ሐዋሳ፡- ላለፉት አርባ ዓመታት ከቤተሰባቸው ጋር ሳይገናኙ የቆዩት የተረት አባት በ2011 ዓ.ም ፈጣሪ ረድቶኝ ቤተሰቤን አግኝቼ ተደሰትኩ፤ ደስታዬ ወደር አጣ አሉ። ላለፉት አርባ ዓመታት በዓሳ አጥማጅነት፣ በጥበቃ፣ ጫማ አሳማሪነት፣ ሱቅ በደረቴና በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ሕይወታቸውን ሲመሩ የነበሩት የ58 ዓመቱ አባት በ2011 ዓ.ም በልጅነት ከተለዩዋቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር በአጋጣሚ ለመጀመሪያ ጊዜ መገናኘታቸውን ተናግረዋል።
ሀድያ ምስራቅ ባደዋቾ 1953 ዓ.ም የተወለዱት አቶ ታደሰ አሰፋ ሎንቺን በምትባል መኪና ሐምሌ በ1969 ዓ.ም በአንድ ብር ከ90 ሳንቲም ከፍለው ወደ ሐዋሳ ከተማ በመሄድ ሕይወት ጀምረው በዚያው መቅረታቸውን ገልፀዋል። አቶ ታደሰ እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ የተማሩ ሲሆን፤ በ1966 ዓ.ም የአብዮት ፍንዳታ ወቅት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። አሁንም በ58 ዓመታቸው መማር ያስባሉ። አቶ ታደሰ በአሁኑ ወቅት፤ በሃዋሳ ከተማ ሌዊ ሪዞርት ለአገር ውስጥና የዳያስፖራ ልጆች ተረት በመናገር የሚተዳደሩ ሲሆን፤ የጥበቃ ሥራም ይከውናሉ።
ከዘንዶ፣ ጅብና ሌሎች እንስሳት ጋር የጠነከረ ቁርኝት እንዳላቸውና መግባባት እንደሚችሉም ከልዩ ተሞክሯቸው አካፍለውናል። አቶ ታደሰ አመጋገባቸው፣ የሕይወት ፍልስፍ ናቸውና ቀጣይ እቅዳቸው የተለየ ሲሆን ድል ባለ ድግስም የውሃ አጣጫቸው ጋር ቢጣመሩ ደስታቸው ወደር እንደማይኖረው ይናገራሉ። የተረት ተናጋሪው የአቶ ታደሠ ሙሉ ታሪክ በቅርቡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅዳሜ ዕትም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ዓምድ እናቀርባለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ከፍለዮሐንስ አንበርብር