ከሐይማኖታዊው ትምህርት ውጪ የሆኑ የመደበኛ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት በኢትዮጵያ ከተዋወቀ ድፍን 113 ዓመታት ተቆጥረዋል። በነዚህ ዓመታት በርካታ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ወደስራ ገብተዋል። ይሁንና አብዛኛዎቹ የጥራት ችግር ያለባቸው እና ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያላሟሉ ስለመሆናቸው ይነገራል። የትምህርት ስርዓቱን የሚቆጣጠረው ትምህርት ሚኒስቴርም በኢትዮጵያ ያለውን የትምህርት ቤቶች አቅም ለማሳደግ ሀገሪቷ ገና ብዙ መንገድ እንደሚጠብቃት በተደጋጋሚ ጊዜ ገልጿል። በመማሪያ ክፍሎች ብዛትና ጥራት፣ በንጽህና አጠባበቅ እና በግጭት ወቅት በሚደርሱ ጉዳቶች ምክንያት የትምህርት ስርዓቱ እንደሚረበሽ ባለሙያዎች የሚገልጹት ሃቅ ነው።
በዛሬው እትማችን ከኮቪድ ጋር ተያይዞ በትምህርት ዘርፍ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቋቋም የተከናወኑ ስራዎች እና አዳዲስ መማሪያ ክፍሎች ግንባታ ላይ እንዲሁም ለትምህርት ዘርፍ እየቀረቡ የሚገኙ የገንዘብ ድጋፎች ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን አጠናቅረናል። ከዚህ በተጨማሪ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ተማሪዎች ወደትምህርት ቤት እንዲመለሱ በሚከናወኑ ስራዎች እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ታዬ ግርማ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፤ በትምህርት ዘርፉ ላይ ከኮሮና ጋር ተያይዞ የነበረውን ችግር ለመቋቋም ምን አይነት ጉዳዮች ላይ አተኩራችሁ ዝግጅት አድርጋችኋል?
አቶ ታዬ፤ በመጀመሪያ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ነው ትኩረት አድርገን በዋናነት የሰራነው። በተለይ ተማሪዎችን ወደትምህርት ቤት ስናመጣ እንዴት ባለ መልኩ መስተናገድ አለባቸው የሚለው ላይ ትኩረት አድርገናል።
በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት የትምህርት ዘርፉ ላይ ትልቅ ጫና እንደደረሰ ይታወቃል። ጫናውን ለመቋቋም እና ትምህርት ለማስቀጠል ነው ጥረት ሲደረግ የቆየው። በተለይ ለስድስትና ሰባት ወራት ከትምህርት ገበታ ርቀው የቆዩ ተማሪዎች ወደትምህርት በመመለስ ረገድ በሰፊው ጥረት ተደርጓል።
ጉዳዩ ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን በገጠሩ የሀገራችን ክፍል የምትገኝ አንዲት ሴት ከትምህርት ገበታ ለረጅም ጊዜ ስትቀር በተጓዷኝ የምትጠመድባቸው የህይወት ሁነቶች ሰፊ ናቸው። ስለሆነም ዳግም ወደትምህርት ቤት የመመለሷ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ይህንን ባማከለ ሁኔታ ነው በየቤቱ ጭምር በመንቀሳቀስና በማሳመን የተሰራው።
ከትምህርት ገበታ የራቁ ልጆች ደግሞ ዳግም ወደትምህርት ቤት ሲመጡ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎችን በተመለከተ በመንግስት ደረጃ ነው እቅድ ወጥቶ ሲሰራበት የቆየው። በተለይ ተማሪዎች እና መምህራን ኮቪድን እየተከላከሉ መማር ይችላሉ የሚለውን በተግባር ለማሳየት በርካታ ቁሳዊና ሞራላዊ ድጋፎች ቀርበዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትን መስፈርት በተከተለ መልኩ ርቀትን በጠበቀ መንገድ የመማር ማስተማር ክንውን እንዲካሄድ ተደርጓል። እየተባባሰ የመጣውን የኮቪድ ወረርሽኝ ባማከለ ሁኔታ ንጽህናን በመጠበቅና የእጅና አፍ መሸፈኛ ጭንብሎችን አጠቃቀም ልምድ ባሳደገ መልኩ ትምህርት ቤቶች መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛል።
ለዚህ ውጤት የሚረዱ አምስት አይነት ዋና ዋና ዝግጅቶች ቀደም ብለው ተደርጓል። በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተቋማት ከውሃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ምን አይነት አቅም አላቸው?፤ በቂ የመማሪያ ክፍል አላቸው ወይ? የሚሉ ጉዳዮች ላይ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል።
በመቀጠል ለመምህራንም ሆነ በተማሪዎች ላይ የሳይኮ ሶሻል ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው ወስነን ነው ወደስራ የገባነው። ስለትምህርት ሁኔታው መሰረታዊ ተግባቦት እና የግንዛቤ ስራ ለማከናወን የሚያስችል ሰነድ አዘጋጅተን ነበር። በኋላም ስትራቴጂ እና እያንዳንዱ ትምህርት ቤት እና ተማሪ ምን ማሟላት አለበት የሚለውን የሚመራ ፕሮቶኮል በማዘጋጀት ነው ወደስራ የተገባው።
እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተወያየን እና ዝግጅት ካደረግን በኋላ ነው ትምህርት ያስጀመርነው። በመማር ማስተማር ሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በአቅማችን አሟልተን በመሄዳችን ትምህርት በምንፈልገው ወቅት እና ሁኔታ መካሄድ ችሏል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም በዳስ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች አሉ፤ ይህን ሁኔታ ለማሻሻል ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ታዬ፡- ተማሪዎች የስነልቦናቸው ደረጃ ከፍ ብሎ በአግባቡ እንዲማሩ ለማድረግ ደረጃውን በጠበቀ ትምህርት ቤት ውስጥ መማር አለባቸው። በእርግጥ ካለው ድህነት እና የአቅም ማነስ አንጻር በዳስ ውስጥ አቧራማ እና ጸሐይ ያለበት ቦታ ላይ ተቀምጠው የሚማሩ ተማሪዎች ይኖራሉ።
ፍትሐዊ የትምህርት ተደራሽነትን ለማምጣት እነዚህን አስቸጋሪ የሆኑና ለመማር ማስተማር አዳጋች የሆኑ መማሪያ ቦታዎችን የማሻሻል ስራ በክልሎችም ሆነ በማዕከል ደረጃ እየተሰራ ነው። ግለሰቦችም በእራሳቸው ተነሳሽነት የሚያከናውኗቸው ግንባታዎች አሉ።
ዋናው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም አካባቢ በዳስ እና ዝናብ በሚያስገባ ስፍራ ትምህርት መከናወን የለበትም የሚለውን አቋም ይዞ መስራት ነው የሚያስፈልገው። በእርግጥ ይህን በአንድ ጊዜ ስራ ብቻ ለማሳካት አይቻልም።
ይሁንና በጊዜያቶች ሂደት ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎችን ለማዘጋጀት እንዲቻል በየዓመቱ በርካታ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው። በበጀት ዓመቱ እንኳን ከኮቪድ ጋር ተያይዞ የተማሪዎች ጥግግትን ለመቀነስ በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ተችሏል። ይህን ስራ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የኮቪድ ወረርሽኝ ተጽእኖን ለመከላከል በሚል ምን ያክል ተጨማሪ ክፍሎች ተገንብተዋል?
አቶ ታዬ፡- በህዝብም፣ በመንግስት አቅም እና በተለያዩ ተቋማት እና ባለሃብቶች ድጋፍ በርካታ የትምህርት ክፍሎች ተገንብተዋል። በአጠቃላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ እንዲቻል 72 ሺህ የመማሪያ ክፍሎች ናቸው የተገነቡት።
በተዘጋጀው ፕሮቶኮል መሰረት በአንድ ክፍል ውስጥ ከ25 ተማሪ መብለጥ እንደሌለበት ተቀምጧል። ለዚህ እንዲረዳ በሚል ነው ተጨማሪ ክፍሎችን እንዲገነቡ የተደረገው። በእርግጥ አንዳንድ በገጠር የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ልጆች ቁጥር ከ200 ላይበልጥ ይችላል፤ በዚህ ወቅት የክፍሎቹን ደረጃ የማሻሻል እንጂ ተጨማሪ ማስፋፊያዎች አልተገነቡም።
የተማሪ ቁጥራቸው ከፍተኛ በሆነባቸው እና ለግንባታ የሚሆን ቦታ ባላቸው ትምህርት ቤቶች ላይ ደግሞ አዳዲሶቹ ክፍሎች ተገንብተዋል። በርካታ መማሪያ ክፍሎች ተገንብተውም የተማሪዎች ቁጥር ከመመሪያው ጋር ለማጣጣም በሚል እንደ የትምህርት ቤቱ አቅም በፈረቃ የማስተማር ስልት እንዲከተል ነው የተደረገው።
በዚህ አካሄድ ሶስት ፈረቃ ድረስ ከፍለው የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች አሉ። ስለዚህ ተጨማሪ ስራ እንደሚያስፈልግ ይታመናል። በሌላ በኩል በነባር ትምህርት ተቋማት ማስፋፊያ ከማከናወን ባለፈ አዳዲስ ቦታዎች ላይ ትምህርት ቤቶችም ተገንብተዋል። በበጀት ዓመቱ ብቻ በተለያዩ አካባቢዎች 672 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ናቸው የተገነቡት።
ለአብነት በኦሮሚያ ክልል ብቻ 147 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አስገንብቷል። የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ በዚሁ ይበቃናል ተብሎ የሚተው ሳይሆን በቀጣይ ዓመትም በተመሳሳይ ከክልሎች ጋር በመተባበር የሚከናወን ነው። በተመሳሳይ የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡- በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ዝቅተኛ በሆነው የትምህርት ቤቶች ጥራት ላይ ኮቪድ ተደምሮበት በኢትዮጵያ ያለው የትምህርት ቤቶች ጥራት ምን ያክል ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ታዬ፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የትምህርት ቤቶች ጥራት ደረጃ 10 በመቶ ነው። ይህም የሚያሳየው 90 በመቶዎቹ ትምህርት ቤቶቻችን ዓለም አቀፍ ደረጃውን እንዲያሟሉ በርካታ ስራ ይጠይቃል ማለት ነው።
ከደረጃ በታች ሲባል የአይሲቲ መሰረተ ልማት መጓደል፣ የላብራቶሪ፣ የተማሪ ውጤት የተማሪ ክፍል ስፋት የተጓዳኝ ትምህርትና ግብአቶች መጓደልን ያጠቃልላል። ከደረጃ በታች በሆነ ትምህርት ላይ እያስተማርን ደግሞ ኮቪድ ወረርሽኝ ሲመጣ ጫናውን ከፍ እንዲያደርገው ግልጽ ነው።
ይህን ጫና ለመቋቋም ትምህርት ሚኒስቴር ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ ተቋማትን አስተባብሯል። በዚህም 930 ሚሊዮን ብር ለክልሎች ተሰጥቷል። ገንዘቡ በዋናነት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እና የኮቪድን ተጽእን ለመቀነስ እየዋለ ይገኛል።
ተማሪዎች ንጽህናቸው በጠበቀ መልኩ የአፍንጫና አፍ መሸፈኛ እንዲሁም ሳኒታይዘር አቅርቦት እንዲመቻችላቸው እንዲሁም ጤናቸው በተጠበቀ መልኩ ክፍሎቻቸው ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ድጋፍ ተደርጓል።
ከዚህ ባለፈ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ 27 ሚሊዮን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በማቅረብ መማር ማስተማሩን አስቀጥሏል። ስለዚህ በተለያዩ ግብአቶች ምክንያት ከደረጃ በታች የነበሩ ትምህርት ቤቶች በኮቪድ ምክንያት ደግሞ ይባስ ብሎ ከዓለም አቀፉ ደረጃዎች በታች እንዳይሆኑ ጥረት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ከኮቪድ መከላከል ድጋፍ ባሻገር ለትምህርት ቤቶች ጥራት መሻሻል ምን ያክል ድጋፍ አድርጋችኋል?
አቶ ታዬ፡– የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ የድጎማ በጀት በሚል ለየትምህርት ቤቶቹ የሚከፋፈል ገንዘብ አለ። ገንዘቡ በየትምህርት ቤቱ በሚገኙ ተማሪዎች ቁጥር ልክ ተሰልቶ ይከፋፈላል።
በዚህ አካሄድ ለትምህርት ጥራት ማስጠበቅ የድጎማ በጀት ዘንድሮ እስከ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር ፈሰስ ተደርጓል። ገንዘቡ ከአንደኛ ክፍል እስከ አራተኛ ክፍል ምን ያክል ተማሪ አለ?። ከአራተኛ እስከ ስምንተኛ እንዲሁም ከስምንተኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ በሚገኙ ተማሪዎች ልክ ምን ያክል በጀት ያስፈልጋል የሚለው ይታያል።
በአንድ ተማሪ ከ55 ብር አንስቶ እስከ 70 ብር ድረስ ለትምህርት ቤቶቹ ተመድቧል፤ ይህ ሂሳብ ተሰልቶ ለየትምህርት ቤቶቹ ይሰጣል። አነስተኛ ተማሪ ያላቸው ቢሆኑም እንኳን ዝቅተኛ የሚያገኙት ገንዘብ አስር ሺህ ብር ነው። በትምህርት መረጃ ስርአት መሰረት ደግሞ በተማሪያቸው ቁጥር ልክ እየተሰላ ከአስር ሺህ ብር በላይ የሚያገኙ ትምህርት ቤቶች በርካታ ናቸው።
በተጨማሪ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸውን ትምህርት ቤቶች ይሸለማሉ። በአፈጻጸም የተሻለ ትምህርት ቤት 30 ሺህ ብር ድጋፍ ይደረግለታል። በዚህ አሰራር 105 ሚሊዮን ብር ለክልሎች ተሰጥቷል። ገንዘቡ የትምህርት ቤቶችን አቅም ለማጎልበት ነው የሚውለው።
አዲስ ዘመን፡- ለትምህርት ጥራት ማስጠበቅ የሚለቀቀው ገንዘብ ለታለመለት አላማ ውሏል የሚለውን የምትከታተሉበት አሰራር አለ?
አቶ ታዬ፡- በጀቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ነው የሚላከው፤ ሚኒስቴሩ ለወረዳዎች ያከፋፍላል። ወረዳ ትምህርት ቤቶቹ በሚያቀርቡት እቅድ መሰረት ደግሞ ከየወረዳቸው አማካኝነት በጀቱ ይለቀቅላቸዋል። እንደየትምህርት ቤቱ ሁኔታ የሚያገኙትን በጀት ለአራት አላማዎች ሊያውሉት ይችላል።
በአንደኛነት ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ ለማድረግ ይጠቀሙበታል። ይህም ላብራቶሪያቸውን ማጠናከር፣ ቤተመጻሕፍቶችን ማደራጀት እና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን የሚያጠቃልል ነው። በሁለተኛነት የመማር ማስተማር ሰላማዊ ለማድረግ የሚያግዙ ስራዎችን ቀርጸው መተግበር ላይ ሊያውሉት ይችላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ማህበረሰቡን ለማስተባበር ይጠቀሙበታል። ከበጀቱ ላይ ወላጆች ህብረት የተለያዩ ስራዎች ማስኬጃ ማዋል ይችላሉ። በአራተኝነት ደግሞ የትምህርት አመራርን አቅም ለማጎልበት የሚያግዙ ስልጠናዎችም ሆነ ተጓዳኝ ክንውኖችን ለመደገፍ ይውላል።
የትኛው ትምህርት ቤት ምን አቅዶ ምን አይነት አፈጻጸም አከናውኗል የሚለው በወረዳ ጭምር ክትትል ይደረጋል። ለቤተመጽሐፍት ማደራጃ ብሎ የወሰደውን ገንዘብ አሊያም ለላብራቶሪ እቃ ግዥ ተብሎ የተወሰደው መሬት ላይ በአግባቡ ውሏል ወይ የሚለው ይታያል። ገንዘቡም ኦዲትም ይደረጋል።
በማዕከል ደረጃ በየሩብ ዓመቱ የተጠናቀሩ መረጃዎችን በመለየትና ችግር ያለባቸው እንዲስተካከሉ ጥረት ይደረጋል። ፕሮጀክቱ ላይ የተቀጠሩ እና ስራውን የሚከታተሉ ባለሙያዎችም አሉ። ስለዚህ እያንዳንዱ ስራ ተለይቶ ክትትል የሚደረግበት አሰራር አለን።
አዲስ ዘመን፡- በ330 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ የምታደርጉት የትምህርት ቤቶች ንጽህና አጠባበቅ ፕሮግራም ነበረ ፤ ስራው ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ታዬ፡- ፕሮጀክቱ ትምህርት ቤቶች በውሃ እና ንጽህና መጠበቂያ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ የሚያግዝ ነው። በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ 330 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
ከትምህርት ሚኒስትር ጋር የውሃና ኢነርጂ፣ የጤና እንዲሁም የፋይናንስ ሚኒስቴሮች በጋራ የሚመሩት ፕሮጀክት ነው። በፕሮጀክቱ ለ2013 በጀት ዓመት 61 ሚሊዮን ብር ለክልሎች ተከፋፍሏል። በጀቱ በየትምህርት ቤቶቹ ለውሃ አቅርቦት፤ ለመጸዳጃ ቤት እና ለተለያዩ ንጽህና መጠበቂያ ስራዎች ይውላል።
በርካታ ወረዳዎች ላይ አንድም መጸዳጃ ያልነበራቸው ትምህርት ቤቶች አሁን ላይ መሻሻሎችን አሳይተዋል። በውሃ አቅርቦትም ቧንቧ መስመር የሌላቸው በቦቴ መኪና እና በታንከር ጭምር በማመላለስ ለተማሪዎችና መምህራን ማቅረብ ችለዋል።
ፕሮጀክቱ በጥሩ አፈጻጸም እንደቀጠለ ነው። ፕሮጀክቱ በቀጣይነት የሚተገበር በመሆኑ በተቀናጀ መንገድ ድጋፍ በማቅረብ ቀስ በቀስ የትምህርት ቤቶችን አቅም ለማጎልበት ይሰራበታል። አሁን ላይ በንጽህና እና ጤና አጠባበቅ ረገድ በትምህርት ተቋማት ዘንድ ያለው ክንውን እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም በዘርፉ ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅ አያጠያይቅም።
አዲስ ዘመን፡- ከኮቪድ ባለፈ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ምን አይነት ጥረት እያደረጋችሁ ነው?
አቶ ታዬ፡- በትምህርት ጉዳይ የአደጋ ጊዜ ስራ /Education Emergency/ የሚል አሰራር አለን። ይህም ትምህርትን በአደጋ ጊዜም ማስቀጠል ይቻላል የሚል ሃሳብ አለው።
ትምህርት በግጭት ወቅት ብቻ ሳይሆን በጎርፍ አደጋ፣ በረሃብ እና በሌሎች ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ይቋረጣል። ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች እንደ አጣዬ ፣ ወለጋ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ላይ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንደመፍትሄ የሚወሰደው የማካካሻ ትምህርት መስጠት ነው።
እንደሀገር ከተቋቋመው ከብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ እንሰራለን። የአደጋ ምላሽ ተዘጋጅቶ በምን የተፈናቀሉ ዜጎችም እንዲመለሱ እና ትምህርት ቤቶች ዳግም እንዲደራጁ ጥረት እናደርጋለን።
በዚህ አግባብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝም ሆነ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ላይ ባከናወናቸው ስራዎች ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ተመልሰው የማካካሻ ትምህርት እያገኙ ነው። ይህንን ስራ በተመለከተ በክላስተር ደረጃ የተቋቋመና የሚቆጣጠር አካል አለ።
የመማር ማስተማር ስራ የተቋረጠባቸው እና እንዲቀጥል የተደረገባቸው አካባቢዎች የማካካሻ ትምህርት ምን ደረጃ ላይ ነው የሚለውን በቅርበት እንገመግማለን። ይህን ተከትሎ ለውጥ የሚታይባቸው በርካታ ቦታዎች አሉ።
በዛው ልክ ደግሞ ግጭቶች በተባባሰባቸውና ትምህርት የተቋረጠባቸውም በርካታ ቦታዎች አሉ። ከህወሓት ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ተቋርጧል። ነገሮች ሲስተካከሉ ተማሪዎችን በመቀበል የማካካሻ ትምህርት እንዲሰጥ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- ትግራይ ክልል ባለው ችግር ምክንያት ትምህርት ለረጅም ጊዜ ተቋርጧል፤ ነገሮች ወደቀደመው ጊዜ የሚመለሱበት ሁኔታ ሲኖር ትምህርት ለማስቀጠል እንዲያመች ካሁኑ ምን አይነት የቅድመ ዝግጅት ስራ ያስፈልጋል?
አቶ ታዬ፡- ትግራይ ክልል መንግስት የህግ ማስከበር እርምጃ ከወሰደ በኋላ ትምህርት ዳግም ለማስጀመር ሰፊ ጥረት ነበር የተደተረገው። በወቅቱ ግን ህወሓትም የሚያደርገው እንቅስቃሴ እና የተለያዩ ችግሮች ተዳምረው ዳግም ትምህርት ሳይጀመር ቀርቷል።
ትምህርት ቤት ዜጋ የሚፈራበት እና ትውልድ የሚቀረጽበት ቦታ ነው። ይህንን በአግባቡ ለህብረተሰቡ ማስረዳት እና ችግሮች እንዲስተካከሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች ዞሮ ዞሮ የመንግስት እና የህዝቡ እዳ ሆነው ነው የሚቀጥሉት።
ምን ማለት ነው አሁን ላይ ህወሓትም ሆነ የትኛውም ግለሰብ ትምህርት ቤቶችን ሲያወድሙ ከግጭቱ በኋላ መንግስት እና ህዝብ ላይ ነው ትምህርት ቤቶቹን የማደስ እና ለትምህርት ዝግ የማድረግ ኃላፊነቱ የሚወድቅባቸው። ስለዚህ ህዝቡ መልሶ መገንባት የሚጠይቀውን ስራውን አስቦ ካሁኑ የጥፋት ስራዎችን መከላከል እንደሚገባው በተለያዩ አማራጮች ማሳወቅ ይገባል።
ተጎጂውም ሆነ የመከራው ገፈት ቀማሽ ህብረተሰቡ መሆኑን በበቂ ሁኔታ በማሳወቅ የየአካባቢውን ማህበረሰብ ማንቃት ያስፈልጋል። ይህ ስራ ደግሞ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን በቅንጅታዊ አሰራር የሰብአዊ አቅርቦት ላይ የተሰማሩ ተቋማትም በጋራ ሊያከናውኑት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ችግሩ ባይፈጠር መልካም ነበር፤ ከመጣ በኋላ ግን ያለው አማራጭ የመልሶ ማቋቋሚያ እቅድ ማዘጋጀት ነው የሚያስፈልገው። 90 በመቶዎቹ ትምህርት ቤቶቻችን ከደረጃ በታች ናቸው እያልን እንደዚህ አይነት ግጭት ሲከሰት ደግሞ ችግሩ እየተባባሰ ነው የሚሄደው።
በትግራይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ወደደረጃ ሶስት እና አራት እናሳድጋለን ብለን ልንሰራ የምንችለውን ክንውን ወደኋላ የሚጎትት ጉዳይ ተፈጥሯል። ስለዚህ ግጭቱ ሲረጋጋ እና አካባቢው ወደነበረበት ሁኔታ ሲመለስ በርካታ ትምህርት ቤቶችን መጠገን እና ለትምህርት ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ጊዜም ሆነ ገንዘብን የሚጠይቅ ነው።
በተመሳሳይ አካባቢው ያሉ ችግሮቹ ተስተካክለው ወደመደበኛው ሰላም ሲመለስ ለረጅም ጊዜያት ከትምህርት ርቀው የቆዩ ልጆች ዳግም ወደትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ሰፊ ጥረት ያስፈልጋል። ለዚህ ስራ ደግሞ መንግስት የጀመረው የሀገር ህልውና የማስከበር ስራ ሲጠናቀቅ በሙሉ አቅም ህብረተሰቡን በማስተባበር ወደስራ የምንገባበት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በትምህርት ቤቶች የጾታ ምጥጥን በማሳደግ ረገድ በ2013 በጀት ዓመት ምን ያክል አፈጻጸም ተመዝግቧል?
አቶ ታዬ፡- የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ እና ምጥጥን ላይ በተያዘው በጀት ዓመት አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከወንዶች እኩል ሴት ልጆችም ወደትምህርት ገበታ መሄድ አለባቸው የሚል እሳቤ በማደጉ በተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጭምር ጥሩ ውጤት ታይቷል። ሴቶች በብዛት ወደትምህርት ገበታ መላክ እንደ ግዴታ እና አግባብ እንደሆነ ልምድ የሚቆጥሩ በርካታ ማህበረሰቦች ለዚህ ውጤት መገኘት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። ይሁንና አሁንም ችግሮች የሚታዩባቸው አካባቢዎች መኖራቸው ግን የአፈጻጸም ክፍተቶች እንዲታይ አድርጓል።
በቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የሴቶች ትምህርት ምጥጥን ከዚህ በፊት ከነበረው አንጻር ክፍተት እንዳለበት ታይቷል። ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ቀጣይ ጊዜያት በዘመቻ መልክ ለመስራት ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል።
በዘመቻው የባለድርሻ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሚዲያ እንዲሁም መላውን ህብረተሰብ ያማከለ ስራ ይከናወናል። ሁሉም የገጠር አካባቢዎች ወላጆች ላይ ያለ አድልኦ ልክ እንደወንድ ልጆቻቸው ሁሉ ሴት ልጆቻቸውንም ወደትምህርት ቤት እንዲልኩ የማሳመን ጥረት ይደረጋል።
ቤት ለቤት ጭምር በሚከናወኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ለቀጣይ ዓመት የትምህርት ዘመን በርካታ ሴቶች ወደትምህርት ቤት መመለስ እንደሚቻል እምነት ተጥሏል። ሴት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ከማምጣትም ባሻገር የማቆየትና ለውጤት እንዲበቁ የማድረግ ሥራ በተመሳሳይ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።
ትምህርት ሚኒስቴርም በሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬቱ እንዲሁም በየክልል ቢሮዎች አማካኝነት እና በሚኒስቴሮችም ደረጃ ሴቶች በስፋት ወደትምህርት ቤት እንዲመጡ ይሰራል። ለዚህም ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ህፃናትን እና በተለያዩ ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ ከፍተኛ ስራ ይከናወናል።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን የሚያስገነቡ ሀገር ወዳዶች አሉ፤ ከእነሱ ጋር በቅርበት የምትሰሩበት መንገድ እስከምን ድረስ ነው?
አቶ ታዬ፡- በተለያዩ የኢትዮጵያ ገጠራማ ቦታዎች ላይ ትምህርት ቤቶችን የሚያስገነቡ ኢትዮጵያውያን አሉ። ለግንባታ ከሚመጡት ጋር ሁሉ በመተባበር ስሜት ነው የምንሰራው። ከዚህ ውስጥ የቀዳማይት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት ተጠቃሽ ነው።
ትምህርት ሚኒስቴርም ለቀዳማይ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከ30 በላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በማስገንባታቸው እውቅና ሰጥቷል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሽፋን 40 በመቶ ያክል ነው።
ስለዚህ 60 በመቶውን አካባቢ ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም። በዚህ ረገድ ቀዳማይ እመቤቷ እያከናወኑ የሚገኘው ስራ የሚመሰገን ነው፡፡ ሚኒስቴሩም በሚያከናውኗቸው ስራዎች ላይ ተባባሪ ነው። በቀጣይም በሚያከናውኗቸው ግንባታዎች ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እክል አይኖርበትም።
በተመሳሳይ ህብረት በመፍጠር በአካባቢ ተወላጅነት፣ በበጎ ፈቃድ ተነሳሽነት እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ተነሳስተው ትምህርት ቤቶችን የሚሰሩ ግለሰቦችና ማህበራት አሉ። ከነሱም ጋር በተመሳሳይ መልኩ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በጋራ በመስራት እየተሳተፍን ይገኛል።
ሀገራችንን በትምህርት ዘርፍ የተሻለ መጓዝ እንድትችል የሚያግዙ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ሚኒስቴሩ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተረድተው ቀርበው ቢያናግሩ መልካም መልስ ያገኛሉ። በዚህ የትብብር መንፈስ ከሰራን በየአካባቢው የሚገኙ ልጆችም የትምህርት እድል በሰፊው እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በየትምህርት ቤቱ የሚያስፈልጉ የላብራቶሪ እና የቤተመጻሕፍት ግብአቶችን ወደሃገር ውስጥ ለማስገባት እንዲረዳ ከዲያስፖራዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ምን ያክል በቅንጅት እየሰራችሁ ይገኛል?
አቶ ታዬ፡- ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ያለን ግንኙነት ጠንካራ ነው። በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በትምህርት ቤት ግንባታውም ሆነ ትምህርት ቤቶችን በማዘመን ረገድ የበኩላቸውን እየተወጡ ነው።
በተለይ ደግሞ ዘመናዊ የላብራቶሪ መሳሪያዎችን በማስገባት እና ቤተ መጻሕፍትን በማደራጀት ረገድ ዲያስፖራው በተናጠል የሚያደርገውን ጥረት በተቀናጀ መልኩ ማስኬድ የሚቻልበት መንገድ አለ። በተለይ ዲያስፖራው ማህበረሰብ ያቋቋመው የፈንድ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር አለ፤ ይህን ፈንድ ለትምህርት ዘርፍም እንዲያውለው ጥረት እየተደረገ ነው።
ከዲያስፖራው ባለፈ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እንሰራለን። ዩኔስኮ፣ ከጀርመን የተራድኦ ድርጅት (ጂአይዜድ) እና የተለያዩ ተቋማትም በቅርበት እየሰሩ ይገኛል። ስለዚህ ይህን የቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር ትምህርት ቤቶችን የማዘመን ስራውን ማጎልበት ያስፈልጋል።
የላብራቶሪም ሆነ የቤተ መጻሕፍት ማደራጀት ስራ በትምህርት ቤቶች አቅም አሊያም በትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ማከናወን ይከብዳል። ስለዚህ ዲያስፖራው እና ዓለም አቀፍ ተቋማትም የበኩላቸውን እንዲወጡ ቀለል ያሉ አሰራሮችን እየተገበርን ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ታዬ፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2013