ማይካድራ እንደ ወትሮዋ ሞቅ ደመቅ ብላለች።የእለት ጉርሳቸውን ሸቅለው የሚያድሩ የቀን ሰራተኞችም ከተንጣለሉት ሰፋፊ እርሻዎች ውስጥ የሚቆረጠውን ይቆርጣሉ፤ የሚታረመውን ያርማሉ፤ ለገበያ የደረሱትንም በመልክ በመልካቸው እያዘጋጁ መኪና ላይ ይጭናሉ።
አብዛኞቹ የማይካድራ ነዋሪዎች የአማራ ተወላጆች ይሁኑ እንጂ የቀን ሥራ ሰርተው የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ከኦሮሚያ፤ ከደቡብና ከቤኒሻንጉል የመጡ ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል።ሁሉም በሚባል መልኩ ግን የሰፋፊ እርሻዎቹ ባለቤቶች የትግራይ ተወላጆች ናቸው።የሌሎች ብሄር ብሄረሰብ ተወላጆች ግን የቀን ሥራ ሰርቶ ከማደር ያለፈ መብት የላቸውም።
ላለፉት 30 ዓመታት ማይካድራ በእንዲህ አይነቱ ያልተመጣጠነ ኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ተጽዕኖ ስር ቆይታለች።በተለይ እስከ ጥቅምት 30/2013 ድረስ።ማይካድራን ከአካባቢው ነዋሪዎች በስተቀር ስሟን እንኳን በወጉ የሚያውቅ አልነበረም።ከጥቅምት 30 በፊት በነበሩ ጥቂት ቀናት ግን በከተማዋ አዳዲስ ክስተቶች ታዩ።
በርካታ የአሸባሪው ህወሓት ሰዎች በከተማዋ ውስጥ በስፋት መዋል ማደር ጀመሩ።በየስፍራው እየተዘዋወሩም ሰዎችን የመለየት፣ማንነትን የማወቅ ተግባር ሲከውኑ ቆዩ።ስልታዊ በሆነ ዘዴ መታወቂያ እየጠየቁ የአማራ ተወላጆችን የመለየት ሥራን አጠናቀቁ።ከዚህ ባለፈም የተለዩትን የአማራ ተወላጆች መኖሪያ ቤት ቁጥር በአግባቡ ይዘው ለታቀደው ጭፍጨፋ ዝግጁ አደረጉ።
ከጥቅምት 30 በፊት በአካባቢው ይህንን ጭፍጨፋ የሚያካሂድ ‹‹ሳምሪ›› የተሰኘ አረመኔ የወጣት ቡድን በቂ ልምምድ ሲያደርግ ቆይቷል።ከዘመናዊ መሳሪያ እስከ ባህላዊ መጥረቢያ ፤ቢላዋ፤ገጀራና ጩቤ በመታጠቅም ንጹሃንን ለማረድ በቂ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ነበር።
ቡድኑ አረመኔዊ ድርጊቱን በተገቢው ሁኔታ ለመፈጸም ቀድመው የተለዩ የአማራ ተወላጆች ቤትን መሰረት ያደረገ የሥራ ክፍፍል በመውሰድ ማን ማንን መግደል እንዳለበት የሥራ ድርሻ ወስዶ ተንቀሳቅሷል።ምን አልባትም በየቤቱ ከሚደረገው ጭፍጨፋ የሚያመልጡ የአማራ ተወላጆች ካሉም ተከታትሎ የሚገድል የታጠቀ ቡድን በማዘጋጀት ማንም ከዚህ ጭፍጨፋ እንዳያመልጥ በቂ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።
በተለይም ጥቅምት 30 ከመድረሱ አንድ ቀን አስቀድሞ በከተማው በመዘዋወር የጸጥታ ችግር ስለሚኖር ሁሉም ከቤት እንዳይወጣ በማዘዝ የጥፋት ቡድኑ የእንቅስቃሴ ገደብ አስቀመጠ።ይህንን አምነው የተቀበሉ ነዋሪዎችም የተደገሰላቸውን ባለማወቅ ቤታቸውን ዘግተው ተቀመጡ።
ይህ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረለት አረመኔውና ‹‹ሳምሪ›› የተሰኘው ገዳይ ቡድን ቤቱ ከቶ በተቀመጠው የማይካድራ ነዋሪ ላይ እሳት አነደዱበት።የገሚሱን ቤት ሰብሮ በመግባትም በያዙት መሳሪያ እንደ በሬ አረዱት። ከጅምላ ግድያው በተዓምር የተረፉ የአይን እማኞች እንደተናገሩት በማይካድራ የተደረገው ጭፍጨፋ ፍጹም አረመኔያዊነት የተሞላበት ነው።ሰዎች በቁማቸው አናታቸው በመጥረቢያ ተፈርክሶ ተገድለዋል።ሆዳቸው በጩቤ ተተርትሮም አንጀታቸው ተዘርግፎ ሞተዋል።በቁማቸው ስጋቸው በቢለዋ እየተገፈፈ በከፋ ስቃይ ህይወታቸው ያለፈ በርካቶች ናቸው።አባት እየተማጸነ በልጆቹ ፊት በገጀራና በመጥረቢያ ተጨፍጭፎ ተገድሏል።
በአሸባሪው ህወሓት ስምሪት የተሰጣቸው ‹‹ሳምሪ›› የተሰኙ ጨፍጫፊ ቡድኖች በገደሏቸው ሰዎች ሬሳ ላይ ተቀምጠው ቢራ ሲጠጡ ታይተዋል።በሬሳዎች ክምር መሃል ሆነውም ጨፍረዋል፤ ‹‹እምበር ተጋዳላይ›› ሲሉ ተደምጠዋል።
አማራ ጠሉ ህወሓት የአማራን ታሪክና ህልውና ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ያላደረገው ጥረት አልነበረም ።ከትላንት እስከዛሬ በአማራ ህዝብ ላይ በርካታ በደሎችን ሲፈጽም እንደኖረ ማንም የሚያውቀው ሀቅ ነው። ወጣቱ ሀገርና ህዝብን እንዲጠቅም በስነ ምግባር ከማነጽ ይልቅ በወንድም ህዝቦቹ ላይ እንዲነሳ የጥላቻ ንግግሮችን በማስረጽ ታሪካዊውን እልቂት ፈጽሟል።
ወጣት የጥፋት ኃይሎችን በአደንዛዥ እጽ በማስከር ትውልድ አይቶትና ሰምቶት የማያውቀውን አይነት ጭፍጨፋ ለመፈጸም በቅቷል።የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት እንዳረጋገጠው በማይካድራው ጭፍጨፋ ከ1ሺ 644 በላይ ሰዎች ሰለባ ሆነዋል ።አሸባሪው ህወሓት ዛሬም ድረስ ቦርቀው ያልጠገቡ አንድ ፍሬ ህጻናትን በአደንዛዥ እጽ ህሊናቸውን በማሳት ለጦርነት እያሰለፈ፤ በአዲሱ ትውልድ ላይ ሳይቀር እኩይ አላማውን እያስፈጸመ ይገኛል።
በአፋር ክልል የምትገኘውን ‹‹ፋንቲ ረሱ›› ዞን ጋሊኮማ ቀበሌንም ብዙዎች ከነመፈጠሯ አያውቋትም።ዛሬ ግን በአሸባሪው የህወሓት የሽብር ድርጊት ልማድ ስሟ እየተነሳ ይገኛል።የጋሊኮማ ቀበሌ ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባዮችና የዕለት ጉርሳቸውን ለማሟላት ዘወትር የሚባትሉ ምስኪኖች ናቸው።በየቀኑ አልሞላ የሚል ኑሮን ለማቃናት ደፋ ቀና ከማለት ባሻገር ለአንድ ቀን እንኳን ቀና ብለው ስለ ሀገሪቱን ፖለቲካ በቅጡ አውግተው አያውቁም።
የእነሱ ውሎና ትኩረት ሁሌም የዕለት ጉርሳቸውን ለማሟላት ቀና ደፋ ማለት ነው።ሆኖም ግን አሸባሪው ህወሓት ለእነዚህ ምስኪን ዜጎች ለአፍታ እንኳን አልራራም። በንጹሃን ዜጎቹ ላይ ጥቃት በከፈተ ጊዜ ከጦርነቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው 240 ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል።ከነዚህ ውስጥ 170 የሚጠጉት ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው።በርካቶችም ለከፍተኛ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል።ንብረቶቻቸው በአሸባሪው የህወሓት ጀሌዎች ተዘርፈዋል።
በከባድ መሳሪያ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸውና በዱብቲ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ከሚገኙ የአሸባሪው ህወሓት ሰለባዎች መካከል አቶ ሀሰን አንዱ ናቸው።አቶ ሀሰን በህወሓት የሽብር ድርጊት ምክንያት የቀኝ አይናቸውን አጥተዋል።የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።አቶ ሀሰን የ10 ልጆች አባት ሲሆኑ አሸባሪው ህወሓት ጥቃት ከከፈተባቸው ጊዜ ጀምሮ ልጆቻቸው የት እንደደረሱ አያውቁም፤ ሃብት ንብረታቸው ወድሞ ፤በአሸባሪው ጀሌዎች ተዘርፏል።ግለሰቡ ለፋና ቴሌቪዥን እንደተናገሩትም አሸባሪው ህወሓት ንጹሃንን በከባድ መሳሪያ ከመግደሉና ከማቁሰሉ ባሻገር ሴቶችን ደፍሯል፤በጥይት አቁስሏል።
የጋሊኮማ ነዋሪዎች ይህ ሁሉ እልቂት የደረሰባቸው ለሀገራቸው ለኢትዮጵያ ሲሉ ነው።አሸባሪው ህወሓት በአፋር በኩል የጅቡቲን መስመር በመቆጣጠር ኢትዮጵያውያንን በርሀብ ለመቅጣት ያደረገውን ክፉ ሙከራ በጀግንነት ተዋድቀው የሽብር ቡድኑን እኩይ ሴራ ማምከን ችለዋል።‹‹ከምንም ነገር በፊት ኢትዮጵያን›› ያለው የጋሊኮማ ነዋሪም ህይወቱን ገብሮ የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቋል።ለሀገር መሞት ክብር ነውና በአሸባሪው ህወሓት በግፍ የተገደሉ የጋሊኮማ ንጹሃን ተጋድሎን ታሪክ ሁሌም ሲዘክር ሲያስታውሰው ይኖራል።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6/2013