በዓለም ፖሊሲነቷ ዘመናትን ተሻግራለች። በተለይ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የኢኮኖሚውን ማማ ተቆጣጥራለች። ጦርነቱን ወደ ኢኮኖሚያዊ እድገት መሸጋገሪያ ድልድይ በማድረግ የነበረችበትን የምጣኔ ሀብት ደረጃ መቀየሯም ሚሊዮኖችን ከበላው ጦርነት ጋር ተያይዞ ስሟ መሬት አርፎ አያውቅም፤ ሁሌም እንደተነሳች ነው። በዚህ ብቻም ሳይሆን የተለያዩ አጋጣሚዎችን ወደ እድል በመቀየርና በመጠቀም እዚህ ደረጃ የደረሰች አገር ነች – አሜሪካ።
በቀደም፣ በ1776 ይህን ዓለም የተቀላቀለችው አሜሪካ ይህ የኢኮኖሚ እድገቷ የፈጠረላትን አጋጣሚ በመጠቀም፣ የሌሎች አገራት ወደ ኋላ መቅረትን እንደ አንድ ጥሩ ዓለምን የመቆጣጠሪያ ቁልፍ መሳሪያ አድርጋ በመውሰድ እነሆ ዛሬ “ዓለም እንዴት ሆኖ ከእኔ መዳፍ ውጪ ሊኖር ይታሰበዋል” በሚል የወሸነኔት ስሜት የፈለገችውን እያፈረሰች፤ ቀና ያለውን እየደፈቀች፤ በማደግ ላይ የሆነውን ቀኝ ኋላ እያዞረች እዚህ ደርሳለች።
በተለይ ከ1990ዎቹ፣ “ሶቪየት ህብረት ተፈረካከሰች” ከተባለበት ወቅት ጀምሮ ሩሲያ እስካንሰራራችበት ቅርብ ጊዜ ድረስ ያለ ተቀናቀኝ ዓለምን አሹራለች።
ስለ አሜሪካ ትንፍሽ ማለት ከወደ ዋሽንግተን የሚሰጠው አፀፋ “በዲሞክራሲ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት” የሚል ነው። እሷ እሰው አገር፣ ለዛውም በድንበር አይደለም በአህጉር እንኳን የማትገናኘውን አገር አየር ሰንጥቃ በመሄድ ስታፈርስ ትንሽ እንኳን አይሰቀጥጣትም፤ ሀይ ባይ ተቆጪ አይደለም፤ ሀይ ባይ ሽማግሌ እንኳን የላትም። አገር ካፈረሰች በኋላ መልሳችሁ ትገነቡ ዘንድ እገዛ ላድርግላችሁ በማለት ጨጓራ የምትልጠው ነገር እራሱ ሌላ ህመም ሲሆን ያው የደሀ ነገር … ነውና ለመቀበል እጁን የሚዘረጋው ቁጥሩ ብዙ ነው። የለመደች ጦጣ … እንደሚባለው ይህንን ልምዷን ነው በአሁንም ሆነ ከድሮ ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ ልታደርገው ነው የምትፈልገው።
የትራምፕን መሰናበትና የባይደንን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የእንግሊዙ ጠ/ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ “አሜሪካ በመላው ዓለም ለዲሞክራሲ የቆመች አገር ናት” ሲሉ የሚያንቆለጳጵሷት ብልፁግ አገር፤ የሩሲያው ፑቲን “ዘመን ያለፈበት”ን ስርአት የምትከተል አገርና የእራሷን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ የዓለም የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ለማድረግ የምትጥር ሞኟ አሜሪካ፤ ምርጫውን ተከትሎ በአሜሪካ ም/ቤት በተከሰተው ነውጥ (የትራምፕ ደጋፊዎች)ና ነውጡ ያስከተለውን ፖለቲካዊ ቀውስ አስመልክተው በውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤታቸው በኩልም “በአሜሪካ የምርጫ ስርዓቱ ጊዜ ያለፈበት ነው፤ ዘመናዊ የዲሞክራሲ መስፈርቶችን አያሟላም፤ በዚህም የተነሳ ለበርካታ ጥሰቶች ዕድል ይከፍታል፤ የአሜሪካ ሚዲያም የፖለቲካ ትግል መሳሪያ ሆኗል” በማለት ስለ እሷ እርማቸውን ማውጣታቸውን የሚናገሩላት የዓለም ፖሊሷ ዩኤስኤ “ደካማ” በምትላቸው አገራት ላይ እስካሁንም ክርኗን ልታነሳ አልቻለችም።
የቬንዝዌላ መንግስት በበኩሉ በሰጠው መግለጫ “በዚህ አሳዛኝ ሁነት፣ አሜሪካ በጠብ አጫሪነት ፖሊሲዋ በሌሎች አገራት ላይ የፈጠረችው ዓይነት ችግር ነው የገጠማት” በማለት ያስተላለፈው መልእክት፤ እንዲሁም የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሮሃኒ “አሁን በአሜሪካ የታየው ሁነት የምዕራቡ ዲሞክራሲ ምን ያህል የከሸፈ መሆኑን ያረጋገጠ ነው … ህዝበኛው መሪ የገዛ አገሩን መልካም ስምና ዝና ጥላሸት ቀብቷል” ሲሉ ባይደንን “ተቀበል” ያሉት መልእክት ከላይ ካልነው ጋር አብሮ የሚሄድ በመሆኑ ሳይጠቀስ ሊታለፍ የሚገባው አይደለም። የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት አስተያየት፤ “ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ የዚምባቡዌ የዲሞክራሲ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው በመጥቀስ፤ በአገራችን ላይ ወገብ የሚቆርጥ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥለውብናል። በምርጫው የተስተዋለው ክስተት አሜሪካ የዲሞክራሲ ጠበቃ ነኝ በሚል ሽፋን ሌላ አገር ላይ ቅጣት የመጣል የሞራል ብቃት እንደሌላት አረጋግጧል” ሲሉ የአሜሪካንን ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት አያያዝ ማብጠልጠላቸውም እንደዛው።
ዓለም እንደሚያውቀው ፍጥጥ ያለ “ጣልቃ ገብነት”ን እንደ አንድ ተገቢና ትክክለኛ የዲፕሎማሲ ተግባርና ሀላፊነት አድርጋ የቆጠረች ብቸኛ አገር ብትኖር ከእሷ ሌላ ማንም የለም። የሌላውን አገር ሉአላዊነት መዳፈር ለአሜሪካ የክብርና ማንነት ጉዳይ፣ ለሰብአዊ መብት የመቆርቆር ጉዳይ ሲሆን ለዛኛው አገር ደግሞ በአሜሪካ መቀጥቀጥ፣ ካስፈለገም መፍረስ ከላይ የተሰጠው “የ40 ቀን እድሉ” ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ እያንዣበበች ያለችው ንስር አሞራም አላማ ይሄው ነውና “ወገን አትዘናጋ” ማለት ተገቢ ይሆናል። ከመንግስት ጀምሮ መንግስታዊ የሆኑም ያልሆኑም ተቋማት በአንድ ድምፅ “የውጪን ጠላት ለመመከት ህብረተሰቡ በጋራ ሊቆም ይገባል!!!”፤ “የውክልና ጦርነት እየተካሄደብን ነውና ሁሉም ለውድና አንዲት አገሩ ኢትዮጵያ ዘብ ሊቆም ይገባል!!!” ወዘተ በማለት እያስተላለፉት ያለውን ጥሪም ከዚሁ አኳያ መገንዘብ ይገባል።
አሜሪካ ከፈጣሪዋ ልትታረቅ ይገባት ዘንድ፣ ፈጣሪም ይቅር ይላት ዘንድ “እግዚኦ መህረነ ክርስቶስ” ሊባልላት የሚገባት አገር ነች። ለዚህ ደግሞ ምክንያቶቹ በርካታ ሲሆኑ ከሁሉም በላይ በየቀኑ፣ በየሰዓትና ደቂቃው ሁሉ አጥብቃ እየሰራች ያለችው የወዳጆቿን ቁጥር መቀነስና የጠላቶቿን ቁጥር መጨመር ላይ መሆኑ ነው።
እንደሚታወቀው፣ እየበደለቻትም ቢሆን ኢትዮጵያ እና የኢትዮጰያ ህዝብ የአሜሪካ ወዳጆች ናቸው። ምንም ሆነ ምን የግንኙነት እድሜያቸው ረዥም ነው። ምንም እንኳን ደርግ አልሆንልህ ብሎት፣ ቢያስቸግሩት በ24 ሰዓት ከአገር እንዲወጡ በማዘዝ በኢትዮጵያ የዩኤስኤን ኤምባሲ የዘጋ ቢሆንም፤ ተመልሰው ግንኙነቱ ቀጥሎ እስካሁን አብረን አለን።
እኛና አሜሪካ አብረን እንኑር እንጂ፣ እኛ ለአሜሪካ መልካም ወዳጅ እንሁንላት እንጂ እሷ ግን መሽቶ እስኪነጋ፣ ነግቶ እስኪመሽ ድረስ ለእኛ ጉድጓድ ከመማስ ተቆጥባ አታውቅም። ለዚህ ደግሞ አሁን እያደረገችው ካለው በእጅ አዙር ኢትዮጵያን የማፍረስ እና “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል መግባት ካለብን እንገባለን” የሚለውን አሸባሪ ቡድን በመደገፍ እያደረገች ካለችው እኩይ ተግባር በበለጠ የቀድሞው ጠ/ሚ ፍቅረሥላሴን “እኛና አብዮቱ” መጽሐፍ መመልከት ይቻላል። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ተግባር (የወዳጅን ቁጥር መቀነስና የጠላትን ቁጥር መጨመር) አለ? እግዚኦ ሊባልላት፤ መሪዎቿ በየመድረኩ “እግዚአብሄር አሜሪካንን ይባርክ” የሚሉትንም ከቀልብና ልባቸው እንዲያደርጉት ፈጣሪ ይታረቃችው ዘንድ እንለምንላቸዋለን። እኛ የራሳችንንም የማንሰጥ፤ የሰውም የማንፈልግ ነንና ክፉ ክፉውን አንመኝላትም። እዚህ መጥታም (ቬትናም እንደሆነችው) እንድትዋረድ አንፈልግም።
በአጠቃላይ እኛ ኢትዮጵያዊ ነን እንጂ አሜሪካዊ አይደለንም። በኢትዮጵያ ደግሞ ቀልድ የለም፡፡ በኢትዮጵያ፤ የሚቃጣን ማንኛውንም አይነት ጥቃት የመመከትና ሉአላዊነትን አስከብሮ የመኖር አኩሪ ታሪክ አለን፡፡ ስለሆንም የአሜሪካ መንግስት ሆነ አውሮፓ ከእኛ ሆኑ አልሆኑ በሉአላዊነታችንና በነጻነታችን የምንደራደር ህዝቦች አይደለንም፡፡ በጀመርነውም መንገድ ተጉዘን አሸናፊነታችንን እናረጋግጣለን፡፡
Mኣr
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2013