ነገን ብታልሙ አይፈረድም፡፡ትናንት ከጌቶቻችሁ ፍርፋሪ ተቋዳሾች ነበራችሁ ።የዛኔ ከጥቅሙ ስትጋሩ፣ ከደስታው ስትካፈሉ ሌሎች ወገኖችን አላሰባችሁም።ይህን ላደረገላችሁ ባለውለታ ደግሞ አሁን እያለቀሳችሁ ብትዘፍኑለት አያስገርምም።አዲስ አበባን በቁም እያለማችሁ ቦታ ብታመቻቹም ብርቅ የሚባል አይሆንም፡፡
እውነት ነው ‹‹ ውሻ በበላበት ይጮኃል›› ሆኖባችሁ ዛሬ ላይ ተናፋቂ እንግዳችሁን ለመቀበል ማንጋጠጥ ይዛችኋል።አልገባችሁም እንጂ ቢገባችሁማ የጅቡ የመጀመሪያ ንክሻ የሚጀመርው ከእንደናንተ አይነቶቹ ተልከስካሽ ውሾች ይሆናል።
አዎ! በህወሓት ታሪክ ውለታና ዝምድና ይሉት እውነት ታይቶ አያውቅም ።ማንም በጥቅሙ የመጣበት አካል ቢኖር መንገዱን የሚያጸዳው ደም በማፍሰስ ህይወትን በማጥፋት ይሆናል፡፡
እናንተ ህልመኞቹ እንደምታስቡት ሆኖ አሸባሪው ሀይል አዲስ አበባ ቢገባ ቂምና እልሁን የሚወጣው እንደማይካድራ ሰዎች ማንነትን በመታወቂያ እየለየ፣ዘር ከብሄር፣ቋንቋ ከሃይማኖት እየመደበ ነው።በእሱ የተቀባበለ መርዛማ ጥይት ሳይገደል የሚውል፣ሳይሞት የሚነሳ የሰው ዘር አይኖርም፡፡
እናንት ህልመኞች የምትቃዡለት አሸባሪው ቡድን አዲስ አበባ ቢገባ በውርደት የለቀቀውን ታላቁን ቤተመንግሥት በአድናቆት እየጎበኘ አይቆይም፡፡ አልያም የመስቀል አደባባይን ለውጥ ባሻገር እያየ እጁን ከአፉ አይጭንም፡፡ወይም ደግሞ የየክልሎችን የባህል ማዕከላት ምሪት እያስተዋለ በግርምት አያልፍም።ከእንጦጦ ፓርክ አፋፍ ቆሞም የከተማውን ድንቅ ውበት አይቃኝም፡፡
አሸባሪው ህወሓት አዲስ አበባ ቢመጣ ውበት አይወድለትምና ባለፉት ሶስት ዓመታት የተሰሩ የአዲስ አበባን ውብ ገጽታዎች ያጠፋል፤በምትኩ የቆሻሻ ክምር ያኖራል፡፡የአንድነት እና የወዳጅነት ፓርክ የሚባሉትን ፓርኮች አፍርሶ የመለያየት ፓርኮችን ይተክላል፡፡
ከመጀመሪያዎቹ የጥፋት እርምጃዎቹ ተንደርድሮ ውጥን ሴራዎቹን ይቋጫል፣ ጅምር ወንጀሎቹን ይዳውራል።በብሄር ብሄረሰቦች ሰበብ የሸመነውን ክር ተርትሮም ዳግም ራሱን ለመስራት በርካቶችን የእግሩ ስር ካብ ያደርጋል፡፡በብሄር ብሄረሰቦች ስም በተሸፈነ ካባ ዳግም እርስ በእርስ ማቃቃርና ማጋጨትን ይጀምራል፡፡አንዱ ብሄር ለሌላው ጠላት እንደሆነ ስልታዊ በሆነ መልኩ ይሰብካል፡፡የደም ጥሙንም ማርካት ይጀምራል፡፡መጠገን የጀመረችውንም ሀገር ዳግም ይሰነጣጥቃታል፡፡
አይሳካም እንጂ የእናንተ ህልም ቢሳካ ህወሓት ከተቀበረበት ጉድጓድ ሊወጣ አፈሩን የሚያነሳው እንደለመደው በሌሎች ድካምና ጉልበት ብቻ ተንተርሶ ነው።ወንበሩን አስፋፍቶ ለመያዝም የእሱን መሰል ጥቂቶችን ሰብስቦ ብሄርተኝነትን ለማስፋት፣መለያየትን ለማስረጽ ዕንቅልፍና እረፍት አይኖረውም፡፡የተወሰኑ ቡድኖችን ሰብስቦም የሀገሪቱን ሃብት መቀራመቱን ይቀጥላል፡፡በመልሶ ማልማት ስም ጥቂቶች የሚበለጽጉበት መንገድ በረቀቀ መልኩ ይተገበራል፡፡ አርሶ አደሩ ከቀረችውም መሬቱ ተፈናቅሎ ጎዳና ተዳዳሪ ይሆናል፡፡
ህልመኞች ሆይ ! እኛ ግን ዛሬ ቁርጣችሁን እወቁ አደባችሁን ግዙ እንላችኋለን፡፤ አሁን ህወሓት ይሉት የህዝብ ደመኛ ዳግም አይወለድም፡፤ዛሬ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለአንድነቱ ጥቅም ስለማንነቱ ቀለም ለማሳየት ነጋሪ አያሻውም።አሸባሪው ቡድን የዘራውን መርዛማ እሾህ ነቃቅሎ ፍቅርና ሰላምን እየዘራ ነው።ቀድሞ ህወሓት ከምዕራባውያን ጋር የፈጸመውን እርኩስ ጋብቻ አፍርሶ ኢትዮጵያን ትዳሬ ጎጆዬ ማለት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
አሁን በባንዲራው፣ በህልውናው የሚደራደር ትውልድ የለም፡፡በሰለጠኑ አገራት ሳሎን ተቀምጠው ምላሳቸውን ለሚዘረጉ ከሀዲያን መልስ የሚሰጥ ፤እንደናንተ በሞቀበት ከበሮ አዝሎ የሚጨፍር ዜጋ አይገኝም።ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ዘረኝነት፣ብሄርና ቋንቋ ይሉት ክፍፍል አይገባውም፡፡
ህወሓትን የተሸከመበት ጫንቃው ዳግም እንዳይላጥ ፣ግፍና በደል ያዘለበት ትከሻው እንዳይጎብጥ የህልውና ዘመቻ ይዟል፡፡ዘመቻው በህዝቦች አንድነት የደመቀ፣በቃልኪዳን ህብር የታሰረ ነው፡፡አሁን ለማንነቱ ክብር ፣ለሀገሩ ክብር በፈቃዱ ግንባሩን የሚሰጥ ዕልፍ ሆኗል።በየቀኑ በድጋፍ ሰልፍ ታጅቦ አቋሙን የሚገልጽ ፣ሀሳቡን የሚያጋራ ዜጋ ተበራክቷል ፡፡
አገሩን ለግል ጥቅሙ አሳልፎ የሰጠውን የህወሓት ቡድንና ጀሌዎቹን በመፋለም አዲስ ቀን ለማንጋት ፣የቆሰለች አገሩን ለማከም የሚተጋው ህዝብ ሁሌም በሥራ ላይ ነው።ህዳሴውን ዕውን ለማድረግ፣ሰላሙን ለማስከበር፣ጠላቱን ለማደባየት የኢትዮጵያ ህዝብ ከጀመረው ጉዞ ፈጽሞ አይመለስም፡፤
ህልመኞች ሆይ ! እንግዲህ ቁርጣችሁን እወቁ።የእናንተው ህወሓት እንዳለፈ ክረምት፣ እንደፈሰሰ ውሀ ማለት ነው፡፡ ከእንግዲህ የማይመለስ ጉዳይ አትናፍቁ፣ የማይመጣ እንግዳን አትጠብቁ ፣ኮሽ ባለ ቁጥር ከበሮ ይዞ መደለቅ፣በፌስቡክ መስኮት ብቅ ብሎ ‹‹አለን›› ማለት ‹‹የሞተን ማንሳት መሳሳት›› ይሆናል።አሁን የእናንት ተናፋቂ መሽቶበታል። አይናችሁ አዬቃብዝ ፤የየእጃችሁ አበባ አይድረቅ፤ አዎ ፤እሱን አትጠብቁት።መቼም፣የትም፣ በምንም አይመጣም ።አዎ! አይመጣም፡፡
ከጓንጉል
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6/2013