አዲስ አበባ፦ የአባይ ተፋሰስ አገራት የኢትዮጵያ ደራስያን ጉባዔ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር አስታወቀ።
ማኅበሩ ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ደራሲ አበረ አዳሙ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን እንደቤታቸው የሚቆጥሩ አፍሪካውን፤ የአፍሪካ ደራስያን ማህበር ጽሕፈት ቤት ወደ አዲስ አበባ የሚዘዋወርበትን ቀን ሲጠባበቁ ቆይተዋል። ይሁንና የኢትዮጵያን ሰላም መደፍረስ ዜና በሰሙባቸው ጊዜያት ስጋት ገብቷቸው እንዳዘኑና ይህንንም ለማኅበሩ ሲገልጹ እንደነበር ተጠቁሟል።
«በመሆኑም እንዲህ ነው እንዲያ ነው የሚል መልስ ለእያንዳንዱ ደራሲ ከመንገር ይልቅ በአካል መጥተው የአገራችንን ሁኔታ አይተው እውነታውን እንዲገነዘቡ ነው ጉባዔው በአዲስ አበባ የሚካሄደው» ሲሉ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከኤርትራ ደራስያን ማኅበርም ጋር መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶች መጀመራቸውንና ያንን አጠናክሮ ለማስኬድ የታሰቡ የእቅድ ሥራዎች መኖራቸው ተገልጿል። በዚህም «ጉዞ ፊያሜታን ፍለጋ» በሚል ርዕስ የፕሮጀክት መነሻ ሃሳብ ለማኅበሩ መቅረቡን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህም ለማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ቀርቦ የሚወሰነውን ውሳኔ በመከተል ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
የማኅበሩ የሕዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ደራሲ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው፤ ጉባዔውን በተመለከተ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚነሱት ደራስያን ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ጊዜ ተዟዙረው አገሪቱን እንዲያዩና ታላቁን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች እንዲጎበኙ መታሰቡን ገልጸዋል። ወደ አርባ የሚጠጉ አፍሪካውያን ደራስያን ይሳተፉበታል በተባለው በዚህ ጉባዔም፤ ልምድ የሚያካፍሉበት መድረክ እንደሚመቻችም አያይዘው ጠቅሰዋል።
ማኅበሩ እነዚህንና ሌሎችም ተግባራት በብቃት ለማከናወን እንደወትሮው የአባላቱ፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የሥነ ጽሑፍ አፍቃርያን ትብብር እንዳይለያቸው ጥሪ ቀርቧል።
በተጨማሪ በመግለጫው በማኅበሩ የታሰቡ የሥራ እቅዶች የቀረቡ ሲሆን፤ ከጉባዔው ባሻገር የጥበብ አምባ መገንባት አንዱ ነው ተብሏል። ማኅበሩ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተረከበው ቦታ ላይ የማህበሩን ጽሕፈት ቤት ግንባታ ለማከናወን በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።
እንዲሁም ሥነ ጽሑፍ ለአገራዊ መግባባት የሚኖረውን ፋይዳ መሰረት ያደረገ ወርሃዊ የሥነ ጽሑፍ ምሽት የሚከናወን ሲሆን ማኅበሩ በየዓመቱ የሚያከናውነው «ሕያው የጥበብ ጉዞ» ም በዚህ ዓመት «ሕያው የጥበብ ጉዞ ወደ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ እና ወደ ዳኛቸው ወርቁ (አደፍርስ) ምድር» በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል።
ማኅበሩ በ2003ዓ.ም የአፍሪካ ደራስያን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ማካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ደራስያን ማኅበር ማረፊያ እንድትሆን ሃሳብ የቀረበው በዛን ወቅት ነበር።
ሊድያ ተስፋዬ